>

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ-ማርያም ማን ነበሩ? ምን ሠርተው አለፉ? የሕይወት ታሪካቸውን የቃኘ ዘገባ...!!! (ዳንኤል ድርሻ)

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ-ማርያም ማን ነበሩ? ምን ሠርተው አለፉ? የሕይወት ታሪካቸውን የቃኘ ዘገባ…!!!

ዳንኤል ድርሻ  –  ዋዜማ ራዲዮ

/መስፍን-ወልደማርያም-1922-2013

የአደባባይ ምሁሩ መስፍን ወ/ማርያም የተዋጣላቸው ጸሐፊ ናቸው፤ ገጣሚ፣ መምሕር፣ የሠብዓዊ መብት ተሟጋች እና ፖለቲከኛነታቸው ጎልቶ ይጠቀሳል፡፡ በመንፈሳዊ ትምሕርት ዲቁና፣ በዓለማዊው ዶክትሬት ደርበዋል፤ በምርምር ሥራቸው የፕሮፌሰርነት ማዕረግ አግኝተዋል፡፡ ከ15 በላይ መጽሐፍትን ለንባብ አብቅተዋል፡፡ ፍትሕና እኩልነት ይሰፍን ዘንድ ላደረጉት አስተዋጽኦ የአውሮፓ ሕብረት የሳካሮቭ አዋርድ የ2016 ዕጩ ነበሩ፡፡
›‹ ›‹ ›‹ ›‹ ›‹
በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ዘመነ መንግሥት ከወሎ (የጁ) እና ከሸዋ የመጡት እናትና አባታቸው፣ አዲስ አበባ አገኛኝቷቸው፣ መስፍን ወ/ማርያም ስድስት ኪሎ አካባቢ ተወለዱ፡- በ1922፡፡
ትምሕርት በመጥላታቸው የተነሳ በእግር ብረት ታስረው በ5 ዓመታቸው ወደ “የኔታ” ትምሕርት ቤት ገብተው ቅዳሴ፣ ውዳሴ ማርያምና ዜማ አጥንተዋል፤ ዲቁና ተቀብለዋል፡፡ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምሕርትን በተፈሪ መከንን እና ጄኔራል ዊንጌት ተከታትለው ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ገብተዋል፡፡ ከፍተኛ ትምሕርታቸውን ቀጥለው ከሕንድ ፑንጃብ በፍልስፍና ቢኤ፣ ማሳቹሴትስ ዩኤስኤ ከሚገኘው ክለርክ ዩኒቨርሲቲ ኤምኤ አግኝተዋል፡፡
መስፍን ወደ ሀገራቸው እንደተመለሱ ሥራ የጀመሩት በካርታና ጂኦግራፊ ኢኒስቲቲዩት ነበር፤ የሥራው ሁናቴ ስልላተመቻቸው ወደ አ.አ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ተዛውረው ማስተማር ጀመሩ፡፡ 1950ዎቹ ሀገሪቱ በለውጥ አየር የምትናጥበት፣ ዩኒቨርሲቲውም የንፋሱ ማዕበል የሚቀሰቀስበት ሆነ፡፡ በታሕሳስ 1953 ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ወደ ብራዚል መሄዳቸውን ተከትሎ የተሞከረው መንግሥት ግልበጣ በክቡር ዘበኛ ቢከሽፍም የፖለቲካ ጡዘቱን ግን በእጀጉ አጋለው፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራውን ደግፈው ሠልፍ ሲወጡ፣ መስፍን ወ/ማርያም የተማሪዎቹን ትዕይንት በመቀላቀል በቀጥታ ፖለቲካዊ ተሳትፎ ያደረጉበት የመጀመሪያ ኹነት ሆኖ ይመዝገብ እንጂ ከዚያ ቀደምም በተለያዩ እንቅስቃሴዎች ተሳትፈዋል፡፡
›‹ ›‹ ›‹ ›‹ ›‹
በ1951 በትግራይ ኃይለኛ ረሀብ ገብቶ፣ ሕዝብ በችጋር በጅምላ ያልቅ ነበር፡፡ የረሀቡ መከሰት ለንጉሠ ነገሥቱ ባይደርስም ለትግራይ መኳንንት እና ለሌሎች ባለሥልጣናት ግን ድብቅ አልነበረም፡፡ መስፍን ወ/ማርያም ገና የ29 ዓመት ወጣት ነበሩ፡፡ ወጣቱ መስፍን በትግራይ ረሀብ ገብቶ ሰዎች በችጋር እያለቁ መሆኑን ከአንድ ባለጸጋ ወይዘሮ ይሰማሉ፡፡ ጉዳዩን እንደሰሙ በራሳቸው ወጪ አዲግራት ድረስ ሄደው ችግሩን ከተመለከቱ በኋላ ሕዝብ እንዲያውቅና እርዳታ መሰብሰብ እንዲቻል ጽሁፍ አዘጋጅተው ለጋዜጣ ይልካሉ፡፡ ጽሁፉን በጋዜጣ ማውጣት ስላልተቻለ በእንደራሴዎች በኩል ለፓርላማ ለማቅረብ ሞከሩ፡፡ ይሕም አልተቻለም፡፡ በሚያውቋቸው ባለሥልጣናት በኩል ነገሩ መፍትሔ እንዲገኝለት ቢጥሩም አልተሳካም፡፡
በመጨረሻ ተፈሪ መኮንን ት/ቤት አብሯቸው የተማረውና የጃንሆይ ልዩ ጸሐፊ ሆኖ የሚያገለግል ወዳጃቸውን አግኝተው በሥፍራው ተገኝተው ያነሱትን የረሀብተኞቹን ሠቆቃ የሚያሳይ ሁለት ፎቶግራፍና ደብዳቤ ለጃንሆይ እንዲሰጥላቸው ይጠይቃሉ፡፡ ወዳጃቸውም መልዕክቱን ለጃንሆይ ያደርሳል፡፡ ጃንሆይ መልዕክቱ እንደደረሳቸው ለተጎጂው ሕዝብ እርዳታ በአስቸኳይ እንዲሰጥና ወጣቱ መስፍንም የኮሚቴ አባል ሆኖ እርዳታ እንዲያከፋፍል አዘዙ፡፡
በ1964/65 ዓም ችጋር ለሁለተኛ ጊዜ በተለይ በወሎ ብዙ ሕዝብ መፍጀት ጀመረ፡፡ ይሄኛውም እንደ 1951 የትግራይ ረሀብ ሁሉ ከንጉሱና ከሕዝቡ ይደበቃል፡፡ መስፍን በድጋሚ የሕዝቡን ሠቆቃ ለማየት ብርታት አጡ፡፡ እናም ሁኔታውን ለባልደረቦቻቸው (ጌታቸው ኃይሌ፣ አብርሀም ደሞዝ እና ሌሎችም) ካስረዱ በኋላ፣ በሥፍራው ተገኝተው ሰቆቃውን በፎቶግራፎችና በመቅረጸ ድምጽ ቀርጸው እንዲያመጡላቸው ያደርጋሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ፕ/ር መስፍን እንደ 1951ዱ የትግራይ ችጋር በየባለሥልጣናቱ ደጃፍ ደጅ አልጠኑም፡፡
በቀጥታ በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ባለው ቢሮአቸው ውስጥ አውደ ርዕይ (ኤግዚቢሽን) አዘጋጅተው የረሀብተኞቹን ፎቶና የጣር ድምጽ ለተማሪዎችና ለዩኒቨርሲቲው ማሕበረሰብ አቀረቡት፡፡ ተማሪዎች ሌሊቱን አምጸው አደሩ፡፡ በዚህ መልክ የወሎ ረሀብ ለመጀመሪያ ጊዜ ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለዓለም ተጋለጠ፡፡ የለውጥ አየሩም ይበልጥ እንዲግም ያደረገ ክስተት ሆኖ አለፈ፡፡
›‹ ›‹ ›‹ ›‹ ›‹
የተማሪዎች አመጽ በተቀጣጠለበት በ1964 መስፍን ከበረከት ኃብተሥላሴ (ፕ/ር) ጋር በመሆን የወንጂ ስኳር፣ የምድር ባቡር እና ቃጫ ፋብሪካ ሠራተኛ ተወካዮችን በምስጢር በማሰባሰብ በህቡዕ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማሕበርን ለመመስረት ማደራጀት ያዙ፡፡
ጓደኛቸው በረከት ምስጢሩን ለመንግሥት አሳልፈው በመስጠታቸው መስፍን ወልደማርያም ከዩኒቨርሲቲው ተነስተው በዕድገት ሠበብ “የጊሚራ አውራጃ ገዢ” ተብለው ግዞት ቢላኩም ብዙም ሳይቆዩ ተመልሰዋል፡፡
በ1965 ዓ.ም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ተማሪዎች በአፍሪካ አዳራሽ “ገጠሪቱ ኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ ባዘጋጁት ውይይት በተጋባዥነት የተገኙት ፕሮፌሰር መስፍን ባደረጉት ንግግር “…በኢትዮጵያ ኃላፊነቱ ያልተወሰነ የአክስዮን ማሕበር እንጂ መንግሥት የለም” ማለታቸው እንደገና መንግሥት ጥርስ ውስጥ አስገባቸው፡፡ ይሕን ንግግራቸውን ተከትሎ የጊምቢ አውራጃ አስተዳዳሪነት ተሹመዋል በሚል ከአዲስአበባ እንዲርቁ ተወሰነባቸው፡፡ ትዕዛዙን ለመቀበል አሻፈረኝ በማለታቸው “የንጉሠ ነገሥቱን ትዕዛዝ ባለመቀበል” በሚል ክስ 3ኛ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው ከተለቀቁ በኋላ ወደ ሥፍራው ሔደዋል፡፡ በጊምቢ ሹመታቸው ብዙም ሳይቆዩ የንጉሡን ሥልጣን የነቀነቀው አብዮት በመጋጋሉ መስፍን ወደ አዲስ መበባ ተመለሱ፡፡
›‹ ›‹ ›‹ ›‹ ›‹
ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ከሥልጣን ከመውረዳቸው አስቀድሞ “በሥልጣን ባልገዋል፣ ረሀቡ እንዲሸሸግ አድርገዋል” የተባሉ ባለሥልጣናትን ጉዳይ የሚፈትሽ “መርማሪ ኮሚሲዮን” በአዋጅ ተቋቋመ፡፡ 15 አባላት ያሉት ኮሚቴም በንጉሱ ፊት ቃለ መሐላ ፈጸመ፡፡ መስፍን ወልደማርያም የኮሚቴው ሊቀ መንበር ሆነው በአባላቱ ተመረጡ፡፡
ለ60ዎቹ የቀ/ኃ/ሥ መንግሥት ባለሥልጣናት ግድያ ፕሮፌሰር መስፍንና መርማሪ ኮሚሲዮኑ እጃቸው እንዳለበት በተለያየ ጊዜያት ሲገለጽ ይሠማል፡፡ ሆኖም ግን ፕሮፌሰር መስፍን ደርግ ገና አራተኛ ክፍለ ጦር ግቢ እያለ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃ/ማርያም ኮሚሲዮኑ አብሯቸው እንዲሠራ ጥያቄ ቢያቀርቡላቸው እምቢኝ እንዳሉ ይገልጻሉ፤ በአውስትራሊያ ከሚታተመው አሻራ መጽሔት ስለ ጉዳዩ ለቀረበላቸው ጥያቄ ፕሮፌሰር መስፍን ሲያብራሩ እንዲህ ብለዋል፡-
“…መንግስቱ ኃይለማርያም መርማሪ ኮሚሲዮኑን ወደሱ ለማስጠጋት ፈልጎ ኑና አብረን እንስራ ብሎ ጠይቆኝ ነበር፤ እኔ ከናንተ ጋር በምንም መንገድ ልሰራ አልችልም! እኛ የማልንበት ሌላ ጉዳይ ነው፤ እናንተ ደግሞ አልማላችሁም፤ ስለዚህ እኔ በማልኩበት ነው ለመጽናት የምሻው ብዬ ገለጽኩለት፤ ቆይቶ ይሕንኑ ጥያቄ አነሳብኝ፤ እኔም መልሼ አይ የራሴን ሀሳብ ነግሬሀለሁ፣ ኮሚሲዮኑ ኦፊሻል መልስ እንዲሰጥህ ከፈለግህ ሀሳቡን አነሳላቸውና መልሳቸውን አሳውቅሀለሁ አልኩት፡፡ እሱም ጥሩ እንደሱ አድርግና አሳውቀኝ አለኝ፡፡ ሰበሰብኳቸውና ሰውየው አብረን እንስራ እያለ ነው፣ ሃሳባችሁ ምንድነው ብዬ ጠየቅኩ፡፡ ባሮ ቱምሳና በረከት ኃብተሥላሴ ከደርግ ተጠግቶ መስራት ፈልገው ነበር፤ ሌሎቹ ግን በፍጹም አብረን አንሰራም አሉ፡፡ ይሕንኑ ለመንግስቱ ነገርኩና በዚሁ አበቃ፡፡”
ኅዳር 14/1967 ስድሳዎቹ ባለሥልጣናት ከተገደሉበት ዕለት ጀምሮ ወደ መርማሪ ኮሚሲዮኑ መሄድ ማቆማቸውንና የስንብት ደብዳቤ ማስገባታቸውን በገለጹበት “አገቱኒ” መጽሐፋቸው “በህይወቴ በሥልጣን ላይ ላሉ ሰዎች ቅርብ የሆንሁት የመርማሪ ኮሚሲዮን ሊቀ መንበር በነበርሁበት አጭር ጊዜ ውስጥ ነው፤ ከማናቸውም ጊዜ የበለጠ ሥልጣን በጥፍሩ ይዞ ሊጎትተኝ የሞከረበት ወቅት ነበር፤ በማምለጤ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ” ነው ያሉት፡፡
›‹ ›‹ ›‹ ›‹ ›‹
ከአብዮቱ በኋላ ፕሮፌሰር መስፍን ሙሉ በሙሉ በማስተማር ሥራቸው ተጠመዱ፡፡ በርካታ የምርምርና ጥናት መጽሐፍቶቻቸውን ያዘጋጁበት ወቅት ነበር፡፡
የፕሮፌሰርነት ማዕረግ የሚያገኙበት ጊዜ ለተወሰነ ጊዜ እንዲዘገይ ተደረገባቸው፡፡ ዘግይቶ የፕሮፌሰርነት ማዕረግ እንደሚሰጣቸው ዩኒቨርሲቲው ቢገልጽም፣ እሳቸው ግን በሥነ ሥርዓቱ ላይ ለመታደም ፈቃደኛ አልነበሩም፡፡ የዩኒቨርሲቲ የትምሕርት ቆይታ ወደ 3 ዓመት እንዲያጥር፣ የመመረቂያ ነጥብም ዝቅ እንዲል መደረጉ፣ የአካዳሚ ነጻነት መገፈፉ ፕሮፌሰር መስፍን ሌላ ተቃውሞ እንዲያሰሙ አስገደዳቸው፡፡ ለሁኔታው ማስተካከያ ያሉትን ሀሳብ በጽሑፍ አዘጋጅተው ለዩኒቨርሲቲው ማሕበረሰብ ማሰራጨታቸው በኃላፊዎች እንደ ዋዛ አልታለፈም፤ ከዚያ ቀደም የአስመራ ዩኒቨርሲቲ እና የቤተሰቦች ጥናት ኢኒስቲቲዩትን በኃላፊነት እንዲመሩ የቀረበላቸውን ጥያቄ አልቀበል ማለታቸው ከጸረ ማርክሲስትነት ጋር ተዳምሮ በጊዜያዊ ዕገዳ ሠበብ መስፍንን ከዩኒቨርሲቲው ለማግለል ተሞከረ፡፡ እሳቸው ደሞ ይሕንን ተጠቅመው ጡረታ ለመውጣት ጥያቄ አቀረቡ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ፍቅረስላሴ ወግደረስ ጭምር የጡረታውን ሀሳብ እንዲቀለብሱ ቢማጸኗቸውም ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀሩ፤ ጡረታው ተፈቀደላቸው፡፡ ኢሕአዴግ ሲገባ ከ42ቱ ምሁራን ጋር ያልተሰናበቱትም አስቀድመው ጡረታ በመውጣታቸው መሆኑን ያወሱታል፡፡
›‹ ›‹ ›‹ ›‹ ›‹
ሚያዝያ 1983 ኮሎኔል መንግስቱ በሥልጣን ዘመናቸው ማምሻ ዕድሜ… ብሔራዊ ሸንጎውን ሰብስበው የምሁራኑን ክፍል ቀልብ ለመሳብ በሚመስል መልኩ አዲስ የሠላም ጥሪ ሀሳብ አቀረቡ፡፡
የአጋጣሚ ነገር ሆኖ በዚያው ሰሞን አዲስ አበባ 11ኛውን የኢትዮጵያ ጥናት ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ በማስተናገድ ላይ ነበረች፡፡ እናም ፕሮፌሰር መስፍንን ጨምሮ አስራ አንድ ምሁራን “የባለ አደራ መንግስት እንዲቋቋም” የሚጠይቅ የመፍትሔ ሀሳብ አዘጋጅተው ደብዳቤውን ለኮሎኔል መንግስቱ ሠደዱ፡፡ የነ ፕሮፌሰር ደብዳቤ… የባለአደራ መንግስት እንዲቋቋም፣ በሀገሪቱ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ እስኪካሄድ ሥልጣን በሽማግሌዎች እጅ እንደሚቆይ፣ ከምርጫው በኋላ ባለአደራው ሥልጣን እንደሚያስረክብ የሚያትት ነበር፡፡ ስልጣን ልቀቁ የሚል ደብዳቤ የደረሳቸው ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም እና የኮንስትራክሽን ሚኒስትሩ ካሳ ገብሬ በሸንጎው ፊት ፕሮፌሰር መስፍንን ዘለፉ፡፡ “መስፍንን ፕሮፌሰር ያደረገው ማነው? እኛ አይደለንምን?” የሚል ብስጭታቸው ቢሠማም የተፈራው ሳይደርስ ኮሎኔል መንግስቱ ብዙም ሳይቆዩ ወደ ዚምባቡዌ ማምራታቸው ሁኔታውን አቅልሎታል፡፡
›‹ ›‹ ›‹ ›‹ ›‹
ኢትዮጵያ ሠላም አጥታ፣ አብላጫው የሀገሪቱ ክፍልም በአማጽያኑ እጅ በወደቀበት ወቅት በግንቦት 1983 የቀድሞው መንግስት ባለሥልጣናትና የበረኸኞቹ ተወካዮች በለንደን በአሜሪካውያኑ ዲፕሎማቶች ይደራደሩ በነበረበት ወቅት ነው ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያምና አቶ መለስ ዜናዊ ለመጀመሪያ ጊዜ በአካል የተገናኙት፡፡ “ከጠመንጃ ኃይል በተገኘ ሥልጣን” ኢሕአዴግ መንበረ ሥልጣኑን ከተረከበ በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ የተገናኙት የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያምና የአቶ መለስ ዜናዊ የቲቪ ክርክር ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲተላለፍ ተደርጓል፡፡ መስፍን ወልደማርያም ከአጼ ኃይለሥላሴ፣ ከኮ/ል መንግስቱ እና ከጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ጋር በአካል በመገናኘት ለሀገሬ ይበጃል ያሉትን ሀሳብ አካፍለዋል፡፡
›‹ ›‹ ›‹ ›‹ ›‹
ፕሮፌሰር መስፍን ከሕግ ባለሙያ ወዳጆቻቸው ጋር በመሆን መስከረም 29/1984 ዓም የኢትዮጵያ ሠብዓዊ መብት ጉባዔን (ኢሠመጉ) አቋቋሙ፡፡
በኢሠመጉ ውስጥ ለሠባት ዓመታት በመብት ጥሰት መርማሪነት የሠራውና ዛሬ በስደት ቤልጂየም የሚገኘው የሠብዓዊ መብት ተሟጋች ያሬድ ኃይለማርያም እማኝነቱን ሲሰጥ “…ከፕሮፌሰር መስፍን የተማርነው እጅግ በርካታ ነገር ቢኖርም… ለሰው ልጅ ሁሉ ያላቸው እኩል አክብሮትና ሚዛን፣ ለፍትሕና ለሠብዓዊ መከበር ያላቸውን ተቆርቋሪነትና ጽናት በምንም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንኳን እንደማይዛነፍ እመሰክራለሁ፤ ለዚህም የኢትዮ ኤርትራን ጦርነት ተከትሎ በኤርትራውያን ከኢትዮጵያ መባረር ላይ የነበራቸው ጠንካራ አቋም አንድ ጥሩ ማሳያ ነው፤ በርካታ የሕግ ባለሙያዎች፣ ፖለቲከኞችና የሠብዓዊ መብት ተሟጋቾች ሳይቀሩ በዚህ ሁኔታ ላይ ሚዛን የሳተ አቋም ሲይዙ ፕ/ር መስፍን ግን መንግስት የፈጸመውን የመብት ጥሰት ኢሰመጉ እንዲያወግዘው ከማድረጋቸው ባሻገር በግላቸውም አደባባይ ወጥተው ድርጊቱን አውግዘዋል” በማለት አስታውሷል፡፡
ፕሮፌሰር መስፍን በኢሕአዴግ ዘመን ለመጀመሪያ ጊዜ ለእስር የተዳረጉት በኢሠመጉ ስብሰባ ላይ ካደረጉት ንግግር ጋር በተያያዘ ነበር፡፡ መጋቢት 30/1993 ኢሰመጉ “የአካዳሚክ ነጻነት መብቶች” በሚል ርዕስ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የአንድ ቀን ዐውደ ጥናት አዘጋጅቶ ነበር፡፡ ዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥ እንዳይካሄድ በመከልከሉ ኢሰመጉ የብሔራዊ ሎተሪ አዳራሽን ተከራይቶ ዐውደ ጥናቱ ተካሄደ፡፡ ተናጋሪዎቹ ፕ/ር መስፍንና ዶክተር ብርሀኑ ነጋ ነበሩ፡፡ በማግስቱ ተማሪዎች “የአካዳሚ ነጻነት ይከበር”፣ “መብታችንን አሁኑኑ” የሚል መፈክር ይዘው ተቃውሞ ወጡ፡፡ ተቃውሞው በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ተቀጣጠለ፡፡ የአገዛዙ ታጣቂዎች 42 ንጹሀንን ገደሉ፡፡ ሚያዝያ 30/1993 ፕሮፌሰር መስፍንና ዶክተር ብርሀኑ ህቡዕ ቡድን አደራጅተው መንግስት ለመገልበጥ ሞከረዋል ተብለው ከታሰሩ ከቀናት በኋላ በዋስ ተፈትተዋል፡፡
›‹ ›‹ ›‹ ›‹ ›‹
በ1997 መጀመሪያ ፕሮፌሰር መስፍን ከዶ/ር ብርሀኑ ነጋ፣ ዶ/ር በፈቃዱ ደግፌ እና ዶ/ር ሽመልስ ተ/ጻድቅ ጋር በመሆን “ቀስተ ደመና” ፓርቲን መሰረቱ፡፡ ዓላማቸውም የተበታተኑትን ፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ አንድ በማምጣት በምርጫ 97 ጠንካራ ተፎካካሪ እንዲሆኑ ማድረግ ነበር፡፡ ይሕም ተሳክቶላቸው ቅንጅት ለአንድነትና ዲሞክራሲን ዕውን አድርገዋል፡፡ በቅንጅት አመራር ውስጥ ያልነበሩትና በምርጫም ያልተወዳደሩት ፕ/ር መስፍን ከምርጫ 97 ግርግር በኋላ በኢሕአዴግ ወሕኒ ከመውረድ አልዳኑም፡፡ ከሌሎች የፓርቲው አመራሮች ጋር ዕድሜ ልክ ተፈርዶባቸው ከሁለት ዓመት በኋላ ተፈትተዋል፡፡ ከወሕኒ መልስም ከእነ ወ/ት ብርቲካን ሚደቅሳ ጋር አንድነት ፓርቲን መስርተው የምክር ቤት አባል የነበሩ ቢሆንም በፓርቲው ውስጥ በተፈጠረ ክፍፍል እንዲገለሉ ተደርገዋል፡፡ ከእስር በኋላ የጻፋቸው አገቱኒ፣ እና መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክን መሰል አነጋጋሪ መጽሐፍትን ለሕትመት አብቅተዋል፡፡ አንድ ተጨማሪ መጽሐፋቸውም በሕትመት ላይ መሆኑን በቅርቡ ገልጸው ነበር።
›‹ ›‹ ›‹ ›‹ ›‹
በ90 ዓመታቸው ያረፉት የሁለት ሴት ልጆች አባት፣ “ቅድሚያ ለሴቶች” (ሌዲስ ፈርስት) ለሚለው እምነት ትኩረት እንደሚሰጡ የምትናገረው በማሳቹሴትስ የምትኖረው የመጀመሪያ ልጃቸው መቅደስ መስፍን “የሰው ሀሳብ በትዕግስት ያደምጣል፤ እሱም ያለ መሰልቸት ያስረዳል፤ ሀሳብን የመመርመር ችሎታና ትዕግስቱን አደንቃለሁ፤ ያመነበትን ነገር ፊት ለፊት ከመናገር የሚያቆመው የለም” ትላለች የአባቷን ባሕርይ በመጠኑ ስታስረዳ፡፡
 
ዋዜማ ሬዲዮ ለፕሮፌሰር መስፍን ቤተሰቦችና ወዳጆች መጽናናትን ትመኛለች ።
[ዋዜማ ራዲዮ]
Filed in: Amharic