>

"...ፈጣሪ ጥቁር ነው ስንል ...ምስጢር ነው፤ ከሰው አእምሮ በላይ ነው የሚለውን ለማሳየት ነው ...!!!'' (የዋቄፈና እምነት ተከታዮች)

“…ፈጣሪ ጥቁር ነው ስንል …ምስጢር ነው፤ ከሰው አእምሮ በላይ ነው የሚለውን ለማሳየት ነው …!!!”
 
የዋቄፈና እምነት ተከታዮች

ዋቄፈና የቀደምት ኦሮሞ ሕዝቦች እምነት ሲሆን የእምነቱ ተከታዩች ሁሉን በፈጠረ አንድ አምላክ እንደሚያምኑ ይናገራሉ።
አቶ አስናቀ ተሾመ ኢርኮ፣ ላለፉት 20 ዓመታት ስለ ዋቄፈና እምነት  ቦረና አካባቢ በመሄድ ጥናታቸውን እንዳደረጉ ገልፀው “ፈጣሪ ስሙ መቶ፣ ሆዱ እንደ ውቅያኖስ ሰፊ፣ ሃሳቡ ደግሞ ንጹህ ነው፤” ድሮ ድሮ ሰው ሃጥያት መስራት ሳይጀምር በፊት የፈጣሪን ድምጽ የሰሙ ሰዎች ነበሩ ይባላል ይላሉ።ስሙ መቶ ነው የሚለው ደግሞ ፈጣሪ “አንድ” እና ከሁሉ በላይ የሆነ መሆኑን እና ሀይማኖቶች ወይንም እምነቶች ግን ብዙ መሆናቸውን ለማሳየት መሆኑን አቶ አስናቀ ያብራራሉ።ይሁንና ፈጣሪን በዓይኑ ያየው ሰው የለም በማለት ነው ኦሮሞ የሚያምነው ሲሉ ያስረዳሉ። ኦሮሞ ‘ፈጣሪ ጥቁር ነው’ ይላል።የኦሮሞ ፈጣሪ ጥቁር ነው ሰንል ግን ይኼ የሚታየውን መልክ ወይም የቀለም ጉዳይ ሳይሆን፣ “ፈጣሪ ጥልቅ ነው፤ ፈጣሪን ማየት፤ መለየት አይቻልም የሚለውን ለመግለጽ ነው። ማንም ተመራምሮ ሊደርስበት አይችልም።” ብለዋል።”ፈጣሪ ምስጢር ነው፤ ከሰው አእምሮ በላይ ነው የሚለውን ለማሳየት ነው በጥቁር መልክ የሚገለፀው።”
ዘፍጥረት
እንደ ዋቄፈና እምነት፤ ፈጣሪ ሁሉን ነገር የፈጠረው በቀደመ ዘመን ከነበረ ውሃ እንደሆነ ይታመናል። ፈጣሪም ይህንንም ውሃ ‘የላይኛውና የታችኛው ውሃ’ በማለት ለሁለት ከፈለው የሚሉት አቶ አስናቀ፣ የላይኛው ውሃ ጠፈር ውስጥ የሚገኙ አካላትን ሰማይን እንዲሁም ፀሀይንና ከዋክብትን ይይዛል።የታችኛው ውሃ ደግሞ፣ የውሃ አካላትን እንደ ውቅያኖስ፣ ባህርን፣ ደረቅ መሬትን ይይዛል።
ዋቄፈና በዚህ ምድር ላይ ያሉ ፍጥረታት በሙሉ በ27 ቀናት ተፈጠሩ ብሎ ነው የሚያምነው።
መጀመሪያ ሰውን ፈጠረ፣ ከዚያም ወንድና ሴት ብሎ እኩል ለሁለት ከፈላቸው። ሌሎች ፍጥረቶችንና ተክሎችን እንደዚሁ በቅደም ተከተል ፈጠራቸው።
ፈጣሪ ምድርን ሲፈጥር ሰው በስነ-ስርዓት እንዲኖር ሕግንም አብሮ ፈጠረ። እነዚህም ሕጎች የሰው ሕግ፣ የከብቶች ሕግ፣ የፈረሶች ሕግ፣ የዱር አራዊት ሕግ፣ የእጽዋትና የፀሀይና የከዋክብት ሕግ ይሰኛሉ።
‘ሰፉ’ የማይቀየር የፈጣሪ ሕግ ነው። ይህም ክልክል የሆኑትን ሰውን መግደል፣ መስረቅ፣ ዝሙት እና መዋሸትን ተላልፎ መገኘት ነው።ፈጣሪን፣ ምድርን እንዲሁም ሌሎችን ፍጥረቶች ሁሉ ማክበር የፈጣሪን ሕግ መጠበቅ ነው።
ክልከላዎች ‘ለጉ’ የሚባሉት የማህበረሰቡን አይነኬ ተግባራት ለመጠበቅ የወጡ ናቸው። አንድ ሰው ሀጥያት ሰራ የሚባለው እነዚህን የፈጣሪን ሕግና ክልከላዎች ሲጥስ/ ሲተላለፍ ነው።
ከሞት በኋላ ሕይወት?
ቀደምት የኦሮሞ ሕዝቦች ሰው ሲሞት ነፍሱ ወደ ፈጣሪ ወይንም ደግሞ ወደ እውነት ቦታ ትሄዳለች ብለው ነው የሚያምኑት። እንደ ዋቄፈና እምነት ሰው ከውሃ፣ ከነፋስ፣ ከእሳት እና ከአፈር በአንድ ላይ ተበጅቷል።
ስለዚህ ሰው ሲሞት አካሉ ከአፈር ይቀላቀላል፣ ደሙ ወደ ውሃ ይሰርጋል። ነፍሱ ደግሞ ወደ ፈጣሪው ይሄዳል።
“እንደ ሌሎች እምነቶች ዋቄፈና ሰው ከሞተ በኋላ ይነሳል ወይንም በሕይወት ይኖራል ብሎ አያምንም። እንዲሁም በሴጣን መኖርና ፈጣሪን የሚገዳደር ሌላ ኃይል አለ ብሎ አያምንም። ሰዎችንም ኃጥያት እንዲሰሩ የሚያስገድዳቸው ኃይል የለም ብሎ ነው የሚያምነው” ይላሉ አቶ አስናቀ።
ይኹን እንጂ “ክፉ መንፈስ አለ ብሎ ያምናል” በማለት፣ ሰው የማይቀየረውን የፈጣሪን ሕግ ከተላለፈ፣ ስለሚጠየቅ እና ርግማንም ወደ ሰባት ትውልዱ ስለሚተላለፍ ኃጥያት መስራት በጥብቅ የተከለከለ ነው። ሕዝቡም ይህንን ይፈራል።
ለምሳሌ አንድ ሰው፣ ነፍስ አጥፍቶ ሳይናገር ከሞተ በፈጣሪ ዘንድ ስለሚጠየቅ ቤተሰቦቹ ወይንም ዘመዶቹ የሙት መንፈስን የሚያናግሩ “አዋቂዎች” ዘንድ ይሄዱና ካሳውን “ልክ በሕይወት እንዳለ ሰው” ይጠይቃሉ።
በዚህ እምነት ገሃነም ወይንም ገነት የሚባል ነገር የለም። እንዲህ ማለት ግን ሰው የፈለገውን እያደረገ ይኖራል ማለት አይደለም። በእነዚያ በፈጣሪ በማይቀረው ሕግ ስር መመላለስ አለበት።በዚህ መንገድም በፍጥረታት እና በሰዎች መካከል ያለ ሚዛን ተጠብቆ በሰላም መኖር ይቻላል ብሎ ያምናል፤ ዋቄፈና።
አቶ ተሻገር የአገር ሽማግሌዎች ‘እዳየነው እንደሰማነው’ በማለት ሲናገሩ፣ ኦሮሞ ፈጣሪን ሴት ወይንም ወንድ ብሎ ለይቶ አይጠራም። ነገር ግን ሲጠሩት በወንድ ጾታ ነው። ይህ ግን ጾታውን ለማመለክት አለመሆኑን.ይናገራሉ።
የዋቄፈና እምነት ተከታዮች
አቶ ደሳለኝ ደሜ በቢሾፍቱ ሆረ አርሰዴ የዋቄፈና ቤተ እምነት “ዋዩ” ናቸው። ዋዩ ማለት የዋቄፈና ቤተ እምነት ውስጥ ያሉ የአስተዳደር ጉዳዮችን የሚሰበስብና የሚመራ ሰው ነው።
አቶ ደሳለኝ ዋቄፈና ከአባቶቻችን ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ የመጣ እምነት ቢሆንም፣ እኛ የአሁኖቹ ትውልዶች ደግሞ ስርዓት እና ባህሉን ሳይለቅ ለአሁኑ ዘመን በሚመች መልኩ በ1990ዎቹ ቤተ እምነት መስርተን ኃይማኖቱን አቋቁመናል ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
እኛ እንደ እምነታችን ሁሉን በልጦ የሚያስተምር መምህር የለንም ያሉት አቶ ደሳለኝ ደሜ፣ ምክንያቱን ሲያስረዱ ስለዚህ እምነት ጉዳይ ሁሉም ከአባቱ ወርሶ ተምሮ መምጣቱን ይጠቅሳሉ።ይሁን እንጂ የውይይት ጥላ የሚባል ዝግጅት እንዳላቸው ገልፀዋል። በዚያም ስለፈጣሪ ተነጋግረን ፈጣሪን ለምነን እንገባለን ሲሉም ያክላሉ።
“በአጠቃላይ ግን እምነቱን በበላይነት የሚመራው ‘ቃሉ’ ነው።”
በአሁኑ ጊዜ በቢሾፍቱ ከተማ ብቻ አራት የዋቄፈና ቤተ እምነቶች አሉ። ከቢሾፍቱ በተጨማሪ በአዳማ፣ ባቱ ፣ ሰበታ እና ወሊሶ እንዲሁ ቤተ እምነቶች ይገኛሉ።በየዓመቱ ደግሞ አንድ ቤተ እምነት እንደ ክብረ በዓል ያዘጋጅና ሁሉም በአንድነት ያከብራሉ።የሆረ አርሰዴ ቤተ እምነት በግምት ከ5000 በላይ አባላት እንዳሉት አቶ ደሳለኝ ይናገራሉ። አብዛኛዎቹ አባላት ተማሪዎች ሲሆኑ፣ ሰራተኞችና በተለያየ የኑሮና የስራ ዘርፍ የሚገኙ ሰዎችም አባላት ናቸው።
የዋቄፈና የአምልኮ መርሃ ግብር
ቤተ እምነቱ ሁሌም ለሁሉም ሰው ክፍት ቢሆንም ዘወትር እሁድ ግን አባላቶች በአንድነት ተገናኝተው የአምልኮ ስነ ስርዓት ያካሄዳሉ።ጠዋት ሲገናኙ ማንኛውም ስነ ስርዓት ከመጀመሩ በፊት አንዱ ለአንዱ ይቅርታ የማድረግ ስርዓት ይፈፀማል።
“በዚያ ቤተ እምነት ውስጥ የሚገኝ ሰው እርቀ ሰላም ካላወረደ፣ ፈጣሪ አይሰማም ተብሎ ስለሚታመን እርቀ ሰላም ይቀድማል” የሚሉት አቶ ደሳለኝ፣ ከዚህ በመቀጠል በእድሜ ታላቅ የሆኑ እና አካባቢን መሰረት በማድረግ የምርቃት ስነ ስርዓት መርሃ ግብር ይካሄዳል።ከዚህ በኋላ ዋቄፈናን የሚመለከቱ ጉዳዮችን በማንሳት በውይይቱ ጥላ ስር ያሉ አባላቶች ይማማራሉ።
አሁን ፀሎትና ምስጋና ይቀጥላል። በዚህም ጊዜ የቡና ማፍላት ስርዓት ይከናወናል። የታመመ ሰው ይፀለይለታል፤ ቤተሰቦቹ የፈጣሪን ሕግ ጥሰው ከሆነ ፈጣሪ እንዲታረቃቸው ይለመናል።
ከዚህ በፊት ፀሎታቸው የተመለሰላቸው ሰዎች ካሉ ደግሞ ምስጋና ያቀርባሉ።በዚህ ሁሉ መካከል ‘ጄከርሳ’ መዝሙር ይዘመራል።ይህ መዝሙር በስነ ስርዓቱ መክፈቻና መዝጊያ ላይ የሚካሄድ ሲሆን ከመጨረሻው መዝሙር በፊት ግን አንድ “ባልቻ” የሚባል የመባ መስጠት ስርዓት ይካሄዳል።ይህ ስርዓት የቤተ እምነቱ አባል የሆነ ሰው የገንዘብ የሃሳብና የንብረት ድጋፍ የሚያደርግበት ነው።በአሁኑ ጊዜ ከመንግሥት በኩል እውቅና የማግኘትና የአምልኮ ስፍራ ለማግኘት ትልቅ ችግር እንዳለባቸው አቶ ደሳለኝ ጨምረው አስረድተዋል።
Filed in: Amharic