>
5:28 pm - Sunday October 10, 8371

ጥላሁን ገሠሠ የምእት አመቱ ታላቅ የሙዚቃ ሰው ሥራዎችህ በኢትዮጵያውያን እዝነ ልቦና ውስጥ ሲነቀለቀሉ ይኖራሉ (ደረጀ መላኩ) (

ጥላሁን ገሠሠ የምእት አመቱ ታላቅ የሙዚቃ ሰው ሥራዎችህ በኢትዮጵያውያን እዝነ ልቦና ውስጥ ሲነቀለቀሉ ይኖራሉ

ደረጀ መላኩ ( የሰብአዊ መብት ተሟጋች )

Tilahungesses@gmail.com

 


መንደርደረያ
ጋሼ ጥላሁን ገሠሠ በምእት አመታት አንዴ ሊፈጠሩ ከሚችሉ እጹብ ድንቅ የሙዚቃ ከዋክብቶች አንዱ ነው፡፡ ጥላሁንን የመሰለ የመድረክ ተወርግራጊና ድምጻዊ ቢያንስ በዚህ
ዘመን አልተፈጠረም፡፡ ከተሳሳትኩ ልታረም ዝግጁ ነኝ፡፡  በሀገር ፍቅር ስሜት የነደደውና የተቃጠለው ጋሼ ጥላሁን በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ሁነኛ ስፍራ ካላቸው ታላላቅ የሙዚቃ ሰዎች አንዱ  ነበር፡፡ ነበር ልበል ዛሬ በሕይወት ስለማይገኝ፡፡ ሆኖም ግን ጊዜ የማይሽራቸው፣ ጊዜ የማይከዳቸው የሙዚቃ ስራዎቹ በኢትዮጵያውያን የሙዚቃ አፍቃሪዎች እዝነ ልቦና ውሰጥ ሲነቀለቀሉ ይኖራሉ፡፡ ከ መስከረም ዓ.ም የተወለደው ጋሼ ጥላሁን በህይወት ቢኖር ኖሮ ዘንድሮ አመት ይሞላው ነበር ፡፡ ለማናቸውም ይህን ታላቅ የሙዚቃ ሰው እናስታውሰው፡፡ እነዘክረው፡፡ በቅድሚያ ግን ስለ ኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክና የክቡር ዘበኛ የሙዚቃ ኦርኬስትራ አመሰራረት በተመለከተ በወፍ በረር ካስቃኘኋችሁ በኋላ በትዝታ ፈረስ የኋልዮሽ በመሄድ ጥልዬን እንዘክራለን፡፡

ኢትዮጵያ  በቅድመ ታሪክ ፣ በታሪክና በጥንታዊ ሥልጣኔ የታወቀችው ኢትዮጵያ የድንቅ ቅርሶች ባለቤት ናት፡፡ በሰው ዘር አመጣጥ ቀዳሚውን ቦታ የያዙት የ3.2 ሚሊዮን ዓመት እድሜ ያላት ‹‹ የድንቅነሸ ›› ወይም ‹‹ ሉሲ ›› እና የ 3.6 ሚሊዮን ዕድሜ ባለቤቱ የካዳኑም መገኛም ናት ኢትዮጵያ፡፡ የጢያ የድንጋይ ላይ ቅርጾች፣ የተለያዩ የዋሻ ሥእሎች፣ በሐረርና ሲዳማ ከድንጋይ ላይ የተቀረጹ የእንሰሳት ምስሎች ( ኢንግሬቬንግስ ) እና ሌሎችም የቅድመ ዘመንን ታሪክ ያንጸባርቃሉ፡፡ የአክሱም ዘመነ መንግስት የፈጠረባቸው ድንቅ ሐውልቶች፣ ቅርጻ ቅርጽ፣ ጌጣጌጦችና ፊደሎች፣ በሰው ልጅ ጥንታዊ ሥልጣኔ ቅረስነታቸው ከፍተኛ ስፍራ ይዘዋል፡፡

ከ11ኛው እሰከ 12ኛው ክፍለ ዘመን በኢትዮጵያ የሥልጣኔ ታሪክ ታላቅ ቦታ የሚሰጣቸውና በአስደናቂ ቅርስነታቸው በአለም የታወቁት የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ፣ የጣና አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማት ፣ ጥንታዊ ሥእሎችና የብራና ጽሁፎች፣ ጥንታዊቷ የሐረርና ከተማና ግንቦቿ፣ በ17ኛው ምዕተ ዓመት የተሠሩት የጎንደር ግንቦች፣ አብያተ ክርስቲያናት፣ የዜማ፣ የቅኔና የሥነጽሁፍ ቅርሶች   የኢትዮጵያን የረጅም ዘመናት የታሪክና የኪነ ጥበብ ባለጸጋነት ይመሰክራሉ፡፡ ጊዜ የሰጠው ቅል……እንዲሉ ጊዜ ያነሳቸው ሃሳሂመሲሆች እንደሚደሰኩሩት ሳይሆን ኢትዮጵያ ረጅም ዘመን ታሪክ ያላት ጥንታዊት ሀገር መሆኗን የአሁኑ ትውልድ መገንዘብ አለበት፡፡ መገንዘብ ብቻ ሳይሆን የታሪክ መጽፍትን አፈላልጎ ፣ማንበብና መመርመር አለበት፡፡ ጊዜውን በዋዛ ከማሳለፍ መጽሐፍትን በተለይም የሀገሩን ታሪክ ለማወቅ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የተጻፉ መጽሐፍትን
እንዲያነብ ሳስታውስ በታላቅ አክብሮት ነው፡፡ በአውሮፓ የእግርኳስ አቅሉን የሳተው አብዝሃው ወጣቱ ትውልድ የኢትዮጵያን ታሪክ መጸሀፍት ማንበብና መመርመር  ሚያስችል የህሊና ዝግጅት ማድረግ ከቻለ ከወፍ ዘራሽ የጎሳ አምበሎች ሴራ ይገላገላል ብዬ አስባለሁ፡፡ የጎሳ አምበሎችም መጫወቻ ሆኖ አይቀርም፡፡ የወያኔ አገዛዝ እውነተኛ የኢትዮጵያን ታሪክ በመከለስና በመበረዝ የተጫወተብን ይበቃና፡፡ አሁን ወደ ህሊናችን እንመለስ፡፡

ኢትዮጵያ የብሔረሰቦች ሙዚየምም ነች፡፡ የተለያዩ ቋንቋዎች ይነገሩባታል፡፡ የተለያዩ ባህሎች፣ ወጎች፣ ልማዶች፣ የአኗኗር ዘይቤዎችና እምነቶች ይገኙባታል፡፡ በኢትዮጵያ ከሰባ በላይ ብሔረሰቦችና ከሰማንያ የማያንሱ ቋንቋዎች እንዳሉም ይነገራል፡፡ የሀገሪቱን  ሙዚቃ ስንመለከት ደግሞ በነዚሁ ብሔረሰቦች በርካታ ዝማሬዎችና ጭፈራዎች
እንዲሁም ባህላዊ የሙዚቃ መሳሪያዎች የበለጸገ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ እንዚህን ልዩ ልዩ ዝማሬዎችም ሕዝቡ በሥራ ፣ በሐዘን፣ በሠርግ፣ በአደን፣ በሃይማኖት፣ በዓላትና በሌሎች አጋጣሚዎች ይጠቀምባቸዋል፡፡

ሙዚቃችን ሕዝብን መሰረት ያደረገ የረጅም ዘመን ታሪክ ያለው ነው፡፡ እንዲህ ያለው አመቺ አጋጣሚም በዘመናዊ መልክ ለማደግ፣ የሙያው ዝንባሌ ላላቸው የሥራ ዕድል ለመፍጠርና ለሀገሪቱም ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማስገኘት ያስችላል፡፡ በአጼ ምኒሊክ ዘመነ መንግሥት እንደ አንድ የሥራ መስክ መታየት የጀመረው ሙዚቃችን እንቅስቃሴው ለዓመታት አዝጋሚና በአዲስ አበባ የተወሰነ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ይህም ማለት ከመቶ ዘጠናው የሀገሪቱ ክፍል ለእድገትና ዘመናዊ አኗኗር የተመቸ አልነበረም ማለት ነው፡፡ የሙዘቃውም ዘርፍ የችግሩ አካል ከመሆን አልዳነም፡፡ ለዚህም ዋናው ምክንያት ማህበረሰበችን ለሙያውና ለሙያተኞች የነበረው አመለካከት የተዛባ መሆኑ ነው፡፡ ከእንግዲህ
ግን በሙዚቃው መስክ ያሉ ችግሮችን እንዳላዩ አይቶ የማለፉ ልማድ መቆም ይኖርበታል፡፡

በሌላ በኩል ሙያውን የሚመሩና አቅጣጫ የሚያሲዙ ባለሙያዎችን ማፍራት እንደሚገባን መገንዘብ ይኖርብናል፡፡ በሙዚቃው ዘርፍ ምሳሌ የሚሆኑ ጠንካራ ተቋማት ለመመስረት ገና ብዙ  ጎዳና ይጠብቀናል፡፡ ስለሆነም ከሀገሪቱ የእድገት ጎዳና ፕሮግራም ጋር በተዛመደ መንገድ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ይህም ማለት በሀገሪቱ ዋና ከተማ የሙዚቃ ትምህርት ቤቶች የሚቋቋሙበት ሁኔታዎች ቢመቻቹ መልካም ነው፡፡ ቀስ በቀስም ከአዲስ አበባ ከተማ ውጪ በሚገኙ ትላልቅ ከተሞች ሊቋቋሙ ይገባል፡፡

በሀገሪቱ ከሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መካከልም የተወሰኑት ( ቁጥራቸው በሙዚቃ ባለሙያዎች ከተወሰነ በኋላ ቢሆን ይመረጣል)  በዩንቨርስቲ ደረጃ ምርጥ የሙዚቃ ሰዎች ለማፍራት የሚያስችላቸውን ፕሮግራም ቢያዘጋጁ መልካም ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ( እኔ እሰከማውቀው ድረስ አዲስ አበባ ከተማ ጃንሜዳ አጠገብ የሚገኘው ዝነኛወ የያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ደረጃውን ከፍ በማድረግ በድግሪ ደረጃ ተማሪዎችን ማስመረቀ ከጀመረ አመታቶች እየተቆጠሩ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ መቀሌ
ከተማ የሙዚቃና የስነጥበብ ትምህርት ቤት አንዳለ ይሰማል፡፡ ) የሙዚቃ ትምህርት ተሰጥኦና ልዩ ችሎታን የሚጠይቅ እንጂ በድፍረት ብቻ የሚገባበት አይደለም፡፡ በትምህርት ብቻ በመታገዝ እንደው ዝም ተብሎ ታዋቂ ሙዚቀኛ መሆን አይቻልም፡፡
ስለሆነም ጠንካራ መሰረት ለመጣል ይቻል ዘንድ በመጀመሪያው ወቅት የመስኩን ምሁራን የረጅም ጊዜ ታሪክ ካላቸው ሀገራት በማስመጣት ያስፈልጋል ፡፡ ሀገርኛ የሆነውን የባህል ሙዚቃ ለማበልጸግና ሥርአት ለማስያዝ የምንችለውም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ባገኘው የሙዚቃ ትምህርት ላይ ተመርኩዘን ስንቀሳቀስ ይመስለኛል፡፡ ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ፣ አቶ ተስፋዬ ለማ ፣ እማሆይ ጽጌማርያም፣ አቶ ሙላቱ አስታጥቄ፣ ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሐቅ( ከ17 በላይ ቋንቋ ይናገራሉ፡፡ በ1950ዎቹ ወደ ኢትዮጵያ በመሄድ በዘመኑ የነበረውን የፖሊስ ሲምፎኒ ኦርኬስትራ በመምራት ሙዚቀኞችን ሲያበረታቱ የነበሩ ናቸው)፣ ዶክተር ትምክሕት ተፈራ ( የታዋቂው ፒያኒስት የአቶ ተፈራ መኮንን ልጅ ነጭ፡፡
አባቷ በፒያኖ አጨዋወት አራቅቀዋታል፡፤) ፣ አበጋዝ ክብረወርቅ፣ ሄኖክ ተመስገን፣ ግርማ ይፍራሸዋ ( ከእማሆይ ጽጌማርያም ገብሩ በኋላ በፒያኖ አጨዋወቱ ጉልህ ተደናቂነትን
የተጎናጸፈ)፣ ጋሼ ሀይሎ መርጊያ ወዘተ ወዘተ ከኢትዮጵያ አልፈው በአለም አቀፍ ደረጃ ዝናቸው  የናኘው ሀገርኛውን የሙዚቃ ትውፊት ( ቱባውን ባህላዊ የሙዚቃ ሀብታችንን ) ሳይለቁ ከዘመናዊው ሙዚቃ ጋር በማዋሃዳቸው፣ ለረጅም አመታት በማጥናታቸው፣ አንዲሁም የምርምር ውጤታቸውን ተግባራዊ ለማድረግ በመቻላቸው ነው፡፡
መግቢያ ሙዚቃ የሰው ልጆች በከፍተኛ ደረጃ ከሚጠቀሙባቸው ሙያዎች አንዱና ጥበብን የተሞላች ሀብት ናት፡፡ ዓለም በሳይንስና ቴክኖሎጂ ያደረገው መራቀቅ ለሙዚቃም እድገት ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል፡፡ ቀድሞ ሙዚቃን ለማግኘት በቤተክርስቲያን አካባቢ ወይም በዓላትን በመጠበቅ ካልሆነ በየዕለቱ በሙዚቃ መጠቀም አይቻልም ነበር፡፡ ዛሬ በሳይንስና ቴክኖሎጂ በገፉ ሀገሮች ሙዚቃ በየአሳንስሩ፣ በየገበያው አዳራሽ፣ በሆቴሎች፣ በመንገድ ላይ፣ ሌላው ቀርቶ ፣እዬዬ ሲዳላ ነው ካልተባለ፣በመጸዳጃ ቤቶች ሳይቀር ሙዚቃ የሌለችበት የለም ማለት ይቻላል፡፡ ይህም የሚያሳየው ሙዚቃ በሰው ልጆች ዘንድ ምን ያህል ተወዳጅና አስፈላጊም አንደሆነች ነው፡፡
በአሁኑ ጊዜ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ከፍተኛ ሀብት ከሚያስገኙ ሥራዎች አንዱ ሥለሆነ በተለይ በኢንዱስትሪ በገፉት አሜሪካና በአውሮፓ ያሉ አርቲስቶች በሀብታቸውና በዝናቸው በዓለም የገነኑ ናቸው፡፡ የሙዚቃ ሙያ ከተሰጥዎ በተጨማሪ ከፍተኛ ዕውቀት ስለሚያስፈለገውና ውድድርም ስላለበት ተደማጭነትንና ስኬትን ለማግኘት በትምህርት መደገፍ አለበት፡፡
የክብር ዘበኛ አንደኛ ኦርኬስትራ ስለ ጋሼ ጥላሁን ገሠሠ ታላቅ የሙዚቃ ሰውነት እና ልእለ ሥራዎች ስንዘክር ዝነኛውን የክቡር ዘበኛ የሙዚቃ ኦርኬስትራ በፍጹም መዘንጋት
አይቻልም፡፡ ጥላሁን ፣ ጥላሁን ሊሆን የተቻለው በዝነኛወ የሙዚቃ ኦርኬስትራ የሙዚቃ
አቀናባሪዎች፣ ደራሲዎች እና የሙዚቃ አባላቱ
የማይዘነጋ ውለታ ነው፡፡ ምንም እንኳን ጋሼ
ጥላሁን ጩጬ ሆኖ ከወሊሶ ጋሼ ኢየኤል ወደ
ሀገርፍቅር ቲያትር ቤት በማምጣት የሀገር
ፍቅር ስሜት ቢያሰርጹበትም፡፣ ከጥቂት አመታት
በኋላ ወደ ክቡር ዘበኛ የሙዚቃ ኦርኬስትራ
የተቀላቀለው ጥላሁን ሰም ገናና ለመሆን
ችሏል፡፡ በነገራችን ላይ ይህ የሙዚቃ
ኦርኬስትራ የማእከላዊ እዝ የሙዚቃ ኦርኬስትራ
በሚል መጠሪያ ይታወቅ አንደነበር የአሁኑ
ትውልድ መገንዘብ አለበት፡፡ ለማናቸውም
አመሰራረቱን በወፍ በረር ላስቃኛችሁ፡፡
የክብር ዘበኛ አንደኛ ኦርኬስትራ የተቋቋመው
የአጼ ሐይለስላሴን የአውሮፓ ጉብኝት ተከትሎ
እንደሆነ ይነገራል፡፡ የተለያዩ  ሀገራት
መንግስታት ለክብራቸው በሚያዘጋጁት የራት
ግብዣ ላይ ሙዚቃ የሚያቀርቡትን የቻምበርና
የጃዝ ሙዚቀኞች በአድናቆት ተመልክተው
እንደነበር ኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ
ያስተምረናል፡፡ እናም እንዲህ አይነቱ ባህል
በሀገራችን እንዲጀመር ንጉሱ ለጄኔራል
መንግስቱ ንዋይ መመሪያ መስጠታቸውን የሚያሳይ
መረጃ ‹‹ አቶ ተስፋዬ ለማ የኢትዮጵያ ሙዚቃ
ታሪክ በሚል ርዕስ ባዘጋጁት መጽሐፍ ላይ
ይገኛል ›› በትራምፔት ሙዚቃ ተጫዋቺነታቸው
የተደነቁትና የቡድኑ አስተባባሪ የነበሩት
ሻለቃ ጽጌ ፈለቀ በአንድ ወቅት ለአቶ ተስፋዬ
ለማ እንዳጫወቱት በዚያን ዘመን የነበረው
የክብር ዘበኛ አንደኛ ኦርኬስትራ ደረጃ
የሚያስደንቅ ነበር፡፡ ጅምሩ በዚያ ቢቀጥል
ኖሮ፣ አሁን የሚታየው የሀገራችን የሙዚቃ
መልክ ሌላ ይሆን እንደነበር ጨምረው
ነግረዋቸው ነበር፡፡ የክብር ዘበኛ ሰልፈኛ
ሙዚቃ ክፍልና የክብር ዘበኛ አንደኛ
ኦርኬስትራ የተቋቋሙት የሁለተኛው የአለም
ጦርነት ካበቃ በኋላ ነበር፡፡ ዘመኑም
የአሜሪካ ሙዚቃ በአውሮፓና በብዙ ሀገሮች
ጭምር የተስፋፋበት ሰለ ነበር የሰልፈኛውም
ሆነ የኦርኬስትራው ክፍል የሚጫወቱት
በአብዛኛው የአሜሪካንን የሙዚቃ ስልት
ተከትለው ነበር፡፡
የክብር ዘበኛ ሁለተኛ ኦርኬስትራ
በ 1946 ዓ.ም. ገደማ ስድስት ኪሎ፣ ከአንበሶቹ ግቢ
አጠገብ ፣ ዜናና ዘፈን የሚተላለፍበት የራዲዮ
ድምጽ  ማጉያ  ( ላውድ ስፒከር ) አንደነበር
ታሪክ ይነግረናል፡፡ በዚያን ዘመን ራዲዮ
እጅግ እጅግ ውድ ስለነበር በዝቅተኛ ደረጃ
ይገኝ የነበረው አብዛኛው የአዲስ አበባ ህዘብ
የራዲዮ ፕሮግራሞችን የሚሰማው የድምጽ
ማጉያዎች በተሰቀሉበት የከተማዋ ልዩ ልዩ
አደባባዮች  በመኮሎኮል ነበር፡፡ ከአንበሶች
ግቢ አጠገብ በተተከለው የራዲዮ መስሚያ
አማካይነት ከክብር ዘበኛ ዋና መሥሪያ ቤት
የሚተላለፍ ጠቅል የሚባል የራዲዮ ፕሮግራም
ተከፍቶ እንደነበር ከታሪክ እንማራለን፡፡
ይሀው ራዲዮ የታዋቂው ካሳ ተሰማ የክራር
ዘፈኖች፣ በማንዶሊንና በጊታር ይታጀቡ
የነበሩት የጥላሁን ገሠሠ፣ ብዙነሽ በቀለ፣
ላቀው አየለ፣ የመቶ አለቃ ኑሩ ወንድአፍራሽ፣
ሸዋንዳይ በለጠ፣ ተፈራ ካሳና ሌሎችም
በኅብረት የሚዘምሩ ድምጻውያን ሥራዎች
የሚቀርቡበት ተወዳጅ የመዝናኛ የሙዚቃ
ፕሮግራም እንደነበረው የሚያሳዩ መረጃዎች
በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ መጽሐፍ ላይ
ይገኛል፡፡ በዚህም የተነሳ ወሬው በከተማዋ
ዙሪያ መሰራጨት ጀመረ፡፡ በዚያን ዘመን
ከአቡነጴጥሮስ ሐውልት አጠገብ ከነበረው
የኢትዮጵያ ራዲዮ በቀር ሌላ ማስተላለፊያ
አለነበረም፡፡ ( አቡነ ጴጥሮስ አካባቢ (አጠገብ
) የነበረው የቀድሞው ማስታወቂያ ሚኒስቴር
ወይም ራዲዮ ጣቢያ ዛሬ እንዳልነበረ ሆኗል፡፡
በቅጥር ግቢው ውስጥ ግዙፍ ህንጻ
እየተገነባበት ይገኛል፡፡ አንድም ቅርስ
አልተረፈም ሁሉም ፈርሶ ነው ሌላ ዘመናዊ ህንጻ
እየተከመረ የሚገኘው፡፡ ሰሞኑን 85ኛ አመቱን
የኢትዮጵያ ራዲዮ ልደት እየተከበረ ስለመሆኑ
ከመገናኛ ብዙሃን ተሰምቷል፡፡ ይህ ባልከፋ
ሆኖም ግን ይሁንና አቡነጴጥሮስ አጠገብ
የነበረው ራዲዮ ጣቢያ ሙሉበሙሉ ሲፈርስ ለምን
ብሎ የጠየቀ ጋዜጠኛ ስለመኖሩ አልሰማሁም፡፡
ቢያንስ ሰቱዲዮ ክፍል የነበሩት በታሪክ ቅርስ
ቢቀመጡ የአባት ነበር፡፡ ይህ ራዲዮ ጣቢያ እነ
ጋሼ አሳምነው ገብረወልድ፣ በአሉ
ግርማ፣ብርሃኑ ዘሪሁን፣ አሃዱ ሳቡሬ አጠገበኝ
ወሬ፣ ጋሼ ሙሉጌታ ሉሌ፣ ታደሰ ሙሉነህ፣ሂሩት
ታደሰ፣ ጋሼ ንጉሴ አክሊሉ፣ አዲሱ ለገሰ፣
ሻለቃ ግርማ ይልማ ወዘተ ወዘተ በሃላፊነትና
በጋዜጠኝነት ሙያ የሰሩበት ራዲዮ ጣቢያ
ነበር፡፡ቅርስነቱ ግን አልተጠበቀም
ያሳዝናል፡፡) እስከ መቼ ነው የኋላ ታሪካችንን
አሽቀንጥረን በመጣል እንደ አዲስ መጀመራችን
የሚቀጥለው፡፡ የቀድሞው ራዲዮ ጣቢያ ቅጥር
ግቢ ውስጥ የነበሩ ቤቶች ፈርሰው ዘመናዊ ህንጻ
መገንባቱ የእድገት ምልክት መስሎ ቢታይም
ለምልክት ዋና ዋና የሥራ ክፍሎች የነበሩትን
ማስቀረት ይቻል ነበር፡፡ ይህን ለማድረግ
ገርን አልተቻለም፡፡ በእውነቱ ቆሽት
ያሳርራል፡፡ የአደጉት ሀገራት የቀድሞ
አባቶቻቸው የደከሙበትን ስራ ሲያሻሽሉ ፣
የቀደሙ ስራዎችን አፈርድሜ በማስጋጥ
አልነበረም፡፡ በአፍሪካ በተለይም በኢትዮጵያ
ምድር የበቀሉ እንደወያኔ አይነት ቂመኛ
አገዛዞች ያለፉትን ታሪኮች ሁሉ ጥላሸት
በመቀባት እንደ አዲስ መጀመር የተለመደ
ተግባሩ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ የማስታወቂያ
ሚኒስቴርን ( ራዲዮ ጣቢያ ቅጥር ግቢ የሚገኙ
ስቱዲዮችና ሌሎች የስራ ክፍሎች የፈረሱት በ2010
ዓ.ም. በፊት መሆኑን አስታውሳለሁ፡፡ )
በጊዜው የማስታወቂያ ሚኒስቴርንና የሀገር
ፍቅር ቲያትርን ደምረው የሚመሩት ክቡር አቶ
መኮንን ሀብተወልድ ነበሩ፡፡ አቶ መኮንን
ለንጉሠ ነገሥቱና ለዙፋኑ አሰጊ መስለው
የሚታዩ ነገሮችን ዘውትር በንቃት እንዲከታተሉ
ገደብ የሌለው ሥልጣን የተሰጣቸውና በንጉሱም
ዘንድ እምነት የተጣለባቸው ነበሩ፡፡ በዚህም
የተነሳ በብዙዎች ዘንድ የተፈሩ ነበሩ፡፡
የታኅሳሱ ግርግር ዕለት አቶ መኮንን በስድስት
ኪሎ አካባቢ በቮልስዋገን መኪና ሆነው
ሁኔታውን በቅርብ ይከታተሉ አንደነበር
በተለያዩ የታሪክ መጽሐፍት ላይ ሰፍሮ
ይገኛል፡፡
በዚያን ዘመን የወታደሩ ደሞዝ ሃያ ስድስት ብር
ብቻ ስለ ነበር ከምግብ ተርፎ ሶስት ብር
ሊከፍልና ሀገር ፍቅር ገብቶ ቴያትርና ዘፈን
ለማየት አቅሙ አይፈቅድለትም ነበር፡፡ ስለዚህ
በሰራዊቱ ውስጥ የሚገኙትንና ልዩ ልዩ ችሎታ
ያላቸውን በማሰባሰብ ከሰልፈኛው የሙዚቃ ቡድን
የተወጣጡ ሙዚቀኞችን በማደራጀት የክብር ዘበኛ
ሁለተኛ ኦርኬስትራ በ1947 ዓ.ም. ተቋቋመ፡፡ (
የኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ገጽ 149 )
ጄኔራል  መንግስቱና የክብር ዘበኛ መኮንኖች ፣
ለክፍላቸው ከፍተኛ ቀናኢነት ነበራቸው፡፡
በዚህም ተነሳ ከተወዳዳረዎቻቸው ከምድር ጦርና
ከፖሊስ ሠራዊት ልቆ ለመገኘት ያለሰለሰ ጥረት
ያደርጉ ነበር፡፡ ለምሳሌ የክብር ዘበኛ
ሁለተኛ ኦርኬስትራ ሲቋቋም ከኦርኬስትራው
በተጨማሪ የዳንስ ወይም የውዝዋዜ ክፍል ፣
የድምጻውያን የግጥምና የዜማ ባለሙያዎች
እንዲጠቃለሉበት አድርገዋል፡፡
ይህም

ጄኔራል መንግስቱና የክብር ዘበኛ መኮንኖች
ለክፍላቸው ከፍተኛ ቀናኢነት ነበራቸው፡፡
በዚህም የተነሳ ከተወዳደሪዎቻቸው ከምድር
ጦርና ከፖሊስ ሠራዊት ልቆ ለመገኘት ያለሰለሰ
ጥረት ያደርጉ ነበር፡፡ ለምሳሌ የክብር ዘበኛ
ሁለተኛ ኦርኬስትራ ሲቋቋም ከኦርኬስተራው
በተጨማሪ የዳንስ ወይም የውዝዋዜ ክፍል ፣
የድምጻውያን፣ የግጥምና ዜማ ባለሙያዎች
አንዲጠቃለሉበት አድርገዋል፡፡
ይህም እርምጃ ወደ በስትኋላ ለተፈጠሩ የሙዚቃ
ድርጅቶች ምሳሌ የሆነው የክብር ዘበኛ ሁለተኛ
ኦርኬስትራ እንዲቋቋም አስተዋጽኦ
አድርጓል፡፡ ቀደም ባለው ጊዜ የሚደረሱ
የሙዚቃ ግጥሞችና ዜማዎች ከጊዜና ከተወሰነ
ርዕሰ ጉዳይ ተዛምደው ደንብና መመሪያን
ተከትለው የሚዘጋጁ አልነበሩም፡፡ የግጥሙ
ደራሲ፣ የዜማው ደራሲ፣ ሙዚቃውን ያቀነባበረው
ወዘተ የሚለው ሥርአት የተከተለው የክብር
ዘበኛ ሁለተኛ ኦርኬስትራ ከተቋቋመ በኋላ
ነበር፡፡
ይህም የሆነው በ1950ዎቹ መሆኑ ነው፡፡ በክብር
ዘበኛ ሁለተኛ ኦርኬስትራና በድምጻውያን
ይቀርቡ የነበሩ ሙዚቃዎች አዳዲስ ስልቶችን
በማስተዋወቅ የኢትዮጵያ ህዝብ ለሙዚቃ
የነበረውን አስተሳሰብ እንዲያሻሽል
አድርገዋል፡፡ በዚሁ ወቅት የሻምበል አፈወርቅ
ዮሃንስና የአምሳ አለቃ ገዛኀኝ ደስታ ግጥሞች
፣ የአሥር አለቃ ተዘራ ኃይለሚካኤል፣ የመቶ
አለቃ ግርማይ ሐድጎ ( ኋላ ሻለቃ)፣ የአሥር
አለቃ አየለ ማሞ ( ኋላ ሻምበል ) እና የአቶ
አቡበከር አሸጌ የዜማ ድርሰቶች በነ ጥላሁን
ገሠሠ፣ ብዙነሽ በቀለ፣ ማሕሙድ አሕመድና
በመሳሰሉት ድምጻውያን ሲዜሙ የሙዚቃ ታዳሚው
ቁጥር እየጨመረ መጣ፡፡፡ ከ1947 እስከ 1990
በኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ጉልህ ሚና ሲጫወት
የነበረው የክብር ዘበኛ ሁለተኛ ኦርኬስትራ
በተዳከመ መልክም ቢሆን እስከ ፍጻሜ ደርግ
ከቀጠለ በኋላ ጨርሶ ሊፈርስ በቅቷል፡፡
በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ ወተደራዊ መንግስት
የቀድሞ ስሙን ቀይሮ ፣ የማእከላዊ እዝ
ኦርኬስትራ በሚል ስም ቢቀይረውም ይህን ዝነኛ
የሙዚቃ ባንድ አላፈረሰውም፡፡ የቀድሞው ክቡር
ዘበኛ የሙዚቃ ኦርኬስትራም ሆነ የክቡር ዘበኛ
ሰልፈኛ የሙዚቃ ኦርኬስትራ የፈረሱት በህውሃት
አገዛዝ ዘመን ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሰልፈኛ
የሙዚቃ ኦርኬስትራ ታሪክ አሁን ድረስ ተተኪ
ያተገኘለት ዜንጦውና ቴክሱ ‹‹ ሲሳይ ››
የክቡር ዘበኛ ትርፉት ነበር፡፡ ቂመኛውና
ሴረኛው የህውሃት አገዛዝ ‹‹ የኢትዮጵያን
የጦር ሰራዊት ›› ‹‹ የደርግ ሰራዊት ነው ››
በሚል የደካሞች ፍልስፍና ሲያፈርስ፣
የቀድሞውን የክቡር ዘበኛ ኦርኬስትራ መለማማጃ
ህንጻ ሙጃ እንዲበቅልበት በህይወት የነበሩትን
የኢትዮጵያ ባለውለታ ሙዚቀኞች በሀገራቸው
ምድር ባይተዋር አድርጓቸው አልፏል፡፡ እንደነ
ሃምሳ አለቃ ዘውገ፣ ሻምበል አየለ ማሞ፣ ወዘተ
ያሉበት አንድ ሰብስብ ‹‹ የክቡር ዘበኛ ቅርስ
›› የተሰኘ ባንድ በማቋቋም ለጥቂት አመታት
ቢቀጥልም አንድ የሙዚቃ ካሴት ከተዘጋጀ ቡድኑ
የሙዚቃ ቡድኑ ተበትኖ ቀርቷል፡፡ በነገራችን
ላይ የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ከእነ አምሳ አለቃ
ዘውገ ጋር በመሆን ባንዱን መልሶ ለማቋቋም
የበኩሉን ጥረት አድርጎ እንደነበረ አንባቢውን
ያስታውሳል፡፡
ለረጅም ዘመናት በአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ
ተወዳጅ የነበሩት ጥላሁን ገሠሠ፣ ብዙነሽ
በቀለ፣ ተፈራ ካሳና እሳቱ ተሰማ ፣ ታዋቂው
የዜማ አቀናባሪ ኮሎኔል ሳህ ደጋጎ፣ በዘመኑ
በሙዚቃ ድርሰት ተደናቂ የነበሩት ተዘራ
ኃይለሚካኤል፣ ሻምበል አየለ ማሞ፣ የመቶ
አለቃ ኑሩ ወንድአፍራሽና አንጋፋው ድምጻዊ
ማሕሙድ አሕመድ ክብር ዘበኛ ካፈራቸው
ሙያተኞች ውስጥ ዋና ዋናዎቹ ናቸው ማለት
ይቻላል፡፡ ምንም እንኳን የክቡር ዘበኛ
ኦርኬስትራ በወያኔ ቂመኝነት ውሳኔ ቢፈርስም
የሙዚቃው ኦርኬስትራ አባላትና ስራዎቻቸው
በኢትተጵያ የሙዚቃ ታሪክ ያላቸውን የክብር
ስፍራ ማንም ለነጥቃቸው አይቻለውም፡፤ ሻምበል
አፈወርቅ ዮሃሰ፣ አመሳ አለቃ ገዛኀኝ ደስታ፣
ሻለቃ ግርማ ኀድጎ፣ ፣ ኮሎኔል ኃይሉ
ወልደማርያም፣ ኮለኔል አሰፋ ጉርሙ፣ ካሳ
ተሰማ፣ ሻለቃ ጽጌ ፈለቀ፣ተፈራ ካሳ፣ ብዙነሽ
በቀለ፣ እሳቱ ተሰማ፣ አቡበከር አሸጌ በፍጹም
ሊዘነጉ የማይችሉ የሙዚቀ ሰዎች ናቸው፡፡
አምሳ አለቃ ገዛኀኝ ደስታ የክብር ዘበኛ
የመድረክ አስተዋዋቂ ከመሆኑ በተጨማሪ ለልዩ
ልዩ ድምጻውያን ግጥሞችን በማቅረብ የታወቀ
ባለሙያም ነበር፡፡ ከአምሳ አለቃ ገዛኀኝ
ደስታ ግጥሞች አንዱ
እርቦት የነበረ፣ እየተጨነቀ፣
እንጀራ አገኛና ፣ ምሳ በልቶ ሳቀ፡፡
እስቲ ስለ ሻለቃ ጽጌ ፈለቀ  ትንሽ ላስታውስ፡፡
በክብር ዘበኛ አንደኛ ኦርኬስትራ የዛሬ ሃምሳ
ሰባት አመት በፊት በትራምፔት አጨዋወት መሪ
ነበሩ ፡፡ በችሎታቸው ተመርጠው ቪየና
በሚገኘው ከፍተኛ ተቋም ለትምህርት ሄደው
ነበር፡፡ ሻለቃ ጽጌ ባላቸው ከፍተኛ ዕውቀት
የክብር ዘበኛ ሙዚቃ ክፍል ኃላፊም ሆነው
ሠርተዋል፡፡ ከዚህም ሌላ ፣ በያሬድ ሙዚቃ
ትምህርት ቤት መምህር ሆነው አገልግለዋል፡፡
ሻለቃ ጽጌ ተጫዋች፣ በሥራቸው ጥንቁቅና
ቆፍጣና ወታደር ነበሩ፡፡
ውድ የሃበሻ ገጽ አንባብያን ከላይ በወፍ በረር
ያስቃኘኋችሁን ወደር የማይገኝላቸውን የሙዚቃ
ሰዎችን ያፈራውን  ‹‹ የኢትዮጵያ የሙዚቃ
ኦርኬስትራ ዋርካ የክቡር ዘበኛ የሙዚቃ
ኦርኬስትራን ›› ነበር የወያኔ አገዛዝ
ያፈረሰው ፡፡ በእውነቱ ያሳዝናል፡፡ ልብንም
ይሰብራል፡፡ ለማናቸውም የአሁኑ ትውልድ ዘመኑ
በዋጀው ቴክኖሎጂ ኢነትርኔት በመጠቀም
የቀድሞውን የክቡር ዘበኛ የሙዚቃ ስራዎች
በመመርመር ሊማርበት ይገባል የሚለውን
ማስታወሻዬን በማስፈር ወደ ጋሼ ጥላሁን
ትውስታ ልወሰዳችሁ፡፡
ጥላሁን ገሠሠ
ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ በኢትዮጵያ
ሳያቋርጥ የተጠራና ከከተሜው እስከ ገጠሬው
አብዛኛው ህዝብ የሚያወቀው ዝነኛ ስም ቢኖር
የጥላሁን ይሆናል፡፡ ጥላሁን ገሠሠ ከእሱ
በፊት ማንም ሳይኖር የአዘፋፈን ስልትና
የመድረክ አቀራረብን በራሱ ፈጠራ ከእሱ በኋላ
ለመጡ ብዙ ድምጻውያን ምሳሌ በመሆን ምሳሌ
የሆነ ታላቅ ድምጻዊ ነው፡፡ ከእሱ በፊት በዚህ
ደረጃ የሚጠቀስ ሌላ ባለሙያ አልነበረም፡፡
በኢትዮጵያ ብዙ ድምጻውያን የመውጣታቸውን
ያህል እንደ ጥላሁን ገሠሠ ረዘም ላለ ጊዜ
ዝናቸውና ሙያቸው ገኖ የታወቁ ቢኖሩ ከጥላሁን
ቀጥሎ ያለውን ደረጃ የሚይዙ ቢሆን ነው፡፡
በሙዚቃ ሙያ ከአምሳ አመታት በላይ ቀርቶ
ለአምስትና አስር አመታት እንኳን ዝናን ጠብቆ
መቆየት ከፍተኛ ተሰጥኦና ችሎታን ይጠይቃል፡፡
ጥላሁን ገሠሠ በዘፈኑ ያልዳሰሰው ነገር
የለም፡፡ ስለ ፍቅር፣ ጥላቻ፣ ማግኘት፣
ማጣት፣ በሽታ፣ ገንዘብ፣ ቅንነት፣ ስለ ሀገር
ውበት፣ ስለ ጀግንነት፣ ስለ ሰብአዊ መብትና
ስለሌሎችም ጉዳዮች ተደማጭነት ባለው ድምጹ
የሚቻለውን ሁሉ አድርጓል፡፡ ለረጅም ጊዜ
በኢትዮጵያ ሕዝብ የተወደደው ጥላሁን ገሠሠ
ከዚህ አለም በሞት በተለየበት ጊዜ በኢትዮጵያ
ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ  እጅግ ብዙ ሕዝብ
በማይታወቅ ሁኔታ እጅግ ብዙ ሕዝብ ተገኝቶ
አክብሮቱንና ፍቅሩን አሳይቷል፡፡ በብዙ
ሚሊዮን የሚቆጠር ኢትዮጵያዊም በታላቅ ሃዘን
ውስጥ ተዶሎ እንደነበር የቅርብ ግዜ ትዝታችን
ነው፡፡
ጋሼ ጥላሁን ገሠሠ በክብር ዘበና ኦርኬስትራ
ከቀዳሚዎቹ ድምጻውያን አንዱና ዋናው ነው፡፡
ከዚያ በፊት ለጥቂት ጊዜያት በሀገር ፍቅር
ቴያትር ቤት ቢሠራም ፣ ማንነቱንና ተሰጥዎን
በሚገባ ያስመሰከረው ግን ወደ ክቡር ዘበኛ
ሁለተኛ ኦርኬስትራ ከገባ በኋላ ነው፡፡
ከፒያኖ፣ ሳክስፎን፣ ክላርኔት፣ ትራንፔትና
ትሮንቦንን ከመሳሰሉ የሙዚቃ መሳሪያዎች ፊት
ለፊት ቆሞ በማዜም ለዘመናዊ አቀራረብ በር
የከፈተ ፣ የተመልካቹን ስሜት የሳበና ከአምሳ
አመታት በላይ በተወዳጅነት የቆየ ታላቅ
ድምጻዊ ቢኖር ጥላሁን ገሠሠ ነው፡፡ ጥላሁን
ገሠሠ የሙዚቃውን መልዕክት ግልጽ ባለ ሁኔታ
የማስተላለፍ ልዩ ችሎታ ያለው የኢትዮጵያ
ህዝብ ሙዚቃን እንዲያፈቅር ምክንያት የሆነ
ታላቅ ሰው ነበር፡፡ በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ልዩ
ልዩ ውብ ዜማዎችን ውብ በሆነ ድምጹ ያቀረበው
ጋሼ ጥላሁን ገሠሠ የምዕተ ዓመቱ ታላቅ የሙዚቃ
ሰው ቢባል አያንሰውም፡፡
እንደ መደምደሚያ
ያ የክቡር ዘበኛ የሙዚቃ ኦርኬስትራ
ተወረግራጊና ታላቅ የሙዚቃ ሰው ዛሬ በህይወት
የለም፡፡  የዚችን አለም ከተሰናበት ከሰምንት
አመት በላይ አለፈው፡፡ በጣሊያን ምድር
የጣሊያን የሙዚቃ ዋርካ ተብሎ እንደሚጠራው
ሚካኤል ሁሉ ጋሼ ጥላሁንም የኢትዮጵያ የሙዚቃ
ዋርካ ነው ተብሎ ቢጻፍ ሥህተት
አይመስለኝም፡፡ ሚካኤል በሀገሩ ጣሊያን
የተለያዩ የታሪክ ማስታወሻዎች እንደተሰሩለት
በአንድ ወቅት አዲስ አበባ በሚገኘው የጣሊያን
የባህል ማእከል ስራዎቹ ሲዘከሩ ለህዝብ
ሲነገር ቁጭ ብዬ አድምጫለሁ፡፡ እዚህ
ኢትዮጵያ ውስጥ በቀድሞው አራተኛ ክፍለጦር
አካባቢ ለዝነኛው ድምጻዊ ጋሼ ጥላሁን
በአደባባይ ሀውልት ሊቆምለት ነው ተብሎ
ከተነገረ አመታት ቢቆጠሩም አሁን ድረስ
ገቢራዊ መሆን አልቻለም፡፡ ጥላሁን በየአመቱ
ሲዘከር የመጨረሻ ባለቤቱ ወ/ሮ ሮማን በዙና
ቤተሰባቸው ጥረት ነበር፡፡ ወ/ሮ ሮማን ጋሼ
ጥላሁን የተወለደበትን መስከረም 17 ቀን
ምክንያት በማድረግ በየአመቱ የጥላሁን ገሠሠ
እና የክቡር ዘበኛ ኦርኬስትራን ልእለ ሥራዎች
በመዘከራቸው ታሪክ ስፍራውን የሚነሳቸው
አይመስለኝም፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና በየአመቱ
መስከረም 17 ቀን ላይ የጋሼ ጥላሁንን ልእለ
ስራዎች ማቅረብ በቂ አይመስለኝም፡፡ ጋሼ
ጥላሁን የኢትዮጵያ የሙዚቃ ዋርካ ነው፡፡ ጋሼ
ጥላሁን ለእውነት ሲል የኖረ፣ ስለ እውነት
ያለቀሰ፣ ያዜመ በእውነት ምክንያት ያለፈ
የምዕተ ዓመቱ ታላቅ የሙዚቃ ሰው ነው፡፡ የጋሼ
ጥላሁን የሙዚቃ ሥራዎች በኢትዮጵያውያን እዝነ
ልቦና ውስጥ ሲነቀለቀሉ የሚኖሩ ናቸው፡፡
ስለሆነም ለዚህ ታላቅ የሙዚቃ ሰው ቀድሞ
በታሰበለት ቦታ ሀውልቱ ሊቆም ይገባል በማለት
ስጠይቅ በታላቅ ትህትና ነው፡፡ ለዚህ እውን
መሆን ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብና የኢትዮጵያ
መንግስት የባህል ሚኒስትር የስራ ሃላፊዎች
በዋነኝነት ሃላፊነት አለባቸው ብዬ
አስባለሁ፡፡

ከዚህ ባሻግር የሙዚቃ ትምህርት ቤት ለመመስረት እንደነ ታማኝ በየነ፣ ግርማ ተፈራ ካሳ፣ ተቦርነ በየነ፣ ጋሼ መሃሙድ አህመድ፣ አለምጸሃይ ወዳጆ ፣ቴዎድሮስ ታደሰ
(ቴዲ አፍሮ) ( ቴዎድሮስ ታደሰ ከጥላሁን ገሠሠ ወዲህ በህዝብ ዘንድ ልዩ ትኩረት ካገኙት የዚህ ድምጻውያን ነው ብዬ አስባለሁ፡፡) ሃላፊነቱን በመወሰድ ኢትዮጵያዊ ግዴታቸውን እንዲከውኑ ሳስታውስ በታላቅ አክብሮትና ትህትና ነው፡፡ በነገራችን ላይ የጠቀስኳቸው ታላላቅ የሙዚቃ ሰዎች እና ባለሙያዎች ለጥላሁን ያለቸውን
ክብር በአደባባይ ያሳዩ ናቸው፡፡ በተለይ ሆደ ቡቡው ታማኝ እና ታናሹ ተቦርነ የጋሼ ጥላሁንን አብዛኛውን ስራዎች በዘመናዊ የሙዚቃ ማሽን በማስቀመጥ ላደረጉት አበርክቶት ታሪክ ስፍራውን አይነሳቸውም፡፡ እስቲ ለጥላሁን ብቻ ሳይሆን ከዚህም ሰፋ አድርገን አንድ ታላቅ የሙዚቃ ማእከል ለኢትዮጵያውያን ታላላቅ የሙዚቃ ሰዎች መታሰቢያ ለማቆም መንፈሳዊ ወኔ እንታጠቅ፡፡

‹‹ ሆድ ይፍጀው …………›› እንዳለ ሚስጥርህን ሳትነግረን ድንገት በእለተ ፋሲካ የተለየህን  ጋሼ ጥላሁን የዘመናት ሂደት የማይሸራቸው ታላላቅ የሙዚቃ ስራዎችህ
በኢትዮጵያውያን እዝነ ልቦና ውስጥ ሲንቀለቀሉ ይኖራሉ፡፡

Filed in: Amharic