እንኳን ለኢሬቻ በዓል አደረሳችሁ!
ኢሬቻ የምስጋና እና የተስፋ በዓል ነው፡፡ በኦሮሞ ሕዝብ ባህል መሠረት ኢሬቻ የሚከበረዉ ዝናብን፣ ሰላምን፣ ምርት እና የትዉልድን ቀጣይነት የሚሰጥ ፈጣሪ (ዋቃ)ን ለማመስገን ነዉ፡፡
በዝናባማዉ ክረምት በጅረቶችና ወንዞች መሙላት ምክንያት ተቆራርጠዉ የነበሩ ቤተ ዘመዶች የሚገናኙበት በዓል ነዉ፡፡
የጅረቶችና ወንዞች መጉደል ብሎም በጨለማ ሚመሰለዉ የክረምት ወራት አልፎ በብርሃናማዉ የመጸዉ ወቅት መተካት የመከራና የችግር ጊዜያትን በማለፍ አዲስ ብሩህ ተስፋን በመሰነቅ ይመሰላል፡፡
እሬቻ ርጥብ ቄጠማን በመያዝ ለፈጣሪ ምስጋና የሚቀርብት በዓል ነዉ፡፡ ርጥብ ቄጠማ የልምላሜና |የብሩህ ተስፋ ምልክት ነዉ፡፡
በእሬቻ በዓል የበዓሉ ተሳታፊዎች ርጥብ ቄጠማ በመያዝ የዘራነዉ ምርት ደርሶ እሸት የሰጠን፣ ልምላሜ እና ብሩህ ተስፋን ያጎናጸፈን ፈጣሪ ይመስገን በማለት ምስጋና የሚቀርብበት በዓል ነዉ፡፡
በኢሬቻ ላለፈው ምስጋና ይቀርብበታል፡፡ ለወደፊቱ ተስፋ ይሰነቅበታል፡፡ እነዚህ ሁለቱ እንደ ግለሰብም እንደ ሀገርም እጅግ አስፈላጊ ዕሴቶች ናቸው፡፡ ሕይወት ከምስጋና እና ከተስፋ ውጭ አትቀጥልም፡፡ በምስጋና ውስጥ ምሬትም እርማትም አለ፡፡ ምሬቱ ግን ምስጋና ወሰን የሚያወጣለት ምሬት ነው፡፡ በምስጋና ውስጥ እርማት አለ፡፡ እርማቱ ግን ምስጋና ወሰን የሚያወጣለት እርማት ነው፡፡
ልክ በወጥ ውስጥ እንዳሉ ቅመሞች፡፡ በወጥ ውስጥ የሚያቃጥለው በርበሬ፣ የሚቆጠቁጠው ሽንኩርት፣ ከበዛ ሊጎዳ የሚችለው ጨው አሉ፡፡ ሁሉም ግን በልካቸው እንዲሆኑ ‹ወጥ› የተባለው ማሕቀፍ ወስኗቸዋል፡፡
ሁሉም ከሚፈለገው ጣዕምና ውጤት አንጻር ተለክተውና ተመጥነው ይቀርባሉ፡፡ ማቃጠሉም፣ መለብለቡም፣ መቆጥቆጡም ያስፈልጋል፡፡ ግን የወጡን የጣዕም ልኬት እስካላጠፋው ድረስ ብቻ ነው፡፡ የሁሉም መጠሪያና የሁሉም መሰብሰቢያ የሆነውን ወጥ እስካላበላሸው ድረስ ነው፡፡
ምሬትና እርማትም የሚያስፈልጉበት ልክ አላቸው፡፡ ያም የምስጋናውን ልኬት እስካላጠፉት ድረስ ነው፡፡ የሕይወትን መዓዛ፣ የሀገርን ፍቅር እስካላበላሹት ድረስ ነው፡፡ በምስጋና ውስጥ እርማትና ምሬት አለ፡፡ በምሬትና በእርማት ውስጥ ግን ምስጋና የለም፡፡ ልክ በወጥ ውስጥ በርበሬ እንጂ፣ በበርበሬ ውስጥ ወጥ እንደሌለው ሁሉ፡፡
በእሬቻ ጊዜ የምናቀርበው ምስጋናም እንደዚሁ ነው፡፡ የሚያስመርሩ ነገሮች ነበሩ፤ የጠፉ የሚታረሙ ነገሮች ነበሩ፡፡ ፈታኝ መሰናክሎች ነበሩ፡፡ ሕይወትና ንብረት ያጠፉ መከራዎች ነበሩ፡፡ ግን እነዚህን ሁሉ ተሻግረናቸዋል፡፡ አልፈናቸዋል፡፡ ተወጥተናቸዋል፡፡ ስለዚህም ምስጋና ይገባል፡፡
ዕንቅፋቶቻችን ሰብረው አልጣሉንም፤ ጎትተው አላስቀሩንም፤ ስበው አላቆሙንም – ስለዚህም ምስጋና ይገባል፡፡ ከችግሮቻችን ተምረናል፤ ከፈተናዎቻችን ነጥረን ወጥተናል፤ ከስሕተቶቻችን ታርመናል – ስለዚህ ምስጋና ይገባል፡፡ የፈታኞቻችን ዓላማ አልተሳካም፡፡ አሳምመውን ይሆናል፤ ግን አይገድሉንም፡፡ አዘግይተውን ይሆናል፤ ግን አያስቀሩንም፡፡ ስለዚህም እናመሰግናለን፡፡
ኢሬቻ የተስፋ በዓል ነው፡፡ ሰው የትውስታ ዐቅም አለው፡፡ ስለዚህም ትናንትን ያስታውሳል፡፡ በትናንት ውስጥ መኖር ግን አይቻልም፡፡ ከትናንት ተምሮ ወደፊት መጓዝ የግድ ነው፡፡ ተስፋ በሌለበት ነገ የለም፡፡ ሰዎች በተዘጋ ግንብ ውስጥ ለዘመናት ኖረው ኅሊናቸው ሳይጎዳ እንዲወጡ የሚያደርጋቸው ተስፋ ነው፡፡ ነገን በተሻለ ማሰብ፡፡ ነገን እንደ አዲስ መጀመር፡፡ የትናንቱ ኮምጣጤ የነገውን ወተት እንዳያበላሽብን ማድረግ፡፡ የትናንቱ እንክርዳድ የነገውን ስንዴ እንዳይበክልብን ማድረግ፡፡ ተስፋ ማለት እርሱ ነው፡፡
ተስፋ ከሁለት ነገር ይመነጫል፡፡ ከእምነትና ካለማወቅ፡፡ ነገ ያልተነካ ዐቅም ነው፡፡ ያልተነካውን ዐቅም የተሻለ አደርገዋለሁ ብሎ ማመን ወሳኝ ነው፡፡ ነገን ለመለወጥ ዐቅምም፣ ክሂሎትም አለኝ ብሎ ማመን ያስፈልጋል፡፡
በብርሃን አሻግሮ ጨለማ ከማየት፤ በጨለማ አሻግሮ ብርሃን ማየት ይበልጣል ብሎ ማመን፡፡ ከእኔ የተሻለ የነገ ባለቤት መሆን የሚችል የለም ብሎ ማመን – ነው ተስፋ፡፡
ሁለተኛው የተስፋ ምንጭ ስለነገ አለማወቅ ነው፡፡ መገመት ይቻላል፡፡ በርግጠኝነት ግን ነገ ምን እንደሚሆን ሠፍሮና ለክቶ ርግጡን መናገር አይቻልም፡፡ ነገ ባለማወቅ የተሞላ ነው፡፡ ነገን ወደ ዕውቀት መቀየር የብልህ ድርሻ ነው፡፡ አምኖ ከተሠማራ ሰው ውጭ ነገ በርግጠኝነት የተገለጠለት የተለየ ሰው የለም፡፡ ለዚህ ነው ነገ ለሁላችን እኩል የሚሆነው፡፡
ትናንት በምናውቀው ምክንያት ለሁላችን እኩል ባይሆን እንኳን፣ ነገ ግን ለሁላችንም እኩል ነው፡፡ በነገ ውስጥ የምንበላለጠው፣ በተሻለ መልኩ ተዘጋጅተን በተሻለ መልኩ ከሠራን ብቻ ነው፡፡
ኢሬቻ የይቅርታ በዓል ነዉ፡፡ የተጣላና የተቀያየመ ሳይታረቅ፣ ይቅር ሳይባባል ወደ ታላቁን የኢሬቻ በዓል ወደማክበር አይሄድም፡፡ ኢሬቻ ያለፉ ቁስሎች በይቅርታ ታክመዉ የሚድኑበት፣ ቁርሾ እና ቂም በቀል ተወግዶ በዕርቅ የሚተካበት ታላቅ በዓል ነዉ፡፡ ከታላቁ የኢሬቻ በዓል የቂም በቀል እና |የጥላቻን ምዕራፍ በመዝጋት በዕርቅ፣ ይቅር ባይነት የከረሙ ቁስሎቻችን እንዳያመረቅዙ በፍቅር የማከም ሀገር በቀል ጥበብን የምንማርበት በዓል ነዉ፡፡
ኢሬቻ የአንድነት በዓል ነዉ፡፡ በአስደናቂዉና ታላቁ ኢሬቻ በዓል ከሁሉም ኢትዮጵያ ጫፍ የሚመጡ ብሄር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦችን የሚወክሉ ተሳታፊዎች የሚታደሙበት፣ ወንድማቸዉ ለሆነዉ የኦሮሞ ሕዝብ የእንኳን አደረሰህ መልካም ምኞት የሚገጹበት በዓል ነዉ፡፡ ተሳታፊዎች መጪዉ ጊዜ ብሩህ አንዲሆን የሚመራረቁት እና ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን በማጠናከር በወንድማማችነትና በዘመናዊ የማኅበረሰብ ዕሴቶች ላይ የተገነባች ጠንካራ አንድነት ያላትና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ምናደርገዉን ጥረት ለማሳካት የሚጠቅመን በዓል ነዉ፡፡
እሬቻ ላይ ስንሆን እነዚህን ታላላቅ ዕሴቶች እናስባለን፡፡ ቀደምቶቻችን ሀገራችንን ለዛሬ ያደረሷት፣ ሁሉ በእጃቸው ሁሉ በደጃቸው ሆኖላቸው አይደለም፡፡ የሚፈልጉት ተሟልቶ፣ የታገሉለት ተሳክቶ ብቻ አይደለም፡፡ በብዙ ሕመምና በብዙ ውጣ ውረድ ውስጥ አልፈዋል፡፡ የተሻለን ነገ ለማምጣት ሲሉ በትግልና ያለፈውን በምስጋና በመዝጋት ለዛሬ ደርሰዋል፡፡
ምሬት እንደ ቁስል እንዲመዘምዛቸው አልፈቀዱለትም፡፡ ጎትቶ እንዲያስቀራቸውና ጠልፎ እንዲጥላቸው አልተመቻቹለትም፡፡
ለመሆኑ የሀገራችንን ጉዞ ከእነዚህ ዕሴቶቻችን ውጭ ማሰብ እንችላለን? የሀገራችንን ያለፉትን ዓመታት ጉዞ በምስጋና እንዝጋው፡፡ ስኬቶቻችንን ቆጥረን – ይሄንን አግኝተናልና እናመሰግናለን እንበል፡፡ ስሕተቶቻችንንና ድክመቶቻችንን ቆጥረን እነዚህ ስሕተቶቻችን አላስቀሩንም፤ የሚታረሙበትና የሚሻሻሉበት ሌላ ዓመት አግኝተናል – እናመሰግናለን እንበል፡፡ የመሳሳትን ፈተና፣ የማረም ዕድል ያሸንፈዋል፡፡ የጥፋትና የወድመትን መከራ፣ የልማትና የሕዳሴ ዕድል ይረታዋል፡፡
መንገዳችን ያለቀ፤ መጽሐፋችን የተጠናቀቀ፤ ፋይላችን የተዘጋ፣ ወንዛችን የረጋ አይደለም፡፡ ከሠራንበት ዘመን ይልቅ ያልሠራንበት የወደፊቱ ዘመን ይበልጣል፡፡ ችግሩ አስተምሮናል፤ ፈተናው አብስሎናል፤ ስሕተቱ ታይቶናል፡፡ ከትናንቱ ዕውቀታችን የዛሬው፤ ከትናንቱ ብቃታችንም የአሁኑ ይበልጣል፡፡ ስለዚህም ነገን በተሻለ ዐቅም እንጠቀምበታለን፡፡ ትናንትን የሚለውጠው ነገ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ልጆች ሆይ፡፡ ከትናንት ተምረን፤ ትናንትን በምስጋና ዘግተን፤ ነገን የተሻለና የበለጠ ለማድረግ አንድ ሆነን እንነሣ፡፡ በኢሬቻ በዓል ላይ ወደ ንጹሕ የተፈጥሮ ውኃ እንሄዳለን፡፡ ርጥብ የተፈጥሮ ቄጤማ እንይዛለን፡፡ ሆራው ንጹሕ የሆነው፣ የደፈረሰው ጠርቶ ነው፡፡ ቄጤማው ለምለም የሆነው፣ የደረቀው ለምልሞ ነው፡፡ ኢትዮጵያም እንዲሁ ናት፡፡ የደፈረሱት መልኮቿ ደፍርሰው አይቀሩም፣ ይጠራሉ፡፡ የደረቁት ዕሴቶቿ ደርቀው አይቀሩም፣ ይለመልማሉ፡፡ ከሰኔ እስከ መስከረም ያለው ዝናብ በኦሮሞ ባህል የፈተናውን ዘመን ያስታውሳል፡፡ በወንዙ ሙላት መንገድ ይዘጋል፤ በክረምቱ ኃይል ወዳጅ ዘመድ ይለያያል፡፡ እህሉ ስለማይደርስ ቀጠና(ረሃብ) ይኖራል፡፡ Birraa(መከር/መፀው) ግን የተስፋ ዘመን ነው፡፡ እህል ይደርሳል፤ ውኃው ይጠራል፤ መንገድ ይከፈታል፤ ሰማዩ ይገለጣል፤ ወባ ይጠፋል፡፡ ጊዜውም Ganna ይባላል፡፡ የፈተናው ወቅት መዝጊያ ማለት ነው፡፡
ኢትዮጵያ Ganna ወቅት ላይ ናት፡፡ የፈተናውን ጊዜ እየጨረሰች ወደ Birraa(መከር/ መፀው) ዘመን የምትሻገርበት፡፡ Birraa(መከር/መፀው) ምንም እንኳን አስደሳች ወቅት ቢሆን ሥራ ግን ይፈልጋል፡፡ እህሉን ከአጥፊዎች መጠበቅ፣ ዐቅምን አሰባስቦ በአንድነት ማጨድ፣ መከመርና መውቃት፤ ወቅት ሳይጠብቅ የሚመጣ ዝናብ እህሉን እንዳይጎዳው ወትሮ ዝግጁ መሆን እና እህሉ በአጨዳና በዐውድማ ተፋስሶ እንዳይባክን ጥንቃቄ ማድረግ ናቸው፡፡ የሀገራችንም ሁኔታ እንደዚሁ ነው፡፡ የተስፋችን ዘመን – የኛ ትግል፣ ጥንቃቄ፣ ወትሮ ዝግጁነትና ጥበቃ ከታከለበት የተሳካ እንደሚሆን እምነቴ ነው፡፡
በድጋሚ መልካም የኢሬቻ በዓል ይሁን፡፡
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራ፣ ተከብራና በልጽጋ ለዘላለም ትኑር!
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
መስከረም 22፣ 2013 ዓ.ም