>

የጅምላ ግድያና የአገራችን ዕጣ ፈንታ (አርአያ ጌታሁን ተክለአቢብ)

የጅምላ ግድያና የአገራችን ዕጣ ፈንታ

በአርአያ ጌታሁን ተክለአቢብ 

ከቨርጂኒያ አሜሪካ


በኦሮሚያ ክልል በቡራዩ ያሟሸዉ ፍጅት በጥቅምት 2012 ዓ.ም. የ87 ሰዎችን ሕይወት ቀጥፎ በመጨረሻም በሰኔ ወር የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ እጅግ ዘግናኝና መጠነ ሰፊ ዕልቂት ሲያስከትል አስተዉለናል። ይህንን እየተደጋገመ፣ እያደገና እየተስፋፋ የመጣ ጉዳይ ከምንጩ ማድረቅ እስካልተቻለ ድረስ ነገ በምን መልኩ ጎልብቶ ዕልቂት ሊያመጣ እንደሚችል ከወዲሁ መገመት ከባድ ላይሆን ይችላል። ህሊና ላለዉ ሰዉ በብሔር፣ በሃይማኖትና ሌሎች ነገሮችን መሠረት በማድረግ በንጹሃን ዜጎች ላይ የሚደርስ ጭፍጨፋና ለዓመታት የተፈራን ንብረት በሰዓታት ዉስጥ ሲወድም እንደማየት የሚሰቀጥጥ ድርጊት አለ ብዬ አላምንም። ማንኛዉም ኢትዮጵያዊ በአገሩ በምድሩ ላይ በየትኛዉም ክልል የመኖርና ንብረት የማፍራት መብቱ ተነፍጎት መፈናቀሉ አልበቃ ብሎ ወደ ጭፍጨፋና ንብረት ወደማዉደም መሸጋገሩ እንዲሁ በደፈናዉ “አሳዛኝ” ነዉ በሚል ወይም በማዉገዝ ብቻ የሚታለፍ ጉዳይ አይደለም።  

እነዚህ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚፈጸሙት የጅምላ ግድያዎች (mass killings) ታልመዉና የተወሰነ የሕብረተሰብ ክፍል ላይ ያነጣጠሩ (በብሔርና በሃይማኖት) እንደሆኑ በስፋት እየተዘገበ ይገኛል። ይህ ደግሞ የዘር ማጥፋት ወንጀል (Genocide) ወደሚል እንድምታ ያመራል። በርግጥ እስከማዉቀዉ ድረስ በገለልተኛ አጣሪ ተመርምሮ “የዘር ማጥፋት” ወንጀል ተፈጽሟል በሚል ድምዳሜ ላይ የተደረሰበት የጅምላ ጭፍጨፋ የለም። ያም ሆነ ይህ ቢያንስ በ2012 ዓ.ም.  በሰኔ ወር ላይ የአርቲስቱን ሞት ተከትሎ የተፈጸመዉ የጅምላ ግድያ በዘፈቀደ የተደረገ ሳይሆን ስም ዝርዝር ተይዞ በማንነታቸዉ ብቻ ተመርጠዉ በቤታቸዉ ዉስጥ እንዳሉ ንጹሃን ግለሰቦች የግድያ ሰለባ እንደተደረጉ ከተለያየ አቅጣጫ ያጣሩ ሰዎች ምስክርነታቸዉን ሰጥተዋል። በመንግሥት መዋቅር ዉስጥ በአላፊነት ደረጃ የሚገኙ አንዳንድ ግለሰቦችም ይህንኑ አረጋግጠዋል። 

ሁሉም የዘር ማጥፋት ወንጀሎች (genocide) ጅምላ ግድያዎች ናቸዉ። ሁሉም የጅምላ ግድያዎች ግን የዘር ማጥፋት ወንጀሎች ናቸዉ ማለት አይቻልም። በጥቅሉ ጅምላ ግድያ ከፍተኛ ቁጥር ባላቸዉና በዉጊያ ላይ ያልተሰማሩ ሰዎች ላይ የሚፈጸም ግድያ ነዉ። ምን ያህል ቁጥር ያለዉ ሰዉ ሲገደልና አፈጻጸሙስ በምን ያህል ጊዜ ዉስጥ ሲከናወን ነዉ ጅምላ ግድያ ተብሎ የሚፈረጀዉ የሚለዉ ነጥብ ላይ ለመድረስ አንድ ወጥ የሆነ ስምምነት ላይ መድረስ አዳጋች ሊሆን ይችላል። 

የዘር ማጥፋት ወንጀል (genocide) በመንግሥት የሚፈጸም ሲሆን የጥቃቱ ሰለባ የሚሆኑት በዘር (race)፣ በብሔር (ethinicity)፣ በሃይማኖት (religion) ወይንም በቋንቋ (language) የተሳሰሩ ሰዎች ናቸዉ። ከፍተኛ ጥላቻ የሚንጸባረቅበትና ፍጹም ጭካኔ የተሞላበት ጭፍጨፋ ስለሆነ በእጅጉ የተወገዘ ነዉ። አፍሪካን ጨምሮ አለማችን በርካታ የዘር ማጥፋት ወንጀሎችን አስተናግዳለች። ለምሳሌ ናዚ ጀርመን በአይሁዶች ላይ፣ የቦስኒያ ሰርቦች በቦስኒያ ሙስሊሞች ላይ፣ የሱዳን መንግሥት በዳርፉር ላይ፣ ሩዋንዳ በቱትሲዎች ላይ … የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈጽሟል። የዘር ማጥፋት ወንጀል አለም አቀፍ ወንጀል እንደመሆኑ መጠን የትም አገር ቢፈጸም በአለም አቀፍ ሕግ መሠረት በሌላ አገር ሊታይና ሊዳኝ ይችላል። 

ይህ በእንዲህ እያለ ከዘር ማጥፋት ወንጀል በተጓዳኝ ፖሊቲሳይድ (politicide)፣ ዴሞሳይድ (democide) እና ክላሲሳይድ (classicide) የሚባሉ የጅምላ ግድያ ዓይነቶች አሉ። ፖሊቲሳይድ (politicide) የሚባለዉ እንደተለመደዉ የሆኑ ቡድኖች የሚገደሉበት ሆኖ በዘር ማጥፋት ኮንቬንሽን (genocide convention) ድንጋጌ ዉስጥ የማይሸፈን ሲሆን ነዉ። እንደዚህ ዓይነት ግድያዎች የሚፈጸሙት በመንግሥት አካል ሆኖ የፖለቲካ ይዘት አላቸዉ። ዴሞሳይድ (democide) በመንግሥት ወይንም ከፍተኛ ሥልጣን ባለዉ አካል ሆን ተብሎ በሚሰጥ ትዕዛዝ ያልታጠቁ ወይንም ትጥቅ በፈቱ ግለሰቦች ላይ የሚፈጸም ግድያ ነዉ። የዚህ ዓይነት አገዳደል ከፍርድ አካላት ዉጭ ባሉ ተቋማት/አካላት በሚሰጥ ትዕዛዝ የሚፈጸም ግድያን (extrajudicial summary killings) ስለሚጠቀልል በአገራችን በተለምዶ 60ዎቹ እየተባሉ በሚጠሩት የአጼ ሐይለሥላሴ ባለሥልጣናት ላይ የተፈጸመዉን የጅምላ ግድያ ይጨምራል። በመጨረሻም ክላሲሳይድ (classicide) ሆን ተብሎና ሲስቴማቲክ በሆነ መልኩ የአንድ መደብ (social class) አካል የሆኑ ሰዎች ላይ በከፊል ወይንም በሙሉ ለመደምሰስ የሚፈጸም የጅምላ ግድያ ዓይነት ነዉ። ለምሳሌ በቻይናና በሰሜን ቬትናም በመሬት ከበርቴዎች ላይ የተወሰደዉን ዓይነት የግድያ እርምጃ  ማለት ነዉ።

ለጅምላ ግድያ የሚሰጡት የተለያዩ ስያሜዎች የክፋቱን ደረጃና የጉዳቱን መጠን ለማስቀመጥ ካልሆነ በስተቀር የድርጊቱን ፈጻሚዎች የጥፋት ደረጃ ከማቅለል ጋር የሚያያዝ አይደለም። ምንም ዓይነት ስያሜ ይሰጠዉ የጅምላ ግድያ በሰዉ ልጅ ላይ ሊፈጸም የሚችል እጅግ የከፋና የሚሰቀጥጥ ወንጀል መሆኑ አያጠያይቅም። ከሁሉም በላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል የበለጠ የከፋና መጠነ ሰፊ በመሆኑ በየትም አገር ዳግም ሊከሰት የማይገባ ፍጹም አረመኔያዊ ድርጊት ነዉ።

የጅምላ ግድያ በምንም መልኩ እንደሌላ ወንጀል አጥፊዎችን በመቅጣት ብቻ የሚቆም አይደለም። በሌሎች አገሮች እንደታየዉ እያደገና እየተስፋፋ የሚመጣ ጉዳይ ነዉ። ስለሆነም ጉዳዩን ቀለል አድርጎ በማየት እንደተራ የብሶት መገለጫ አድርጎ በመቁጠር ወይም ከዚህ ብሔር ይህንን ያህል ሰዎች … ከዚያ ብሔር ደግሞ ያንን ያህል ሰዎች ናቸዉ የሞቱት በሚል እንደሒሳብ ሕግ “ማጣፋት” የሚመስል ትንታኔ መስጠት አንድም የችግሩን ጥልቀት ያለመረዳት ወይንም የራስን ብሔር ከጅምላ ተጠያቂነት ለማዳን የሚደረግ ርብርብ ከመሆን ባሻገር ወደፊት ተባብሶ ሊመጣ የሚችለዉን ችግር ከመፍታት አኳያ የሚፈይደዉ አለ ብየ አላምንም። ስለሆነም  ቆም ብሎ  የጥንስሱ መጀመሪያ ላይ አበክሮ በመሥራት ችግሩን ከሥሩ ነቅሎ መጣልን ይጠይቃል። አለበለዝያ ግን “ራስን መከላከል” በሚል ዘይቤ ወይም “በሰይጣናዊ የብቀላ መንፈስ በመሞላት” ወይም ደግሞ በአሁኑ ጊዜ እንደምናየዉ በቄሮ (ወይም ኦነግን አምላኪዎች) ላይ የተዘራዉ ክፉ ሀሳብ የዛሬ ተበዳዮችም ላይ በተመሳሳይ መልኩ እንዲዘራ ቢደረግ ማንም በቀላሉ ሊያቆመዉ በማይችል ደረጃ ፍጅትን እንዳያስከትል ሥጋት አለኝ። በርግጥ ከእግዚአብሔር ምህረት ቀጥሎ ኢትዮጵያዊ ጨዋነት እዚያ ደረጃ እንደማያደርሰን እምነት አለኝ። የሆነዉ ሆኖ ለግንዛቤ እንዲረዳ የቡሩንዲንና የሩዉዋንዳን ልምድ እንደምሳሌ ማንሳቱ ጠቃሚ ይመስለኛል። በዚያዉም ጅምላ ግድያ በታሪክ ሔደት ዉስጥ ምን ያህል እንደሰንሰለት እንደሚያያዝና ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዴት እየተስፋፋና እየከፋ እንደሚሄድ መረዳት ያስችላል። 

ሩዋንዳና ቡሩንዲ ተመሳሳይ ብሔር/ጎሣ ያላቸዉ እንደመንትያ ሊቆጠሩ የሚችሉ ሁለት ጎረቤት አገራት ናቸዉ። ሁለቱም አገራት ዉስጥ የሚገኙት ብሔረሰቦች ሁቱ፣ ቱትሲና ኢዋ (IWA) ናቸዉ። ከሁሉም በላይ የሚያስደንቀዉ የብሔር ስብጥሩም ተመሳሳይ ይዘት አለዉ። ማለትም ሁቱ ከ85 -86%፣ ቱትሲ 14-13% እንዲሁም ኢዋ 1% ናቸዉ። በሁለቱም አገራት ተመሳሳይ ቋንቋ ይነገርበታል። ሁለቱም አገራት በተለያየ ጊዜ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ አስተናግደዋል። እንዲሁም ሁለቱም አገራት ዉስጥ በሚፈጸም ቀዉስ ምክንያት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸዉ ዜጎች ወደ ጎረቤት አገራት ለስደት ተዳርገዋል።

በቡሩንዲ ከተፈጸሙ የዘር ማጥፋት ወንጀሎች መካከል እ.አ.አ. የ1972 እና የ1993 ዓ.ም.  ተጠቃሾች ናቸዉ። በ1972 ዓ.ም. በቱትሲ የበላይነት የሚመራዉ ጦርና መንግሥት በአገሪቷ ላይ በሚኖሩ ሁቱዎች ላይ ዘር ማጥፋት ፈጽሟል። በዚህ ጭፍጨፋ ያለቁ ሰዎች ከ100,000 እስከ 150,000 ሲገመቱ አንዳንዶች ግን እስከ 300,000 ድረስ ያደርሱታል። እንዲሁም በ1993 ዓ.ም. ቱትሲዎች ከፍተኛ ቁጥር ባላቸዉ የሁቱ ሕዝቦች ተጨፍጭፈዋል። ይህንንም ክስተት የአለም አቀፍ አጣሪ  ኮሚሽን (International Commission of Inquiry) የዘር ማጥፋት ነዉ ሲል ፈርጆታል።

ሩዋንዳ ለዓመታት ከፍተኛ በሆነ የጎሣ ዉጥረት (ethnic tension) ዉስጥ አልፋለች። ብዙዎችም ለስደት ተዳርገዋል። በርካታ ግድያዎችንም አስተናግዳለች። በመጨረሻም እ.ኤ.አ. 1994 ዓ.ም. ለሰዉ ልጆች ህሊና እጅግ የሚከብድና ዘግናኝ የሆነ የዘር ማጥፋት ለመከሰት በቅቷል። በ100 ቀናት ዉስጥም 800,000 ቱትሲዎች በሁቱዎች ተጨፍጭፈዋል። በርግጥ ከተገደሉት ዉስጥ ለዘብተኛ ሁቱዎችና የኢዋ ጎሣ አባላትም ይገኙበታል። የሆነዉ ሆኖ ይህን ጭፍጨፋ በስፋት ያካሄደዉ በወቅቱ የገዢዉ ፓርቲ (MRND) የወጣት ክንፍ የነበረዉና በሒደት ወደ ሚሊሺያ የተቀየረዉ ኢንተራሃምዌ (Interahamwe) ይባል የነበረዉ ነዉ።

በማንነት ላይ ተመስርቶ የሚደረግ እንቅስቃሴ ተፈጥሮአዊ የሆነዉን የሰዉ ልጅ ምክንያታዊነትንና ሚዛናዊነትን ስለሚያጠፋ በዚያ መንፈስ ሆነዉ ወደ ማጥቃት በሚሸጋገሩበት ጊዜ የአዉሬነት ባህሪ ይላበሳሉ። ስለዚህም ነዉ ለማዉራትና ለመጻፍ በሚከብድ መልኩ ክቡር የሆነዉን የሰዉ ልጅ አካል እስከመቆራረጥ ደረጃ በሩዋንዳ ዕልቂትም ሆነ በእኛም አገር እስከመከሰት የደረሰዉ። 

በእንደዚህ ጊዜ የእምነት ተቋማት ድርጊቱን ማዉገዝና የማዳን ተግባር መፈጸም ይጠበቅባቸዋል። ሩዋንዳ ላይ የሆነዉ ግን በተቃራኒዉ ነዉ። እንደ 1999 ሂዩማን ራይት ዎች (Human Rights Watch) ዘገባ በዚህ ፍጅት ላይ የእምነት ተቋማት እጃቸዉ እንደነበረበት አረጋግጧል። ለዚህም የኢንታሃማ ቤተክርስቲያን (Ntarama Church) ተጠቃሽ ነዉ። እ.ኤ.አ. ሚያዚያ 15 ቀን 1994 ዓ.ም. በዚህ ቤተክርስቲያን ተጠለለዉ የነበሩ 5,000 ቱትሲዎች በቆንጨራ፣ በእጅ ቦንብ፣ በመሣሪያና ከነሕይወታቸዉ በማቃጠል በጅምላ ተጨፍጭፈዋል። በወቅቱ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የነበረዉ ይህ ተቋም በአሁኑ ሰዓት ወደ መታሰቢያነት ተቀይሯል። እንደምንሰማዉ የእኛ አገር የእምነት ተቋማት ግን ከጥቃት ላመለጡ ሰዎች መጠጊያ በመሆን የእርዳታ እጃቸዉን ዘርግተዉላቸዋል። በዚህም ሊመሰገኑና በርቱ ሊባሉ ይገባል። በርግጥ አንዳንድ እምነታቸዉን በጎሰኝነት የለወጡና ህሊናቸዉን ለጥቅም ካስገዙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል “ … ሰዎቹ የተገደሉት ለእየሱስ ሲሉ ሳይሆን ምኒሊክን እያሉ ነዉ … ” እስከማለት የደርሱ አሳፋሪዎችም ይገኙበታል።  

ትናንትና የተፈጸመዉ ዓይነት ጭፍጨፋ እንዳይደገም በሩዋንዳ ጠንከር ያለ ሥራ ተሠርቷል። ከነዚህም መካከል መታወቂያ ላይ ብሔር እንዳይጻፍ ተደርጓል። ከዚያም በላይ ስለብሔር ማዉራት በራሱ ሕገወጥ ነዉ። በዚህ አቋም ላይ አንዳንዶች መንግሥት ደም መፋሰስ እንዳይኖር በማሰብ የተደረገ ነዉ በማለት ሲደግፉት ሌሎች ደግሞ ይህ ዓይነት አካሄድ እዉነተኛ ዕርቅን እንደሚገታና በራሱ ሌላ ዉጥረት (tension) በመፍጠር ወደፊት ሌላ ዕልቂት እንዳያቀጣጥል ሥጋታቸዉን ይገልጻሉ። 

የሆነዉ ሆኖ የሩዋንዳ ዕልቂት ከሩብ ዓመት በላይ ያስቆጠረ ቢሆንም ዛሬም ድረስ ስለተፈጸመዉ ሰቆቃ በተለያየ መልኩ መዘገቡ አልቀረም። አሁንም ፊልሞች፣ ዶክሜንተሪዎች፣ የምርምር ጽሑፎች … ወዘተ በመሠራት ላይ ናቸዉ። በዚህም የአጥፊዎች ስም ይጠቀሳል፣ የጭካኔዉና የግፉ መጠን ይወሳል፣ ልጆች በልጅነት አዕምሮዋቸዉን በቤተሰቦችቸዉ ላይ ሲፈጸም ያዩትን ይጽፋሉ፣ ይተርካሉ … ይህ ሁሉ ሲሆን ያንን ሰቆቃ የፈጸሙትና በሕይወት ያሉትም ጭምር ያ አጸያፊ ታሪካቸዉ ሲነገር፣ ሲተረክና ሲወገዝ ለማየትና ለመስማት በቅተዋል። ምን ስሜት ሊፈጥርባቸዉ እንደሚችል ማንም ሰዉ መገመት ይችላል። ለምሳሌ ያህል አንድ ሰዉ መጥቀስ እፈልጋለሁ።   

ሰላስቲን ሃብንሹቲ (Celestin Habinshuti) ይባላል። አንምሪ እማምና (Anne-Maria Umimana) የተባለች የጎረቤቱን ሁለት ልጆች በቆንጨራ (mechete) በጭካኔ ገድሎባታል። እሱም አምኗል። እናም በዚህና ሌሎች ሰዎች ላይ በፈጸመዉ ግድያ ምክንያት አሥር ዓመት ተፈርዶበት እስሩን ጨርሶ ወጥቷል። ይህ ግለሰብ በአንድ ወቅት ቢቢሲ (BBC) ባዘጋጀዉ ዶክመንተሪ ፊልም ላይ ቀርቦ “ … ልጆች ሃጢአት የሌለባቸዉ መላዕክት ናቸዉ። የነሱ መሞት ኢፍትሃዊ ሲሆን በወቅቱ የነበረዉ አይዶሎጂና መጥፎ አመራር ዉጤት ነዉ። እናም እነዚህ ልጆች ፍትሕ ተነፍጓቸዋል። እኔም ራሴን እንድጠላና (I’m filled with self-loathing) በሐፍረት ለመሸማቀቅ ተዳርጌአለሁ … ” በማለት ጸጸት በሚያሰቃየዉ የሰለለ ድምፅ ገልጿል። ምንም እንኳን ግለሰቡ ጥፋቱን አምኖ ከዕልቂቱ የተረፉትን ሰዎች እየዞረ ይቅርታ መጠየቁን ቢናገርም ተበዳዮችን ባየ ቁጥር እየተሳቀቀ ፊቱን ሸፍኖ እንደሚያልፍና ራሱን እንደጨካኝ ገዳይ (savage killer) እንደሚቆጥር አልደበቀም። በሌላም በኩል ዉድ ልጆቿን የገደለባት እማምና ይህንን አረመኔ ግለሰብ ሠፈር ዉስጥ ባየችዉ ቁጥር ልቧ እንደሚመታ፣ መላ ሰዉነቷን ቅዝቃዜ እንደሚሰማትና እንደሚያንዘፈዝፋት በማልቀስ ገልጻለች። በዚያ ብቻ አልተወሰነችም። እሷንም እንደልጆቿ አንድ ቀን  ይገድለኛል በሚል ፍራቻ ዉስጥ እንደምትገኝ ልብ በሚነካ መልኩ ተናግራለች። በነገራችን ላይ እማምና በዚህ አረመኔ የተገደሉባትን ጨምሮ አራት ልጆቿና ባለቤቷ በአይኗ እያየች የታረዱባት ምስኪን ሴት ነች።  

ወደ አገራችን ስንመጣ በፖለቲከኞችና “አክቲቪስት” ነን ባዮች በሚፈጸም ትርክትና እኩይ ቅስቀሳ ተገፋፍተዉ ንጹሃን ሰዎችን ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ የሚገድሉና ንብረት የሚያወድሙ ሰዎች ቆም ብለዉ ሊያስቡ ይገባል። ዛሬን ያመለጡ ቢኖሩም ወደፊት አንድ ቀን በሕግ መጠየቃቸዉ አይቀርም። ከዚያም በላይ የፈሰሰዉ የንጹሃን ደም እንደሰላስቲን እድሜያቸዉን በሙሉ እየተከተለ ሰላም እንደሚነሳቸዉ አያጠራጠርም። ያኔ ከጀርባ ሆነዉ የሚቀሰቅሱዋቸዉና በዉሸት ትርክት የሚሞሏቸዉ ሰዎች አንዳቸዉም ከጎናቸዉ ሆነዉ ለማጽናናት አይበቁም። እንደዉም ፊታቸዉን አዙረዉ በተቃራኒ ጎን እንደሚቆሙ ከመሰል የታሪክ ፍሰት መረዳት ይቻላል።

ጊዜ ዛሬ ብቻ አይደለም። ትናንትም ሆነ ነገ በጊዜ ባቡር ዉስጥ ነዉ ያሉት። ዛሬ ላይ ሆኖ ጊዜዉ የእኛ ነዉ በሚል ዕብሪት የሚፈጸም ወንጀል ነገ ሌላ ገጽታ እንደሚኖረዉ አያጠራጥርም። ዛሬ በቄሮ ስም የሚፈጸመዉ የጅምላ ግድያ፣ ሰዉን ከቀየዉ ማፈናቀል፣ የንጹሃን ንብረት ማዉደም፣ ዝርፊያ … ወዘተ ነገ ላይ ሲደረስ እንደዛሬዉ የሚያስፎክር፣ የሚያኩራራና ደረትን ገልብጦ የሚያስኬድ ተግባር ሆኖ አይዘልቅም። ዛሬ “ቄሮ” ነኝ እያለ የሚኩራራ ሰዉ ነገ በቄሮነቱ አፍሮ ራሱን ለመደበቅ ሲሯሯጥ ቢገኝ አይገርምም። ትናንት በጊዜአቸዉ አይነኬ የነበሩት ግዙፎቹ የደርግ አባላት ምን እንደደረሰባቸዉ አይተናል። በቅርቡም ወያኔ ላይ የደረሰዉን አይተናል። ብዙዎቻችን አንድ ጉዳይ ለመጨረስ በቢሮክራሲ ዉጣ ዉረድ ስንላጋ ባለጊዜዎቹ የ“ጊዜዉን ቋንቋ” በመናገራቸዉ ብቻ ያልጠየቁትንም ጭምር ሲፈጸምላቸዉ ስንታዘብ ኖረናል። ትናንትና ሲኩራሩበትና የተዘጋን ኬላ ያስከፍት የነበረ “ቋንቋ” ዛሬ ግን በአደባባይ ተናግረዉ ማንነታቸዉ እንዳይታወቅ ሲዉተረተሩ ቢታዩ አያስደንቅም። ምክንያቱም የጊዜ ጉዳይ ነዉ። ትናንት ሌላ ዛሬ ሌላ …

“አክቲቪስት” በሚል ሽፋን አንዱን ሕዝብ ከሌላዉ ለማጫረስ የሚደረጉ ንግግሮችና ጽሑፎች ነገ ተጠያቂነት ማስከተላቸዉ አይቀርም። በመሠረቱ አክቲቪስቶች የሕዝብን ጉዳይ ወደ አደባባይ ይዘዉ በመዉጣት ታግለዉ የሚያታግሉ፣ ራሳቸዉን ለመስዋዕትነት የሚያስቀድሙ፣ ቆራጥና ሚዛናዊነት የሚንጸባረቅባቸዉ ሐቀኛና የመርሕ ሰዎች ይመስሉኝ ነበር። የእኛ አገር አክቲቪስቶች ግን ከጥቂቶች በስተቀር መስፈርቱን የሚያሟሉ አይደሉም። የሚያነሱት ጉዳይ ከሕዝብ የመነጨ አይደለም። ግራ ቀኙን በማየት የሰዉን ቀልብ በመሳብ ተከታይ እናፈራበታለን የሚሉትን አጀንዳ ነዉ ሕዝቡ ላይ የሚጭኑት። አንዳንዶቹማ በግል ሕይወታቸዉ የተሸንፉበትንና በራሳቸዉ ድክመት አልሳካ ያላቸዉን ጉዳይ ወደ አደባባይ በማምጣት የሕዝብ አጀንዳ ለማስመሰል ሲዉተረተሩ ይታያል። ዉሸትማ ዋና መሣሪያቸዉ ነዉ። መተጣጠፍና ማስመሰል በእጅጉ ተክነዉበታል። በዚያ ላይ አላፊነት ስለማይሰማቸዉ የሚያደርጉት ንግግርም ሆነ ጽሑፍ ስለሚያስከትለዉ ጉዳት  መጨነቅ አይፈልጉም። ከሁሉም የሚያሳዝነኝ እነሱን ተከትሎ ለጥፋት የሚሰማሩት ናቸዉ። እርስ በርሱ የሚጋጭና ወጥነት የጎደለዉ አካሔድ ሲከተሉ እንኳን ትናንትና እንደዚህ ስትሉ ወይንም ስታደርጉ አልነበረም ወይ በሚል አለመጠየቃቸዉ ይገርመኛል። ለማንኛዉም ሁሉንም ልቦና ይስጣቸዉ ከማለት በስተቀር ምን ማለት ይቻላል?!

 እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይጠብቃት!

የዚህን ጽሑፍ አቅራቢ ለማግኘት “mekonnen_ashagre@yahoo.comበሚል የኢሜል አድራሻ ሊጽፉልኝ ይችላሉ።

Filed in: Amharic