የጋራ ጠላት እንጅ ሀገራዊ የጋራ ራዕይ የላቸውም
ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ ታዬ
ትህነግ/ኢህአዲግ፣ ብአዴን/ብልፅግና እና ኦህዴድ/ብልፅግና የጋራ ጠላት(አማራ እና አማርኛ ቋንቋ) አላቸው እንጅ የጋራ ራዕይ ወይም አጀንዳ የላቸውም፡፡ ይህን እንድል ያስገደደኝ ምክንያት ለአለፉት ሰላሳ ዓመታት የአማራው ህዝብ በሚደርስበት በደል፣ሞት እና ሰቆቃ የአማራውን ህዝብ እንወክለዋለን የሚሉት መሪዎች ከአክራሪ ብሄርተኞች ጋር ሲተባበሩ እንጅ ድርጊቱን ሲያስቆሙት አይታዩም፡፡ ለአስረጅነት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት በቅርቡ የተናገሩትን እንመልከት፡
‘’የአማርኛ ቋንቋ እንዲዳከም በማድረግ አሟሟቱን ማፍጠን… ከምርጫ በፊት የአማርኛን ቋንቋ በሚገድል አቅጣጫ የኦሮሞኛ ቋንቋን የፌደራል የስራ ቋንቋ ማድረግ… በ1987 ዓ.ም. ኦሮምኛ በ13% ከአማርኛ በታች የነበረውን በመቀየር አሁን አፋን ኦሮሞ ኢትዪጲያ ውስጥ አማርኛን ከ10% በላይ እንዲበልጥ ተደርጓል፡፡ ከደቡብ ተገንጥሎ የወጣው ሲዳማ (ሀዋሳን ጨምሮ) የስራ ቋንቋ ከአማርኛ ወደ ሲዳማኛ ተቀይሯል፡፡ በቀጣይም እየፈራረሱ ያሉት የደቡብ ክልሎች ሲጠናቀቁ በደቡብ አማርኛ የቁልቁለት ጉዞውን ይቀጥላል፡፡ ቤንሻንጉል 37% አፋን ኦሮሞ የሚናገሩባት ሁኔራ ተፈጥሯል፡፡ በጋምቤላ፣ ሀረሪ፣ሶማሌ ውስጥ አማርኛ እየሞተ በመምጣት ወደታች እየሄደ ነው‘’ (ሽመልስ አብዲሳ፣ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ከተናገሩት የተወሰደ)
እንደዚህ አይነት ንግግሮች እና ቅስቀሳዎች የአማራው ህዝብ የጥቃት ሰለባ እንዲሆን ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ ከክልሉ ውጭ ያለው የአማራው ህዝብ ለሰላሳ ዓመታት ያህል የጥቃት ኢላማ ሁኖ ንሯል፡፡ ዛሮም በእንዲህ አይነት ንግግሮች ምክንያት ሲገለል፣ ሲገደል፣ሲጠቃ፤ ሲሸማቀቅ እና አንገቱን እንዲደፋ ሲደረግ ቆይቷል፣ እየተደረገም ነው፡፡ ለዚህ ሁሉ ጥቃት ዋና ተዋናኝ የክልሉን ህዝብ እንወክለዋለን የሚሉት የብአዴን/የአዴፓ/እና የአማራው ብልፅግና መሪዎች ናቸው፡፡
የአማራን ህዝብ እና ቋንቋውን በእንዲህ አይነት መንገድ የሚያዋርደውን እና የሚገድለውን ግለሰብ የአማራን ህዝብ እንወክለዋለን የሚሉት መሪዎች ይህን ግለሰብ ይቅርታ እንዲጠይቅ ሊያደርጉት ሲገባ ካባ አልብሰው የጀግና አቀባበል ሲያደርጉለት ሲታይ ሸላሚዎች የድርጊቱ ተሳታፊ እንደሆኑ በቂ ማስረጃ ብቻ ሳይሆን ተሸላሚው በጉዳዩ እንዲቀጥልበት ጥሩ መበረታች ለመስጠት ታስቦ ነው፡፡ ይህ ክስተት እንዴት ያማል፤ ምንስ አይነት ውርደት ነው? ምን አይነት የሞራል ውድቀት ነው ይህን ሊያስደርግ የሚችል? ምንስ አይነት ወኔ ነው የተነገበው? ሸላሚዎችና ተሸላሚዎች በተጎጅ ቤተሰቦች እግር ላይ ሁነው ጉዳዩን እንዴት ማየት እንደተሳናቸው አላውቅም፡፡ ይህ ክስተት በህዝቡ ላይ ሊፈጥረው የሚችለውን ቁጭት አመራሮች የተረዱት አይመስልም፡፡ ለነገሩ ይህን መረዳት ቢችሉ በቦታው ላይ መቀመጥም ባልቻሉ ነበር፡፡ ይህንን ሊረዱበት የሚችል የግንዛቤ ጥግ ቢኖራቸው የሚመሩትን ህዝብ የልብ ትርታ አዳምጠው፣ በውሸት ሳይሆን በአመራር ጥበብ እያማለሉ ህዝባቸውን ይታደጉት ነበር፡፡
’’አያያዙን አይተው፣ ጭብጦውን ቀሙት’’ ነውና ብሂሉ የአመራሮችን ቁመና እና ትክሻ መለካካት አይተው እንጅ ቆፍጣና ተወካይ የአማራ ህዝብ ቢኖረው ንሮ እነዚህ ፅንፈኞች የሚያወሩትን እንቶ-ፈንቶ እንኳንስ መፈፀም ማሰብም አይችሉም ነበር፡፡
ታዲያ ምን ይሆናል? ለራሳችሁ እና ለምትወክሉት ህዝብ እንጥፍጣፊ ክብር ጠፍቶባችሁ፣ ለሰላሳ ዓመታት የአድርባይነት ማንነትን አንግባችሁ፣ የታሪክ ተወቃሽ ከምትሆኑ በድርጊታችሁ አፍራችሁ እርምጃ ብትወስዱ በተሻላችሁ ነበር፡፡ ሞትን ተሸክመን እየኖርነ፣ ለአጭርና ቅፅበታዊ ለሆነ ምድራዊ ህይወት እንዴት ዘላለማዊነትን በልባችሁ ቋጠራችሁ እንመራዋለን የምትሉትን ህዝብ አንገት ታስደፋላችሁ? እንዴት ለእውነት መቆም ተሳናችሁ? ከ1983 ዓ.ም. ከበደኖ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ዘር ተኮር በሆነ ጥቃት በአማራው ህዝብ ላይ እንዲህ አይነት ሰቆቃ እየተፈፀመ፣ ደም በከንቱ እየፈሰሰ እንዴት ዝም ይባላል?
በተለያዩ በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በሱማሊያ እና በቤንሻንጉል- ጉምዝ ክልሎች፣ በተለያየ ጊዜ ለበርካታ ዓመታት ዘር ተኮር ጥቃት እየተፈፀመ ነበር፤ አሁንም እየተፈፀመ ነው፡፡ ስልታዊ በሆነ መንገድ አማርኛ ተናጋሪን እና አማራን ከምድረ-ገፅ ለማጥፋት ታልሞ እየተሰራ እንደሆነ ፀሀይ የሞቀው ጉዳይ ነው፡፡ በኦሮያ ክልል የሚገኙ ወጣቶች በሀሰት ትርክት ተሞልተው በአማርኛ ቋንቋ እና በአማራ ላይ ስር-የሰደደ ጥላቻን አዳብረዋል፡፡ ዜጎች አማራ በመሆናቸው ብቻ ጉድጓድ ላይ ተጥለዋል፣ ታርደዋል፣ ተፈናቅለዋል፣ መዘባበቻ ሁነዋል፣ ከስራ ተባረዋል፣ በቤታቻው ውስጥ ተቃጥለዋል፣ታስረዋል፣ ንብረታቸው ወድሟል፣ በአጠቃላይ የሲቪል፣ የሰብዓዊ እና የፖለቲካ መብታቸው ተጥሶ ከሰው በታች ሁነው ኑረዋል፣ እየኖሩም ነው፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ብአዴን የአማራ ተወካይ ሁኖ ለይስሙላ በተሰጠው የስልጣን ማማው ላይ ነበር፡፡
ከሁለት ዓመት ተኩል (ከለውጡ በኃላ) ወይም ባለ ስልጣኖች የስልጣን ሽግሽግ ካደረጉ በኃላ ቢባል ይሻላል እነዚህ ህገ – ወጥ ድርጊቶች ከመቆም ይልቅ እየቀጠሉ ከመሄዳቸው በላይ በተለያዩ ቦታዎች የጥቃቱ ይዘትና ስፋት ዕለት ዕለት እየጨመረ መጥቷል፡፡ ዛሬም እንደ ትናንቱ ይህ ህዝብ የጥቃት ዒላማ ካለመሆን የታደገው ምድራዊ ኃይል የለም፡፡ ዛሬም የአማራ ሴት ወጣቶች ታግተው እስካሁን የደረሱበት አልታወቀም፡፡ ህዝብን አስተዳድራለሁ የሚል መንግስት በተሰየመበት ሀገር ሴት እህቶች ታግተው ይጠፋሉ፡፡ ይህ ሲሆን ብአዴን/ብልፅጋና የአማራ ተወካይ ሁኖ ለይስሙላ በተሰጠው የስልጣን ማማው ላይ ነው፡፡
በኢትዪጲያ ባህል ነፍሰ-ጡር ሴት ትከበራለች፤ በማናቸውም ጉዳይ ላይ ቅድሚያ ይሰጣታል፡፡ የአማራ ነፍሰ-ጡር ሴት ግን የአማራ ልጅ እንዳይወለድ ሲባል በግፍ አድራጊዎች ከልጆችዋ ፊት በሳንጃ ትታረዳለች፡፡ በሻሸመኔ፣ በዝዋይ፣ በዶዶላ፣ በዴራ እና በተለያዩ የኦሮሚያ ክልሎች አዛውንቶች በኖሩበት፣ ልጅ ባሳደጉበት አገር ታርደዋል፣ ሙሉ የቤተሰብ አባላት ተገድለዋል፣ ሴቶች ተደፍረዋል፡፡ ዜጎች አማራ እና ክርስቲያን በመሆናቸው ብቻ ተሰደዋል፣ ንብረታቸው ወድሟል፣ አሰቃቂ የሰብዓዊ ጥሰት ደርሶባቸዋል፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ብአዴን/ብልፅጋና የአማራ ተወካይ ሁኖ ለይስሙላ በተሰጠው የስልጣን ማማው ላይ ነው፡፡
የገፅታ ግንባታውን ሂደት እንዳያበላሹ ተብለው ትኩረት የተነፈጋቸው፣ ለበቂ የሚዲያ ሽፋን ያልበቁ እጅጉን የጥቃት ሰለባ የሆኑም ወገኖችም አሉን፡፡ በድሮው በጎጃም ግዛት አስተዳደር አንዱ አውራጃ በነበረው መተከል ውስጥ በርካታ የአማርኛ ተናጋሪ ዜጎች ይኖሩበት ነበር፡፡ በዚህው ረጅም ዘመን በኖሩበት ቀየ የጥቃት ሰለባ ሁነዋል፡፡ ህፃን ያዘለች ሴት ልጅ በቀስት ተመታ አስከ ልጇ ለህልፈት ተዳርጋለች.፣ ህፃናት እንደ ፍየል ጠቦት እየጮሁ በስለት ታርደዋል፣የቤተሰብ አባላት እንዳሉ ለሞት ተዳርገዋል፡፡ ዜጎች በሚናገሩት ቋንቋ ተለይተው የጥቃት ሰለባ ሁነዋል፣ ንብረታቸው ወድሟል፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ብአዴን/ብልፅጋና የአማራ ተወካይ ሁኖ ለይስሙላ በተሰጠው የስልጣን ማማው ላይ ነው፡፡
የአማራ ህዝብ መሪ በሌለው መርከብ ላይ በውቅያኖስ ላይ የሚንሳፈፍ ጀልባን ይመስላል፡፡ ከየትኛውም አቅጣጫ የሚነሳው አውሎ-ንፋስ ወደ ፈለገው አቅጣጫ የሚገፋው መርከብን ይመስላል፡፡ ለዚህ ሁሉ ጥቃት እና ሰለባ ምክንያት የሆኑት ግን እምነትና በጎ ህሌና የሌላቸው፣ አዕምሮዓቸው ሆዳቸው በሆነባቸው የአማራ ተወካይ ነን በሚሉ ጀሌዎች ነው፡፡
የፍጡር አስተሳሰብ በቦታ፣ በጊዜ፣ በአቅም የተወሰነ ነው፡፡ በስጋዊ አስተሳሰብ የተያዘ ፍጡር ከሚታየው ነገር በላይ ማሰብ እንደማይችለው ሁሉ በተመሳሳይ ሁኔታ የዘመኑ ባለስልጣናት ከወንበራቸው እና ከስልጣናቸው በላይ ማሰብ አይችሉም፡፡ ሰው የንሮ እርካታውን ከቁሳዊ ነገር ጋር ብቻ ካዛመደው ከእንሰሳት የሚለይበት ምንም ነገር አይኖርም፡፡ ሰው የመንፈስ እና የግብረ-ገብ ልዕልናው ልቆ ካልወጣ የስጋ ባህሪው በማንነቱ ላይ ገዝፎ ይታያል፡፡ የመንፈሳዊ ህይወት መላላት እና የሞራል መላሸቅ ለእንዲህ አይነት የሰብዕና ውርደት ይዳርጋል፤ ይህም ለማህበራዊ ቀውስ ዳርጎናል፡፡
በመንፈስ ደክማችሁ፣ በነፍሳችሁ አንሳችሁ፣ በእዕምሮ ዝጋችሁ ለህዝባችሁ የወዳጅ ጠላት ሁናችሁ ከምትኖሩ፣ የስጋችሁን ድሎት ትታችሁ፣ በ‘’V-8’’ መኪና መፈላሰሱ ቀርቶባችሁ፣ በተንጣለለ የመንግስት ቤት መኖር ንቃችሁ፣ ለእውነት ኑራችሁ፣ ለእውነት ቁማችሁ፣ ለእውነትን ታግላችሁ ከህዝባችሁ ጎን ብትቆሙ እና የህዝባችሁን ድምፅ ብትሰሙ መልካም ነበረ፡፡ ታላቁ መሪ ሙሴ ከፈርኦን ቤት የድሎት ህይወት ይልቅ ከእግዚአብሄር ህዝብ ጋር መከራን መቀበል መረጠ ይላል መፅሀፉ(ዕብ.11፣24)፡፡ በህዝብ ላይ ለዓመታት ስደት፣መፈናቀል፣ሞት፣ሰቆቃ፣ ውርደት እየተካሄደበት ዝም ከማለት እና የግላዊ ምቾትን ጠብቆ ከመኖር ይልቅ ከሚሞተው እና ከሚፈናቀለው ህዝብ ጎን ቁሞ መከራ መቀበልን መምረጥ የታሪክ ተወቃሽ አያደርግም፤ አዕምሮም ላለውም ሰው የአዕምሮን ሰላም ይሰጣል፡፡ የአዕምሮ ሰላም ደግሞ ከስጋ ምቾት ይበልጣል፡፡