>
5:28 pm - Thursday October 9, 6673

ፍ/ቤት የለቀቀውን ሰው ፖሊስ ማገት አይችልም...!!! (ጠበቃና የህግ አማካሪ ወንድሙ ኢብሳ)

ፍ/ቤት የለቀቀውን ሰው ፖሊስ ማገት አይችልም…!!!

ጠበቃና የህግ አማካሪ ወንድሙ ኢብሳ

* ሰዎችን ካለፍ/ቤት ትእዛዝ በእስር የማቆየቱ ህገወጥ አሰራሮች ብቅ ብቅ ማለታቸው ለለውጡ ኪሣራ ነው፡፡ በአፋጣኝ ማስተካከያ ማድረግ ይገባል፡፡ በተለይ ዋስትና የተሰጠው ሰው የሚጠበቅበትን ካሟላ፣ ለ1 ሰዓት እንኳ ታግቶ መቆየት የለበትም፡፡ ፍ/ቤት ያረጋገጠለት መብቱ ወዲያው ነው መጠበቅ ያለበት፡፡

በፍ/ቤት የተሰጠ ዋስትና በፖሊስ የሚከለከልበት የህግ አግባብ ይኖር ይሆን? በሠኔ 22 እና 23 ግርግር ተጠርጣሪዎች ላይ የሚቀርቡ ክሶችስ ምን መልክ አላቸው? በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከ600 በላይ ለሚሆኑ የፀረ ሽብር ተከሳሾች ጥብቅና በመቆም በሸብር ክስ ጉዳዮች የዳበረ ልምድ ያላቸውን ጠበቃና የህግ አማካሪ ወንድሙ ኢብሳን የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ እንደሚከተለው አነጋግሯቸዋል፡፡

ፍ/ቤት ዋስትና የሠጣቸው ተጠርጣሪዎችን በፖሊስ በእስር ማቆየት ከህግ አንፃር እንዴት ይታያል?

የኢትዮጵያ የወንጀል ስነስርአት ህግ የወጣው በ1954 ነው፡፡ ይህ የወንጀል ህግ እስከ ዛሬም ስራ ላይ ነው፤ እንጠቀምበታለን። በደርግም በህወኃት/ኢህአዴግም፤ በዚህ መንግስትም በስራ ላይ ያለው ይሄ ህግ ነው። በዚህ ህግ መሠረት፤ ማንም ሰው በወንጀል ሊጠረጠር፣  ጥርጣሬው በተጨባጭ ማስረጃ የሚደገፍ ከሆነ ይታሠራል፡፡ በ48 ሰአት ውስጥ ወደ ፍ/ቤት መቅረብ አለበት። ከ28 ቀን ያልበለጠ ቀጠሮም በየ7 ቀናት ተከፋፍሎ ይሰጣል። በዚህ ጊዜ ውስጥ ፖሊስ በቂ ማስረጃ ካላቀረበና ክስ መመስረት ካልተቻለ፣ ፍ/ቤቱ ተጠርጣሪውን በዋስ ይለቀዋል፡፡ ይሄ ላለፉት 50 አመታት በስራ ላይ ያለ አሠራር ነው፡፡ ፍ/ቤት የለቀቀውን ፖሊስ አለቅም ማለት ህጋዊ አይሆንም፤ ነውር ነው፡፡ ህዝብ ምን ይለኛል ማለት አለበት፡፡ የፍ/ቤት ውሳኔ በማንኛውም ደረጃ ካልተከበረ፣ ለፍትህ የሚሰጠውን ክብር ይቀንሳል፡፡ ይሄ አሁን እየተካሄደ ያለው ከኢህአዴግም የባሰና ያንኑ ስርአት ያስቀጠለ ነው፡፡ ለምሣሌ አቶ ልደቱ የ100ሺህ ብር ዋስ ተፈቅዶላቸው ከፍለዋል፡፡ እኚህን ሰው በምንም መመዘኛ ለ1 ሰዓት ያህል እንኳ ማቆየት ህገወጥነት ነው፤ በፍፁም የሚደገፍ አይሆንም፡፡ ይሄን በትክክለኛ ስሙ ስንጠራው “እገታ” ነው። ፖሊስ በዜጐች ላይ እገታ ፈፀመ ማለት እንችላለን። ፍ/ቤት የለቀቀውን ማቆየት እገታ ነው፡፡ ፖሊስ የህግ አካል ነው፤ እገታን ይከላከላል እንጂ ማገት አይችልም፡፡ ድሮ መንግስት የሚያስቸግሩትን ግዞት እያለ ወዳልታወቀ ቦታ እየወሰደ ያቆይ ነበር። አሁንም የሱ አይነት መልክ ነው ያለው፡፡ በነገራችን ላይ አቶ ልደቱ ታዋቂ ሰው ስለሆነ ነው እንጂ ከአርቲስት ሃጫሉ ሞት በኋላ በርካቶች ታስረው፣ ያለ ዋስትና እና ፍ/ቤት ሳይቀር ዝም ብለው ታግተው የተቀመጡ በርካታ ናቸው፡፡  ይሄ በእውነት ለመንግስት በጣም አሳፋሪ ነው፡፡ በዚሁ ከቀጠለ የፍትህ ስርአቱ ላይ ሊመጣ የታሰበው ለውጥ ላይ ኪሣራን የሚያስከትል በመሆኑ ፈጥኖ መታረም አለበት፡፡
እኔ በደርግ ጊዜ 150 ቀን ፍ/ቤት ሳልቀርብ ታስሬ ወጥቻለሁ፡፡ አሁንም የዚህ አይነት እስር ብቅ ብቅ ማለታቸው ለለውጡ ኪሣራ ነው፡፡ በአፋጣኝ ማስተካከያ ማድረግ ይገባል፡፡ በተለይ ዋስትና የተሰጠው ሰው የሚጠበቅበትን ካሟላ፣ ለ1 ሰዓት እንኳ ታግቶ መቆየት የለበትም፡፡ ፍ/ቤት ያረጋገጠለት መብቱ ወዲያው ነው መጠበቅ ያለበት፡፡
አቃቤ ህግ ለአንድ ተጠርጣሪ በተሰጠ ዋስትና ላይ ይግባኝ መጠየቅ የሚችለው በምን አኳኋን ነው? ግለሰቡን አስሮ አቆይቶ መጠየቅ ይችላል? በዚህ ላይ ህጉ ምን ይላል?
አንድ ተጠርጣሪ በፍ/ቤት ዋስትና ከተሰጠው በኋላ የሚጠበቅበትን ካሟላበት ሰአት ጀምሮ ከፖሊስ ቁጥጥር ነፃ መሆን አለበት፡፡ ይግባኝ የሚጠየቀው በቀጠሮ መሠረት ነው፡፡ ሰውየውን ፖሊስ እንዲያግተው አድርጐ መጠየቅ ራሱ ወንጀል ነው፡፡

ይሄን ወንጀል የሚያደርግ የህግ አንቀጽ መጥቀስ ይቻላል?

ህጉ፤ የዋስትና መብቱ የተጠበቀለት ሰው፤ የሚፈለግበትን አሟልቶ ይፈታል ነው የሚለው እንጂ ፖሊስ ከፈለገ ማገት ይችላል የሚል አንቀጽ በየትኛውም የህግ ድንጋጌ የለም፡፡ ከፍ/ቤት ትዕዛዝ ውጪ ለ1 ሰዓት እንኳ አቆይ የሚል የህግ አንቀጽ የለም፡፡ ይግባኝ የሚጠየቀው በቀጠሮ ነው። በይግባኝ ወቅት ሰውየው የዋስ መብቱ መጠበቅ አልነበረበትም ከተባለ ተመልሶ ይታሠራል እንጂ ፖሊስ አግቶ አቆይቶ ይግባኝ መጠየቅ በራሱ ወንጀል ነው፡፡ ገና ለገና ይግባኝ እጠይቅበታለሁ ብሎ ሰዎችን አስሮ ማቆየት፣ ከህወኃት/ኢህአዴግ የዘፈቀደ አሠራር የተወሰደ መጥፎ ውርስ ነው፡፡ ይሄ በደል ፈጥኖ መቆም አለበት፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ሲመጡ ባደረጓቸው ንግግሮች፣ “ከእንግዲህማስረጃ ሳንይዝ የምናስረው ሰው አይኖርም” ብለው ነበር፡፡ አሁን የሚታየው ሰዎችን አስሮ ማስረጃ የማፈላለግ ነገር እንዴት ይታያል?
ጠ/ሚኒስትሩ ሳናጣራ አናስርም ብለዋል፡፡ የጠ/ሚኒስትሩ ንግግር ግን ፖለቲካዊ ንግግር ነው፤ እንደ ህግ ሊጠቀስ አይችልም፡፡ እኔ አሁንም በሽብር ለሚከሰሱት ጠበቃ ሆኜ በተደጋጋሚ ጠ/ሚኒስትሩ ያሉትን አንስቼ ለመከራከር ሞክሬያለሁ፡፡ ዳኞቹ ያሉኝ “ይሄ በህግ ሊጠቀስ የሚችል አይደለም፤ ጠ/ሚኒስትሩ መልካም ምኞታቸውን ነው ለህዝብ የገለፁት እንጂ ንግግር ተጠቅሶ የሚቀርብ ክርክር መኖር የለበትም”  በእርግጥም እውነት ነው፡፡ የጠ/ሚኒስትሩ ንግግር የፖለቲካ ንግግር እንጂ የህግ አይደለም፡፡ አጣርቶ የማሠር ሀሳባቸው በሀሳብ ደረጃ ትክክል ነው፡፡ ነገር ግን ይሄ እንደ ኢትዮጵያ ባለ ሀገር ውስጥ ቶሉ የሚሳካ አይደለም፡፡ ለኔ አሁን ትልቁ ችግር ሰው ከታሰረ በኋላ ፍ/ቤት የሠጠውን መብት በፖሊስ ወይም በሌላ አካል መጣሱ ነው፤ ማስረጃ ይዞ ማሠር የረቀቀ የህግ ስልጣኔን ይፈልጋል፡፡ የሰዎችን ዋስትና መብት በሃይል ደፍጥጦ አግቶ ማቆየት፣ ለመንግስት እጅግ አሳፋሪ ነው፡፡ ይሄን በእጅጉ ማሰብና ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡ ይህ አይነቱ እገታ የተፈፀመባቸው አቶ ልደቱ ብቻ አይደሉም፤ በርካቶች አሉ፡፡ ኢ/ር ይልቃል ጌትነትም ለበርካታ ቀናት ያለ ምንም ማስረጃ ታስረው ነው የተለቀቁት፡፡ እኚህ ሰውዬ ካሣ እንኳ ማግኘት አይችሉም፡፡ ለደረሰባቸው የህሊና የኢኮኖሚና ሌሎችም ጉዳት እንኳ ካሳ የላቸውም፡፡ በህግ ካሣ የለም፤ በሌሎች ነገሮች እንዲህ ያለው ካሣ አለ፡፡
በተለይ ፍ/ቤት ዋስትና የሰጣቸው ሰዎችን ካሣ በሌለበት የህግ ስርአት አግቶ ማቆየት፣ ከህግ ጥሰት ባለፈም ግፍ ነው፡፡ የፍትህ ስርአቱን ተዓማኒነት የሚቀንስና ሰዎች የፍትህ ስርአቱን በጥርጣሬ እንዲመለከቱ የሚያደርግ ነው፡፡ መንግስት ያወጣውን የራሱን ህግ ሳያከብር፣ ዜጐቹ እንዲያከብሩ መጠበቅ የሚያስኬድ አይደለም፡፡ በተለይ ፖለቲከኞች በፍ/ቤት የተሰጣቸው መብት ተጥሶ ሲታገቱ፣ የበለጠ የሚጐዳው መንግስት ነው፡፡ ተአማኒነቱ ይወርዳል። የኢትዮጵያ ዳኞች በህግ የተሰጣቸውን መብትና የህሊና ነፃነት እስከ መጨረሻው መጠቀም መቻል አለባቸው፡፡
አሁን በተለይ በሰኔ 22 ግርግርና ሁከት ጉዳይ ተጠርጥረው በታሠሩ ሰዎች ላይ እየቀረቡ ያሉ ክሶችን እንዴት ይመለከቷቸዋል?
በኢህአዴግ ጊዜ የነበረው የፀረ ሽብር አዋጅ በቀጥታ ተቃዋሚዎችን ለመጉዳት ያለመና የፖለቲከኞችን አፍ ለማስያዝ የተዘጋጀ ነበር፡፡ አሁን የወጣው አዋጅ ግን ዲሞክራሲን የሚያበረታታና ተቃዋሚዎች ላይ ትኩረት ያላደረገ ነው፤ የአዋጁ መንፈስ። ነገር ግን ከሰሞኑ በዋና ዋና ፖለቲከኞች ላይ የቀረቡ ክሶችን ስመለከት፤ ከዚህ የአዲሱ አዋጅ መንፈስ የወጣና ለቀድሞ አዋጅ የቀረበ ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡
በምሳሌ ሊያስረዱኝ ይችላሉ?
ለምሣሌ ከእስረኛው አያያዝ ብንጀምር፣ ቀደም ሲል ይደረግ እንደነበረው፣ ስም አለው ታዋቂ ነው የሚባል ሰው፤ ሰብአዊ መብቱ ይከበራል፤ መብቱም ይጠበቃል፤ በአንፃሩ ብዙም የማይታወቁት መብታቸው ይጣሳል፡፡ ከብዙ እስረኞች ጋር ታጭቀው እንዲታሠሩ ይደረጋል፤ መጠነኛ እንክብካቤ ነው የሚደረግላቸው፡፡ ስም ላላቸው ደግሞ ከፍ ያለ እንክብካቤና የመብት ጥበቃ ይደረጋል፡፡ አሁንም ይህ የቀድሞ አካሄድ ነው የቀጠለው፡፡ ትልልቅ ስም ያላቸው እስረኞች አያያዝ በአንፃራዊነት በእንክብካቤ የታጀበ ነው፡፡ ይሄ እጅግ መጥፎ ነው፡፡ በህግ ፊት ንጉሡም ሃብታሙም ድሃውም እኩል ነው፤ አያያዙም እኩል ነው መሆን ያለበት። ሁሉም በአንድ አይን ነው መታየት ያለበት። ሌላው ክሱ ሲቀርብ ቀድሞ ይቀርብ በነበረበት አውድና ተመሳስሎሽ ባለው ሃተታ ነው፡፡ ዳኞች አካባቢ አሁንም ሙሉ መብታቸውን እየተጠቀሙ አይመስልም፡፡
እስረኞች አያያዝ መሻሻል የለም ማለት ይቻላል?
መሻሻል በሚገባ አለ፡፡ ከቀድሞ አንፃር መልካም አያያዝ ነው ያለው፡፡ እኔም በማደርገው ክትትል፤ የሚደበደብ፣ ጥፍሩ የሚነቀል የለም፡፡ መሻሻል አለ፡፡ ነገር ግን በሽብር ዜጐችን መክሰስ ጥሩ ትርጉም አይሰጥም፡፡ ዜጐችን በሽብር መክሰስ ለውጥ አያመጣም፡፡ አብዛኞቹ ተዘርዝረው ያየናቸው ክሶች፤ በቀላሉ በወንጀል ህጉ ሊቀርቡ የሚችሉ ነበሩ፡፡ ዝም ብሎ ሁሉንም ነገር ወደ ሽብር ክስ መተርጐም፣ የሽብርን ትርጉምና ክብደት ማቃለል ነው፤ የበፊቱ አይነት ቀልዶች ተመልሰው እንዲመጡ ያደርጋል፡፡ ዛቻ፣ ሙከራ፣ ማነሳሳት የሚሉ ናቸው የክሶቹ ዝርዝሮቹ፡፡ ይሄን በወንጀል ህጉም መክሰስ የሚቻልበት ጉዳይ ነው፡፡ ለምሣሌ የእስክንድር ነጋ ክስ ላይ አንድን ማህበረሰብ በማይገባ ቃል በመጥራት ማንቋሸሽ ይላል፡፡ ይሄን በሽብር ከመክሰስ ይልቅ ስም በማጥፋት ተራ ወንጀል መክሰስ ይቻላል፡፡
መንግስት ለውጡን በተግባር ማሳየት ያለበት፣ እንዲህ ያሉ የህግ ሸፍጦችን በማስቆም ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በኦሮሚያና ጋምቤላ  ደንበኞች አሉኝ። ብዙ የህግ ጥሰቶቹ እየተፈፀሙባቸው ያሉ ሂደቶች አሉ። እነዚህ ሁሉ እየተጠኑ መታረም አለባቸው፡፡ በየቦታው ዋስ በፍ/ቤት ተጠብቆላቸው ግን በጉልበት ታግተው የሚገኙ በርካታ ሰዎች አሉ፡፡ የእነዚህ ሰዎች ጉዳይ በአፋጣኝ መፍትሔ ማግኘት አለበት። የታሰሩ ፍትህ ማግኘት አለባቸው። የተሳደበና፣ የዛተን ሁሉ በሽብር ክስ መከሰሱም ወደቀድሞ አካሄድ የሚወስደን ይሆናልና ከወዲሁ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ለኔ የሽብር ክስ የሚባለው በሆቴል ወይም ሰው በሚሰበሰብበት ቦታ ቦንብ ወይም ፈንጂ አፈንድቶ፣ የሠላማዊ ሰው ህይወት ለማጥፋት ሲታሰብ ወይም ሲፈፀም ነው። ከዚህ ባለፈ ግን በንግግሮች የሢፈፀሙ የስም ማጥፋት ድርጊቶችን በሙሉ የሽብር ጉዳይ አድርጐ መተርጐም ትልቅ ኪሣራ ነው የሚያስከትለው፡፡ ለፍትህ ስርአቱም አደጋ ነው፡፡

Filed in: Amharic