የብሄር አቃፊ የለውም አትቀፈኝ…!!!
(ሙክታሮቪች)
* እፈራለሁ! እሰጋለሁ! አንድ ቀን ና ልቀፍህ ብለህ ጨምቀህ አፍነህ እንደማትገለኝ ምን ማረጋገጫ አለኝ? አትቀፈኝ! የመኖር፣ ተንቀሳቅሶ የመስራት፣ ንብረት የማፍራት እና ህጋዊ የጥበቃ መብቴን ባንተ አቃፊ ነን ችሮታ ሳይሆን ማግኘት የምሻው የዚህች ሀገር ዜጋ ስለሆን ማግኘት ያለብኝ መብት ነው….!
እየተንጣጣ ነው።
ሰውዬው ትክት ያለው ነገር ያለ ይመስላል…..
በአዳራሽ ውስጥ ካሉት አንዱ የሚከተለውን አስተያየት እየሰጠ እያለ ብድግ ብሎ አጠገቡ ያለውን ማይክ አንስቶ ነው ….. የተንጣጣው
አስተያየት ሰጪው ምን እያሉ ነበር:—
“የኛ ብሄር አቃፊ ነው፣ ከጥንት አባቶቻችን የተረከብነው የአባቶቻችን እሴት ነው አቃፊነት”
እያሉ በነበረበት ነው ሰውዬው የሚከተለውን አስተያየት በከረረ ድምፀት እየተንጣጣ የተናገረው:—
“ማንም ማንንም አያቅፍም፤ ሁሉም በኢትዮጵያ ምድር እኩል የመኖር መብት አለው፡፡ ከመኖሪያ ቤትህና ከአጥር ግቢህ ውጭ የአንተ አይደለም፡፡ የምን አቃፊ ነን ፉከራ ነው!?”
“እና ምን እንበል፣ ማቀፍ ነውር አይደልም መቼም” አሉ ሰውዬው፣
መለሰ፣
“የፈለገ በማህበር ይታቀፍ፣ የፈለገ በሚስቱ ይታቀፍ። በፖለቲካ ግን ተቃቃፊ ነን እንጂ ማንም አቃፊ ማንም ታቃፊ አይደለም ፣ እኔም እቅፈሃለው ፣ አንተም ታቅፈኛለህ። እርስበርስ ተቃቃፊ ነን። ብቻህን እንደበረደው ሰው ና ልቀፍ አትበለኝ። ዜጋ ነኝ። በሀገሬ ሰርቶ የመኖር መብት አለኝ። ይህ መብቴ በሁሉ የኢትዮጵያ ምድር ላይ ፅኑ ነው። ይህ መብቴን አክብርልኝ። ያንተንም መብትህ አከብርልሃለው። የኔ መብት ላንተ ግዴታ ነው፣ ያንተ መብት እኔ ላይ ግዴታ ነው፣ በሚል መርህ እንተቃቀፍ። ብሄሬ አቃፊ ነው ስትለኝ ይጨንቀኛል። እፈራለሁ። እሰጋለሁ። አንድ ቀን ና ልቀፍህ ብለህ ጨምቀህ አፍነህ እንደማትገለኝ ምን ማረጋገጫ አለኝ? አትቀፈኝ! የመኖር፣ ተንቀሳቅሶ የመስራት፣ ንብረት የማፍራት እና ህጋዊ የጥበቃ መብቴን ባንተ አቃፊ ነን ችሮታ ሳይሆን ማግኘት የምሻው የዚህች ሀገር ዜጋ ስለሆን ማግኘት ያለብኝ መብት ነው። አንተም ይህን የማክበር ግዴታ አለብህ። አትቀፈኝ!!”