>
5:28 pm - Monday October 9, 1273

ጠቅላዩ ምን ተሰማቸው? (ዶ/ር በቃሉ  አጥናፉ  ታዬ)

ጠቅላዩ ምን ተሰማቸው?

/ በቃሉ  አጥናፉ  ታዬ


ጥቅምት 12 ቀን 2012ዓ.ም. አቶ ጃዋር መሀመድ በፀጥታ ሀይሎች ተከብብሁ በሚል ስበብ በተፈጠረ ሁከት መንግስት ባመነው ቁጥር እንኳን ከ86 በላይ ሰዎች እንደሞቱ እና ከስምንት ወራት በኃላም ደግሞ ሰኔ 23 እና 24 2012ዓ.ም. የሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በዚህው በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ከ200 በላይ ዜጎች አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ እንደተገደሉ እና በርካታ ንብረት እንደወደመ ይታወቃል፡፡ ጳጉሜ 1 እና ሁለት ቀን 2012ዓ.ም. በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ከ160 በላይ የአማራ እና የአገው ተወላጆች  አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ እንደተገደሉም ተዘግቧል፡፡ ከጥቂት ቀናት በኃላም በዚህው ክልል በቤኒሻንጉል ጉምዝ በተመሳሳይ ሁኔታ መስከረም 14 ቀን 2013ዓ.ም. 20 አማራዎች በሌሊት ጥቃት እንደደረሰባቸው አሁንም ተዘግቧል፡፡ ይህ ሁሉ ጥቃት ሲደርስ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ እርሰዎ በአካል በቦታው ሂደው ተጠቂዎችን ሊጎበኙ፣ ሊያፅናኑ እና እርዳታ ሊያደርጉላቸው በተገባ ነበር፡፡ ይህን ማድረግ ካልቻሉም በቴሌቪዥን ቀርበው የተሰማዎትን ሀዘን መግለፅ፣ ማፅናኛ መልዕክት ማስተላለፍ ይጠበቅበዎት ነበር፡፡ ምንም አይነት የማስተዛዘኛ፣ የማፅናኛ ንግግር አለማድረግዎ ለተጠቂዎች ምን አይነት መልዕክት ሊሰጥ እንደሚችል ልብ ብለውት ይሆን? የተጠቂዎችን የውስጥ ቁስል እና ያረበበውን ህመም መረዳት ያልቻለ መሪ ለተጎጅዎች ምን ትርጉም ይሰጣል? የሚመራው ህዝብ በግፍ ሲጠቃ፣ ጉዳዩን አይቶ እንዳላዩ መሆን፣ በተጎጅው እግር ስር እራስን አስቀምጦ አለማየት ለተጎጅው ዜጋ ምን ያህል ህመም፣ ቁስል፣ እና ትካዜ እንደሚጨምር መረዳት አልቻሉምን? 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቢሮዓቸው የሉም እንዳንል ለተመሳሳይ ጥቃቶች የማፅናኛ ምላሽ ሲሰጡ እንሰማለን/እናያለን፡፡ በሊባኖስ ቤሩት በደረሰው ፍንዳታ 150 ሰዎች በማለቃቸው ምክንያት ለሊባኖስ መንግስት የማፅናኛ መልዕክት እንደላኩ ሰምተናል፡፡ እንዲሁም ሱዳን በጎርፍ ስትጠቃ ተመሳሳይ መልዕክት ልከዋል፡፡ በሀጫሉ ሁንዴሳም ግድያ የተሰማውትን ሀዘን ሲገልፁ ሰምተናል/አይተናል፡፡ እነዚህ ሁሉ ተገቢና ትክክል ናቸው፡፡ ታዲያ ምነው  በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት እና በቤኒሻንጉል ጉምዝ ለሚያልቁ ዜጎች ስሜት አላባ የሆኑት?

ጠቅላዩ በሚያስተዳድሩት ሀገር ዛሬም እንደ ትናንቱ የጥቃት ሰለባዎች ስጋት ላይ ናቸው፡፡ ምክንያቱም ለዚህ ጥቃት ተሳታፊ የነበሩት ወንጀለኞች እና የየወረዳው አመራሮች በጥቃቱ ተጠያቂ እንደሚሆኑ እና ለፍትህ እንደሚቀርቡ/እንደቀረቡም በመንግስት ሚድያ ቢገልፅም፤ ነባራዊ ሁኔታው ግን የተለየ እንደሆነ ተጠቂዎችም ገልፀዋል፡፡ ለማሳያነት ኢሳት መስከረም 14 ቀን 2013ዓ.ም. ያስተላለፈው ዜና አስረጅ ሲሆን የሰው ህይወት ያጠፉ ወንጀለኞች እና ንብረት ያወደሙ ወጣቶች በህግ ቁጥጥር ስር አለመዋላቸው እና  አሁንም ስጋት እንዳለባቸው፣ በዚህም ምክንያት አካባቢውን እየለቀቁ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ የፅጥታው ሁኔታ አሁንም አስተማማኝ እንዳልሆነ እና ለህይወታቸው እንደሚሰጉ ነው ተጠቂዎች ያሳወቁት፡፡ እንደተጠቂዎች ገለፃ ዋና ዋናዎች አጢፊዎች እንዳልተያዙ እና ፖሊሶች ወንጀለኞችን ይዘው እንደሚለቋቸው፣ ፖሊሶች እና የወረዳና የቀበሌ አመራሮች በጉዳዩ ተባባሪ እንደሆኑ፣ አይዟችሁ ሲሉዓቸው እንደነበር፣ አካባቢውን ለቃችሁ ውጡ ከምትታረዱ ተብለው ተጠቂዎች እንደሚዛትባቸው፣ አሁንም እንደሚያስፈራሯቸው ጠቅሰዋል፡፡ መንግስት ተጠቂዎችን ወደ ቄያቸው መልሻለሁ ቢልም የጥቃት ሰለባዎች ግን አሁንም ወደ ቦታቸው እንዳልተመለሱና እንኳን ለማቋቋም ይቅርና ለህይወታችው አስጊ ሁኔታ እንደሆነ እና ከመንግሰት ምንም አይነት እርዳታ እንዳልተደረገላቸው አስረድተዋል፡፡ 

የሚመሩት ህዝብ በሰብዓዊ መብት እጦት እየቆዘሙ ባለበት ሁኔታ፤ ዜጎች በሻሸመኔ፣ በዴራ፣ በዝዋይ፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ በሀረር እና በተለያዩ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በተከታታይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዜጎች ንብረታቸው ሲወድም፣ እንደ እንሰሳት ሲታረዱ፣ ነፍሰ-ጡር ሴት በምትናገረው ቋንቋ እና በምትከተለው እምነት ተፈርጃ ከባለቤትዋ እና ከልጆችዋ ፊት ስትታረድ፣ አምስት ሰዎች የአንድ ቤተሰብ አባላት ሲገደሉ፣ ፍች-አልባ በሆነ ልማድ ሰዎች ሰቆቃ እና ግፍ እየተፈፀመባቸው እሮሮ እያሰሙ ባሉበት ሀገር የተጠቂዎችን ስሜት ተረድቶ ከጎናቸው አለመሆን ስርዓቱ መልክና ምህዳር እንደጠፋበት ማሳያ ነው፡፡ 

የሰብዓዊ መብት ተሟጋችዋ ማያ አንጌሎ ስሜትን በተመለከተ እንዲህ ብላ ነበር፡፡ ‘’ሰዎች የተናገርህውን ሊረሱት ይችላሉ፤ ሰዎች የሰራህውንም ስራ ሊረሱት ይችላሉ፤ነገር ግን ሰዎች እንዲሰማቸው ያደረግኸውን ጉዳይ አይዘነጉትም’’ አለች፡፡ እውነት ነው፡፡ የተጎዳን ስሜት፣ የቆሰለን ልብ ፍቅር ከተሞላበት እንክብካቤ ውጭ ምንም ነገር ሊጠግነው አይችልም፡፡ መንፈስ አዘል ጥቂት የማፅናኛ ቃላት የደማን ልብ ልታዋዛው ትችላለች፡፡ ቤተሰቦቻቸውን አሰቃቂ በሆነ ሞት ተነጠቀው፣ ንብረታቸው ወድሞ፣ ማስፈራሪያ እና ዛቻ አሁንም እየተሰጣቸው በራሳቸው ሀገር ሰው ሁነው ከሰው በታች እየታዩ የሚኖሩ ዜጎች ምን ይሰማቸዋል ብሎ ማሰብ አለመቻል ለአዕምሮ እረፍትን የሚነሳ ጉዳይ ነው፡፡

Filed in: Amharic