>

‹‹ምኒልክ››፡- ሞቶም ያላረፈው ንጉሥ! (እውነት ሚድያ አገግሎት)

‹‹ምኒልክ››፡- ሞቶም ያላረፈው ንጉሥ!

እውነት ሚድያ አገግሎት

✍️ የወቅቱ ፖለቲካ ለየክልሎቹ የተለያዩ ሥርዓተ ትምህርቶችን ከመቅረጹ የተነሣ ምኒልክን ለአንዱ ‹‹ጭራቅ››፣ ለሌላኛው ደግሞ ‹‹መልአክ›› አድርጎ በመሳሉ ትውልዱ እንዳይስማማ አድርጓል!
✍️ ለማንኛውም ጥፋት (ለጥንቱም፣ ለአሁኑም ሁኔታችን) ከ100 መቶ ዓመታት በፊት የሞተውን ንጉሥ ተጠያቂ የማድረግ አባዜ የዘመናችን ፖለቲካና ትውልድ አካሄድ ሆኗል!
✍️ ንጉሡ ከሌሎች ‹‹የተለየ ግፍ›› በምኒልክ ተሠርቷል ወይ? ከሌሎች ብሔሮች የተገኙ ነገሥታትና ባላባቶችስ የባሰውን ግፍ አልሰሩም ነበር ወይ? ምኒልክስ ምንም መልካም ነገር ስላልነበራቸው ወይስ እንዲነገርላቸው ስለማይፈለግ ነው? ብሎ መጠየቅ ብልህነት ነው፡፡
✍️ የወቅቱ ፖለቲካ ምኒልክን ለይቶ የሚያወግዝበት፣ እንደ ጭራቅም የሚያጥላላበት ምክንያቱስ ምን ሊሆን ይችላል? ይህም በስፋት ተተንትኖአል፡፡
✍️ ‹‹…ከሁሉም በላይ ለኦሮሞ ወንድሞቼ ማስገንዘብ የምወደው ከምኒልክ አስከሬን እና ሐውልት ጋር በሀሳብ በመታገል ወይንም የጎበናን የሙት መንፈስ በማሳደድ የዛሬ ኦሮሞዎች የሚያገኙት አንዳችም ጥቅም አለመኖፈሩን ነው፡፡›› (ዶ/ር መረራ ጉዲና)
✍️ ባናሞግሳቸው እንኳን ከመቃብር እየጠራን ከምንወቅሳቸው #ንጉሡ_እንዲያርፉ_ብንተዋቸውስ?!
““““
ወትሮውን አንድ ሰው ሲሞት ‹‹ዐረፈ›› ይባል ነበር፤ አንድም ከዚህች ዓለም ውጣ ውረድ፣ አንድም ደግሞ ከዚህ በኋላ መልካምም ሆነ ክፉ ነገር ላይሠራ፡፡ የሀገራችን ሰውም ‹‹የሙት ወቃሽ አትሁን!›› ብሎ የሚገሥጸው ሟች በሕይወት እያለ ላደረጋቸው መልካምም ይሁን ክፉ ነገር ከዚህ በኋላ የመናገር (የመከራከር) ዕድል ስለሌለው ነው፡፡ ተከሳሽ በሌለበትና ማስተባበል በማይችልበት ሁኔታ ደግሞ ከሳሽ ሆኖ መቅረብ (ነገሩ ምንም ያህል እውነታነት ቢኖረው እንኳን) ተቀባይነት አይኖረውም!  ንጉሥ ምኒልክ (ኢትዮጵያን ከ1882-1906 ዓ.ም ለ24 ዓመታት የመሩት) ከሞቱ ቢያንስ መቶ ዓመታት አልፏቸዋል፤ ከሳሾቻቸው ግን አሁንም አሉ፣ ወደፊት ለሚወለዱትም የክሱን መዝገብ ‹‹ታሪክ›› በሚል ጽፈው አስቀምጠውላቸዋል፡፡ እናም በሟች ላይ የክሱ ፋይል በየጊዜው ይከፈታል፤ ክሱን የሚያስተባብል ግን ባለመኖሩ ‹‹በሌለበት›› እየተባለ ፍርደ ገምድሉ ይቀጥላል!
1. አወዛጋቢው ንጉሥ፡- ለአንዱ ሰይጣን፣ ለአንዱ መልአክ!
————————————-
ዐጼ ምኒልክ በዘመናችን የጎሣ ፖለቲካ ውስጥ እጅግ አወዛጋቢና በርካታ ምስጋናዎችም ሆኑ ወቀሳዎች ከሚሰነዘሩባቸው የኢትዮጵያ ነገሥታት ዐጼ ምኒልክ የአንበሳውን ድርሻ ይይዛሉ ለማለት ያስደፍራል፡፡ ከፊሎቹ በአንደኛው ጽንፍ ቆመው ተከፋፍላ የነበረች ጀርመንን አንድ ባደረገው ሰው ስም ‹‹ኢትዮጵያዊው ቪስማክ›› በሚል ቅጽል ሲያሞካሹአቸው በአንጻሩ ሌሎች ደግም በሌላኛው ጽንፍ ሁነው በሌላኛው ጨካኝ ጀርመናዊ ‹‹ኢትዮጵያዊው ህትለር›› እስከማለት ይደርሳሉ፤ ‹‹ቅኝ ገዢው፣ ነፍጠኛውና ከአማራው ጎሣ ውጭ ያሉት ጎሣዎች ሁሉ ጨፍጫፊ ንጉሥ›› እያሉም ያብጠለጥሏቸዋል፡፡ ይህ ጽሑፍ የሁለቱንም ወገኖች አሳቦች የመደገፍም ሆነ የመቃወም ዒላማ ያነገበ አይደለም፤ ያለውን እውነታ ብቻ ለመግለጥ እንጂ፡፡
የችግሩ ዋና መንሥኤ ስለ አንዱ ንጉሥ ‹‹ለየክልሉ የሚመች ትርክት›› በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ተጋብቶ ለትውልድ መተላለፉ ነው፤ ዛሬ ያሉት ማንነታችን፣ ጥያቄዎቻችን እና ድርጊቶቻችን ደግሞ የተቀዱት ከአገሪቱ የትምህርት ካሪኩለም ይዘት መሆናቸው ይታወቃል፡፡ በተለያዩ ክልሎች የተለያዩ ‹‹የኢትዮጵያ ታሪኮችን›› ተምረናል፡፡ ትውልዱም በጥያቄ የተሞላው በአንዲት አገር ውስጥ የታሪክ ትምህርታችንም ‹‹ክልላውዊ›› ሆኗልና ነው፡፡ በጦርነት ያልቻሉን ነጮች፣ በሃይማኖት ትምህርት (መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃዎች) ያልረቱን ተቃዋሚዎች፣ በሰይፍ ስለት አስፈራርተው ያላንበረከኩን አክራሪዎች፣ በጎሣ-ተኮር ቅስቀሳ ወንበር ያላገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምን መሣርያ ድባቅ እየመቱን እንደሆኑም ግልጽ ማሳያ ነው፡- ትርክተ ምኒልክ!
2. ዛሬም ድረስ፣ ሁሉም ጥፋት ‹‹ምኒልክ የፈጸመው›› ነው!
—————————————–
በአንድ ወቅት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ አንድ በቀልድ ቢጤ የተዘጋጀ የካርቱን ሥዕል ይዘዋወር ነበር፡፡ ነገርዬው ግን ቀልድ ብቻ አልነበረም፤ ምናልባትም በዘመናችን ባለው አብዛኛው ትውልድ አእምሮ ውስጥ ከሚመላለሱት ጥያቄዎች ዋነኛውን ጉዳይ የያዘ ነበር፡፡ የካርቱን ሥዕሉ የሚገልጸው በአጭሩ፡- አንድ ልጅ ዘወትር የምኒልክን ስም ሲያጠፋ ከሚውለው ሚዲያ ላይ ሲያፈጥ ዉሎ በመሃል እናቱ ድንገት በንዴት ወደርሱ መጥታ ‹‹ማን ነው ይህንን የልብስ መስቀያ ገመዳችንን የበጠሰው?›› ብላ አፋጠጠችው፡፡ ልጁም ከመርበትበቱ የተነሣ ቶሎ የመጣለት ምላሽ ‹‹ምኒልክ!›› የሚል እንደነበር ነው፡፡ ለማንኛውም ጥፋት (ለጥንቱም፣ ለአሁኑም ሁኔታችን) ከአንድ ሙሉ ክፍለ ዘመን በፊት የሞተውን ንጉሥ ተጠያቂ የማድረግ አባዜ! ተፈልገው ላልተገኙት ወንጀለኞች፣ በረቀቀ የቴክኖሎጂ ስልት ጥቃት ለሚያደርሱ ሕገ ወጦች፣ ማንነታቸው በግልጽ እየታወቀ እንኳን እንዲጠየቁ ለማይፈለጉ ግፈኞች ሁሉ ዛሬም ድረስ ምኒልክን ግንባር ቀደም ተጠያቂ ለማድረግ የሚዳዳቸው አሉ፡፡ ልክ አንዳንድ ሃይማኖተኞች በራሳቸው ድክመት ለሚፈጽሟቸው ኃጢአቶች ‹‹ሰይጣን አሳስቶኝ›› ብለው ተጠያቂነትን እንደሚያሸሹ ሁሉ የዘመናችን ፖለቲከኞችም ምኒልክን የክፍተቶቻቸው ሁሉ ማሳበብያ ያደርጉታል፤ ሰይጣንና ምኒልክ ባይኖሩ ግን የሁለቱም ገመና ፍንትው ብሎ በተገለጠ ነበር!
3. የምኒልክ ግፍ ‹‹የተለየ›› ነውን? ግፈኞች ከሌሎች ብሔሮች ውስጥስ አልነበሩምን? 
———————————————–
አሁን ባለው (በተለይ የኦሮምያና ትግራይ) ትውልድ ዘንድ ዐጼ ምኒልክ ‹‹እንደ ጭራቅ›› ከመታየታቸውም በላይ እርሳቸው ብቻ ተለይተው ግፍ የሰሩ፣ ሌሎች ነገሥታት ግን አንጻራዊ መልካምነት እንደነበራቸው ስምምነት ላይ የተደረሰ ይመስላል፡፡ በመሠረቱ ይህ የንጉሡን ሌላኛውን ሰብእና (መልካምነታቸውን) ለመስማት ካለመፈለግ ብቻ ሣይሆን የሌሎችንም ቀደምት መሪዎች (ባላባቶቹንና ነገሥታቱን) ችግሮች አለማወቅ ጭምር ይመስላል፡፡ ምንም እንኳን የዐጼ ምኒልክን አዎንታዊ ማንነት ለመግለጽ የግድ የሌሎችን ጭካኔ መዘርዘር አስፈላጊ ባይሆንም ትውልዱ ወደ ትክክለኛው መሥመር ይመጣ ዘንድ ግን ‹‹ንጉሡ ከሌሎች ምን የተለየ ነገር አድርገው ነው? ሌሎች ነገሥታት አልበደሉም ነበር ወይስ የእርሳቸው ተለይቶ ለምን ገነነ? ምኒልክን የሚነቅፉ የኦሮሞና የትግራይ ብሔርተኞችም ሆኑ ሌሎች ከራሳቸው አብራክ የተገኙቱ መሪዎች ያደረጉትን በትክክል ያውቃሉ ወይ?›› ብሎ ማሰብ ስለሚያስፈልግ በመጠኑ መጠቋቆም ሳይሻል አልቀረም፡፡
በአብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ዘንድ በጀግንነታቸው የሚወደሱት ዐጼ ቴዎድሮስ እንኳን ለመናገርና ለመስማት የሚሰቀጥጡ የጭካኔ ድርጊቶችን ፈጽመዋል፤ ለሀገሪቱ አንድነት ከነበራቸው ጽኑ ዓላማ አንጻር ተመዝነው ይቅር ተብለው ካልሆነ በቀር፡፡ አለቃ ተክለ ተክለ ኢየሱስ ዋቅጅራ ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ›› በተባለው መጽሐፋቸው ምዕራፍ 33 ሙሉውን (ከገጽ 233-236) ‹‹ዐጼ ቴዎድሮስ ስለ ፈጸማቸው አሰቃቂ የጅምላ ጭፍጨፋዎች›› በሚል ርእስ የጻፉትን ስንመለከት፡- ንጉሡ በነገሡ በ14 ዓመት (1859 ዓ.ም) የአማራ ሳይንት ሰዎች ክደት (መንቅለ መንግሥት) ስላሰቡ 400 ሰዎችን በጥይት አስደብድበዋል፤ በዋድላም እንደዚሁ ‹‹ሊከዱ ነው›› የሚል ወሬ ስለተሰማ ብቻ ‹‹ለሕዝቡ ደሞዝ እሰጣለሁ›› ብለው አዋጅ በማስነገር ሁሉም እንዲሰበሰብ ካደረጉ በኋላ 650 የየጁን ጦር አስፈጅተዋል፤ 400 የሜጫና አገው ሰዎችንም በተመሳሳይ ምክንያት በቀን ሐሩር፣ በሌሊት ቁር እንዲሰቃዩ ከማድረጋቸውም በላይ በረሃብና  በጥም ገድለዋቸዋል፤ ቃሮዳ በሚባል ቦታ 700 ሕጻናትን ቤት አስገብተው በእሳት አቃጥለዋቸዋል፤ እንደዚሁ በደብረ ታቦር 6,700 ሰዎችን በይፋግ ከተማ ከሣር ቤት አስገብተው በእሳት አቃጥለዋል፤ (ስብሐት ገ/እግዚአብሔር፤ እነሆ ጀግና፤ 4ኛ እትም፤ 2010፡30 ላይ ‹‹የሥጋ ደዌን ለማጥፋት ነው›› ብሏል)፤ ማኅደረ ማርያም ላይ ሊቀበሏቸው ወረብ ሲያቀርቡ  የነበሩ 450 ካህናትን በነፍጥ አስፈጅተዋል፤ የቤገምድርን እህል አስዘርፈው ‹‹ለጋማ ከብቶች ይህንን እህል እንጂ ሣር አትስጡ›› ብለው ሕዝቡ ግን ለረሃብ አጋልጠዋል፤ 961 ቅዱሳት መጻሕፍትን ከጎንደር አድባራት ዘርፈው ወደ መቅደላ ወስደዋል (በኋላ እንግሊዞች ወደ ሀገራቸው ወስደዋቸዋል)፡፡ እንደዚሁም የእስረኞችን እጅና እግር እየቆረጡ፣ አልያም እንዲሁ እንዳለ የፊጥኝ በማሰር ከመቅደላ አፋፍ ወደ ገደል ይጨምሩ ነበር፤ የችካኔአቸውን ጥግ የሚያሳየው ደግሞ እነዚያ እጅና እግራቸው የተቆረጠ ሰዎችን በሰልፍ በፊታቸው እንዲያልፉ በማድረግ ደስታን ለማግኘት መሞከራቸው ነበር (ተክለ ጻድቅ መኩሪያ፣ ዐጼ ምኒልክና የኢትዮጵያ አንድነት፣ 1983፡24-25፤ ገብረ ሥላሴ፣ ታሪከ ዘመን ዘዳግማዊ ምኒልክ፣ 2008፡42፤ ታቦር ዋሚ፣ የውገና ድርሰቶችና የታሪክ እውነቶች፣ 2006፡382፣ 413)፡፡
ትግራዋይ በሆኑት መኳንንትና ነገሥታት ከተፈጸሙ የግፍ ተግባራት መካከል ደግሞ ጥቂቶችን በምሳሌነት እንጥቀስ፤ ግፍና ጭካኔ ከአንድ ብሔር ጋር የሚወለድ ‹‹የሥጋ ቁራጭ፣ የአጥንት ፍላጭ›› እንዳይመስል፡-
✍️ የአድዋው ተወላጅ (ትግራዋይ) ራስ ሚካኤል ስሁል ክርስትና መሠረቱን በጣለበት የሀገራችን ማኅበረሰብ ውስጥ ተወልደው ያደጉ ነበሩ፡፡ ነገር ግን በክርስትናው አስተምህሮም ሆነ ‹‹ሰማይ አይታረስ፣ ንጉሥ አይከሰስ›› ከሚለው የኢትዮጵያውን እሴት ተቃራኒ በሆነ መልኩ በዙፋን ላይ የነበረውን ዐጼ ኢዮአስን (ኦሮሞ) በኃይል ከዙፋን አውርደው በሻሽ አሳንቀው አስገድለዋል፤ ግድያውን ያጋለጡት ግን  የጎንደር ደባትራን ነበሩ (ተክለ ኢየሱስ ዋቅጅራ፤ 2008፡178፤  ታቦር ዋሚ፤ 2006፡309)፡፡ ይኸው ሚካኤል ስሁል ለወረኛ ፋሲል ይዋጉ የነበሩ የኦሮሞ ወታደሮችን ድል አድርጎ ከማረካቸው በኋላ ዐይናቸውን በወስፌ እየጎለጎለ አውጥቶ ጅብ እንዲበላቸው በተከዜ ዳርቻ ጥሏቸዋል (በዕውቀቱ ሥዩም፤ ከአሜን ባሻገር፤ 2008፡194)፡፡ ዋጨቃ የተባለ ሌላ ምርኮኛም በራስ ሚካኤል ፈራጅነት ከነሕይወቱ ቆዳው እንዲገፈፍ ተፈርዶበታል። የሚካኤል ስሑል አድናቂ የነበረ የዓይን ምስክር ይህን አስመልክቶ ሲጽፍ፡- ‹‹ከዚያ በኋላ ዋጨቃን እንደፍየል ይበልቱት ዘንድ አስረከቡት›› ሲል በወቅቱ አገሪቱን የጎበኘው ያዕቆብ ብሩስ ደግሞ የዋጨቃ ቆዳ በአደባባይ ይጎበኝ እንደነበር ዘግቧል። (በዚሁ መጽሐፍና ገጽ ላይ)።
✍️ ትግራዋዩ በዝብዝ ካሣም (በኋላ ዐጼ ዮሐንስ) ቢሆኑ እንደ ቀደምት ነገሥታት ሁሉ ባላንጣቸውን አስገድለው ወደ ሥልጣን ለመምጣት ሲሉ እንግሊዞችን መርተው መቅደላ (ወደ ዐጼ ቴዎድሮስ) በማምጣት አሲረው ለንጉሡ መሞት ምክንያት መሆናቸው መዘንጋት የለበትም (ተክለ ጻድቅ መኩሪያ፤ ዐጼ ዮሐንስና የኢትዮጵያ አንድነት፣ 1982፡24)፤ ከዐጼ ቴዎድሮስ ቀጥለው የነገሡት አማራውን ዐጼ ተክለ ጊዮርጊስ-2ኛን (ዋግ ሹም ጎበዜ) በጦርነት ድል አድርገው ከማረኳቸው በኋላ ሁለቱንም ዓይናቸውን በጋለ ብረት ማጥፋታቸውን በዕውቀቱ ሥዩም የታሪክ ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል (ከአሜን ባሻገር፤ 2008፡196)፤ ምንም እንኳን ግራኝ አስቀድሞ የበረዘውን ሥነ ምግባርና ባህል ለማረቅ ቢሆንም ሱረት የሚስቡ ሰዎችን አፍንጫ በመፎነን፣ ትምባሆ የሚያጨሱ ሰዎችን ከንፈር በመቁረጥ ሲቀጡ ነበር፤ የበደሉትን ሰዎች እጅና እግርም ይቆርጡ ነበር (እዚያው፤ ገጽ.196 ላይ ከእንግሊዛዊው ጀኔራል ጎርዶን [General Gordon’s Journal, P.216]  የተጠቀሰ፤ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ፣ ዐጼ ዮሐንስና የኢትዮጵያ አንነት፣ 1982፡200-201፤ ተክለ ኢየሱስ ዋቅጅራ፤ 2008፡262)፡፡ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ‹‹አልታዘዙልኝም›› በሚል ቂም የጎጃምን ሕዝብ ከየመንገዱና ከሥራ ላይ ጭምር እያስያዙ በጭካኔ አስጨፍጭፈዋል፤ በርካታ ንብረቶቻቸውን ከመመዝበራቸውም በላይ ጳጳሱ አቡነ ሉቃስ ‹‹ደርቡሽን እወጋለሁ ብለህ መጥተህ ለጎጃም ደርቡሽ ሆንኸው!›› ብለው እስኪገሥጹአቸው ድረስ አብያተ ክርስቲያንቱን ጭምር ተዳፍረዋል (ተክለ ኢየሱስ ዋቅጅራ፣ 2008፡277፤ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ፣ ዐጼ ዮሐንስና የኢትዮጵያ አንድነት፤ 1982፡503-506)፡፡
✍️ ትግራዋዩ ራስ አሉላ አባ ነጋም በ1886 የባርያ ብሔረሰብ መሪ በቂ ግብር አላስገባም በማለቱ በነዋሪው ላይ የጅምላ ቅጣት ፈጽሟል፤ ሁለት ሦስተኛው የባርያ ኩናማ ብሔረሰብ ሕዝብና ቀንድ ከብት ማለቁንም ዘግቧል (በዕውቀቱ ሥዩም፤ ገጽ.196 ላይ ከራስ አሉላ አድናቂ ታሪክ ጸሐፊ ሀጋይ ኤርሊክ ‹‹The Biography of Alula, P.105›› ጠቅሶ እንዳሰፈረው)፡፡
መሰል የጭካኔ ሥራ በዘመኑ ጠርዘኛ ፖለቲከኞች ዘንድ ‹‹ነፍጠኞች›› እየተባሉ በሚጠሩት የአማራና የትግራይ መሪዎች ብቻ የሚተገበር ሣይሆን በኦሮሞዎችም ጭምር ይፈጸም እንደነበርም መታወቅ አለበት፤ ግፍና ጭካኔ ዘርም ሆነ ሃይማኖት የላቸውምና። ለምሳሌ፡-
✍️ በግራኝ አህመድ ጂሃድ ጦርነት ማብቂያ ላይ ወደ ኢትዮጵያ የመጣውና  በጊዜው ለነበረው የኦሮሞ እንቅስቃሴ የዓይን ምስክር የነበረው ቤርድሙዝ አስገባሪ [የኦሮሞ] ወታደሮች ምን እንደሚያደርጉ ሲጽፍ፡- ‹‹ባስገበሩት ሀገር ውስጥ ያገኙትን ወንድ ሁሉ ይገድላሉ፤ የወንድ ልጆችን ብልታቸውን ይቆርጣሉ፤ አሮጊቶችን ገድለው ወጣቶችን ለአገልጋይነት ይማርካሉ›› ሲል ጽፏል (Richard Pankhurst, The Ethiopian Borderlands, P.284 ጽፈውት ከአሜን ባሻገር፤ ገጽ 198 ላይ እንደተጠቀሰው)፡፡
✍️ ራስ ወልደሥላሴ ትግራይን ለብቻው በሚያስተዳድርበት ዘመን ከቱለማና ከጃዌ ጎሳ ወገን የሆነው የዘመኑ አባዱላ ጉጂ የተራቀቁ ጭካኔዎችን ይፈጽም ነበር፡- ባላንባራስ ወልደ ተክሌ የተባለውን የላስታ ባላባት ከማረከ በኋላ ጣቶቹ እንዲቆረጡ አድርጓል፤ የትግራዩ ባላባት የፈጸመበትንም ወረራ ለመበቀል ሲል ከህንጣሎ (ትግራይ) 12 ሰላማዊ ሰዎችንም አስጠልፎ  ያሥራ አንዱን ምርኮኞች ዓይን እንደ ሙጃሌ በወስፌ እየጎለጎለ ካወጣ በኋላ የ12ኛውን ዓይን ግን አንዱን ዓይን ብቻ ነቅሎ ትቶታል /ጉጂ ይህንንም ያደረገው እንጥፍጣፌ ርኅራኄ ስለተረፈው ሣይሆን አንድ ዓይናው ሰውየ የታወሩ ሌሎች ባልንጀሮቹን እየመራ ወዳገራቸው እንዲመልሳቸው ነበር/ (በዕውቀቱ ሥዩም፤ ‹‹ከአሜን ባሻገር›› መጽሐፉ ገጽ.195 ላይ ‹‹The Life and the Adventures of Natnael Pearce, P.75›› ከሚለው፣ ጉጂን በአካል ከሚያውቀው የዓይን ምስክር ናትናኤል ፒርስ ጠቅሶ  እንዳሰፈረው)፡፡
✍️ በንጉሥ ሣህለሥላሴ ዘመን ኢትዮጵያን የጎበኘው ሀሪስ፣ Ethiopian highlands በተባለው መጽሐፉ ቅጽ ሦስት (ገጽ.160) ላይ ስለ ጎማው ኦሮሞ ባላባት ሲነግረን፡- ‹‹የጎማው ባላባት የሚፈጽመውን ጭካኔ ለማሰብ ይከብዳል። ጥፋተኞች እጃቸውን፣ አፍንጫቸውንና ጆሮአቸውን ይቆረጣሉ። ዓይናቸው በጋለ ብረት ይፈርጣል፡፡ በዚህ ዓይነት ከተቆራረጡ በኋላ ሕዝቡ ይማርባቸው ዘንድ በገበያ መሃል እንዲያልፉ ይደረጋል። የጦር ምርኮኞች በመቶ በመቶ እየተመደቡ አንገታቸው ላይ ድንጋይ ታስሮ ዳማ ተብሎ ይጠራ በነበረው ወንዝ ውስጥ ይወረወራሉ›› በማለት ጽፏል (በዕውቀቱ ሥዩም፤ ከአሜን ባሻገር፤ 2008፡199)።
4. ምኒልክስ አንዳችም መልካም ነገርና ርኅራኄ አልነበራቸው ይሆን?
—————————————————
ስለ ዐጼ ምኒልክ ጭካኔ እጅግ በበዛ ክፍለ ጊዜ (Credit Hour) ተምረናል፤ ቋቅ እስኪለን ድረስም ተጎንጭተናልና አሁን እርሱን በመዘርዘር ጊዜ ማጥፋቱ አስፈላጊ አይደለም፡፡ ይልቁንስ ‹‹ሰበር ዜና›› የሚሆነው ንጉሡ መልካም ነገር አላቸው፣ ርኅሩሕ ናቸው፣ እንኳንስ በመወለድና በጋብቻ የተዛዷቸውን ሕዝቦች ቀርቶ ጠላቶቻቸውን ጭምር እንኳን ሳይገድሉ በምሕረት አሰናብተዋል የሚል ታሪክ ካለ ነው፡፡ ይኸኛው የታሪክ ክፍል ደግሞ አልተነገረላቸውም እንጂ ጠፍቶ አይደለም፤ ልክ ተደጋግሞ የተነገረ ውሸት እውነት ወደመሆን እንደሚቃረብ ሁሉ ሁልጊዜ በዝምታ የሚታለፍ ታሪክም ‹‹የለም፣ አልነበረምም›› ወደሚል ማምራቱ አይቀሬ ነውና፡፡ እስቲ ጥቂቶችን በማስረጃ አስደግፈን እንጠቁም፡-
✍️ ዐጼ ምኒልክ እንደነገሡ ‹‹ሁሉም እንደ እምነቱ ይኑር›› የሚል የሃይማኖት ነጻነት አዋጅ በማወጃቸው ተሰድደው የነበሩ በርካታ የወሎ ሙስሊሞች ወደ ትውልድ አገራቸው ተመልሰዋል፡፡
✍️ ምንም እንኳን ይደረጉ የነበሩ የግፍ ቅጣቶችን ንጉሡ ሙሉ በሙሉ አስቀርተዋል ብሎ ለመናገር ባያስደፍርም ዐጼ ምኒልክ በዘመናቸው በኦሮሞ፣ ትግራይ፣ ከፋ፣ ዐማራና አፋር ወታደሮች የሚተገበረው ምርኮኞችን የመስለብ ባህል እንዲቀር አውጀዋል (በዕውቀቱ ሥዩም ወደ ወላይታ አብሯቸው ዘምቶ ከነበረው ፈረንሳዊው ወዶ ገባቸው ጠቅሶ እንደጻፈው፤ ከአሜን ባሻገር፤ 2008፡200)፡፡
✍️ ዛሬ ላይ የምናያቸው አብዛኞቹ የቴክኖሎጂና የሥልጣኔ ጭላንጭሎች የተወጠኑት በዐጼ ምኒልክ አማካይነት መሆናቸውን ማንም አይክድም፡፡ ለአብነት ያህል፡- ዘመናዊ ጋዜጣና ስልክ በ1882 ዓ.ም፤ ፖስታ፣ ገንዘብና የውኃ ቧንቧ በ1886 ዓ.ም፤ ጫማ፣ የሙዚቃ ት/ቤትና የጽሕፈት መኪና በ1887 ዓ.ም፤ ኤሌክትሪክ፣ ዘመናዊ መኪና፣ ሲኒማ፣ የሙዚቃ ሸክላና ቀይ መስቀል በ1889 ዓ.ም፤ [ዳግማዊ ምኒልክ] ሆስፒታል በ1890 ዓ.ም፤ ባቡርና ብስክሌት በ1893 ዓ.ም፤ የብር ሕትመት በ1895 ዓ.ም፤ የመንገድ ሥራ በ1896 ዓ.ም፤ ፍል ውኃ በ1897 ዓ.ም፤ [አቢሲኒያ] ባንክ፣ [እቴጌ ጣይቱ] ሆቴል፣ ማተሚያና ላስቲክ በ1898 ዓ.ም፤ ድልድይ፣ አራዊት ጥበቃና የጥይት ፋብሪካ በ1899 ዓ.ም፤ ጋዜጣ፣ አውቶሞቢልና ዘመናዊ አስተዳደር (የሚኒስትሮች ሹመት) በ1900 ዓ.ም ለመጀመርያ ጊዜ እውን ያደረጉት እርሳቸው ናቸው (የጳውሎስ ኞኞ ‹‹ዳግማዊ ዐጤ ምኒልክ››፤ 1984 ዓ.ም ሙሉ መጽሐፍ እና ታየ ቦጋለ፣ መራራ እውነት፣ 2011፡ 242-244 ይነበብ)፡፡
✍️ ዐጼ ምኒልክ ለጠላቶቻቸውም ርኅራኄን ያሳዩ ነበር፡፡ ጸሐፌ ትእዛዛቸው እንደገለጹት ንጉሡ እንደ አባት፣ እንደ እናት ሁነው በርኅራኄ ብቻ ይገዙ ነበር (ገብረ ሥላሴ፤ ታሪከ ዘመን ዘዳግማዊ ምኒልክ፤ 2008፡265)፡፡ በርካቶች ‹‹እምዬ ምኒልክ›› የሚሏቸው ከዚህ አንጻር ይመስላል፡፡
✍️ ከተቀናቃኞቻቸው ጋር ተሰልፈው ከወጓቸው በኋላ ተሸንፈው (ተማርከው) በንጉሡ ፊት ይቀርቡ የነበሩት አብዛኞቹ መልካም አቀባበልና ምሕረት አግኝተዋል፡፡ ለምሳሌ፡- ገና የሸዋ ንጉሥ እያሉ እንኳን በእምባቦ ጦርነት ላይ ድል ካደረጉ በኋላ ቆስለው የተማረኩ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖትን ሐኪም ፈልገው በማሳከም፣ ፍሪዳና ማር እንዲሁም ቅቤ እየመገቡ፣ ከምንም በላይ ደግሞ በፍጹም የርኅራኄ ስሜት ጧትና ማታ እየጠየቁ ማዳናቸው በታሪክ ይዘከራል፤ ‹‹የማረክን እኛ ብንሆን ኖሮ እርስዎን ቆራርጠን ለአሞራ እንሰጥ ነበር›› ብለው በድፍረት የተናገሯቸው የንጉሥ ተክለ ሃይማኖትን ወታደሮችንም ያለ አንዳች ቂም ምግብ አዝዘውላቸው ከግዛት አውጥተዋቸዋል (ተክለ ኢየሱስ ዋቅጅራ፤ 2008፡267)፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ከድቷቸው የነበረ የበዛብህ ሠራዊትን ‹‹ዜጎቼ ሆናችሁ ሳለ መልሳችሁ ወጋችሁኝ›› ብለው እንዳልጠሏቸው፤ ተቀናቃኛቸው ግን ለሦስት ጊዜያት ተይዘው በምሕረት ቢለቀቁም ለመመለስ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ብቻ መቀጣታቸው ተገልጾአል (ገብረ ሥላሴ፤ ታሪከ ዘመን ዘ ዳግማዊ ምኒልክ፤ 2008፡44-45)፡፡
✍️ ከእነ ዐጼ ዮሐንስና ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ጋር በነበሩ ግጭቶችም ‹‹ተው፤ የሰው ደም አናፍስስ›› የሚል መልእክት ያስቀድሙ እንደነበር በታሪካቸው ጸሐፍት ተደጋግሞ የተዘገበ ነው፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ጣልያን ኢትዮጵያን ስትወርር ለውጊያው አዋጅ ሲያውጅ እንኳን ‹‹እኔ የሰውን መራብ፣ የከብቱንም ማለቅ አይቼ ዝም ብለው…›› የምትል ንግግራቸው ንጉሡ ከጠብ በፊት ለሕዝባቸው ደኅንነት ይጨነቁ እንደነበር ያሳያል፤ የመሪ ወጉ ይህ ነውና!
✍️ በዚያ የክፉ ቀን (የጽኑ ረሃብ ዘመን) ሰባት ልጆችን በልታ ለፍርድ በፊታቸው የቀረበችን ሴት ራሳቸው ይቅር ከማለትም አልፈው ሕዝቡን ‹‹ቢጨንቃት፣ ቢርባት ነውና ለእኔ ብላችሁ ማሩልኝ›› ሲሉ ሕዝባቸውን ተማጽነው ታድገዋታል (ተክለ ኢየሱስ ዋቅጅራ፤ 2008፡287)፡፡
✍️ ሰዎች ከሚሰሩት ሥራና ከሀብታቸው የተነሣ የበላይና የበታች እየተደረጉ የሚሰደቡበትን ሁኔታ በማስቀረት፣ ሥራና ትጋትን በተግባር በማሳያት ረገድ ፋና ወጊ ሚና ነበራቸው (ተክለ ኢየሱስ ዋቅጅራ፤ 2008፡288)፡፡
✍️ በባርያ ንግድ ይታወቁ ለነበሩት የጅማው ንጉሥ አባጅፋርም፡- ‹‹ሁላችንም የእግዚአብሔር ባሮች ነን እንጂ የሰው ባርያ የለውም፤ እናም እንደ ከብት ልሽጠው፣ ልለውጠው አትበል›› ሲሉ የምክር ደብዳቤ ጽፈውላቸዋል (ታየ ቦጋለ፤ መራራ እውነት፤ 2011፡247)፡፡
5. ታዲያ የወቅቱ ፖለቲካ ምኒልክን ብቻ እንደ ‹‹ጭራቅ›› የሳለበት ምክንያቱ ምንድን ነው?
—————————————————————-
በሐረርጌ ውስጥ በቆመው የጨለንቆ ሰማዕታት ሐውልት ላይ፡- ‹‹በወራሪው ሚኒልክ አማካይነት የተጨፈጨፉ ከ17 ሺህ በላይ የሐረሪ ሰማዕታት መታሰቢያ›› የሚል ተጽፏል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በአርሲ አኖሌ ሐውልት ላይም በጨካኙ ንጉሥ ዐጼ ሚኒልክ አማካይነት እጅና ጡታቸው የተቆረጡ የኦሮሞ ሕዝቦች ጭፍጨፋ ታሪክ ተዘክሯል፡፡ እነዚህን የሚያነብና የሚለከት የኦሮሞ ትውድል ዐጼ ሚኒልክ ለኢትዮጵያ ነጻነት የታገሉ ሳይሆን የሀገሪቱን ልጆች የፈጁ አረመኔ፣ አገሪቱን ከቅኝ ግዛት የተከላከሉ ሳይሆን ራሳቸውም ቅኝ ገዥ እንደነበሩ ቢያስብ ምን የሚገርም ነገር አለው?
በተመሳሳይ መልኩ በሐዋሣ ከተማ በተገነባው የሲዳማ ባህል ሙዚዬም የፊት ግድግዳ ላይም ‹‹ወራሪው የምኒልክ ጦር›› እንዴት ሲዳማን በግፍ እንደተቆጣጠራት የሚገልጽ ሥዕላዊ መግለጫ ሰፍሯል፡፡ ስለዚህም በዚህ ቀመር መሠረት ምኒልክ ለደቡብ ሕዝብ ጠላቱ እንጂ ምኑ ሊሆን ይችላል?
ያም ሆነ ይህ አሁን ባለው ትውልድ ዘንድ ዐጼ ምኒልክ ‹‹እንደ ጭራቅ›› እንዲሳሉ ያደረገው የሕወሓት ወገናዊ ፖለቲካ እንደሆነ ለመመስከር ብዙ መዳከር አያስፈልግም፤ ሁሉም ነገር ተፈጭቶና ተቦክቶ የተጋገረው በዚሁ ትውልድ ዘንድ ነውና፡፡ ባይሆን የሚያጠያይቀው ‹‹ሕወሓትስ ቢሆን ለዐጼ ምኒልክ ይህንን ያህል የከረረ ጥላቻ ሊያዳብር የቻለው በምን ምክንያት ነው?›› የሚለው ነው፡፡
ምናልባትም ዐጼ ምልክን ከኢትዮጵያ ገዢነታቸው ይልቅ የአማራ ገዢው መደብ ፊታውራሪ እድርገው ከመውሰዳቸው የተነሣ ሊሆን ይችላል የሚለው ቀዳሚው መላምት ነው፡፡ ለምሳሌ፡- ዐጼ ዮሐንስ-4ኛ (ትግራዋይ) የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት በነበሩበት ወቅት ዐጼ ምኒልክ ደግሞ የሸዋ ንጉሥ ነበሩ፡፡ ንጉሥ ምኒልክ ከጎጃሙ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ጋር በእንባቦ ላይ ያደረጉትን ውጊያ በድል ቢያጠናቅቁም በንጉሠ ነገሥቱ ግሣጼ ሁለቱ እርቅ ማውረዳቸው ብቻ ሣይሆን በቅጣት መልክ ከየግዛቶቻቸው ተቆርሶ ለሌሎች ሹማምንት መሠጠቱ ሳያበሳጫቸው አልቀረም፡፡ እናም ዐጼ ምኒልክ ከደርቡሾች ጋር በምሥጢር እየተገናኙ ይዶልቱና ዐጼ ዮሐንስን ለማስገደል ያሤሩ እንደነበር፣ ዐጼ ዮሐንስ ለመሞታቸው ምክንያቱም ይኸው እንደነበር የታሪክ መዛግብት ይጠቁማሉ (ተክለ ኢየሱስ፤ 2008፡268-280)፡፡ በጎንም ያለ ዐጼ ዮሐንስ እውቅና በኋላ ከተዋጓት ጣልያን ጋር በኅቡዕ ይጻጻፉ እንደነበር ተነግሯል፡፡ እናም ይኸ ታሪክ በሕወሓቶቹ ማሕቀፈ እሳቤ ቋት ውስጥ ገብቶ ሲተነተን ‹‹አማሮች በትግራይ ሕዝብ ላይ ያሤሩት ሤራ›› ተደርጎ ይሆን?
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከትግራይ አከባቢ የወጡ አንዳንድ ጸሐፊዎችም ‹‹ዐጼ ምኒልክ የኢትዮጵያ ጠላትና ለሽያጭ ገበያ ያቀረቧት፣ ዐጼ ዮሐንስ ግን ብቸኛና እውነተኛ የኢትዮጵያ መሪ እንደነበሩ›› በድፍረት መናገር የጀመሩት ከዚህ አኳያ ይመስላል፡፡ በመሠረቱ ‹‹አንዱን መልአክ ለማድረግ ሌላውን ሰይጣን›› ማድረግ አይጠበቅብንም ነበር፡፡ በተለይ ለትውልድ የሚተላለፍ ታሪክ ሲጻፍ ሚዛናዊነቱን ጠብቆ፣ እውነትን መሠረት አድርጎ ቢሆን ከትዝብት ባተረፈ ነበር፡፡
ዋናው የጽሑፋችን ማጠንጠኛም አንድን የታሪክ ሤራ ለመበቀል ሲባል ሌላ ታሪካዊ ሤራ እየተሠራ መሆኑን መጠቆም ብቻ ነው፡፡ ሕወሓት ምኒልክን ‹‹አማራ››፣ አማራን ደግሞ ‹‹ነፍጠኛ›› ብሎ ከፈረጀ በኋላ ሁለቱን ለመበቀል ሲል በተሳሳተ የታሪክ ትርክት ሌሎች የሀገሪቱ ሕዝቦችን በእነዚህ ላይ የክተት ዐዋጅ አስነግሮ አዘመተ፡፡ የዚህ ስኁት ትርክት ሰለባ ከሆኑት ደግሞ የኦሮሞ ሕዝብ ዋነኛው ነው፡፡ ኦሮሞን በአማራ ሕዝብና በዐጼ ምኒልክ ላይ ለማዝመት ደግሞ ከዐጼ ዮሐንስ ጋር የተያያዘውን ያንን የቆየ ቂም ከበርካታ ዓመታት በኋላ ምኒልክ ወደ ደቡባዊ የሀገሪቱ ክፍል ካደረጉት የአንድነት ጉዞ ጋር አቆራኝቶ ማናከሱ የሤራው ቁንጮ ሆነ፡፡
እናም ዛሬ ላይ ምናልባትም ‹‹ሁሉም›› በሚባል ደረጃ ኦሮሞ ወደ ዛሬዋ ኢትዮጵያ የተጠቃለለው በምኒልክ ዘመን እንደሆነ ስምምነት ላይ የተደረሰ ይመስላል፡፡ እውነታው ግን እንደርሱ አይደለም፡፡ እንዲያውም ዐጼ ቴዎድሮስ አስቀድመው የወሎ ኦሮሞዎችን ማስገበር ጀምረው እንደነበር፣ አብዛኛው የደቡብና የኦሮምያ ክልሎች ግን በቁጥጥር ሥር የዋሉት በዐጼ ዮሐንስ 4ኛ ዘመነ መንግሥት እንደሆነ ደኀርት የብሔረሰቡ ታሪክ ጸሐፍት ጭምር የመሰከሩት ነው (ታቦር ዋሚ፤ 2006፡109)፡፡ ከጎጃሙ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ጋር በእንባቦ የተካሄደው ጦርነትም ምኒልክ ገና የሸዋ ንጉሥ ሆነው ሳሉ (የሀገሪቱ ንጉሠ ነገሥት ዐጼ ዮሐንስ) እያሉ መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ በተማሳሳይ መልኩ ሐረርና አርሲም ወደ ዛሬዪቱ ኢትዮጵያ የተጠቃለሉት ዐጼ ምኒልክ የሸዋ ንጉሥ ሆነው፣ በዐጼ ዮሐንስ ንጉሠ ነገሥት ፈቃድና እውቅና መሆኑ መረሳት የለበትም፤ ያለ ንጉሠ ነገሥቱ ይሁንታ የሚካሄድ መሰል ዘመቻ አይኖርምና፡፡ እውነታው ይህ ከሆነ ዘንዳ በተለይ ከሕወሓት መራሹ ኢህአዴግ ዘመነ መንግሥት በኋላ ስለ ኦሮሞ ‹‹መጠቃት›› ታሪክ ሲነሳ ግን ከዐጼ ዮሐንስ ይልቅ ዐጼ ምኒልክ ስማቸው ጎልቶ እንዲነገር የተፈለገበት ምክንያት ለምን ይሆን? ብሎ መመርመር ብልህነት ነው፡፡ ምናልባትም ሁለቱን ሕዝቦች (ኦሮሞንና አማራን) ከፋፍሎ በማናከስ አንዱን በሌላኛው በማስፈራራት ለመግዛት ታቅዶ እንደሁም ማጤን ተገቢ ይሆናል፡፡
ሌላው ገራሚው ነጥብ አብዛኛውን የኦሮምያ ክፍል በፊታውራሪነት በማስገበር የሚታወቁት የዐጼ ምኒልክ አርበኛ (ኦሮሞው) ጎበና ዳጬ የተሰጣቸውን ተልእኮ አጠናቅቀው ያረፉት (የሞቱት) ዐጼ ምኒልክ ገና የሀገሪቱ ንጉሠ ነገሥት ከመሆናቸው በፊት (በ1881 ዓ.ም) መሆኑ ነው፡- በደብረ ሊባኖስ በሚገኘው መቃብራቸው ላይም ‹‹ከሸዋ እስከ ሱዳን ያቀናው አርበኛ፣ ጎበና አባጥጉ እዚህ አርፎ ተኛ›› ተብሎለታል (ታቦር ዋሚ፤ 2006፡505)፡፡ ከዚህ ሁሉ የምንረዳው ቢኖር ሂደቱ በአዎንታም ይታይ በአሉታ፣ ኦሮሞ ከሰሜናውያን ወንድሞቹ ጋር ለመዋሐድ የበቃው በዐጼ ቴዎድሮስ በተጀመረ ውጥን፣ በዐጼ ዮሐንስ በተጠናከረ አቋምና በዐጼ ምኒልክ በተፈጸመ ተልእኮ እንጂ በአንድ ንጉሥ ፍላጎት ብቻ አለመሆኑን ነው፡፡ ይህ ከሆነ ዘንዳ ደግሞ አንዱን ብቻ ነጥለን፣ ያውም በወቅቱ ከፍተኛ የአመራር ደረጃ ላይ ያልነበረውን መርገም ከምን ሊመጣ እንደቻለ መጠየቅ ይኖርብናል፡፡
በተለይ ‹‹ነፍጠኛው ዐጼ ምኒልክ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ የከፋ በደል ፈጽመዋል›› እየተባለ ከሚነገረው ጋር የንጉሡ እናት ኦሮሞ መሆናቸው፣ ከኦሮሞ ጋር ተጋብተው መውለዳቸውና ልጃቸው ሸዋረጋን ለኦሮሞ መዳራቸው ሁሉ አብሮ መዘከር ነበረበት፡፡ በንጉሡ ዙርያ የነበሩት አብዛኞቹ ባለሥልጣናት (መኳንንትና መሳፍንት) ማንነትም መፈተሽ ነበረበት፤ ሌሎቹ ቢቀሩ፡- የጦር (መከላከያ) ሚኒስትር እና የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰብሳቢው ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ (ቁሴ) ዲነግዴ፣ የፍትህ ሚኒስትሩ አፈንጉሥ ነሲቡ መስቀሎ፣ የቤተ መንግሥት ግምጃ ቤት ኃላፊው ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ (አባ ነፍሶ፣ በአባታቸው)፣ የእልፍኝ አስከልካዮቹ ሻለቃ ኢብሳና ፊታውራሪ ደቻሳ፣ ዋና አስተርጓሚና አማካሪያቸው ገብሬል ጎበና፣ የሀገር ውህደት ዘመቻ መሪው ራስ ጎበና ዳጬ፣ ደጃዝማች ወልደ ሚካኤል ጉዲሣ (የአንኮበር አከባቢ/ጎላ ገዥ) ሁሉ ከኦሮሞ ማኅበረሰብ አብራክ እንደተገኙ ይታወቃል (ተክለ ጻድቅ መኩሪያ፣ ዐጼ ምኒልክና የኢትዮጵያ አንድነት፣ 1983፡695-703፤ ታየ ቦጋለ፣ መራራ እውነት፣ 2011፡249)፡፡ እናም ጥፋተኝነትና ተጠያቂነት ‹‹በዘር የሚተላለፍ›› ከሆነ ገፊውም፣ ተገፊውም ከኦሮሞ ብዙም አይርቅም፤ አብዛኞቹ የንጉሡ ሹመኞችና የጦር አዛዦች ከማኅበረሰቡ የተገኙቱ ነበሩና! ሌላው ቀርቶ ከሞት እንደማይተርፉ ሲያውቁ እንኳን የንግሥና ሥልጠናቸውን የተናዘዙት ከወሎ ኦሮሞ ለሚወለደው፣ ወደ እስልምናውም ለሚቀርበው ለልጅ ልጃቸው ኢያሱ ነበር፤  ምኒልክ መሥፈርታቸው ሀገር እንጂ ዘርና ሃይማኖት አልነበረምና! እናም በአንድ በኩል ‹‹የዓድዋ ድል ዋና ተዋናይ ኦሮሞና ፈረሱ ነበሩ›› እያሉ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ‹‹በአኖሌና በጨለንቆ ኦሮሞን የፈጀው ምኒልክ ነው›› ማለት ሚዛናዊ አይለም፤ በታየ ቦጋለ አገላለጽ ‹‹መርጠህ የምትወስደው ድል፣ መርጠህ የምትተወው ክፋት አይኖርም!››
የጽሑፋችንን ጭብጥ ዶ/ር መረራ ጉዲና በአንድ ወቅት ባስተላለፉት መልእክት እንቋጭ፡- ‹‹…ከሁሉም በላይ ለኦሮሞ ወንድሞቼ ማስገንዘብ የምወደው ከምኒልክ አስከሬን እና ሐውልት ጋር በሀሳብ በመታገል ወይንም የጎበናን የሙት መንፈስ በማሳደድ የዛሬ ኦሮሞዎች የሚያገኙት አንዳችም ጥቅም አለመኖፈሩን ነው፡፡›› (ጦብያ መጽሔት፣  ቅጽ 3፣ ቁጥር 12፣ 1987 ዓ.ም፤ ገጽ.16/17)፡፡
6. ማጠቃለያ፡- ‹‹ነቢይ በሀገሩ›› ብቻ ሣይሆን ‹‹ንጉሥም በሀገሩ›› አይከበርም!
—————————————————————-
ዐጼ ምኒልክ የረቀቀውን የጣሊያንን ፖለቲካዊ ሤራና ሀገር የመቀራመት ብሎም ማንነትን በማጥፋት ቅኝ የመግዛት ሕልም በዓድዋው ጦርነት ላይ አክስመው፣ ጥቁር ነጭን ያሸነፈበት የመጀመርያው የድል ታሪክን በማስመዝገብ ዓለምን ጉድ አሰኝተዋል፡፡ በዚሁ አግባብም አገሪቱ ዛሬም ድረስ የመላ አፍሪካውያን ተስፋና የጽ/ቤታቸውም ዋና መቀመጫ እንድትሆን ዐጼ ምኒልክ ጉልኅ ሚና የተጫወቱ መሪ ናቸው፡፡
ፋሺሽት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ስትወርር በካቶሊካውያኑ ‹‹ቅዱስ ጦርነት›› ተብሎ የታወጀም በመሆኑ ‹‹ሃይማኖታዊ›› ጭምር ነበር ማለት ይቻላል፡፡ እናም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንም የሀገርን ዳር ድንበር ለማስጠበቅ ከንጉሡ ጋር ታቦተ ጊዮርጊስን በመያዝ፣  በጸሎት እያገዘች (ወታደሩን በመንፈሳዊ ሞራል እየመራች) ዓለማቀፋዊ እውቅና ከመጎናጸፏም በላይ ለስብከተ ወንጌል ተልዕኮዋ ፈር ቀያሽ ሆኖላት አልፎ ነበር፡፡ ይኸውም የቀለም ልዩነት ጉዳይ ሣይሆን ካቶሊካውያኑ በኦርቶዶክሳውያኑ ላይ ያወጁት ጦርነት ስለነበር ከጦር መሣርያው ይልቅ የኦርቶዶክሳዊት ሃይማኖት ታላቅነት የተመሠከረበት ጭምር መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ በዐጼ ምኒልክ የተመራው የዓድዋ ድል አማካይነት አፍሪካ እንደ አህጉር፣ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር፣ ኦርቶዶክስ እንደ ሃይማኖት ልዕልናቸውን የተቀዳጁበት ድርብርብ ድል ነበር፡፡
ከዚህ አንጻር በዓለም ደረጃ ብዙዎች ‹‹የአፍሪካ መሪ›› እያሉ ሲያሞካሹአቸው፣ ‹‹ኢትዮጵያኒዝም›› የሚል የፀረ-ቅኝ ግዛት እንቅስቀሴ ሲመሠርቱ፣ ጎዳናቸውን በስማቸው ሲሰይሙ፣ ጥቂት የማይባሉ የምዕራብና መካከለኛው አፍሪካ ሀገራት ሰንደቅ ዓላማቸውን ወደ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ቀለማት ሲቀይሩ በአንጻሩ በገዛ ሀገራቸው በኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ ‹‹ቅኝ ገዢ፣ ጨፍጫፊና አረመኔ›› ተደርገው መወገዛቸው ልብ ይሰብራል፤ ያሳፍራልም፡፡ አብዛኞቹ ሚዲያዎቻችን እንኳን ከዘመኑ የሀገሪቱ ፖለቲካ ጋር ተሞዳሙደው ለማደር ሲሉ ብቻ የጥንቱን የአፍሪካ አባት (ምኒልክን) ከጉያቸው ውስጥ ሸጉጠው ደቡብ አፍሪካን ከአፓርታይድ አገዛዝ ነፃ ለማውጣት ታግሎ ያልተሳካለትን የቅርቡን ኒልሰን ማንዴላ ታሪክ ከሌላ ሀገር በማፈላለግ ‹‹የአፍሪካ የነጻነት አባት›› እያሉ ማንቆለጳጰሳቸው ያስተዛዝባል፤ ኢትዮጵያ ለትግሉ ፋና ወጊ፣ ለእርሱም አሰልጣኝ እንደነበረች ከመዘንጋቱም በላይ ፈጽማ ቅኝ ባልተገዛች ሀገር ሆኖ ከቅኝ ግዛት ለመላቀቅ የመጨረሻዋ የሆነች ሀገርን የማወደስ ድንቁርና! ‹‹ንጉሥም በሀገሩ አይከበርም›› የሚያሰኘውም ይኸው ሐቅ ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን ቀደምት መሪዎቻቸውን የተበቀሉ መስሎአቸው ለሌሎቹ ወገኑና ነገርዬው ‹‹ባለቤት የናቀውን አሞሌ…›› ሆኖ በቅርቡ እንኳን የዛሬው አፍሪካ ኅብረት ባለውለታ አባት ዐጼ ኃ/ሥላሴ ቸል ተብለው የጋናው ኩዋሚ ኑኩሩማ ‹‹የአፍሪካ አባት›› ተብለው በኅብረቱ ቅጽር ግቢ የመታሰቢያ ሐውልት እንዲቆምላቸው ሆነ፡፡ ይልቁን የቀደምቶቻችንን ስም ለማጠልሸት ያባከንነውን አእምሮ፣ ጊዜና ጉልበት ለጋራ ሰላማችንና ልማታችን ብናውል ኖሮ የሀገራችን እድገት ምን ያህል ይመነደግ እንደነበር ሲታሰብ እጅግ ያስቆጫል፡፡ እናም ለዐጼ ምኒልክ አዎንታዊ እውቅና መስጠትና በሚገባቸው ልክ ማክበሩን ብንተው እንኳን ዘወትር ከመቃብር እየጠራን የምንራገምበትን ልማዳችንን ብናቆም፣ ከሙታን መንፈስ ጋር ከመታገል የሕያዋን ሥልጣኔ ጋር ለመድረስ ብንተጋ፣ እርሳቸው ከሞቱ ከ100 ዓመታት በኋላ እንኳን ‹‹በሰላም እንዲያርፉ›› ብንተዋቸውስ?!
Filed in: Amharic