>

ኢትዮጵያዊነት ጨፍላቂነት ነውን? (ሰይፉ ታሪኩ)

ኢትዮጵያዊነት ጨፍላቂነት ነውን?

ሰይፉ ታሪኩ


ሩሲያዊው አሳሽ አሌክሳንደር ቡላቶቪች ‹‹ከአጼ ምኒልክ ሠራዊት ጋር›› በተሰኘው የ1892 ዓ.ም መጽሓፉ በወቅቱ የነበረው የኢትዮጵያን ግዛት ዳግም የመመለስ (Reunification) ዘመቻን አብሮ በመሳተፍ የደረሰበት ድምዳሜ ኢትዮጵያዊ ማንነት ለሳላድ ቦውል ኀልዮት (Salad Bowl theory) የቀረበ፣ ከሁሉም የተውጣጣ የጋራ ማንነት የመፍጠር እንጂ አንዱን በአንዱ የመጨፍለቅ አለመሆኑን፤ የኢትዮጵያዊያን(ሀበሾች) ባህልም እንዳልሆነ በሚከተለው አጭር አንቀጽ አረጋግጧል፡፡

‹‹ኢትዮጵያዊን ቀስ በቀስ የተቀበሏቸው የአውሮፓ ሥልጣኔዎች አልጎዷቸውም፡፡ ኢትዮጵያ ከነዚህ ሥልጣኔዎች ጠቃሚ ነገሮችን ወርሳ በበኩሏ የጎረቤት ጎሳዎችን ድል እያደረገችና ወደ ግዛቷም እያዋሀደች የራሷን ባህል በመሃላቸው ስታስፋፋ አንድም ጎሳ ከምድረ ገጽ ያላጠፋች ከመሆኗም ሌላ ሁሉም ግላዊ ባህሪያቸውን ጠብቀው እንዲቆዩ ዕድል ሰጥታለች››

ይህ የቦላቶቪች ድምዳሜ መሰረቱን ያደረገው በወቅቱ አውሮፓውያን በምን ያህል ዕቅድና ትግበራ የአፍሪካውያንን ማንነትና ባህል በማጥፋት ላይ የተመሰረተ ቅኝ የመመስረት ፍላጎት እንደነበራቸው የአሜሪካና የህንዶች ጨርሶ የመጥፋት አመክንዮን እንደ አባሪ በማንሳት ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን አንዳችን በአንዳችን ውስጥ ተሳስረን የምንኖር ፤ ባህላችን የተቀየጠ ፤ የኑሮ ይትበሃላችን የተዛነቀ መሆኑ የጋራ ሀገር ይዞ ለመቀጠል ከየትኛውም ሐገር ያላነሰ በጎ ዕድል የተቸርን ህዝቦች ስለመሆናችንም ቡላቶቪች ይጠቅሳል፡፡ ለኢትዮጵያውያን ቋንቋ ዘለል የሆነ የወል ማንነትን ማዳበርና በዚያ ጠለልም ሥር መኖርም እንግዳ አለመሆኑን የሚጠቅሱ ሌሎች ምሁራንም አልጠፉም፡፡

ዶ/ር ሀሰን አዳል መሐመድ በ2009 ዓ.ም ባሳተሙት ‹‹ቋንቋ እና ብሔርተኝነት›› በተባለው መጽሓፋቸው ደጋግመው የሚያነሱትም ይህንኑ ሀቅ ነው፡፡ እንደርሳቸው አመለካከት “ወሎዬነት” በቋንቋ ልዩነት ያልተገደበ የአምስት ማኅበረሰቦች የወል ማንነት ነው፡፡ አማርኛ፣ አገውኛ፣ አሮምኛ፣ አፋርኛና ራይኛ ተናጋሪ የወሎ ሕዝብ ልሣነ ብዙሓነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ራሱን እንደ ወሎዬ የሚገልጽና የሚኮራ መሆኑ ከቋንቋና ከባህል ልዩነት ከፍ ያለ የጋራ ሠፊ ማንነትን ማዳብር ፤ በኢትዮጵያ ልማድ ውስጥ ለጨፍላቂነት የሚጠጋ ዳራዊ ትርጉም እንደሌለው አስረጂ አድርገው ይናገራሉ፡፡ የኢትጵያዊ ብሔርተኝነት የከፍታው ልኬትም በቋንቋ ልዩነት አጥር አበጅቶ ከተወሰነ (Specific) ማኅበረሰብ ጥቅም የተሻገረ ለሁለም ዜጋ በእኩል የመታገል ፣ የኢትዮጵያ የሆነ ሁሉ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ይዞታ የሚሆንበትን አግባብ የሚያመቻች ርዕይ ነው፡፡ ‹‹ቀልቀሎ ስልቻ ፤ ስልቻ ቀልቀሎ›› በማለት የጋራ ማንነትን በምሳሌያዊ አነጋገር እያዛነቁ መገንባትን ገንዘቡ ባደረገ ሕዝብ ኢትዮጵያዊነት የወል ማንነት እንጂ ማንም በማን የመጨፍለቅያ (Assimilation) መድረክ አልነበረም ፤ አይሆንምም፡፡

Filed in: Amharic