>
5:09 pm - Saturday March 2, 5782

የሀገር አልባነትን ፖለቲካ...!!! (ሰይፉ ታሪኩ)

የሀገር አልባነትን ፖለቲካ…!!!

ሰይፉ ታሪኩ


ሀገር አልባነት(Homelessness) ሠፊ ብያኔን የተጎናጸፈ ንባበቃል ነው፡፡ ቃሉ እንደሀገራቱ ተጨባጭ እውነታ የሚሰጠው ትርጉም የተለያየ ቢኾንም ከተከታዮቹ ሦስት የትርጓሜ ቅንፎች አይርቅም፡፡ የመጀመሪያው ሀገር አልባ(ቤት አልባ)ነት የሚኖሩበት የገዛ መኖሪያ አጥተው በየጎዳናው፣ በየመንገዱ ውሎና አዳራቸውን ያደረጉ ዜጎችን ለመግለጽ ጥቅም ላይ የሚውል ነው፡፡ ኹለተኛው ደግሞ የራሴ የሚሉት መኖሪያ ስለሌላቸው በተለያዩ ጊዜያዊ መጠለያዎችና በየሰው ቤት በጥገኝነት የሚኖሩ ዜጎችን እውነታ ለመጠቆም የሚያገለግል ነው፡፡ ሦስተኛው ግን ከኹለቱ ብየናዎች ለየት ባለ መልኩ የኔ የሚሉትን በተለያየ ምክንያት አጥተው ሠላምና ደህንነታቸው ዋስትና በሌለው ሁኔታ ላይ የወደቁ ዜጎችን የሚገልጽ ነው፡፡ ሀገር አልባነት በእነኚህ ሦስት የትርጉም ማዕቀፎች ውስጥ መብራራት ቢችልም በዘውግ ፖለቲካ ዕሳቤ ውስጥ ግን ከቤትና መኖሪያ ማጣት የተሻገረ ልዩ ጽንሠሃሳብ ኾኖ ይገኛል፡፡
ጆይ ሞሰስ የተባለ ጸሐፊ በነጮቹ 2019 “New Data on Race, Ethnicity and Homelessness” በተባለ ዘገባው በአሜሪካ ጥቁሮች እና የላቲን ዝርያ ያላቸው ዜጎች የገጠማቸውን የከፋ ሀገር አልባነት በዳታ ያስረዳል፡፡ ዓቢይ በሚባሉ የሥራ መስኮች ላይ ያላቸውን ሚናና ሓላፊነት በማንሳትም ኢ-ፍትሓዊ የቤት እጦት ላይ ለመውደቅ መገደዳቸውን ሳይደብቅ ያትታል፡፡ በአንጻራዊነት ነጭ አሜሪካዊያንና ትውልደ ኤሲያዊያን የቤት ባለቤት የኾኑበት እውነታ እንዳለም ይጠቁማል፡፡ ይኽ የሞሰስ ዘገባ በዘውግ ፖለቲካ አንብሮ ውስጥ የተለያየ ትርጉም ሊኖረው የሚችል ነው፡፡ በዘገባው በተጨባጭ መረጃ እንደተገለጸው ጥቁሮች ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር በያዙባቸው እና ሠራተኛ በኾኑባቸው ሥፍራዎች የቤት ባለቤትነታቸው አናሳ ነው፡፡
አሜሪካ የዜጎችን እኩልነት በማረጋገጥ ረገድ ከሕግና መዋቅር መስተካከል አኳያ ብዙ ትችት አይነሳባትም፡፡ “ጥቁሮች አንድ ሦስተኛ ሰውነትን አያሟሉም” ከሚለው ሕገመንግሥቷ ተነስታ ጥቁርን ፕሬዚዳንት እስከማድረግ የደረሰ የዐይነት ለውጥ አድርጋለች፡፡ በዚህ ተራማጅነቷና ሥልጡንነቷ የቱንም ያህል መወድስ ቢዘንብላትም የሕዝቧ ማኅበራዊ ሥነልቦና(Social Psychology) ጥቁሮችን እንደዜጋ መቀበል ላይ በየዘመኑ ሳንካ ሲገጥመው ተስተውሏል፡፡ ይኽ ደግሞ በዋናነት በዘውግ ፖለቲካ ዕሳቤ ውስጥ “የሀገሩ ቀዳሚ (ዋና) ባለቤት እኛ ነን” ከሚል የተንሸዋረረ እይታ እንደሚመነጭ አያጠራጥርም፡፡ አያሌ ምዕራባዊያን ከማይታሙበት ዴሞክራሲያዊ ባሕል ጎን ነጥረው የሚታዩባቸው እነኚህ ቀለምን ማዕከል ያደረጉ መግፋቶች (Isolation) እንደ አፍሪካ ባሉ አሕጉራት ደግሞ ማንነትን፣ ሃይማኖትንና ጎሰኝነትን ምክንያት አድርገው የከፋ ግጭትና ደም መፋሰስን ሲወልዱ ታይቷል፡፡

ኢትዮጵያ አሁናዊ ምሳሌ
የአውሮፓውያን ቅኝ አገዛዝ ዘመን ማክተምን ተከትሎ በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ጎሳና ሃይማኖትን ማዕከል አድርገው የተሰሩት የጥላቻ ግንቦች ለበርካታ የእርስ በርስ ቁርቁሶችና ግጭቶች ምክንያት ኾነው ቆይተዋል፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ በኩል ሜዳውን የተቀላቀለችው እጅግ ዘግይታ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ለዚህ ዐቢይ ምክንያቱ ደግሞ ቅኝ ገዢዎች በሌሎች የአሕጉሪቱ ሀገሮች ላይ የፈጸሙትን ሴራ ኢትዮጵያም ላይ ለመድገም ዕድል በመነፈጋቸው ነበር፡፡ ፕሮጄክታቸው ዓድዋ ላይ በተባበረ ከንድ መመታቱና ኢትዮጵያም የውስጥ ነጻነቷን አስጠብቃ መቆየቷ በቅኝ ገዢዎቹ ዘንድ አዲስ መላ እንዲፈለግላት አስገድዷል፡፡ በዚህም የትምህርት ፖሊሲን፣ ስኮላርሺፕን፣ ቴክኖሎጂንና መሠል ዘዴዎችን በመጠቀም የሰውና የሀብት ኪሳራቸውን በቀነሰ መንገድ የክፍለዘመናት ሕልማቸውን ለማሳካት ሞክረዋል፡፡
ለዘመናት በኢትዮጵያዊያን መካከል የተገነባውን የአንድነትና የውሕደት ታሪክ ወደጎን በሚገፋ ተረክ ላይ የተወለደው የመገፋፈት ፖለቲካ “ጨቋኝ” እና “ተጨቋኝ” ተበጅቶለት የመጠፋፋት ነጋሪት ሲጎሰምም የግጭቶቹ ባለቤቶች (entrepreneurs) የትምህርትም ይኹን የኑሮ ዳራ ከፍ ተብለው ከተጠቀሱት ኃይሎች የራቀ አልነበረም፡፡ ይኽ ዘመን ዘመንን እየወለደ እኩይ ሃሳቡ ከተራ መታገያነት ወደ መዋቅርነት ፤ ከአስተሳሰብ ወደ ገዢ ሕገመንግሥትነት ተሻግሮ “መጤ” እና “ሰፋሪ” የሚሉ ድምጾች በርክተው በኢትዮጵያ የሀገር አልባነት ፖለቲካ መሠረት እንዲይዝ አድርጎታል ማለት ይቻላል፡፡

ማሳያዎቹ ምንድናቸው?
በኢትዮጵያ የዜጎች ሀገር አልባነት ከጊዜ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ ምስክር አያሻውም፡፡ እነኚህ ሀገር አልባ እንዲኾኑ የተፈረደባቸው ኢትዮጵያዊያን ዜጎች የቱንም ያህል ሀገራቸው ኢትዮጵያ፣ እነርሱም ኢትዮጵያዊያን እንደኾኑ ቢያምኑም፣ ይኽ ዕምነታቸው ሀጢያት ኾኖባቸው ከመሳደድ ግን አልዳኑም፡፡ ያለፈውን ሃምሳ ዓመት በጥቅል፣ የቅርቦቹን ሠላሳ ዓመታት ደግሞ በተለይ በአትኩሮት መመልከት ከቻልን የመዓቱ ሰለባ የሚኾኑትን ወገኖች በአራት ምድብ ውስጥ ወድቀው እናገኛቸዋለን፡፡ እነርሱም፡-
ሀ) ብዙኃን የከተማ ተወላጆች (The majority of urban dwellers)
ለ) ቅይጥ ማንነት ያላቸው ዜጎች (Citizens of mixed identity)
ሐ) ሕዳጣን ማኅበረሰቦች (minorities communities) እና
መ) “ኢትዮጵያዊ ነን” የሚሉ ዜጎች ናቸው፡፡
በቀዳሚነት የተቀመጡት “ብዙኃን የከተማ ተወላጆች” በኢትዮጵያ የዛሬ እውነታ ውስጥ በሀገር አልባነት ረገድ ቀዳሚ ሰልፈኞች ናቸው፡፡ እነኚህ በተለይም ከአዲስ አበባ ጀምሮ በስተደቡብ፣ ምዕራብና ምሥራቅ ከተሞች ውስጥ በስፋት የሚኖሩ ዜጎች እውነታ ፈረንጆቹ “Cosmopolitan” የሚሉት ዐይነት ነው፡፡ ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር፣ የሥራና የትምህርት ቋንቋቸውን የመወሰንና ወዘተ… መብት ሊጎናጸፉ የሚገባ ቢኾንም ከሀገር ባለቤትነት ተቀንሰው በጥገኝነት እንዲኖሩ ተፈርዶባቸዋል፡፡ ኹለተኛዎቹ “ቅይጥ ማንነት ያላቸው ዜጎች” ደግሞ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል በሕዝቡ የዘመናት የውሕደት ታሪክ ውስጥ ተፈጥረው እየኖሩ የሚገኙ ዜጎች ናቸው፡፡ እነኚህ ዜጎች ከኹለት ወይም ከሦስት ማንነት ካላቸው ዜጎች መወለዳቸው ወንጀል ኾኖ ግን መሳደድ፣ መፈናቀልና መጠቃት ዕጣ ፈንታቸው የኾነበት አጋጣሚ ከበረከተ ሰንብቷል፡፡ “አንዱን ምረጡ” የሚል ማስገደጃም ሲከተላቸው የኖሩና አሁንም ያሉ ናቸው፡፡ “ሕዳጣን ማኅበረሰቦች” ስንል የጠራናቸው ሦስተኞቹ ወገኖች ደግሞ የራሳቸው ማንነት ያላቸው ቢኾኑም በተለያየ አካባቢ ተበታትነው በአነስተኛ ቁጥር የሚኖሩ ከመኾናቸው አኳያ በ”ሰፋሪነት” የሚጠቁ፣ በ”መጤ”ነት የሚፈናቀሉና የሚገደሉ ናቸው፡፡ ለዘመናት ያፈሩት ሀብት በእሳት የሚጋይባቸው፣ ሁልጊዜ ለመኖር ዋስትና አጥተው በስጋት ንፍቀክበብ ውስጥ የሚኖሩ ሀገር አልባዎች ናቸው፡፡
የመጨረሻዎቹ ሀገር አልባዎች ደግሞ የትኛም ንዑስ ማንነት ይኑራቸው ራሳቸውን ግን እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ የሚቆጥሩና “ኢትዮጵያዊ” ከሚለው ማንነት በላይ ገላጭ የለንም ብለው የሚያምኑ ናቸው፡፡ እነኚህ ወገኖች በሕገመንግሥቱ የተዘነጉ፣ በሀገሪቱ የሥልጣን መዋቅርም ቢኾን የማይታወቁ በመኾናቸው በሀገር አልባነት ፍዳቸውን ከሚያዩ ዜጎች ተርታ የሚሰለፉ ናቸው፡፡
እነኚህ ሁሉ የሀገር አልባነት ማሳያዎች እንደተጠበቁ ኾነው ታዲያ ቢያንስ እንደ ዜጋ ቢበዛ እንደ ሰው ልጅ የመኖር መብታቸው ጥያቄ ውስጥ የወደቀበት ልክ የለሽ እውነታ እንዴት ሊፈጠር ቻለ ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በዋነኝነት ሦስት ዐበይት ምክንያችን ማስቀመጥ የሚቻል ይመስላል፡፡ እነርሱም አብዛኛዎቹ ክልሎች የተዋቀሩበት መንገድ “ባለቤት” እና “መጤ” መቸንከሩ፣ ስሁት ትርክቶች ገዢ መኾቸው እና የመንግሥት የበዛ ዳተኛ መኾን ናቸው፡፡
“ባለቤት” እና “መጤ” ላይ የተቸነከረው የክልሎች አወቃቀር እንደሚታወቀው የአልባኒያው ኮሚኒስት ህወሓት ዐሥራ ሰባት ዓመታትን በጫካ ኖሮ ሀገርን በጉልበት ሲቆጣጠር የመጀመሪያ ሥራው ደደቢት ያረቀቀውን ሕገ አራዊት “ሕገ መንግሥት” አድርጎ ጥቅም ላይ ማዋል ነበር፡፡ በዚህም የይስሙላ “አሳታፊነት”ን ለማሳየት ሕገ መንግሥት አርቃቂ ኮሚቴ አቋቁሞ በአምስት የሽግግር ዓመታት የሕዝቡን አሰፋፈርና አኗኗር በማጥናት የአገዛዙን እድሜ ለማርዘም በሚያስችል መልኩ ቀደሞ የነደፈውን ረቂቅ ለማጠናከር ችሏል፡፡
ቀጥሎም ዜጋን ሳይኾን ቡድንን፣ ግለሰብን ሳይኾን ብሔርን የሚያውቀውን ሕገ መንግሥት አጽድቆ በሕዝብ ጫንቃ ላይ ጫነ፡፡ ሕገ መንግሥቱ የቋንቋ ነገድና የአቅጣጫ ስያሜን ተንተርሶ የተዋቀረ ከመኾኑም በላይ ለስደተኞች የሚሰጠውን የዜጎች ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ የመስራት፣ የመኖርና ሀብት የማፍራት መብት ለሀገር ባለቤቶቹ ኢትዮጵያዊያን ያከናነበ ሕገ መንግሥት ነው፡፡ ይህ ሕገ መንግሥት ሀገሪቱን ዘጠኝ ቦታ ሸንሽኖ ዜጎችን በቋንቋና ነገዳቸው በመመተር መሬት ብሔር እንዲኖረው በማድረግ ዜጎችን ሀገር አልባ አድርጓል፡፡
እንደ ሐረር፣ ድሬዳዋ፣ አዳማ(ናዝሬት)ና ደብረዘይት ያሉ አካባቢዎች ላይ ነዋሪውን በቋንቋ የሚሰፍረው ሕገ መንግሥት ገሸሽ ተደርጎ በከተሞቹ ብዙ ተናጋሪ ያለውን ቋንቋ የሚወክለውን ሕብረተሰብ ክፍል በማግለል ፖለቲካዊ ደባም ተሰርቷል፡፡ በድሬደዋ ከተማ አብዛኛው የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪ በኾነበት ሁኔታ ከተማውን የማስተዳደር ፖለቲካዊ ሥልጣን የተሰጠው ለኦሮምኛና ሶማሌኛ ተናጋሪ ብቻ መኾኑ የ40/40/20 ፖሊሲ ማረጋገጫ ነው፡፡ በሐረር አብዝኃው የማሕበረሰብ ክፍል አማርኛ ተናጋሪ ኾኖ ሳለ የአስተዳደር መብቱ የተሠጠው ሙሉ ለሙሉ በወቅቱ በነበረው እስታቲክስስ ሰላሳ ሺህ ለሚኾነው ሀደሬ ማኅበረሰብ ብቻ ነው፡፡ በአዳማ(ናዝሬት) ከስልሳ ዘጠኝ ፐርሰንት በላይ የሚኾነው ሕዝብ አማርኛ ተናጋሪ ሲኾን የአስተዳደር ሥልጣኑ ግን ለኦሮምኛ ለሚናገር ብቻ የተፈቀደ ነው፡፡
በሌላ በኩል እንደ ቤንሻንጉል ያሉ ክልሎች ብዙኃኑን የሕዝብ ክፍል ያገለለ የክልል አወቃቀር እንዲከተል በመደረጉ ዜጎች በየጊዜው የሚገደሉበትና የሚሰቃዩበት የሞት ቀጠና ሊኾን ችሏል፡፡ በአጠቃላይ ሕገ መንግሥቱን መሠረት ተደርገው የተዋቀሩት ክልሎች በውስጣቸው ለሚኖሩ ዜጎች እውቅና መንፈጋቸው ግለሰቦችን የግፍና የሰቆቃ ሰለባ እንዲኾኑ አድርጎቸዋል፡፡ ክልሎች ሲወቀሩ የነበረው የአከላለል ሥርዓትም አንዱ የችግር ምንጭ ነበር፡፡ ለምሳሌ በአማራና በትግራይ(ወልቃይት ራያ)፣ በኦሮሚያና በአማራ(ደራ)፣ በደቡብና በኦሮሚያ(ጉጂ ገዲዮ)፣ በአፋርና በሱማሌ፣ በሶማሌና በኦሮሚያ(ሞያሌ)፣ በአማራና በቤኒሻል ጉሙዝ(መተከል) አዋሳኝ የተከሰቱ ግጭቶች ሕገ መንግሥቱ የወለዳቸውና ከማንነት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ በዚህም ዛሬ ላይ የወልቃይት ፣የራያ እና መሰል ጥያቄዎች ያለ ጦርነትና ትርምስ የሚፈቱ እስከማይመስሉ ድረስ ውጥረት እንዲነግስባቸው አስገድዷል፡፡

ስሁት ትርክቶች ገዢ መኾን
በኢትዮጵያ የሃገረ መንግሥት ታሪክ ውስጥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክርስቲያን ግዙፍ ሚና እንንደነበራት የሚታወቅ ነው፡፡ ኾኖም ከሰባና ሰማንያ ዓመታት በፊት ኃያላኑ አውሮፓውያን አፍሪካን በቅኝ ሲቀራመቱ ለኢትዮጵያ ካስቀመጡት ፖሊሲ አንዱ ቤተ ክህነትን ማዳከም ነበር፡፡ የዚህ ሀሳባቸው መነሻም የሀገሪቱ የመንግሥትነት ምንጭ ከቤተ ክርስቲያን ይቀዳ ስለነበር መኾኑ አያጠያይቅም፡፡ ዛሬ ላይ ደግሞ ቤተክርስቲያን ቀደም ሲል ይደርስባት ከነበረው ጥቃትና መደፈር በዘለለ መልኩ የተለየ የጥቃት ዒላማ ኾናለች፡፡ ለምሳሌ ከዕምነቱ ተከታይ ውጭ ያሉ ዜጎችና አክቲቪስቶች የተለያዩ ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ከመንግሥት ምላሽ ሲነፈጋቸው ቤተክርስቲያንን ማንደድ አንዱ የመታገያ መንገዳቸው እየኾነ መጥቷል፡፡ ይህን ለማየት ደግሞ የጅጅጋውን፣ የሻሸመኔውን፣ የአርሲውን፣ የሲዳማውን በምዕመኑና ቤተክርስቲያን ላይ የደረሰው ቃጠሎና አሰቃቂ ግድያ መታዘብ በቂ ነው፡፡ በዚህም በርካታ አማንያን በሃይማኖታቸው ምክንያት ሀገር አልባ ሊኾኑ ችለዋል፡፡
ዘመናትን የዋጀችው ቤተክርስቲያንም ሰላምና ፍቅርን በሚሰብከው አስተምህሮዋ ምክንያት ተሳዳጅና ተጠቂ ለመኾን ተገዳለች፡፡ የማሳደድ ሴራው ቤተክርስቲያንን በማቃጠል፣ አማንያንን በመግደል፣ በማፈናቀልና በማሰቃየት ብቻ የተገደበ ሳይኾን በመከፋፈል ላይም የተመሠረተ ነው፡፡ ለምሳሌ ጥቂት የመንግሥት ባለሥልጣናት በየቢሯቸው ቤተክርስቲያኒቱ “የቋንቋ ብዙኃነትን አታስተናግድም” በሚል ጥራዛዊ ፍረጃ ሃይማኖት ሲያበጁ መታየታቸው የአደባባይ ሀቅ ነው፡፡
በተለይም ዛሬ ላይ ቀደም ባለው ጊዜ ሥርዓት አምልኮዋን ትፈፅምባቸው የነበሩ ይዞታዎቿ ሳይቀሩ መነጠቃቸው ፖለቲካዊ ወገንተኝነት የፈጠረው ሀገር አልባ የማድረግ ግብ እንደሆነ አያጠራጥርም፡፡ ይኽ ሀሰተኛ ትርክት ገዢ ኾኖ ሃይማኖትንና አማኒያንን ሀገር አልባ የማድረግ እንቅስቃሴ በብዙ መልኩ የኢትዮጵያን ሕልውና ቅርቃር ውስጥ ለመክተትና ለዘመናት ሲደገስ የነበረውን ኢትዮጵያን የማፍረስ ትልም ወደጫፍ ለማምጣት ከሚፈለግባቸው መንገዶች አንዱ ኾኖ ቀጥሏል፡፡
የመንግሥት ዳተኝነቶች
ከፍ ሲል የዘረዘርናቸው ቀውሶችና ጥፋቶች በሀገር ላይ እንዲከሰቱ ቀደም ሲል በመንግሥትነት ተሰይሞ የነበረው ቡድን ምክንያት መኾኑ አያወላዳም፡፡ ለሥልጣን ዕድሜው ሲል ዜጎችን በብሔርና በሃይማኖታቸው ማናከስን መደበኛ ሥራው አድርጎ የቆየው ይኽ አገዛዝ ከተገረሰሰ በኋላም ቢኾን በመንግሥትነት ዙፋኑን የያዘው ኃይል የዜጎች ሀገር አልባነት ውል አልባ በሚባል ደረጃ እንዲጨምር ሰበብ ከመኾን አላመለጠም፡፡ ያለፉትን ከኹለት ያለፉ ዓመታት በዜጎች ላይ ይደርሱ የነበሩ ራሮት-አልባ ጭፍጨፋዎች በብዙ መንገድ ከመንግሥት ዳተኝነት ጋር የሚያያዙ ነበሩ፡፡
የጥፋት ነጋሪቶች በሚዲያ ሲጎሰሙ፣ ትጥቅ ያነገቡ ኃይሎች “ክተት” ሲያውጁ፣ የመንግሥት የጸጥታ ኃይላት የወንጀሎች ተባባሪ ሲኾኑ መንግሥት ያሳየው ምንግዴነት አሰቃቂ የዜጎች ሞት እንዲሁም የከፋ የንብረት ውድመት እንዲከሰት መንገድ ጠርጓል፡፡ ጉዳዩን ይበልጥ አሳዛኝ የሚያደርገው ደግሞ አሁንም መንግሥት ከስህተቶቹ ተገቢውን ትምህርት ለመውሰድ አለመቻሉና የዜጎች ሀገር አልባነት መቀጠሉ ነው፡፡ ሰሞነኛው የመተከል ዞን ጭፍጨፋ ምን ያህል በየደረጃው ባለው አመራር እና የክልል ጸጥታ ኃይል ዘንድ ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ ዝግጅትም ይኹን ምክክር እንዳልተደረገ ጠቋሚ ነው፡፡


ሀገር አልባነትን በሀገር ባለቤትነት:-

የሀሳባችንን መቋጫ የምናደርገው የሀገር አልባ ዜጎችን ሰቆቃ ለማቆም ብቸኛውና ዋነኛው መፍትሔ ዜጎችን በዜግነታቸው የሀገር ባለቤት ማድረግ ሲቻል ነው የሚል ምክረ ሃሳብ በማስቀመጥ ነው፡፡ የዜጎችን ዋይታና ለቅሶ ለማስቆም ያለው የማርያም መንገድም ይኼው ብቻ መኾኑን አስረግጦ መንገር ዛሬም ኢትዮጵያ እንድትድን የሚሹ ወገኖች ድምጽ መኾን አለበት፡፡ በዘውግ ሥነአዕምሮ(Mentality) የታጠረ የአካባቢም ይኹን የክልል ባለቤትነት ዕልቂትን፣ መጠፋፋትንና ብተናን ከመጋበዝ ውጪ የሚያመጣው በጎ ነገር እንደሌለ አሁንም ጎላ አድርጎ መናገር ይገባል፡፡ በርግጥም የደም ዋጋ እየተከፈለበትም ቢኾን የዕሳቤው ጠንቀኝነት ቢያንስ ባለፉት ኹለት ዓመታት ታይቷል፡፡ የዜግነት መብት የሀገሩ ሕግ መጀመሪያም መጨረሻም እንዲኾን ሲጠየቅም ከከፈልነው አስከፊ መስዋዕትነት በላይ ዳግም መክፈል ስለማይገባን መኾኑን ለሁሉም ማሳወቅ ይገባል፡

Filed in: Amharic