ኦሮምኛ የተስፋፋበት የገዳ ሥርዓት የቋንቋ ፖሊሲና አማርኛን አስፋፋ በተባለው የኢትዮጵያ ነገሥታት የቋንቋ ፖሊሲ መካከል ያለው ግልጽ ልዩነት ሲመረመር!
አቻምየለህ ታምሩ
ዛሬ አማርኛ ተጭኖበታል እየተባለ በስሙ የሚነገድበት ኦሮምኛ ተናጋሪ የሆነው ሕዝብ ከዘጠና በመቶ በላዩ የኦሮሞ የገዢ መደብ የሆነው ሉባ ባሕልና ቋንቋ በግድ ሳይጫንበት በኢትዮጵያ ፊደል የሚጽፍ፣ በግዕዝ የሚቀድስ፣ በዐረቢኛ ዱአ ያደርግ የነበረውን ክርስቲያንና ሙስሊም የነበረ ሕዝብ ነው። ይህ ሕዝብ ኦሮምኛ ተናጋሪ እንዲሆን የተገደደው «ኦሮምኛ የሚናገር “ቢርመዱዳ እንጡቂና” ኦሮምኛ የማይናገር “ዲና በሌሣ”» የሚል የቋንቋ ፖሊሲ ሲያራምድ በነበረው የኦሮሞ ገዢ መደብ በግዳጅ ኦሮምኛ እንዲናገር ተጭኖበት ነው። «ኦሮምኛ የሚናገር “ቢርመዱዳ እንጡቂና” ኦሮምኛ የማይናገር “ዲና በሌሣ”» የሚለው የገዳ ሥርዓት የቋንቋ ፖሊሲ ትርጉም «ኦሮምኛ የሚናገር ወገናችን ነው ይገብር፤ ኦሮምኛ የማይናገር ጠላታችን ነው ይጥፋ”» እንደ ማለት ነው። ይህ የአባገዳ የቋንቋ ፖሊሲ ኦሮምኛ ከሚናገረው ማኅበረሰብ ውጭ ያለውን ከሀያ ስምንት በላይ የኢትዮጵያ ነገዶች ቋንቋ በተሳካ ሁኔታ ያጠፋ የቋንቋ ፖሊሲ ነው።
ከገዳ ሥርዓት የቋንቋ ፖሊሲ በተቃራኒ የነበረው የኢትዮጵያ ነገሥታት ዘመናዊ ኢትዮጵያ ታሪክ ከጀመረበት ከዐፄ ቴዎድሮስ በኋላ በተለይም ከዐፄ ዮሐንስ ዘመነ መንግሥት ጀመሮ የነበራቸው ብሔራዊ የቋንቋ ፖሊሲ ቋንቋ የሚያጠፋ ሳይሆን ኢትዮጵያውያን አፋቸውን ከፈቱበት ቋንቋ በተጨማሪ ከዳር እስከ ዳር የሚግባቡበትን አማርኛን በተደራቢነት እንዲማሩ የሚያደርግ፣ የተለያዩ የኢትዮጵያ ነገዶች የነበራቸውን ቋንቋ የሚያጠፋ ሳይሆን በነበራቸው ቋንቋ ለይ የሚጨምር ስርዓት ነበር።
በሁለቱ የቋንቋ ፖሊሲዎች መካከል ያለው ልዩነት የሰማይና የምድር ያህል ነው። አንዱና ዋናው ልዩነት የገዳ ሥርዓት የቋንቋ ፖሊሲብ የአንድን ነገድ ማንነት፣ ቋንቋና ባሕል የሚያጠፋ ሲሆን የኢትዮጵያ ነገሥታት የቋንቋ ፖሊሲ ግን በአንድን ነገድ ማንነት፣ ቋንቋና ባሕል ላይ ጭማሪ የሚያደርግ ነው።
ሁለተኛው ልዩነት በገዳ ሥርዓት የቋንቋ ፖሊሲ አንድ ሰው የራሱን ቋንቋና ባሕል ትቶ ኦሮምኛ ብቻ ለመናገር ካልፈቀደ ያለው እድል አንድ ብቻ ነው፤ መገደል። ባሕሉንና ቋንቋውን ትቶ ኦሮምኛ መናገር ቢፈቅድ እንኳ ገርባ እንጂ ባለ ርስት ባለ መሬት አይሆንም። ይህ ብቻ ሳይሆን የአመጋገብ ሥርዓቱም ይለያል። ገርባ እንደ ኦሮሞ ጥሩ ምግብ መብላት አይፈቀድለትም። ኢኔሪኮ ቸሩሊ «Folk-literature of the Galla of Southern Abyssinia» በሚለው ጥናቱ እንደነገረን በበአል ጊዜ ለኦሮሞው ጠቦት ወይም ኮርማ ሲታረድለት ለገርባው ግን ይታረድለት የነበረው ያረጀችና የነጠፈች ላም ተፈልጋ ነው። የኮርማ ስጋ የበላ ገርባ ቢኖር ይታረዳል።
በገዳ ሥርዓት የቋንቋ ፖሊሲ ቋንቋውን እንዲያጣ የተደረገ ገርባ መብት የለውም ብቻ ሳይሆን፣ ባለቤቱ በፈለገው ጊዜ የሚሸጠውም እቃ ነው። ሰው ያለባሕሉ፣ ያለአባቱ፣ ያለ ቋንቋው ምሉዕ አይደለም። አካል ነው፤ ስጋ ነው። የኦሮሞ አባገዳዎች «ኦሮምኛ የሚናገር “ቢርመዱዳ እንጡቂና” ኦሮምኛ የማይናገር “ዲና በሌሣ”» በሚለው የቋንቋ ፖሊሲያቸው የሰውን ማንነት ሲያጠፉ አካሉን እንጂ ሰውነቱን አልፈለጉም። ሰው ስጋው ብቻ ከቀረ ከጋማ ከብቶቻቸው አንዱ ይሆናል።
አባገዳዎች ሲስፋፉ ሰውን ለጦርነት ሲማግዱና በባርያ ንግድ ሸቀጥ አድርገውት የኖሩት እንዲህ አድርገው አዋርደውት ነው። ከኢትዮጵያ ኤክስፖርት የሚደረጉ ባሪያዎች ኦሮምኛ ተናጋሪ የነበሩበትም ምክንያት ይህ ነው። የአባገዳዎች ጭካኔ የገርባቸውን ልጆች ነጥቀው በሞጋሳ ቤታቸው ውስጥ ካሳደጓቸው በኋላ ጭቡ አድርጎ እስከመሰጥ ድረስ ነው።
በኢትዮጵያ መንግሥታት የቋንቋ ፖሊሲ እንደዚይ አይነት ሰውን የሚያዋርድ ጭካኔ ኖሮበት አያውቅም። የኢትዮጵያ ነገሥታት የቋንቋ ፖሊሲ ኢትዮጵያውያን በተደራቢነት እየተናገሩ በጋራ ይግባቡበት የነበረውን ቋንቋ ብሔራዊ ቋንቋ አድርጎ የዘረጋና ኢትዮጵያውያን ተምረውት በተደራቢነት እንዲናገሩትና እንዲገለገሉበት ያደረገ እንጂ የአፍ መፍቻ ቋንቋን በመደምሰስ አንድ ቋንቋ ብቻ እንዲናገሩ የሚያስገድድ፣ የሰውነት ደረጃ የሚወጣና ቋንቋ የመለያ መሳሪያ የሚያደርግ አይደለም።
ባጭሩ በገዳ ሥርዓት የቋንቋ ፖሊሲና አማርኛን አስፋፋ በሚባለው የኢትዮጵያ ነገሥታት የቋንቋ ፖሊሲ መካከል ያለው ትልቅ ነው። በገዳ ሥርዓት የቋንቋ ፖሊሲ ኦሮምኛ የተስፋፋው ኦሮምኛ የማይናገረውን ማኅበረሰብ ባሕል፣ማንነትና ቋንቋ በተሳካ ሁኔታ አጥፍቶ ሲሆን አማርኛ ግን የተስፋፋው አማርኛ በማይናግረው ማኅበረሰብ ባሕል፣ማንነትና ቋንቋ ላይ ጭማሪ ሆኖ ነው።
አባ ገዳዎች «ኦሮምኛ የሚናገር “ቢርመዱዳ እንጡቂና” ኦሮምኛ የማይናገር “ዲና በሌሣ”» በሚለው የቋንቋ ፖሊሲያቸው እየተመሩ ቋንቋና ባሕላቸውን ላጠፉባቸው፣ መሬታቸውን ነጥቀው ገርባ ላደረጓቸው፣ ባሪያ አደርገው ለሸጧቸው ከሀያ በላይ የኢትዮጵያ ነገዶች በይፋ ይቅርታ ሊጠይቁ ይገባል።