>
5:28 pm - Friday October 10, 5541

“እየደረሰ ያለው ጥቃት ‘የንፁሀን ህልፈት’ እየተባለ የሚሽሞነሞን ሳይሆን - የዘር ማጥፋት ወንጀል ነው...!!!"  (የህግ አማካሪ መርኃጽቅ መኮንን)

“እየደረሰ ያለው ጥቃት ‘የንፁሀን ህልፈት’ እየተባለ የሚሽሞነሞን ሳይሆን – የዘር ማጥፋት ወንጀል ነው…!!!” 
የህግ አማካሪ መርኃጽቅ መኮንን 
አዳሙ ሽባባው

ለዘመናት በተሰራው የተሳሳተ ትርክት ብሔርን መሰረት ያደረገው ጥቃት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በደቡብ እና በኦሮሚያ ክልሎች በሚኖሩ አማራዎች ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል እየተፈጸመባቸው ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ የህግ ማብራሪያ እንዲሰጡን  የህግ ጉዳዮች አማካሪ መርኃጽድቅ መኮንን ጋር አብመድ ቆይታ አድርጓል።
እንደ አቶ መርኃጽድቅ ማብራሪያ በቀደሙት ዘመናት የአማርኛ ተናጋሪው ሌላውን ማኅበረሰብ ተጭኖ እንደኖረ ተደርጎ በተሰበከው ጥላቻ ፅንፈኛ አካላት በተደራጀ መንገድ ብሔር ላይ ያነጣጠረ ጥቃት እያደረሱ ነው፡፡ የለውጥ ማሻሻያ እርምጃዎች ከተወሰዱ በኋላ  አማራውን ዒላማ ያደረገ ጭፍጨፋ መድረሱን የተናገሩት የህግ ጉዳዮች አማካሪው “ይህንን በድፍረት ለመናገር በመንግሥት አካላት ላይም ድፍረቱም የለንም፤ ከፍተኛ የሆነ የወንጀል ጥቃት እየደረሰ ነው፤ የተደራጀ ወንጀል እየተፈጸመ ነው፤ ድርጊቱን በስሙ የመጥራት ድፍረት ሊኖረን ይገባል” ብለዋል።
በቀደሙት ዘመናት ህወሀት እና ኦነግ አማራው ከስልጣን ገለል እንዲል፣ በኢኮኖሚ እንዲዳከም በሌላው ማኅበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ የጥላቻ ስብከት ለዘመናት ሲሰሩ መቆየታቸውን የህግ አማካሪው አስረድተዋል። የተከማቸው ጥላቻ ሙሉ በሙሉ እንዲወገድ የማይፈልጉ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ አሁንም ያሉ አካላት እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡ የመንግሥት መዋቅሩ ከቀበሌ እስከ ፌዴራል ያልተቀየረ በመሆኑ በአማራው ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት ማስቆምና በዘላቂነት ለመፍታት ውስብስብ እንዳደረገው ተናግረዋል። “የህግ አስከባሪ አካላት ራሳቸው ምን ያህል ከችግር የፀዱ ናቸው የሚለው ጉዳይም አነጋጋሪ ነው” ብለዋል አቶ መርኃፅድቅ፡፡
አማካሪው በማብራሪያቸው መንግሥት በዚህ አካሄድ ሙሉ አቅሙን ተጠቅሞ የህግ የበላይነትን እያስከበረ ነው ለማለት እንደማያስደፍር ጠቅሰዋል፡፡ አማካሪው መርኃጽድቅ መኮንን የመንግሥት ቀዳሚ ተግባር የኅብረተሰቡን ሠላም እና ደኅንነት ማስጠበቅ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ ዜጎች በየአካባቢው ያለውን የህግ የበላይነት ተማምነው በሠላማዊ መንገድ ሥራቸውን አከናውነው እንዲገቡ መንግሥት ቁልፍ ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
መንግስት ይህንን ኃላፊነት መወጣት ካልቻለ በሀገር ውስጥ እና በዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ዘንድ ተቀባይነትን እና ተአማኒነትን እንደሚያሳጣው ያብራሩት የሕግ አማካሪው መርኃጽድቅ የኢትዮጵያ ህገ መንግስት አንቀጽ 28 በስብእና ላይ ስለሚፈጸሙ ወንጀሎች አሁን እየሆነ ያለውን ብሔር ተኮር ጥቃት በከፍተኛ ወንጀል ደረጃ የሚፈርጅ እንደሆነም ተናግረዋል። አሁን እየተፈጸመ ያለውን ብሔር ተኮር ጥቃት የሀገሪቱን ህገ መንግስት እና የዓለም አቀፍ ህጎችን የጣሰ የዘር ማጥፋት ወንጀል ነው ሲሉም አስረድተዋል። ብሔርን መሰረት ተደርጎ እየደረሰ ያለው የዘር ማጥፋት ድርጊት ደግሞ በኢትዮጵያ እና በዓለም አቀፍ ሕጎች ይቅርታ እና ምህረት እንኳን የማያሰጥ ወንጀል እንደሆነ ማብራሪያ ሰጠዋል።
በተለይም ዜጎችን በማንነት፣ በብሔር፣ በሚናገሩት ቋንቋ እና ባህላቸውን አነጣጥሮ የጅምላ ወንጀል መፈጸም በሀገሪቱ የወንጀል መቅጫ ህግም ከ25 ዓመታት እስከ ፅኑ እስራት የሚያስቀጣ ለአብነት ጠቅሰዋል። አቶ መርኃጽድቅ መኮንን በኢትዮጵያ ሕገ መንግስት አንቀጽ ዘጠኝ ንዑስ አንቀጽ አራት ሥር እንደተደነገገው ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ሕጎችን የራሷ የሕግ አካል አድርጋ ስለተቀበለች አጥፊዎችን በዚህ ሕግ ልትጠይቅ እንደሚገባም ተናግረዋል። ኢትዮጵያ የዘር ማጥፋት ወንጀል ለመከላከል እና ለመፍታት በ1948 ዓ.ም በታኅሣሥ ወር ላይ የተደነገገው እና በተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባዔ ቁጥር 260/A3  የጸደቀውን ሕግን ተስማምታ መፈረሟንም ነግረውናል፡፡
የሕግ ምሁሩ በዚህ ስምምነት አንቀጽ 2 ሥር ደግሞ መግደል፣ ዘር ማጥፋት፣ ማደን፣ ማሳቀቅ፣ ዘር እንዲጠፋ ቅድመ ሁኔታዎችን ማስቀመጥ በዝርዝር እንደተደነገጉ አስረድተዋል። ድርጊቱን ማንም ይፈፅም ማን ኃላፊነቱን የሚወስደው በዚያ አካባቢ የሚገኘው የመንግስት አካል እንደሆነም አቶ መርኃጽድቅ መኮንን አስገንዝበዋል። በአካባቢው የሚገኝ የፀጥታ አካል፣ ደኅንነት፣ የመከላከያ ሰራዊት እና ወታደራዊ ሃይል እነዚህን ጥቃቶች መከላከል ካልቻለ የመንግሥትን እና የዜጎችን ህልውና መታደግ እንደማይችልም ለአብነት ጠቅሰዋል። አደገኝነቱ ለሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለመንግሥትም ጭምር መሆኑን በመጥቀስ። እናም በተደራጀ መንገድ መከላከል አስፈላጊ እንደሆነ አሳስበዋል፡፡
አቶ መርኃጽድቅ መኮንን እንዳሉት ሕዝቡ ለዘመናት አብሮ የሚኖር እና የማይነጣጠል በመሆኑ ጥቃት አድራሾችን በጋራ ሊከላከላቸው ይገባል፤ ጥቃት የሚደርስባቸው ዜጎች ቁጥር እየበዛ በመሆኑ የችግሩን ክብደት ማመን እና ሙሉ አቅምን በመጠቀም መቋጫ መፍትሔ መፈለግ እንደሚገባ የህግ አማካሪው ተናግረዋል። በተለይም በብሔር ፌዴራሊዝም ላይ የተመሰረተን ሕገ መንግሥት ጽንፈኞች ላልተገባ ጥቅም ሲያውሉት እየታየ በመሆኑ ሕገ መንግሥቱ እሰኪ ለወጥ ድረስ የክልል እና የፌዴራል መንግሥታት የዜጎችን ደኅንነት መጠበቅ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ መንግስት ደግሞ ያለምንም አድሎ ሁሉንም ዜጎች የመጠበቅ ግዴታ እንዳለበት በህገ መንግስት አንቀጽ 25 እና 32 ስለሚደነግግ ይህንን ኃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
Filed in: Amharic