>
5:18 pm - Tuesday June 15, 2128

የፈራነው ነገር መጣ ተመልሶ...!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

የፈራነው ነገር መጣ ተመልሶ…!!!

ያሬድ ሀይለማርያም

ጦርነት ክፉ ነገር ነው፤ በጀብደኝነት የሚፈጸም ነገር አይደለም። በተለይም እንደ እርስ በርስ ጦርነት አስከፊ ነገር የለም። አንደኛ ማቆሚያው አይታወቅም። ሁለተኛ ደግሞ ማዶና ማዶ ሆነው የሚገዳደሉት ወንድማማቾች ናቸው። ባለፉት አምሳ እና ስልሳ አመታት ውስጥ ኢትዮጵያ በማያባራ የእርስ በርስ ጦርነቶች በመቶሺ የሚቆጠሩ ልጆቿን ተነጥቃለች። ዛሬም ከታሪክ ባልተማሩ እና በውይይት የአገሪቱን ችግሮችን መፍታት ባልቻሉ ድኩማን ፖለቲከኞች ሌሎች ልጆቿን ልትነጠቅ የጦርነት አዋጅ ታውጇል። በዝርፊያ ገንዘብ፣ በመጠጥ እና በጫት ናላቸው የዞረ እና ለጸብ ሲቅበዘበዙ የነበሩ የህውሃት ሹመኞች የተመኙት የእርስ በርስ ጦርነትን ትላንት ማምሻውን ተለኩሶላቸዋል።
እንግዲህ ምንም አቅም እንደሌለው ሰው እና የሕዝብ አካል፤ የህውሃትን እድሜ አሳጥርልን፣ በግራም ሆነ በቀኝ የሚጠፋውን የሰው ህይወት እና የሚደርሰውን የጉዳት መጠን ቀንስልን፣ በተለይም ጦርነቱ በሚካሄድበት አካባቢ ያሉ የትግራይ ነዋሪዎችን ከከፋ አደጋ ጠብቅልን፣ አገር ለሚመሩት እና ግራ ለገባቸው የብልጽግና አመራሮችም ልቦና ስጥልን ብሎ ከመጸለይ ሌላ ምን ማድረግ ይቻላል? ይህ ጥቃት በህውሃት አመራሮች ላይ ብቻ ያነጣጠረ እና መቀሌ መሽገው አገር የሚያተራምሱትን የወያኔ ሹሞችና ጀሌዎች አንጠልጥሎ ለፍርድ በማቅረብ ላይ ያተኮረ፣ በአጭር ጊዜም ውስጥ የሚጠናቀቅ እንዲሆን እመኛለሁ። ኢትዮጵያ ሌላ የወንድማማቾች እልቂት የምታስተናግድበት ትከሻ የላትም። ድል ሰላም ለሚወዱ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ!
Filed in: Amharic