>
5:33 pm - Tuesday December 5, 6856

"መዘግየቱ ወይስ መዋጋቱ?" ( ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ)

“መዘግየቱ ወይስ መዋጋቱ?”

ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ

ትህነግ ከጦርነት በስተቀር ለመንግስት ምንም የሰላም መንገድ አልተወለትም፡፡ መንግስት መጠየቅ የሚገባው አሁን ወደ ጦርነት በመግባቱ ሳይሆን፣ እስከዛሬ በመዘግየቱ ነው፡፡ እነዚህ ማፍያዎች ከምስረታ ጀምሮ ከመግደል፣ ከመዝረፍና ከመዋጋት በስተቀር ታሪክ የላቸውም፡፡ የመንግስትነት ታሪካቸውም ቢሆን ከዚህ የራቀ አይደለም፡፡ በታሪካቸው አንድም በድርድር የፈቱት ችግር፣ ያሰፈኑት ሰላም የለም፡፡ አሰብን በድርድር ማስቀረት ሲቻል ለመደራደር ሳይፈቅዱ ሰጡት፡፡ ለድርድር አንዴ ቢቀመጡ ባድሜን አስረክበው መጡ፡፡
.
ጠቅላይ ሚንስትሩ የሚጠየቁት፣ ማፍያነታቸውን ከማንም በላይ እያወቁ፣ እድሜያቸው ያልደረሰ ህጻናትን ሳይቀር የሚያሰለጥኑበት፣ መሳሪያ የሚሰበስቡበት፣ ምሽግ የሚቆፍሩበት፣ ሰላዮቻቸውንና አሸባሪዎቻቸውን በመላው ሀገሪቱ የሚያሰማሩበት ጊዜ በመስጠታቸው፤ ሀገር እስኪያተራምሱና የንጹሀንን ደም እስከሚያፈሱ፣ በመጨረሻም የመከላከያ ሰራዊቱን እስከሚያጠቁ በመጠበቃቸው ነው፡፡
.
አንዳንዶች ‹‹ሰላም ከጦርነት አይገኝም፤ ሞት እንጂ›› ሲሉ እሰማለሁ፡፡ ይህ አባባል ሚዛናዊነት የጎደለው፣ ለትህነግ የሚሰጥ አይንአፋር ድጋፍ ነው፡፡ ላለፉት ሁለትና ሶስት አመታት በሀገሪቱ ጭራሽ አንድ ሰው ሞቶ የማያውቅ፣ ሞት የተጀመረው ትላንት ከጦርነቱ ጋር ይመስል፡፡ እስቲ 2013 ከገባ እንኳን የሞተውን እናስብ! እና ያለ ጦርነት እየቀበሩ መኖር ሰላም ነው?
.
ለማንኛውም ሰላም በሁለት መንገድ ሊገኝ ይችላል፤ ከድርድርና ከጦርነት፡፡ ጣርነት ለሰላም የሚከፈለው ከፍተኛ ዋጋ ነው፤ ህይወት ይጠፋል፣ ኢኮኖሚ ይወድማል፡፡ ከትህነግን ማፍያ መሪዎች ጋር በድርድር ሰላም ማምጣት እንደማይቻል ከእኛ በላይ እማኝ የለም፤ የሀይማኖት አባቶችና ሽማግሌዎች በተደጋጋሚ ተልኮባቸዋል፡፡ ሰላምን ከድርድር ለማግኘት መንግስት ያሳለፈውን ሁለት አመት፣ የተጠቀሙበት ጦር ለማሰልጠንና ሀገር ለማተራመስ ነው፡፡ ከልደታቸው ጀምሮ እዚህ ያደረሳቸውን፣ አሁንም እስከወንጀላቸው መሸሸጊያ የሆናቸውን የትግራይ ጭቁን ህዝብ ውለታ በምን እንደከፈሉት ለመገንዘግ፣ ከጉያው መንጭቀው ክላሽ ያሸከሟቸውን ህጻናት ማየት በቂ ነው፡፡
.
ይህን ጦርነት በተቻለ መጠን ሲቪሉን እየጠበቁ፣ ባነሰ ጥፋትና ባጭር ጊዜ በድል መወጣትና እነዚህን ለሀገርና ለህዝብ ደንታ የሌላቸው ማፍያዎች ሴራ ማምከን፣ የሀገራችንን የውስጥ ሰላም ለማምጣት መሰረታዊና የመጀመሪያ እርምጃ ነው፡፡
Filed in: Amharic