>
5:18 pm - Wednesday June 15, 2360

ነፃነትን የማያውቅ ነፃ አውጪን አልከተልም! አልደግፍም! (አሰፋ ሀይሉ)

ነፃነትን የማያውቅ ነፃ አውጪን አልከተልም! አልደግፍም!

አሰፋ ሀይሉ

ነፃነትን በጥሬ ጉልበት የሚያፍኑ፣ ነፃነትን ሊያመጡ አይችሉም! ነፃነትን የማያውቅ፣ ነፃ አውጪ ሊሆን አይችልም! ይህን እውነት ጠንቅቀን መረዳት አለብን! ይህ ለአፍታም መዘንጋት የሌለበት ትልቅ እውነት ነው! እስክንድር ነጋ በህይወቱ እና በነፃነቱ ታላቅ ዋጋ ከፍሎ የዋለልን ውለታ – በማስመሰል የተሸፋፈነውን የአብይ አህመድ አሊን እውነተኛ ማንነት ግልጥልጥ አድርጎ ለዓለም ማሳየቱ ነው! እስክንድር የታሠረው የዛሬውን ተረኛ አምባገነን እውነተኛ ምንነት ምንቅርቅር አድርጎ ለእኛ ለማሳየት ነው፡፡
ይህን እስክንድር በአደባባይ ነፃነቱን ከፍሎ ያሳየንን እውነት ለማየት ዓይናቸውን የሚጨፍኑ – የዓይን ብቻ ሳይሆን የህሊናም እውሮች ናቸው! ከአምባገነን ጎን አልሰለፍም! አምባገነንን በቻልኩት ሁሉ መንገድ እዋጋለሁ! ከአንዱ አምባገነን ጋር ተሰልፎ፣ ሌላውን አምባገነን መውጋት ነጻነትን አያመጣም! ነፃነትን የማያውቁ ነፃ አውጪዎች ይህ እንደ እስክንድር ነጋ ያሉ የነፃነት ታጋዮች መስዋዕትነት ከፍለው የሚያስተላልፉት የተግባር እውነት አይታያቸውም! እውነትን አናይም ብለው ለአሳሪ አምባገነን የወገኑ፣  ከእውነት ፀር ጋር አብረው ተሰልፈው እውነትን የሚያፋልጉ ነሆለሎች ከእንቅልፋቸው እስኪነቁ፣ እኛ ከእውነት እና ከእውነት ጋር ብቻ እንቆማለን!
ነፃነትን ያፈነ፣ ነፃነትን ሊያመጣ አይችልም! ከአይጥ ጉድጓድ ቁና ጥሬ፣ ከአንበሣ መንጋጋ ሙዳ ሥጋ፣ ከነፃነት አፋኝ ቅንጣት ነፃነት ሊገኝ አይችልም!
አስመሳዩ አብይ አህመድ አሊ፡-  የነፃነት አንደበት በመሆኑ እስርቤት የጣልከውን እስክንድር ነጋን ፍታ!
ABIY AHMED ALI: RESPECT HUMANRIGHTS FIRST! FREE ESKINDER NEGA NOW!
ነፃነትን የማያውቅ ነፃ አውጪን አልከተልም! አልደግፍም!
ድል ለነፃነት ሰማዕቱ ለእስክንድር ነጋ! እና ለሌሎችም ስለታፈነች ነፃነት በመቆማቸው በግፍ በእስር ለሚማቅቁ እውነተኛ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች!
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!
ኢትዮጵያ በነፃነት ለዘለዓለም ትኑር!
Filed in: Amharic