>

የወዲ አፈወርቂ ነገር ... (ታምራት ነገራ)

የወዲ አፈወርቂ ነገራ …

ታምራት ነገር

*  …ኢሳያስን የፈለገ ብትጠሉት በንቀት የምትገጥሙት ባላንጣም ፣ ምንም አያመጣም ብላችሁም የምታቅፉት ወዳጅም አይደለም። የአንድን አዳኝ ችሎታ ለማወቅ ከፈለጋችሁ ግዳዮቹን ማየት ብቻ በቂ ነው
*     *     *
 
ስለ ኢሳያስ አፈወርቂ እኩይነት ሰው ባይመሰክር ሳር ቅጠሉ መናገሩ አይቀርም። ጋሽ ስብሃት ገ/እግዛብሔር ክፉ ሰውን ለመግለፅ “የሰይጣን ግራ እጅ” የሚለው የኢሳያስ አይነቱን ሰው መሆን አለበት። የስንት እናቶች እንባና የስንት ንፁሃን ደም ሲፈስ እንደ አንድ ሲሲ ውስኪ መደፋት እንኳን እንደማይገደው ታሪክ መስክሯል።
ኢሳያስ እኩይ ነው ማለት ግን ዝም ብሎ ግብታዊ ጨካኝ፣ በደመነፍስ ብቻ የሚኖር ፣ተራ አረመኔ ወንበዴ ነው ማለት አይደለም። ኢሳያስ የሚንቀሳቀሰው እጅግ በሰፊው በተጠና፣ በተደጋጋሚ ተሞክሮ ስኬትም ኪሳራም ባስገኘ፣ በደንብ የተመተረ ስልት ( Method) እንደሆነ ከውጤቱ መረዳት ይቻላል።
ኢሳያስን የፈለገ ብትጠሉት በንቀት የምትገጥሙት ባላንጣም ፣ ምንም አያመጣም ብላችሁም የምታቅፉት ወዳጅም አይደለም። የአንድን አዳኝ ችሎታ ለማወቅ ከፈለጋችሁ ግዳዮቹን ማየት ብቻ በቂ ነው። መቼም መቼም ምን ዳኝነት ቢጓደል ጠዋት ለሽንት ሲወጣ ሸለምጥማጥ በድንጋይ የገደለና አድኖ አንበሳን የገደለ በአንድ ማዕረግ “ገዳይ” ተብለው አይጠሩም። እናማ ባለፉት 50+ የኢትዮጵያና አፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ ኢሳያስን ገጥመው የተሸነፉትን ማየት ብቻ ኢሳያስ የዋዛ እንዳልሆነ ለማወቅ በቂ ምስክሮች ናቸው። የኢሳያስ ስልት ምንድን ነው? ይህ በጣም በጣም መጠናት ያለበት ከባድ እጅግ ወቅታዊ ጥያቄ ነው። ይሄን እስከአሁን ካላወቅን ረፍዶብንም ሊሆን ይችላል። ለዛሬ ግን ቢያንስ ሰውየው የተለየ ሚዛን የሚሰጠው እንደሆነ መስማማት ይበቃል።
Filed in: Amharic