>

በኢትዮጵያ የርስ በርስ ጦርነት እንዳይከሰት መፍሔው ምን ይሆን ? (ደረጀ መላኩ - የሰብአዊ መብት ተሟጋች )

በኢትዮጵያ የርስበርስ ጦርነት እንዳይከሰት መፍሔው ምን ይሆን ? ፣ ወያኔ  የፈጸመው የሰብአዊ መብት ጥሰት በወፍ በረር ሲቃኝ

ደረጀ መላኩ ( የሰብአዊ መብት ተሟጋች )

Tilahunges@gmail.com

መንደርደሪያ

 የኢትዮጵያ መንግስት በሰሜናዊት ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል የህግ የበላይነትን ከማስከበር አኳያ ከሚያደርገው ትግል ጎን ለጎን የዲፕሎማሲ መንገዶችን  እንዲከተል ጸሃፊው የራሱን የግል አስተያየት ለማቅረብ ይሞክራል፡፡ የዲፕሎማቲክ ጥበብ ገቢራዊ ሳያደርጉ ጉልበትን ብቻ መጠቀም ውጤታማ ነው ብዬ አላስብም፡፡ አንድ ሀገር የተማሩና የሀገር ፍቅር ስሜት ያላቸው የዲፕሎማቲክ ባለሙያዎች ያስፈልጓታል ብዬ አስባለሁ፡፡ ወያኔ ኢትዮጵያ ላይ ስለፈጸመው ክህደት ለውጪ ሀገራት መሪዎች በዲፕሎማቲክ ቋንቋ ማስረዳት ተገቢ ነው፡፡

የወያኔ ቡድን የፈጸማቸው የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በወፍ በረር ሲቃኙ

የወያኔ የፖለቲካ ፊትአውራሪዎች ባለሥልጣን በነበሩበት ጊዜ የኢፌዴሪ ሕገመንግሥትን ማክበርና ማስከበር ሲገባቸው ሕገ-መንግሥቱን ያዋረዱት እነሱ ራሳቸው ሆኑ። በወያኔ የተረጋገጡት ዋና ዋና ሕገመንግሥታዊ ድንጋጌዎች የሚከተሉት ናቸው።

አንደኛውና ዋናው ”ማንኛውም ሰው በሕይዎት የመኖር መብት አለው። ማንኛውም ሰው በሕግ በተደነገገ ከባድ የወንጅል ቅጣት ካልሆነ በስተቀር ሕይዎቱን አያጣም።” የሚለው ነው። በዚህ ወንጀል ተጠያቂዎች ገዳይም አስገዳይም ናቸው።

ሁለተኛው ”ማንኛውም ኃላፊና የሕዝብ ተመራጭ ኃላፊነቱን ሲያጓድል ተጠያቂ ይሆናል።” ከሚለው ጋር የተያያዘ ነው። በዚህ ወንጀል ዋነኞቹ ተጠያቂዎች ከፍተኛ ሥልጣን ላይ ያሉት ናቸው።

ጉዳዩ በዋነኛነት ከዚህ በታች የተዘረዘሩት በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የተካተቱት አንቀጾች፣ በተለይም፡- አንቀጽ 10፡ (ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች)፣ አንቀጽ 14፡ (የሕይዎት፡ የአካል ደህንነትና የነፃነት መብት)፣ አንቀጽ 15፡ (የሕይዎት መብት)፣ አንቀጽ 25፡ (የእኩልነት መብት) ተጥሰዋል የሚል ነው፡፡ 

  • አንቀጽ 10፡ (ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች) – ሰብአዊ መብቶችና ነጻነቶች ከሰው ልጅ ተፈጥሮ የሚመነጩ የማይጣሱና የማይገፈፉ ናቸው፡፡ (ንዑስ አንቀጽ 1.)
  • አንቀጽ 14፡ (የሕይዎት፡ የአካል ደህንነትና የነፃነት መብት) – ማንኛውም ሰው ሰብአዊ በመሆኑ የማይደፈርና የማይገሰስ በሕይዎት የመኖር፡ የአካል ደህንነትና፡ የነፃነት መብት አለው፡፡ 
  • አንቀጽ 15፡ (የሕይዎት መብት) ማንኛውም ሰው በሕይዎት የመኖር መብት አለው፡፡ ማንኛውም ሰው በሕግ በተደነገገ ከባድ የወንጅል ቅጣት ካልሆነ በስተቀር ሕይዎቱን አያጣም፡፡ 
  • አንቀጽ 25፡ (የእኩልነት መብት) – ሁሉም ሰዎች በሕግ ፊት እኩል ናቸው፤ በመካከላቸውም ማንኛውም ዓይነት ልዩነት ሳይደረግ በሕግ እኩል ጥበቃ ይደረግላቸዋል፡፡ በዚህ ረገድ በዘር፡ ብሔረሰብ፡ በቀለም፡ በፆታ፡ በቋንቋ፡ በሃይማኖት፡ በፖለቲካ፡ በማኅበራዊ አመጣጥ፡ በሀብት፡ በትውልድ ወይም በሌላ አቋም ምክኒያት ልዩነት ሳይደረግ ሰዎች ሁሉ እኩልና ተጨባጭ የሕግ ዋስትና የማግኜት መብት አላቸው፡፡
  • የኢትዮጵያ ሕዝብ ያነሣው ጥያቄ የኢፌድሪ ሕገ መንግሥትን ለማክበርና ለማስከበር ያቃታቸው የወያኔ ባለሥልጣኖች ይጠየቁ የሚል ነው፡፡ ጉዳዩም ከዚህ በታች የተዘረዘሩት በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የተካተቱት አንቀጾች፣ በተለይም፡- አንቀጽ 9፡ (የሕገ መንግሥት የበላይነት)፣ አንቀጽ 12፡ (የመንግሥት አሠራርና ተጠያቂነት)፤ አንቀጽ 13፡ (ተፈጻሚነትና አተረጓጎም)፤ አንቀጽ 28፡ (በስብዕና ላይ ስለሚፈጸሙ ወንጀሎች)፣ በሚያዙት መሠረት እርምጃ ይወሰድ የሚል ነው፡፡ 
  • አንቀጽ 9፡ (የሕገ መንግሥት የበላይነት)

o ሕገ ምንግሥቱ የሀገሪቱ የበላይ ሕግ ነው፡፡ ማንኛውም ሕግ፡ ልምዳዊ አሠራር፡ እንዲሁም የመንግሥት አካል ወይም ባለሥልጣን ውሳኔ ከዚህ ሕገ መንሥት ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈጻሚነት አይኖረውም፡፡ (ንዑስ አንቀጽ 1.)

o ማንኛውም ዜጋ፡ የመንግሥት አካላት፡ የፖለቲካ ድርጅቶች፡ ሌሎች ማኅበራት እንዲሁም ባለሥልጣኖቻቸው፡ ሕገ መንግሥቱን የማክበርና ለሕገ መንግሥቱ ተገዢ የመሆን ኃላፊነት አለባቸው፡፡ (ንዑስ አንቀጽ 2.)

o በዚህ ሕገ መንግሥት ከተደነገገው ውጭ በማናቸውም አኳኋን የመንግሥት ሥልጣን መያዝ የተከለከለ ነው፡፡ (ንዑስ አንቀጽ 3)

o ኢትዮጵያ ያጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የሀገሪቱ ሕግ አካል ናቸው፡፡ (ንዑስ አንቀጽ 4.)

  • አንቀጽ 12፡ (የመንግሥት አሠራርና ተጠያቂነት) – ማንኛውም ኃላፊና የሕዝብ ተመራጭ ኃላፊነቱን ሲያጓድል ተጠያቂ ይሆናል፡፡ (ንዑስ አንቀጽ 2.)
  • አንቀጽ 13፡ (ተፈጻሚነትና አተረጓጎም) – በዚህ ምዕራፍ የተዘረዘሩት መሠረታዊ የመብቶችና የነፃነቶች ድንጋጌዎች ኢትዮጵያ ከተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሕግጋት፡ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶችና ዓለም አቀፍ ሠነዶች መርሆዎች ጋር በተጣጣመ መንገድ ይተረጎማሉ፡፡ (ንዑስ አንቀጽ 2.)
  • አንቀጽ 28፡ (በስብዕና ላይ ስለሚፈጸሙ ወንጀሎች) – ኢትዮጵያ ባጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች እና በሌሎች የኢትዮጵያ ሕጎች በሰው ልጅ ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎች ተብለው የተወሰኑትን ወንጀሎች፡ የሰው ዘር ማጥፋት፣ ያለፍርድ የሞት ቅጣት እርምጃ የመውሰድ፣ በአስገዳጅ ሰውን የመሰወር፤ ወይም ኢሰብአዊ የድብደባ ድርጊቶችን በፈጸሙ ሰዎች ላይ ክስ ማቅረብ በይርጋ አይታገድም፡፡ በሕግ አውጪው ክፍልም ሆነ በማንኛውም የመንግሥት አካል ውሳኔዎች በምሕረት ወይም በይቅርታ አይታለፉም፡፡ (ንዑስ አንቀጽ 1.)

በጠጨማሪም፡- የሰብአዊ መብቶች ዓለም አቀፋዊ መግለጫ አንቀጽ 30 አና የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል ኪዳን አንቀጽ 50 በኢፌድሪ ሕገ መንግሥት ውስጥ የተካተቱት አንቀጾች አፈጻጸም ምን ማሟላት እንዳለበት በማያሻማ መንገድ በግልጽ ያመለክታሉ፡፡ (ምንጭ፡ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን)

  • የሰብአዊ መብቶች ዓለም አቀፋዊ መግለጫ አንቀጽ 30፡ በዚህ መግለጫ የተጠቀሰ ማንኛውም አንቀጽ አንድ መንግሥት፣ ቡድን ወይም ግለሰብ እዚህ የተዘረዘሩትን ማናቸውንም መብቶችነና ነፃነቶች ለመጣስ በሚያስችል ድርገጊተት ወይም እንቅስቃሴ የመሳተፍ መብት እንዳለው በሚያስመሰስለል መንገድ ፈጽሞ መተርጎም የለበትም፡፡ 
  • የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል ኪዳን አንቀጽ 50፡ ፌደራላዊ አስተዳደር ባላቸው አገሮች የዚህ ቃል ኪዳን ድንጋጌዎች በሁሉም የአስተዳደር ክልሎች ያለምንም ገደብ ወይም ልዩነት ተፈጻሚ ይሆናሉ፡፡

የወያኔ ግድያ የጀመረው ገና ሥልጣን ላይ እንደወጣ ነው። የወያኔ ግፍ በሰሜን፡ በደቡብ፡ በምሥራቅ፡ በምዕራብና በመሀል ኢትዮጵያ ተዳርሷል። 

ወያኔን የተጠናወተው በሽታ አሁን የጀመረው ላለመሆኑ ቀደም ካሉት ተመሳሳይ ግድያዎች ውስጥ በአዋሳ የተካሄደውንና በኢሰመጉ መግለጫ የቀረበውን ከዚህ በታች ማንበብ ይቻላል።

በአዋሳና አካባቢው በሚገኙ ነዋሪዎች ላይ የደረሰ አስከፊ የመብት ረገጣ

51ኛ ልዩ የኢሰመጉ መግለጫ

ግንቦት 21 ቀን 1994 ዓ.ም

መግቢያ 

በአዋሳ ከተማና አካባቢው በሰላማዊ ሰልፍ አማካይነት ጥያቄውን በማሰማት ላይ በነበረው በሲዳማ ሕብረተሰብና በመንግሥት ታጣቂ ኃይሎች መካከል ግንቦት 16 ቀን 1994 ዓ.ም የተፈጠረው ግጭት በብዙ ሰው ላይ የሕይዎትና የአካል ጉዳት እንደዚሁም እስራት ከማስከተሉ በላይ ችግሩ አሁንም አለ።

የግጭቱ መንስኤ

የአዋሳ ከተማ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥትና የሲዳማ ዞን መስተዳደር የጋራ ዋና ከተማ ወይም ማዕከል ሆና መቆየትዋ ይታወቃል። ይሁን አንጂ አዋሳ የክልሉ መንግሥት ርዕሰ ከተማ ብቻ እንድትሆንና የሲዳማ ዞን መስተዳደር ግን ወደ አለታ-ወንዶ ከተማ እንዲዛወር ተወስኗል በሚል (ስለመወሰኑ በይፋ ከመንግሥት የተሰጠ መግለጫ የለም) የተወሰኑ የሲዳማ ብሔረሰብ አባላት ቅሬታቸውን ለመንግሥት በሰላማዊ ሰልፍ ለመግለጽ ተዘጋጁ። 

ሕዝቡም በሰላማዊ መንገድ በመሰብሰብ ቅሬታውን ለመንግሥት ለመግለጽ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 30 ላይ ያለውን መብት መሠረት አድርጎ ሰላማዊ ሰልፍ የሚያደርግበትን ምክኒያት፣ ሰልፍ የሚያካሂድበትን ቀን፤ ሰዓቱንና ቦታውን ለይቶ በሰልፉ አስተባባሪዎች አማካይነት ጥያቄውን ለሚመለከተው መንግሥታዊ አካል አቀረበ። በወጣው ፕሮግራም መሠረት ሰልፉ ግንቦት 16 ቀን 1994 ዓ.ም እንደሚካሄድና መነሻውም ከአዋሳ ከተማ በስተደቡብ በአምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከምትገኘው “ሉቄ” ከተባለች ከተማ ሆኖ የሰልፉ መጨረሻም አዋሳ ከተማ ውስጥ ከሚገኘው አብዮት አደባበባ እንዲሆን ታቅዶ ነበር።

ከላይ በተጠቀሰው ዕለት በሲዳማ ዞን መስተዳደር ውስጥ ከሚገኙ የተለያዩ የወረዳ ከተሞችና የቀበሌ ገበሬ ማኅበራት ውስጥ ነዋሪ ከሆነው ሕዝብ መካከል 7000 (ሰባት ሺ) ያህል ሕዝብ ተቃውሞውን ለመግለጽ በባህሉ መሠረት የእንሰት ተክል ዝንጣፊና እፍኝ ሳር በእጁ ይዞና የኢትዮያን ባንዲራ የያዙትን ሰልፈኞች ግንባር ቀደም አድርጎ፣ 

  • “ሲዳማ ክልል የመሆን ሕገ መንግሥታዊ መብቱ ይጠበቅለት፣” 
  • “የኢሕአዴግን ዓላማ አንቃወምም፣”
  • “አዋሳ ከተማ የሲዳማ ዞን ርዕሰ ከተማ እንዳትሆን ለምን ተፈለገ?”

የሚሉትንና የመሳሰሉትን መፈክሮች በመያዝ ወደ ሰልፉ መድረሻ የሚወስደውን ጎዳና ተከትሎ ጎዞውን ቀጠለ።

በዚህ ሁኔታ ሰልፈኛው ከመነሻ ስፍራው ጀምሮ ሦሰት ኪሎ ሜትር ያህል በሰላም ተንቀሳቅሶ አዋሳ መግቢያ በር እንደደረሰ በአካባቢው መሽጎ ይጠባበቅ የነበረው ታጣቂ የመንግሥት ኃይል የፊሽካ ድምፅ እንደተሰማ በመኪናዎች ላይ የተጠመደውን ፒ.ኬ.ኤም የድግን መትረስ አፈሙዞች ወደ ሰልፈኛው አነጣጥሮ ለአስር ደቂቃ ያህል ያወረደው የጥይት ናዳ የገደለውን ገድሎና ያቆሰለውን አቁስሎ ቀሪውን ሰልፈኛ በተነው።

አስከ አሁን ድረስ ለኢሰመጉ በፎቶግራፍ ተደግፎ በደረሰው መረጃ መሠረት በዚሁ ግጭት ምክኒያት ሕይወታቸው ያለፈውን፣ የመቁሰል አደጋ የደረሰባቸውንና ለእስራት የተዳረጉትን ግለሰቦች ስም ዝርዝር ከነአድራሻቸው ከዚህ በታች በቀረቡት ሰንጠረዦች አማካይነት ቀርቧል። ኢሰመጉ ስለደረሰው ግጭት አሁንም በማጣራት ላይ ስለሆነ ተጨማሪ መረጃዎች እንደደረሱት ስለተከሰተው ሁኔታና ጉዳት በሌላ መግለጣ ለሕዝብና ለሚመለከታቸው ሁሉ ለማቅረብ ይጥራል።

ሰንጠረዥ 1፡ በመንግሥት ታጣቂ ኃይል ሕይዎታቸው ያለፈ 

ወረዳ፡ ገበሬ ማኅበር

(1) አቶቴ አሊቶ ወሊሶ፡ ዕድሜ 45፡ ሥራ – ገበሬ፡ አድራሻ – አዋሳ ወረዳ፡ ቱላ ገበሬ ማኅበር፡ (የኢትዮጵያ ባነንደዲራ እንደያዙ) 

(2) ማርቆስ መንገሻ፡ ዕድሜ 16፡ ሥራ – ነጋዴ፡ አድራሻ – አዋሳ ወረዳ፡ ጨፋ ሲኒ ገበሬ ማኅበር፡ ()

(3) አየለ ጨካሞ፡ ዕድሜ 16፡ ሥራ – ተማሪ፡ አድራሻ – (አልተመዘገበም)፡

(4) ኑኡሻ ሪቢሶ፡ ዕድሜ 42፡ ሥራ – ነጋዴ፡ አድራሻ – አዋሳ ከተማ፡ ከፍተኛ 2 ቀበሌ 07፡ (የኢትዮጵያ ባነንደዲራ እንደያዙ) 

(5) በላይ ቡቲ፡ ዕድሜ 13፡ ሥራ – ተማሪ፡ አድራሻ – አዋሳ ወረዳ፡ አላሙራ ገበሬ ማኅበር፡ 

(6) ዳንኤል ሆበሳ፡ ዕድሜ 15፡ ሥራ – ተማሪ፡ አድራሻ – አዋሳ ወረዳ፡ አቤላ ሊዳ ገበሬ ማኅበር፡ 

(7) ሃምሳ ክኤሳ፡ ዕድሜ 16፡ ሥራ – ተማሪ፡ አድራሻ – አዋሳ ወረዳ፡ ቆርኬ መቅሰለ ገበሬ ማኅበር፡ 

(8) ሰቃቻ ማቲቻ፡ ዕድሜ 35፡ ሥራ – ነጋዴ፡ አድራሻ – አዋሳ አጎባ ወረዳ፡ ገበሬ ማኅበር፡ 

(9) ሀርዳታ ግዴሳ፡ ዕድሜ 20፡ ሥራ – ተማሪ፡ አድራሻ – አዋሳ ወረዳ፡ ጎና ጎያ ገበሬ ማኅበር፡

(10) ቡና ቡለኖ፡ ዕድሜ 22፡ ሥራ – ነጋዴ፡ አድራሻ – ሸበዲኖ ወረዳ፡ አቤላ ሊዳ ገበሬ ማኅበር፡

(11) ከዲር አብድልቃድር፡ ዕድሜ 25፡ ሥራ – ገበሬ፡ አድራሻ – (አልተመዘገበም)፡ 

(12) ለበሎ ዱከሞ፡ ዕድሜ 25፡ ሥራ – ገበሬ፡ አድራሻ – አዋሳ ወረዳ፡ ፈንጨሞ ገበሬ ማኅበር፡ 

(13) ቶሎሞ ቱማቶ፡ ዕድሜ 16፡ ሥራ – ተማሪ፡ አድራሻ – አዋሳ ወረዳ፡ በቢጨሮሮ ገበሬ ማኅበር፡ 

(14) ቡናራ ጉናማ፡ ዕድሜ 15፡ ሥራ – ተማሪ፡ አድራሻ – ሸበዲኖ ወረዳ፡ አቤላ ሊዳ ገበሬ ማኅበር፡ 

(15) ረኪሳ ቦሻለ፡ ዕድሜ 30፡ ሥራ – ገበሬ፡ 

(16) ታፈሰ የበ፡ ዕድሜ 16፡ ሥራ -ተማሪ ፡ አድራሻ – ሸበዲኖ ወረዳ፡ ቦነያ ምርዴ ገበሬ ማኅበር፡ 

(17) ከፍያለው ዶያሞ፡ ዕድሜ 15፡ ሥራ – ተማሪ፡ አድራሻ – አዋሳ ወረዳ፡ ጨፋ ገበሬ ማኅበር፡ 

(18) ዮሴፍ ኢሳያስ (10 አለቃ)፡ ዕድሜ 40፡ ሥራ – የክልል ፖሊስ ሠራዊት፡ አድራሻ – አዋሳ ከተማ፡ (ሰልፈኞቹ አደገኛውን መስመር አልፈው እንዳይሄዱ በመከላከል ላ እንዳለ በፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ ከጀርባው በተተኮሰ ጥይት ተመትቶ ኩየራ ሆስፒታል እንደደረሰ ሕይወቱ ያለፈ)

(19)ታደሰ ኪአ (ወ/ር) ፡ ዕድሜ 45፡ 

(20) ዮሴፍ ዲዳ ሴፋ፡ ዕድሜ 16፡ ሥራ – በታቦር መለስተኛ 2ኛ ደ/ት/ቤት የ8ኛ ክፍል ተማሪ፡ 

(21) አኒሳ ኪኤሳ በራሳ፡ ዕድሜ 15፡ ሥራ – የታቦር መለስተኛ 2ኛ ደ/ት/ቤት የ7ኛ ክፍል ተማሪ፡ 

(22) ሣቶ ሣቂቻ ማቲቻ፡ ሥራ – ገበሬ፡ አድራሻ – አዋሳ ወረዳ፡ አላሙራ ገበሬ ማኅበር፡ 

(23) ሰይድ ቱንጋሞ ቱራ፡ ዕድሜ 16፡ ሥራ – የ10ኛ ክፍል ተማሪ፡ (ይርጋለም ሆስፒታል ህክምና እርዳታ ሲደረግለት ቆይቶ በ16/9/94 አርፏል)

(24) ብዙነህ ላንቃሞ ዱሜ፡ ሥራ – ነጋዴ፡ አድራሻ – አዋሳ ከተማ፡ ከፍተኛ 2 ቀበሌ 07፡

(25) ስለሽ ጨካሞ፡ ዕድሜ 15፡ ሥራ – የቱላ 1ኛ ደ/ት/ቤት የ8ኛ ክፍለል ተማሪ፡ አድራሻ – ቱላ ገበሬ ማኅበር፡

በሰንጠረዥ 2፡ በመንግሥት ታጣቂ ኃይል የአካል ጉዳት የደረሰባቸው 26 ሰዎችን (ስም፡ዕድሜ፡ ሥራ፡ አድራሻ፡ የጉዳት መጠን እና ልዩ ሁኔታ ያካተተ) ዝርዝር አቅርቧል። 15ቱ ተማሪዎች ነበሩ፤ ከነሱም ውስጥ ስድስቱ እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ትንንሽ ልጆች ነበሩ።

በሰንጠረዥ 3፡ በሰልፉ ምክኒያት ለእስራት የተዳረጉ 36 ሰዎችን (ስም፡ ዕድሜ፡ ሥራ፡ አድራሻ፡ የታሰሩበት ቀን፡ ያካተተ) ዝርዝር አቅርቧል። 

ማጠቃለያ

…. ሣርና ቅጠል በመያዝ ሰላማዊ ሰልፍ ወጥቶ ጥያቄውን ለመንግሥት በማቅረብ ላይ በነበረው ሕዝብ ላይ የመንግሥት ታጣቂ ኃይሎች በወሰዱት ሕገ ወጥ የኃይል እርምጃ በሰው ሕይዎትና መብት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል።

ስለዚህ መንግሥት፡

  • ለግጭቱ መንስኤ ናቸው የሚላቸውን ችግሮች ከኃላፊነት አንጻር ተገቢው ትኩረት ሰጥቶ በሰላማዊ መንገድ ከሕዝብ ለቀረበለት ጥያቄ ሕጋዊና ፍትሐዊ መልስ እንዲሰጥ፤
  • በግጭቱ ለጠፋው የሰው ሕይዎትና ለደረሰው የአካል ጉዳት ተጠያቂ የሆኑ ግለሰቦችና የመንግሥት ባለሥልጣኖች ሕግ ፊት እንደዲቀርቡ እንዲደረግ፤
  • በግጭቱ ምክኒያት ለደረሰው ጉዳት ሁሉ መንግሥት ተገቢውን ካሣ ለጉዳተኞቹና ቤተሰቦቻቸው እንዲከፍልና፤
  • በሕገ-ወጥ ሁኔታ የታሰሩትም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ፤ 

ኢሰመጉ ጥያቄውን ያቀርባል።

ለሕግ ሉዓላዊነትና ለሰብአዊ መብቶች መከበር የቆማችሁ ግለሰቦች፡ የመንግሥት ተወካዮች እና ብሔራዊም ሆነ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሁሉ ከዚህ ቀጥሎ ለተጠቀሱት የመንግሥት አካላትና ባለሥልጣኖች የኢሰመጉን ጥሪ በመደገፍ ጥያቄያችሁን በየአድራሻቸው እንድታስተላልፉ ኢሰመጉ ትብብራችሁን ይጠይቃል።

  • ለኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ጽሕፈት ቤት፣ 
  • ለኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ጽሕፈት ቤት፣
  • ለኢ.ፌ.ዴ.ሪ.ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት፣
  • ለኢ.ፌ.ዴ.ሪ.ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣
  • ለደቡብ ብ.ብ.ሕ. ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ጽሕፈት ቤት፡ 

(የያንዳንዱ ጽሕፈት ቤት፡- የፖ.ሣ.ቁ.፡ የኢ-ሜል፡ የፋክስ፡ የስልክ፡ አድራሻቸው በመግለጫው ላይ ተካቷል።)

ከደቡብ ክልል በተጨማሪ በሌሎችም በምሳሌነት የሚታዩ በመንግሥት ታጣቂዎች የተደረጉ ሕገ-ወጥ ግድያዎች ከዚህ በታች ቀርበዋል።

(2) በኦሮሚያ ክልል የተፈጸሙ ሕገ-ወጥ ግድያዎች

————————————————-

በኦሮሚያ ክልል በመንግሥት ታጣቂዎች ምን ያህል እንደሆነ አሁን የተሟላ መረጃ ማግኜት የሚቻል አይመስለኝም። ሆኖም የችግሩን አስከፊነት ለመገመት ከውስን መረጃዎችም ቢሆን መረዳት ይቻላል። በትኅሳስ ወር 2008 ዓ.ም በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ፡ በሰላማዊ ሰልፍ ላይ በተሳተፉ ሰዎች ላይ ከተፈጸሙ ግድያዎች ውስጥ የሚከተሉት አሥር ሰዎች ይገኙበታል። ከአስሩ ውስጥ ሦሰቱ ልጆች ናቸው፤ የ14፡ የ15፡ የ16 ዓመት ልጆች። አንዲት ሴት አለችበት። የሁለት ሃይሞኖት ተከታዮች (የፕሮቴስታንት እና የኦርቶዶክስ) ይኑበታል። መረጃው የተገኘው ከሰመጉ (ኢሰመጉ) 140ኛ ልዩ መግለጫ ነው።

የአሥሩ ሰዎች ዝርዝር እንደሚከተለው ነው።

(1) አቶ በቀለ ሰቦቃ፡ኅዳር 27 ቀን 2008 ዓ.ም እንጪኒ በተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ በታጠቁ የመንግሥት ኃይሎች ተገድሎ በኅዳር 28 ቀን 2008 ዓ.ም ሙገር ሩፋኤል ቤተክርስቲያን የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ተፈጽሟል።

(2) (ተማሪ) ጸጋዬ አበበ፡ እድሜ 15፡ ታኅሳስ 3 ቀን 2008 ዓ.ም በተደረገ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ በመንግሥት የታጠቁ ኃይሎች ጀልዱ ከተማ ላይ ተገድሎ የፕሮቴስታንት መካነ መቃብር የቀብሩ ሥነ ሥርዓት ተፈጽሟል።

(3) ወይዘሮ ብርቱካን በዳዳ፡ በጀልዱ ወረዳ ኮሉ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ነዋሪ ነበረች በፕሮቴስታንት መካነ መቃብር የቀብሩ ሥነ ሥርዓት ተፈጽሟል። ታኅሳስ 3 ቀን 2008 ዓ.ም በሰላማዊ ሰልፉ ላይ በመንግሥት የታጠቁ ኃይሎች ተገድላ ጀልዱ ከተማ በሚገኘው የፕሮቴስታንት መካነ መቃብር የቀብሯ ሥነ ሥርዓት ተፈጽሟል። 

(4) አቶ ለሜሳ ኮኩና፡ ጀልዱ ከተማ ታኅሳስ 4 ቀን 2008 ዓ.ም በተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ በመንግሥት የታጠቁ ኃይሎች ተገድሎ ጦቢ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲን የቀብሩ ሥነ ሥርዓት ተፈጽሟል።

(5) አቶ ባይሳ ወጋ፡ ጀልዱ ከተማ ታኅሳስ 4 ቀን 2008 ዓ.ም በተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ በመንግሥት የታጠቁ ኃይሎች ተገድሎ ጦቢ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲን የቀብሩ ሥነ ሥርዓት ተፈጽሟል።

(6) ወጣት ዘውዴ ሥዩም፡ እድሜ 25፡ አምቦ ኮሌጅ ተማሪ ነበር። ታኅሳስ 7 ቀን 2008 ዓ.ም ሙገር ከተማ ቀንና ሌሊት ሰልፍ በነበረበት ወቅት በታጠቁ የመንግሥት ኃይሎች በጥይት ተመትቶ ሕይወቱ አልፏል። የቀብሩ ሥነ ሥርዓት ታኅሳስ 9 ቀን በዳንሴ ማርያም ቤተክርስቲን ተፈጽሟል።

(7) (ወጣት)በዳዳ ከበበ፡ ታኅሳስ 7 ቀን 2008 ዓ.ም ሙገር ከተማ ቀንና ሌሊት ሰላማዊ ሰልፍ ነበረበት ወቅት በታጠቁ የመንግሥት ኃይሎች በጥይት ተገድሎ በታኅሳስ 9 ቀን 2008 ዓ.ም ጉትቻ ማርያም ቤተክርስቲያን የቀብሩ ሥነ ሥርዓት ተፈጽሟል።

(8) አቶ ለማ መገርሳ፡ የመኪና ረዳት የነበረ ሲሆን፣ ታኅሳስ 7 ቀን 2008 ዓ.ም ሙገር ከተማ በተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ በታጣቂዎች ተገድሎ ታኅሳስ 9 ቀን ጉትቻ ማርያም ቤተክርስቲያን የቀብሩ ሥነሥርዓት ተፈጽሟል።

(9) (ተማሪ) ፍቃዱ ግርማ ደበላ፡ እድሜ 16፡ ታኅሳስ 29 ቀን 2008 ዓ.ም ጉዶ (ጨሊያ) ላይ በተደረገ ሰላማዊ ሰልፍ በመንግሥት የታጠቁ ኃይሎች ተገድሏል።

(10) (ተማሪ) ደረጀ ጋዲሳ ታዬ፡ እድሜ 14፡ ታኅሳስ 30 ቀን 2008 ዓ.ም ባብቾ ላይ በተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ በመንግሥት የታጠቁ ኃይሎች በበተኮሰ ጥይት ተገድሏል።

(3) በአማራው ክልል የተፈጸሙ ሕገ-ወጥ ግድያዎች

————————————————–

በአማራ ክልል በመንግሥት ታጣቂዎች ምን ያህል እንደሆነ አሁን የተሟላ መረጃ ማግኜት የሚቻል አይመስለኝም። ሆኖም የችግሩን አስከፊነት ለመገመት ከውስን መረጃዎችም ቢሆን መረዳት ይቻላል። ለዚህም ታኅሳስ 26 ቀን 1986 ዓ.ም (January 4, 1994). “የጎንደሩ ጭፍጨፋ (The Gonder Massacre)” በሚል ርእስ በወጣው የኢሰመጉ 6ኛ መደበኛ መግለጫ ተጨባጭ መረጃ ሊሆን ይችላል።

ሰኞ ዕለት ጳጉሜ 2 ቀን 1985 በርካታ አማኞችን ያካተተ ሕዝብ ጎንደር ከታማ ውስጥ በሚገኘው ኢየሱስ አደባባይ ተሰብስቦ ነበር። አባ አምሃ እየሱስን ለመያዝ የመጡ የመንግሥት ታጣቂ ኃይሎች በተሰበሰበው ሕዝብ ላይ ተኩስ ከፍተው ብዙ ሰዎች የግድያና የመቁሰል አደጋ ደረሰባቸው። አባ አምሃ እየሱስን ለመያዝ በርካታ አማራጮች ነበሩ። ለፀሎት በተሰበሰቡ በሺዎች በሚቆጠሩ ሕዝብ ላይ ይህን ዓይነት ጉዳት ማድረስ ከፍተኛ ግፍ ነው። ይህ የወያኔ/ኢሕአዴግ ታጣቂዎች ድርጊት ሕገ-ወጥ ግድያንና የእምነት ነፃነት መድፈርን የሚያካትት ወንጀል ነው። 

ኢሰመጉ 6ኛ መደበኛ መግለጫውን እስካወጣበት ጊዜ ድረስ 18 ሰዎች መገደላቸውን አረጋግጧል። እነሱም፡- (1) አባ ክንፈሚካኤል ወርቁ፡ (2) አቶ ፀጋው መንበሩ፡ (3) ያልታዬ ሙቄ ነጋሽ፡ (4) ነጋሽ ምሕረቴ፡ (5) ሞላ ሙጬ፡ (6) ክፍሌ ኃይለማርያም፡ (7) የማነ ብርሃነን፡ (8) ውዱ መርሻ፡ (9) አበበ ብርሃኑ፡ (10) አስማሩ ፈንቴ፡ (11) ባዘዘው ማለዳ፡ (12) ገብረአምላክ ገበያው፡ (13) ዘሩ ብሩክ፡ (14) ፈቃዱ አሰፋ፡ (15) ወንድሙ ጌትነት፡ (16) እንየው ወርቄ፡ (17) ወሰንሰገድ መርሻ፡ (18) ፀጋ ዘዓብ፡ ናቸው።

 

የኢትዮጵያ መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር ከህውሃት ቡድን ጋር ከሚያደርገው ጦርነት ባሻግር ምን ይጠበቅበታል ?

የሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ግንባር የፖለቲካ ፊትአውራሪዎችን የሰውነት ባህሪ በጥሞና ለሚያስተውል ኢትዮጵያዊ ዜጋ ‹‹ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ›› ( Amharic proverb “When I am dead, said the donkey, may no couch grass grow  ) ያለችውን እንሰሳ በመጥቀስ  አባቶች የተናገሩትን ምሳሌያዊ ኣባባል  ያስታውሰናል፡፡ አባቶቻችን ይህን ምሳሌያዊ አነጋገር እንደው ዝም ብለው ያለምክንያት አልተጠቀሙበትም ነበር፡፡ አባቶቻችን አጥፍተው ለመጥፋት የተዘጋጁ የከንቱ ከንቱዎችን፣ ለእነርሱ ካልበጀ ሌላው አፈር ድሜ ይጋጥ የሚሉ ደካሞችን፣ እራስ ወዳዶችን፣ አድርባዮችን መሰሪ ተግባር ለመግለጽ የሚጠቀሙበት ገላጭ ቃል ነው፡፡ የወያኔ የፖለቲካ ፊተአውራሪዎች ከውልደታቸው እስከ አዛውነት የእድሜ ዘመናቸው ድረስ ለኢትዮጵያዊ ዜጎች የሚደማ ልብ እንደሌላቸው በተለያዩ ጊዜያት በተግባር አሳይተውናል፡፡ ስልጣናቸውን ላለማጣት የማይበጥሱት ቅጠል፣ የማይመሱት አፈር የለም፡፡ በአጭሩ የሚያሳዩት ባህሪያ ሲጠቃለል እኔ ከሞትኩ………የሚለውን ምሳሊያዊ አነጋገር ያስታውሰናል፡፡ ላለፉት 28 አመታት የነበረውን ስልጣን ( በማእከላዊ መንግስቱ የነበረውን የአንበሳውን ድርሻ ከተነጠቀ በኋላ ማለቴ ነው) መቀመጫውን ሰሜናዊት ትግራይ መቀሌ ማድረጉ ሁላችንም የምናውቀው ጉዳይ ነው፡፡ እንደምናስታውሰው በቀድሞው አጠራር የትግራይ ራስ ገዝ ዛሬ የትግራይ ክልላዊ መስተዳድር የኮሎኔል መንግስቱ ወታደራዊ አገዛዝ ተገርስሶ ከመወደቁ  ሁለት አመት ቀደም ብሎ  ወይም በፊት በህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ቡድን ቁጥጥር ስር ወድቃ ነበር፡፡ ( መላውን የኢትዮጵያ ግዛት የተቆጣጠሩት ትግራይን ከተቆጣጠሩ ሁለት አመት በኋላ ነበር፡፡ ) የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት ሲጸነስ  መስራቾቹ በፖለቲካ ፕሮግራማቸው ላይ እንዳሰፈሩት ከሆነ ትግራይን ከእናት ኢትዮጵያ ገንጥለው አንዲት ሉአላዊትና ነጻ ሀገር ለማድረግ ምኞት ነበራቸው፡፡ ምኞት ብቻም አልነበረም ብዙ ርቀት ተጉዘው ነበር፡፡ ሆኖም ግን የሆነላቸው አይመስለኝም፡፡ ከተሳሳትኩ ልታረም ዝግጁ ነኝ፡፡ እውነታው በግልጽ እንደሚያሳየን ግን በጂኦግራፊ አቀማመጥ ትግራይ ከኤርትራ የተለየች ናት፡፡ ትግራይ አንዲት ሉአላዊት ሀገር ለመሆን በብዙ መልኩ አዳጋች ይሆንባታል፡፡ ኤርትራ ራሷ በቀይ ባህር ላይ አንድ ሺህ ኪሎሜትር የሚረዝም የባህር በር ፣ ምጽዋና አሰብ የሚባሉ ሁለት የባህር  ወደብ ባለቤትና ስትራቴጂክ የጂኦግራፊ አቀማመጥ ቢኖራትም፣ ነጻ ሀገር ለመሆን በቃች ብትባለም ህዝቧን ከድህነት ማጥ ውስጥ ማውጣት አልተቻላትም፡፡ ለምን ? መልሱን ህሊና ለፈጠረባችሁ ኢትዮጵያውያን ትቼዋለሁ፡፡ እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ከባርነትና ነጻነት የቱ ይሻላል ? ከሚሉ ምርጫዎች አንዱን ‹‹ ነጻነትን ›› ከመረጠች ሰላሳ አመት ቢሞላትም ቢያንስ አሁን ድረስ ህዝቧ በምጣኔ ሀብት የዳበረ ህይወት መምራት አልሆነለትም፡፡ ኤርትራ የአፍሪካ ሲንጋፖር ትሆናለች ተብሎ በብዙ የተደሰኮረላት የፖለቲካ ፕሮፓጋንዲስቶች ጩሀትም፣ ጩሀት ሆኖ ቀርቷል፡፡ ኤርትራውያን ወንድሞቻችን፣ እህቶቻችን በአለም ላይ እንደ ጨው ዘር መበትን ብቻ ነው፡፡ እርግጥ ነው ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ኤርትራዊ ወንድሞቻችን በምእራቡ አለም ሀብትና ንብረት አፍርተው ሊሆን ይችላል፡፡ በእውቀትም በልጽገው ይሆናል፡፡ ሆኖም ግን የአካለ ጉዛይ፣ ከረን፣ ደቀመሐሪ፣ ኩናማ፣ መንደፈራ፣ ናቅፋ፣ባሬንቱ፣ አፋቤት ወዘተ ወዘተ አካባቢ ገበሬዎች የዘመናዊ እርሻ ባለቤት ሆነው የተትረፈረፈ ምርት አላገኙም፡፡ ኤርትራ በቀይባህር ላይ ያለውን የአሳ ክምችት በዘመናዊ ዘዴ አምርታ ለውጭ ገበያ ከማቅረብ አኳያ ቢያንስ በአፍሪካ ደረጃ ስሟን ማስጠራት አልቻለችም፡፡ ምናልባት ኤርትራ ስሟ በበጎ የሚነሳው በመንፈሰ ጠንካራ ብስክሊተኞቿ ስኬታማ ውጤት ሳይሆን አይቀርም፡፡

ዛሬም በተመሳሳይ መልኩ የህውሀት የፕሮፓጋንዳ አታሺዎች ‹‹ ትግራይ ከኢትዮጵያ ተለይታ ብቻዋን መቆም ትችላለች፣ ከእናቷ ኢትዮጵያ ብትለይ በኢኮኖሚ የበረታች ሀገር›› ለመሆን ትችላለች በማለት በብዙ መልኩ ይደሰኩራሉ፡፡ እውነታው ግን ለየቅል ነው፡፡ በርካታ ስመጥር ኢትዮጵያዊ የምጣኔ ሀብት ጠበብት በየጊዜው አበክረው እንደሚያስተምሩት ወይም ምክረ ሀሳብ እንደሚያቀርቡት ከሆነ በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ የሚገኙት ክልላዊ መስተዳድሮች ( የትግራይን ክልል ጨምሮ፣ ወደ እድገት ጎዳና መራመድ የሚችሉት፣ የነጻነት ቀንዲል መለኮስ የሚቻላቸው፣ የፍትህ ሸማ መከናነብ የሚችሉት፣ አንገታቸውን ቀና አድርገው መራመድ የሚሆንላቸው የህብረት ፍልስፍና መከተል ሲችሉ ነው፡፡ ለዚህ ምስክሩ የመከራው ገፈት ቀማሽ ከሆኑት ኢትዮጵያውያን ውጪ ማንም ሊሆን አይቻለውም፡፡ በትግራይ ክልል ብቻ ሳይሆን በሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎችም ቢሆን የአንድነት መላላት ከባድ ዋጋ ያስከፈለን ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ቢያንስ ቢያንስ ላለመስማማት መስማማት በሚል መርህ ስር እንኳን ተሰባስበው የአንድነት መሰረታቸውን ማጠንከር ባለመቻላቸው የተነሳ ለመጠነ ሰፊ ችግሮች ተጋልጠው ቆይተዋል፡፡ ከአሁን በኋላ ግን ለሌላ መከራ፣ ለሌላ የችግር አዙሪት ራሳቸውን ማጋለጥ ያለባቸው አይመስለኝም፡፡ (In fairness, this is not only true of Tigray of course but of every so-called Killil, or federal regional state of Ethiopia. Balkanization

በአንዳንድ የአለም ክፍል ውስጥ እንዳየነው ( በተለይም በምስራቅ የአውሮፓ ክፍል የነበሩ የባልካን አካባቢ ሀገሮችና በቀድሞዋ የሶቪዬት ህብረት ግዛት ውስጥ እንደተከሰተው አይነት) ከመራር ጦርነትና ሰላማዊ ሁኔታ አዳዲስ ሲወለዱ ታይቷል፡፡ ለብዙ ግዜም ሰላም ማግኘታቸውን ከአለም የፖለቲካ ታሪክ ተምረና፡፡ ይህ እውነት ግን በኢትዮጵያ እውን ሊሆን አይቻለውም፡፡ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያ ለብዙ ዘመናት በባል፣ ታሪክ፣ ሀይማኖት፣ ጋብቻ፣ ንግድ፣ ጦርነት፣ ሰላም፣ እርሻ…..ወዘተ ወዘተ የተሳሰሩ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ያላቸው እድል በአንድነትና ህብረት ፍልስፍና ተጋምደው ወደ ብልጽግና ማምራት እንጂ ተለያይተው መኖር በእጅጉ የሚያዳግታቸው ይመስለኛል፡፡ ኢትዮጵያውያን ተለያይተን መቼውንም ቢሆን ወደ እድገት ጎዳና መራመድ አይሆንልንም፡፡ እንደ ስመጥሩ ምሁር ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ( ነፍሳቸውን ይማር)፣ የምጣኔ ሀብቱ ጠበብት ዶክተር ፍቃዱ በቀለ፣ ፕሮፌሰር በፍቃዱ ደግፌ ወዘተ ወዘተ በጥናት በደረሱበት ድምዳሜ መሰረት ‹‹ አነስተኛ የቆዳ ስፋት ወይም ትልቅ የቆዳ ስፋት፣ እምቅ የተፈጥሮ ሀብት አለን የሚሉ ወይም ጥቂት የተፈጥሮ ሀብት አላቸው የሚባሉ የኢትዮጵያ ክልሎች ›› ቢሆንላቸውና ወግ ደርሷቸው ሉኣላዊ መንግስት ለማንበር ብችሉ፣ለብቻቸው፣ ተለያይተው ጠንካራ ኢኮኖሚ ያለው መንግስት ለማቆም በእጅጉ ይከብዳቸዋል፡፡ ከዚህ ባሻግር በክልሎች መሃከል ያለው እልባት ያልተገኘለት የድንበር መስመር ብቻውን አንድ ትልቅ ራስ ምታት ነው፡፡ ለአብነት ያህል በሶማሌና አፋር፣ በአፋርና አማራ፣ በሶማሌ እና ኦሮሞ ፣ በተለይ ደግሞ በደቡብ ኢትዮጵያ በበርካታ የዞን መስተዳድር ወይም ወረዳ ( ቀበሌ) ሳይቀር በድንበር ይገባኛል ምክንያት ላለፉት ሃያ ምናን አመታት የተከሰቱትን ግጭቶች ( ቁርቋሶች) ስናስተውል የኢትዮጵያ እድል አሳዛኝ መሆኑን አንገነዘባለን፡፡ በአጭሩ ለኢትዮጵያ አንድነት ይበጃታል ሲባል እንደው ዝም ብሎ ቃላት ለማሳመር ወይም ለላንቲካ አይደለም፡፡ ከዳቦና ኬክ አንዱን ከመምረጥም ይለያል፡፡ የኢትዮጵያ አንድነት የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ 

For Ethiopia, staying united is not a matter of sentimental choice; it is simply a question of survival.

ከማአከላዊ የመንግስት ስልጣናቸው ተሸንጥረው የወደቁት የወያኔ የፖለቲካ ፊትአውራሪዎች ሰሜናዊት ኢትዮጵያ መቀሌ ከተማ መቀመጫቸውን ከአደረጉ ወዲህ በርካታ የሰላም እድሎችን ያመከኑ መሰለኝ፡፡ እነርሱ ጊዜያቸውን ያባከኑት ዝንተ አለም ከመከራ ያልወጣውን የትግራይን ገበሬ ብረት በማስታጠቅ ነበር፡፡ ጥንካሬያቸውንና ድክመታቸውን በሚገባ የሚያጠናውና የሚያውቀው የኢትዮጵያ መንግስትም በትኩረት ይከታተለቸው ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና በወርሃ ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ የህውሃት የፖለቲካ ፊትአውራሪዎች በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ላለፉት 20 አመታት ድንበር ሲጠብቅ በነበረው የኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት( የሰሜን እዝ)  ላይ ድንገተኛ ጥቃት እንዲደርስበት ለልዩ ሀይላቸው ትእዛዝ በመስጠታቸው ምክንያት በኢትዮጵያ ወታደሮች ላይ ጉዳት መድረሱን ከኢትዮጵያና አለም አቀፍ የዜና አውታሮች ተሰምቷል፡፡ በእውነቱ ለመናገር ልብን ያደማል፡፡ ኢትዮጵያም ሳትወድ በግድ ወደ ጦርነት አውድ ውስጥ ተዶላለች፡፡ የወያኔ ቡድን ጠመንጃ አንጋቾች በሰሜን እዝ ላይ ድንገተኛ ጥቃት በመክፈት ጉዳት ካደረሱ በኋላም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶክተር አቢይ አህመድ በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብለው ኢትዮጵያ የህግ የበላይነትን ለማስከበር  ስትል ብቻ  ጦርነት ውስጥ መዶል ግዴታዋ ሆኗል ሲሉ ነበር ለኢትዮጵያ ህዝብ የተናገሩት፡፡ በነገራችን ላይ ጦርነት የሰው ልጅን ህይወት ጭዳ እንደሚያደርግ፣ የሀገር አንጡራ ሀብትን ዶግ አመድ እንደሚደርግ ሁላችንም የምንገነዘብ ይመስለኛል፡፡ ሆኖም ግን ኢትዮጵያ ከህውሀት ጋር የገጠመችው ጦርነት በአስገዳጅ ሁኔታ የተከሰተ ነው፡፡ ጦርነቱ የተቀሰቀሰው የህወሀት ጦር በሰሜን እዝ ጦር ላይ ድንገተኛ ጥቃት በመክፈቱ ምክንያት እንደሆነ ከመገናኛ ብዙሃን ተሰምቷል፡፡ በአለም የጦርነት ታሪክ ውስጥ በገዛ ሀገር ጦር ሰራዊት ላይ ድንገተኛ ጥቃት ከፍተው ጉዳት ያደረሱ የዛው ሀገር ተወላጆች ስለመኖራቸው የሚያወሳ መራር ሁነት ያነበብኩ አይመስለኝም፡፡ ወያኔዎች ግን አድርገውታል፡፡ ያሳዝናል፡፡ ማሳዘን ብቻ አይደለም ህሊናን ያደማል ሆድንም ይበጠብጣል፡፡

ከላይ ከሰፈረው መራር ሁነት ተነስተን የወያኔ ፖለቲካ ፊትአውራሪዎች በኢህአዲግ ማእከላዊ ኮሚቴ( ዛሬ ብልጽግና ፓርቲ) የነበራቸውን ስልጣን በመነጠቃቸው እና ዳግም ወደ ማእከላዊ መንግስት ተመልሰው ስልጣን የመያዝ እድላቸው ያከተመለት ስለመሆኑ በቅጡ የተረዱት ስለሆነ ነው በማለት መደምደም ይቻላል፡፡ በአጭሩ ባልበላውም……..በሚል የደካሞች ፍልስፍና ተነሳስተው ነው በሀገር ላይ ዳግማዊ ክህደት የፈጸሙት፡፡ በነገራችን ላይ ክህደት ለወያኔዎች ብርቅ አይደለም፡፡ ወያኔዎች በተደጋጋሚ ግዜ አብልታ ያሳደገቻቸውን ኢትዮጵያን ስለመክዳታቸው በታሪክ ጥቁር መዝገብ ላይ በጉልህ ተጽፎ ይገኛል፡፡

ኢትዮጵያን ዲሞክራቲክ ሀገር እንድትሆን የበኩላቸውን ድርሻ ከመወጣት ይልቅ እነርሱ የመረጡት ጉዞ ከኢትዮጵያ በመነጠል የራሳቸውን ጎጆ ለመቀለስ ሴራ መጎንጎን ነው፡፡ የእነርሱ የህልም እንጀራ ህልም ሆኖ የሚቀር ይመስለኛል፡፡ ምንአልባትም እንኳን አለም አቀፍ እውቅና የተነፈጋት የራስ ገዝ አገዛዝ ለማንበር በለስ ቢቀናቸው መጨረሻው አያምርም፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የወያኔ ፖለቲካ ፊተአውራሪዎች ፍላጎትና ምኞት ባለፉት 28 አመታት ለሰሩት ግፍ ያለመከሰስ መብታቸው ተጠብቆ እንዲቆይ ነው፡፡( ይህን ጽሁፍ በማዘጋጅበት ጊዜ ህዳር 3 ቀን 2013 ዓ.ም. የኢትዮጵያው ፓርላማ የወያኔ ፖለቲካ ፊትአውራሪዎችን ያለመከሰስ መብት መግፈፉን ከመገናኛ ብዙሃን ተሰምቷል፡፡) ከዚህም እልፍ በማለት የወታደራዊውን ደርግ አገዛዝ ከስልጣኑ በመገርሰሳችን በኢትዮጵያ ሶስት አስርተ አመታት የፈጀው የርስበርስ ጦርነት አንዲያከትምለት ከባድ መስእዋትነት ከፍለናል፣ ሥለሆነም ምስጋና ይገባናል ባይ ናቸው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ እንደሚያምነው ሰሜን ኢትዮጵያ ደደቢት በረሃ ላይ ተጸንሶ ወደ ደቡብ አቅጣጫ ዘመቻ በማድረግ የምኒሊክ ቤተመንግስትን የተቆጣጠረው የወያኔ አገዛዝ የደርግን መንግስት ገርስሶ የጣለው ( የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች፣ የምእራባውያን መጠነ ሰፊ እርዳታ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ደርግን ፊት መንሳቱ ሳይዘነጋ ማለቴ ነው) የኢትዮጵያን ህዝብ ነጻ ለማውጣት አለነበረም፡፡ ወያኔዎች እስትራቴጂክ የሆነ የምጣኔ ሀብት ማግበስበስ አቅድ ነበራቸው፡፡ ስልጣን በያዙበት ጊዜ ያካበቱትን ሀብት የሚረሳ ኢትዮጵያዊ ያለ አይመስለኝም፡፡ ከዚህ ባሻግር አገዛዙ የማእከላዊ መንግስቱን ስልጣን ከተቆጣጠረ በኋላ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ ታይቶም ተሰምቶም በማያውቅ በከፋፍለህ ግዛ የዘረኝነት አገዛዝ ስልት በመከተል ኢትዮጵያን ወደ ሶስት አስርት አመታት ለሚጠጋ እድሜ ገዝቷል፡፡ ወያኔ አናሳ ቁጥር ያላውን የጎሳ ቡድን እወክላለሁ የሚል ስለሆነ ፣ ኢትዮጵያውያን ቁጭ ብለው በሰለጠነ መንገድ ተነጋግረው ያላቸውን ልዩነት በመሃከላቸው  የባቢሎን ግንብ በመገንባት የሚታወቅ እኩይ ቡድን ነው፣በተለይም ሁለቱን ታላላቅ ጎሳዎች ርሰበርስ በማጋጨት ነበር የሥልጣን እድሜውን ያራዘመው፡፡ በዚሁ መሰሪ የፖለቲካ ሴራው አመኃኝነትም  ለ28 አመታት በስልጣን ማማ ላይ ተነሰራፍቶ ለመቀመጥ አስችሎት ነበር፡፡

ለሁላችንም ግልጽ መሆን ያለበት ጉዳይ ቢኖር የወያኔ የፖለቲካ ፊትአውራሪዎች የፈጸሙት ሙስና እና የወንጀል ድርጊት በመጋለጡ ምክንያት የሚያሰሙት ኡኡታና አቤቱታ ፍትሃዊ አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ የመንግስት ታሪክ እንደ ወያኔ በጎሳ ፖለቲካ የሰከረና ያበደ፣እንዲሁም ጠባብ ቡድን የማእከላዊውን መንግስት ተቆጣጥሮ የሚያውቅ እንዳልነበር በርካታ የስነ መንግስት ምሁራን የሄሱት ጉዳይ ነው፡፡ በአጭሩ ወያኔ የስነ መንግስት ህሙማን ይመስለኛል፡፡

ባለፉት 28 አመታት በኢትዮጵያ ምድር የተፈጸመውን ሙስና ብቻ ጥናት ቢደረግበት ( እርግጥ ነው እንድ ትራንስ ኢንተርናሽናል የመሳሰሉ አለም አቀፍ ድርጅቶች አጥነተውታል)  የወያኔ ካድሬዎች የአንበሳውን ድርሻ ይይዛሉ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በጣም ግልጽ ነው ፡፡ የወያኔ ካድሬዎች በርካታ ቁልፍ የሥልጣን ኮርቻዎች፣ ለአብነት ያህል በወታደራዊው ክፍል፣በቢሮክራሲው እና በውጭ ሀገር በሚገኙ የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽ/ቤቶች ወይም ኤምባሲዎች አታሼነት እና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደርነት ስልጣን ላይ ( በአውስትራሊያ ሀገር በሚገኘው የኢትዮጵ ኤምባሲ ተሹመው የነበሩት ባልና ሚስቶች አንድ ማሳያ ነበሩ፡፡) ስተፈናጠው ስለነበር ነው፡፡  ስለሆነም በእነርሱ የአዞ እምባ የሚሞኝ የለም፡፡ይህ ማለት የስልጣን ሸሪኮቻቸው ከሙስና ነጻ ናቸው ማለት አይደለም፡፡

there has never been in Ethiopia a more blatantly tribalist and parochial an administration as the TPLF’s

በነገራችን ላይ በወያኔ የተጀመረው ጦርነት፣ የትግራይን ህዝብ እንደማይመለከት ሌላው ኢትዮጵያዊና ትግራይ ወንድሞቻችን በእውነትና ምክንያት ላይ ቆመው መረዳት አለባቸው ባይ ነኝ፡፡ የጦርነቱ ፍጻሜ የህግ የበላይነትን ለማስከበር መሆን አለበት የሚለው ሌላው መልእክቴ ነው፡፡ የወያኔ የፖለቲካ ፊተአውራሪዎች የጀመሩት ጦርነት ነጻ ራስ ገዝ ለመመስረት ያለመ ይሁን ወይም የማእከላዊ መንግስቱን ለመቆጣጠር የሚያውቁት ራሳቸው ናቸው፡፡ ሆነም ግን ይሁንና የተጀመረው ጦርነት በፍጥነት መቋጫ ካተገኘለት ሀገሪቱን ለከፋ ጉዳት ይዳርጋታል የሚል የግል ስጋት አለኝ፡፡ ከዚህ ባሻግር በታሪካዊቷ ሰሜናዊት ኢትዮጵያ ክፍል በምትገኘው የትግራይ ግዛት መጠነ ሰፊ ሰብአዊ ጉዳት ሊደርስ ይችላል፡፡ የወያኔ የፖለቲካ ፊትአውራሪዎች ለታሪክና ለትግራይ ህዝብ በእውነት የሚጨነቁ ከሆነ በፍትህ አደባባይ ለመቆም መንፈሳዊ ወኔ መታጠቅ አለባቸው ፡፡ ኢትዮጵያውያን ሁሉ መጠቀም የሚችሉት ከበሳል መሪና ሰላም እንጂ ከጦርነት አይደለም፡፡ የጦርነት ውጤት የህይወት መቅሰፍትና ንብረት ውድመት ብቻ ነው፡፡ ለማናቸውም ቸር ወሬ ያሰማን፡፡

የርስበርስ ጦርነት መጨረሻው ታሪካዊቷን ኢትዮጵያ ብቻ አይደለም የሚጎዳው፡፡ ዳፋው ለቀጠናው ሀገራትም የሚተርፍ ነው፡፡ የጦርነቱ ጊዜ በተራዘመ ቁጥር ኢትዮጵያን ዋጋ ስከፍላታል፡፡ አክራሪ ብሔርተኞችም የጦርነቱን እሳት በሌሎች የኢትዮጵያ ግዛት ለማቀጣጠል እንደማይተኙ ታዝበናል፡፡ እነርሱ ተከባሮ፣ አንቺ ትብሽ በመባባል አንድ ላይ ተፈቃቅሮ ለመኖር የሚደማ ልብ የላቸውም፡፡ ለዚህም ነው በሰሜናዊት ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል   የህግ የበላይነትን ለማስከበር የተጀመረው ጦርነት በፍጥነት መቋጨት አለበት በማለት ኢትዮጵያዊ የህሊና ጋዜጠኞች በብርቱ የሚያሳስቡት፡፡ ዝነኛዋ የፍትህ መጽሔት በአንክሮ እንዳሳሰበችው ‹‹ የአንበጣ መንጋና የክረምቱ ዝናብ አለመመጣጠን ከሚፈጥረው ቀውስ ባሻግር ጦርነቱ ሊያመጣ የሚችለውን ተጨማሪ ችግር ግምት ውስጥ በማስገባት የትኛውንም መንገድ ተጠቅሞ ( የሲቪል ዜጎችን አደጋ ላይ እንዳይወድቁ የሚደረገው ጥንቃቄ እንደተጠበቀ ሆኖ ማለቴ ነው ፡፡) ጦርነቱን መቋጨት የመንግስት እዳ ነው፡፡ ቀውስንና ወንጀልን የሚጠየፉ ዜጎችም ለዚህ ተልእኮ ስኬት የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡ ››

የኢትዮጵያ መንግስት የህግ የበላይነት ለማስከበር የሚያደርገውን ጦርነት በፍጥነት መቋጨት ከተሳነው ወደ ሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ግጭቶችን ለማስፋፋት አሰፍስፈው የከንቱ ከንቱዎች በር ይከፍታል የሚል የግል ስጋት አለኝ፡፡ ይህም ብቻ አይደለም የአፍሪካው ቀንድ ሀገራትም ሰላም ሊናጋ ይቻለዋል፡፡ ሥለሆነም የኢትዮጵያ መንግስት የጀመረውን የህግ የበላይነት የማስከበር ጦርነት በፍጥነት ለመቋጨት መትጋት አለበት፡፡

ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ድርጅቶች፣የኢትዮጵያ ህዝብ፣ የሲቪል ማህበረሰቡ አባላትና መሪዎች የተጀመረው የህግ የበላይነትን የማስከበር ጦርነት ወደየርስበርስ ጦርነት እንዳይቀየር የራሳቸውን ድርሻ መወጣት አለባቸው፡፡ በተለይም በዲፕሎማቲክ ትግሉ መንግስትን ማገዝ አለባቸው፡፡ ጦርነቱን ማን እንደጀመረው፣ የኢትዮጵያ መንግስት የህግ የበላይነት ለማስከበር ጦርነት ውስጥ ስለመዶሉ በተመለከተ፣ ጦርነቱ የሚካሄደው በኢትዮጵያ የፌዴራል መንግስት ወታደሮችና በህውሃት ልዩ ሀይል ታጣቂዎች መሃከል ስለመሆኑ፣ የወያኔ ልዩ ሀይል አባላት በሰሜናዊት ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ድንበር ሲጠብቅ፣ ሰላም ሲያስከብር በነበረው የሰሜን እዝ ወታደሮች ላይ ሳይታሰብ በውድቅት ለሊት ተኩስ በመክፈት ጉዳት ስለማድረሳቸውና ኢትዮጵያን ስለመክዳታቸው፣ በዚህም ምክንያት ጦርነቱ እንደተጀመረ ለውጪው አለም ማስረዳት ያለባቸው ይመስለኛል፡፡

መደምደሚያ

ተቀማጭነታቸው በሰሜን አሜሪካና በአውሮፓ ያደረጉ ሰባት የኢትዮጵያ ሲቪክ ድርጅቶች በጋራ በመሆን የኢትዮጵያ መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር፣  የህወሃት የፖለቲካ ፊትአውራሪዎች ወደ ህግ ፊት ለማቅረብ በትግራይ ውስጥ የጀመረውን ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ የአለም አቀፍ ማህበረስብ ትክክለኛውን ግንዛቤ እንዲጨብጥ፣ ብሎም እንዲደግፍ ባለ ሶስት ገጽ ደብዳቤ ማሰራጨቱን ከተለያዩ ማህበራዊ ድረገጾች ላይ ማንበቤን አስታውሳለሁ። ደብዳቤው ለተባበሩት መንግስታት፣ ለአፍሪካ ህብረት፣ ለአለም አቀፍ ሚዲያ ተቋማት፣ ለልዩ ልዩ አለም አቀፍ ተቋማት እንዲደረ መደረጉንም አንብቤአለሁኝ።

ጦርነቱ በተጀመረ ማግስት የህወሃት/ትነግ የአለም አቀፍ የፕሮፖጋንዳ ማሽነሪ ፣ ሌሎች ጽንፈኛ ሃይሎች፣ ኣንዲሁም ባእዳን ጋዜጠኞችና ምሁራን ጋር በማበር በአለም አቀፍ ደረጃ በሚዲያዎች፣ በፓርላማ አባላት፣ በሶሻል ሚድያ የሚደረግ የተቀነባበረ ዘመቻ በኢትዮጵያ ውስጥ እየሆነ ያለውን፣ ግጭቱ መቼ፣ ለምን፣ ከምን ተነስቶ ለሚሉ ጉዳዮችን በሚመለከት በርካታ የሃስት ትርክቶች ከማስራጨትም አልፎ “የእርስ በእርስ ጦርነት” እንደሆነ፣ መንግስት ተገዶ የገባበት መሆኑ እውነታው ሆኖ ሳለ “ትግራይን ለመውረር” እንደሚደረግ ለማቅረብ የተሄደበትን ውዥንብሮችና ውሸቶችን ርቀት ለማጥራት በማሰብ ድርጅቶቹ በጋር ስብሰባ በማድረግ የተዘጋጀ ደብዳቤ ስለነበር በእኔ በኩል ምስጋናዬን ሳቀርብ በታላቅ አክብሮት ነው። የዚህን ደብዳቤ ይዘት መነሻ በማድረግ የኢትዮጵያ ጉዳይ የሚያሳስባችሁ ኢትዮጵያውያን በምትገኙባቸው ሀገሮች መንግስታት፣ ለጋዜጠኞች፣ ለፓርላማ አባላት፣ ለሲቪክ ተቋማት ፣ በተለይም ጽንፈኞቹና የህወሃት አባላት የውጭ ተባባሪዎች ትኩረት ያደረጉባቸውና ፡ የተሳሳተ ግንዛቤ ያላቸውን፣ የተሳሳተ መግለጫ ላወጡ ልዩ ልዩ የመንግስትና ከመንግስት ውጭ የሚገኙ ተጽእኖ ፈጣሪዎች ፣ እንዲሁም ለሚዲያዎች፣ ጋዜጠኞች በተለያዩ መንገዶች እንድታሳውቁ ሳስታውስ በታላቅ አክብሮት ነው። የኢትዮጵያ መንግስትም ቢሆን በመላው አለም በሚገኙ ኤምባሲዎቹ አማካኝነት የህግ የበላይነትን ለማስከበር ከሚያደርገው ትግል ባሻግር ለአለም አቀፉ ህብረተሰብ የማሳወቁን ሂደት በተጠናና እውቀት መሰረት ላይ ሆኖ ቢቀጥል ውጤታማ ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡

ታሪክ ቦታና ጊዜው ይለይ እንጂ ራሱን ይደግማል። በኢራቅ ጦርነት ወቅት ሳዳም ሁሴን እስራኤልን ወደ ጦርነቱ ለማስገባት ሶቬየት ሕብረት ሰራሽ ስከድ ሚሳይሎቹን ወደ እስራኤል ተኩሶ ነበር ። ይህም ዐረቦች እስራኤል ጦርነቱ ውስጥ ከገባች ይረዱኛል በሚል እሳቤ ነው ። ይህንን ያወቁ እስራኤሎች ወደ ጦርነቱ አልተጎተቱለትም ። ውስጥ ውስጡን ግን መርዳታቸውን አላቆሙም ። ውጤቱም ለእስራኤል አስጊ ያልሆነች ኢራቅን መፍጠር ሆነ።

ዛሬ ደግሞ ወያኔ ኤርትራ ላይ ሮኬት መተኮሱን ከዜና አውታሮች ሰምተናል። ኤርትራን ወደ ጦርነቱ የመጎተት ሙከራ ይመስለኛል ። ከወዲያኛው ሀገር ተመሳሳይ ምላሽ አለመሰጠቱ ብልህነት ይመስለኛል፡፡  ለኤርትራ የፖለቲካ ሰዎቸም  ይህ የሚጠፋቸው አይመስለኝም ። ወያኔ ማን እንዲደግፈው ነው ይህንን የሚያደርገው? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። የዶክተር ቴድሮዎስ አድሃኖም የግብጽ ጉብኝት እውነት ከሆነ ከሰሞኑ እንቅስቃሴው አንጻር የሚጠረጠር ነው። የኢትዮጰያ መንግስትም ይህንን መከታትል ይኖርበታል ብዬ አስባለሁ።

እነ ሳዳም የመጨረሻው ሰአት ላይ ይታዩባችው የነበሩት ባህርዮች ሁሉ ዛሬ ወያኔዎች ላይ እያየናቸው ይመስለኛል ። ጦርነቱን መቀጠል እንደማይችሉ ያወቁትም ይመስለኛል ። የማርያም መንገድም ያጡም ይመስላል። ወያኔ ወደ ስልጣን ለመመለስ በተለያዩ የኢትዮጵያ ግዛቶች የርስበርስ ግጭቶች እሳትን ማቀጣጠል የሚለው የትግል ስልት አለም አቀፍ ፍርድ ቤት የሚያስቀርብ መሆኑን ከማይካድራ በኋላ ተረድተውታል። ለዚህም ነው እስከ መሰዋዕትነት ድረስ እንዋጋለን የሚል መግለጫ ዶክተር ደብር ጽዮን የሰጡት ።

የወያኔ ሁኔታ አሁን ባለው ሁኔታ እዳው ገብስ ይመሰላል። ዋናው ጥያቄ ከድል በኃላ እንዴት ነው ሃገሪትዋ የምትጓዘው? የሚለው ይሆናል። ጊዜው ሲፈቅድ እንመለስበታልን ።

ለአሁኑ ስለሃገሪቱ በጎ የሚያስብ በሰላም ይክረም !

Filed in: Amharic