” ህገ መንግስት” አስቀጥለህ፣ ኦነግን በጉያህ ሸሽገህ ህወሀትን “አሸባሪ” ማለት በንጹሀን ደም መሸቀጥ ነው…!!!
አቻምየለህ ታምሩ
የማይካድራውን ጅኖሳይድና ፍጅት የፈጸመው ሕወሓት በአሸባሪነት እንዲፈረጅ የወሳኔ ሀሳብ ወደ ፓርላማ ተብዮው በመቅረብ ላይ መሆኑን ለማወቅ ችለናል። ማንም ያድረገው ሕወሓትን በአሸባሪነት ለመፈረጅ የሚቀርብ የውሳኔ ሀሳብን እደግፋለሁ። ነገር ግን ኦነግ የሚባለው የሕወሓት የርዕዮተ አለም ወንድምም ከሕወሓት ያላነሰ በንጹሐን ደም የጨቀየና ፖለቲካውን የአማራን ዘር ማጥፋት ያደረገ ወንጀለኛ ድርጅት ነውና ኦነግም ልክ እንደ ሕወሓት ሁሉ በአሸባሪነት ሊፈረጅ ይገባዋል። ከዚህ በተጨማሪ ሁለቱ ድርጅቶች በፈጸሙት ወንጀል ተጠያቂ መደረግ ያለባቸው ለውጥ የሚባለው ነገር ከተጀመረ ጊዜ ወዲህ ወይም በማይካድራው ጭፍጨፋ ብቻ ሳይሆን ከተመሰረቱበት ጊዜ ጀምሮ ባካሄዱት ፍጅትና የዘር ማጥፋት ወንጀል ሁሉ ተጠያቂ ሊሆኑ ይገባል።
ከዚህ በተጨማሪ ሕወሓትንና ኦነግን እንደ ድርጅት ሕወሓትና ኦነግ እንዲሆኑ ያደረጋቸው፤ ተነግሮ የማያልቅ የዘር ማጥፋት ወንጀል እንዲፈጸሙ ያስቻላቸው በፕሮግራም ደረጃ የያዙት የዘር ማጥፋት አስተሳሰብ፣ ሕጋዊ ያደረጉት የአፓርታይድ ደንብ፣ ኢትዮጵያን ያዋቀሩብት ሕገ መንግሥት የሚባለው የወንጀል ሥነ ሥርዓትና መዋቅር የዘረጉለት የአፓርታይድ አሰራር በመሆኑ ሁለቱ ድርጅቶች ሲፈጽሙት የኖሩት አይነት አለማቀፍ ወንጀል ወይም የማይካድራው አይነት የዘር ማጥፋትና ፍጅት ድጋሚ በንጹሐን ዜጎች ላይ እንዳይፈጽም ለማድረግ ሁለቱ ድርጅቶች ሕጋዊና ተቋማዊ ያደረጓቸው አስተሳሰቦች፣ የአፓርታይድ ደንቦችና ካልተተገበረ ሞተን እንገኛለን የሚሉለት ሕገ አራዊት ጭምር አብረው ሊታገዱና ከድርጅቶቹ ጋር ሊከስሙ ይገባል።