* … ልክ በዚህ ሰሞን በህዳር አጋማሽ… ነገር ግን እንደኢትዮጵያ አቆጣጠር 1892 ዓ.ም ምኒልክ ለትግራዩ ራስ መንገሻ ዮሃንስ ይህን ደብዳቤ ጻፉላቸው። ደብዳቤውን ከማስነበባችን በፊት ግን ደብዳቤው የተጻፈበትን ምክንያት እንንገራቹህ። ራስ መንገሻ ዮሃንስ የአጼ ዮሃንስ ልጅ ናቸው። አባታቸው ከሞቱ በኋላ ትግራይን የበላይ ሆነው እንዲገዙ በአጼ ምኒልክ ተሾሙ።
እስከ1888ቱ የአድዋ ጦርነት ድረስ ከኢትዮጵያ ጦር ጋር በመሆን አገለገሉ። የአድዋ ድል አንድ አመት እንኳን ሳይሞላው፤ ራሳቸውን ንጉሥ ብለው ከኢትዮጵያ መንግስት እውቅና ውጪ ከጣሊያን መንግስት ጋር ግንኙነት ማድረግ ጀመሩ። ለንጉሥ ምኒልክም “አልገዛም” አሉ። በዚህን ጊዜ የኢትዮጵያ ሰራዊት ትግራይ ድረስ ዘምቶ፤ ጦርነት ለማድረግ ተዘጋጀ::
ልክ በዚህ ሰሞን ነው። የትግራዩ ዋና ገዢ የአጼ ዮሃንስ ልጅ፤ ራስ መንገሻ ለማዕከላዊ መንግስት “አንገዛም!” ብለው አሻፈረኝ አሉ። በዚህን ጊዜ የአገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች መቀሌ ድረስ የእርቅ ደብዳቤ ይዘው ሄዱ። ከሞላ ጎደል ደብዳቤው እንዲህ የሚል ነበር።
ይድረስ ለራስ መንገሻ። ወልዱ ዮሃንስ ንጉሠ ጽዮን ።
የተላከ ከመምህራን ወሊቃውንት፣ ዘደብረሊባኖስ ወኩሉ አድ ያሚሃ ለብሔረ ሸዋ።
“…እግዚአብሔር ቸርነቱን አያርቅብዎ ብለን እጅ እንነሳለን። ይህ የሰማነው ነገር እጅግ አሳዘነ። የኛ ድካም የመንገዱ ርቀት ነው እንጂ፤ እኛንም ሁላችንንም የሚያስመጣ ነበር። አሁንም ይህን የጻፍንልዎን ወረቀት በንጹህ ልቦና ይቀበሉን። ቃሉም ይህ ነው።
(ራስ መንገሻ ዮሃንስ ለኢትዮጵያ ያደረጉትን መልካም ነገር ይዘረዝርና ደብዳቤው እንዲህ ይቀጥላል)
“…ያው የአጼ ዮሃንስ እርግማን እስከዛሬ ድረስ ከትግሬ ሰው ላይ አልተነሳምና እርስዎን በጤና አላስገዛም ብሎ እንጂ፤ ሌባ ቀማኛ፣ ወንበዴ፣ በጠፋበት ጊዜ፤ ሴት ልጅ ወርቅ በራስዋ አድርጋ ብትሄድ በማትነካበት፣ ሰው እና እህል በተስማማበት ጊዜ፤ ዳር እስከ ዳር አገሩ ሁሉ ጸጥ ብሎ በተገዛበት ጊዜ፤ በስሜን፣ በቤጌምድር፣ በጎጃም ነቅዕ አልወጣ፤ደርቡሽ እንኳን በእግዚአብሔር ቸርነት ባገራችን ብቅ አላለም። እንደርስዎ ያለ ሰው የጌታ ልጅ ለበጎ አርአያነት አብነት ይሆናሉ እንጂ፤ ከዚህ መካከል ራስ መንገሻ ከዳ ሸፈተ ይባላሉን?
“አጼ ምኒልክ እንደፈጣሪ ቸር ናቸው እንጂ፤ ክፉ ነገር መቼ በሰው ይሰራሉ? ይህንን ሰይጣን ያነቃውን እናጥፋው። ክንፉን እንስበረው። ስለተሰቀለው ጌታ፣ ስለ ኩርአተ ርዕሱ ብለው ይተዉልን።” በማለት ትላልቅ ሽማግሌዎች እና አባቶች ትግራይ ድረስ ተጉዘው፤ መስቀል ተሸክመው፤ መስቀሉን ይዘው ከፊታቸው ተደፍተው ሲለምኗቸው ራስ መንገሻ ዮሃንስ ግን ሳቁባቸው።
ከዚያም አጼ ምኒልክ ለትግራይ ህዝብ ይህን ደብዳቤ ላኩ።
“ስማ የትግሬ ሰው!
”ራስ መንገሻን ብሾመው ከዳኝ። አሁን ደግሞ እሾሁን ነቅዬ፣ አደላድዬው ብመጣ እኔን አባቱን ከዳኝ። የትግሬ ሰው አድባራቱም፣ መኳንንቱም፣ ራስ መንገሻን ስወደው ጠልቶኛልና ግፌን እይልኝ። እኔ ግን የአጼ ዮሃንስ ወረታ እመልሳለሁ ብዬ መኳንንት እና ወታደር ሳይወደው በግድ ሹሜው ነበር። መሬት አሰናበተችው እንጂ እኔ በድየው አይደለም። አሁንም የትግሬ ሰው ወዳጄ ነህ። ራስ መንገሻ ከዳኝ ብዬ በሱ ተናድጄ አላጠፋህም። እግዚአብሔር የሰጠኝን አገሬን በጄ አድርጌ አለማዋለሁ። ደስ አሰኝሃለሁ። አይዞህ ግባ በያባትህ እተክልሃለሁ። አባትህን እርገም፤ አባትህን መርቅ።” የሚል አዋጅ አስነገሩ።
ከዚያም ራስ ሚካኤል እና ራስ መኮንን ጦራቸውን ይዘው ወደ መቀሌ አመሩ። ሆኖም ራስ መንገሻ መቀሌን አጥፍተው ወደ እዳጋሃሙስ በመሄድ ጣሊያን አሰርቶት ከነበረው ምሽግ ውስጥ ተቀመጡ። ራስ ሚካኤል እና ራስ መኮንን እዳጋ ሃሙስን ከበው፤ ራስ መንገሻ እጃቸውን እንዲሰጡ በድጋሚ ጠየቋቸው። ራስ መንገሻ ግን አሁንም እጃቸውን ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተው ለመዋጋት ተዘጋጁ። አራት ሺህ ያህል ጠመንጃ የያዙ የራስ መንገሻ ወታደሮች በአጋሜ በኩል ትንሽ ውጊያ አደረጉና እየሸሹ ወደ እዳጋ ሃሙስ ሄደው መሸጉ።
ከዚያ በኋላ የሆነው ነገር ያስገርማል። በስፍራው የነበሩት ጸሃፌ ትዕዛዝ ገብረስላሴ ስለመጨረሻዋ ሰአት እንዲህ ብለው ጽፈዋል። “የአስ መንገሻ ዮሃንስ ጦር ከሰፈረበት ምሽግ አጠገብ ትልቅ ተራራ ነበር። በሰማይ ደመና ሳይዞርና ዝናብ ሳይኖር በጠራራ ፀሃይ ከቀኑ በ6፡00 ሰዓት ሲሆን ትልቁ ተራራ ምንም ሳይነካው መናድ ጀመረ። የተቀመጡበት መሬት እንደከዳቸው ያኔ አወቁ። ተራራ እና ገደሉ በተናደበት ወቅት እነ ራስ መኮንን ሰፈር ድረስ ተሰማ። በዚህን ጊዜ ‘ጦር መጣ ይሆን? የመድፍ ተኩስ ነው?’ በማለት ጦር ሰራዊቱ ታጥቆ እና ተዘጋጅቶ መጠበቅ ጀመረ። ሆኖም የመሬቱ ጩኸት ለአንድ ሰአት ያህል ቆየ።” በማለት በወቅቱ የሆነውን ገልጸዋል።
እናም የራስ መንገሻ ዮሃንስን ወታደሮች ገደል ተጎድጉዶ፣ ተራራ ተንዶ እግዚአብሔር ፈጃቸው። ያለምንም ጦርነት፤ ራስ መንገሻ ከዚህ መአት ተርፈው፤ “እጄን ሰጥቻለሁ።” ብለው፤ ተማርከው ወደ አዲስ አበባ ለፍርድ ተወሰዱ። በወቅቱ አገራቸውን በመክዳታቸው በዚህ ወንጀል ተከሰው፤ አማላጅ ሽማግሌዎች ቢላኩባቸውም እምቢ ብለው ለጦርነት በመዘጋጀታቸው፤ በአገር ክህደት ጥፋት ተከሰሱ።
መጀመሪያ ላይ ራስ መንገሻ ዮሃንስ ፍትሃ ነገሥት ተጠቅሶ፤ ልከሰስ አይገባም። ጉዳዬን ዳኞች ይዩልኝ ብለው አስቸገሩ። ከዚያም እሳቸው ባሉ መሰረት ፍትሃ ነገሥቱ ሳይጠቀስ፤ ግራና ቀኙ ዳኞች ጉዳዩን በፍርድ ችሎት ተመለከቱ። በመጨረሻ በፍርድ ቤት ክርክር ከተረቱ በኋላ፤ እስር ተፈረደባቸው። ከዚህ በኋላ በተደጋጋሚ ለአጼ ምኒልክ የምልጃ መልዕክቶችን ላኩ። ከዚያም አጼ ምኒልክ የሚከተለውን ደብዳቤ ለራስ መንገሻ ላኩላቸው።
ይድረስ ከልጄ ከወዳጄ ራስ መንገሻ
ከድቼ ከሆነ አደባባይ አይቶት እንደገና በብርቱ እስራት ልቀጣ” ብለህ ላክብኝ። አገርህንስ ትግራይን የተሻርክበት አንተስ እስካሁን ከኔ የተለየህበት፤ ከፍቃዴ ብትወጣ ብትከዳኝ ነው እንጂ፤ ያለዚያማ ይህ ሁሉ ለምን ተደረገ? …ደግሞስ እነራስ ሚካኤል፣ እነራስ መኮንን ትግራይ ድረስ የዘመቱት ባንተ ክዳት ነው እንጂ ማንን ሊፈልጉ ትግራይ ድረስ ሄዱ?” በማለት ልክ በዚህ ሳምንት በህዳር ወር አጋማሽ ነገር ግን እንደኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1892 ዓም. ጻፉ።
በነገርዎ ላይ… ራስ መንገሻ ዮሃንስ፤ በአንኮበር እስር ቤት ሳሉ በ42 አመታቸው ህዳር 6 ቀን 1899 በሞት ተለዩ።