>

የኢትዮጵያ ነባራዊ የፖለቲካ ሁኔታ በእኔ እይታ (ደረጀ መላኩ - የሰብአዊ መብት ተሟጋች)

የኢትዮጵያ ነባራዊ የፖለቲካ ሁኔታ በእኔ እይታ

ክፍል አንድ

ደረጀ መላኩ ( የሰብአዊ መብት ተሟጋች)

Tilahungesses@gmail.com


ለብሄራዊ ውይይት ይበጅ ይሆን በሚል ቀና መንፈስ በታማኝት የቀረበ አስተያየት

እንደ መግቢያ  

በአንዳንድ አካባቢ የበቀሉ አክራሪ የጎሳ ቡድን ታጣቂዎች የሚፈጽሙት አስከፊ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ( በምእራብ ወለጋ ደምቢዶሎ አካባቢ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተክል ዞን ይጠቀሳሉ፡፡) የኢትዮጵያን የፖለቲካ አቅጣጫ ከድጡ ወደ ማጡ ስለመዶሉ ሁነኛ እና ተጨባጭ ማሳያዎች ናቸው፡፡

በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች ጎሳን መሰረት ባደረጉ ግድያዎች የተነሳ ኢትዮጵያ ተጨንቃለች፡፡ በአንዳድ አካባቢዎች የድንበር ይገባኛል ጥያቄዎች መልስ አልተገኘላቸውም፡፡ የምጣኔ ሀብት ችግሮች አሁን ደርስ ሰራሄ መፍትሔ አልተገኘላቸውም፡፡ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ከመቼውም ጊዜ በላይ ኢትዮጵያን ለማዳከም የማይቆፍሩት ጉድጓድ የማይቆርጡት ቅጠል የለም፡፡ የኢትዮጵያን አንድነት ለማዳከም የትግራዩ ነጻ አውጪ ድርጅት እና በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ አክራሪ ጎሰኞች እንቅልፍ አጥተው ማደር ከጀመሩ ውለው አድረዋል፡፡

ሁላችንም ( ኢትዮጵያውያን ሁሉ ማለቴ ነው) የምንኖረው በችግር መሃል ላይ ነው፡፡ የገጠመን ችግር በምንም አይነት ሚዛን ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ከፊታችን የተደቀነው ችግር እጅጉን ከባድ ነው፡፡ ይህ ቸግር በየጊዜው አፈር ድሜ እያስጋጠን ነው፡፡ ህይወታችንን አደጋ ላይ ጥሎታል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም የምንወዳትና እትብታችን የተቀበረባትን እናት ኢትዮጵያን አንድነት እየተፈታተነ ነው፡፡ ለገጠመን ስር የሰደደ ችግር ሰራሄ መፍትሔ ለማግኘት የማንንም እርዳታ አንፈልግም፡፡ የማንንም ሀገር ደጅ መጥናት ያለብን አይመስለኝም፡፡

ለገጠመን መሰረታዊ ችግር ተጨባጭ መልስ ለማግኘት ወደ ውጭ ወደ ሌላ ሀገር ማንጋጠጥ ያለብን አይመስለኝም፡፡ በመሬት ላይ ያለው እውነታ፣ በኢትዮጵያ ምድር የሚታየው መከራና ግፍ እራሱ መፍትሔ እንድንፈልግ ያመላክተናል፡፡ ከእኛ የሚጠበቀው ዋናው ቁምነገር እውነታውን መረዳት ብቻ ነው፡፡ በመሬት ላይ ያለውን እውነተኛ ችግር ምንም ሳንቀባባ መረዳት ነው፡፡ ይህን ለማድረግ መንፈሳዊ ወኔ ከታጠቅን ለገጠሙን ችግሮች እውነተኛ መፍትሔ ማምጣት ይቻለናል፡፡ ለአብነት ያህል በአንድ አካባቢ አክራሪ ጎሰኞች ጎሳን መሰረት ያደረጉ ፍጅቶች ከፈጸሙ በኋላ በሁለት ጎሳዎች መሃከል በተቀሰቀሰው ግጭት ምክንያት የበርካታ ሰዎች ህይወት አለፈ፣ ንብረቶች ወደሙ፣ መንግስት ግጭቱ ወደተከሰተበት ስፍራ በፍጥነት በመንቀሳቀስ የአካባቢው ሰላም ወደ ቀደመው ሁኔታ ተመልሷል ወዘተ የሚሉ ዜናዎች ወደ መፍትሔው አይወሰዱንም፡፡

ለችግሮቻችን ዘላቂ መፍትሔ ለማግኘት ከፈለግን ለምናስበውና ለተግባራችን መሬት ላይ ካለው እውነት መራቅ የለብንም፡፡ ምክንያታዊና እውነተኛ ሰዎች፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ ምድር ላይ ስላለው እውነት እና ተጨባጭ ሁኔታዎች መረዳት አለብን፡፡ ስሜት ወይም አድርባይነት ለችግሮቻችን መፍትሔ አያስገኙልንም፡፡ ከዚህ ባሻግር ተጨባጭ እወነታዎችን ለራስ ጥቅም ወይም በጥላቻ መንፈስ እንዲጠመዱ መፍቀድ የለብንም፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የራስን ጥቅም ብቻ ማስቀደምና የጥላቻ መንፈስ ወደ የተሳሳተ ድምዳሜ እንደሚወስዱን ማወቁ ተገቢ ነው፡፡

በነገራችን ላይ የፖለቲካ መልካም ፈቃደኝነት ችግሮቻንን ለመፍታት ከሚረዱን ነገሮች አንዱና ዋነኛው መሆኑን ማወቅ ያለብን ይመስለኛል፡፡ አሁን ለገጠመን ከባድ ችግር መፍትሔ ለመስጠት ያስችላቸው ዘንድ ዋነኞቹ ውሳኔ ሰጪ አካላት ስምምነት ላይ መድረስ አለባቸው፡፡ የፖለቲካ መልካም ፈቃደኝነት መሬት ላይ ከሚገኘው ችግር ጋር የሚጣጣም ከሆነ ለችግሮቻን መፍትሔ ለማስገኘት ይረዳል፡፡ ለአብነት ያህል የኢትዮጵያ መንግስት የጎሳ ፖለቲካ ደርጅቶችን በጎሳ መደራጀት የሚከለክል ህግ ለማውጣት መንፈሳዊ ወኔ ቢታጠቅ ለኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ችግሮች ጥርጊያ መንገድ የሚከፍት ይመስለኛል፡፡

እኛ ፎቶ ኮፒ መሆን የለብንም፡፡ እውነተኞች መሆን ይገባናል፡፡ የእኛ ትንተና እና አስተሳሰብ የሌሎች ጥገኛ መሆን የለበትም፡፡ ራሳችንን መግዛት አለብን፡፡ ውሳኔአችን በሌሎች ተንኮለኞችና መሰሪዎች እኩይ በሆኑ ግለሰቦች መበከል የለበትም፡፡ በሌሎች ደካሞች ሀሳብ መጠለፍ የለብንም፡፡ በራሳችን ውሳኔ ለመገዛት፣ በእውነተኛ ሀሳባችን ለመጽናት ከፈለግን በራሳችን መተማመን ግዴታችን ነው፡፡ በሁለት ቢለዋ መቁረጥ መቀመቅ አወረደን እንጂ አልጠቀመንም፡፡ ምክንያታዊ ያልሆነና ያልተጠና የሌሎች ሰዎች መሰሪ ሀሳብ አይጠቅመንም፡፡

ሀገራችንን ከአንገት ሳይሆን ከልባችን እንውደዳት፡፡ አንድን ሀገር መውደድ ስሜታዊ ብቻ ሳይሆን ምክንያታዊም ጭምር ይመስለኛል፡፡ እኛ ማን እንደሆንን፣ የእኛ ማንነት የተጋመደው ከሀገራችን ጋር ነው፡፡ አንድ ግለሰብ ሀገሩን ሊከዳ ወይም በህጋዊ መንገድ ዜግነቱን ሊቀይር ይቻለዋል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ከተወለደበት፣ እትብቱ ከተቀበረበት ሀገር ስረ መሰረቱን መቀየር በፍጹም አይቻለውም፡፡ ሀገር በሰውነታችን ውስጥ በጥልቅ የተቀመጠ ነው፡፡

ሀገራችንን በጎሳ ማንነታችን መተካት ወይም መቀየር አይቻለንም፡፡ ብዝሀነታችን ውበታችን ነው፡፡ በአንድ ሀገር ብዝሃነትን ማየት ውበት ብቻ ሳይሆን ለአንድነታችንም ደንቃራ ሊሆን አይቻለውም፡፡ ከብዝሀነታችን ባሻግር ለአንድነታችን ቅድሚያ መስጠት ተገቢ ሳይሆን አይቀርም፡፡ በሀገራችን የፖለቲካ እንቅስቃሴና ዲሞክራ እውን መሆን የሚቻለው ሰላምና ፍቅር ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ከጎሳ ከረጢት ውስጥ ሰብረን( ቀደን) በመውጣት የሀገራችንን ሉአላዊነትና አንድነት ማስቀደም የቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ መሆኑን በፍጥነት መረዳት ያለብን ይመስለኛል፡፡

. Let us break out from our ethnic cocoon and prioritize the unity and sovereignty of the country.

ኑሮአችን የተመሰረተው ወይም የተያያዘው በአንድ ክልል ከሚኖሩ የጎሳ አባላቶቻችን ጋር ብቻ ሲሆን እውን አያሳዝነን ይሆን ?

        የኋላ ታሪክ ( Background )

ከሁለት አስርተ አመታት በላይ ኢትዮጵያን ይገዙ የነበሩት ጨቋኞች ነበሩ፡፡ ውጤቱ በግዜው ባይታወቅም በ2008 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ህዝብ ኢህአዲግን ገርስሶ ለመጣል ታግሏል፡፡ መስእዋትነትም ከፍሏል፡፡ ይህን ተከትሎ ከራሱ የኢህአዲግ አጋር ድርጅቶች ውስጥ የለውጥ አራማጅ በመሆን ብቅ በማለት የህዝቡን ጥያቄዎች ለመመለስ ዝግጁ ነን በማለታቸው በኢትዮጵያ ህዝብ ይሁንታ እንደተሰጣቸው እናስታውሳለን፡፡

ከሁለት አመት በፊት የተከሰተው የፖለቲካ ለውጥ የፖለቲካ ነጻነትን ያስገኘም ነበር፡፡ ለአብነት ያህል የፖለቲካ ነጻነቱ በውጭ ሀገር በነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፣ ማህበራዊ ደርገጾች፣ የፖለቲካ አክቲቪስቶች ላይ ተጥሎ የነበረውን ማእቀብ ከማንሳቱ ባሻግር በርካታ የፖለቲካ እስረኞች ከእስር ቤት እንዲወጡ፣ በፕሬሱ አንገት ላይ የነበረውን ሸምቀቆ ማላላቱ የታወቀ እውነት ነበር፡፡

ሆኖም ግን ይሁንና የፖለቲካ ነጻነቱ እውን የሆነው በህገመንግስቱ መሰረት ነበር፡፡ ይህ ህገመንግስት ደግሞ  ድረስ እንዲሻሻል በርካታ ምሁራን ይጠይቃሉ፡፡ እንዴት መሻሻል እንዳለበትም ኢትዮጵዊ ምሁራን በርካታ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡበት ጉዳይ ነው ፡፡ ሰሚ ግን አልተገኘም፡፡ ይህ ህገመንግስት የተረቀቀው በዋነኝነት በወያኔና ጋሻ ጃግሬዎቹ ነበር፡፡ ይህ ህገመንግስት መሰረታቸውን በጎሳ ላይ ያደረጉ የፖለቲካ ድርጅቶች እንደ አሽን እንዲፈሉ የሚፈቅድ በመሆኑ የሀገሪቱን አንድነት አደጋ ላይ የሚጥል እንደሆነ እንደ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ( ነብሳቸውን ይማር)፣ ፕሮፌሰር ጌታቸው ሀይሌ፣ ዶክተር ታዬ ወልደሰማያት፣ ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳና ሌሎች በርካታ ኢትዮጵያዊ ምሁራን አይናቸው ደም እስኪመስል፣ እጃቸው እስኪዝል ምክረ ሀሳባቸውን አቅርበው ነበር፡፡ ሰሚ ጆሮ አግኝተው ይሆን መልሱን ህሊና ለፈጠረባችሁ ኢትዮጵያውያን ትቼዋለሁ፡፡ በሌላ የሳንቲሙ ግልባጭ የሚገኙ እንደ ፕሮፌሰር አንድርያስ፣ ፕሮፌሰር መራራ ጉዲና ፣ አቶ በቀለ ገርባ፣ ወዘተ ወዘተ የጎሳ ፖለቲካ ደርጅቶች እውን እንዲሆን የሚፈቅደው የህገመንግስቱ አንቀጽ መነሳት የለበትም ባይ ናቸው፡፡ የችግሩ ገፈት ቀማሽ የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ በነጻነት ሀሳቡን የሚያቀርብበት፣ ድምጸ ውሳኔውን ለማሰማት እድሉን ማግኘት አልተቻለውም፡፡ ከዚህ ባሻግር በህገመንግስቱ መግቢያ ላይ የተጻፈው ትኩረት ሰጥቶ ለሚያነበው ግለሰብ ግራ አጋቢ ነው፡፡ ወያኔ የኢትዮጵያን የረጅም ዘመን ታሪክን ከድቷል፡፡

ህገመንግስቱ የኢትዮጵያን የረጅም ግዜ ታሪክ ዘንግቶታል ወይም ሆን ብሎ አልጠቀሰውም፡፡ ቁጥሩ ቀላል የሚባል ኢትዮጵያዊም ቢሆን ህገመንግስቱን በጥልቀት የፈተሸ አይመስለኝም፡፡ ወይም የሚያውቀው አይመስለኝም፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያ ህዝብ ህገመንግስቱን በተመለከተ ያለውን ሀሳብ በነጻነት እንዲያቀርብ መንግስት መድረኩን እንዲያዘጋጅ ሳስታውስ በአክብሮት ነው፡፡ ይህ የህጎች ሁሉ የበላይ የሆነው የህግ ሰነድ የእያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ ህይወት የሚነካ በመሆኑ ኢትዮጵውያን ሁሉ መምከር አለባቸው ባይ ነኝ፡፡

በእኔ የእውቀት ደረጃ ለመገንዘብ እንደቻልኩት በኢትዮጵያ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሃከል፣ እንዲሁም በብዙ ምሁራን መሃከል ያለው መሰረታዊ ልዩነት የሚያጠነጥነው በህገ መንግስቱ ላይ ነው፡፡ ከተሳሳትኩ ልታም ዝግጁ ነኝ፡፡ ከዚህ ባሻግር መሰረቱን ጎሳ ወይም ቋንቋ ማንነት ላይ ባደረገው የጎሳ ፌዴራሊዝም ሥርአቱ ላይ እንዲሁ ልዩነቱ ሰፊ ነው፡፡

ከ 2010 ዓ.ም. ወዲህ ማእከላዊ መንግስቱን የተቆጣጠረው የኢትዮጵያ መንግስት የህዝብን ቅሬታ መሰረት በማድረግ አንዳንድ የመዋቅር ለውጦችን ማድረጉ የሚካድ አይደለም፡፡ ለአብነት ያህል በመከላከያ እና በጸጥታ ተቋማት ውስጥ የመዋቅር ለውጥ ስለመደረጉ ከመገናኛ ብዙሃን ሰምተናል፡፡ በተለይም በመከላከያ ሰራዊት ውሰጥ የኢትዮጵያ ጎሳዎችን ስብጥር  ተመጣጣኝ ለማድረግ በርካታ ስራዎች ስለመከወናቸው የሚመለከታቸው የመከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ የጦር መኮንኖች በየጊዜው በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብለው ከሚሰጡት ቃለ ምልልስ የተረዳን ይመስለኛል፡፡

የእኛ ሀገር የተመሰረተችው  የራሳቸው ህገ መንግስት፣ የራሳቸው የአካባቢ ሚሊሻ ወይም ልዩ ሀይል ባላቸው ( አሁን ባለው የፌዴራል አወቃቀር ማለቴ ነው) ጎሳን መሰረት ባደረጉ አስር ክልሎች ነው፡፡ከዚህ በመነሳት የአካባቢ ልዩ ሀይል አባላት ከክልላቸው አልፈው ለኢትዮጵያ የሚደማ ልብ አላቸውን ብለን መጠየቅ ያለብን ይመስለኛል፡፡ 

ለአብነት ያህል የማእከላዊው መንግስት ህግን እና የህግ የበላይነትን ለማስከበር ሲል በአንድ የጎሳ አስተዳደር መሪዎች ላይ ህጋዊ ወታደራዊ ዘመቻ ለመክፈት ቢነሳ እውን የክልሉ ልዩ ሀይል ታማኝነቱ ለሀገሪቱ ነው ወይንስ ለክልሉ መንግስት ? መልሱን ህሊና ለፈጠረባችሁ ትቼዋለሁ፡፡ በእን በኩል ይህ የሚያም እውነት አለው ብዬ አስባለሁ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ሁላችንም ድምጻችንን ከፍ አድርገን ማሰማት ያለብን ይመስለኛል፡፡ ዝምታ የበለጠ መጥፎ ነው፡፡ ሁሉም የታፈኑ እውነቶች ወደ መርዝነት ይቀየራሉ፡፡

እኛ የምንኖረው በአደገኛ የጎሳ ፖለቲካ ከባቢ አየር ውስጥ ነው፡፡ ስለሆነም በየክልሉ የሚገኙ የልዩ ሀይል አባላት ያላቸውን የስነ ልቦና ሁኔታ እና ለየጎሳ አባሎቻቸው ያላቸውን ታማኝነት በተመለከተ ( ለኢትዮጵያ ስላላቸው ታማኝነት ጋር በማነጻጸር ማለቴ ነው) ችላ ማለት የደካማነትን ባህሪ የሚያሳይ ነው፡፡ በተመሳሳይ መልኩ የሀገር መከላከያ ሰራዊታችንን ብሔራ ስሜት በተመለከተ ኢትዮጵያውን ሁሉ መገንዘብ ያለብን ይመስለኛል፡፡ ከዚህ ባሻግር አሁን ያለው የኢትዮጵያ የፌዴራል ስርአት የጥንታዊት ኢትዮጵያን ታሪክ ስለመዘከሩ መመርመር ኢትዮጵያዊ ግዴታችን ነው ብዬ አስባለሁኝ፡፡

በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ መንግስት የፖለቲካ ነጻነትን በመፍቀዱ ሊመሰገን ይገባዋል፡፡ ምስጋናው ሞራላዊና ስነምግባራም ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ውጤቱ ሲታይ ፣ ይህንኑ የፖለቲካ ነጻነት ተገን በማድረግ በብዙ የሀገሪቱ ክፍሎች ችግሮችና መዘዞችን ይዞ ብቅ ብሏል፡፡ በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች ህግ የማይገዛቸው፣ የጎሳ አክራሪዎች፣ ብረት አንጋቾች እንደ እንጉዳይ ፈልተዋል፡፡ አክራሪ ጎሰኞች፣ በብዙ የሀገሪቱ ክፍሎች ዜጎችን ያፈናቅላሉ፣ይገደላሉ፣ ንብረት ያወድማሉ፡፡ በአንዳንድ የጎሳ ክልሎች ተደጋጋሚ የዜጎች መፈናቀል እንደሚከሰት የታወቀ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ መንግስት የዜጎችን የሰብአዊ መብት ለማስከበር የመዘግየት ሁኔታ ስለሚታይበት( ፈጣን ምላሽ ስለማይሰጥ) በብዙዎች ዘንድ ወቀሳ ሲደርስበት ይሰማል፡፡ ይህም በነቢብም በገቢርም የሚስተዋል መራር እውነት ነው፡፡

ሁላችንም እንደምናውቀወ የወያኔ ቡድን የህዝቡን ስነ ልቦና ወደ ራሳቸው አጀንዳ በመለወጥ ለመጠቀም ይሞክራሉ፡፡ እነርሱ በውሸት ፕሮፓጋንዳ በታጨቀ ቅስቀሳቸው ህዝቡ ለማንነቱ ክብር ሲል መዋጋት አለበት በማለት ይሰብካሉ፡፡ የእኛ ጎረቤት የሆነው ክልላዊ መስተዳድርና የማእከላዊ መንግስቱ ክልላችንን አደጋ ላይ ሊጥሉ ነው የሚሉ እና ሌሎች ቅስቀሳዎችን ያደርጋሉ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፈው ክረምት በትግራይ ክልል የተካሄደው የምርጫ ውድድር ከሀገሪቱ ህገመንግስት ተጻራሪ በሆነ መልኩ የተካሄደ ነበር፡፡ ከዚህ የምንረዳው ቁምነገር ቢኖር ለኢትዮጵያ አንድነት ስጋትን የሚያመጣ መሆኑን ነው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በግብጽ፣ ዲጂቡቲ፣ ሶማሌ ላንድ፣ሶማሊያ፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን ምድር ውስጥ የሚደረጉ የፖለቲካ ወታደራዊ እንቅስቀሴዎች ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ በጎረቤት ሀገራት ስለሚገኙ ወታደራዊ ቤዞችም በተመለከተ መጨነቅ ወይም መገምገም ያለባት ይመስለኛል፡፡ ከዚህ ባልተናነሰ መልኩ የአክራሪ ሽብረተኞች እንቅስቃሴ በጎረቤት ሀገራት እና በኢትዮጵያ ምድር ስለሚያስከትለው ዳፋም በተመለከተ በትኩረት መከታተል ያለባት ይመስለኛል፡፡

ያለምንም ማገነን የምንገኝበት የጂኦፖለቲካል አቅጣጫ ለግጭት የተጋለጠ ነው፡፡ ይህ አካባቢ የአፍሪካው ቀንድ ማለቴ ነው ብዙ ሀገሮች ሀይላቸውን ለማሳየት የሚሞክሩበት የአለም ክፍል ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ይህ የአለም ክፍል የጸጥታ ስጋት አለበት፣ የፖለቲካ አለመረጋጋትም ይታይበታል፡፡

የሀገራችን የውጪ ፖሊሲ ዘመኑን የዋጀ፣ በአለም አቀፍ የትምህርት መስክ ሰፊ እውቀት ያላቸው ኢትዮጵያውያን የተዘጋጀ ቢሆን መልካም ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ የኢትዮጵያን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የሚያረቁና የሚያዘጋጁ ምሁራን የኢትዮጵያን የጸጥታ ችግሮችና የደህንነት ስጋቶችን በተመለከተ በጥልቀት ቢያጠኑ መልካም ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

የመንግስት ድክመት ተጠቃሎ ሲቀመጥ

  1. መንግስት ህግ ማስከበር፣ የሀገሪቱን ብሔራዊ ጸጥታና የዜጎቹን ደህንነት መጠበቅ መንግስታዊ ግዴታው ነው

በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍል የሚኖሩ ኢትዮጵያዊ ዜጎች ( ለአብነት ያህል በጉራፈርዳ፣ በምእራብ ወለጋ አንዳንድ አካባቢዎች፣ በቤኒሻንጉል ክልል መተክል ዞን ወዘተ ወዘተ) የሰብአዊ መብት ጥሰት ሳይፈጸምባቸው በፊት መንግስት ሊደርስላቸው ባለመቻሉ የተነሳ መንግስት የዜጎችን ሰብአዊ መብት ለመጠበቅ ወይም ለመከላከል ትኩረት አልሰጠውም በሚል በብዙ ኢትዮጵያወያን ዘንድ ሲወቀስ ይስተዋላል፡፡ የገፈቱ ቀማሽ የሆኑ ኢትዮጵያውያን በአንዳንድ መገናኛ ብዙሃን እየቀረቡ በመንግስት ቁታቸውን ሲያሰሙ መስማት ወይም መመልከት ብርቅ አይደለም፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና መንግስት በተለይም ከላይ በጠቀስኳቸው የሀገሪቱ ክፍል አክራሪ ጎሰኞችና ብረት አንጋቾችን ድራሻቸውን ማጥፋት የተቻለው አይመስለኝም፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያ መንግስት በማናቸውም የሀገሪቱ ክፍሎች የሚኖሩ ዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ መንግስታዊ ግዴታውን መውጣት አለበት የሚለው የግል አስተያየቴ ነው፡፡ በነገራችን ላይ አንዳንድ የውጪ ሀገር እና ኢትዮጵያዊ ምሁራን ያዘጋጁትን የምርምር ጽሁፎች ለማንበብ ሞክሬአለሁ፡፡ እነኚሁ ምሁራን

 መንግስት የመጀመሪያ ዋነኛ ሀላፊነቱን አልተወጣም ከሚል ምክንያት ተነስተው በደረሱበት ድምዳሜ ‹‹ ኢትዮጵያን ከወደቁ ሀገራት ተርታ መመደባቸው ›› ስህተት ይመስለኛል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ችግሮች እየተባባሱ ከመጡ የተፈራው እውን ሊሆን ይቻለዋል፡፡

በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች ለተለያዩ ስራዎች መንቀሳቀስ ለአደጋ ይጋብዛል፡፡( ለአብነት ያህል በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል  መተክል ዞን ሰዎች ከቦታ ወደ ቦታ በሰላም መንቀሳቀስ እንዳልቻሉ የሚያሳዩ አሳዛኝ ዜናዎች መስማት የተለመደ ነው፡፡) በተጠቀሰው ክልል አዋጅ ሳይታወጅ (is unofficially sanctioned.  ) የመዘዋወር ነጻነት የተከለከለ ይመስላል፡፡ እንደ ጉራፈርዳ ፣ መተክል ዞን አካባቢ ከሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች የመጡ ዜጎች ነግደው ወይም አርሰው ለመኖር ሥጋት ውስጥ ከተዶሉ ሰነበቱ፡፡ ከጎሳ ፖለቲካ የተረፈን ውርስ ( እንደ ውርስ ከተቆጠረ ማለቴ ነው፡፡ ) የዜጎች ፍጅትና ንብረት ውድመት ብቻ ነው፡፡

በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች መንገዶችን እየዘጉ የሰው ህይወት የሚያጠፉ፣ ንብረት የሚዘርፉ ነብሰ በላዎች ሞልተው ተርፈዋል፡፡ 

ኢትዮጵያ አንዳንድ የክልል መስተዳድሮችና የፌዴራሉ መንግስት የዜጎችን መብት ከመከላከል አኳያ ድክመት በማሳየታቸው ይቅርታ እንዲጠይቋት ትፈልጋለች፡፡ ከዚህ ባሻግር የተፈጸሙ ወንጀሎችን በትክክለኛ ስማቸው ለመጥራት አለመፈለገም ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡ ለአብነት ያህልም ጅምላ ፍጅት ወይም የዘር ፍጅትን የሚያሳዩ ወንጀሎችን በስማቸው ለመጥራት የማይፈልጉ አንዳንድ የክልል ባለስልጣናት አሉ፡፡ ኢትዮጵያዊ ዜጎች የተፈጸመባቸውን ወንጀል በትክክለኛው ስም አለመጥራት ይቅርታ አያሰጥም፡፡ ይህም ብቻ አይደለም የተሰጣቸውን መንግስታዊ ሀላፊነት በብቃት እንዳልተወጡም ያመላክታል፡፡

በየአካባቢው የሚኖሩ ሰዎች እና የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪዎች እንደታዘቡት፣ በአይናቸው እንደተመለከቱት ከሆነ በአንዳንድ አካባቢዎች በሚኖሩ ኢትዮጵያዊ ዜጎች ላይ የተፈጸመው ወንጀል አሰቃቂ ነበር፡፡ በህይወት የተረፉ አንዳንድ ዜጎች ለመገናኛ ብዙሃን ከሰጡት ቃለምልልስ በመነሳት ( ለአብነት ያህል በቤኒሻንጉልና ጉራፈርዳ አካባቢዎች በሚኖሩ ኢትዮጵያዊ ዜጎች ላይ የተፈጸመው ጥቃት) ማንነት ላይ ያነጣጠረ እንደነበር፣ የጥቃቱም አቀነባባሪዎች በበቂ ሁኔታ ተዘጋጅተውበት ነበር ለማለት ያስደፍራል፡፡ ከዚህ ባሻግር በአንዳንድ አካባቢዎች በዜጎች ላይ ጥቃት ሲደርስ ጥቃት በተፈጸመበት አካባቢ የሚገኙ  ፖሊሶችና የጸጥታ ሀይሎች ተመልካች እንደነበሩ የተጎጂ ቤተሰቦች ለተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ከሰጡት ቃለምልልስ ማወቅ የሚቻል ይመስለኛል፡፡ ከዚህ ባሻግር በዜጎች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት በሚደርስባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ተራ ዜጎች በደህንነት ስጋት ወይም የአካባቢው የመንግስት ታጣቂዎች ደህንነታችንን ሊጠብቁልን አይችሉም በሚል ስጋት ወይም  ምክንያት ለዘመናት ከኖሩበት አካባቢ ለቀው መሄድ ግድ ብሏቸዋል፡፡

መንግስት የሰብአዊ መብት ጥሰት ከደረሰ በኋላ የሚያወጣው መግለጫ ወይም ጥቃት አድራሾቹን መያዝና ማሰር እንዲሁም ህጋዊ እርምጃ መውሰድ)፣ ለወደፊቱም አስከፊ የሰብአዊ መብት ጥሰት ስላለመፈጸሙ ለዜጎች ማስተማመኛ ለመስጠት ባለመቻሉ በብዙ ስፍራዎች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ስጋት ላይ ወድቀዋል፡፡

በነገራችን ላይ ህግን እንደ ማጥቂያ መሳሪያ መጠቀም፣ሥልጣንን አለአግባብ ለመጠቀም መንገድን ይከፍታል፡፡ ሀገሪቱ መሪዎቿ በምድሯ ላይ የሚከሰቱ ችግሮችን እንዲፈቱላት ትፈልጋለች፡፡ ለራሳቸው የግል ዝና እና ክብር ብቻ የሚጨነቁ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣኖች ለሀገሪቱ መጪው ጊዜ አደጋ የሚያመጡ ናቸው፡፡ 

ከሰው ልጆች ታሪክ ለመማር እንደቻለነው ምንም ማሸነፍ አይችሉም ወይም ውጤታማ አይደሉም፡፡ መሪዎች ችግር ከመፈጠሩ በፊት ወይም አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ከተፈጸመ በኋላ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ አለባቸው ሲባል አምባገነን ይሁኑ ማለት አይደለም፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የማእከላዊ መንግስት መሪዎችና የክልል ባለስልጣኖች የዜጎቻቸው ሰብዓዊና ህጋዊ መብቶች እንዲከበሩ በፍጥነትና አንድነት መስራት ያላባቸው ይመስለኛል፡፡

የአንድ ሀገር ባለስልጣኖች  ለራሳቸው ብቻ ማሰብ የለባቸውም፡፡ የዜጎች የሰብዓዊ መብት ከመጣሱ በፊትም ለመከላከል መዘግየት የለባቸውም፡፡ የመንግስት አካሎች አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ከተሳናቸው በሀገሪቱ ግርግርና እረብሻ ሊቀሰቀስ ይቻለዋል፡፡ ከድክመትና ስንፍና ምንም ትርፍ ማግኘት አዳጋች ነው፡፡

ማስታወሻ፡- የፌዴራል መንግስቱ በሀገሪቱ ሰላምና ጸጥታ እንዲሰፍን፣ የዜጎች መብት እንዲከበር ቅድሚያ መስጠት አለበት፡፡ ( The federal government should make it top priority to ensure peace and stability in the country and safeguard its citizen. )

  1. የድርጊት መዘግየት (Procrastination in action-)

ከአለም የፖለቲካ ታሪክ እንደምንማረው መዘግየት ማለት ሞት ማለት ነው፡፡ (“procrastination is death.” )  ስለሆነም የኢትዮጵያ መንግስት በሀገሪቱ ዕና በህዝቡ ጠላቶች ላይ ሳይውል ሳያድር እርምጃ መውሰድ አለበት፡፡ ከመገናኛ ብዙሃን እንደሚሰማው ከሆነ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ሰዎች ከእብድ ውሻ በከፉ አረመኔዎች ንጹሃን ዜጎች እንደሚገደሉ፣ ዝንተ አለም ጥረው ግረው ያፈሩት ንብረቶቻቸው ዶግ አመድ እንደሆነባቸው ተሰምቷል፡፡ ሀገሪቱ በቃላቸው የሚሸነግሉ የመንግስት ወኪሎችን ወይም ባለስልጣኖችን ሳይሆን እውነተኛ የፖለቲካ መሪዎችን ትሻለች፡፡ በነገራችን ላይ የሀገራችን ህልውና እንዲከበር ከእንቅልፋችን መንቃት ያለብን ይመስለኛል፡፡ የዝምታ ዋጋ ወይም ትርፉ በህዝብ ህይወት ላይ አደጋ መጋበዝ ብቻ ነው፡፡ የሰው ህይወት እየጠፋ ስለ ነጻና ገለልተኛ ምርጫ ማውራት በዲሞክራሲ ላይ ማሾፍ ይመስለኛል፡፡

በሀገሪቱ መሰረታዊ የሰብዓዊ መብቶች ሳይከበሩ ስለ ነጻነት እና ፍትህ በምንም ተአምር ማሰብ አንችልም፡፡ የዜጎች መብት ሲገፈፍ፣ ዲሞክራሲ አደጋ ላይ ይወድቃል፡፡ የአንድ ሀገር ህብረት አደጋ ላይ ስትወድቅ ዲሞክራሲም አደጋ ላይ መውደቁ አይቀሬ ነው፡፡  ይህም ብቻ አይደለም ሰላም ከሌለ ዲሞክራሲ የለም፡፡

ማስታወሻ፡- መንግስት ለሀገሪቱ እና ለህዝብ ጠላቶች እድል መስጠት የለበትም፡፡ በአንድ አካባቢ ችግሮች ከመፈጠራቸው በፊት አፋጣኝ ጥበቃ ማድረግ መንግስታዊ ሀላፊነቱ ነው፡፡

  1. ህግን መጠቀም (- Manipulating the law-)

ባለፉት ሃያ ስምንት አመታት ( ከ2010 ዓ.ም. በፊት ማለቴ ነው) ህግ ተቺ የተቃዋሚ ፖለቲካ መሪዎች እና አባላትን፣ ተቺ ጋዜጠኞችን፣ የመንግስትን ፖሊሲ ክፉኛ ይነቅፉ የነበሩ የሙያ ማህበራትን ለመቅጣት፣ ለማሰር ይውል እንደነበር የታወቀ ጉዳይ ነው፡፡ በኢትዮጵያ በአንዳንድ ክልሎች አንዳንድ ሰዎች ከታሰሩ በኋላ የተከሰሱበትን ማስረጃ መፈለግ የተለመደ ይመስላል፡፡ መንግስት አንድን ግለሰብ ወይም ብዙ ሰዎችን በጥርጣሬ ካሰረ በኋላ ማስረጃ ለመሰብሰብ ጊዜና ገንዘብ ያባክናል፡፡ እንዲህ አይነት አሰራር ፍትህን ሊያዛባ ስለሚያስችል በፍጥነት መታረም ያለበት ይመስለኛል፡፡ በነገራችን ላይ ባለፉት ሃያ አመታት አንዳንድ የፖለቲካ ባላንጣዎች ወይም ጋዜጠኞች እጃቸው በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች ከታሰሩ በኋላ ማስረጃ የተገኘባቸው ሲታሰሩ፡፡ ማስረጃ አልተገኘባቸውም የጠባሉት በፖለቲካ ውሳኔ መፈታታቸውን ከነጻው ፕሬስ አለም ጋዜጠኞች የህትመት ውጤት ላይ ለማንበብ ችለናል፡፡

 ስለሆነም የሕግ ሥርአቱ ተቃዋሚዎችን ወይም ተቺ ጋዜጠኞችን ዝም ለማሰኘት ወይም ለመቅጫነት ሲውል ስልየጣንን አለአግባብ መጠቀም እንደ ደንብ ሊቆጠር ይቻለዋል፡፡ የጸጥታ ሀይሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ስብሰባ እንዳያደርጉ ይከለክላሉ፡፡ ነጻ መንፈስ ያለቸውን ተቺ ጋዜጠኞችን እንደፈለጉ ዘብጥያ ይወረውራሉ፡፡ በጣም አሳሳቢውና አስጨናቂው ጉዳይ ደግሞ ፈርድ ቤት ነጻ ናቸው በማለት ከእስር እንዲወጡ የፈቀደላቸውን የህግ ታራሚዎች ህግ አስፈጻሚው በራሱ ትእዛዝ አስሮ የማቆየቱ ዚቅ ነው፡፡ የህግ ሥርአቱ ከወደቀ ነጻ ዳኝነት ይዳከማል፡፡ በመጨረሻም በተሰበረ የህግ ስርአትና  ዳኝነት ውስጥ  ሁኔታ የህዝብ ነጻነት ሊታሰብ አይቻለውም፡፡

ማስታወሻ፡- አንዱና ዋናው የመንግስት ግዴታ የታወቁ፣ ለህዝብ የተሰጡ ህጎችን ማክበር ነው፡፡ መንግስት የግል መብቶችን፣ ነጻነቶችን፣በህይወት የመኖር መብትን መጣስ የለበትም፡፡

( notice :-One of the government’s duties is to respect and make the law known to the people, but not to deprive the personal freedom, life, and liberty by manipulating it. )

  1. የፌዴራሉ ወታደራዊ ሀይል ሀላፊነት

የፌዴራል መንግስት መከላከያ ሀይል በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ያለውን የጸጥታ ችግሮችን በተመለከተ መፍትሔ መስጠት ያለበት ይመስለኛል፡፡ በነገራችን ላይ እያንደንዱ ክልል ቀላል የማይባል ገንዘብ በመመደብ የአካባቢ ሚሊሻ እንደሚያሰለጠኑ ነው፡፡ ሆኖም ግን ባለፉት ሁለት አመታት በተለያዩ አከባቢዎች የታጠቁ ወንጀለኞች በሰላማዊ ዜጎች ላይ የፈጸሙትን ግፍ ለማስቆም አልቻሉም ነበር( በቅርቡ በአንዳንድ ክልሎች በተለይም በሰለማዊ ዜጎች ላይ ግድያ በሚፈጽሙ የኦነግ ሸኔ አባላት ላይ የሚወስዱት እርምጃ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ በተለይ በሰሜን ሸዋ ደራ አካባቢ በወንጀለኞቹ የኦነግ ሸኔ አባላት ላይ የተወሰደው እርምጃ ተስፋ ሰጪ ነው፡፡)

በእኔ አስተሳሰብ በአንዳንድ ክልሎች ግጭቶች ከተከሰቱ በኋላ የፌዴራሉ መከላከያ ሀይል ሰላም ለማስከበር ሲንቀሳቀስ ሁለት መሰረታዊ ችግሮች ያጋጠሙት ይመስለኛል፡፡ እነኚህም፡-

1ኛ. የፌዴራሉ ሀይል እንደ ፖሊስ አይነት ተግባር ስለሚያከናውን የተሰላቸ ይመስላ

2ኛ. የክልል አስተዳደሮች ራሳቸውን እንደ ነጻ ክልል አድርገው ማሳመናቸው( አንዳንዶች በክልላችን ማንም ጣልቃ መግባት የለበትም ባይ ናቸው፡፡) The regional administration has a mindset of dependency.

አንድ ሀገር አክራሪ ጎሰኞችና ወንበዴዎች የሚርመሰመሱባት ከሆነ ሰላም ይርቃታል፡፡ በእንዲህ አይነት አካባቢ ግድያ፣ የጎሳ ግጭቶች፣ እልፍ ብሎ ሀገሪቱ ወደ ውድቀት ስለማምራቷ ለማወቅ ብርቅ አይደለም፡፡ ስለሆነም የፌዴራል መንግስቱ ሀይል፣ የክልል ልዩ ሀይልን እንቅስቃሴ መቆጣጠር አለበት፡፡

ይህቺ ሀገር በሌላት ጥሪት ከፍተኛ ቁጥር ላቸውን የክልል ሚሊሻዎችን ስታሰለጥን ማየቱ ልብን 

ይሰብራል፡፡ ለምንድን ነው  የክልል ሚሊሻ ? አባላት እንዲሰለጥኑ የሚፈለገው ? ለብዙ የገጠሪቱ ኢትዮጵያ ግፉአን ገበሬዎች ንጹህ የውሃ ምንጭ እንደማጎልበት፣ የትምህርት አምባዎችን እንደማስፋፋት፣ የጤና አምባዎችን እንደመክፈት ለምንድን ነው የሀገሪቱ ገንዘብ የሚባክነው ? እኛ የማናውቀው እንቆቅልሽ ይኖር ይሆን  የክልል ሚሊሻ ስልጠና መስፋፋት ለብሄራዊ ኩራትችን የሚያመጡት ፋይዳ ይኖር ይሆን ? ጠብ ጫሪነትን የሚጋብዙ ናቸውን ?  መልሱን ህሊና ለፈጠረባችሁ ትቼዋለሁ፡፡

አንዳንድ የክልል ባለስልጣኖች ሀላፊነታቸውን ባለመወጣታቸው ምክንያት በብረት አንጋቾች ለሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተጠያቂ የሚሆኑት መቼ ነው ( ለአብነት ያህል የብዙ ኢትዮጵያዊ ዜጎችን ልብ እያደማ በሚገኘው የመተክል አካባቢ የሰብዓዊ መብት ጥሠት ተጠያቂው ማን ነው ? በዚህ ክልል መተክል ዞን ተብሎ በሚታወቀው የሀገሪቱ ክፍል የመከላከያ ሰራዊቱ ከመድረሱ በፊት ሰዎች ይገደላሉ፡፡ ንብረቶች ይወድማሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን ለጥቂቶች ሰዎች ብለን እስከ መቼ ነው የምንቆራቆሰው ? በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል የሚኖሩ ዜጎች የመንግስት ባለስልጣናት ተጠያቂ እንዲሆኑ ምኞታቸው ነው፡፡ ግን መቼ ነው ሀላፊነታቸውን ያልተወጡ የመንግስት ባለስልጣናት በህግ የሚጠየቁት ? የሰው ልጅ ህይወት እየረገፈ የሚገኘበት አስጨናቂ ግዜ እንደሆነ ሁላችንም የምንረዳ ይመስለኛል፡፡

የፌዴራሉ መንግስት በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ጸጥታ ለማስጠበቅ የሚከተሉትን ተግባራት መከወን አስፈላጊ ነው፡-

  • ሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች በቂ የተማረ  የጸጥታ ሀይል እንዲኖራቸው በእወቀት ላይ የተመሰረቱ ሥራዎችን መከወን፡፡ የዚህ ውጤት ደግሞ እያንዳንዱ ክልል የአካባቢውን ሰላም ለማስከበር ይረዳል፡፡
  • በየክልሉ የሚገኙትን የልዩ ሀይል አባላትን ከፌዴራል የመከላከያ ሰራዊት አባላት ጋር ማቀላቀል፡፡ የኢትዮጵያ የፌዴራል መንግስት የመከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ የጦር አታሼዎችና አዛዦች የክልል ልዩ ሀይል አባላትን በፌዴራል እዝ ስር በማድረግ አንድ የፌዴራል መከላከያ ሰራዊት ሀገሪቱ እንዲኖራት ለማድረግ መንፈሳዊ ወኔ ከታጠቁ የሀገሪቱ ሰላምና ጸጥታ ዘለቄታዊ ሊሆን ይቻለዋል ብዬ እገምታለሁ፡፡ ይሄም ብቻ አይደለም የሀገሪቱ የዛሬና የነገ የፖለቲካ መሰረታዊ ችግር ሰራሄ መፍትሔ ሚገኝም ይመስለኛል፡፡ 
  • እያንዳንዱ የክልል መስተዳድር ዲስፕሊን ያለው፣ የተማረ፣ የሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብት የሚያከብርና የሚያስከብር የፖሊስ ሀይል ማሰልጠን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ጠንካራ የፖሊስ ሀይል ባለበት ሁኔታየእለት ከእለት ስራ እና ህይወት የተቃና ይሆናል፡፡
  • ማስታወሻ፡- የመከላከያ ሰራዊት ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ የጎሳና እርዮት አለም ወገንተኛ መሆንም የለበትም፡፡ ይህ ገቢራዊ እንዲሆን እውን ፣ በእውነት እና ነጻነት  ላይ የቆመ አንድነታችንን ማጠንከር አለብን፡፡  በህግ መንግስቱ የሰፈረውን የገለልተኝነት እሳቤ ገቢራዊ እንዲሆን መተባበር ይገባል፡፡ የሁሉም ዜጎች ፍትህ መከበር አማራጭ የለውም፡፡
  1. ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ( በጊዜው አጠራር የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓለቲካ ፓርቲዎች) በሞራል እና እውነት መሰረት ላይ የቆመ ግንኙነት ስለማድረግ ( ግንኙነት ላመድረግ ፍላጎት ማጣት)

የጥንታዊ አባቶቻችን ‹‹ እንዳያማህ ጥራው፣ እንዳይበላ ግፋው ›› የሚል ዘመን አይሽሬ ተምሳሌት ሲናገሩ፣ እንደው ዝም ብለው ከመሬት ተነስተው አልነበረም፡፡ (There is a saying in Amharic, “welcome him not to be faulted, but force him out not to take part.)በማህበራዊ ህይወታችን፣ ወይም በተለያዩ የሲቪል ማህበር ድርጅቶች፣ በተለይም የማእከላዊው መንግስትን ስልጣን የተቆጣጠረው ቡድን የተቃቀዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችን በሀገር ውስጥ እንዲንቀሰቃሱ ከጋበዘ ወይም ከፈቀደ በኋላ መጠነ ሰፊ መሰናክል በመደቀን የፖለቲካ ድርጅቶቹን ከጨዋታ ውጭ እንዲሆኑ ማድረግ የተለመደ ተግባሩ ነው፡፡ ለአብነት ያህል የወያኔ አገዘዛዝ ከኢዲሀቅ እስከ ቅንጅት ለአንድነት የመሳሰሉትን ድርጅቶች እንዴት ጉድ እንዳደረጋቸው ማስታወስ የሰውነት ባህሪ ነው፡፡ ከ2010 ዓ.ም. ወዲህ ደግሞ የተፎካካሪ ፖለቲካ ድርጅቶች ሁሉ በነጻነት እንዲንቀሳቀሱ የፈቀደው የኢትዮጵያ መንግስት በወንጀል ጠርጥሬአቸዋለሁ ከሚላቸው የፖለቲካ ድርጅቶች በቀር በሰላማዊ እና በሰለጠነ መንገድ ለዲሞክራቲክ መንግስት ምስረታ እንታገላለን ለሚሉት ሁሉ በእውነትና ሞራል መሰረት ላይ የቆመ ግንኙነት ቢያደርግ ፣ ሆደ ሰፊነቱን ለሁሉም ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ድርጅቶች ሆሰፊነቱን እኩል ቢያሳይ፣በኢትዮጵያ የሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች፣ የህግ የበላይነት ይከበራሉ ብዬ አስባለሁ፡፡ በነገራችን ላይ የፖለቲካ አለመረጋጋት ወይም የፖለቲካ ነጻነት አለመኖር ከጎሳ ማንነት ጋር የሚያያዝ አይደለም፡፡ ይህ ውደቀት ነው፡፡ ተሰሚነት አለመኖር ነው፡፡

ፖለቲካችን ከአፍራሽነት ወደ መተባበር መሄድ ያለበት ይመስለኛል፡፡ ይህን የተቀደሰ አላማ እውን ለማድረግ ግን ከቀና አስተሳሰብ እና እውነት ፣ እንዲሁም ሞራል ላይ የተመሰረተ ብሔራዊ ውይይት ለማድረግ ዝግጁ መሆን አለብን፡፡ ከዚህ ባሻግር ከመንግስት አኳያ ኢትዮጵያ ዛሬ ለገባበት ቅጥአምባሩ ከጠፋበት የፖለቲካ አቅጣጫ እንድትወጣ የሚያግዝ የፖለቲካ መልካም ፈቃደኝነት ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

ህሊና የፈጠረባቸው በርካታ የፖለቲካ ሃያስያን ( እንድ እነ ዶክተር በፍቃዱ በቀለ፣ ዶክተር ታዬ ወልደሰማያት፣ ፕሮፌሰር ጳውሎስ ሚልኪያስ፣ፕሮፌሰር ሚንጋ ነጋሽ፣ ፕሮፌሰር ሀሰን ሰይድ፣ ፕሮፌሰር በፍቃዱ ደግፌ፣ ዶክተር ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ፣ ጋሼ ክፍሌ ሙላት፣ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም እና ጋሼ ሙሉጌታ ሉሌ ( የሁለቱንም ታላላቅ የኢትዮጵያ ልጆች ነፍስ ከደጋጎቹ ኢትዮጵያውያን ነፍስ ጎን ያሳርፍልን) ወዘተ ወዘተ ይጠቀሳሉ ፡፡ ) በተለያዩ በሳል የጥናት ወረቀቶቻቸው ላይ እንዳሰፈሩት ከሆነ የአብዛኞቹ ኋላቀር ሀገራት የአንድነት ፖሊሲ ገቢራዊ የሚሆነው በአጠቃላይ ስምምነት ሳይደረስበት ነው፡፡

In underdeveloped countries, the policy framework for national unity is not the result of consensus.

ሁላችንም እንደምናውቀው  የሀገሪቱን የፖለቲካ አቀጣጫ፣ የሀገሪቱን ቅርጽ ወዘተ የሚወስኑት በስልጣን ኮርቻ ላይ የተፈናጠጡት የፖለቲካው ፊትአውራሪዎች ብቻ ናቸው፡፡ ለአብነት ያህል ባለፉት ሃያ ስምንት አመታት ( ከ2010 ዓ.ም. በፊት ) ስልጣን ላይ የነበሩት ወያኔዎች በኢትዮጵያ ምድር የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲን ለብቻቸው ገቢራዊ በማድረግ ኢትዮጵያን የስቃይ ምድር አድርገውበታል፡፡ ስለሆነም በአሁኑ ግዜ የማእከላዊ መንግስቱን ስልጣን የጨበጠው የኢትዮጵያ መንግስት በርካታ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ድርጅቶችና የኢትዮጵያ ህዝብ ሳይመክርበት ገቢራዊ የሆነውን የጎሳ ፌዴራሊዝም ስርአት በተመለከተ ኢትዮጵያውያን ሁሉ እንዲመክሩበት መጠየቅ  የቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው፡፡

በነገራችን ላይ የገዢው ፓርቲም ሆነ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖለቲካ ፕሮግራም አንድ አይነት መሆን አይጠበቅበትም፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ሁለቱም በጋራ አላማ ላይ  ለአብነት ያህል በብሔራዊና ክልላዊ የጸጥታ ጉዳዮች ላይ መነጋገር፣ መወያየት ያለባቸው ይመስለኛል፡፡ ከዚህ ባሻግር ወረርሽኝ፣ የተፈጥሮ አደጋዎች ለሁለቱም የጋራ ችግሮች ናቸው፡፡ ሌሎች እንደ የሥራ እድል መክፈት፣የወጣቶች ተሳትፎ የመሳሰሉት በመንግስትና በተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች አኳያ ትብብር ያስፈልጋል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና በኢትዮጵያ የፖለቲካ መልክኣ ምድር በአብዛኛው ገቢራዊ መሆን አልቻለም፡፡ በጣም ጥቂት የፖለቲካ ፓረቲዎች ናቸው ነጻነታቸውን በመጠበቅ ከላይ በጠቀሰኳቸው የጋራ ችግሮች ላይ ከመንግስት ጋር የሚተባበሩት፡፡ ስለሆነም መንግስትም የፖለቲካ ሜዳውን ማስፋት አንዱ ግዴታው ሲሆን ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች  ደግሞ ነጻነታቸውን ሳያስነኩ በሀገሪቱ የጋራ ችግሮች ላይ መተባበር እንዳለባቸው ሳስታውስ በታላቅ ትህትና ነው፡፡ 

የሀገሪቱን ስልጣን የተቆጣጠረው ከቃላት ባሻግር የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ነጻነታቸው እንዳይገፈፍ መርዳት ያለበት ይመስለኛል፡፡ ከዚህ በተቃራኒው መልኩ የተፎካካሪ ፖለቲካ ድርጅቶች አመራሮች እና አባላቶች በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ተንቀሳቅሰው የፖለቲካ ፕሮግራማቸውን ለህዝብ ማቅረብ ካልቻሉ፣ ህዝባዊ ውይይት በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ማካሄድ ከተከለከሉ የፖለቲካው አውድ ችግር ውስጥ ይዶላል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፣ በመንግስትና በተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች መሃከል ያለው ግንኙነት ጤናማ ላይሆን ይቻለዋል፡፡ ሁለቱም ማለትም መንግስትና የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እርስበርሳቸው እንደማይተማመኑ ከሚያሳዩት ባህሪ መረዳት ይቻላል፡፡ በነገራችን ላይ አለመተማመን እና ጥላቻ ስር ሲሰድ በጋራ አጀንዳ ላይ መተባበርና የፖለቲካ መልካም ፈቃደኝነት እንዴት እውን ሊሆን ይቻለዋል ? 

የግል ማስታወሻ፡- እነርሱ በገቢርም ሆነ በነቢብ ለህዝብ መቆማቸውን ማሳየት አለባቸው፡፡ ለግል ጥቅምና ዝና፣ ለስልጣን ብቻ መስገብገብ ያለባቸው አይመስለኝም፡፡ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ መንግስትን ጨምሮ ለህዘብ  ጥቅም መቆም አንዳለባቸው ፣ በመሃከላቸው ያለውን ልዩነቶች በሰለጠነ መንገድ መነጋገር አለባቸው፡፡ በኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት በጽኑ መሰረት ላይ እንዲቆም የማእከላዊ መንግስት በሞራል እና እውነት መሰረት ላይ ቆሞ ሁሉንም ሰላማዊ የፖለቲካ ተፎካካሪ  ፓርቲዎች  አሳታፊ  ማድረግ ያለበት ይመስኛል፡፡

  1. ግልጽነት አለመኖርና መገናኛ ብዙሃን

ግልጽነት ማለት መረጃን ከህዝብ ፍላጎት አንጻር ማስተላለፍ ማለት ነው፡፡ ከህዝብ ፍላጎት ውጭ የሚቀርቡ መረጃዎች ወይም ለህዝብ ትክክለኛውን መረጃ መደበቅ ወይም ሚስጥር ማድረግ ከግልጽነት አስተምህሮ ተጻራሪ ነው፡፡

ለአብነት ያህል ወንጀለኞችን ማደንና ህግን ገቢራዊ ስለማድረግ መጥቀስ ይቻላል፡፡ በሀገራችን በርካታ አሰቃቂ ወንጀሎች ስለመፈጸማቸው ከተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ሰምተናል፡፡ በመጀመሪያ የሚጠቀሰው ጠቅላይ ሚንስትሩን ለመግደል የተሞከረው ወንጀል ነበር፡፡ በባህርዳር የተፈጸመው ግድያ ፣ በአዲስ አበባ በሁለት የጦር ጄኔራሎች ላይ የተፈጸመው ግድያ፣ በጌዲኦ፣ሻሸመኔ፣ ቤኒሻንጉል፣አርሲ፣ ወለጋ እና ሌሎች አካባቢዎች በሚኖሩ ዜጎች ላይ የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ ወዘተ ወዘተ ይጠቀሳሉ፡፡ስለሆነም  ህዝቡ ወንጀለኞች በፍትህ አደባባይ ቆመው በህግ እንዲጠየቁ ፍላጎቱ ነው፡፡ 

በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ግድያ የሚፈጽሙ ቡድኖች የጦር መሳሪያ ከየት ነው የሚያገኙት ? መልሱን ህሊና ላላችሁ ትቼዋለሁ፡፡ ለማናቸውም መንግስት ወንጀል የሚፈጽሙ  ቡድኖች ሙሉ በሙሉ ትጥቃቸውን አስፈትቶ በህግ ፊት ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡

ከጎረቤት ሀገር ኤርትራ ጋር  የተደረገው የሰላም ስምምነት ዘለቄታዊ እንዲሆን ገና ብዙ መሰራት ያለበት ይመስለኛል፡፡ የኢትዮጵያ የውስጥ ፖለቲካ እንዲረጋጋ ከሚያግዙ ቁምነገሮች አንዱ ከጎረቤት ሀገራት ጋር መልካም ጉርብትና አስፈላጊ ነው፡፡

አንድ ሀገር ዲሞክራቲክ፣ ገለልተኛ፣ ነጻነት የሰፈነባት እንድትሆን ከተፈለገ መገናኛ ብዙሃን ወሳኝ ናቸው፡፡ መገናኛ ብዙሃን ለህዝቡ ሁሉንም ነገር በግልጽ መናገር አለባቸው፡፡ መንግስት ተጠያቂነት እንዳለበት በነጻ መንፈስ ማስተማር አለባቸው፡፡ እውን በኢትዮጵ የሚገኙ መገናኛ ብዙሃን ግልጽ ናቸው መልሱን ህሊና ለፈጠረባችሁ ትቼዋለሁ፡፡  በእኔ አስተሳሰብ ጋዜጦችም ሆኑ መገናኛ ብዙሃን የአንድ ፓርቲ ልሳን ብቻ መሆን የለባቸውም፡፡

የግል ማስታወሻ፡- መንግስት ገለልተኛና ነጻው ፕሬስ እውን እንዲሆን በእጅጉ ማገዝ አለበት፡፡ ነጻው ፕሬስ በሰፈነበት ሀገር ዲሞክራሲ ያብባል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና በፕሬስ ስም የጥላቻ መርዝ የሚረጩትን መቆጣጠር የመንግስት ስራ መሆን አለበት፡፡

 

ክፍል ሁለት ይቀጥላል

Filed in: Amharic