>

አቶ ልደቱ አያሌዉ በ30,000 ብር ዋስትና ከእስር ተፈቷል...! (ዘላለም ጥላሁን)

አቶ ልደቱ አያሌዉ በ30,000 ብር ዋስትና ከእስር ተፈቷል…!

ዘላለም ጥላሁን

የታፈነ ፍትሕ
ልደቱ እንኳን ደስ አለህ። የልደቱ እናት እንኳን ደስ አለዎት። ወልጋዳ ከሆነው የፍትሕ ስርዓትና ከልብ ህመም አምልጦ በህይወቱ መውጣቱ ትልቅ ነገር ነው። የልደቱ የፖለቲካ አቋም ተመቸንም አልተመቸንም፣ በእሱ ላይ የተሰራው የተንሻፈፈ #የፍትሕ ስርዓት፣ አሁንም ነፃ ተቋማትን የመገንባት ሂደቱ ላይ ብዙ ደንቃራ እንዳለ ነው። ዛሬ በልደቱ የፈረዳችሁ፣ ነገ የእሱ እጣ እንዲገጥማችሁ አልመኝም።
ልደቱም ሆነ እሰክንድር፣ ስንታዬሁም ሆነ ሌሎች፣ በሐሳብ እንጂ በነፍጥ አልሞገቱም። “የተደፈቀ ሐሳብ ደግሞ ነፍጥ ይወልዳል”… ህውሃት ይሙት ስለዚህ የሐሳብ ነፃነት ይከበር። እነ እስክንድርም ይፈቱ።
 የታፈነ ፍትሕ፣ አፋኙን ማፈኑ አይቀርም። ከትህነግ ተማሩ።
 በሐሳብ የበላይነት የምታምን ነፃ ሀገር ይኖረን። አሊያ ነገሩ ሁሉ ዘጭ እንቦጭ ነው።
<<የታፈነ ፍትሕ፣ ሹም የከለከለው
ከነገ ባሻገር፣ የጊዜ ዳኛ አለው>>
የኢትዮጵያን ፖለቲካና ፍትሕ ደጋግሞ የፈተነው አወዛጋቢው ሰው-ልደቱ አያሌው፤
ከ 97 ማግስት መንገድ ስቶ የተገለበጠ መኪና ሳይቀር #ልደቱ የሚል ቅፅል ስም በአዲስ አበባ ወጣቶች ይሰጠው እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡
ከ ባምቢስ እስከ ለገሃር፣ ከኤግዚቭሽን ማዕከል እስከ እስጢፋኖስ፥ ከመሿለኪያ እስከ አምባሳደር የተረበበው ወፈ ሰማይ ህዝብ በአንድ ድምፅ #ልደቱ ብሎ እንዳልጮኸ፤ ከምርጫ ማግስት ልደቱን ድርቅ መታው፡፡ ልደቱ የከሃዲነትና የአቋመ ቢስ ሰው መገለጫ ተደርጎ ተወሰደ፡፡ ቦግ ብሎ ለደበዘዘው የኢትዮጵያ ፖለቲካ የመተማመን ክር የበጠሰ ሰው ተደርጎ ከሊቅ እስከ ደቂቅ እንደ አሪዎስ ተወገዘ፡፡ ተንሸራታች የእጅ ስልክ በስሙ ተሰዬመ። ልደቱ ጩኸቱ ሁሉ የሞድረ በዳ ጩኸት ሲመስለው አልፎ አልፎ ከፖለቲካው ወጣ ገባ ማለት ጀመረ። እውነቱን አጋጥሞ የሰማ የለም። የሌሎችን እንጂ የልደቱን እውነት የሰማ የለም። ወይም የልደቱን ስህተት በማስረጃ የደገፈ የለም። አሉቧልታ ሲገዛን ኖረ።እየገዛንም ነው።
ልደቱ የራሱ እውነትና እምነት ነበረው፡፡ ነገር ግን <እሳት በሌለበት ጭስ አይጨስም> የሚለው ብሒል በቀላሉ የሚታለፍ አይደለም፡፡ <<እንዲ ባይሆን ኖሮ፣ እንዲ ቢሆን ኖሮ>>….እያለ ህልማዊ የሆነ የጉዞ ብያኔ ውስጥ ለገባ ማህበረሰብ እሳት የለም ብለህ ብታስረዳው፣ እሳት አለመኖሩን ከማረጋገጥ ይልቅ <<ጭሱ አለ>> ብሎ ይከራከርሃል።
እንደገባኝና እንዳየሁት የኢትዮጵያ ፖለቲካ የመጠላለፍና የመበላላት ፖለቲካ ነው፡፡ ትንንሾች አሳዎች ብቅ ሲሉ ትልልቆቹ ቀድመው ያከስሟቸዋል፡፡ እጅግ ስግብግብነትና  ግብዝነት በፈነጠዘበት የኢትዮጵያ የሴራ ፖለቲካ ውስጥ <የከሌ> ነው ስህተት፥ የከሌ ልክ ነው ብሎ መተቸት ትንሽ ያስቸግራል፡፡
ምክንያቱም በሌሎች የሚያላክክ እንጂ ከስህተቱ እንኳን ተፀፅቶ ይቅርታ የሚጠይቅ ፖለቲከኛ አላየንም፡፡
እንደማሳያ የደርግ ባለስልጣናትን ማንሳት ይቻላል፡፡ ኮ/ል ፍስሃ <ባለማወቅ ያጠፋሁትን፥ የኢትዮጵያ ህዝብ ይቅር ይበለኝ> ብሎ ይጀምራል መፅሐፉ ላይ፡፡ ዶ/ር ዳኛቸው ይህን  ጉዳይ <<ይህ ትልቅ ቅጥፈት ነው፡፡ አሁንም አልተፀፀተም፡፡ የህግ ባለሙያ የሆነ ሰው እንዴት ሰው መግደልን <ባለማወቅ> ብሎ ያታልላል>> ብለው ይተቻሉ፡፡
መንጌም <በትግላችን> መፅሐፍ  ተመሳሳይ ስሜት ያለው ነገር ፈንጥቀዋል፡፡
ይህ በሽታ አብሮ አድጎ የገዥውም ሆነ የተቃዋሚው አንጃ ውስጥ እንደ ካንሰር እየሰረሰረ የኢትዮጵያን መፃኢ ተስፋ ያጨለመ/የሚያጨልም በሽታ ነው፡፡ እግራቸው ጉድጓድ ዳር መሆኑን እያወቁ፥ የሞት አፋፍ ላይ ሆነው እንኳ “ወረትን” እንጂ “እውነትን” ተናዘው የሚያልፉ ሰዎች በጣም ጥቂት ናቸው፡፡
የኢትዮጵያን የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም በመተንተን ልደቱ አቻ የተገኘለት ሰው አለመሆኑን ብዙ ሰው ያምናል። ነገር ግን ብዙ ሰው ሐሳቡን ያምንና እሱን አያምነውም? እንደ ልደቱ የጠራ የፖለቲካ ዶክመንት የማዘጋጀት አቅም ያለው ሰው አላዬንም። ብዙዎችን በተስፋ ባህር ያዋኘው የለውጥ ሐዲድ ሰላማዊውን ሰው ያለ ሐጢያቱ አስሮታል። የታሳረው ሚዛን የሚደፋ ሐሳብ በማንሳቱ ነው። የታሰረው የድንብርብር ፖለቲካውን አደጋ ላይ በመጣሉ ነው። የታሰረው <<በሐሳብ አምናለሁ>> ያለውን ኃይል በሐሳብ በማሸነፉ ነው። አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ የፍትሕ ስርዓት ገለባ መሆኑን አሳይቶናል። የባለስልጣን የግል እስረኛ መሆኑ ደጋግሞ ታይቷል። ፖሊስ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንደማይቀበል አሳይቶናል። ከፍትሕ ስርዓቱ ይልቅ የአንድ ባለጊዜ ባለስልጣን ድምፅ እንደሚበልጥ አዬን። ፍትሕ ተገልብጣ ወደቀች። <<የባሰ አለ….>> ነው ነገሩ።
አወዛጋቢው ሰው፤
ምን አልባት የኢትዮጵያ ህዝብ ያልተረዳው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ወጌሻ ይሆን? ወይስ አሁንም አወዛጋቢ ሰው?
Filed in: Amharic