“የመናበብ” ነገር…!!!
መስከረም አበራ
የሁለት አለም ሰዎችን ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል ማናበቡ አይከብድም…!!!
እስክንድር ነጋ እና ጃዋር መሃመድ “ተናበው ሰሩ” ከተባለ ወዲህ የመናበብ ትርጉሙ እያደናገረኝ መጥቷል። መታሰር ብርቁ ያልሆነው ፣አጥንተ ብርቱው እስክንድር ነጋም ከእስሩም በላይ ‘ከነጃዋር ጋር ተናበህ ሰራህ’ መባሉ በጣም እንዳስቆጣው ወ/ሮ አዳነች አበቤን” ስሜን እንዳቆሸሻችሁ አትቀሩም” ሲል በቁጭት መናገሩ ምስክር ነው።
ወ/ሮ አዳነች ታዲያ “ተናበው ሰሩ አልኩ እንጅ አብረው ሰሩ አላልኩም” ብለው አሳማኝ ያልሆነ ማሳመኛ ለማቅረብ ሞክረው ነበር። ሳይተባበሩ መናበብ ከየት እንደሚመጣ በብልፅግና ቤት ካልኖሩ የሚገባ ነገር አይደለም። ጃዋር ራሱ “እኔን እና እስክንድርን ተናቦ በመስራት መጠርጠር አስገራሚ ነገር ነው” ብሎ ነበር።
ይህች መናበብ የምትባል ነገር ማስረጃ በሌለበት የሚጠሉትን አካል ስምለማጥፋት የብልፅግና ባለስልጣናት የቀየሷት መንገድ ነች። በእጅጉ የሚተቿቸውን ሚዲያዎች ፣ግለሰቦች ወዘተ ለማፈን ሲባል ውሃ እና ዘይት ተናበቡ የሚል አድማጭን የናቀ ፈሊጥ አምጥተዋል።
ሃገር የሚመራ ሰው አድማጭን የሚያሳምን መረጃ ይዞ ብቻ ነው ሚዲያዎችንም ሆነ ሰዎችን መውቀስ ወይም ማውገዝ የሚችለው። መረጃ ካለ ደግሞ ተወቃሹን አካል በፍርድ ቤት ተጠያቂማድረግ እንጅ መንግስትን ከተናቀው በላይ የሚያስንቅ ነገር ይዞ ወደ ሚዲያ መምጣት የሚጎዳው ሃገርን ነው።
ከሁሉም በላይ ወያኔን ገንዘብ ከፍሎ ግለሰቦችን እና ሚዲያዎችን በማናገር ለመክሰስ መንግስት ራሱ ለማንም ምንም ከፍሎ አናግሮ የማያውቅ መሆኑን እርግጠኛ መሆን አለበት። ይህን ለማለት የሚደፍር ግን አይመስለኝም!!!!!!
ሚዲያ የዲሞክራሲ ዋና አጋፋሪ ነው።የሃሳብ ልዩነት የሚፋጨው በሚዲያ ነውና።ሚዲያዎች ሲያጠፉም ጥፋቱ ከባድ ጦስ ያለው ነገር ያመጣል።ስለዚህ ሚዲያዎችን በተመለከተ ከመንግስት ባለስልጣናት የሚመጣው ክስ ተጨባጭ መረጃ ያለው መሆን አለበት።ካልሆነ ተቃዋሚ ልሳናትን ዘግቶ የወያኔን ወንበር ላይ ለመቀመጥ የሚደረግ መንደርደር ነው የሚሆነው።