መጽሐፍ ቅዱስ ሥዕላትን ይፈቅዳልን ?
ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ገብቶ የሚመለከት ሰው እጅግ የተዋቡ የጌታችን ፣ የድንግል ማርያም ፣ የመላእክትና የቅዱሳን ሰዎች ሥዕላት ቤተ መቅደሱን ሞልተውት ያገኛል፡፡ ኦርቶዶክሳዊያን በሥዕላቱ ፊት ዕጣን ሲያጥኑ ፣ መብራት ሲያበሩ ፣ ሲሳለሙና ሲሰግዱ ኦርቶዶክስ ያልሆኑ ደግሞ ‹ይኼ እኮ ጣዖት አምልኮ ነው!› ‹‹በላይ በሰማይ ካለው ፤ በታች በምድርም ካለው ከምድርም በታች በውኃ ካለው የማናቸውንም ነገር ምሳሌ ለአንተ አታድርግ አትስገድላቸው አታምልካቸውም›› ተብሎ በዐሠርቱ ትእዛዛት ላይ ተጽፎ የለምን? ብለው ይከራከራሉ፡፡ (ዘጸ. 20፡4)
በእርግጥም እግዚአብሔር በሰማይም ፣ በምድርም ፣ ከምድርም በታች ባሉ በማናቸውም ነገር የተቀረጸ ምስል አታድርግ ብሎ በግልጥ ማዘዙ ማስተባበያ የሌለው እውነት ነው፡፡ ታዲያ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ይህ ትእዛዝ በግልጥ ተጽፎ ካለ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን በሰማይ ካሉ የመላእክትን ፣ በምድር ካሉ የቅዱሳን ሰዎችን ሥዕላት ለመቅረጽም ሆነ ለመሳል እንዴት ደፈረች? እውነት ይኼንን በግልጥ የተቀመጠ ሕግ እያየች ሥዕላትን ለማዘጋጀት ምን አነሣሣት? የሚለው ጥያቄ የግድ መመለስ ያለበት ነው፡፡
በቀጥታ ወደ ምላሹ ከመግባታችን በፊት ከዚያው ከኦሪት ዘጸአት ሳንወጣ ጥቂት ምዕራፎችን እንሻገርና እናንብብ፡፡ እግዚአብሔር ለሙሴ እንዲህ አለው ፡-
‹‹ሁለት ኪሩቤል ከተቀጠቀጠ ወርቅ ሥራ … አንደኛውን ኪሩብ በአንድ ወገን ሁለተኛውን ኪሩብ በሌላ ወገን አድርገህ ሥራ … ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ወደ ላይ ይዘርጉ ፤ የስርየት መክደኛውን በክንፎቻቸው ይሸፍናሉ ፤ ፊታቸውም እርስ በእርሱ ይተያያል … እኔም በሁለቱ ኪሩቤል መካከል ሆኜ አነጋግርሃለሁ›› (ዘጸ. 25፡18-22)
ልብ አድርጉ ፤ ከአምስት ምዕራፎች በፊት ‹ከሰማይ ፣ ከምድርና ከባሕር የማናቸውንም ምሳሌ የተቀረጸ ምስል ለአንተ አታድርግ› ብሎ ለሙሴ ያዘዘው እግዚአብሔር አሁን ደግሞ በሰማይ ካሉ መላእክት መካከል የሆኑትን የኪሩቤልን ሁለት ምስል ከተቀጠቀጠ ወርቅ ሥራ ፣ ክንፎቻቸውን እንዲዘረጉና እንደሚናተፍ ዶሮ እንዲተያዩ አድርጋቸው ፣ እኔም በእነርሱ መካከል አነጋግርሃለሁ አለው፡፡ከዘጸአት ሳንወጣ እግዚአብሔር አሁንም ለሙሴ እንዲህ አለው ፡-‹‹መጋረጃውንም ከሰማያዊና ከሐምራዊም ከቀይም ግምጃ ከተፈተለ ከጥሩ በፍታ አድርግ ፤ ብልህ ሠራተኛ እንደሚሠራ ኪሩቤል በእርሱ ላይ ይሁኑ›› በማለት ከወርቅ ከተቀረጹት ሁለት ኪሩቤል በተጨማሪ በመጋረጃ ላይ በጥልፍ መልክ ኪሩቤል እንዲሣሉ አዘዘው፡፡ (ዘጸ. 26፡30-31) እግዚአብሔር በሰማይ ካሉት የማንንም ምሳሌ አታድርግ ብሎ ያዘዘውን ትእዛዝ ራሱ የሚጥስ አምላክ ነው ሊባል ይችላልን? ኪሩቤል ‹በሰማይ ካለው ማናቸውም ነገር› ውስጥ አይደሉምን? የተቀጠቀጠ ወርቅስ የተቀረጸ ምስል አይደለምን? ይህን ጥያቄ እንደ ዋዛ መተው እንዴት ይቻላል?
መጽሐፍ ቅዱስ ኦሪት ዘጸአት ብቻ ቢሆን ሁለት ማስረጃ ጠቅሰን እንተወው ነበር፡፡ ሆኖም መጽሐፉ በዚህ አላበቃም ፤ እግዚአብሔር ‹‹እጅግ ብዙ ጥበብና ማስተዋል በባሕርም እንዳለ አሸዋ የልብ ስፋት ሠጠው›› ተብሎ የተነገረለት ጠቢቡ ሰሎሞን ቤተ መቅደሱን ሠርቶ ሲፈጽም ይህንን አደረገ ፡-
‹‹በቅድስተ ቅዱሳኑም ውስጥ ቁመታቸው ዐሥር ክንድ የሆነ ከወይራ እንጨት ሁለት ኪሩቤል ሠራ ፤ የኪሩብም አንደኛው ክንፍ አምስት ንድ ነበረ ፤ ከአንደኛው ክንፍ ጫፍ ጀምሮ እስከ ሌላኛው ክንፍ ጫፍ ድረስ ዐሥር ክንድ ነበረ … ኪሩቤልንም በወርቅ ለበጣቸው›› ይላል፡፡ (1ነገሥ. 6፡23-28)
ጠቢቡ በዚህ አልበቃውም ፤ የቤተ መቅደሱን ግንብ ዙሪያውን ባዶ እንዲሆን አልተወውም ‹‹በቤቱም ግንብ ዙሪያ በውስጥና በውጪ የኪሩቤልና የዘንባባ ዛፍ የፈነዳም አበባ ምስል ቀረጸ›› ይላል፡፡ (1ነገሥ. 6፡29) በአጭሩ ጠቢቡ ሰሎሞን እንደ ሙሴ በመጠን ያነሡ ሳይሆኑ ዐሥር ክንድ የሚረዝሙ ኪሩቤልን ከወይራ ሠርቶ በወርቅ ሲለብጥ ከምድርም አበባና ዘንባባን በቤተ መቅደሱ ምስል አድርጎ ቀረጸ፡፡
‹የተቀረጸ ምስል ለአንተ አታድርግ› የሚለው ቃል የመላእክትን ሥዕልና ቅርጽ የሚከለክል ከሆነ ይህ ሕግ ክብር ይግባውና ሕጉን ባወጣው በእግዚአብሔርና በባሪያዎቹ በሙሴና በሰሎሞን ተጣሰ ማለት ነው፡፡ ሆኖም የእግዚአብሔር ሕግ ስለእነዚህ ዓይነቶቹ የቅዱሳን ሥዕላት የወጣ ሕግ አልነበረም፡፡ ሕጉ የሚጠናቀቅበት ‹አትስገድላቸው አታምልካቸውም› የሚለው ሐረግ እግዚአብሔር የከለከላቸው የተቀረጹ ምስሎች አምላኬ ነህ ተብለው ለፈጣሪ የሚገባ የአምልኮ ስግደት የሚሰገድላቸው ጣዖታትን እንደሆነ በግልጽ ያስረዳል፡፡ ለማንኛውም በእግዚአብሔር የሚያምን ሰው ከሰማይ ከምድር ከባሕር ያሉ ፍጥረታትን በምስል ቀርጾ አምላኬ አንተ ነህ ብሎ እንዳይሰግድ የተከለከለው ክልከላ እግዚአብሔር ያከበራቸውን ቅዱሳን መላእክት መቅረጽ አይገባም ለማለት ማስረጃ አድርጎ ማቅረብ የተሳሳተ መሆኑን ራሱ ባለቤቱ ሕጉን ከሠራ በኋላ በዚያው ዘመን የመላእክቱን ሥዕልና ቅርጽ በማሠራት አሳይቶናል፡፡
እዚህ ላይ አንድ ነገር እናስተውል ፤ ከላይ ባየናቸው የቤተ መቅደሱ ውስጥ ሥዕላት በተደጋጋሚ የተሣሉት መላእክት ብቻ ከመላእክትም ኪሩቤል ብቻ ናቸው፡፡ ዛሬ በቤተ ክርስቲያን እንደምናየው ከሙሴ በፊት የነበሩ እንደ አብርሃም ይስሐቅ ያዕቆብ ያሉ ቅዱሳን ሥዕላቸው በቤተ መቅደሱ ለምን አልተሣለም? ምናልባት ለቅዱሳን ሰዎች ሥዕል አይገባ ይሆን? ያሰኛል፡፡
አይደለም ፤ እንደሚታወቀው ቤተ መቅደሱ የሰማያት ምሳሌ ሲሆን በሰማያት በልዕልና የሚኖር አምላክ ከሕዝቡ መካከል በረድኤት የሚገለጥበት ሥፍራ ነው፡፡ በቤተ መቅደሱ ያሉት ነገሮች ሁሉም በሰማያት በእግዚአብሔር መንግሥትና ከእግዚአብሔር ጋር ያሉትን ነገሮች የሚወክሉ ናቸው፡፡ ቅዱሳን ሰዎች ሁሉ ጽድቃቸው እንደ መርገም ጨርቅ ሆኖ ወደ ሲኦል በወረዱበት በዚያ በብሉይ ኪዳን ዘመን ከእግዚአብሔር ረድኤት ርቀው በሞት ጥላ መካከል ናቸውና የእግዚአብሔር መንግሥት ምሳሌ በሆነው መቅደስ ውስጥ አልተሣሉም፡፡ በዚያ ቤተ መቅደስ የተሣሉት መላእክት ከመላእክትም ለታቦቱ ዙፋንነት ምሥጢር የሚቀርቡት በእግዚአብሔር መንግሥት ዙፋኑን የሚሸከሙት ኪሩቤል ናቸው፡፡
± ሥዕላት ለምን ይጠቅማሉ? ±
ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ ሥዕላትን የሰማይ መስኮቶች ይላቸዋል፡፡ በቤተ መቅደስ ቆሞ የመላእክቱን ሥዕል ፣ የሥላሴን ዙፋን ፣ የቅዱሳኑን ኅብረት የሚመለከት ሰው ለአፍታ በሕሊናው ወደ ሰማያት መመሰጥና የላይኛውን ነገር ማሰብ ይችላልና ሥዕላት የሰማይ መስኮቶች ናቸው፡፡ የሚያስደንቀው ሥዕላት ከመጽሐፍ ቅዱስ የሚበልጡ የእግዚአብሔር ቃል መማሪያዎች ናቸው፡፡ አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን ሊገነዘብ የሚችለው ወይ ሊያነበው በሚችለው ቋንቋው ተተርጉሞ ሲቀርብለት ነው ፤ አለዚያም ደግሞ ማንበብ የሚችል ፊደል የተማረ ሰው ከሆነ ብቻ ነው፡፡
ሥዕላት ግን ከዚህ መድልዎ የጸዱ አስተማሪዎች ናቸው፡፡ የየትኛው ቋንቋ ተናጋሪ ያለ አስተርጓሚ ሥዕላትን አይቶ ሃሳባቸውን ለመረዳት ይችላል፡፡ ምንም ፊደል ያልቆጠረ ሰው ቢሆንም ሥዕላትን አይቶ መማርና መጠቀም ይችላል፡፡ የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪዎችን ከጌታችን የዕለተ ዓርብ መከራ ሥዕላት ፊት ብናቆማቸው ሁለቱም የጌታችንን ሥቃይ ፣ መውደቁን መነሣቱን ፣ መገረፉንና መሰቀሉን አይተው ያለቅሳሉ፡፡ ያለ ቋንቋ እንቅፋትነት አብረው ሊማሩ የሚችሉት ስብከት የሚገኘው ሥዕላት ላይ ብቻ ነው፡፡ ያልተማረ ሰውም ከሌሎች የማነስ የበታችነት ሳይሰማው እኩል መረዳት የሚችልበት አስተማሪው ቅዱሳት ሥዕላት ናቸው፡፡
የቤተ ክርስቲያን ሐኪሞች (Doctors of the Church) ከሚባሉት አባቶች አንዱ የሆነው ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ የጌታችንን ስቅለት የሚያሳይ ሥዕልን ባየ ጊዜ የተሰማውን ሲገልጥ ‹‹ይህንን ሥዕል በተመለከትሁ ጊዜ ያለ ዕንባ ልመለከተው አልችልም ፤ ምክንያቱም ሰዓሊው በጥበባዊ መንገድ ታሪኩን ፊቴ ላይ ስላመጣብኝ ነው›› ብሏል፡፡ ይህንን የጎርጎርዮስን ምስክርነት ያየው ዮሐንስ ዘደማስቆ ደግሞ በእንተ ሥዕላት አምላካዊያት (On the Divine Images) በተባለው ጥንታዊ መጽሐፉ ‹‹ሥዕላት እንዲህ ዓይነቱን የቤተ ክርስቲያን ሐኪም እንዲያለቅስ ከረዱት ለአላዋቂ የዋሐንማ ምን ያህል ይረዳቸው ይሆን?›› ብሎ አድንቋል፡፡
ውድ አንባቢ ፤ ሁሉም ሰው እግዚአብሔርን የሚያገለግለው በጸጋው እንደሆነ መቼም ታምናለህ፡፡ የመዘመር ጸጋ ያለው ሰው የክርስቶስን መከራውን የሚገልጽ ዝማሬን ሲዘምር ሰዎች ዝማሬውን ተጠቅመው ከፈጣሪ ጋር በተመስጦ ይገናኛሉ፡፡ ጥሩ የመስበክ ጸጋ የተሠጠው ሰው ደግሞ የጌታን መከራ በርቱዕ አንደበቱ በመግለጽ ሰዎች በሕሊናቸው ወደ ቀራንዮ እንዲገሰግሱ ያደርጋል ፤ ጸሐፊው ደግሞ በብዕሩ መሣሪያነት ሰዎች የጌታን መከራ እንዲያስቡ ያደርጋል፡፡ ሠዓሊስ?
ጥሩ የመሣል ጸጋ ያለው ሰው እንደ ዘማሪው መዘመር ፣ እንደ ጸሐፊው መጻፍ ፣ እንደ ሰባኪው መስበክ ባይችል በተሠጠው ጸጋ የጌታችንን በደም የተለወሰ ፊት ፣ በመስቀል እንደ ቆዳ የተወጠረ ሰውነት በቀለምና በብሩሹ ተጠቅሞ በመሣልና በማሳየት ምስል መከሰትና ሰዎች የተዋለላቸውን ውለታ እንዲረዱ ማድረግ ይችላል፡፡ እንግዲህ ለቤተ ክርስቲያን ሥዕል አያስፈልግም የሚሉ ሰዎች በተዘዋዋሪ እያሉ ያሉት ‹‹ሠዓሊያን በተሠጣቸው ጸጋ አያገልግሉ›› ነው፡፡ (ይኼን ጉዳይ የሠዓሊያን ማኅበር ቢያስብበት ሳይሻል አይቀርም)
የሰባኪ ዓላማው ክርስቶስን በሰዎች ልቦና እንዲሣል ማድረግ ነው፡ ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ ‹‹ልጆቼ ሆይ ክርስቶስ በእናንተ እስኪሣል ድረስ ስለ እናንተ ምጥ ይዞኛል›› ብሎ ነበር፡፡ አክሎም ‹‹የማታስተውሉ የገላትያ ሰዎች ሆይ በዓይናችሁ ፊት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተሰቀለ ሆኖ ተሥሎ ነበር ፤ ለእውነት እንዳትታዘዙ ማን አዚም አደረገባችሁ›› ብሎም ገሥፆአቸው ነበር፡፡ (ገላ. 4:19 ፣ 3፡1) ይህ ሁሉ ጥረቱ ሰዎች ክርስቶስንና የመሰቀሉን ነገር በልባቸው እንዲሥሉ ማድረግ ነበር፡፡ በዚህ የሐዋርያው ንግግር ሁለት ነገሮችን መረዳት እንችላለን፡፡ አንደኛው ምጥ እስኪይዘው በሰዎች ልብ በስብከቱ ለመሣል የሞከረውን የክርስቶስ መከራ ሠዓሊ ቢሆን ኖሮ ሥሎ ከማሳየት እንደማይመለስ፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በጳውሎስ ትምህርት ሰዎች ጌታን እንደተሰቀለ ሆኖ በልባቸው መሣል (imagination) ከተፈቀደላቸው በልባቸው የሣሉትን የመስቀሉን መከራ የሥዕል ችሎታ ኖሯቸው በወረቀት ላይ ሲያሠፍሩት ኃጢአት ሊሆን አይችልም የሚለውን ነው፡፡
ሥዕልን መከልከል የሠዓሊነትን ጸጋ ለጣዖት አምልኮ እንጂ ለክርስትና የማይሆን ጸጋ ነው እንደማለት ነው፡፡ ‹ሥዕላት ከማስተማሪያነት ያለፈ እግዚአብሔርን ለማምለክ ይውላሉ ወይ?› ከተባለ መልሱ ስብከትና መዝሙር ለአምልኮ አይውልም ወይ ነው፡፡ ሥዕላት ማለት የተሣሉ ስብከቶች ፣ የተሣሉ መዝሙራት ናቸው፡፡ ሠዓሊያንም በቡሩሽ የሚሰብኩና የሚዘምሩ ድምፅ አልባ ሰባኪያንና ዘማርያን ናቸው፡፡
ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን በሥዕላት አማካይነት ፈጣሪዋን ታመልካለች ፣ ቅዱሳንን ደግሞ ታከብራለች እንጂ ሥዕላቱን አታመልክም፡፡ በመዝሙር ፈጣሪን ማምለክ ማለት መዝሙርን ማምለክ እንዳልሆነ ሁሉ በሥዕል ፈጣሪን ማምለክም ሥዕሉን ማምለክ አይደለም፡፡ በሥዕላቱ ፊት የምናደርገው ስግደትና አክብሮትም ለሥዕሉ ሳይሆን ለሥዕሉ ባለቤት ነው፡፡ በድርሳነ ሚካኤል ‹አኮ ዘንሰግድ ለረቅ ወለቀለም ወለ ግብረ ዕድ› ‹የምንሰግደው ለወረቀቱ ለቀለሙ ወይም ለሰው የእጅ ሥራ አይደለም› ተብሎ እንደተጻፈው በሥዕሉ ፊት የምናደርገው ነገር ሁሉ የሚመለከተው በሥዕሉ የተወከለውን አካል እንጂ ሥዕሉን አይደለም፡፡
በዓለም ታሪክ እንደሚታወቀው በስምንተኛው ክፍለ ዘመን በክርስትናው ዓለም የሥዕላት ውዝግብ (Icon controvercy) ተነሥቶ ብዙ ደም አፋስሶ ነበር፡፡ ክርስቲያኖች ሥዕላትን የሚያመልኩ (iconolatrilism) እና ሥዕላትን የሚጠሉ (iconoclasm) ሆነው በሁለት ጎራ ተከፍለው ነበር፡፡ በወቅቱ ሥዕል ጠሎቹ ከቄሣሩ ጋር ተመሣጥረው መተኪያ የማይገኝላቸውን ጥንታውያን ሥዕሎች ሲያቃጥሉና በመዶሻ ሲያፈርሱ ነበር፡፡ ቄሣሩም የክርስቶስን ሥዕል በመሬት ላይ አስነጥፎ እየረገጠ ‹እኔ ክርስቲያን ነኝ ይኼን ሥዕል ግን ጌታ ስላልሆነ እረግጠዋለሁ›› እስከማለት ደርሶ ነበር፡፡
የኒቆማድያው እስጢፋኖስ የተባለ አባት በቄሣሩ ፊት ታስሮ በቀረበ ጊዜ በወቅቱ የቄሣር ምስል ይታተምበት የነበረውን መገበያያ ገንዘብ ከመሬት ላይ ጥሎ ረገጠው፡፡ ወታደሮቹ ነገሩን ሳያስተውሉ ‹እንዴት የቄሣርን ምስል ትረግጣለህ› ብለው ሊመቱት ሲቃጡ ‹‹ይህ ቄሣርን የሚወክል ምስል እንጂ ቄሣር አይደለም ስረግጠው ግን ተቆጣችሁኝ ፤ የሰማይና ምድር ንጉሥ የክርስቶስ ምስልን ግን ቄሣራችሁ ሲረግጠው እያያችሁ ክርስቶስ አልተነካም ብላችሁ ዝም ትላላችሁ›› ብሎ ገሥፆአቸዋል፡፡
በዚህ በምዕራቡ ክርስትና የሁለት ጎራ ውዝግብ ያልተሳተፈችው ምሥራቃዊቷ ቤተ ክርስቲያናችን በዚያ ብትኖርም ኖሮ ሁለቱንም ጎራ አትደግፍም ነበር፡፡ ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያናችን ሥዕላትን አትጠላምም ፤ አታመልክምም፡፡ በሥዕላት የሚከበረው የሥዕሉ ባለቤት ነውና የሚሠጠውም ቦታ እንደተወከለው ባለቤት ማንነት ይወሰናል፡፡ ይህ ውዝግብ ያበቃው በታሪክ ሰባተኛው የአብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ (The seventh ecumenical council) ተብሎ በሚታወቀው ጉባኤ ላይ ቅዱስ ዮሐንስ ዘደማስቆን የመሳሰሉ አባቶች ባቀረቡት ሚዛናዊው ኦርቶዶክሳዊ አቋም ነው፡፡
ስለ ሥዕል መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረትና አስፈላጊነት ይህችን ታህል ካየን በሥዕላት ተአምር ይፈጸማል ወይ? የሚለውን አጭር ጥያቄ ተመልክተን እንቋጭ፡፡ ለዚህ ጥያቄ መልሱ ‹‹ጳጳሱ ቅስና አላቸው ወይ›› ብሎ ለጠየቀው ‹‹ተርፏቸው ይናኙታል›› የተባለው መልስ ትዝ አለኝ፡፡ ሥዕላት ተአምር እንደሚሠሩ ከማስረዳት መልሱ ኪሩቤል የተሣሉባት ታቦተ ጽዮን ተአምር ሠርታለች ወይ ብሎ መጠየቅ ይቀልላል፡፡
የቅዱስ ጴጥሮስ ጥላው ያረፈባቸውን ሕሙማንን ይፈውስ ነበር፡፡ (ሐዋ. 5፡15) የጴጥሮስ ጥላው ያለ ብሩሽ በብርሃን ረዳትነት የተሣለ ሥዕሉ አይደለምን? የጳውሎስስ ልብስ አልፈወሰምን? (ሐዋ. 19፡11) ልብሱስ የጳውሎስ በረከት ያደረበት ጨርቅ አይደለምን? በፈጣሪና በቅዱሳኑ ስም የተሣሉ ሥዕላትም በራሳቸው ኃይል የላቸውም፡፡ በሥዕላት የተወከሉት ቅዱሳን ግን ከፈጣሪ በተሠጣቸው ሥልጣን በሥዕሉ ላይ ተአምር ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ ለዚህም ከጥቅስ ይልቅ ወዝ የሚፈስሳቸውን የእመቤታችንን ሥዕላት ፣ በሀገራችን ዓመት ጠብቆ በማሕሌት መካከል በከበሮው ምት ትክክል በሥዕሉ ላይ ያለው ፈረስ የሚዘልለው የቅዱስ መርቆሬዎስ ሥዕልን እንድትጎበኙ እንጋብዛለን፡፡