>

ለትግራይ ክልል አስቸጋሪ ሁኔታ፣ ምን ይበጅ ይሆን ? (ደረጀ መላኩ - የሰብዓዊ መብት ተሟጋች )

የኢትዮጵያ ነባራዊ የፖለቲካ ሁኔታ በእኔ እይታ

ደረጀ መላኩ ( የሰብዓዊ መብት ተሟጋች )

Tilahungesses@gmail.com

ለብሔራዊ ውይይት ይበጅ ይሆን በሚል ቀና መንፈስ የቀረበ

ክፍል ሁለት

 ለትግራይ ክልል አስቸጋሪ ሁኔታ፣ ምን ይበጅ ይሆን ?

የህውሃት የፖለቲካ ፊትአውራሪዎች ከማእከላዊ የመንግስት ስልጣን ተሸቀንጥረው ከወደቁ ወዲህ ( ከ2010 ዓ.ም. ወዲህ ) መቀመጫቸውን ሰሜን ትግራይ መቀሌ ከተማ ማድረጋቸው የሚታወቅ ጉዳይ ሲሆን ሆኖም ግን ይሁንና የኢትዮጵያ መንግስት ህግን ለማስከበር ባደረገው ጦርነት ቅዳሜ ህዳር 19 ቀን 2013 ዓ.ም. መቀሌን ከተማን በመቆጣጠሩ ምክንያት በማእከላዊው መንግስት የሚታደኑት የወያኔ ፖለቲካ ፊተአውራሪዎች መቀሌን ለቀው መሄዳቸውን የሚሳዩ ዜናዎች ከመገናኛ ብዙሃን ተሰምቷል፡፡ 

በነገራችን ላይ የትግራያን ህዝብ የሰብአዊ ጋሻ በማድረግ ጦርነቱን የጀመሩት የህውሃት የጦር መሪዎችና ጋሻ ጃግሬዎቻቸው በውሸት የታጀለ ምክንያቶችን በማቅረብ በደል እንደደረሰባቸው ለአለሙ ህብረተሰብ የሚያሰሙት አቤቱታና ጩሀት በቀላሉ የሚታይ አይመስለኝም፡፡ ምንም እንኳን ሰዎቹ የሚያቀርቡት አቤቱታ መሰረት የሌለውና ውሸት ቢሆንም ችግሩን ቻላ ማለት ወደ መፍትሔ አይወስደንም፡፡ ሁላችንም እንደሚገባን በጦርነት በተለይም በአንድ ሀገር ውስጥ በሚገኙ ሀይሎች ( ለአብነት ያህል በማእከላዊው መንግስትና በትግራይ ልዩ ሀይልና ሚሊሻ ጦር መሃከል እየተካሄደው ባለው ጦርነት ) አሸናፊና ተሸናፊን ለማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ ስለሆነም በእኔ በኩል አራት መሰረታዊ ቁምነገሮች ትኩርት እንዲሰጣቸው ሳስታውስ በአክብሮት ይሆናል፡፡

1.የአብዛኛው ትግራይ ህዝብ ምርጫ የወያኔ ህውሃት ድርጅት እንዳልሆነ ማወቁ ተገቢ ሳይሆን አይቀርም ( በእኔ አስተሳሰብ ህውሃት ሲባል በመቶ የሚቆጠሩትን ከፍተኛ መሪዎችን ብቻ የሚያካትት ብቻ ሳይሆን በመቶሺዎች የሚቆጠሩትን አባላቱን ያጠቃልላል፡፡ ስለሆነም ከጦርነቱ ፍጻሜ በኋላ የህውሃት የጎሳ ድርጅት፣ እንድ አንድ የፖለቲካ ድርጅት ህልውናው ይቀጥል ይሆን የሚለው መሰረታዊ ጥያቄ የኢትዮጵያ ጉዳይ እንቅልፍ የነሳቸው ኢትዮጵያውያን ጥያቄ ይመስለኛል፡፡

 1. የቀድሞዋ የትግራይ ጠቅላይ ግዛት ዛሬ የትግራይ መስተዳድር የአብዛኞቹ ኢትዮጵያውያውያን የታሪክና የባህል መሰረት እንደሆነች መዘንጋት የለብንም፡፡
 2. በነገራችን ላይ የትግራይ ጉዳይ ወያኔዎች ምን ያህል እንደተጠቀሙበት፣ ምን ያህል የኢትዮጵያን ህዝብ ሀብት ለማጋበስ ማወቅ አለብን፣ እነኚህ እኩያን በትግራይ ህዝብ ስም ኢትዮጵያውያንን ሁሉ እሪ ኡ ኡ ያሰኘ ግፍ እንደሰሩ፣ በክላስትር ኢኮኖሚውን፣ የጦር ሀይሉን ለመቆጣጠር ያደረጉት ጥረትና ገቢራዊነት እንዲህ በአጭር ግዜ አይዘነጋም ፡፡
 3. የወያኔ ጥያቄ እና ነባራዊ እውነታው በፍጹም የተለያዩ ናቸው፡፡ በነገራችን ላይ ጸሃፊው ከህውሃት የፖለቲካ ፊትአውራሪዎች ወይም ጋሻ ጃግሬዎች ጋር ምንም አይነት ጥላቻ የለውም፡፡ ጸሃፊው የህውሃት መሪዎችና አባላት አስተሳሰብ ግን ለኢትዮጵያ አይበጃትም ብሎ ያምናል፡፡

በእኔ አስተያየት ወያኔዎች የማእከላዊው መንግስትን ስልጣን ለመቆጣጠር በፍጹም ሀይል ወይም አቅም እንደሌላቸው በሚገባ ያውቁታል፡፡ ጦርነት የከፈቱት የማያሸንፉትን እውነት ለማሸነፍ ነበር ፡፡ ግን አልቻሉም፡፡ ስልጣንን ለዝንት አለም ለመጨበጥ የቀየሱት ዘዴ መልሶ ለራሳቸው መርዝ ሆኖባቸዋል፡፡ ወያኔዎች ራሳቸው አርቅቀው ላጸደቁት ህገመንግስት ሳይቀር ተገዢ መሆን ያልቻሉ፣ በየጊዜው ህገመንግስቱን የጣሱም ጉዶች ነበሩ፡፡ 

የእስከአሁኑ እርምጃ እንደተጠበቀ ሆኖ የኢትዮጵያ መንግስት ግጭቶችን የማስወገድ ዘዴ ዘመናዊና ውጤታማ መሆን አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡ ግጭትን የማስወገጃ ዘዴዎች ግጭቶችን የሚያባብሱ ሳይሆኑ ፣ ለግጭቶች አለመኖር ሁነኛ መፍትሔ ሰጪዎች መሆን አለባቸው፡፡

እዚህ ላይ የፖለቲካ መልካም ፈቃደኝነት ወሳኝ መሆኑን ማስታወስ ተገቢ ሳይሆን አይቀርም፡፡ አንደኛው የፖለቲካ ቡድን ሌላውን መውቀስ ብቻውን መፍትሔ አያመጣልንም፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ችግሮች መሰረታዊ በሆነ ሁኔታ ለመፍታት መዘጋጀትም ያለበት ይመስለኛል፡፡ በእኔ አስተያየት በኢትዮጵያ ምድር የሰፈነውን ፖለቲካዊ ችግር ከስር መሰረቱ ለመፍታት ያስችል ዘንድ ብሄራዊ የውይይት እና እርቅ መድረክ መዘጋጀት ያለበት አይመስለኝም፡፡ ለዚህ እውን መሆን የእውነታና እርቅ ኮሚሽን መመስረት ያለበት ይመስለኛል፡፡

ተጠያቂነት፣ የፖለቲካ መልካም ፈቃደኝነት እና ግልጽነት፣ የሃሳብ ልእልና ከስምምነት ላይ ለመድረስ በእጅጉ ጠቃሚ ቁምነገሮች ናቸው፡፡ መንግስት እና የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ለሀገሪቱ ጥቅም ሲሉ እውነተኛ እርቅ ለመፍጠር ፍላጎቱ ካላቸው የተተቀሱትን ዘዴዎች መተግበር ግድ ይላቸዋል፡፡ ከዚህ ባሻግር የሀገሪቱን አንድነት ለማስከበር የማህበራዊ ባህልና ታሪክ እጅጉን ጠቃሚ መሆናቸውን ማወቅ ያለብን ይመስለኛል፡፡ ለዚህ ደግሞ በሀገሪቱ የሚገኙ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ እና አመራር በቅንነትና በታማኝነት መነጋገር ያለባቸው ይመስለኛል፡፡ ሁለቱም በእውነት መሰረት ላይ ሆነው መተባበር የቅንጦት ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው፡፡

በነገራችን ላይ በሚነሱ ጥያቄዎችና በመሬት ላይ ያለው የፖለቲካ እውነታ የሚገናኙ አይደሉም፡፡ ለአብነት ያህል የትግራይ ነጻ አውጪ ወይም ህውሃት የሚያነሳቸው ጥያቄዎችና በመሬት ላይ ያለው እውነት አይጣጣምም፡፡ ሆኖም ግን የኢትዮጵያ ህዝብ፣ የኢትዮጵያ መንግስት ሀላፊነትና ተጠያቂነት በተሞላበት መንፈስ ወንጀለኞች ለፍርድ የሚቀርቡበትን መንገድ በፍጥነት እንዲያካሂድ በጉጉት እየጠበቀ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄ መሰረታዊ የኢትዮጵያ ችግሮች በእውነትና ሀቅ መሰረት ላይ እንዲፈቱለት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ በወያኔ አገዛዝ መሪር ሀዘን ውስጥ ወድቆ ስለነበር፣ ከእንግዲህ ወዲያ የነጻነት አየር መተንፈስ ፍላጎቱና ምኞቱ ነው፡፡ ምኞት ብቻም አይመስለኝም ገቢራዊውም እንዲሆን ይፈልጋል፡፡

ህገመንግስቱ

ህገመንግስቱ በግሪክ አፈታሪክ የተጠቀሰውን ፓንዶራ ያስታውሰናል፡፡ ‹‹ ዘስ ተብሎ ይታወቅ የነበረ ንጉስ ፓንዶራ የተሰኘውን ሳጥን የፕሮሜተስ ወንድም በሆነው ኢፒሜተስ ላይ አስቀምጦት ነበር፡፡ ይህ የፓንዶራ ሳጥን ሲከፈት በውስጡ በሽታ፣ ሞት እና ሌሎች በርካታ ሰይጣናዊ ድርጊቶች ተገኝተዋል፡፡ በመጨረሻም እነኚህ ወደ አለም ተሰራጭተዋል፡፡

The constitution reminds us of the Greek mythology of Pandora. “Zeus, the king of the gods, took vengeance by presenting Pandora to Prometheus’ brother Epimetheus. Pandora opened a jar left in her care containing sickness, death, and many other unspecified evils, which were then released into the world.”[2]

ወያኔ እና አፋሽ አጎንባሾቹ የነበሩ የፖለቲካ ሀይሎች፣ አድርባይ ምሁራኖች በፌደራል ስርአት ስም ለኢትዮጵያ ህዝብ ያቀረቡት የፓንዶራ ሳጥን ስጦታ ህገመንግስቱ ነው፡፡ ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል ልዩነትን ማስፋት፣ ጥላቻን ማራገብ፣ የኢትዮጵያን የብዙ ሺህ አመታት ታሪክ አለመጥቀስ፣ በህገመንግስቱ ውስጥ ‹‹ ህዝብ ›› የሚለውን ቃል ‹‹ ህዝቦች ›› በማለት ማስቀመጥ፣ ድምጽ በለሌው መሳሪያ የህዝቡን አንድነት ማላላት፣ ኢትዮጵያዊ ዜግነትን ባይተዋር ያደረጉ ክልሎችን መፍጠር ወዘተ ወዘተ በወያኔ እና ጋሻ ጃግሬዎቹ በኢትዮጵያ ምድር ላይ የተረጩ መርዞች ነበሩ፡፡

አሁን ድረስ የወያኔ መርዝ ማርከሻው ሙሉበሙሉ የተገኘለት አለመስልህ አለኝ፡፡ ስለሆነም በእኔ አስተሳሰብ ወያኔ እና የፖለቲካ ሸሪኮቹ ያጸደቁት ህገመንግስት ፍጹም ሰላማዊ እና በሰለጠነ መንገድ የኢትዮጵያ መንግስት፣ የፖለቲካ ተፎካካሪዎች፣ የሲቪል እና የሙያ ማህበረሰቡ መሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ተወካዮች የሚገኙበት አንድ የምክክር ጉባኤ መዘጋጀት ያለበት ይመስለኛል፡፡ ይህንን ሀገራዊ ጉባኤ ለማዘጋጀት ሀላፊነቱን የሚወስደው ከማናቸውም ወገኖች ገለልተኛ የሆነ ድርጅት  ቢሆን ውጤታማ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ይህንን ገቢራዊ ለማድረግ መንፈሳዊ ወኔ ከከዳን ለችግራችን ሰራሄ መፍትሔ የምናገኝ አይመስለኝም፡፡ ነገሩ ውሃ ወቀጣ ሆኖ ይቀራል፡፡ በነገራችን ላይ አሁን ያለው የኢትዮጵያ ህገመንግስት ቢሻሻል እንኳን ላለፉት ሃያምናን አመታት የተከሰቱ ችግሮች ጠባሳ ለመሻር ብዙ ጊዜያትን እንደሚፈጁ ነው፡፡ ስለሆነም ህገመንግስቱ ይሻሻል ተብሎ ሲጠየቅ ቅንጦት ሳይሆን፣ የህልውና ጉዳይ መሆኑን ማወቅ ብልህነት ነው፡፡

ሀገሪቱን ወደ ተሻለ የእድገት ጎዳና ለመውሰድ፣ ምሉሄበክሉሄ የፖለቲካ ነጻነት እንድትጎናጸፍ ከተፈለገ ህገመንግስቱ በነጻነትና በእኩልነት መንፈስ መሻሻል አለበት፡፡ ይገባኛል ህገመንግስቱን ከማሻሻል አኳያ መጠነ ሰፊ ደንቃራዎች አሉ፡፡ ህገመንግስቱን ለማሻሻል እንደው ዝም ብሎ ቁጭ ብሎ ወደ ሰማይ በማንጋጠጥ፣ ወደ እግዜአብሔር ብቻ በመጮህ የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ህገ መንግስቱ ለኢትዮጵያ ህዝብ ጠንቅ ነው፣ ለኢትዮጵያ አይበጃትም የሚሉ ወገኖች በአንድ በኩል፣ ህገመንግስቱ ለኢትዮጵያ ህዝቦች አንድነት ዋስትና ነው የሚሉት የብሔር ፖለቲካ ድርጅቶች መሪዎች በሌላ በኩል ማዶ ለማዶ ሆነው መጮህ ለኢትዮጵያ የሚበጃት አይመስለኝም ፡፡ ሁለቱም ሀይሎች ከላይ ከጠቀስኳቸው ኢትዮጵያውያን ጋር ቁጭ ብለው በሰለጠነ መንገድ እንዲወያዩ እማጸናለሁ፡፡ ይህን ማድረግ ከተሳነን ሰላምና አንድነት ምኞት ብቻ ሆነው ይቀራሉ፡፡ በነገራችን ላይ አሁን ያለው ህገመንግስት በተለይም  ‹‹ የሰብዓዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን ›› በተመለከተ ያካተታቸው አንቀጾች በአለም አቀፍ ደረጃ ሳይቀር ተቀባይነት ያላቸው ናቸው፡፡ በሌላ አነጋገር በአለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሰነዶች ላይ የተካተቱ አብዛኞቹ አንቀጾች በኢትዮጵያ ህገመንግስት ውስጥ አሉ፡፡ በሌላው የሳንቲሙ ግልባጭ ደግሞ ህገመንግስቱ የያዛቸው አንዳንድ አንቀጾች መርዝ ብቻ ሳይሆኑ፣ ጊዜውን ጠብቆ እንደሚፈነዳ ፈንጂ አይነት ናቸው፡፡ ለአብነት ያህል በርካታ ስመጥር ኢትዮጵያዊ ምሁርን በጥናት ወረቀቶቻቸው ላይ አበክረው እንዳሰፈሩት አንቀጽ ‹‹ 39 ›› ግዜውን ጠብቆ እንደሚፈነዳ ፈንጂ አይነት ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ልብ ልንለው የሚገባን የፌዴራል አወቃቀሩ ላይ ብቻ በርካታ ልዩነቶች አሉ፡፡ እንዲህ አይነት ልዩነቶቻችንን በሰለጠነ መንገድ ቁጭ ብለን ተነጋግረን መፍታት ለነገ የሚባል አይደለም፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያዊ ስርአታዊ፣ ህገመንግስታዊ እና ፖለቲካዊ መፍትሔ የሚሰጣትን መንግስት ትሻለች፡፡

በነገራችን ላይ ህገመንግስታዊ ስርአት ቢያንስ በንድፈ ሀሳብ ደረጃ የፖለቲካ መረጋጋትን የሚያስገኝ እንደሆነ የታወቀ ጉዳይ ነው፡፡ በሌላ በኩል ዲሞክራሲ በህዝብ መሃከል ግጭቶች እንዳይከሰቱ ወይም ግጭቶች ከተከሰቱ በኋላ በሰለጠነ መንገድ ለመፍታት የሚያስችል ነው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ባለፉት ሁለት አስርተ አመታት ስልጣን ኮርቻ ላይ ተፈናጠው የነበሩት ህውሃቶች ግጭቶች ሲከሰቱ ከህገመንግስቱ ጋር ለማያያዝ ነው የሚሞክሩት ፡፡ የህግ አውጪውን፣ ህግ ተርጓሚውን እና ህግ አስፈጻሚውን ስልጣን ሙሉበሙሉ ተቆጣጥረውት ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ወይም በውጤቱ የሥልጣን ሚዛን በኢትዮጵያ ተሰብሮ ቆይቷል፡፡ ወይም የስልጣን ሚዛን አደጋ ላይ ወድቋል፡፡

ስለሆነም የፌዴራል ስርአትና የስልጣን ክፍፍልን ገቢራዊ ማድረግ መንግስት ጨካኝ እና አፋኝ እንዳይሆን ይረዳል፡፡ መንግስት ለተወሰኑ ጎሳዎች ብቻ የቆመ መሆን የለበትም፡፡ መንግስት ለኢትዮጵያውያን ሁሉ እኩል መቆም አለበት፡፡ መንግስት ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በእኩልነት መንፈስ ስለመቆሙ በነቢብም በገቢርም ማሳየት መንግስታዊ ግዴታው ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ መንግስት የወያኔ ቡድንን መጨረሻ ካወቀ በኋላ ህውሃት ጥሎ የሚሄደውን በርካታ የፖለቲካ ጠባሳ ጉዳዮችን በፍጥነት መፍትሔ መስጠት አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡

ታሪክ እንደሚያስተምረን ዲሞክራሲ እና ህገመንግስት ብቻቸውን ምንም ቁም ነገር ሊሰጡን አይቻለቸውም፡፡ ዲሞክራሲም ሆነ ህገመንግስት በስልጣን ጥመኞች ሊጨናገፉ ይችላሉ፡፡ ዲሞክራሲም ሆነ ህገመንግስቱን ለራሳቸው ስልጣን ማስጠበቂያ ብቻ ገቢራዊ ሲያደርጓቸው አይተናል፡፡

እኛ ህገመንግስቱ በልዩነት አንድነትን የሚያጎናጽፍ ፣ የህዝብ ፍላጎትን የሚያሟላ፣ የዒትዮጵያን የረጅም ጊዜ ታሪክ ያካተተ እንዲሆን እንፈልጋለን፡፡ ይህ ካሆነልን ግን እጣ ፈንታችን አንድ እርምጃ ወደፊት፣ ሁለት እርምጃ ወደኋላ መሆኑ አይቀሬ መራር ሀቅ ነው፡፡ 

ማስታወሻ፡- የህገ መንግስት መሻሻል ለኢትዮጵያ መጻኢ እድል እና ለሀገሪቱ አንድነት ማስተማመኛ ነው፡፡ አሁን ባለው ህገመንግስት ማናቸውም ኢትዮጵያውያን የሚጠቀሙ አይመስለኝም፡፡ ከተሳሳትኩ ልታረም ዝግጁ ነኝ፡፡

የሚበጀን አንድነት እንጂ፣ መለያየት አይመስለኝም (Let us Uphold Unity and Trample the Division-) 

 

 • በየእለቱ በየቀኑ፣ በየሰአቱ ስለሀገራችን አሳሳቢ ሁኔታ መወያየት፣ መነጋገር፣ የራሳችንን መፍትሄ መሻት ኢትዮጵያዊ ግዴታችን ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ በእለታዊ ውይይታችን ላይ ስለብሔራዊ አንድነታችን በተመለከተ መነጋገር ከተሳነን አንድነታችን አደጋ ላይ ይወድቃል፡፡ ለምን አንድነታችን ላላ፣ አፈርድሜ ጋጠ፣ ወደ መሃል በመምጣት ለምን መስማማት አቃተን ወዘተ ወዘተ ለሚሉት መሰረታዊ ጥያቄዎች እያንዳንዱ ሰው ወይም ኢትዮጵዊ በሰውነት ደረጃ ላይ ቆሞ መወያየት መፍትሔ መፈለጉ የሰውነት ባህሪ ነው፡፡ በውይይታችን ላይ መከባበር፣ ከጎሳ ማንነት በፊት የሰውነት ባህሪን ማስቀደም፣ ሰውን ሊከፋፍሉ ከሚችሉ አስተያየቶች በመቆጠብ ወደ መሃል መንገድ የሚወስዱ የስምምነት ጎዳናዎችን መጥረግ ከኢትዮጵያውያን ይጠበቃል፡፡
 • የአንድን የጎሳ ቡድን አባላት መፈረጅ፣ ወይም ማግለል ልዩነትን ያሰፋል፣ መልካም ግንኙነትን ያሻክራል፡፡ ማናቸውም የኢኮኖሚና የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ታላቅ ውጤት ሊያመጡ የሚችሉት ጠንካራ እና አንድነቷን የጠበቀች ሀገር ስትኖር እንደሆነ ማወቅ አለብን፡፡
 • ፖለቲካ በልብ ውስጥ ያለ ነው፡፡ ፖለቲካ የቃላት ጦርነት የሚካሄዱበት የጦር ሜዳ ነው፡፡ ጦርነት በሰዎች ንቃተ ህሊና ውስጥ የሚደረግ ውድድር ነው፡፡ ስለሆነም የእኛ ፖለቲካ ከክፍፍል  ይልቅ ስለ አንድነት መስበክ ይኖርበታል፡፡ከአንድነት አኳያ  የህዝብ ንቃተ ህሊና ከፍ ማለት ያለበት ይመስለኛል፡፡ በነገራችን ላይ አንድነት የሚመጣው ከመንግስት አኳያ ከሚደረግ ጥረት ወይም ውሳኔ ብቻ አይደለም፡፡ ህዝቡ እራሱ የአንድነትን ጥቅም በመረዳት ተከባሮ እና ተፋቅሮ ወደ አንድነት የሚወስደውን ጎዳና ማዘጋጀት አለበት፡፡ ከዚህ ባሻግር የተከፋፈሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የፖለቲካ ልሂቃን ራሳቸው የህዝቡን አንድነት ይጎዳሉ፡፡ ግራም ነፈሰ ቀኝ ለኢትዮጵያ አንድነት ወሳኙ አካል ግን የኢትዮጵያ ህዝብ ስለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ለዚህ ምስክሩ ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ ለብዙ ሺህ አመታት አንድነቱን ጠብቆ አሁን ድረስ መቆየቱ ነው፡፡
 • ምንአልባት ሌሎች ተጨማሪ ራስገዝ ክልሎች እንዲኖሩ የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ለዚህ እውን መሆን ግን ዲሞክራቲክና ነጻነቱን የጠበቀ ውሳኔ ህዝብ ግድ ይላል፡፡
 • ሁላችንም እንደምናስታውሰው  ከሁለት አመት በፊት ኢትዮጵያ ሀገራችን በከባድ ፈተና ውስጥ ነበረች፣ የሀገሪቱ አንድነትም አደጋ ላይ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና  ከዛ አሳሳቢ የፖለቲካ አጣብቂኝ በመውጣት ዛሬ ላይ ደርሰናል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ሀገራችን በድጋሚ አደጋ ውስጥ እንዳትወድቅ በብርቱ መጨነቅ መጠበብ አለብን፡፡ ዳግም ወደ ጎሳ ፖለቲካ ውስጥ መዶል የለብንም፡፡ ዛሬም ኢትዮጵያን ከሞት አፋፍ ለማዳን ጊዜ እድሉን ሰጥቶናል፡፡ እንጠቀምበት፡፡ ካለፈው ከባድ ስህተት ተምረን አንድነታችንን ማጥበቅ አለብን፡፡ እባካችሁ ውድ ኢትዮጵያውያን አባቶች፣ እናቶች፣ ወንድሞች፣ እህቶቻችን ወደ ቀልባችን እንመለስ፡፡  የአበራሽን ጠባሳ ያየ በእሳት አይጫወትም፡፡ 
 • የግል ማስታወሻ፡- እድል ለሌላ ተጨማሪ ግዜ ከውድቀት ያድነናል ብለን ማሰብ የለብንም፡፡ እራሳችንን መጠበቅ አለብን፡፡ እንደ አንድ የተማረ እና ማሰብ የሚችል ሰው ለሀገራችን አንድነት መስራት አለብን፡፡ ይህን ገቢራዊ ለማድረግ መንፈሳዊ ወኔ ከታጠቅን ለችግሮቻችን መፍትሔ ማግኘት ያስችለናል፡፡
 • በሀገራችን ለግጭት እና እልቂት የሚወስዱ ጎዳናዎችን መገንባት የለብንም፡፡ ኢትዮጵያውያን ራሳችንን ከአደጋ ለመከላከል የሚከተሉትን መፈጸም አለብን

 

 1. መከፋፈል ( መለያየትን) ፤- አንተ እከሌ ነህ፣ እነርሱ እነ እከሌ መባባሉ ይቅር
 2. መከባበር፣መቻቻል፣ራስን ማክበር፣ የሰው ልጅን መብትና ክብርን መጠበቅ የዘውትር ተግበራችን ይሁን
 3. የጥላቻ ንግግርን ማስቀረት
 4. የክልል ሚሊሻዎችን ቁጥርን መቀነስ ከተቻለም ማሰልጠን ማቆም፡፡ በምትኩ የክልል ሚሊሻዎች ( ወይም የክልል ልዩ ሀይል ተብለው የሚጠሩት) ወታደራዊ ስልጠና ከተሰጣቸው በኋላ በፌዴራል መከላከያ ሰራዊት ውስጥ የሚቀላቀሉበት መንገድ ቢፈለግ
 5. በአንዳንድ አካባቢዎች ጎሳን ወይም ሀይማኖትን መሰረት ያደረጉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዲቆሙ መጠየቅ ወይም መከላከል የኢትዮጵያ ህዝብ ጉዳይ መሆን አለበት፡፡
 6. ለኢትዮጵያ ሰላም ማጣት ካንሰር የሆኑ የፖለቲካ ቡድኖችን መለየትና አለመተባበር የኢትዮጵያ ህዝብ ጉዳይ ነው፡፡

ከላይ ያሰፈርኳቸው አንኳር ነጥቦችና ሌሎች ለአብሮነት ህይወታችን እጅጉን ጠቃሚ የሆኑ ተግባራቶችን ለመከወን መንፈሳዊ ወኔ መታጠቅ ከቻልን በሀገራችን ሰላም ይሰፍናል፣ ወደ የምንመኛው የእድገት ጉዞ መራመድ ይቻለናል፡፡

በሌላ በኩል እውነተኛው የፌዴራሊዝም ተፈጥሮ በተለያዩ ምክንያቶች በክልሎች ውስጥ የሚቀሰቀሱ ግጭቶችን እና አለመረጋጋቶችን መቆጣጠር የሚያስችል መሆኑ መታወቅ ያለበት ይመስለኛል፡፡ ስለሆነም በኢትዮጵያ ያለው የፌዴራል ስርአት በዲሞክራቲክ መሰረት ላይ እንዲቆም ኢትዮጵያውያን መወያየት መነጋገር አለባቸው ብዬ አስባለሁ፡፡

ሥራ እጥ ወጣቶች፣ በኢኮኖሚ ድቀት ውስጥ ያለ ህዝብ ትእግስቱን ያጣል፣ መልካም ጊዜ ይመጣ ይሆን በማለት ተስፋ ያደርጋል፣ በታጠቁ ቡድኖች ንብረቱን የሚዘረፍ ህዝብ፣ ህይወቱን የሚያጣ ግለሰብ ቤተሰብ፣ በጎሳ ማንነታቸው ብቻ ጥቃት የሚደርስባቸው ዜጎች በዚህ አይነት ምስቅልቅሎሽ ውስጥ መኖር የሰውነት ተፈጥሮአቸው አይፈቅድላቸውም፡፡ ይህም ብቻ አይደለም በተወሰኑ አካባቢዎች የተከሰተው አለመረጋጋት በቶሎ መፍትሔ ካልተበጀለት በብዙ የሀገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ሁከት ሊበራከት ይቻለዋል፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያ መንግስት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሰብዓዊ መብት የሚደፈጥጡ ግለሰቦችን በህግ ፊት ማቅረብ፣ የሠብዓዊ መብቶች የማስከበር መንግስታዊ ሀላፊነቱን መወጣት አለበት የሚለው ሌላው መልእክቴ ነው፡፡ ከዚህ ባሻግር የክልላዊ መስተዳድር ሀላፊዎች የተሰጣቸውን ሀላፊነት በህግ መሰረት ላይ ሆነው መፈጸማቸውን የማእከላዊው መንግስት ማረጋገጥ ያለበት ይመስለኛል፡፡ ይህን ገቢራዊ ለማድረግ ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ማወቅ ያለብን ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም በክልላዊ መንግስታት ስራ ላይ ጣልቃ ሳይገባ የተሰጣቸውን መንግስታዊ ሀላፊነት ስለመወጣታቸው በህግ መሰረት ላይ ሆኖ መቆጣጠር አስፈላጊ በመሆኑ ይመስለኛል፡፡ በአጭሩ ፍትህ፣እርትእ እና እኩልነት እንዲከበሩ የመንግስት አካላት ሁሉ መንግስታዊ ሀላፊነታቸውን መወጣት ግዴታቸው ነው፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ልዩነት መከበር እንዳለባቸው አምናለሁ፡፡( ለአብነት ያህል ማንም ሰው የራሱ አመለካከት ሀሳብ ሊኖረው ይቻለዋል፡፡ ይህ ወንጀል አይመስለኝም) ከዚህ ባሻግር  ከአንድ ቡድን የበላይነት ይልቅ እኩል ውክልና ለኢትዮጵያ የፖለቲካ መረጋጋት እጅጉን ጠቃሚ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ በሀገሪቱ የፖለቲካ አውድ እንዳይካፈል የታገደ ቡድን ካለ ለግጭት በር ይከፍታል፡፡ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎችና መንግስት በመከባበር ላይ የተመሰረተ ትብብር ማድረግ አለባቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ የአብዛኛውን ህዝብ ድጋፍ አገኘሁ የሚለው ፓርቲ አላማውን ወይም ፕሮግራሙን በሌሎች ፓርቲዎች ላይ በግድ መጫን የለበትም፡፡ መንግስት በማናቸውም መልኩ አንድነትን የሚያጠነክሩ ተግባራትን መከወን ለኢትዮጵያ የሚጠቅማት ነው፡፡

የምርጫ ጉዳይ

በያዝነው አመት ኢትዮጵያ ምርጫ ለማድረግ ዝግጅት ላይ ስለመሆኗ ከተነገረ ወራቶች እየተቆጠሩ ነው፡፡ በነገራችን ላይ የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ችግሮች ለመፍታት አንዱ ቁልፍ ፍትሃዊ፣ ርትኣዊ፣ ነጻና ገለልተኛ የምርጫ ውድድር ማዘጋጀት እንደሆነ ክርክር ያለው አይመስለኝም፡፡ በንድፈ ሀሳብ ደረጃ ምርጫ የዲሞክራሲና የመልካም አስተዳደር መሰረት ነው ተብሎ ይታመናል፡፡ ሆኖም ግን በኢትዮጵያ የፖለቲካ አውድ ውስጥ ርእዮት አለምን መሰረት አድርገው የሚፎካከሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በብዛት ለማየት አልታደልንም፡፡ በኢትዮጵያ ስልጣን ለመጨበጥ ፉክክር ከሚያደርጉት የፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ አብዛኞቹ የጎሳ ፖለቲካ ድርጅቶች ናቸው፡፡ ስለሆነም በተለይም ባለፉት የኢትዮጵያ የምርጫ ውድድሮች ላይ ( ከግንቦት 1997 ዓ.ም. ምርጫ በቀር፣ በዚህም ግዜ የጎሳ በጥቂቱም ቢሆን የጎሳ ፍላጎት ያከላቸው ከገዢውም ከተቃዋሚው ጎራ ታይተው ነበር) የጎሳ ፍላጎቶች ጎልተው ይታዩ ነበር፡፡ በመጪው የምርጫ ውድድርም ቢሆን የፖለቲካ ፓርቲዎች ራሳቸውን ከርእዮት አለም ፍልስፍና ለማዘጋጀት መንፈሳዊ ወኔ መታጠቅ ከተሳናቸው የተጠቀሰው ችግር በከፋ መልኩ መደገሙ የማይቀር ነው፡፡ በሌላ አነጋገር የጎሳ ፍላጎት በምርጫው ሂደት ላይ ትልቅ ተጽእኖ ይኖረዋል፡፡

ለእኔ የጎሳ ቡድን ያዘጋጀሁት ምርጥ ፖሊሲ አለኝ፣ ለጎሳ ቡድን አባላቴ በርካታ መዋእለ ንዋይ ለመገንባት ዝገጁ ነኝ ወዘተ ወዘተ በማለት የፖለቲካ ፉክክር ማድረጉ በአንድ ጎሳ ቡድን ውስጥ ያሉ አባላትን ሳይቀር አንድነት ሊያላላ ያስችለዋል፡፡ በእንዲህ አይነት የፖለቲካ አውድ ውስጥ ሆነን አንድነታችንን ለማጠንከር እንቸገራለን፡፡

በመጪው ምርጫ ውድድር ላይ የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከርእዮት አለም አኳያ ቢያንስ ወደ ግማሽ መንገድ ድረስ በመምጣት መስማማት አለባቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ ሰጥቶ መቀበል በሚለው የፖለቲካ አስተምህሮ መነቃቃት አለባቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ ከሁከት ውስጥ ለመውጣት ንቁ ተመልካች እና ንቃተህሊናው የዳበረ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ማፍራት ግድ ይለናል፡፡ በደመነፍስ የምንደግፋቸው የፖለቲካ ድርጅቶች ነገ ተነገወዲያ አንገት ሊያስደፉን ይቻላቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ የሚነጋገሩ፣ የሚደማመጡ፣በሃሳብ የሚሟገቱ፣ የሃሳብ የበላይነት ያላቸውን የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችን በብዛት ትሻለች፡፡ እኛ የተለያዩ የጎሳ ቡድን አባላት ልንሆን እንችላለን፡፡ ነገር ግን ሁላችንም ኢትዮጵያ በምትባል በአንድ ሀገር ውስጥ እንደምንኖር ማወቅ አለብን፡፡ ከጎሳ ማንነታችን በፊት ኢትዮጵያን እናስቀድም፡፡ ይህ የሰውነት ባህሪ ነው፡፡

ክፍል 3 ይቀጥላል

Filed in: Amharic