>
5:13 pm - Saturday April 19, 9023

ከአማርኛ ቋንቋ አተረፍን እንጂ አልጎደለብንም....!  (ሙስጠፋ ዑመር፣ የሶማሊ ም/ርዕሰ መስተዳድር)

ከአማርኛ ቋንቋ አተረፍን እንጂ አልጎደለብንም….! 

ሙስጠፋ ዑመር፣ የሶማሊ ም/ርዕሰ መስተዳድር

 

የOMN ጋዜጠኞች እዚህ ጅጅጋ ዩኒቨርስቲ መጥተዋልና በትምህርት ፍኖተ ካርታው ላይ ሀሳብህን ይፈልጋሉ አሉኝ። ግዴለም ይቅርብኝ፣ አቋሜ ለአቋማቸው ስለማይጥም አያስተላልፉትም አልኳቸው። እውነቴን ነው።
ለምሳሌ በቋንቋ ጉዳይ የሶማሌ ልጆች አማርኛን በደንብ መማር አለባቸው። እኛ አማርኛን የቻልን እና በአማርኛ የተለያዩ እውቀትን የገበየን፣ ቅኔን፣ ተረትና ምሳሌውን፣ ቀልድና ተረቡን፣ አሽሙርና የቃላት ስንጠቃውን አሳምረን ያወቅን የሶማሌ ተወላጆች ከዚህ ቋንቋ አተረፍን እንጂ አልጎደለብንም። የሶማሌ ልጅ በኢትዮጵያ ሀገሩ ጉዳይ በደንብ ከዳር ወደ መሀል መጥቶ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር ጥቅሙን ለማስከበር፣ መብቱን ለመጠየቅ፣ የራሱን የሚገባውን ከሀገር ሀብት ድርሻውን በአፅዕኖት አስረግጦ ለመከራከር የአማርኛ ቋንቋ ያስፈልገዋል ።
የሚያስፈልገው ለእራሱ ጥቅም ሲል እንጂ ለማንም አይደለም። አማርኛን ስላወቀ ሶማሌነቱ አይጠፋበትም፣ እንዲህ የሚያስቡ ሰዎች ለፖለቲካ ትርፍ ትውልድ የነሱን ሀቲት ብቻ እንዲሰማ ፣ ዞርዞር ብሎ ታሪክ እንዳያይ የሚፈልጉ ናቸው።
ቋንቋ መግባቢያ ነው። ብንችል ሰማንያ ቋንቋን ብናውቅ ጥሩ ነበር። ሰው ቋንቋን ካወቀ ስራን፣ ቢዝነስን እና እድሉን ከማስፋት አልፎ ጠላት እንኳ ቢኖረው ቋንቋን በማወቁ ከሞት ይተርፋል። ታሪክ ማወቅ ጥሩ ነው። አብርሆት ይሰጣል። በኢማም አህመድ (አህመድ ግራኝ) ጊዜ ሰራዊቱ የንጉሱን ካንፕ ሾልኮ ለመሰለል ስለፈለገ አህመድ ሶማሌ ወታደሮችን አማርኛ እንዲማሩ አድርጎ ነበር። በጥቂት ወራት ለምደው የንጉሱን የካምፕ ጠባቂዎች “እየህ ቤቶች፣ እንደምን ዋላችሁ” እያሉ አልፈው ሰልለው ይወጡ ነበር።
ይህ ታሪክ ነው። ከዚህ ኢማም በታች የሚያስቡ ሰዎች አሁን መኖራቸው በጣም ይገርማል። በ1535 አካባቢ ሰው የቋንቋን ጥቅም አውቆ ሀገር ሲመራ፣ አሁን ሀገርን የመምራት እድሉን ያገኘ አካል እንዴት ስለቋንቋ እንዲህ የተዛባ አመለካከት ይኖረዋል ። በጣም ነው የሚገርመኝ።
Filed in: Amharic