>

በጁንታ ፖለቲካ፤ ማን ከሰረ፣ ማን አተረፈ፣ ለደረሱትስ ጉዳቶች ማነው ተጠያቂው? (ያሬድ ሀይለማርያም)

በጁንታ ፖለቲካ፤ ማን ከሰረ፣ ማን አተረፈ፣ ለደረሱትስ ጉዳቶች ማነው ተጠያቂው?

ያሬድ ሀይለማርያም

ያለፉት ጥቂት ሳምንታት ኢትዮጵያ እንደ አገር የተፈተነችበት ከባድ ወቅት ነበር። የጦርነት እወጃውን ተከትሎ የሰማናቸው የነውር ሥራዎች እና አሰቃቂ የወንጀል ተግባራት ሁሉንም ሰው ጥልቅ ሀዘን ውስጥ እና ሰቅጣጭ ስሜት ውስጥ ከቶ ነበር። በሰሜን እዝ የመከላከያ አባላት ላይ የተፈጸመው አስነዋሪ ድርጊት እና ጥቃት፣ በማይካድራ የተፈጸመው ጭፍጨፋ እና በትግራይ ክልል ውስጥ ጦርነቱን ተከትሎ የደረሰው ሰብአዊ ቀውስ ኢትዮጵያዊያንን አስቆጥቶም ክፉኛ አሳዝኖም ነበር። በዚህ ወቅት የሰከነ ውይይትም ሆነ በአገሪቱ ችግሮች ላይ ምክክር ለማድረግ ስለማይቻል ጥቃቶችን ከማውገዝ ባለፈ በሌሎች ጉዳዮች ላይ ሃሳብ ከመሰንዘር ተቆጥቤ ነበር። ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር የሚል ንፋስ አየሩን ስለሞላው ቁልፍ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት አቧራው መስከን ነበረበት። አሁን አንጻራዊ ሰላም በክልሉ ውስጥ ስላለ እና መንግስትም ክልሉን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሬያለው ስላለ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ በግልጽ መነጋገሩ ሳይበጅ አይቀርም።
ጁንታ ምንድን ነው?
ይህን ትርጉም ማስቀመጥ የፈለኩበት ምክንያት ብዙ ሰዎች ጁንታ ለሚለው ቃል የተሳሳተ ትርጉም እየሰጡ በቴሌቪዥን ጭምር ብቅ እያሉ ሲተነትኑ ስለሰማሁ ነው።
ጁንታ ማለት አንድ ወታደራዊ ቡድን ወይም የፖለቲካ ኃይል በሕዝብ ተመርጦ ሳይሆን በኃይል ወይም በነፍጥ ሥልጣን ይዞ ከሕዝብ ይሁንታ ሳያገኝ አገርን በጉልበት የሚያስተዳድር አካል ማለት ነው። የCambridge Dictionary ላይ በግልጽ እንደተቀመጠውJunta የሚለውን ቃል በአጭሩ እንዲህ ይተረጉመዋል a government, especially a military one that has taken power in a country by force and not by election.
ባጭሩ ስልጣን በጉልበት ይዞ፤ በጉልበት አገር ሲያስተዳድር የቆየ ወይም እያስተዳደረ ያለ አካል ማለት ነው።
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ጁንታ ማን ነው?
በቅርብ ጊዜ ታሪካችን ውስጥ ደርግ የወታደራዊ ጁንታ ተብሎ ይጠራ ነበር። ምክንያቱም ሥልጣኑን በወታደራዊ ኃይል ከያዘም በኋላ በወታደራዊ አስተዳደር ስለቆየ ወታደራዊ ጁንታ (Military Junta) እየተባለ በአለም አቀፍ መድረኮች ጭምር ይጠቀሳል። ደርግን በጉልበት የተካው የወያኔ አስተዳደርም ሥልጣን የያዘው በጉልበት ቢሆንም እራሱን ወደ ሲቪል አስተዳደር ለውጦ በይስሙላ ምርጫ ሕዝብን እያጭበረበረ፣ እያፈነ፣ እያሰረ እና እያሰደደ በጉልበት ለሃያ ሰባት አመታት በሥልጣን ቆይቷል። ህውሃት መራሹ የኢህአዴግ መንግስትም በሲቪል አስተዳደር ስም የተዋቀረ ነገር ግን የጁንታ ባህሪ የተላበሰ ነበር። አገርን በሕዝብ ምርጫና ፍላጎት ሳይሆን በጉልበት ነበር ሲያስተዳድር የነበረው። ስለዚህ አገሪቱ ከደርግ ወታደራዊ ጁንታ ወደ ኢህአዴግ የሲቪል ጁንታ አስተዳደር ነበር የተሸጋገረችው ማለት ይቻላ። በዚህ እሳቤ ህውሃት ዛሬ ሳይሆን ከዛሬ ሃያ አመት በፊት ነበር ጁንታ መባል የነበረባት። ባጭሩ አገሪቱ ከንጉሳዊ አስተዳደር ከወጣችበት ጊዜ ጀምሮ በጁንታዎች እጅ ነበረች ማለት ነው።
ዛሬ የገባንበት ቅርቃር፤
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ላለፉት ስድስት አመታት በነውጥ ውስጥ ነው የቆየው። የመጀመሪያዎቹ ሦስት አመታት ወጣቶች በየጎጣቸው ተቧድነው ህውሃት መራሹን ጁንታ ሲታገሉ የቆዩበት ወቅት ነው። በሺዎች ተገድለው፣ በአሥር ሺዎች ታስረው እና በርካቶች ቆስለው በከፈሉት መስዋዕትነት ብልጽግና ፓርቲን ያዋለደው የለውጥ ጀምበር ታየ። ለውጡ ብዙዎቻችንን አጓጉቶን ነበር። በተለይም አራቱ የኢህአዴግ ድርጅቶች ኑዛዜ ይሁን ንስሃ የመሰለ ይቅርታ ለሕዝብ አቅርበው ዳግም እድል ይሰጠን ሲሉ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ በይሁንታ ተቀብሎ ዳግም እድል ሰጠቱዋቸዋል። ያስገመገመው የለውጥ እንቅስቃሴም አቢዮታዊ ከመሆን ተገትቶ ለመደመር ፖለቲካ እጁን ሰጠ። በጎበዝ አለቆች እየተመራ የመጣውና እየቆየም ወደ ደቦ እርምጃ የተሸጋገረው አቢዮታዊ የሚመስል የለውጥ ንቅናቄ ጫፍ ሲደርስ ለውጡን ለራሱ ለኢህአዴግ አስረክቦ ተአምር ይጠብቅ ገባ። ለውጡ ሙሉ በሙሉ በኢህአዴግ ልሂቃን፤ ቆይቶም በብልጽግና ሆኖ በመጣው ኃይል እጅ ስር ወደቀ።
ለሃያ ሰባት አመታት አብረው ያጨቀዩትን እና ያቆሸሹትን የአገሪቱን ፖለቲካ ሊያጸዱ ቃል ገብተው ጉዞ የጀመሩት የኢህአዴግ ጁንታ አመራሮች አንድ እርምጃም ሳይጓዙ እርስ በርስ መናቆር፣ በአደባባይ መወነጃጀል እና መጓተት ጀመሩ። የእነሱ የውስጥ ንቁሪያ አገሪቱን የከፋ አደጋ ላይ ጣላት። ለአክራሪ ብሄረተኞችም መጠናከር ምቹ ሁኔታን ፈጠረ። ያለፉትን ሦስት አመታትም አገሪቱ ማባሪያ ወደሌለው የዘር ተኮር ግጭት እና አንዳንድ ቦታዎችም ዘር ተኮር ጭፍጨፋ ወደታየባቸው ክስተቶች ውስጥ ገባች። ይህ የአውራው ፓሪቲ የተሰጠውን እድል በአግባቡ መጠቀም አለመቻልም ሆነ የማዕከላዊ መንግስቱ ክፉኛ መዳከም ከዚህ የሚከተሉትን ችግሮች ወለደ፤
+ ክልሎች አብጠው እና ፈርጥመው በመውጣት እርስ በርሳቸው ብቻ ሳይሆን የአገሪቱንም ህልውና የሚገዳደር አይነት አቋም መያዝ ጀመሩ።
+ በክልሎች መካከል ያለው ፉክክር፣ የድንበር ይገባኛል ጥያቄዎች እና በግልጽ የሚታዩ የሥልጣን ሽኩቻዎች እየከረሩ ሲመጡ እያንዳንዱ ክልል፤ በተለይም ውዝግብ ያለባቸው ክልሎች የራሳቸውን ወታደራዊ ኃይል ልዩ ኃይል በሚል ሽፋን ማደራጀት ጀመሩ።
+ ማዕከላዊ መንግስቱ ይህን በክልሎች መካከል ያሉ ፍጥጫዎችም ሆነ የአንዳንድ ክልሎችን ከሕግ በላይ መሆን እና መረን መውጣት ችላ በማለት ትኩረቱን በሌሎች ጉዳዮች ላይ በማድረግ ለአንዳንድ ክልሎች ማፈንገጥ የራሱን የጎላ ድርሻ ተጫውቷል።
+ በአንዳንድ ክልሎች በሕገ መንግስቱ የተቀመጡ የዜጎች መብቶች በገፍ ሲጣሱ፣ ዜጎች በዘራቸው እየታደኑ ሲጨፈጨፉ የማዕከላዊ መንግስቱ በክልሎች ሥራ ጣልቃ አልገባም በሚል ሰበብ የዳር ተመልካች በመሆን ዙሪያውን ሲቀጣጠል የቆየውን እሳት መሃል ቁጭ ብሎ ሲሞቅ ቆየ።
+ የሕግ ተጠያቂነት እንዲሰፍን፣ አገራዊ የምክክር መድረኮች እንዲዘጋጁ፣ እርቅ እና መግባባትን የሚፈጥሩ መድረኮች እንዲፈጠሩ ይቀርቡ የነበሩ ውትወታዎችን መንግስት ጆሮ ዳባ ልበስ በማለት ትኩረት ሳይሰጣቸው ቆይቷል።
+ ከኤርትራ ጋር ሰላም በመፍጠር አለም ያደነቀው ዶ/ር አብይ በሚያስተዳድራት አገር ውስጥ ግን ከባለድርሻ አካላት ጋር እርቅ መፍጠር እና የተረጋጋ የፖለቲካ ምህዳር ማምጣት ተስኖት በመቆየቱ ችግሮቹ ፈርጀ ብዙ መልክ እየያዙ ሌሎች ችግሮች እድዲፈለፈሉ ዋነኛ ምክንያት ሆኗል።
+ ከላይ የተጠቀሱት ሁኔታዎች ለሃያ ሰባት አመት በጁንታነት የቆየችው ህውሃት መቀሌን ማዕከል አድርጋ የተለመደ የሸር ፖለቲካዋን አጠናክራ እንድትቀጥል ትልቅ ምቹ ሁኔታ ፈጠረላት። ለዚህም የፌደራል መንግስቱ ትልቅ እገዛ አድርጓል።
+ ጥጋብ የማትችለው ህውሃት ይህን ምቹ ሁኔታ ተጠቅማ እራሷን ካደራጀች በኋላ ማንም አይደፍረኝም በሚል ትቢት ካሳደገቻቸው ልጆቿ ጋር ከእንኪያ ሰላምታም አልፋ በጡጫ ግጠሙኝ አለች። ዝታም አላበቃችም በሰሜን እዝ አባላት ላይ የፈጸመችውን አስነዋሪ የወንጀል ተግባር ተከትሎ የለየለት ጦርነት ውስጥ ተገባ።
ይህን ትላንት የአንድ ፓርቲ አባላት የነበሩ እና ከለውጡ ማግስት ብልጽግና እና ህውሃት በሚል ማዶና ማዶ ተፋጠው የተሰለፉ የአንድ የፖለቲካ መንደር ሰዎች በሃሳብ እና በአካሄድ አለመግባባት አገሪቱን ወዳልተፈለገ ጦርነት ዶላት። መንግስት ጉዳዩን የሕግ ማስከበር እርምጃ ቢለውም ዞሮ ዞሮ ጦርነት ተካሂዷል። ዓላማው የሕግ ማስከበር መሆኑ ጦርነት መካሄዱን አላስቀረውም። በተፈጠረው የእርስ በርስ ጦርነት በርካቶች ሞተዋል፣ ብዙዎች ቆስለዋል፣ በአሥር ሺዎች ተሰደዋል፣ የአገር ሃብት እና ንብረት ወድሟል።
እንደ አገር በዚህ ጦርነት ያተረፍነው ነገር ያለ አይመስለኛም። ይህ ጦርነት የፖለቲካችንን ዝቅጠት፣ የፖለቲከኞቻችንን ግብዝነት ብቻ ሳይሆን ዛሬም ለሥልጡን የፖለቲካ አካሄድ እሩቅ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው። ዛሬም በውይይት እና በድርድር ሳይሆን በጉልበት የምንገዛና የምንገዛ መሆናችንን ይህ ጦርነት ለአለም አሳብቆብናል። ዛሬም ይህ ጦርነት ምን ያህል እርስ በርሳችን የምንጨካከን እና ፖለቲከኞቻችን በግብረ አራዊት እንደሚመሩም የሚያሳይ ነው። ለዚህ ጥሩ ማሳያው በማይካድራ የተፈጸመው ጭፍጨፋ ነው። የህውሃት አመራሮች ሃያ ሰባት አመት የተሸከማቸውን ሕዝብ በዚህ መልኩ ተጨፍጭፎ እንዲገደል ትዕዛዝ መስጠታቸው፣ ወጣቶቹም ትእዛዙን ተቀብለው በአንድ ሌሊት ከስድስት መቶ ሰዎች በላይ ጨፍጭፈው ማደራቸው ዛሬም ከአራዊት መንደር ፈቅ አለማለታችንን ነው የሚያሳየው።
አዎ ከዚህ ጦርነት ምንም አላተረፍንም። ምናልባትም በአሥር አመታት ወደ ኋላ ጎትቶን ይሆናል እንጂ። የዶ/ር አብይ መቀሌን መርገጥ ብቻውን ድል ሊሆን አይችልም። የህውሃት ሹማምንቶችን ገሚሱን ገድሎ ገሚሱን ለፍርድ ማቅረብ ብቻውን ድልና ትርፍ ሊሆን አይችልም። በዚህ ጦርነት በሕዝቦች መሃል አዲስ መቃቃር እና ቂም እንዲፈተር ሊያደርጉ የሚችሉ አዳዲስ ፈንጂዎች ተቀብረዋል። እነሱ ደሞ መቼ እንደሚፈነዱ አይታወቅም። ዛሬ ትግራይ ላይ የፈነዳው ፈንጂ ከብዙ አመታት በፊት ሕውሃት የቀበረችው ነበር።
ማጠቃለያ
አዎ ዛሬ ኢትዮጵያ እንደገና በአለም መድረክ ተዋርዳለች። አዎ ልጆቿ በዚህ በሰለጠነ ዘመን ችግሮቻቸውን በውይይት እና በድርድር መፍታት አቅቷቸው እርስ በርሳቸው እየተራረዱ እና አንዱ ሌላውን እያሳደደ የሚገድልባት አገር መሆኗን አለም ሰምቷል። አዎ ዛሬም ኢትዮጵያዊያን ጦርነት ሸሽተው የሚሰደቡባት አገር ሆናለች። አዎ ዛሬ ኢትዮጵያ በአለም አደባባት በጦርነት ሳቢያ በተፈጠረ ሰብአዊ ቀውስ፣ በፖለቲካ አለመረጋጋት፣ በእርስ በርስ ግጭት፣ በዘር ላይ ያነጣጠሩ ጭፍጨፋዎች እና በሰላም እጦት ስሟ መክፉ እየተጠራ ነው።
እነዚህም መጥፎ ጥላዎች ከላያችን ላይ ማንሳት ብዙ ሥራ ይጠይቃል። በቅድሚያ ግን አሁን ላለንበት ችግር ቢያንስ ዋነኛ በሆኑት ችግሮች ላይ ልንስማማ እና ልንግባባ ይገባል። ጠአት መጠነቋቆሉን ትተን እንደ አገር እራሳችንን የዚህ ነውር ክስተት ተጠያቂዎች ማድረግ ይኖርብናል። እንደ እኔ ለዚህ ሁሉ ችግር ከላይ ከጠቀስኳቸው ዋና ዋና ነጥቦች በተጨማሪ ኃላፊነት መውሰድ ያለባቸውን አካላት በግልጽነት ቁጭ በልው ሊነጋገሩ ይገባል። እንደ እኔ ዛሬ ላለንበት ጠቅላላ ችግር በግንባር ቀደምነት ተጠያቂው የትላንቱ ኢህአዴግ፤ የዛሬው ብልጽግና ፓሪቲ ነው። ድርጅቱ በተሰጠው እድል ባለፉት ሁለት አመታት በአግባቡ አልተጠቀመበትም። ነገሮች ከተበላሹና አገር አደጋ ላይ ከወደቀች በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ ቀርበው ኃጢያቱን ሁሉ ጁንታ ላሉት የህውሃት ኃይል ለመቆለል ያደረጉት ሙከራ ለጊዜው ስሜታዊ አድማጭና ደጋፊ ያስገኝላቸው ይሆናል እንጂ ለአገር ምንም ጠብ የሚል ነገር ወይም ፋይዳ የለው።
አሁንም በክልሎች መካከል የሚታየው መገፋፋት እና ፉክክር ወደ ሌላ ዙር ጦርነት ላለማምራቱ ምንም ዋስትና የለንም። ቀጣዩ ጦርነት በቤኒሻንጉል ጉምዝ ምድር ወይም በሌላ በአንዱ ክልል ውስጥ ሊሆን የሚችልበት እድል ሰፊ ነው። እንዲህ አይነቶቹ ውጥረቶች ሌላ ዙር አለመረጋጋት እና ጦርነትን ሊያስከትሉ መቻላቸው ብቻ ሳይሆን ሌላ ጁንታ የማዋለድ አቅማቸውም ከፍ ያለ ነው። በመሆኑም መንግስት አሁን ከህውሃት መክሰም ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ወሳኝ የሆኑ የፖለቲካ እርምጃዎችን መውሰድ ይጠበቅበታል። ከእነዚህም መካከል ጥቂቱን ለመጥቀስ ያህል፤
1ኛ/ በአፋጣኝ የክልሎችን ልዩ ኃይል አፍርሶ ሰልጣኞቹን ወደ ፖሊስ እና መከላከያ ሠራዊት በማስገባት፣
2ኛ/ በክልሎች ያለውን የጸጥታ ኃይሎች አደረጃጀት የዘር ስብጥር ማስተካከል፣
3ኛ/ በክልሎች ውስጥ የጸጥታ ማስጠበቁን ሥራ የፌደራል መንግስቱ በበላይነት መቆጣጠር እና በተለይም ችግር ባለባቸው ክልሎች ውስጥ ሙሉ በሙሉ ጣልቃ በመግባት መቆጣተር፣
4ኛ/ በክልሎች መካከል አወዛጋቢ የሆኑት የድንበር ይገባኛል ጥያቄ የተነሳባቸውን አካባቢዎች ለጊዜው ሙሉ በሙሉ በፌዴራል መንግስቱ ቁጥጥር ስር እንዲውሉ ማድረግ እና አለመግባባቶቹ የሕግ እና የፖለቲካ ውሳኔ እስኪያገኙ ድረስ ቢያንስ ለአንድ አመት ቢበዛ ለሁለት አመት የባለቤትነት ውዝግብ የተነሳባቸውን ቦታዎች የሲቪል አስተዳደሩን፣ የጸጥታ ዘርፉን እና ሌሎች መዋቅሮቹን በፌደራል መንግስቱ ሥር ሆነው እንዲቆዩ ማድረግ፣
5ኛ/ አሁንም ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚደረጉ አገራዊ የውይይትና የምክክር መድረኮች ከምርጫ ባለፈ በአገሪቱ ቀጣይ እጣ ፈንታዎች ላይ የሚደረጉ ምክክሮች በስፋት እንዲሰራባቸው፤
6ኛ/ መንግስት የሕግ ማስከበር በሚል የገባበት ጦርነት መጠናቀቁን ይፋ አድርጓል። በጦርነቱም በሕግ ከሚፈለጉት የህውሃት አመራሮች መካከል አብዛኛዎቹ በቁጥጥር ስር መዋላቸው በመገናኛ ብዙሃን ሲገለጽ ሰምተናል። ይሁን እና እነማን ታሰሩ? በምን ሁኔታ ታሰሩ? ተመተውና ቆስለው በቁጥጥር ስር የዋሉ አሉ ስለተባለ እናማን ናቸው? ዛሬ በምን ሁኔታ እና የት ይገኛሉ? የፍርድ ሂደትስ ተጀምሯል ወይ? ካልተጀመረስ ለምን? እነማንስ ገና እየተፈለጉ ነው? የሚሉት ጥያቄዎች በአግባቡ ሊመለሱ እና ለሕዝብም ግልጽ መረጃ መስጠት የመንግስት ኃላፊነት ነው። መንግስት ከተወሰኑ ግለሰቦች በቀር በዜና እወጃዎቹ ላይ የጁንታው አባላት በቁጥጥር ስር ዋሉ የሚል ድፍን መረጃ ነው የሚሰጠው። ይህ ግልጽነት የጎደለው የመንግስት መግለጫ ሌላ ክፍተት ሊፈጥር እና የመብት ጥሰትንም ሊያስከትል ይችላል።
ቸር እንሰንብት!!
Filed in: Amharic