>

ሃይማኖታዊው እና ባህላዊው ‹የግጭት አፈታት› እና ‹የዕርቀ-ሰላም› መልካም የሆኑ እሴቶቻችን ሊጠናከሩ ይገባቸዋል!! (በዲ/ን ተረፈ ወርቁ)

ሃይማኖታዊው እና ባህላዊው ‹የግጭት አፈታት› እና ‹የዕርቀ-ሰላም› መልካም የሆኑ እሴቶቻችን ሊጠናከሩ ይገባቸዋል!!

በዲ/ን ተረፈ ወርቁ


ከጥቂት ዓመታት በፊት የዓለም የዕርቅና ሰላም የተባለ አገር በቀል ግብረ-ሠናይ ድርጅት፤ ‹‹የሕግ ታራሚነት እና ዕርቅ ለሰላማዊ ሕይወት በኢትዮጵያ፣ ክፍተቶቹ እና መፍትሔዎቹ›› በሚል አጀንዳ አዘጋጅቶት በነበረው ዓመታዊ ስብሰባና ውይይት መድረክ ላይ ለመሳተፍ ዕድሉን አግኝቼ ነበር፡፡ በዚህ ስብሰባ ላይም በግጭት አፈታትና በዕርቀ-ሰላም (Conflict Resolution and Mediation) ጉዳይ ላይ ሰፊ ጥናትና ምርምር እያደረጉ ያሉ በአገር ቤትና በውጭ አገር የሚኖሩ ምሁራን፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የፍትሕና አካላትና ፖሊስ፣ ወጣቶች ተሳታፊዎች ነበሩ፡፡

በምሁራኑ ባቀረቧቸው የጥናት ወረቀቶችና የውይይት መነሻ አሳቦች ላይም ብዙዎችን በንቃት ያሣተፈ ውይይትና ምክክርም ተደርጎ ነበር፡፡ ታዲያ በዚህ በዚህ የውይይት መድረክ ላይ አቶ አሰፋ ከሲቶ፣ ለሦስት ዓመት ያህል የኢፌዲሪ ፍትሕ ሚ/ር ኾነው በሠሩበት ወቅት የሕግ ታራሚዎች ሕጉ ከሚጥልባቸው ቅጣት ባሻገር፣ ለዘመናት በኢትዮጵያ ሕዝቦች መካከል ጸንቶ የቆየው ባህላዊና ሃይማኖታዊ የሆነው የግጭት አፈታትና የዕርቀ-ሰላም እሴቶቻችን ያላቸውን ፋይዳ በማስመልከት- በአንድ ወቅት በቤሻንጉል ጉምዝ የሆነ ያስገረማቸውን አንድ ገጠመኛቸውን ለስብሰባው ተሳታፊዎች እንዲህ አውግተውን ነበር፡፡

ታሪኩ እንዲህ ነው፡፡ በቤሻንጉል ጉምዝ የሚኖሩ ሁለት ጎረቤታሞች በጊዜያዊ ግጭት በተፈጠረ ጠብ አንደኛው ጎረቤት አንድ ማታ ላይ ጨለማን ተገን አድርጎ ጠበኛው የሆነውን ጎረቤቱን አገረ ሰላም ነው ብሎ ወደ ቤቱ ሲገባ አድብቶ ይገድለዋል፡፡ ይህ ወንጀለኛም በፖሊስ ተይዞ ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት እንዲያመራ ይሆናል፡፡ ገዳይም ጥፋቱን በማመኑ ለፈጸመው ወንጀል የ15 ዓመት ጽኑ ቅጣት ተወስኖበት ወደ ወኅኒ ያመራል፡፡ ይህ የሕግ ታራሚም የተሰወነበትን ቅጣቱን ፈጽሞ በሰላም ወደ ቤቱ ይገባል፡፡

ከማረሚያ ቤት ተሰናብቶ ወደ ቤቱ የገባውን ደመኛውን ያየ የሟች ወንድምም ያን ሰው ከወኅኒ በወጣ ማግሥት አንድ ማታ ላይ ወደ ቤቱ ሲገባ አድብቶ በጦር ደረቱን በመውጋት የወንድሙን ደም ይበቀላል፡፡ ገዳይም በፖሊስ ተይዞ ወደ ፍርድ ቤት ይቀርባል፡፡ ዳኛውም ለዚህ ወንጀለኛ አንድ ጥያቄ ያቀርቡለታል፤ እንዲህ ሲሉ፡- ‹‹ለወንድምህ ገዳይ ለሆነው ወንጀለኛ ሰው በሕግ አግባብ ተገቢው ቅጣት ተሰጥቶት፣ ቅጣቱን ፈጽሞ ነው ከማረሚያ ቤቱ የተሰናበተው፡፡ ታዲያ በሕግ የተጣለበትን ተገቢውን ቅጣቱን ፈጽሞ የወጣን ሰው ለምን በጦር ወግቶ እንደገደለው ይጠይቁታል፡፡››

ገዳይም ለዳኛው እንዲህ ሲል መልስ ይሰጣል፡፡ ‹‹እውነት ነው ሕጉ ለወንድሜ ገዳይ ተገቢውን ቅጣት ሰጥቶታል፡፡ ግና እንደ ባህላችን የእኔና የእርሱ ቤተሰብ ዕርቅ አላወረደም፤ አልታረቀንም፡፡ እንደ ኖረው ባሕላችን ደም አፍሰን የእኔና የእርሱ ቤተሰብ ዕርቀ-ሰላም ማውረድ ነበረበት፡፡ ስለዚህ የወንድሜን ገዳይ የገደልኩት ስላልታረቅንና አሁንም ጠበኞች ስለሆንን እንጂ የፍርድ ቤቱን ሕግ ላለማክበር ወይም ሕጉ ተገቢውን ቅጣት አልሰጠውም በሚል አይደለም፡፡›› ሲል ፈርጠም ብሎ ምላሽ ይሰጣል፡፡

የዚህን የአቶ አሰፋ ከሲቶ አስገራሚና አሳዛኛ ገጠመኝ ተከትለን ጥቂት የውይይት ሐሳቦችን ለማንሳት ወደድኹ፡፡ በአገራችን የዘመናት ታሪክ ሂደት ውስጥ በሕዝቦች መካከል የተፈጠሩ ግጭቶችና አለመግባባቶች አንዳንዴም እጅግ ደም አፋሳሽ ወደኾኑ እልቂቶች ለማምራት መንገድ የጀመሩ አለመግባባቶችንና ግጭቶችን ለመፍታት አሉን የምንላቸው ሃይማኖታዊና ባህላዊ የግጭት አፈታትና ዕርቀ-ሰላም የማውረድ መልካም የሆኑ እሴቶቻችን በእኛ ዘመን በሚገባ ተጠብቀው አሉ ወይ?

እነዚህ በዋጋ ሊተመኑ የማይችሉ መልካም እሴቶቻችንስ ፋይዳቸውስ በቅጡ ጠንቶ፣ ታውቆና ታምኖበት፣ በሚገባ ተጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፉ በማድረግ ረገድስ ምን ያህል እየሠራን ነው?! የሰላም፣ የፍቅርና የዕርቅ መዝገብ ናቸው የሚባሉት የሃይማኖት ተቋማት መሪዎችና የሀገር ሽማግሌዎችስ በዚህ ዘመን የሰላም መልእክተኛ የመሆን መንፈሳዊ ግዴታችውን እንዴት እየተወጡ ነው… የሚሉ ወቅታዊ ጥያቄዎችን ማንሳት ያስፈልገናል፡፡

በታሪካችን፣ በሃይማኖቶቻችንና በባህላችን ውስጥ ለዘመናት ተከብረው የዘለቁ፣ ዛሬ አገራችንም ሆነ ዓለም ለሚተዳደርበትና ለሚመራበት ዘመናዊው ሕግና የፍትሕ ሥርዓት መሠረት የሆኑ የአብሮነት፣ የሰላም፣ የዕርቅና የፍቅር እሴቶቻችንንስ ለገባንበት ቀውስ ምን ያህል መፍትሔ እየኾኑን ነው?! በማለት አብረን ጥቂት እንቆዝም እስቲ፡፡

እንደ ሕዝብ በሰላምና በወንድማማችነት መንፈስ አስተሳስረውን የቆዩት እጅጉን ልንኮራባቸውና ልንጠብቃቸው የሚገቡን የሰላምና የዕርቅ መሠረት የሆኑ ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶቻችን እጅጉን እየተናዱብን ስለመሆኑ በርካታ ማሳያዎችን መጠቅስ የሚቻል ይመስለኛል፡፡

በመግቢያዬ ላይ ያቀርብኩት የቀድሞው የፍትሕ ሚ/ሩ የአቶ አሰፋ ከሲቶ አሳዛኝ ገጠመኝም ከሰላምና ከዕርቅ፣ ከአብሮነት፣ ከማኅበራዊ ኑሮአችንና መስተጋብራችን ጋር ሃይማኖታዊና ባህላዊ የሆኑ ዘመናትን ያስቆጠሩ መልካም እሴቶቻችን አሁን እየተመራንበት ካለው ከዘመናዊው ሕግ ጋር ቢያንስ በመርሕ ደረጃ ተናበውና ተስማምተው መሥራት ካልተቻለ፣ ለሃይማኖቱና ለባህሉ ከፍተኛ ግምትና ቦታ በሚሰጥ እንደ አገራችን ኢትዮጵያ ባሉ ሕዝቦች መካከል ዘመናዊው ሕግ ብቻውን ፍትሕን፣ ዕርቅንና ሰላምን ያሰፍናል ማለት እምብዛም ሊያራምድን እንደማይችል ትልቅ ማሳያ ነው፡፡

ይህን ጽሑፍ እያዘጋጀሁ እያለሁ Minority Rights Group International የተባለ ዓለም አቀፍ ተቋም ከጥቂት ዓመት በፊት ያወጣወውን ሪፖርት ስመለከት ነበር፡፡ የዚህ ተቋም ጥናት ሪፖርት እንደሚሳየው በዓለማችን  በግጭትና በቀውስ ውስጥ ካሉ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት አገራት ከሰሃራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገራት እንደሆኑ በማተት፤ ሪፖርቱ በእነዚህ አገራት የሚነሡ ግጭቶችንና አለመግባባቶችን በሰላም ለመፍታት በአገር፣ በአኅጉርም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተሞከሩ ያሉ የግጭት አፈታት ዘዴዎችና ዕርቀ-ሰላምን ለማውረድ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች በዋንኛነት ያጋጠማቸውን ተግዳሮት እንዲህ ገልጾታል፡፡

ግጭትና ለአመግባባት በሰፈነባቸውና አንዳንዴም እነዚህ አለመግባባቶችና ግጭቶች ተባብሰው ወደ እርስ በርስ ጦርነት በሚያመሩባቸው ማኅበረሰቦች መካከል የቆየው ባህላዊውና ሃይማኖታዊው የግጭት አፈታት ዘዴዎች ተገቢው ትኩረት እንደተነፈጋቸው ያስረግጣል፡፡ በተጨማሪም ይህን ሊፈጽሙና ሊያስፈጽሙ የሚችሉ በማኅበረሰቡ መካከል የሚፈሩና የሚከበሩ የማኅበረሰቡ መሪዎችና ሽማግሌዎች በሚገባ ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ አለመቻሉ ወይም ጭራሹኑ አለመፈለግ በተለያዩ ደረጃዎች መንግሥት፣ የፀጥታ ኃይሎች፣ የፍትሕ አካላትና ዓለም አቀፍ ተቋማት የግጭቶቹን ምንጭ ከሥሩ ለማድረቅና ለመፍታት እያደረጉት ያለው ሙከራ እምብዛም ስኬታማ እንዳልሆነ ነው ሪፖርቱ ይፋ ያደረገው፡፡

ይኸው ሪፖርት ለማሳያነት ከተጠቀመባቸው አገራት መካከል ኡጋንዳንና ሀገራችንን ኢትዮጵያን ይጠቅሳል፡፡ በሀገራችንም ሆነ በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የሚነሱ ግጭቶችን ለመፍታት መንግሥትም ሆነ ዓለም አቀፍ ተቋማት የእነዚህ ሕዝቦች ሃይማኖት፣ ታሪክ፣ ባህልና ትውፊት ባላማከለ መልኩ የሚወስዷቸው የመፍትሔ ዕርምጃዎች አቅመ ደካማና ዘላቂነት የሌላቸው ጊዜያዊ ብቻ እንደሆኑ ነው ሪፖርቱ ያሳየው፡፡

የማይኖርቲ ራይት ኢንተርናሽናል ሪፖርት በማጠቃለያውም፡- ‹‹Activists from both in Ethiopia and Uganda emphasized the need to rely on traditional community methods to help curb the violence and the loss of lives. … However the traditional methods have neglected with the development of governmental structures.›› በማለት በአፍሪካ ሀገራት በተደጋጋሚ የሚከሰቱትን አለመግባባቶችንና ግጭቶችን መፍትሔ ለመስጠት የቆየው ባህላዊው የግጭት አፈታት ዘዴ ያለውንና ሊጫወት የሚችለውን ጉልህ ሚና በማስመር፤ ይሁን እንጂ እነዚህ ባህላዊ የሆኑ የግጭት አፈታት ዘዴዎችም ከዘመናዊው አኗኗር ዘዴና ከመንግሥታዊ የፍትሕ ተቋማት መስፋፋት ጋር ተያይዞ የመፍትሔ አካላት የመሆን ፋይዳቸው እየተዘነጋ እንዳለ ነው የደመደመው፡፡

እንግዲህ በመግቢያዬ የጠቀስኩትን የአቶ አሰፋ ከሲቶን አሳዛኝ ገጠመኝና ‘‘የማኖሪቲ ራይት ኢንተርናሽናል’’ ሪፖርት መሠረት አድርገን ለሺ ዘመናት በአኩሪ ታሪክ፣ በገናና ሥልጣኔ ቀድሞ የታወቀ፣ ከዓለም በፊት በሃይማኖትና በሚያስቀና ባህል ጥላ ሥር የኖረው ሕዝባችን ግጭቶችንና አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገዶች በመፍታት ረገድ ያጋጠመውን ተግዳሮት ከቅርብ ጊዜ ታሪካችንንና አሁን ያለንበትን ነባራዊ ኹኔታ ባናበበ መልኩ ጥቂት ለመወያያ የሚሆኑ፣ የሚጠቅሙ አሳቦችን ለማንሳት ልሞክር፡፡

እንደሚታወቀው ከምንኮራበት ገናና የሥልጣኔ ታሪካችን ባልተናነሰ ሌላኛውን የታሪክ ምዕራፋችንን ገጽ ስንገልጸው በበርካታ ግጭቶች፣ አለመግባባቶችና የእርስ በርስ ጦርነትና እልቂቶች የደመቀ የደም፣ የእልቂት ታሪክ ነው ያለን፡፡ አለን የምንላቸውን ልዩነቶቻችንን በመግባባት በሰላም፣ በጨዋ ደንብ ቁጭ ብሎ በሰላማዊ መንገድ ተነጋግሮ፣ ተወያይቶ ለመፍታት ያለን ቁርጠኝነትና ከልብ የሆነ ትጋትና ቅንነት ትልቅ ጥያቄ ውስጥ የወደቀ ነው፤ ብል እምብዛም ያጋነንኩ አይመስለኝም፡፡

የቅርብ ጊዜ የትናንትና ታሪካችን የሚነግረን እውነታ ቢኖርም ከገጠር እስከ ከተማ፣ ከአፈ ነቢብ እስከ ምሁር፣ ከአለቃ እስከ ምንዝር ድረስ በረጋና በሰከነ መንፈስ መነጋገር፣ መወያየት የሚል የጨዋ ወግ ከመካከላችን ተሰዶብን፣ እርስ በርስ ለመስማማት ባለመቻላችንና ከእኔ በቀር በሚል ትእቢትና ጋግርት በከንቱ የፈሰሰው የወንድማማቾች ደም፣ በዚህ ጦስም መጠጊያ፣ መደበቂያ ሽተው በባዕድ ምድር ተሰደው ያሉ የብሶተኛ ወገኖቻችን ቁጥር፣ የወደመው የአገር ሀብትና ንብረት የትየለሌ እንደሆነ ነው ታሪካችን የሚነግረን፡፡

ለዘመናት የቆየው የአብሮነት፣ የአንድነት ታሪካችን በቂም በቀል፣ በቁርሾ ታሪክ ትርክት ዳግም ታድሶና ነፍስ ዘርቶ ዛሬም ድረስ እርስ በርሳቸው ለቂም የሚፈላለጉ የአገራችን ሕዝቦች በእኛው መካከል አሉ፡፡ ላለፉት ዓመታት የታዘብነው መራር የሆነ እውነታም ይኸው ነው፡፡ እንደ ሕዝብ በፍቅር፣ በአንድነትና በወንድማማችነት መንፈስ በሰላምና በአብሮነት መኖር እንችል ዘንድ በአገራችን ለዘመናት የኖሩት የግጭት አፈታትና ዕርቀ-ሰላም የማውረድ ሃይማኖታዊና ባህላዊ መልካም የሆኑ እሴቶቻችን ተጠናክረው ይቀጥሉ ዘንድ ትኩረት ሊቸራቸው ይገባል፡፡

እነዚህ መልካም እሴቶቻችን የአንድነታችን ውበት፣ ጌጥና ሽልማት ሆነው ይቀጥሉ ዘንድ፣ መንግሥት፣ ምሁራን፣ የታሪክ ተመራማራዎች፣ የግጭት አፈታት ዘዴ አጥኚዎች፣ በሰላም ጉዳይ ላይ የሚሰሩ ምሁራንና የሰላም አምባሳደሮች፣ የሃይማኖት አባቶችና አገር ሽማግሌዎች የበኩላቸውን ጉልህ ሚና ሊጫወቱ ይገባል፡፡

ሰላም!

Filed in: Amharic