>

ከ "ዳንዲ – የነጋሶ መንገድ" ለትውስታ የተጨለፉ ቁምነገራዊ ጨዋታዎች...!!! (በዳንኤል ተፈራ ጀ)

ከ “ዳንዲ – የነጋሶ መንገድ” ለትውስታ የተጨለፉ ቁምነገራዊ ጨዋታዎች…!!!

በዳንኤል ተፈራ ጀ.

ጨዋታ አንድ፡- ስለ ወ/ሮ ሬጊና እና የችግር ዱብ’ዳ!
1. “[በሰኔ 10፤ 1997 ዓ.ም.] በጣም ደነገጥን፡፡ ይሄ ሊሆን አይችልም!! የምገባበት የለም፤ ቤት የለንም፤ ሌላ ቤት ለመስራት ቀርቶ ለኪራይ እንኳ ገንዘብ አልነበረንም፤ ለመኖርም እንኳ ከጥቂት ወራት በስተቀር ገንዘብ የለንም፡፡ ባቤቴ ሬጊና ስራ አልነበራትም፡፡ ከጥቅምት 1998 ዓ.ም. በኋላ ከፓርላማ ከማገኘው 2700 ብር ደሞዝ በስተቀር ምንም ዓይነት ገቢ አልነበረንም፡፡ ከ1997 – 98 በጣም ተቸግረን ስለነበር የረጊና ታናሽ ወንድም ትንሽ ገንዘብ አበደረን፡፡” (- ገጽ 269)
2. “በደስታም ሆነ በሃዘን ከጎኔ ያለችው ውዷ ባለቤቴ ረጊና፤ ካልተዘመረላቸው ብዙ ጀግና ሴቶች የምትመደብ እጅግ ጀግና ናት፡፡” (- ገጽ 330)
ጨዋታ ሁለት፡- ስለ ወ/ሮ ብርቱካን ሚደቅሳ እና ፓርላማ!
1. “በተለይ ‹‹ቅንጅት መንፈስ ነው!›› የሚለውን የብርቱካን ሚደቅሳን ንግግር አልረሳውም፡፡ በአዳራሹ ያለው ህዝብ ያደረገልኝን አቀባበልም የምረሳው አይደለም፡፡ (- ገጽ 285)
2. “ከቅንጅት አካሄድ ቅር ያለኝ የቅንጅት አመራር በራሱ እንደ አመራር የሚያምንበትን አቋም መውሰድ ሲገባው ህዝብን እንወያይ ማለቱ ነው፡፡ የዚያኔም ሆነ ከዚያ በኋላ አካሄዱ ትክክል ነው ወይ? የሚል ጥያቄ አጭሮብኝ ነበር፡፡”
3. “ምንም እንኳየኔ ፓርላማ ውስጥ መኖር ምንም ለውጥ ባያመጣም፤ እንደ አንድ የግል የፓርላማ አባል ያለችውን ቀዳዳ በመጠቀም፤ በተገኘው አጋጣሚ ለህዝብ ሀሣቤን እየገለፅኩ ብቀጥልበት ይሻላል ብዬ በማሰብ ነው ፓርላማ የገባሁት፡፡” (- ገጽ 289)
ጨዋታ ሶስት፡- ስለ ወ/ሮ አዎሪ አረዳ እና የነፍጠኛ ባህርያት!
1. “ምዕራፍ 35 – የነጋሶ ጀግና እንስቶች” በሚለው ምዕራፍ ውስጥ ስለሴት አያታቸው እንዲህ ያነሳሉ፡-
“በእኔ ህይወት ውስጥ ብዙ ሚና የተጫወቱ ሴቶች አሉ፡፡ ለምሣሌ፡- አያቴ አዎሪ አረዳ በልጅነቴ በፖለቲካ አመለካከቴ ወይም ዕውቀቴ ላይ ብዙ አስተዋፅዖ አድርገዋል፡፡ በተለይ ስለነፍጠኛ ስርዓት እንድገነዘብ ያደረጉኝ እሳቸው ናቸው፡፡” (- ገጽ 326)
2. “የነፍጠኛ አሰራር” ስለሚባለው ‹‹መፈክር›› ሲያብራሩ ደግሞ እንዲህ ይላሉ፡-
“‹‹ነፍጠኛ›› የሚባሉት በምኒልክ ወረራ ጊዜ መሣሪያ ይዘው፤ በየአካባቢው የሰፈሩ ገዢዎችና ሰራዊቶቻቸው ሲሆኑ የገዥው መደብ ቁንጮ አባላት የሆኑት በተለይ ከሰሜን ሸዋ የተውጣጡ አማሮች ናቸው፡፡ ነገር ግን ከሸዋ፤ ከወሎ፤ ከትግራይ፤ ከጎንደርና ከጎጃም የተቀላቀሏቸውም አሉ፡፡ እነዚህ ነፍጠኞች በሰፈሩበት አካባቢ ፍትህና የሰብአዊ መብት አጠባበቅ ብሎ ነገር የለም፡፡ መገለጫቸው ማሰር፤ መደብደብና መዝረፍ ነበር፡፡ የበላይ ሹማምንቶች ሲመጡ ጌታዋን እንዳየች ውሻ ይሽቆጠቆጣሉ፡፡ አንዳንድ የኦህዴድ አባላትም ይሄን የነፍጠኛ ባህርይ ያሳዩ ነበር፡፡” (- ገጽ 211)
ጨዋታ አራት፡- ስለ ዘመቻ ፀሐይ-ግባት እና የአልጄርሱ ስምምነት!
1. “አብዛኛው የስራ አስፈጻሚ [የኢህአዴግ] የተስማማበት ‹‹ሻዕቢያን እንደምስሰው!›› በሚለው ነበር፡፡ እንዳልነውም ብናደርግ አቅም ገንብተናል፡፡ ግን ሉዓላዊነትን መዳፈር ይሆናል፤ ከድንበራችን ካስወጣን ይበቃል የሚለው ሃሣብ ስላሸነፈ፤ ስራ አስፈጻሚው ስብሰባ ላይ ‹‹ድንበራችን ከጦርነቱ በፊት ወደነበረበት ሁኔታ እስካልተመለሰ ድረስ ስምምነት አንፈርምም›› በሚል ‹ቴክኒካል አሬንጅመንቱ› ላይ 17 ለ 2 አሸንፈን ውሣኔ አሣለፍን፡፡ መለስና ካሱ ብቻ ተቃወሙ፡፡ ከዛ በኋላ የተኩስ አቁሙን በይፋ እንዲቀር አድርገን ወደ ጦርነት ገባን፡፡ ‹‹ዘመቻ ፀሃይግባት›› በሚል ስያሜ ሻዕቢያን ለማጥቃት የተወሰነው አዲግራት በሻዕቢያ አውሮፕላን ከተደበደበች በኋላ ነው፡፡” (- ገጽ 225)
2. “ከኢትዮጵያ ድንበር አልፈን የተወሰነ የኤርትራ መሬት ከተቆጣጠርን በኋላ መለስ ‹‹በቃ የእኛ ተልዕኮ ሻዕቢያን ከመሬታችን ማስወጣት እንጂ ሻዕቢያን መደምሰስ አይደለም፡፡›› አለ፡፡ […] ሆኖም ከአደራዳሪዎቹ [አንቶኒካ ሊክ፣ ራይስ እና ፖል ካጋሜ] በተለይም ከአሜሪካ ግፊት ነበር፡፡ ግፊት ብቻም ሣይሆን ማስፈራራትም ነበረበት፡፡ መገስገሳችን ቀርቶ ወደ አልጀርሱ ስምምነት የመሄድ አቋም ላይ ተደረሰ፡፡” (- ገጽ 225 – 26)
3. “የአልጀርሱን ስምምነት ለመፈረም በተስማማንበት ወቅት አዲሱ ለገሰ መናደዱ ትዝ ይለኛል፡፡ ‹‹ከዚህ በኋላ በሻዕቢያና በህወሃት መካከል ችግር ተፈጥሮ ወደ ጦርነት የምንገባ ከሆነ የኛን ህዝብ ሂዱና ተዋጉ ብዬ አልቀሰቅስም!›› አለ፡፡” (- ገጽ 227)
– (ስለቀድሞው ፕሬዚደንት ክቡር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ – .፤ ሰኔ 2003 ዓ.ም¨< መጽሐፍ )
ከመጽሐፉ ስለተጠቀሱ አባባሎችና ሃሳቦች ባለታሪኩ ከልብ ከመነጨ ምስጋና ጋር፤ አበቃሁ፡፡ መልካም ጊዜ፡
Filed in: Amharic