>
5:26 pm - Wednesday September 15, 2027

ዳግማዊ ምኒልክ በአማን ወልዱ ለሰሎሞን ወልደ ዳዊት...!! (አሰፋ ሀይሉ)

 

ዳግማዊ ምኒልክ

በአማን ወልዱ ለሰሎሞን ወልደ ዳዊት…!!!

አሰፋ ሀይሉ

   (— በአፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ፣ 1901 ዓ.ም.፣ በሮማ ከታተመው መጽሐፍ)
ወይ ግሩም! ግሩም ነው ግሩም፣ የግሩም ግሩም! ምኒልክ ትበል እንዲህ እናት! ስምን መላክ ነው የሚአወጣው፡፡ ምኒልክ ማለት የሰሎሞን ልዥ የዳዊት የልዥ ልዥ በመሆኑ አያስደንቅም፡፡ ምኒልክ ማለት ምን ይልክ ይሆን እግዚአብሔር ማለት ነው፡፡
እግዚአብሔር እሄው ምኒልክን ላከ፡፡ ላከ ማለት አነገሠ ማለት አይደለም፡፡ መንገሥማ እነቴዎድሮስ፣ እነዮሐንስ፣ እነተክለ ጊዮርጊስ፣ እስንቱ ሌላው ሁሉስ ነግሦ አልነበረምን? ምኒልክ ግን እንደሌሎች አልነገሠም፡፡ ዳግማዊ ምኒልክንስ እግዚአብሔር መርጦ፡- ሂድ ኢትዮጵያ ተጎድታለች፣ የኢትዮጵያ ሰው አልቅሷል፣ በሕዝቡ ድንቁርና በዝቶበታልና ሂድ ኢትዮጵያን አይዞሽ በላት፣ የደሀውን እንባ አድርቅለት፣ ድንቁርና ጨለማ እውቀት ግን ብርሃን ነውና በኢትዮጵያ ጨለማው እንዲሻር፣ ብርሃን እንዲወጣ፣ ለህዝቡ የረቀቀውን በልብ የጎላው በዓይን እንዲከሰትለት አስተምረው፣ አርመው፣ ጠብቀው፣ ላንተ አይደለም፣ ለኢትዮጵያ ነው ያነገሥሁህ ብሎ ላከው፡፡
ዳግማዊ ምኒልክም በተላከው እሄው ወዲአው ከመንገሡ ደሀውን ከባርነቱ አርነት አወጣ፡፡ እስከ ትላንት ድረስ በነቴዎድሮስና በናፄ ዮሐንስ ጊዜ የኢትዮጵያ ድሃ ለወታደር መጨዋቻ ባርያ ነበረ፡፡ ባርያ በገዛ ራሱ ማዘዝ እንደማይሆንለት፣ የኢትዮጵያ ደሀም በገዛ ቤቱ ማዘዝ አይሆንለትም ነበረ፡፡ የሚአዝበት ቆርፋፋ ጋሻ ያነገበና አንድ ባለጌ ጦር የያዘ አንድ የመሸበት ደበናንሳ የጀራረገውና ተሰገባው በስፍራ ተጣልቶ ፀሐይ የሚሞቀው ጎራዴ መሳይ በወገቡ ያጎነበጠ ቅማላም ወታደር ነበረ፡፡
ይሄው ወታደር ግን እሱን ደስ ሳይለው የሌላውን ደስታ ሲከለክል፣ ለገዛራሱ ላያልፍለት፣ የደሀውን ንብረት ሲአፈርስ ይኖር ነበረ፡፡ ይሄው ወታደር እንኳንስ ተሰሪነት ገብቶ ለቅሉጥ ሂዶም ባደረበት አገር ሳይቀር ደሀውን የፊጥኝ አስሮ ‹ነጭ ኑግ፣ ጥቁር ወተት ውለድ› ሲልና ባለቤቶቹ፣ ምሽቲቱ እንደገረድ፣ ባልዮው እንደሎሌ እግር አጥበው፣ አልጋ አንጥፈው፣ ትራፊውን በልተው፣ እነሱ ተምድር እሱ ታልጋ ተኝተው ያድሩ ነበረ፡፡
ከቶም አንዳንድ ጊዜስ መልከ ቅን ምሽት የነበረችው ባላገር በመከራ ላይ መከራ፣ በግፍ ላይ ግፍ፣ በውርደት ላይ ውርደት ታክሎበት ያድር ነበረ፡፡ ከነዚሁ መከረኞች አንዱ መልከ ቅን ምሽት ነበረችው፡፡ አንድ ቀን በቴዎድሮስ ጊዜ አንድ ቅጫማም ነፍጠኛ ተቤቱ ተመርቶ ገባና ባለቤቲቱ መልከ ቅን ሁና ባያት ጊዜ ነፍጡን ተጉልበቱ ላይ አድርጎ፡- ‹አንተ እሂች እትህ እስንት ዓመቷ ነው? ቁርጥ አንተን ትመስላለች› አለው፡፡ ያ ባላገር ግን ምሽቴ ናት ማለቱን ፈራ፡፡ ያም እርጉም ነፍጠኛ በጥፊ እያጣፈረ ያችን ምሽቱን ይዞበት አደረ፡፡ ከዚህ በኋላ ያ መከረኛ ደሀ አዘንና ንዴት ያዘውና፡- ‹ታገር እኖር ብየ፣ ከብት እነዳ ብየ፣ ልዥ አሳድግ ብየ፣ ለባሻ ዳርሁለት፣ ምሽቴን እቴ ብየ› ብሎ አንጎራጎረ፡፡
የውነት ነው፣ እንዲህ ያለውን ስራ እነዚያ ንጉሦች አድርጉ ብለው አልነበረም፡፡ ነገር ግን በነዚኣ ንጉሦች ጊዜ ማን ደፍሮ ከወታደር ጋራ ይናገር ነበረ፡፡ ለነዚያ ንጉሦች የበህር ልዣቸው ወታደር ብቻ ነበረ፡፡ ባላገሩንማ እንደ እንጨት ጠርበው፣ እንደጭቃ አንቦልቡለው የሰሩት ያስመስሉት ነበር እንጂ እንደነሱ በአራያ ሥላሴ የተፈጠረ አይመስላቸውም ነበረ፡፡ ነገር ግን ደንቆሮነታቸው ነው እንጂ ሁሉም እንደነሱ ትክክል የተፈጠረ ነበረ፡፡ አለደሀ ዘውድ፣ አለገበሬ ማድ፣ ጀግና ማስከተል እንዳይቻልና ‹ደሀን ካስለቀሱ፣ ተሥላሴ ይወቀሱ፣ መንግሥተ ሰማያትን አይወርሱ› መሆኑን አውቀውት ቢሆን ደግ ነበር፡፡ በሆነ ባልሆነው እግዚአብሔር አሳምሮ የሰራውን አካል ዓይን በሳት ሲአስፈርጡ፣ እጅና እግር በስለት ሲአስቆርጡ፣ ምላስ በምላጭ ሲአሳጥሩ ይኖሩ ነበረ፡፡
አሁን በደጉ በዳግማዊ ምኒልክ ጊዜ ግን ያ ሁሉ መከራ፣ ያ ሁሉ ግፍ ቀረ፣ በኢትዮጵያ ፀሐይ ወጣ፣ ጨለማ ተሻረ፣ ወታደርና ባላገር ትክክል ያድር ጀመረ፣ ደሀና ባለጠጋ ትክክል ተናግሮ ሁሉም እንደልቡ ተዛንቶ ይኖር ጀመረ፣ አለፈለት፣ ደስ አለው፣ በዓለም እንቅልፉን ይተኛ ጀመረ፡፡
በናጤ ቴዎድሮስና በናጤ ዮሐንስ ጊዜ ከጅብ አምልጦ የቀረ፣ ቆርብት የመሰለ፣ ጨርማዳ ጋሻ በብብቱ ያጣበቀና ባለቋድ ወይም ሲሶ እንጨት ብረት ወሳይ በጫንቃው አጋድሞ ብቅ ያለ እንደሆነ፣ አንድ እከካም ነፍጠኛ ብቻውን ሁኖ አንድ መንደር ሲአሥር፣ ሲፈታ፣ ሲአስጨንቅ ያድር ነበረ፡፡ በዳግማዊ ምኒልክ ጊዜ ግን እንኳን ነፍጥ ተሸክሞ፣ መድፍም በጎኑ አሟቅሎ ቢሄድ ለወታደር የሚፈራ ባላገር የለም፡፡ በምኒልክ ጊዜ ወታደርም፣ ባላገርም፣ ሁሉም በየውለታው ትክክል ያድራል፣ ሁሉም ትክክል ነው፡፡
ትናንት ባጤ ዮሐንስ ጊዜ ንጉሡ አልፈው ሲሄዱ ትክ ብሎ አክብሮ እንደ ብርቅ ንጉሡን ያየ ሰው፣ እንደ ክፉ አድራጊ በጀርባው የዱላ ማት ይፈላበት ነበረ፡፡ ደጉ ምኒልክ ግን ማንም የተገፋ ደሀ፣ ማንም ሰራተኛ፣ ማንላቾውም ባላገር ቀርቦ ጉዳቱን፣ ጥቃቱን ቢነግረዎ፣ እንዳባት ስቀው፣ እንደ ንጉሥ አውቀው፣ ለምን ደፈረኝ ሳይሉ በምሕረት ዓይነዎ አይተው ፊተዎን አብርተው ሰምተው ደስ ያሰኙታል፡፡ ምኒልክ ለደሀው አባት ነው እንጂ ንጉሥ አይደለም፡፡ ለምኒልክ ምን ኩራት፣ ምን ንፍገት፣ ምን ሰሀ፣ ምን አመል አለው፡- የምኒልክ አመሉ ሰው ሁኖ መፈጠሩ፡፡
ሰው ተሆነ ዘንድ እንደሰው አደገ፣ እንደ ጀግና ተዋጋ፣ እንደ ንጉሥ ዘውድ ጫነ፣ ሉል ጨበጠ፣ ነገር ግን እንደ ንጉሥ አልገዛም፣ ብቻ እንዳባት አሰበ፣ ለደሀው እንደናት አዘነ፡፡ የሱ አመሉ ሥጋ ለብሷልና አንደሰው ታደገ፣ እንደ ሰው አረጀ፣ ሞት አይቀርምና እንደ ሰው ይሞታል፣ ሞት አይቀርለትም፡፡ የዳግማዊ ምኒልክ ይሄ ነው አመሉ፣ ይሄ ነው የኢትዮጵያ ጉዳት፣ ይሄ ነው ያበሻ መከራ፡፡ ምነው እንደ ሰው የማታረጅ፣ እንደ መላክ የማትሞት፣ የማትታመም፣ የማትደክም ሁነህ ተፈጥረህ ቢሆን፣ አንተ እናት ንጉሥ!፡፡
— ዳግማዊ ፡ አጤ ፡ ምኒልክ (ንጉሠ ፡ ነገሥት ፡ ዘኢትዮጵያ)፣ አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ፣ ዘብሔረ ዘጌ፣ በ1901 ዓመተ ምሕረት ሮማ ከተማ የታተመ፡፡ Prof. Afevork A Yohannes, Tenero Figliulo Dell’Autore L’Editore, Biografia dell’Imperatore Menilek II,
ታሪክ ምስክር ነው!
እምዬ ምኒልክ ብሩክ ነፍስዎት ትቀደስ በሠማይ!
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!
Filed in: Amharic