>

ታሪክ ራሱን ሲደግም ...!!!! (ሳሚ ዮሴፍ)

ታሪክ ራሱን ሲደግም …!!!!

ሳሚ ዮሴፍ

ራስ መንገሻ ዮሐንስ የአጤ ምኒልክን ንጉሠ ነገሥት ባለመቀበል አመጹ፤ የአሳዳጊዬ የአባቴ ስልጣን የሚገባው ለኔ ነው በማለት አሻፈረኝ አሉ። አጤ ምኒልክ ደጋግመው መልእክተኛ ቢልኩም ራስ መንገሻ እምቢ አሉ መልእክተኞቹም እኛ አልሆነልንም እርሶ የሚያደርጉትን ያድርጉ ብለው መልእክተኞቹ ለአጤ ምኒልክ ተናገሩ።
አጤ ምኒልክ “ለልጄ ለወዳጄ ለራስ መኮንን
 በሐረርጌ ላይ ትግሬን ሰጥቸዋለሁ” ብለው ሾሟቸው ቀጥሎሞ ይህ አዋጅ ታወጀ።
                            ስማ የትግሬ ሰው
“ራስ መንገሻ ፊት ደጃች ስዩምን አስሬ እሱን ብሾሙው ከዳኝ።
አሁን ደግሞ እሾሁን ነቅዬ አደላድዬ ሾሜው ብመጣ (ጣልያንን አባርሬ ማለታቸው ነው)  እኔን አባቱን ከዳኝ።
የትግሬ ሰው አድባራቱም፣ መኳንንቱም፣ ራስ መንገሻ ስወደው ጠልቶኛልና ግፌን እይልኝ። እኔ ግን የአጤ ዮሐንስን ወሮታ እመልሳለሁ ብዬ መኳንንትና ወታደር ሳይወደው በግድ ሹሜው ነበርና መሬት አሰኔበተችው እንጂ እኔ በድዬው አይደለም። አሁንም የትግሬ ሰው ወዳጄ ነህ። ራስ መንገሻ ከዳኝ ብዬ በእሱ ተናድጄ አላጠፋህም፤ እግዚአብሔር የሰጠኝን ሀገሬን በእጄ አድርጌ አለማዋለሁ፣ ደስ አሰኝሃለሁ፤
አይዞህ ግባ በየአባትህ እተክልሃለሁ።  አባትህን መርቅ፣ አባትህን እርገም። ልብህ ያሰበውን የሚያደርግልህን፣ ለባህሪህ የሚስማማህን ልጄ ወዳጄን ራስ መኮንንን ሰጥቼሃለሁ። ከሐረርጌ ጋር ትግሬን ማድረጌ አንተን እንዲያለማህ፣ አንተን እንዲጠቅምህ ብዬ ነው።
የእሱን ይሰጣችኋል እንጂ ከትግሬ የሚፈልገው ነገር የለም።
አራሽም እረስ፣ ነጋዴም ነግድ። ከዚህ ወዲያ ከመንገሻ ጋር የተገኘህ ሰው በነፍስህም ተገዝተሃል በሥጋህም እኔ እቀጣሃለሁ። ርስትህን፣ ጉልትህን እስከ ሶስት ትውልድህ እነቅልሃለሁ።”
አጤ ምኒልክ ይህን ካወጁ በኋላ ምናልባት ራስ መንገሻ ጦርነት ያስነሱ ይሆናል በማለት ከአዲሱ ተሿሚ ከራስ መኮንን ጋር ራስ ሚካኤልን፣ ዋግሹም ጓንጉልን እና ደጃዝማች አባተን አብረው እንዲሄዲ አዘዟቸው። እነኚህም መኳንንቶች መቀሌ ሲደርሱ ራስ መንገሻ ከመቀሌ ወጥተው ጣልያኖች በሰሩት እዳጋ ሐሙስ ካለ ምሽግ ውስጥ ገቡ።
ከራስ መኮንን ጋር የሄደው ጦርም አዳጋ ሐሙስ  ምሽጎን ከብቦ ተቀመጠ።  ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ራስ መንገሻ በሰላም እጃቸውን እንዲሰጡ ይጠየቁ ጀመር። በተለይም ራስ ሚካኤል የአጤ ዮሐንስ ክርስትና ልጅ በመሆናቸው ከራስ መንገሻ ጋር ልጁ ወዳጅነት ነበራቸውና
 “…እባክህ እኔ ላስታርቅህ ምን ሆንክ እና ነው? የአንተን ሀገር የሚሾምብህ የለ፣ አትታሰር፣ ደርሰህ አጤ ምኒልክን እናትህን እቴጌ ጣይቱን ክደህ ከደን ትገባለህ…” እያሉ ደጋግመው ደብዳቤ ጻፉላቸው። ራስ መኮንንም እንደዚሁ እያሉ እያባበሉ ደብዳቤ ቢፅፉላቸው ራስ መንገሻ የሁሉንም አልሰማ ብለው እምቢ አሏቸው።
ከዚህ በኋላ ከራስ መኮንን ጋር ያሉት መኳንንት መክረው በመዋጋቱ ወሰኑ። ወስነውም እነርሱ በግንባር፤  ከበስተኋላ ደግሞ በአጋሜ በኩል አራት ሺህ ጠመንጃ የያዘ ወታደር አሰለፉ። ለመሰለል የወጣ የራስ መንገሻ ጥቂት ሠራዊት በአጋሜ በኩል ከተሰለፉት ወታደሮች ጋር ተገናኝተው ተኩስ ከፈቱ። የራስ መንገሻ ሰዎች ተጎድተው የተረፉት ሸሽተው ወደ ምሽጋቸው ገቡ። ከዚህ በስተቀር ሌላ ምንም ግጭት አልተደረገም። ስለመጨረሻው ሁኔታ ፀሐፌ ትእዛዝ ገብረስላሴ በፃፉት ታሪክ እንዲህ ይላሉ…
“…የሰፈረበት ሰፈር ከአጠገባቸው ያለ ተራራ በሰማይ ደመና ሳይዞርና ዝናብም ሳይኖር በጠራራ ፀሐይ ከቀኑ 6 ሰዓት ሲሆን ገደሉ ተናደበት። የተቀመጡበት መሬት እንደከዳቸው ያንጊዜ አወቁት። ገደሉ በተናደበት ጊዜ እነ ራስ መኮንን ከሰፈሩበት ድረስ ተሰማ። እነርሱም ይህ ነገር የመድፍ ተኩስ ነው፣ ጦር መጣ ይሆን ብለው ታጥቀው ተሰልፈው እስቲወጡ ድረስ የመሬቱ ጩኸት ድምፁ እየተሰማ አንድ ሰዓት ያህል ጊዜ  ቆየ…እሱም ከዚያ ወዲያ ትግሬ ሀገራቸውን የወደዱትን ይሹሙበት፤ እኔን ለጄ አስምሩኝ ብሎ አስተማምኖ ገባ…”
አጤ ምኒልክም ትግራይን ለሶስት ከፍለው ከወር ወንዝ ወዲያ ያለውን ሀገር ለደጃዝማች ገብረስላሴ፣ ከወር ወንዝ ወዲህ ያለውን ሀገር ለደጃዝማች አብርሃ፣ አጋሜን ለሹም አጋሜ ደስታ ሰጡ። ራስ መንገሻም አንኮበር ላይ ታሰሩ።
ራስ መንገሻም በእስር ላይ ሆነው ” ጥፋት የለብኝምና እንደገና ፍርድ ይታይልኝ፤ ጥፋተኛ ሆኜ ብገኝ ከዚህ ካለሁበት እስር የባሰ ልታሰር።” ብለው ወደ አጤ ምኒልክ ላኩ። አጤ ምኒልክም ይሄንን ደብዳቤ መልስ ጻፉላቸው።
ይድረስ ከልጄ ወዳጄ ራስ መንገሻ
ከድቼ ብገኝ አደባባይ አይቶት እንደገና ከብርቱ እስራት ልግባ
ብለህ ላክብኝ፤ ሀገርህንስ የተሻርክበት አንተስ እስካሁን ከእኔ የተለየህበት ከፍቃዴ ብትወጣ ብትከዳኝ ነው እንጂ አለዚያማ በምን ምክንያት ይህ ሁሉ ተደረገ። እኔም ይህን አደባባይ ይታይ እንዳልል ከዚህ በፊት አደባባይ አይውጣ፣ፍትሐ ነገሥት አይታይ ብለህ ሰዉን ሁሉ አማልክ።
ደግሞስ እነ ራስ ሚካኤል፣ እነ ራስ መኮንን የዘመቱት በአንተ ክህደት ነው እንጂ ማንን ሊፈልጉ ሄዱ።  ደግሞም ደብዳቤ አለኝ ትላለህ አሉ። አሁንም ደብዳቤውንም በተረፈ ነገሩም እኔን በውል እንዲገባኝ አድርገህ ሁሉንም ገልጠህ ለታመነ ሰው ላክብኝ። ከኔም ዘንድ ይኸውና በጅሮንድ ገድሌን ልኬልሃለሁ።
ኅዳር 16 ቀን 1889 ዓ.ም
ራስ  መንገሻ በእስር ላይ እንዳሉ በተወለዱ በ42 ዓመታቸው
በ1899 ኅዳር 6 ቀን አንኮበር ላይ ሞቱ።
በራስ መንገሻ ግዛት ላይ ትግራይን ተካፍለው የተሾሙት ደጃች አብረሃ ለጥቂት ዓመታት ከምኒልክ ጋራ ወዳጅ ሆነው ከቆዩ በኋላ ከድተው ሸፈቱ። ጦር ታዞም ድል ሆነው ደጃች አብረሃ ተይዘው ታሰሩ። ይህንን የተደጋገመ የክህደት በደል ያየው ህዝብም በትግሬዎች ላይ ቂም ይዞ በያገኘበት ቦታ ሁሉ ይሰድብ ጀመር። ይህንንም ድርጊት ምኒልክ እንደሰሚ የሚከተለውን አዋጅ በኅዳር ወር 1902 ዓ.ም  አወጁ።

 አዋጅ

አንድ ሰው ደጃች አብረሃ ቢከዳ እዚህ የተቀመጠውን እኔን የሚወደኝን የትግሬን ሰው ሁሉ ታስቀይማለህ አሉ። አባያ ወንድሙ ይታሰርበታል እንጂ ይታረዳልን። አሁንም ዳግመኛ በአደባባይ ያለውን የትግሬን ሰው የሚያስቀይም ነገር የተናገርክ ትቀጣለህ። አደባባይ ያለህም የትግሬ ሰው የሚያስቀይም የተናገረህን ሰው ተያይዘህ አምጣልኝ ዳኝነት ይታይልሃል።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!!
Filed in: Amharic