>

ለካርቱም - ከዲፕሎማሲ  አንስቶ  የቤት ሥራ እስከመስጠት....!!!! (መለሰ ነጋሽ)

ለካርቱም – ከዲፕሎማሲ  አንስቶ  የቤት ሥራ እስከመስጠት….!!!!

መለሰ ነጋሽ

ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሱዳን ጋር  ጥንቃቄ በሚጠይቅ የድንበር ውዝግብ ውስጥ ናት። በትኩረት ልንሰራባቸው ከሚያስፈልጉን ተግባራት ውስጥ ዲፕሎማሲ ቀዳሚው ነው።
ከሱዳን ጋር የዲፕሎማሲ አማራጮችን እስከ 11ኛው ሰዓት መጠቀም አትራፊ ነው። የሱዳን ሽግግር ም/ቤቱ የቆይታ ዘመን ሊጠናቀቅ ከአንድ ዓመት ያነሰ ዕድሜ የቀረው በመሆኑ ይህን የቀውስ ጊዜ በከፍተኛ ጥበብ መምራት ይጠይቀናል።
“የዲፕሎማሲ አማራጩ አልሰራ ሲል እንደ አስፈላጊነቱ ለሱዳን የቤት ስራ መስጠት ተገቢ ሊሆን ይችላል” የሚሉት የሰላምና ደህንነት አማካሪ የሆኑት ሙሏለም ገብረ መድህን “የኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር ይዞታ” (ታሪካዊ ምልከታ) ሲል የከተበውን ትንሽ የረዘመች ነገር ግን ጠቃሚ ሐተታ ቅርፃዊ አርትኦት በትንሹ ሰርቼበት አካፍያችኋለሁ።

የኢትዮ ሱዳን የድንበር ግጭቶች ቅኝት

ለረዥም ዓመታት በሱዳን እና ኢትዮጵያ መካከል የዘለቀው ግንኙነት ወጥ መልክ ያልነበረው ነው። የኢትዮጵያ የግዛት ወሰን ከመጽናቱ ቀደም ብሎ በነበሩ ጊዜያት የኢትዮጵያ ነገስታትና የጦር አበጋዞች በኢትዮ – ሱዳን ጠረፍ አካባቢ ከግብጽ ተስፋፊ  ኃይልና ከሱዳን የንቅናቄ (መሐዲስት) ኃይል ጋር ተደጋጋሚ ጦርነት አድርገዋል፡፡ በአፄ እያሱ ብርሃነ ሰገደ የንግስና ዘመን የኢትዮጵያ ድንበር ‹‹ገዳሪፍ››ን እንደሚያልፍ (ከዛሬዋ ሱዳን ግዛት መቶ ኪሎ ሜትር ይዘልቅ) ነበር (ተከለ ፃዲቅ መኩሪያ፣‹‹ከአፄ ልብነ – ድንግል እስከ አፄ ቴዎድሮስ›› የሚለውን መጽሃፍ ያስታውሷል) ይህን የታሪክ ጭብጥ እናቆየውና በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ዋዜማ የካሳ ኃይሉ (ኃላ ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ) የአባቱ ልጅ የሆነው ደጃች ክንፉ በ1829   ‹‹ወድ ከልተቡ›› በተባለ ሥፍራ በሱዳን በኩል የመጣውን የግብጽ ተስፋፊ ጦር ድል መትቶ ሰዷል።
 እርሱ (ካሳ) ‹‹ቱርክ›› ብሎ ከሚጠራቸው ኦቶማናዊ ኃይሎች ጋር ያደረገው የዕድሜ ልክ ፍልሚያና ኢየሩሳሌምን ከነሱ ነፃ አወጣለሁ የሚለው ሕልምም የተፀነሰው (ጓንግ ወንዝ ላይ) በኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር ላይ ነው። (በይበልጥ የተክለፃዲቅንና የባህሩ ዘውዴን ሥራዎች ያጤኗል)፣ገፊ -ምክንያቶቹ የተለያዩ ቢሆንም መተማ ላይ የአፄ ዮሐንስ አራተኛ አሳዛኝ የጦር ሜዳ ህልፈትም ስለ አገር ግዛት ሉዓላዊነት የተከፈለ መስዋዕትነት መሆኑን ታሪክ ሲያወሳው የሚኖር ጉዳይ ነው፡፡

በኢትዮ ሱዳን ድንበር ግጭት  እንግሊዝ መሰሪ እጅ

ፕ/ር ማርካኪስ “National and Class Conflict in the Horn of Africa” በሚለው መጽሐፋቸው ስለኢትዮጵያ ሀገረ-መንግሥት ምስረታ (State Formation) “በአፍሪካ ደረጃ ከውስጥ ወደ ውጭ በሆነ የማስፋፋት መንገድ የተፈጠረች ብቸኛ አገር ነች” ይላሉ፡፡ የሱዳንና የሌሎች የአፍሪቃ አገራት (በርግጥ ኤዥያና ላቲኖችም ይጋሩታል) እንደ አገር ስሪታቸውም ሆነ ድንበራቸው በቅኝ ገዥዎቻቸው የተሰመረ አርቲፊሻል ድንበር ነው፡፡ ግዛታቸው የሰፋው በቅኝ ገዥዎቻቸው ፍላጎት ሲሆን፤ ሂደቱ ከውጭ ወደ ውስጥ ነበር፡፡ የሱዳንን ከውጭ የመጣው የእንግሊዝ ኃይል ወደ ውስጥ ገብቶ ሲያሰፋው የኢትዮጵያን የሚለየው በነገስታቱ የተመራ መሆኑ ነው፡፡ መቀመጫ ግዛቱ ቢለያይ እንኳ ግዛቱ የተስፋፋው በኞቹ ነገሥታት ነው፡፡ የኢትየጵያና የሱዳን ድንበር ውዝግብ በመነሻነት መሠረታዊው ችግር የሆነው ይህ ይመስለኛል (ድኀረ-1983 ሌላ ነው ጉዳዩ፡፡ ይህኛው ጽሁፍ ቅድመ-1983 ላይ ነው ትኩረቱ)
 –
በቅኝ በተገዛችና ቅኝ ባልተገዛች አገር መካከል ያለ መሠረታዊ የግዛት አረዳድ ችግር አለ። የታሪክ ሰነዶች እንደሚያስረዱት እንግሊዝ ሱዳንን በቅኝ ገዥነት ከመያዟ በፊት የኢትዮጵያና የሱዳን ወሰን ‹‹ጓንግ›› ተብሎ የሚጠራው ወንዝ እንደሆነ ተደርጎ ይወሰድ ነበር፡፡ በዳግማዊ ምኒልክ የንግሥና ጊዜ (ድህረ – አድዋ) ሱዳን በእንግሊዝ ቅኝ ገዥነት በነበረችበት ወቅት የኢትዮጵያና የሱዳን ወሰን እንዲካለል ከእንግሊዝ በቀረበው ጥያቄ መሰረት በአፄ ምኒልክ ተቀባይነት አግኝቶ ግንቦት 8፣ 1894 ዓ.ም. ውል ተፈረመ።ይሁንና ስምምነቶቹ በአፈፃፀም ላይ ችግሮች ነበሩባቸው።ካርታ ዘርግቶ ድንበር ከመከለል ባሻገር በቦታው ተገኝቶ ድንበሩን በምልክት መለየት አልተቻለም ነበር (በይበልጥ የባህሩ ዘውዴን የምርምርስራዎች ያጤኗል)
ይህም ሆኖ ከዳግማዊ ምኒልክ ህልፈት በኋላ የልጅ ኢያሱን አጭር የንግሥና ዘመናት ተሻግረን ‹‹በንግሥት ዘውዲቱና በልዑል አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን ጊዜ የኢትዮጵያ ወሰን ጓንግ ወንዝ ድረስ መሆኑ ስለታመነበት፣ ሱዳኖች የጓንግ ወንዝ እንዳይሻገሩና ከተሻገሩም ለሚያገኙት ጥቅም ሁሉ የግጦሽ ሳርን ጨምሮ ግብር እንዲከፍሉ በተደረገው ስምምነት መሰረት ከፍተኛ ጎደቤና መተማ ላይ ጉምሩክ ተቋቁሞ ይህን ህግ የሚያስከብሩ የአካባቢው ተወላጆች በጠረፍ ኃላፊነት ተመድበው ነበር።ለጠረፍ መጠበቂያ 16ዐ ያህል የጦር መሳሪያ ተመድቦ እንደነበርም ይነገራል (ነገዱ አባተ፣ ‹‹የጠረፍ ጀግኖች›› የሚለውን ጽሁፋቸውን ያጤኗል)››፡፡
 –
ይህ አሰራር በየጊዜው እየተደራጀና የጉምሩክ ሥራው እየዘመነ ከሞላ ጎደል በረዥሙ የአፄ ኃይለሥላሴ 44 የንግሥና ዘመናት ተፈፃሚ ሆኗል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ አልፎ አልፎ የአማራ አርሶ አደሮች ከሱዳን አርሶ አደሮች (ዘላኖች ጭምር) ግጭት የነበረ ቢሆንም ለክፉ የሚሰጥ አልነበረም፡፡ በአፄው የንግስና ዘመን መገባደጃ ላይ 1965 ዓ.ም. የሱዳን መንግስት የአማራ አርሶ አደሮች ጓንግ ድረስ ማረሳቸውን በግልጽ ተቃውሞ ለንጉሱ የወሰን ማካለሉ ሥራ እንግሊዝ በሰራችው የቅኝ ግዛት ካርታ መሰረት እንዲሆን ጠየቀ፡፡ በጊዜው በለውጥ ትናጥ የነበረችው ኢትዮጵያ የድንበሩን ጉዳይ በይደር ይዛ የማታ ማታ በደርግ የተጠለፈውን አብዮት አስተናገደች። የድንበር ማካለል ዳግም ጥያቄው ተንከባሎ የደርግ ትከሻ ላይ አረፈ፡፡
በ197ዐ ዓ.ም. በፕሮፌሰር መስፍን ወ.ማሪያም የሚመራ የታሪክ ምሁራን የተካተቱበት የወሰን ኮሚሽን ተቋቁሞ ጉዳዩን አጥንቷል።የሱዳን ቅኝ ገዥ የነበረችው እንግሊዝ፣ ሎንደን ድረስ በመሄድ መረጃዎችን በማሰባሰብ የሱዳን መንግስት የሚያቀርበው የወሰን ጥያቄ መሰረታዊ መነሻ የሌለው መሆኑንና፣ጉዳዩ የቅኝ ግዛት ውርስ ዕዳ እንደሆነ የወሰን ኮሚሽኑ መግለጫ ያመለክታል፡፡
(በነገራችን ላይ ሱዳኖች በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ወቅት በፊልድ ማርሻል ዳዊን ተሰመረ የሚሉትንና ካርታው ላይ ወደ ኢትዮጵያ ገባ ብሎ የሚታየው በተለምዶ ‹ጊወን ላይን› የሚባለውን መሰመር እንደ ወሰን ይቆጥሩታል፡፡ በዚህም እስከ አብደራፊ መዳረሻ ያለውን ቦታ የኛ ነው ብለው ያስባሉ፡፡  እኛ ኢትዮጵያዊያን ይህን ባለመቀበል የሀገራችን ደንበር  ጓንግ ወንዝ ላይ ነው የሚል የተጨበጠ የታሪክ ሙግት አለን። በዚህ በኩል ስምምነት ያለመኖሩ ዋነኛ ምክንያት፣ ሱዳን ድንበሯ በቅኝ ገዥ የተሰመረ መሆኑ ሲሆን፤ የኛ ደግሞ ከውስጥ ወደ ውጭ በተደረገ የግዛት ማስፋፋት ከቅድመ እንግሊዝ ወረራ ያጸናነው ድንበር በመሆኑ ነው፡፡ በፕ/ር መስፍን ወልደማርያም ይመራ የነበረው የወሰን ኮሚሽኑ የያኔው መግለጫ/ሪፖርት ያመለከተውም ኢትዮጵያ ታሪካዊ ግዛቷን እንድታጸና፤ የሱዳን ጥያቄ ከቅኝ ገዥዋ እንግሊዝ የወረሰችው ስለመሆኑ ይጠቅሳል)
 –
ከዚህ መግለጫ በመነሳት የሱዳን መንግስት የደርግን የአገር ግዛት ሉዖላዊ ቀናኢ ስሜት በወራሪው የሶማሊያ ኃይል ያሳረፈውን ክንድ አይቷልና ጥያቄውን ደግሞ ደጋግሞ ከማንሳት  ተቆጠበ፡፡ ይልቁንስ ዛሬ የሞተ ታሪክ ለመሆን የበቃው  ትሕነግ ያኔ በጫካ ቆይታው በመርዳትና ነፃ መሬት በመስጠት ኢትዮጵያን ሰላም መንሳት እንደአማራጭ ፖሊሲ የያዘው የሱዳን መንግሥት የደንበር ውዝግቡን በይበልጥ አወሳስቦታል፡፡ የደርግ አፀፋም ከዚህ የተለየ አልነበረም።  የዛሬዋን ደቡብ ሱዳን እንደአገር ለመመስረት የአንበሳውን ድርሻ የሚይዘውን የጆን ጋራንግን አማፂ ቡድን በመርዳት ተጠመደ፡፡ በመሀል ቤት የድንበሩ ጉዳይ ተዘነጋ፡፡ በዚህ ሂደት ጓንግ ወዲህ ያለው የኢትዮጵያ መሬት ውስጥ ከደርግ መንግሥት ቁጥጥር ውጭ ሆኖ፣ የሱዳን አርሶ አደሮች፣ ትልልቅ ባለሃብቶች ከሱዳን ጀኔራሎች ጋር በመጋራት በዚህ አካባቢ ድንበር ጥሶ በመግባት የሚያርሱበት ፖለቲካዊ ዕድል አግንተው ሲጠቀሙበት ቆዩ፡፡ በወቅቱ ትሕነግ ወልቃይትን ያህል ስትራቴጅክ መሬት በቁጥጥር ስሩ ያዋለ በመሆኑ በዘላቂነት ለማጽናት ከጦርነቱ ጎን ለጎን፣ ሰፊ ዝግጅት ላይ ነበር፡፡
ድህረ – ደርግን ተከትሎ የሱዳን መንግስት አርሶ አደሮቹንና ዘላኖችን በጦርነቱ ጊዜ የተላመዱትን ቦታ ለማጽናት ቀስ በቀስ ወደ ኢትዮጵያ ለም መሬት በቋሚነት ማስፋፋቱን ተያያዘው፤ ይህ መንግስታዊ ድጋፍ ያለው ተስፋፊነት በአካባቢው የሚኖሩ የአማራ አርሶ አደሮችን ቢያስቆጣም፣ በወቅቱ ማዕከላዊ ‹‹መንግስቱን›› የተቆጣጠረው ትሕነግ ለሱዳን ተስፋፊ ኀይል ፖለቲካዊ ይሁንታ የሠጠ በመሆኑ ሱዳን የኢትዮጵያ ተፈጥሯዊ ድንበር የሆነውን ጓንግ ወንዝን ተሻግራ እግሯን ለመትከል በቃች፡፡ በሂደትም የያኔው  የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር በነበረው አባይ ጸሐዬ በኩል መሬቱን አሳልፎ የመስጠት ፊርማ ተከናወነ። ያም ሆኖ ለግዛታዊና ልዖላዊ ማንነቱ ፍጹም ቀናዒ የሆነው የአማራ አርሶ አደር መሬቱን አላስነካ ብሎ እንዳስከበረው ይገኛል። አልፎ አልፎ በተለይም በሰሊጥ እርሻ ወቅት (ግንቦት-ሰኔ) እና በመኽር ወቅት (ሕዳርታ-ህሳስ) አካባቢው የግጭት ቀጣና መሆኑን አላቆመም።

እንደ-መውጫ

እንዳለመታደል ሆኖ የትግረኛ ቋንቋ ተናጋሪ መሐዲስቶች የኢትዮጵያ ግዛታዊ ልዖላዊነት ጠላት ሆነው ተነስተዋል። ይህ ተቃርኖ ሊፈታ የሚችለው ቅድሚያ የውስጥ ሰላማችንን በአስተማማኝ ሁኔታ በማረጋገጥ ሲሆን፤ በዚህ ሂደት ለባዕድ ፍላጎት ታማኝ የሆነን ባንዳ አይቀጡ ቅጣት መቅጣት ይገባል። ቀጥሎ ከሱዳን ጋር የዲፕሎማሲ አማራጮችን እስከ 11ኛው ሰዓት መጠቀም ይኖርብናል። የሱዳን የሽግግር ም/ቤቱ የቆይታ ጊዜ ሊጠናቀቅ ከአንድ ዓመት ያነሰ ጊዜ የቀረው በመሆኑ ይህን የቀውስ ጊዜ በከፍተኛ ጥበብ መምራት ይጠይቃል። ሱዳን ከወታደራዊ መኮንኖች ተጽዕኖ ነጻ ትወጣለች ተብሎ ባይታመን፣ በሕዝባዊ ምርጫ ከሚመረጠው መንግሥት ጋር ለመደራደር ጊዜና ሁኔታዎችን መጠበቅ አልፎም ‘ማመቻቸት’ ይጠበቃል።
Filed in: Amharic