>

የመቀሌው ምሽግ...!!! (ሳሚ ዮሴፍ)

የመቀሌው ምሽግ…!!!

ሳሚ ዮሴፍ

* ታህሳስ 29 ቀን ምኒልክና ጣይቱ መቀሌ ደረሱ። መቀሌ እንደደረሱ ጣይቱ የቀደሙትን መኳንንት እነ ራስ መኮንን ሰብስበው “…ይህ ነው ለአቀባበል ያዘጋጃችሁልን ግብር? አንድ የኢትዮጵያ ሹም እናንተን ሁሉ ንቆ እንዲህ እስቲመሽግ ድረስ ዝም ብላችሁ መቆየታችሁ አፈርኩባችሁ” አሏቸው። ከዚህ በኋላ ራስ መኮንን “…ያሠራሁትን ምሽግ እኔ አፈርሰዋለሁ” ብለው ጦርነት ገጥመው ብዙ ሰው አለቀ።
* የመቀሌ የጠላት ምሽግ በወንዶቹ ጀግንነት አልፈታ አለ።  ከዚህ በኋላ የሴት ብልሃት ተተካ። የመቀሌውን እልቂትና ትግል ጣይቱ በየቀኑ ይመልከቱ ነበር። የጣይቱ ማዘንም ሆነ ወንዱን ማበረታታት ትርፉ እልቂት እንጂ ውጤት አልሰጠም።
በዚህ የተናደዱት ጣይቱ ዘዴ ፈጠሩ።
ፀሐፌ ትእዛዝ ገብረስላሴ እንደጻፉት….
“…ንግሥቲቱም እቴጌ ጣይቱ ከድንኳን ብቅ ብለው ግምጃውን አጥር አስገልጠው ሲመለከቱ አዛዥ ዛማኔል አጠገባቸው ቆሞ ነበርና ወደ እሱ ዐይናቸውን ዞር አድርገው ተናገሩ። አንተ ሂድና ውሃውን ለመያዝ ይመች እንደሆን ስፍራውን ሰልለው። ለሊቀ መኳስ አባተም አማክረው ብለው አዘዙ። ሊቀ መኳስ አባተም ስፍራው ጎድጓዳ ነው ለኢጣልያኖችም ቅርባቸው ነው።
የውሃውና የምሽጉ ርቀት 150 ክንድ ይሆናል። ነገር ግን እኔ በመድፍ በሩን እጠብቀዋለሁ። ዘበኞውም ለዐይን ሲነሳ ገብቶ ከወንዙ ይተኛል ብሎ ላከ። ይህም ነገር በእቴጌ ዘንድ የተወደደ ሆነ። ለንጉሠ ነገሥቱም አመለከቱ፤ ንጉሡም እሺ እንዳልሽ አሏቸው።
እቴጌም አሽከሮቻቸውን እንዲህ ብለው አዘዙ…
“እናንተ ከጉድባ ገብተን ካልተዋጋን እያላችሁ ስትመኙ ነበር።
ነገር ግን ለብዙ ሠራዊት ጥቂት ስፍራ አይበቃውምና ከኢጣልያው ነፍጥ ይልቅ እናንተ እርስ በእርሳችሁ ትተላለቃላችሁ። ከውሃው ተኝታችሁ ውሃ እንዳይቀዳ ጠብቁ። ለጉድባው ላይ ሄደን እንዋጋለን ያላችሁ ከሜዳው ላይ ሞት እንደማትፈሩ ተስፋ አለኝ። በሕይወት ያለውንም ባዘዝኳችሁ ነገር እሸልመዋለሁ፤ የሞተውንም ተዝካሩን አወጣለሁ፤ ልጁን አሳድጋለሁ። እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን” ብለው አሰናበቷቸው። እነሱም አምረው ተሰልፈው የተቆጣ ነብር መስለው በአስራ አንድ ሰዓት ወደ ወንዙ ወረዱ።
እቴጌም ሌሊቱን ሙሉ በኅዘን እና በጭንቀት ሲያለቅሱ አደሩ።  ከሌሊቱ 11 ሰዓት ሲሆን የእልፍኝ አሽከሮቻቸው ተነሱ ስማቸውም ገብረጊዮርግስ፣ ድልነሴ፣ ሸዋዬ ይባላሉ።
እነዚህም አሽከሮች የ300 ነፍጥ ሹሞች ናቸው።  ከነሰዎቻቸው ተሰልፈው ወደ ወንዙ ወረዱ። መታኮሻቸውን አዳረጁ ውሃውንም ደፈኑት። እንደ አዳራሽ እንደ እልፍኝ አመቻችተው ወንዙን ተቀመጡበት…”
ከአምባላጌ ጦርነት የተረፈው የኢጣልያ ሠራዊት እየሸሸ መቀሌ ውስጥ ታጎረ። መታጎር ብቻ ሳይሆን የመቀሌው ምሽግ ተጠናክሮ እንዲሠራ በመታዘዙ ኢጣልያኖች ከአምባላጌው ውድቀታቸው በሶስተኛው ቀን የመቀሌውን ምሽግ አጠናክረው መሥራት ጀመሩ። የመቀሌው ምሽግ አሠራር እንዲህ ነበር…በደቡብ ሶስት ሜትር ስፋት ያለው ግንብ እየሆነ ተገነባ። ምሽጉ ዙሪያ ክቡን ካለው ጥብቅ አጥር ሌላ ከግንቡ ሰላሳ ሜትር ያህል ራቅ ብሎ በጣም የሾሉ እንጨቶች በብዛት ተተከሉ። ከአንዱ ሹል እንጨት እስከ አንዱ ሹል እንጨት ያለው ርቀት ሃያ ሴንቲ ሜትር ነበር።
ከመሬት በላይ ያላቸው ከፍታ ሰላሳ ሴንቲ ሜትር ነው።
ከሹሉ እንጨቶቹ አልፎ ደግሞ እሾካማ ሽቦ እየተድበለበለ በምሽጉ ዙሪያ እየተተከለ ተከምሯል። እንኳን ሰው ወፍ አትሾልክም። ከሽቦው በኋላ ደግሞ ጠርሙስ እየተሰበረ እንዲነሰነስ ተደረገ። ምክንያቱም የኢትዮጵያ ሠራዊት ጫማ ስለሌለው እየወጋና እየቆረጠው እንዲያስቀረው ነው።
በርክሌይ እንደጻፈው…
“…ኢጣልያኖች በብዙ መቶ የሚቆጠር ፋሽኮና ጠርሙሶች እየሰበሩና እያሾሉ ደረደሩ። የኢጣልያ መኮንኖች አዲስ ነገር መፈልሰፋቸው ነው። በኔ ግምት ግን ትልቅ ስህተት ነው።
በእነኚያ ሁሉ ፋሽኮና ጠርሙሶች ውሃ ሞልተውባቸው ቢይዙ ይሻል ነበር። በመጨረሻዎቹ 11 ቀናት ለአንድ ወታደር የተሰጠው የውሃ ራሽን በቀን ግማሽ ሊትር ነበር። በዚህ ግምት አንድ ጠርሙስ ውሃ ለአንድ ወታደር ለሁለት ቀን ይሆነው ነበር…።”…ብሏል።
እንዲህ የተሠራውን ምሽግ በጦርነት እንደማይፈታ ያወቁት ብልሃተኛዋ እቴጌ ጣይቱ ውሃውን አስከብበው ያስጠብቁ ጀመር።
ፀሐፌ ትእዛዝ ገብረስላሴ እንደጻፉት…
“…እቴጌ ጠይቱም ውሃውን ለሚጠብቁት ዘበኞች ጠጁ በብዙ ቀንድ እየተሞላ በማለፊያ ወጥ እንጀራ እየተፈተፈተ በመሶብ ሆኖ ፍሪዳው ታርዶ ሥጋው በእንቅብ እየሆነ ከሌሊቱ በዘጠኝ፣ በአስር ሰዓት ይሰዱላቸው ነበር።
 እነሱም ነፍሳቸውን ለጌታቸው ለመንግሥታቸው ለውጠውታልና ትጥቃቸውን ሳይፈቱ እንቅልፍ ሳይተኙ በአንድ ቀን የሚያስመርረውን ጦርነት 15 ቀን ሙሉ ሌሊትና ቀን እየተዋጉ ውሃውን ከልክለው በጭንቀት ኢጣልያኑን ከእርዱ (ከምሽጉ) እንዲወጣ አደረጉት….” ብለዋል።
Filed in: Amharic