>
5:26 pm - Saturday September 15, 3657

የኢትዮጵያቴያትር ከየት ወዴት…..አለ??? የለም???  (በግሩም ተ/ሀይማኖት)

የኢትዮጵያቴያትር ከየት ወዴት…..አለ??? የለም??? 

  በግሩም ተ/ሀይማኖት

ቴያትር በኢትዮጵያ ውስጥ መድረክ ላይ በ1909 እንደተጀመረ ነው የሚነገረው፡፡ ቴያትርን ከመድረክ ውጭ በዚህ ጊዜ ተጀመረ ማለት አይቻልም፡፡ ጥንት ለአደን ሲወጡ ለማጥመድ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ አድነው ሲመለሱ..ብቻ ሰው በባህሉ በእምነቱ የተለያየ ስርዓታዊ ክዋኔ ሲፈጽም፣ በጋብቻ ወቅት..ለጦርነት ሲነሱ የነበረው ፉክራና ቀረርቶ..ሁሉ ቴያትራዊ ሂደት ነበራቸው፡፡ ቴያትር ዘመነ ተብሎ በመድረክ ተከሽኖ ለመጀመሪያ ጊዜ አሁን አንፊ ቴያትር የተባለበት ሴጣን ቤት በመባል የሚታወቀው ቦታ በበጅሮንድ ተክለሀዋሪያት የተደረሰ ቴያትር ቀረበ፡፡ ከዛን ጊዜ ጀምሮ መቶ አመት ያልሞላው የኢትዮጵያ ቴያትር ጥበብ አደገ አላደገም የሚያስብል ደረጃ ደርሶ ይሁን ለማከራከሪያ ብቻ ተፈልጎ ግራ በሚያጋባ ሁኔታ ለብዙ ጊዜ ሲከራከሩበት ያስገርመኝ ነበር፡፡ አላደገም ለሚሉትም አንጋፋዎች ቢሆን ዘመኑ ሲሰለጥን፣ ሲለወጥ የማይለወጥ፣ ቴክኖሎጂ የማይዘልቀው፣ የመከነ ፍሬ አልባ ጥበብ ነው እንዴ ያወረሱን የማያድገው? የማይለወጠው? አልስማማም፡፡ አድጓል፡፡ ይለወጣል፡፡
ካላደገ እንኳን ተጠያቂ እነሱ ናቸው ማለት ነው፡፡ ምክንያት ጥበብ ብለው ያሳዩን፣ ሲሰሩ ያየነውን የተከተልነው የእነሱ ፈለግ ነው፡፡ የማያድግ የጫጨ ከሆነ ያወረሱንም እነሱ ይጠየቁበት፡፡ በአፋጀሽኝ ‹‹ፋቡላ›› (በእንሰሳት) ቴያትር ተጀምሮ እዚህ ደርሷል፡፡ በእርግጥ ያኔ ለጥበብ ስለጥበብ ተጨንቀው ተጠበው ሲሰሩት ዘንድሮ ለጥበብ ብቻ ሳይሆን ለቀለብም ታስቦ ይሰራል፡፡ ፍራንካዋን ያሰበ ሁሉ ጥሩ አይሰራም ማለት ደግሞ ፈጽሞ ጭፍንነት ይሆናል፡፡
በመጀመሪያ ደረጃ በተለያየ ወቅት፣ በተለያየ ስልጣኔ፣ በተለያየ ቴክኖሎጂ..የተራራቀን ነገር እንዴት ማወዳደር ይቻላል? በዛን ወቅት ዘንድሮ ያለው ቴክኖሎጂ አልነበረም፡፡ ዘንድሮ ያለው ስልጣኔ፣በትምህርት የተደገፈ ተስዕጦ… ጥበቡም ይህን ያህል ተቀባይነት አልነበረውም፡፡ ይህ ሁሉ ባልተሟላበት፣ ባልነበረበት ሁኔታ ይሰሩ የነበረውን ሲታይ ጥንካሬያቸው የሚደነቅ ነው፡፡ ለዛሬውም መሰረት ሆነዋል፡፡ በእነ አርቲስት ተስፋዬ ሳህሉ (እኛ አባባ ተስፋዬ በሚለው መጠሪያቸው ነው ብዙ የለመድናቸው) በእነሱ ዘመን ሴት ልጅ ወደ መድረክ ብቅ የማትልበት ወቅት ነበር፡፡ እነ  (አርቲስት)አባባ ተስፋዬ የሴት ገፀ-ባህሪያትን ለመሸፈን ሴት ሆነው መድረክ ላይ ይምነሸነሹ ነበር፡፡ አሁን በቴያሩም ሆነ ፊልም ተብሎ በተሰሩት ፊልሞቻችን ላይ ኦርጅናሏን ሴት አቅፎ እየሳመ ሴቷም የራስዋን ጥበብ እየተጠበበች እናያለን፡፡ የዘመን ለውጥ ያመጣው ለውጥ ነው፡፡
ወንዱ ሴት ሆኖ ሲሰራ እና ሴቷ ራሷ ስትሰራ ማየት ተጽኖስ፣ ለውጥስ አያመጣ ይሆን? ለነገሩ አሁን ደግሞ ሴቷ ጠፍታ ሳይሆን ወንዱ በሰለጠንኩ ባይነት ሴታሴትነቱ ተጣብቶት ተሾርቦ እና ተኳኩሎ ብቅ እያለ ነው፡፡ ጥበብን ለመጠበብ ጸጉርን ማሳደግ እና መኳኳል ግድ ነው የተባለ እየመሰለን ነው፡፡ የጥበብ ሰው ነን ብለው ሲውተረተሩ ከምናያቸው በዛ ያሉት ጉድሮ መሆን ጆሮ ጌጥ፣ መቀባባት… ሴታሴት እንቅስቃሴ ማሳየታቸው ከመብዛቱ አንጻር አብዛኛዎቹ ሜርኩሪ ሆቴል ስብሰባ የጠሩትን ሰዎች (ጌይ) እየመሰሉን ተቸግረናል፡፡ ይህን ባህሪ ስላሳዩ ናቸው ብሎ መደምደም ግን አይቻልም፡፡ አይደሉምም ማለት አይቻልም፡፡
አነሳሴ ቅጥ ስላጣው ድርጊታቸው ለማንሳት አልነበረም፡፡ ነገርን ነገር ጠለፈው እና ዘው አልኩበት፡፡ ምን ይደረግ አርቲስት የሀገሩ አምባሳደር መሆን ሲገባው አንገት የሚያስደፋው በዛብኝና ነው፡፡ ለነገሩ በነካ ኮምፒዩተሬ ላይ ሌላ ቀን ሰፋ አድርጌ በዚህ ዙሪያ እተይበዋለሁ፤ እናንተም ታነቡታላችሁ፡፡ አሁን ወደ ተነሳሁበት የፊልም ሂደት ልመለስ፡፡ የቴያትር ጥበብን አደገ አላደገ እያሉ ‹‹ቴያትር ድሮ ቀረ!..›› ሊሉ የሚዳዳቸውን አንጋፋ ተብዬ እድሜ ጠገቦች ያጋጥሙናል፡፡ የዛውን ያህል ‹‹..ያኔ ምን ስራ ሰርተው ነው አሁን ያለነው የምንሰራው እኮ ሪል አርት ነው…›› ብለው ደፍደፍ ያሉባትን ቢጥቂሌ መድረክ ቴሌስኮፕ ከሚያጎላው በላይ የሚያደምቁ፣ መስታዎታቸው የራሳቸውን ካልሆነ ሌላ የማያሳያቸውም ያጋጥሙናል፡፡
በአንድ ወቅት ቃለ-ምልልስ ስናደርግ ረ/ፕሮፌሰር ሀይማኖት አለሙ ያለኝን ለዚህ ሀሳቤ መደምደሚያ ላድርግ፡፡ በቴያትር ጥበብ ዘርፍ በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ረ/ፕሮፌሰር የሆነው ሀይማኖት አለሙን ‹‹..የቴያትር ጥበብ አድጓል አላደገም ብለው የሚከራከሩ ሰዎች አሉ አንተ የትኛውን ትላለህ?…›› አልኩት፡፡ ‹‹..በጣም አድጓልም አላደገምም ማለት አይቻልም፡፡ ሁሉም የሚለካው በራሱ ወቅት ነው፡፡ ለእነ ዮፍታሄ የእነሱ ዘመን ወርቃማ ዘመን ነበር፡፡ ለእኔ ያ-ያሳለፍኩት ከወጋየሁ ንጋቱ፣ ከደበበ እሸቱ ጋር ደምቀን የነበረበትን ጊዜ እመርጣለሁ፡፡ አሁን ያሉትን ብትጠይቅ ደግሞ ያሉበትን ይመርጣሉ፡፡ ይህን ያልኩህ መብለጡን አለመብለጡን ሳይሆን ሁሉም በዘመኑ መለካቱን ለመግለጽ ነው..›› ብሎኝ ነበር፡፡ ይሄ አድጓል አላደገም ጥያቄ ሲነሳ ብዙ ጊዜ አባቴ እና እኔን የማወዳደር ያህል ነው የሚታየኝ፡፡ በእነሱ ዘመን ገጠር ትምህርቱ የለም፡፡ ቢኖር እንኳን ሲመሽ በኩራዝ ሲያጠና፣ ትራንስፖር የለ…እኔ ስማር ወይም ት/ቤቱ እንደልብ፡፡ በመብራት አጥንቼ..ብዙ ለውጥ አለ፡፡ እኔ የምኖርበት የአሁኑ ዘመን እና አባቴ የኖረበት ትላንትና እንዴት ይወዳደራል፡፡
ይሄ ቴያትር ላይ የነበረው አድጓል አላደገም ውዝግብ ደግሞ ገና እንደጎረምሳ ፂም በማቀምቀም ላይ ያለው የፊልም ጥበብንም እየነካ ነው፡፡ አድጓል አላደገም የሚል መጠይቅ በተለያ መገናኛ ተነስቷል፡፡ ለመሆኑ ከየት ተነስቶ ነው ያደገው? ከምንም ተነስቶ ማቆጥቆጥ ላይ ከሆነ አላደገም የሚባልበት ደረጃ ይኖር ይሆን?
Filed in: Amharic