የቤተልሔም ኮኮብ
መስፍን አረጋ
ኢየሱስ ቤተልሔም በተወለደ ጊዜ፣ ሰብአ ሰገል (የጥበብ ሰወች) የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት ነው፣ ኮኮቡን በምሥራቅ አይተን፣ እነሆ ልንሰግድለት መጥተናልና አሉ (የማቴወስ ወንጌል 2፡1-2)
ይህ ጦማር የተጦመረው፣ ከጥቂት ቀናት በፊት የተከሰተውን፣ ከሁለት ሺ ዓመታት በፊትም በተመሳሳይ መንገድ ተከስቶ ይሆናል ተብሎ የሚገመተውን የቤተልሔም ኮኮብ (Bethlehem star) የተሰኘውን ራማዊ ክስተት ባጭሩ ለማብራራት ነው፡፡
ማሳሰቢያ (ኦሮሙማውያንና ኩሽ)
በዚህ ጦማር ላይ ኩሽ የሚለውን ቃል የምጠቀምበት፣ ከ 12 ዓመታት በፊት በ2000 ዓ.ም ባሳተምኩት ሰገላዊ አማረኛ (አማሮምኛ) በተሰኘው መጽሐፌ ላይ ጨምሮ፣ ከመጽሐፉ በፊትና በኋላ በጻፍኳቸው በሁሉም ጽሑፎቸ ላይ በምጠቀምበት መንገድ ነው፡፡ ይህ የኔ አጠቃቀም ደግሞ ጎጠኞቹ ኦሮሙማውያን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቃሉን ሊጠቀሙበት ከሚሞክሩበት መንገድ ፍጹም ተቃራኒ ነው፡፡ ኩሽ የሚለው ቃል የጥቁር ሕዝብን ልዕልና የሚገልጽ፣ ጦቢያን ማዕከሉ ያደረገ ጦቢያፍናዊ (Ethiopianistic) ቅዱስ ቃል ሲሆን፣ ከቅርብ ግዜ ወዲህ ግን ርካሾቹ ኦሮሙማውያን ጠልፈው አርክሰውታል፡፡
እብራይስጦች ኩሽ የሚሉትን ግሪኮች ኢትዮፕያ (Aithiopia) ስለሚሉት፣ ሊቃውንቶቻችን ብሎይ ኪዳንን ከጽርእ (ግሪክ) ወደ ግእዝ ሲተረጉሙ ኢትዮፕያ የሚለውን ኢትዮጵያ በማለት ያገራችን የጦቢያ መጠርያ አደረጉት፡፡ ኩሽ የሚለው ቃል ግን ያሁኒቷን ጦቢያን ብቻ ሳይሆን፣ ግብጽ የሚባለውን የጥንቱን ከመትን (Kemet) ጨምሮ መላውን አፍሪቃን፣ ካፍሪቃ ማዶ ደግሞ ወደ እስያ የተደመሩትን፣ ዐረብ ከጥቁር ነጥቆ የሰፈረባቸውን፣ ሳኡዲ ዐረቢያን፣ የመንን፣ ኦሞንን እና የቀሩትን ያረብ አገሮችን የሚያጠቃልል ታላቅ ምድር ነበር፡፡ ለዋቢነት ያህል መዝሙረ ዳዊት (71-9፣ 73-14፣ 87-31)፣ 2ኛ ዜና መዋዕል (14-9፣ 14-12፣ 14-13፣ 16-8)፣ ሁለተኛ ነገሥት (19-9)፣ ትንቢተ ኢሳያስ (37-9)፣ ትንቢተ ሕዝቅኤል (30-4፣ 30-5፣ 30-9)፣ የሐዋርያት ሥራ (8-27) ሊጠቀሱ ይቻላሉ፡፡ ለበለጠ መረጃ ደግሞ የታላቁን ሊቅ ያለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌን መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ዐዲስ (ገጽ 13 እና 248) መመልከት ይቻላል፡፡
ለምሳሌ ያህል 2ኛ ዜና መዋዕል (ምዕራፍ 14) “ኢትዮጵያዊው (ማለትም ኩሹ) ዝሪ አንድ ሚሊዮን ሰወችና ሦሰት መቶ ሠረገሎች ይዞ ወጣባቸው …” እያለ፣ አሳ በሚባለው የይሁዳ ንጉሥና በዘመናቸው በሠረገላ ጥበብ የተራቀቁ በነበሩት በኩሾች መካል ስለተካሄደው ጦርነተት ያትትና፣ ከጦርነቱ በኋላ ይሁዳወቹ “ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ” ይላል፡፡ ይህ የሚያመለክተው ደግሞ ኢየሩሳሌምን የከበበው ምድር ሁሉ የኩሾች (የጥቁሮች) ምድር እንደነበረና፣ ከዚያ በፊትም ራሷ እየሩሳሌም የኩሾች ምድር ሳትሆን እንደማትቀር ነው፣ ኩሾች የመጡት የተቀሙትን ምድር ለማስመለስ ሊሆን ይችላልና፡፡ ንጉሥ ሰለሞን ደግሞ እሱ ራሱ “ጥቁር ነኝ ነገር ግን ውብ ነኝ ” ብሎናል (መኃልይ መኃይል ዘሰለሞን፣ 1፡5)፡፡ የኩሽ ሚስጥር ይሄውና ይሄው ነው፡፡
የድንቅነሽ ዐጽም እንደሚመሰክር
ጦቢያ ስለሆነ ቀዳሚ የሰው ዘር፣
ሰውን በአምሳሉ መፍጠሩን ሲናገር
ጌታ ማለቱ ነው ነኝ እንደሱ ጥቁር፡፡
ለዚህም ኩሽና ኦሮሙማ ቅዠታዊ እንጅ አንዳችም እውናዊ ግንኙነት የላቸውም፡፡ ኦሮሙማውያን ኩሽ የሚሉት ኦሮሞና ኦሮሞ ብቻ ለማለት ነው፡፡ የቦረና አርብቷደሮች የኩሽ እምብርት ወደነበረችው ወዳሁኒቷ ጦቢያ የተስፋፉት ግን አሁን ትናንትና በ1500ወቹ ነበር፡፡ በፀረጦቢያወቹ በሻቢያና በወያኔ ታዝለው ከመጓዝ በቀር በገዛ እግራቸው አንድም እርምጃ ተራምደው የማያውቁት ፀረጦቢያወቹ ኦነጋውያን፣ የኩሽ ኢምፓየር ምናምን እያሉ ከምራቸው መዘበራረቅ የጀመሩት አሁን ትናንትና (ባገር ወዳድ ጦቢያውያን ጫንቃ) ስልጣን ለመያዝ አፋፍ ላይ ከደረሱ በኋላ ነው፡፡ እኔ መስፍን አረጋ ግን ኩሽ የሚለውን ቃል መጠቀም የጀመርኩትና ያገራችን የጦቢያ ሞክሸ ስም እንዲሆን የጠቆምኩት ከሃያ አምስት ዓመታት ገደማ በፊት ነበር፡፡ መስፍን አረጋ ዘነገደ ኩሽ፣ የትብቱ ቀብር ደሴ ሳላይሽ፡፡
መጽሐፌ ሄኖክና ጠፈርሲን
በጠፈር (ህዋ) ውስጥ የሚገኙ ራማዊ አካሎች (celestial objects) ጥናት ጠፈርሲን (astronomy) ሲባል፣ አጥኝወቹ ደግሞ ጠፈርሲነኞች (astronomers) ይባላሉ፡፡ የጠፈርሲን ጥናት የተጀመረው ደግሞ በጥንት ጊዜ ኩሽ ይባል በነበረው በጥቁር ሕዝብ ምድር ላይ ነበር፡፡ የጠፈርሲን አባት ደግሞ መጽሐፈ ሄኖክን የጻፈው ታላቁ ጦቢያዊ (ኩሻዊ) ሊቅ ሄኖክ ነበር፡፡
የመጽሐፈ ሄኖክ አምስቱ ምዕራፎች (ምዕራፍ 21 እስከ 25) ሙሉ በሙሉ የሚያወሱት ስለ ጠፈርሲን ብቻ ነው፡፡ ዘመናዊ ጠፈርሲን (modern astronomy) በተለይም ደግሞ ንጸራዊ ጠፈርሲን (observational astronomy) ማለት፣ መጽሐፈ ሄኖክን አምልቶና አስፍቶ፣ አብራርቶና ተንትኖ ከመጻፍ ባሻገር አዲስ ነገር እምብዛም የለውም፡፡ ለምሳሌ ያህል
- ጨረቃ ራሷ የምታመነጨው ብርሃን እንደሌላትና፣ የምታበራውም የፀሐይ ብረሃንን በመፀብረቅ (reflect) እንደሆነ በመጀመርያ የተገነዘበው ሄኖክ ነበር (22፡5)
- ከምድራዊ ነጻሪ (observer) አንጻር የፀሐይና የጨረቃ ዘዌያዊ መጠን (angular size) በቅርበዛ (approximately) እኩል መሆኑን፣ ጨረቃ ከፀሐይ ፊት ለፊት ከሆነች ፀሐይን እቅጩን (precisely) (ሳይበዛም፣ ሳያንስም) ለመከለል እንደምትችል፣ ምሉዕ የፀሐይ ግርዶሽ (total solar eclipse) የሚከሰተውም በዚሁ ምክኒያት እንደሆነ የገለጸው ሄኖክ ነበር (21፡57)፡፡
- ከምድር አድማስ (horizon) ሳይወጡም ሆነ ወደ ምድር አድማስ ሳይጠልቁ ራማ ሉል (celestial sphere) ላይ የሚታዩ፣ በዘመናዊ አጠራር ሠቅዋልታዊ (circumpolar) የሚባሉ ኮኮቦች መኖራቸውን ለመጀመርያ ጊዜ የዘገበው ሄኖክ ነበር (24፡14)፡፡
- የጨረቃ ሻጃወች (phases) (ማለትም መልኮች) እየተቀያየሩ ጨረቃ አዲስ (new)፣ ሙሉ (full)፣ ሐኔ (cresent)፣ ሰኒም (gibbous) የምትሆነው፣ ጨረቃ በምድር ዙርያ በመሖሯ ምክኒያት፣ የፀሐይ ብርሃን ከሚያገኘው የጨረቃ ግማሽ ክፍል ውስጥ ለምድራውያን የሚታየው መጠን ስለሚቀንስና ስለሚጨምር እንደሆነ ለመጀመርያ ጊዜ ተገንዝቦ የዘገበው ሄኖክ ነበር (ምዕራፍ 26)፡፡
- ፈለኮች (planets) በፀሐይ ዙርያ እንደሚሖሩ ለመጀመርያ ጊዜ የተገነዘበውና፣ እነዚህ ፈለኮች ለፀሐይ የተገዙ መሆናቸውን ለመጠቆም በግእዝ ቅኑይ (የተገዛ፣ የተነዳ) ብሎ የሰየማቸው ሄኖክ ነበር (24፡8)፡፡ በሌላ አባባል ፀሐይና ፈለኮች ባንድነት ሁነው፣ በፀሐይ አዛዥ ናዛዥነት የሚተዳደረውን፣ በዘመናዊ አጠራር ጀንበራዊ ስርዓት (solar system) የሚባለውን ስርዓት እንደሚመሠርቱ ተረድቶ ያስረዳው ሄኖክ ነበር፡፡
- የራማዊ አካሎችን (celestial objects)፣ በተለይም ደግሞ የፀሐይንና የጨረቃን ሑሰት (motion) ለመግለጽ ይረዳው ዘንድ ራማ ሉልን (celestial sphere)፣ በዘመናዊው አጠራር ቀኝ እርገት (right ascension) እና ዝቅዝቀት (declination) ለሚባሉት ለተለያዩ የሰማይ መስኮቶች ለመጀመርያ ጊዜ የከፋፈለው ሄኖክ ነበር (ምዕራፍ 26)፡፡
- አንድ ዓመት ማለት ምድር ፀሐይን አንድ ሙሉ ሑረት (revolution) ለመሖር (revolve) የሚፈጅባት ጊዜ ማለት እንደሆነ በቅድሚያ የተገነዘበውና፣ እያንዳንዱን ዓመት ለ 364 ዕለቶች የከፋፈለው ሄኖክ ነበር (23፡20)፡፡
- አንድ ዕለት (ቀንና ሌት) ማለት ምድር በዛቢያዋ ላይ አንድ ሙሉ ፉረት (rotation) ለመፉረር (rotate) የሚፈጅባት ጊዜ ማለት እንደሆነ በቅድሚያ የተገነዘበውና እያንዳንዱን ዕለት ለ 18 ሽንሽኖች የሸነሸነው ሄኖክ ነበር (21፡18-22)፡፡ ዘመነኞች ያደረጉት አንድን ዕለት ከ 18 ይልቅ ለ 24 ሸንሽነው፣ እያንዳንዱን ሽንሽን ሰዓት (hour) ብለው መሰየም ብቻ ነው፡፡
በርግጥም ብልሁ ንጉሥ “ከፀሐይ በታች አዲስ ነገር የለም ” (መጽሐፈ መክብብ፣ 1፡10) ያለው መጽሐፈ ሄኖክን አንብቦ ወይም ተነቦለት ሳይሆን አይቀርም፡፡ መጽሐፈ ሄኖክ የተጻፈው ደግሞ በግእዝ ነው፡፡ ታላቁን ጀርመናዊ የግእዝ ሊቅ ኦግስቲን ዲልማንን (Augstin Dillman) ጨምሮ አያሌ የመዱስ ምሁራን (bible scholars) ደግሞ “ወኮነ ኩሉ ምድር አሐተ ከንፈረ ወአሐደ ነገረ ” (ምድር ሁሉ ባንድ ቋንቋና ንግግር ነበረች) (ዘፍጥረት 11፡1) የሚለውን ይዘውና ተመርኩዘው ግእዝ የአዳም ቋንቋ ነው ብለው በድፍረት ይናገራሉ፡፡ ኩሽ የአዳም ምድር፣ ግእዝ የአዳም ቋንቋ፡፡
ትናንት የበታች የነበረው አሕዛቡ ፈረንጅ
ዛሬ የበላይ ሁኖ በሁሉም ዓይነት ፈርጅ
ቢንቅ ቢጸየፋችሁ አሳንሶ ከውሻ ልጅ፣
አዲስ በመፍጠር አይደለም አክብሮ በማንሳት እንጅ
ተንቆ የተጣለውን በናንተው ከናንተው ደጅ፡፡
የቤተልሔም ኮኮብ
ፈለክ (planet) ማለት በኮኮብ ዙርያ የሚሖር (ማለትም የሚዞር) የራሱን ብርሃን የማያመነጭ ግዙፍ አካል ማለት ነው፡፡ በፀሐይ ዙርያ የሚሖሩ ዘጠኝ ፈለኮች አሉ፡፡ እነዚህም ፈለኮች ከፀሐይ እንዳላቸው ርቀት ሃዴተል (Mercury)፣ ክሌተል (Venus)፣ ስሌተል (Earth)፣ ራቤተል (Mars)፣ ሃሜተል (Jupiter)፣ ሳዴተል (Saturn)፣ ሳቤተል (Uranus)፣ ሳሜተል (Neptune)፣ ታሴተል (Pluto) ይባላሉ፡፡
እነዚህ የፈለኮች ስሞች የተገኙት አሃዱ፣ ክልኤቱ፣ ሠለስቱ፣ አርባዕቱ፣ ኀምስቱ፣ ስድስቱ፣ ሰባዐቱ፣ ስምንቱ፣ ተስዐቱ፣ ዐሥርቱ ከሚሉት የግእዝ ቁጥሮች እና ተላይ (ተከታይ) ከሚለው የግእዝ ቃል ነው፡፡ ተላይ (ተከታይ) የሚለውን ቃል የተጠቀምኩት ደግሞ ፈለኮች ለፀሐይ የሚቀነዩ (የሚገዙ) የፀሐይ ጭፍሮች በመሆናቸው ነው፡፡ ይህ የፈለኮች ያማረኛ ስያሜ፣ የፈለኮቹን አቀማመጥ አመላካች ስለሆነ፣ ከንግሊዘኛው ስያሜ ይልቅ በቀላሉ ሊታወስ የሚችል አሰያየም ነው፡፡
በምድርና በፀሐይ መካከል ያሉት ፈለኮች (ማለትም ሃዴተል እና ክሌተል) ውስጣዊ ፈለኮች (interior planets) ሲባሉ፣ ከምድር ጀርባ ያሉት የቀሩት ስድስቱ ፈለኮች (ማለትም ራቤተል፣ ሃሜተል፣ ሳዴተል፣ ሳቤተል፣ ሳሜተል፣ እና ታሴተል) ደግሞ ውጫዊ ፈለኮች (superior planets) ይባላሉ፡፡ ውጫዊ ፈለኮች ከፀሐይና ከምድር አንፃር ያላቸውን አቀማመጥ በተመለከተ፣ የሚከተሉትን ሁለት ስያሜወች እንጠቀማለን፡፡
- ውጫዊ ፈለኩ ምድርንና ፀሐይን በሚያገናኘው ቀጥታ መስመር ላይ ሁኖ፣ ፀሐይና ፈለኩ ከምድር ፊት ለፊት የሆኑበት ሁኔታ ፊትቻ (conjunction) ይባላል፡፡
- ውጫዊ ፈለኩ ምድርንና ፀሐይን በሚያገናኘው ቀጥታ መስመር ላይ ሁኖ፣ ፀሐይ ከምድር ፊት ለፊት፣ ፈለኩ ከምድር በኋላ የሆኑበት ሁኔታ ኋልቻ (opposition) ይባላል፡፡
ውጫዊ ፈለኮች ፊትቻ ላይ ሲሆኑ፣ እንደ ሙሉ ጨረቃ ያበራሉ፣ ኋልቻ ላይ ሲሆኑ ደግሞ እንደ ጠፍ ጨረቃ ይጠፋሉ፡፡ ሁለት ወይም ከሁለት የበለጡ ውጫዊ ፈለኮች ባንድ ቅጽበት ፊትቻ ላይ ከሆኑ ደግሞ፣ የፈለኮቹ ጥምረት ግዙፍና ብሩህ ኮኮብ መስሎ ለምድራውያን በገሃድ ይታያል፡፡
በማቴወስ ወንጌል (ምዕራፍ 2) ላይ እንደተብራራው፣ ሰብአ ሰገል (የጥበብ ሰወች)፣ ሕፃኑን ኢየሱስን እጅ ለመንሳት ወደ ቤተልሔም የመጡት፣ መወለዱን ለማብሰር በተከሰተ በዘመንኛው አጠራር ቤተልሔም ኮኮብ (Bethlehem star) በሚባል አዲስ ምሥራቃዊ ኮኮብ እየተመሩ ነበር፡፡ ባንዳንድ ጠፈርሲነኛወች (astronomers) ግምት ግን፣ ከ 2000 ዓመታት በፊት ሰብዓ ሰገልን ወደ ቤተልሔም የመራቸው ነው የተባለው ኮኮብ፣ በርግጥም ኮኮብ ሳይሆን የውጫዊ ፈለኮች (በተለይም ደግሞ የሃሜተል እና ሳዴተል) ፊትቻወች ጥምረት ሳይሆን አይቀርም፡፡
Email: መስፍን አረጋ mesfin.arega@gmail.com