>
5:26 pm - Friday September 15, 5550

ጽንፍ የረገጠ ነውጠኝነትና ሰብዓዊ ደህንነት በአፍሪካ (ደረጀ መላኩ - የሰብዓዊ መብት ተሟጋች )

ጽንፍ የረገጠ ነውጠኝነትና ሰብዓዊ ደህንነት በአፍሪካ

ደረጀ መላኩ ( የሰብዓዊ መብት ተሟጋች )

Tilahungesses@gmail.com


ክፍል አንድ

እንደ መግቢያ

እንደ ስነህዝብ ጠበብት የጥናት ድምዳሜ ከሆነ ወደ 60 ፐርሰንቱ የሚጠጋው የአፍሪካ ህዝብ እድሜው ከ 25 አመት በታች ነው፡፡ ከሌሎች የአለም ክፍሎች ሁሉ በበለጠ የአፍሪካ ወጣቶች በችጋር ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡ የአፍሪካ ወጣቶች ችግር ስር የሰደደና በየጊዜውም እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ የሚሄድ አይደለም፡፡ የስራ እድል የተነፈገ ወጣት ደግሞ ተስፋ የቆረጠ ቢሆን የሚያስገርም አይደለም፡፡ ይሄም ብቻ አይደለም፡፡ ወንጀለኛ የመሆን እድሉ የሰፋ ነው፡፡ ወይም በተደራጁ የወንጀለኛ ቡድኖች ውስጥ ሊታቀፍ ይቻለዋል፡፡ በብዙ የፖለቲካ አጥኚዎች ምልከታ እንደሚታመነው ከሆነ ‹‹ ጽንፍ ለረገጠ ነውጠኝነት ›› የተጋለጠች ትሆናለች፡፡ ከዚህ ባሻግር ግማሽ የሚሆነው የአህጉሪቷ ህዝብ ኑሮ ( ኑሮ ከተባለ ማለቴ ነው) ከድህነት ወለል በታች እንደሆነ፣ አብዛኞቹ ወጣቶች ሥራእጥ መሆናቸው፣ በርካታ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ በተጠቀሱት እና በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ ብዙዎች የአፍሪካ ወጣቶች አክራሪ ድርጅቶች ውስጥ ሊመዘገቡ ይቻላቸዋል፡፡ እንድነ ዶክተር ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ የመሳሰሉ አፍሪካዊ የፖለቲካ ጠበብት በጥናታቸው በደረሱበት ድምዳሜ መሰረት ‹‹ ጽንፍ የረገጠ ነውጠኝነት የሚፈጽሙ ድርጅቶች  አባላት ›› ውስጥ አብዛኞቹ ወጣቶች ናቸው፡፡ እነኚህ ወጣቶች ደግሞ በብዙ  ያህጉሪቱ ክፍሎች ይገኛሉ፡፡

Members of violent  extremist groups are disproportionally young men and they are geographically  dispersed.  ( Extract from the detail research to be found in www.africaisss.org) 

በነገራችን ላይ አክራሪ ቡድኖች አባላቸው ለማድረግ የሚፈልጉት የህብረተሰብ ክፍል በአብዛኛው ወጣቶችን እንደሆነ ማወቁ ተገቢ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ወጣቶችን መመልመል ለእነርሱ ቀላል ስራ ነው፡፡ አባላቶቻቸው በተወሰኑ ሀገራት ብቻ የሚገኙ፣ከተወሰኑ ጎሳዎች፣ ወይም ሀይማኖት ክፍሎች፣ ወይም አህጉራ ክፍል ብቻ የተወጣጡ አይደሉም፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ አክራሪ ቡድኖች ማነቃቂያቸው( የወጣቶችን ልብ ለማሸፈት) ገንዘብ ወይም የሃይማኖት እምነት ዋነኛ መሳሪያቸው ነው፡፡ እንደ የአፍሪካ ፖለቲካ ተንታኞች ጥናታዊ ጽሁፎች ውጤት ከሆነ አክራሪ ቡድኖች ራሳቸውን የሚያደራጁት ፣ በህይወት ሊኖሩ የቻሉት፣ወይም የዶላር ረብጣ የሚያፍሱት በሚከተሉት ምክንያቶች ነው፡፡

  • የአደንዛዥ እጽ በህገወጥ መንገድ በማዘዋወር  (through illicit drug trafficking)
  • የህገወጥ የጦር መሳሪያ በማዘዋወር (arms  trafficking )
  • በህገወጥ መንገድ ሰዎችን ከአንድ ሀገር ወደሌላው አለም በማሸጋገር ( human trafficking )
  • ባንኮችን በመዝረፍ  (bank robberies, )
  • ሰዎችን በማፈን እና በመደበቅ ላመስለቀቅ ገንዘብ መጠየቅ (kidnappings (ransom) )
  • የባህር ላይ ወንብድና በመፈጸም ( አልሻበብ በህንድ ውቅያኖስ ላይ ይፈጽም የነበረውን የባህር ላይ ወንብድና ማስታወስ ተገቢ ነው) ( maritime hijacking )

በነገራችን ላይ የተደራጀ ውንብድና እና ጽንፍ የረገጠ ነውጠኝነት ያላቸውን ልዩነት ለማወቅ አዳጋች ነው፡፡ ወይም በሁለቱ መሃከል ያለው ልዩነት ኢምንት ነው፡፡

አንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 2017 የተባበሩት መንግስታት የልማት ድርጅት በመቶ ለሚቆጠሩ የአልሻባብ እና ቡኩሃራም አባላት ያቀረቡትን ቃለመጠይቅ መሰረት አድርገው በደረሱበት ድምዳሜ መሰረት ወጣቶች ወደ ጽንፍ የረገጠ ነውጠኝነት ባህሪ ለመላበስ የሚጓዙበት ምክንያት፡-

  • መገለል ስለሚደርስባቸው፣ በሀገራቸው ጉዳይ ቀትጠኛ ተሳታፊ ባለመሆናቸው
  • መሰረታዊ ፍላጎታቸው ሳይሟላ ሲቀር
  • በመንግስታት አስከፊ ጭቆና ሲፈጸምባቸው

የተባበሩት የልማት ድርጅት ባደረገው ጥናት መሰረት ፣ ቃለ መጠይቅ ከደረገላቸው ወጣቶች መሃከል 71 ፐርሰንት ግድም የሚሆኑት በሰጡት ምላሽ ወደ አክራሪ ቡድኖች ሄደው የሚቀላቀሉበት ዋነኛ ምክንያት መንግስታቶች በቤተሰቦቻቸው እና በጓደኞቻቸው በሚፈጽሙት ህገወጥ ግድያ፣እስራትና ማሰቃየት ምክንያት ነው፡፡

አንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1994 የተባበሩት መንግስታት ( የተባበሩት መንግስታት የልማት ድርጅት ሪፖርት ( እ.ኤ.አ. 1194) ‹‹ የጸጥታን ›› ጽንሰ ሀሳብ በድጋሚ ተርጎሞታል፡፡ እንደ ብይነ መንግስታቱ ትርጉም ከሆነ ‹‹ ጸጥታ›› ማለት ወይም ጸጥታ የሚያቅፋቸው ‹‹ የሰብዓዊ መብት›› እና ‹‹ ልማትን›› የሚያቅፍ ጽንሰ ሃሳብ ነው፡፡ ሆኖም ግን ባህላዊው  የጸጥታ ትርጉም የሚያጠነጥነው በአካል ላይ ለሚደርሱ ጉዳቶች ብቻ ነበር፡፡ ይህም ማለት በአንድ አካባቢ የአካል ጉዳት ተፈጽሟል ወይም አከላዊ ድህንነት ስለመጠበቁ አለመጠበቁ ማሳያው የጸጥታ መከበር ወይም አለመከበርን ብቻ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የጸጥታ ትርጉሙ ከዚህ ሰፋ ያለ ጽንሰ ሃሳብ ነው፡፡ በአጠቃላይ የሠዎችን ሁለንተናዊ ደህንነት የሚመለከት ነው፡፡ ጸጥታ በንጹህ አካባቢ፣ የተሟላ የኑሮ ደረጃ ላይ ስለመገኘታችን ወዘተ የሚያጠቃልል ነው፡፡ በአጭሩ ‹‹ ጸጥታ›› ጉዳትን ወይም ጉዳት ስላለመድረሱ ከማመላከቱ ባሻግር ወደ ህዝብ ማእከልነት እየተቀየረ የሚገኝ ጽንሰ ሃሳብ ነው፡፡ (the concept of security has moved from  threat-centric to people-centric )

በተባበሩት መንግስታት ሪፖርት እንደተገለጸው ከሆነ ‹‹ የሰው ደህንነት ወይም ጸጥታ ›› ጉዳይ የሀገር ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በቀጥታ ከህዝብ ጋር የሚገናኝ ነው፡፡ ከዚህ ባሻግር የተባበሩት መንግስታት የመጨረሻው ትንታኔ እንደሚያመላክተው የሰዎች ደህንነት ማለት ለሰዎች ደህንነትና ክብር መቆም ማለት ነው፡፡

the final  analysis human security is a concern with human life and dignity.”

በነገራችን ላይ ህዝብን ማእከል ያደረገ የሰው  ደህንነት ከሀገር ደህንነት ጽንሰ ሃሳብ የተለየ ነው፡፡ ወይም ከፖለቲካው ልሂቃን ደህንነት ጽንሰ ሃሳብ የተለየ ነው፡፡ የተራውን ህዝብ ኑሮ የማያሻሽል የኢኮኖሚ እድገት የህዝብን ደህንነት ወይም  ጸጥታ የሚጥስ ወይም አደጋ ላይ የሚጥል ነው፡፡ ከዚህ ባሻግር የመልካም አስተዳደር ችግር መኖሩን ወይም አስከፊ ወንጀል ስለመፈጸሙ ማሳያ ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የአፍሪካን የኢኮኖሚ እድገት በተመለከተ በዚህ ጽሁፍ አውድ ለመዳሰስ ይሞከራል፡፡

በርካታ አፍሪካዊ የፖለቲካ አዋቂዎች በተለያዩ የጥናት ወረቀቶቻቸው ላይ እንዳሰፈሩት ከሆነ፣ የተደራጁ የወንጀለኛ ቡድኖች እና አሸባሪ ቡድኖች፣ በአንዳንድ የአፍሪከ ክፍሎች በሚፈጽሙት የረብሻ እና አሸባሪ ተግባራት ወይም አሳዛኝ ድራማ ምክንያት የአብዛኛው ህዝብ የኑሮ ደረጃ እንዳይሻሻል ደንቃራ ሆነዋል፡፡

የተደራጁ ቡድኖች በሚፈጽሙት ጥቃት ምክንያት የሚከሰቱ ውድቀቶች በአፍሪካ እና በቀሪው የአለም ክፍል ሰላም፣ መረጋጋት፣ የኢኮኖሚ ልማትና በሰላም ተከባብሮ መኖር ላይ ከባድ ጫና እየፈጠረ ይገኛል፡፡

ህገ ወጥ ታጣቂዎችና የተደራጁ ወንጀለኞች ለምን አንደ አሽን ሊፈሉ ቻሉ?

እንደ የፖለቲካ ተንታኞች የጥናት ውጤት ከሆነ በአፍሪካ ምድር ህገወጥ ታጣቂዎችና የተደራጁ ወንጀለኞች እንደ አሽን ሊፈሉ የቻሉት በሚከተሉት ምክንያቶች ነው፡፡

  1. በደካማ መንግስቶችና የህግ የበላይነት አለመኖር 
  2. የሙስና መስፋፋት፣ የተቋማት በአግባቡ አለመስራት ወይም አለመጠናከር
  3. ተጋላጭ የሲቪል ማህበረሰብ መብዛት በተለይ ለተደራጁ ወንጀለኞች ምልመላ ተጋላጭ መሆን
  4. ድህነት፣ የሥራ አጥነት ቁጥረ መብዛት እና ሌሎች የአክራሪነት ባህሪያት ይጠቀሳሉ፡፡
  5. በብዙ የአፍሪካ ሀገራት ተስፋ መቁረጥና መጪው ጊዜ ጨለማ ነው ብሎ ማሰብ
  6. በብዙ የአፍሪካ ሀገሮች ለግጭቶች ዘላቂ እልባት አለማግኘት ( በተለይ ሰሜን አፍሪከ ሊቢያ፣ምእራብ እና መካካለናው አፍሪካ፣ የአፍሪካው ቀንድ አካባቢዎች ለአብነት ይጠቀሳሉ፡፡)

በነገራችን ላይ በአፍሪካ የጸጥታው ጉዳይ አደጋ ላይ ሊወድቅ የሚቻለው፡-

  • የተፈጥሮ ሀብትን ለማጋበስ
  • ኢንዱስትሪውን ለመቆጣጠር
  • በአየር ጸባይ ለውጥ ምክንያትና በመሳሰሉት ምክንያቶች ነው፡፡

በነገራችን ላይ እነኚህ ወንጀለኞችና አሸባሪዎች ደካማ መንግስት ካጋጠማቸው የሀገሪቱን አንድነትን ህልውና አደጋ ላይ ለመጣል አቅም አላቸው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ጠንካራ መንግስት ያላቸው ሀገራት እነኚህን አሸባሪዎችና የተደራጁ ወንጀለኞችን ለመቆጣጠር አቅሙና ችሎታው እንዳላቸው የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ፡፡

እንደ የአፍሪካ ግጭት ጥናት አጥኚዎች ምርምር ውጤት ከሆነ በተለያዩ የአህጉሪቱ ክፍሎች የሚገኙ የተደራጁ ወንጀለኞች በተለያዩ መንገዶች ሊገናኙ ይችላሉ፡፡ ወይም የግንኙነት መስመር አላቸው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ እነኚሁ እኩያን የተደራጁ ወንጀለኞች ገዳይ መሳሪያዎችን የሚያገኙበት መንገድ እጅግ ውስብስብ ነው፡፡ በነገራችን ላይ እነኚህን የተደራጁ ሽብርተኞች ለማጥፋት አንድ ሁነኛ መፍትሔ ለመሻት አስቸጋሪ እንደሆነ የፖለቲካ ጠበብት ይናገራሉ፡፡ ምክንያቱም በአንድ የሽብርተኛ ቡድን አባልነት የሚመዘገቡ ሰዎች አላማቸው የተለያየ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር የሽብር ቡድኑ አባል የሚሆኑበት ምክንያቶች የተለያዩ ናቸው፡፡ ጽንፈኛ የሃይማኖት ቡድን ውስጥ የሚቀላቀሉ ሰዎች የመጨረሻ ግባቸው ሃይማኖታዊ መንግስት ለመመስረት ነው (The real religious  zealots are after state power ) ፣ በተደራጁ የወንጀል ቡድን ውስጥ የሚገቡ ወንጀለኞች ዋና ግባቸው ገንዘብ ለመዝረፍ ሲሆን (the criminal gangs are after money )፣ አክራሪ የጎሳ ድርጅቶች ( በአንድ ጎሳ ስም ተደራጅተው ሌሎች የእኛ ጎሳ አባላት አይደሉም በማለት ግድያ የሚፈጽሙ፣ የጎሳ ማጽዳት እኩይ ድርጊት የሚፈጽሙ ወዘተ ) ዋነኛ ግባቸው የተፈጥሮ ሀብትን በመቆጣጠር ለእኔ ወይም የእኛ ለሚሉት ማህበረሰብን ለመጥቀም ነው ፡፡ (the ethnic lords  are after controlling resources and protecting their turfs, and for many it is  simply the empowerment to do whatever they want with impunity) ምንም አይነት አላማ ይኑራቸው እንዲህ አይነት ሽብርተኛ ቡድኖች ውጤታቸው አውዳሚ ነው፡፡ በተለያዩ የአፍሪካ ክፍሎች በሚፈጽሙት ኢሰብዓዊ ድርጊት የተነሳ አብዛኛዋ አፍሪካ ደምታለች፡፡ አብዛኛው የአፍሪካ ክፍል ነዋሪ እነዲጎሳቆል አድርገዋል፡፡ በአንዳንድ የአፍሪካ ክፍሎች የሚኖሩ አፍሪካዊ ወንድሞቻችን ደግሞ ዛሬም በሰላም እጦት ፍዳቸውን እንዲበሉ ሁነኛውን ሚና ተጫውተዋል፡፡ ( ለአብነት ያህል በናይጄሪያ የቡክሃራም እና በሶማሊያ የአልሻባብ አሸባሪ ቡድኖች በየጊዜው የሚፈጽሙት አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እዚህ ላይ የሚጠቀስ ነው፡፡) 

በአፍሪካ የፖለቲካ ጉዳይ ላይ የተጠበቡ ምሁራን አፍሪካ ከተደቀነባት አደጋ እንድትድን የሚያስችላትን   ምክረሃሳቦች በብዙ የጥናት ወረቀቶቻቸው ላይ አቅርበዋል፡፡ እጠቅሳለሁ፡፡

  • ሁሉንም የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራትን ሊያስማማ የሚችል ሰነድ መፈረም አለበት፡፡ ወይም የግጭትን መሰረታዊ ምክንያቶች ለማምከን፣ህገወጥ የጦር መሳሪያዎችን ለመቆጣጠር፣ ስለ እያንዳንዱ የአፍሪካ ሀገራት ሉአላዊነት ለማስከበር፣ አህጉራዊ ሰላምን ለማስከበር ወዘተ የሚያስችል ስትራቴጂክ ሰነድ መፈራረለም አለባቸው፡፡ (To be able to defend Africa from this looming catastrophe, AU member states  will have to agree on a common strategic doctrine that addresses the root causes  of violence, the proliferation of small and big arms, including weapons of mass  destruction (e.g. bio-terrorism), and giving up some aspects of state sovereignty  in favor of a common regional and international strategy. )

በዛሬው ዘመን አፍሪካ እንደ ቀድሞ ልጆቿ ሁሉ ጠንካራ፣ በራሳቸው የሚተማመኑ፣ህልም ያላቸውና እና የተማሩ መሪዎችን የምትሻበት አንገብጋቢ ግዜ ላይ ትገኛለች፡፡ ማናቸውም የአፍሪካ ሀገር ያለበትን ችግር በራሱ መፍትሔ ማምጣት አይቻለውም፡፡ የአክራሪዎች ወይም ሽብርተኞች ረብሻ ደንበር ወይም ሀገር የለውም፡፡ ሽብርተኝነት  ክፍለ አህጉራዊ፣ አህጉራዊና አለም አቀፋዊ ባህሪ ያለው ሲሆን አንዳንድ መንግስታትንም ሙሰኞች እንዲሆኑ ከማድረጉ ባሻግር ፣ ለውጭ ሀይሎች የፖለቲካ ሴራ ያጋልጣል፡፡ ወይም የሽብርተኞች መናሀሪያ የሆኑ ሀገሮች የሶስተኛ ሀገሮች የፖለቲካና የጦር ሀይል መራኮቻ የመሆን እድላቸው የሰፋ ነው፡፡ 

ሚስተር ላፓኩ ፒር የተባሉ ምሑር በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸረ አደንዛዥ እጽና ወንጀል ክፍል ተመራማሪ ፣ እንዲሁም የምእራብና መካከለኛው አፍሪካ ተወካይ ( Mr. Lapaque Pierre UNODC  (UN Office on Drugs and Crime) አበክረው እንደሚያስገነዝቡት የጽንፈኛ አሸባሪዎችን ረብሻ ለመቀነስ የሲቪል ማህበረሰቡ ሚና የሚናቅ አይደለም፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ አባላት ወይም መሪዎች በመሬት ላይ ያለውን እውነታ ፍንትው አድርገው ያሳያሉ፡፡ የሲቪል ማህበራት የጽንፈኛ አሸባሪዎችን እንቅስቃሴ ለመክላት ወይም እንቅስቃሴያቸው እንዲቀንስ ለማድረግ፣ ሙስናን ለመቀነስ የሚረዱ ፖሊሲዎችን ለማውጣት አቅም አላቸው፡፡ ወይም የየሐገሩ መንግስታት ዲሞክራቲክ ፖሊሲዎችን እንዲያወጡ ለመርዳት ይችላሉ፡፡

አመታዊ ጠቅላላ ገቢ እና የሰው ደህንነት (GDP and Human Security  )

የአንድ ህዝብ መሻሻል አንዱ ማሳያ የሆነው አጠቃላይ አመታዊ ገቢ ብቻውን ከላይ የሰፈረውን የህዝብ ደህንነትን ትርጉም አመላካች ላይሆን ይችላል፡፡ከዚህ ባሻግር አመታዊ አጠቃላይ ገቢ የህዝብ ሀብት መለኪያ መሆን አይቻለውም፡፡ ይህ መለካት የሚቻለው የአንድ ሀገር ገቢ ብቻ ነው፡፡ አመታዊ ጠቅላላ ገቢ የሚነገረን ነገር ቢኖር አንድ ሀገር ትላንት ስላመረተቻቸው የምርት ጥራትና ውጤቶች፣ አገልግሎት ብቻ ነው፡፡ ስለ ነገ አይነገረንም፡፡ የዛች ሀገር ዜጎችም ስላገኙት ጥቅም የሚገልጸው ነገር የለም፡፡

ለአብነት ያህል ናይጄሪያ የአለም የነዳጅ ዋጋ በናረበት  ጊዜ ተፈጥሮ የቸራትን  ድፍድፍ የነዳጅ ሀብቷን ለአለም የነዳጅ ጥማተኞች ሀብታም ሀገራት በመቸብቸብ በብዙ ሚሊዮን  የሚቆጠር ረብጣ ዶላር አፍሳ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ሀብቷ ወድቆ ነበር፡፡ የነዳጅ ሀብቷ ጥቅም ላይ ውሎ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ገንዘቡ የሕዝቡን እውቀትና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ለማጎለብት አልዋለም ነበር፡፡

የአፍሪካ መሰረታዊ የኢኮኖሚ ድቀት ምክንያቱ በዋነኝነት በአፍሪካውያን የገቢ ምንጭ ልዩነት በእጅጉ የመጨመሩ ጉዳይ ነው፡፡ ( በደሃውና ሀብታም ተብዬው ዘራፊ ክፍል ያለው የገቢ ልዩነት የትዬየሌሌ መሆኑ ነው) በነገራችን ላይ በቀሪው አለም፣ በአለም ደረጃ ማለቴ ነው በህዝቦች መሃከል ያለው የገቢ ልዩነት እየቀነሰ ስለመሆኑ የኢኮኖሚ ጠበብቶች በጥናት ወረቀቶቻቸው ላይ ያሰፈሩት ጉዳይ ነው፡፡ በነገራችን ላይ በአፍሪካ የሚታየው የገቢ ልዩነት በማናቸውም መለኪያ የተረጋገጠ መሪር ሀቅ ነው ተብሎ ሲነገር እንደው ወሬ ለማሳመር ወይም ለላንቲካ አይደለም ፡፡ በብዙ የአፍሪካ ሀገራት፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ በስልጣን ኮርቻ ላይ የተፈናጠጡ እና ሸሪኮቻቸው ባለወረቶች የሀብት መጠን ከግዜ ወደ ግዜ እየጨመረ ሲሄድ የብዙሃኑ አፍሪካዊ ምጣኔ ሀብት እድገት እያሽቆለቆለ የሚገኝ ስለመሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡( በብዙ የአፍሪካ ሀገራት ስልጣን የሐብት ምንጭ ነው፡፡) በብዙ የአፍሪካ ሀገራት ዋና ከተማዎች ቀን የጨለመባቸውን ዜጎች ማየት ብርቅ አይደለም፡፡ ለዚህ እንደ ጥሩ አብነት የምትጠቀሰው ናይጄሪያ ናት፡፡ እንደ አፍሪካዊ የምጣኔ ሀብት ጥናት ውጤት ከሆነ 80 ፐርሰንቱ ናይጄሪያዊ በድህነት ፍዳውን የሚቆጥር ሲሆን፣ ጥቂቶች የናይጄሪያ ቱጃሮች በሀብት ላይ ሀብት እየጨመሩ ይገኛሉ፡፡

“A prime example is Nigeria where the incomes of the poorest  80 percent of the citizenry have declined, while the incomes of the richest have  increased

ምንም እንኳን መላውን አለም ባስደነቀ ሁኔታ ባለፉት ሃያ አመታት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት 10.5 ነው ተብሎ በብዙ መልኩ ቡዘፈንለትም ወይም ቢደሰኮርም አብዝሃው የኢትዮጵያ ህዝብ አላለፈለትም ወይም የኢኮኖሚ እድገቱ የከሳ ስለመሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ እንደ የተባበሩት መንግስታት የህዝብ እድገት ጥናት ውጤት ከሆነ ኢትዮጵያ በአለም ውስጥ በከፋ የድህነት ማጥ ውስጥ ከሚዳክሩ ሃገራት አንዷና ዋነኛዋ ናት፡፡ ኢትዮጵያ ከ189 ሀገራ ውስጥ የድህነት ደረጃዋ 173ኛ ነው፡፡ ( እንደ እድገት ከተቆጠረ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ እድገት 16 ሀገራትን ብቻ ነው የምትቀድመው ) ይህ በእንዲህ እንዳለ አብዛኞቹ ደሃ ሀገራት የሚገኙት ከሰሃራ በስተደቡብ የሚገኙ ሀገራት ናቸው፡፡

Despite the much acclaimed economic growth rate of Ethiopia over the last 20  years averaging 10.5%, which could be an economic miracle in the world,  according to the Human Development Index (HDI) prepared by the United  Nations itself, Ethiopia is actually one of the poorest countries in the world number 173 out of 189.  Most of the others are in Sub-Saharan Africa. (“2019  Human Development”) 

ከዚህ ባሻግር ኦክስፎርድ መልቲዳይሜንሽናል ጥናት መሰረት (The Oxford Multidimensional Poverty  Index ) የኢትዮጵያ የችጋር ሁኔታ ለከቱን ያጣ ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ በኢትዮጵያ በገሃድ የሚታየው ድህነት ገጽ መጠነ ሰፊ ነው፡፡ ወይም ባለሙሉ መልክ ገጽታ ይታይበታል፡፡ በእንግሊዝኛ የተጻፈው የበለጠ ገላጭ ነው፡፡ ለማስረጃም ስለሚጠቅም እንደወረደ ላቅርበው፡፡

The Oxford Multidimensional Poverty  Index measured by  the proportion of  the  population  that  is  multidimensional poor  and  the  average  intensity  of  their  deprivation, ranks Ethiopia as one of those often viewed as emblematic of poverty  with  a  very  high  index  of  0.489  in  2020.  This  is  calculated  from both  the  percentage  of  people in  poverty  (83.5%)  and  the intensity  of  their  deprivation  (61.5% live in severe poverty). (“Global MPI Country Briefing 2020”). 

 እንደ የአለም ዳታ ቤተሙከራ ጥናት ውጤት (World Data Lab  ) ከሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ አፍሪካ ከፍተኛውን የድህነት ቀንበር ተሸካሚ ናት፡፡ ለአብነት ያህል የአፍሪካ ኢኮኖሚ ሞተር ተብላ በምትንቆለጳጰሰው ናይጄሪያ እና የአለም የተፈጥሮ ሀብት ጥማተኞች በሚርመሰመሱባት የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ 150 ሚሊዮን ሰዎች በከፋ የድህነት አዙሪት ውስጥ ይዳክራሉ፡፡

እንደ የአለም ዳታ ቤተሙከራ የጥናት ውጤት ከሆነ አፍሪካ በአለም ላይ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ያስመዘገበች ሀገር ናት፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና 80 ፐርሰንት የሚደርሱት የአፍሪካ ሀገራት  እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 2030 ድረስ ከድህነት አዙሪት ውስጥ መውጣት አይቻለውም፡፡

ዶንፌልድ የተሰኙ ተጠባቢ የአፍሪካን የችጋር መጠን 90 ፐርስንት ያወጡታል፡፡( 90 ፐርሰንቱ አፍሪካዊ በችግር ውስጥ ይገኛል) በዚህ ምክንያት አፍሪካን ከድህነት ለማውጣት የታለመው የ 2030 ( እ.ኤ.አ. ) በየትኛወም መስፈርት ግቡን ሊመታ አይቻለውም፡፡ የዶንፊልድን ጥናታዊ ትንቢት እንደሚከተለው  ሰፍሯል፡፡

“When weighted for  absolute number of people living in poverty, that figure increases to more than 90%.” (Donnenfeld). It has already proved to be an impossible goal under any  circumstances.  

በአፍሪካ የድህነት መጨመር መግፍኤ ምክንያቶች በወፍ በረር ሲቃኙ

በእኔ እይታ በአፍሪካ የድህነት መጨመር ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው ብዬ አሰባለሁ

 

  • የአፍሪካ ፈጣን የሕዝብ ቁጥር እድገት ወይም በፍጥነት መጨመር
  • በጣም አደገኛው ምክንያት የጸጥታ መደፍረስ ነው፡፡ ( አፍሪካ የግጭቶች መፈልፈያ አህጉር እንደሆነች የፖለቲካተንታኞች ይከራከራሉ)
  • በግጭቶች መስፋፋት ምክንያት በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ከሚያገኙት አጠቃላይ አመታዊ ገቢ ውስጥ ከሰው ደህንነት ይልቅ ለመንግስታቸው ደህንነት መጠበቅ ሲሉ ከፍተኛ በጀት በመመደባቸው
  • በብዙ የአፍሪካ ሀገራት ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ምሉሄበክሉሄ በሆነ ሁኔታ ገቢራዊ ባለመደረጉ
  • በብዙ የአፍሪካ ሀገራት የሚገኙ የመንግስት ባለስልጣናት በሙስና እጃቸው የተጨማለቀ በመሆኑ
  • የህዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋማት መዋቅር ወይም አወቃቀር ደካማ መሆን
  • በአንዳንድ የተወሰኑ የአፍሪካ ሀገራት ጠረፋማ ክልሎች ከመንግስት ታጣቂዎች ባሻግር በጎሳ 
  • አለቆች ወይም በተደራጁ ወንበዴዎች መርስመስ ሌላው የድህነት ምክንያቶች ናቸው፡፡ የተደራጁ

 

 ወንበዴዎች ባሉበት አካባቢ የሚኖሩ ገበሬዎች ወይም አርብቶ አደሮች በጸጥታ ምክንያት እለታዊ ስራቸውን በአግባቡ መከወን አይችሉም፡፡ የሀገሬው መንግስት መሰረታዊ የልማት ተግባሮችን በአግባቡ መከወን አይቻለውም፡፡

 

  • በአንዳንድ የአፍሪካ ክፍሎች ሰዎች በማንነታቸው ምክንያት ይገደላሉ፣ ንብረታቸው ይዘረፋል፡፡ ለዘመናት ከኖሩበት መንደር ይፈናቀላሉ፡፡ የዚህ መጨረሻው ደግሞ ድህነትን ያባብሳል፡፡
  • ጽንፈኛ እረባሾች የሆኑ ወንበዴዎች በአንዳንድ የአፍሪካ ክፍሎች አዛዥ እና ናዛዥ ለመሆን በመብቃታቸው የምርት እድገትን በእጅጉ አቀጭጨውታል
  •  ጽንፈኛ የተደራጁ ወንበዴዎች በብዙ የአፍሪካ ክፍሎች እንደ ሰደድ እሳት በመስፋፋታቸው አፍሪካ ከችጋር እንዳትገላለገል ዋነኛ እንቅፋቶች ከሆኑ ሰነበቱ

 

የግል ማስታወሻ፡- መቀመጫቸውን ጀርመን ያደረጉት ዶክተር በፍቃዱ በቀለ በምርምራቸው እንደደረሱበት ከሆነ እንደጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር በ2015 እና 2030 ባሉት አመታት ውሰጥ የአፍሪካን የድህነት መጠን በ 5 ፐርሰንት ለመቀነስ የታቀደ ቢሆንም ተቃራኒው መራር እውነት ነበር እውን የሆነው፡፡ በተጠቀሱት አመታት በአፍሪካ ምድር የድህነት መጠኑ ወይም ስፋት ቀደም ባሉት አመታት ከበነረው በእጥፍ ጨምሯል፡፡

ለአብነት ያህል እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ከ2015   በፊት 270 ሚሊዮን ግድም የነበረው የረሃብተኛው አፍሪካዊ ቁጥር ወደ 550 ሚሊዮን አብጦ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ ይህ የችጋር እብጠት ከኮቪዲ 19 በሽታ እና የጽንፈኞች እረብሻ ተጽኖ ውጪ መሆኑን አንባቢው ልብ ሊለው ይገባል፡፡ የሁለቱ ቸግሮች ሲጨመሩበት የረሃብተኛው አፍሪካዊ ቁጥር መጨመሩ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ለማናቸውም ዶነንፊልድ የተባለ ምሁር በጥናቱ ላይ ያቀረበውን እጠቅሳለሁ

swelling from around 270 million in 2015 to more than 550 million in 2030”  (Donnenfeld).   And these projections do not even consider the spreading violent  extremism nor the impact of Coved 19,  in 2020.  

እውን በአፍሪካ ምድር የሰው ደህንነት በመልካም ሁኔታ ይገኝ ይሆን ? ወይንስ አደጋ ላይ ወድቆ ይሆን ? እስቲ በየሰፈራችሁ ተወያዩበት፡፡ በእኔ በኩል በሰው ደህንነት ላይ ቀጥተኛ ተጽኖ የሚፈጥሩትን ላስቀድም፡፡

የሰው ደህንነት ላይ ቀጥተኛ ተጽኖ የሚፈጥሩ አንዳንድ ጉዳዮች

  • ድህነት
  • የህዝብ ፍልሰት ( መፈናቀል)
  • ረሃብ
  • በሽታ
  • የአካባቢ ብክለት
  • ህዝብን ባይተዋር ማድረግ

በነገራችን ላይ ህዘብ የእለት ኑሮውን መምራት የሚቻለው ሰውን ማእከል ባደረገ መልኩ መሆኑን ማወቅ ተገቢ ነው፡፡ ሰዎች የተረጋጋ ህይወት መምራት የሚቻለው ተስፋ መሰነቅ ሲችል፣ ነገ ብሩህ ቀን ነው ብሎ ሲያምን፣ በሰላም የመኖር ፍላጎት ሲኖራቸው፣ በሀገራቸው ምድር ነጻነት ሲጎናጸፉ፣ ክብራቸው ሳይደፈር ሲቀር ወዘተ ወዘተ እንደሆነ መታወቅ አለበት፡፡

ሆኖም ግን ይሁንና በአብዛኛው የአፍሪካ ምድር የተረጋጋ ህይወት ለመምራት የሚያስችሉ የተጠቀሱት ቁምነገሮች አልተሟሉም፡፡ አፍሪካ በራሷ ችግር የተተበተበች ናት፡፡ በአፍሪካ የተለያዩ ክፍሎች የሚከሰቱ ግጭቶች የድህነት መግፍኤ ምክንያቶች ናቸው ተብሎ ሊጻፍ ይችላል፣ ሆኖም ግን የአፍሪካ ሀገሮች በተፈጥሮ ሀብት የታደሉ ሆነው ሳለ ለምን በድህነት ይጠቃሉ ብሎ መጠየቅ የሰውነት ባህሪ ነው፡፡ አፍሪካውያን ለፍትህ መስፈን፣ ለእኩልነት፣ ለነጻነት የሚታገሉ ከሆነ የአፍሪካ ሀገራት በመጥፎ አገዛዞች ለምን ይሰቃያሉ ብለው መጠየቅ ያለባቸው ይመስለኛል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በአፍሪካ ምድር የሚኖሩ አንዳንድ አፍሪካውያን በሃይማኖት እና ጎሳ ልዩነት ምክንያት በየጊዜው የሚቆራቆሱ ከሆነ ራሳቸውን የሚከተለውን መሰረታዊ ጥያቄ መጠየቅ ያለባቸው ይመስለኛል፡፡ ‹‹ እንዴት ከ2000 በላይ የሚገመቱ የአፍሪካ ጎሳ አባላት ከቅኝ አገዛዝ በፊትና በኋላ እንዴት በሰላም እና በፍቅር መንፈስ ሊኖሩ ቻሉ? ብለው ራሳቸውን መጠየቅ አለባቸው፡፡

በነገራችን ላይ በአፍሪካ ምድር የግጭቶች መበራከት መግፍኤ ምክንያቶች ለምን በዙ ብሎ መጠየቅ አግባብነት ያለው ይመስለኛል፡፡ ለዚህ መልሱ አፍሪካን ለሁለተኛ ግዜ ለመቀራመት የተደረገውን ሴራ አስመልክቶ የቀድሞው ታንዛኒያ መሪ ጁሊዬስ ኒሬሬ (Julius  Nyerere of Tanzania predicted )ጊዜ የማይሽረው ንግግር ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ የሙዋሊሙን ( መምህር) ንግግር በአጭሩ እጠቅሳለሁ፡፡ ኒሬሬ እንደተነበዩት ከሆነ ድህነት፣ስደት፣ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች፣የርበርስ ጦርነትና አንዱ ሀገር ሌላውን በሰርጎ ገቦች ማጥቃት ወዘተ ወዘተ በአፍሪካ የፖለቲካ ውድቀትና የአካባቢ አለመረጋጋት ምክንያቶች ናቸው፡፡ እነኚህን መሰረታዊ የአፍሪካ ችግሮች ለመቅረፍ በዋነኛነት በአፍሪካ መሪዎች እና ምሁራኖች ትከሻ ላይ የወደቀ ነው ሲሉ ነበር ትንቢት መሰል ንግግራቸውን ያሰሙት፡፡

አብዛኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰላም አስከባሪ ሀይል፣ ከፍተኛ ወጪ የሚወጣበት የሰላም አስከባሪ ሀይል በአፍሪካ ያለው ተልእኮ እንዴት ሊገለጽ ይቻለዋል መልሱን ህሊና ለፈጠረባችሁ ትቼዋለሁ፡፡ በእኔ አስተያየት ከአለም ክፍሎች ሁሉ የተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ ወጪ በመመደብ በአፍሪካ የሰላም ማስከበር ተልእኮ ላይ መሰማራት ከጀመረ አመታት ተቆጥረዋል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ለድርጅቱ የሰላም ማስከበር ተልእኮ ከፍተኛ የገንዘብ ባጀት ትመድብ የነበረው የተባበረችው አሜሪካ አመታዊ መዋጮ መቀነሷን ከአለም መገናኛ ብዙሃን የተሰማ ጉዳይ ነው፡፡ ግራም ነፈስ ቀኝ በተጠቀሰው ምክንያት የተነሳ ለአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት የሚያንቂያ ደውል ይመስለኛል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም የአፍሪካ ህብረት ለአፍሪካ ሰላም ማስከበር ጉዳይ በብርቱ፣ አህጉራዊ መፍትሔ ለማግኘት ይገባል የሚለውን መልእክቴን ሳቀርብ በአክብሮት ነው፡፡

ማስታወሻ፡- በጥናት ወረቀቶች ላይ እንደተጠቀሰው ከሆነ የተባበሩት አሜሪካ ለተባበሩት መንግስታት የጸጥታ ጥበቃ ከፍተኛውን ገንዘብ የምታዋጣ ሀገር ናት፡፡ የአሜሪካ ኮንግረስም ያጸደቀውን ዶላር በታሰበለት ጥቅም ላይ ስለመዋሉ ቁጥጥር ያደርጋል፡፡ የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባል የሆነችው የተባበረችው አሜሪካ የተባበሩት መንግስታት የሰላም ማስከበር ተልእኮ ላይ ጉልህ ሚና እንዳላት የሚያከራክር አይመስለኝም፡፡ ለአብነት ያህል እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 2020 የተባበረችው አሜሪካ ድርሻ ለተባበሩት መንግስታት የሰላም ማስከበር ተልእኮ የአለም መንግስታት ካወጡት ገንዘብ ውስጥ 27.89 ፐርሰንቱን ይሸፍናል፡፡ የፕሬዜዴንት ትራምፕ መንግስት በመጪው 2021 ( እ.ኤ.አ.) ለተባበሩት መንግስታት የሰላም ማስከበር ስራ ( በአፍሪካ ምድር ማለቴ ነው) 1.07 ቢሊዮን ዶላር በጀት እንደመደበ ከአለም መገናኛ ብዙሃን ተሰምቷል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና  ይህ ሁሉ ከፍተኛ በጀት ተመድቦ በብዙ የአፍሪካ ክፍሎች ሰላም ማስፈን አልተቻለም፡፡ በተቃራኒው በብዙ የአፍሪካ ክፍሎች የዋይታና ሰቆቃ ድምጾች ይሰማሉ፡፡

For  FY2021, the Trump Administration proposed $1.07 billion for U.N. peacekeeping,  a 29% decrease from the enacted FY2020 level of $1.52 billion (“United Nations  Issues”). But peace has not come yet despite these efforts. There are several  major trouble spots. 

የአፍሪካው ቀንድ በተለይም ደቡብ ሱዳን እንደማሳያ

እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ታህሳስ 2013 ( የርበርስ ጦርነት ከተጀመረ በኋላ ማለቴ ነው) የደቡብ ሱዳን የወደቀች ሀገር ስለመሆኗ በብዙ አፍሪካዊ የፖለቲካ ሃያስያን ዘንድ በሰፊው የተሄሰበት ጉዳይ ነው፡፡ ከ 50,000 በላይ ዜጎች አልቀዋል፡፡ አንዳንዶች ይህን የሟቾች ቁጥር ወደ 383,000 ግድም ደርሱታል፡፡ ይሕ በእንዲህ እንዳለ ወደ 4 ሚሊዮን የሚገመቱ ተፈናቃይ የዛች ሀገር ዜጎች በደቡብ ሱዳን ግዛት እና በጎረቤት ሀገራት ተጠልለው ይገኛሉ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ አንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 2018 የሀገሪቱ ፕሬዜዴንት ሳልቫኪርና የተቃዋሚ መሪ በሆኑት ሚስተር ራይክ ማሻር ግጭቶችን አስቁመው የሰላም ስምምነት እንዲፈራረሙ የአለም አቀፉ ህብረተሰብ ተጽእኖ ማሳደሩን፣ በተለይም የተባበረችው አሜሪካ ማእቀብ መጣሏን፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጦር መሳሪያ ማእቀብ መጣሉን፣ የሰላም አስከባሪ ጦር ወደ ደቡብ ሱዳን ግዛት ለመላክ መወሰኑን እናስታውሳለን፡፡ 

በሱዳን ( ሰሜን ሱዳን ) የደራርፉር ጉዳይ አሁን ድረስ መፍትሔ አልተገኘለትም፡፡ አንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ሰኔ 2020 የጸጥታው ምክር ቤት ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት ከአፍሪካ ህብረት እና ከመንግስታቱ ማህበር የተወጣጣ የሰላም አስከባሪ ሀይል ( ይህ የሰላም አስከባሪ ሀይል በእንግሊዝኛ ቋንቋ መጠሪያው  the African Union-United Nations Hybrid  Operation in Darfur (UNAMID) ተብሎ ይታወቃል፡፡)  በሱዳን ዳርፉር ግዛት እንዲሰፍር መደረጉን ከአለሙ መንግስታት የዜና አውታር ተሰምቷል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የደቡብ ሱዳን የሰላም ሁኔታ ዛሬም አስተማማኝ አይደለም፡፡ ሶማሊያ ዛሬም በሰላም እጦት ፍዳዋን የምትቆጥር በአፍሪካው ቀንድ የምትገኝ ሀገር ናት፡፡ (Somalia is still in turmoil ) በዚህ ምክንያት የጸጥታው ምክር ቤት የአፍሪካ ህብረት በዛች ሀገር ላይ ሰላም የማስከበር ተልእኮውን በተመለከተ እውቅና ሰጥቶታል፡፡ በሶማሊያ የምርጫ ውድድር እውን እንዲሆን የአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ሀይል መስፈሩን የምናስታውስ ይመስለኛል፡፡

መካከለኛው የአፍሪካ ክፍል

በዚህ የአፍሪካ ክፍል በተለይም የመካከለኛው የአፍሪካ ሪፐብሊክ ተብላ በምትታወቅ ሀገር እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 2013 ጀምሮ የፕሬዜዴንት ቦዚዚ መንግስት ከስልጣናቸው አሽቀንጥሮ ለመጣል በሚል ምክንያት ሀገሪቱ በርስበርስ ጦርነት ውስጥ ተዘፍቃለች፡፡ ዛሬም ይህቺ በተፈጥሮ የታደለች ሀገር ሰላሟን ማግኘት አልተቻላትም፡፡ በሀገሪቱ ሰላም ለማስከበር በሚል ምክንያት ከ13,000 በላይ የመንግስታቱ ማህበር የላካቸው ወታደሮች ሰፍረው ይገኛሉ፡፡ ( ይህ የመንግስታቱ ሰላም አስከባሪ ሀይል የእንግሊዝኛ ምጽሐረ ቃል መጠሪያ (“MINUSCA”)  በመባል ይታወቃል፡፡

እንደ የአለም ሰላም አስከባሪ ተቋም ገለጻ ከሆነ የተባበሩት መንግስታት በአፍሪካ ምድር ሰባት (7) የሰላም ማስከበር ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡ የአፍሪካ ህብረት በበኩሉ ወደ አምስት (5) ግድም የሚጠጉ የሰላም ማስከበር ስራ ላይ ተሰማርቷል፡፡ የአፍሪካ ህብረት ያሰማራው የሰላም አስከባሪ ሀይል በአለም ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰላም አስከባሪ ሀይል ማሰማራቱን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

በነገራችን ላይ የአፍሪካ ህብረትና የመንግስታቱ ማህበር የሰላም አስከባሪ አባላት በብዙ የአፍሪካ ሀገራት መሰማራት የሚያሳየን ፣ በአፍሪካ ምድር የፖለቲካ ውድቀትና የሰላም አለመኖርን ነው፡፡ በብዙ የአፍሪካ ሀገራት በሰላም ማስከበር ስራ ላይ የተሰማራው የመንግስታቱ ማህበር የሰላም አስከባሪ ሀይል መሰረታዊ በሆነ መልኩ ሰላም ማስከበር አልተቻለውም፡፡ በሌላ አነጋገር ግጭቶች ሙሉሄበክሉሄ በሆነ ሁኔታ መቅረፍ አልተቻለውም፡፡ የብይነ መንግስታቱ ጦር ሰላም ለማስከበር የተሰጠው የግዜ ሰሌዳ ሊጠናቀቅ ጥቂት ቀናት ሲቀሩት ተጨማሪ አመታት የሰላም ማስከበር ወራቶች ወይም አመታት ይጨመርልኝ ብሎ ጥያቄ ከማቅረብ ውጪ በአንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት የተከሰተውን ግጭት በመሰረታዊ መልኩ ማሰወገድ አልተቻለውም፡፡ ለአብነት ያህል በዲሞክራቲክ ኮንጎ ሪፐብሊክ ያለውን መራር እውነት ማየት ይቻላል፡፡ እንደ አንዳንድ አፍሪካዊ ምሁራን የጥናት ውጤት ከሆነ የተባበሩት መንግስታት የሰላም አስከባሪ ሀይል በተሰማራባቸው በብዙ የአፍሪካ ሀገራት ምሉሄበኩልሄ በሆነ ሁኔታ ሰላም ማስፈን የተሳነው ተልእኮው የተወሰነ በመሆኑ ነው፡፡ ይህም ማለት ግን የተባበሩት መንግስታትም ሆነ የአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ሀይላት በአፍሪካ ሀገራት ለሰላም እውን መሆን ምንም ፋይዳ አላመጡም ማለት እንዳልሆነ አንባቢውን ሳስታውስ በአክብሮት ነው፡፡

ሌሎች በበርካታ የአፍሪካ ሀገራት ደግሞ የውስጥ ችግሮች ወይም ግጭቶች ሞልተው ተርፈዋል፡፡ አንዳንዶች የውስጥ ጉዳይ ነው በማለት የመንግስታቱ ማህበር ጣልቃ እንዲገባ የሚፈቅዱ አይደሉም፡፡ ለአብነት ያህል በሰሜን ናይጄሪያ የቡክሃራም ነውጠኛ ቡድን የሰላምና የጸጥታ ችግር የደቀነ ስለመሆኑ የሚያሳዩ ዜናዎች በአለም መገናኛ ብዙሃን በሰፊው የሚነገር ነው፡፡ በሰሜናዊት ኢትዮጵያ ወንጀለኞችን ለማደን የተከፈተው ጦርነት፣ በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ በየጊዜው የሚከሰተው ግጭት መሰረታዊ በሆነ መልኩ እልባት ካልተገኘለት ፣በመተክል ዞን ሰላምን የሚያደፈርሱ ታጣቂዎች፣ ንጹሃንን በአስከፊ ሁኔታ የሚያሰቃዩ፣ የንጹሃንን ኢትዮጵያዊ ዜጎች ህይወት የሚቀጥፉ ብረት አንጋቾችን መቆጣጠር ካልተቻለ  አደጋው የከፋ ሊሆን እንደሚችል በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች የሄዱበት ጉዳይ ስለመሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ በእኔ እይታ በኢትዮጵያ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚታየውን ግጭት በዋነኝነት የኢትዮጵያ መንግስት፣ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በመተባበር ያስቆመዋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ይህን ጽሁፍ ለማዘጋጀት የሚከተሉትን ዋቢ ጽሁፎች ተጠቅሜአለሁ፡-

  1. የዶክተር ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስን ጥናታዊ ጽሁፍ
  2. Extract from the detail research to be found in www.africaisss.org)   

ክፍል ሁለት ይቀጥላል

Filed in: Amharic