>
6:44 pm - Monday May 29, 2023

"እኛ አንዲት ጠጠር ሳንጥል መታገላችንን እንቀጥላለን፣ ደግሞም እናሸንፋለን" እስክንድር ነጋ

አድናቂ እንጂ ጠያቂ የሌለው እስክንድር በቃሊቲ – ዋይታ…!!!
ጋዜጠኛ ካሳሁን ይልማ
እስክንድርን ለማየት አባቴን የማግኘት ያህል ጓጉቻለሁ።ለጋዜጠኛውም ልባዊ አክብሮቴ የመነጨው ከነበረው የትግል ጽናት ነበር። ዝምድና የለኝ፣የልጅነት ጓደኛዬ አይደል፣የሠፈሬ ሰው አይደል…እስክንድር ወያኔ ከምረጫ 97 በኋላ ዳግም በሐሰት የሽብር ክስ ወንጅሎ  ከቀፈደደው ሐምሌ 6,2004ዓም በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የካቲት 7,2010ዓም በፈረንጆቹ የፍቅረኞች ቀን (Feb 14,2018) የነፃነት አየርን በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ተነፈሰ፣ ከቃሊቲ ተፈቶ ወደቤቱ ሲጓዝ ከነበረበት መኪና በመስኮት ብቅ ብሎ ድል ለዴሞክራሲ እያለ ጥማቱን ለሚወደውም ለሚጠላውም ሕዝብ አስታወቀ።
ያ እስክንድር ወደ አሜሪካ ዋና መዲና ዲሲ ውድ ባለቤቱን ሠርኬና ልጁን ናፍቆትን ሊያገኝ ግንቦት 10 2010 ቀን ሲመጣ ለሀገር ለከፈለው ዋጋ ቢያንስ-ቢያንስ አክብሮቴን መግለጽ አለብኝ ብዬ እጅግ በጣም ባልተመቻቸ ሁኔታ ከቴክሳስ የ3:45ሰዓት በረራ ጉዞ አድርጌ ዝግጅቱ ያመልጠኝ ይሆን ብዬ ተጨንቄ ከ9 ሰዓታት በላይ ፈጅቶብኝ ለአቀባበሉ ደርሻለሁ።
እስክንድርን በአካል አግኝቼው ከማርቲን ሉተር ኪንግ መታሠቢያ ሐውልት ስር ፎቶ ስንነሳ በጥቂቱ በአረመኔዎቹ ህወሓቶች ከመታሰሩ በፊት 22 ማዞርያ ገብርዔል ሆስፒታል አካባቢ የነበረው የአዲስ ነገር ጋዜጣ ቢሮ የተገናኘንበትን ዕለት አንስተናል።
ከዚያ አጭር ቃለምልልስ ሳደርግለት የነበረው ምላሽ ግን ትንሽ በግርምት ቅንድቤን ከፍ፣ ግንባሬን ጨምደድ እንዳደርግ አስገድዶኛል። “ዳግም እስር የሕይወትም መስዋዕትነት ሊሆን ይችላል:: 2 እግሬን በሰላማዊ ትግል ላይ ተክዬ ሀገራችን ዴሞክራሲያዊ እስከምትሆን ድረስ እታገላለሁ::መንገድ ላይ ልወድቅ እችላለሁ፣ ላላየው ችላለሁ” ሲለኝ ማመን አቅቶኛል። ያለምንም ወንጀል ሚስቱ ታስራ፣ ልጁ እስርቤት ተወልዶ…እሱ ድጋሚ ታስሮ ከ7 ዓመታት በኋላ ሲፈታም ዳግም መስዋዕትነት ለመክፈል መዝጋጀት… ያስደነግጣል።
እሱ ይበለው እንጂ እኔ እንኳ እስክንድርን ዳግም የሚያስር መንግሥት ይመጣል ብዬ አላሰብኩም። “አስረን አናጣራም፣ሳናጣራ አናስርም” የሚለውን የመሪውን ቃል ይዣለኋ። ከሁለት ወራት በኋላ ከስደት ኑሮ ለመጀመርያ ጊዜ ከታማኝ ጋ ወደ ኢትዮጵያ ስሄድ እስኬውን አገኘሁት። መሐል አራት ኪሎ ቢሮ ከፍቷል፣ ኢትዮጲስ ጋዜጣ መታተም ጀምራለች…ደስ ይላል። ኧረ እንዲያውም ስለ ሕትመት ሚድያ ፈተና ፕሮግራም ሁሉ ሰራሁ። በአራት ኪሎ ጎዳና ዞር-ዞር አልን። አብረን ምሳ በላን፣ ቡና ጠጣን።
ዛሬ እስክንድር በአጠቃላይ ከ9ዓመታት በላይ ተመላልሶ በታሰረበት ቃሊቲ ታስሯል። ሳይጣራ ታስሯል፣ ከበፊቶቹ እስሮች ያለው ልዩነት አንድ ብቻ ነው፣ የበፊቱ እስክንድር ጋዜጠኛና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ነበር። የአሁኑ እስክንድር ፖለቲከኛ ነው።በተረፈ የእስክንድርን ሠላማዊ የትግል መርሆ ከአቋሙ የሚዛነፍ አይደለም።
የዋይታ ጉዞ
ቃሊቲ በር ላይ ተሰልፊያለሁ፣ ደስ ብሎኛል። ሁለት ቀን እዚህ ቦታ ተገኝቼ ሳይሳካልኝ ተበሳጭቼ ተመልሻለሁ። ዛሬ ግን ሊሳካልኝ ነው። እዚህ ቦታ ከቆመኩ ረጅም ዓመታት ተቆጥረዋል፣ ከምርጫ 97 በኋላ ንፁሐን የአዲሳባ ልጆች ከተገደሉና በበቀል በዝዋይ፣በሽዋ ሮቢት፣ጦላይና ደዴሳ ታጉረው ስቃይ በተፈጸመባቸው ጊዜ የቅንጅት መሪዎችም ቃሊቲ ታፍነው ነበር።ያን ጊዜ እነሱን ልጠይቅ ከሄድኩ በኋላ ይኼኛው ሁለተኛዬ መሆኑ ነው።የአሁኑ እንደበፊቱ ከጓሮ ሳይሆን በፊትለፊት በር ሆኗል።
ዓርብ ቀን ስለሆነ ሰልፉ ብዙ አልነበረም። ሕፃናት የያዙ ጠያቂዎች አያለሁ፣ አጠገቤ ጠየም ያለች ሴት ተሰልፋለች። ትንሽ ከርሷ ጋር ማውራት ጀመርሁ። እድሜዋ ወድ 12 የምትሆን ልጅ አብራት አለች። “ቤተሰብ ታስሮባችሁ ነው?” አልኳት ዐይኗ ክርትት የሚለውን ድንቡሽቡሽ ልጇን እያየሁ። “አዎ ባለቤቴ ታስሮ ነው” አለችኝ። “የፖለቲካ እስረኛ ነው? ብዬ ሌላ ጥያቄ አስከተልኩ። “አዎ” ብላ ከታሰሩት የባልደራስ አመራሮች አንዱ የሆነው ስንታየሁ ቸኮል ባለቤት መሆኗን ነገረችኝ።
እኔም እነሱን ልጠይቅ እንደመጣሁና የትኛው የእስረኛ ዞን እንዳሉ እንደማላውቅ ስነግራት ዋይታ የሚባል ዞን ውስጥ አንድ ላይ እንደሆኑ ስትነግረኝ ተራችን ሲደርስ የተሸከመችውን ከበድ ያለ ዘንቢል አግዥያት ወደውስጥ አብረን ገባን። እየገባን ዝቅ ባለ ድምፅ ልጅሽ ምን ይሰማታል፣ ሁኔታውን በደንብ ትረዳለች ወይ አልኳት በዝርዝር ባትረዳም ሳድግ ያሰሩትን ሰዎች እስራቸዋለሁ ትላለች ብላ መለስችልኝ።
የኮሮና ጭምብላችንን ገፈፍ እያደረግን መታወቂያ አሳየን፣ ስማችን ተመዘገበ፣ የምንጠይቀውን ሰውና ዞን አስሞልተን፣ ተፈትሸን፣ የያዝነውን ምግብ አስቀምሰውን አንድ መለስተኛ ጭርንቁስ ሠፈር በሚመስለው ቃሊቲ እስር ግቢ ውስጥ ለ5 ደቂቃ ተጉዘን ደረስን። ውስጡ የተላየዩ ቅጥር ግቢዎች አሉት። እነእስኬው ያሉበት ዋይታ ግቢ ስንደርስ በር ላይ የቆመው ጥበቃ በወንፊት ሽቦ ታግዞ ከታጠረው ፍርግርግ ግርግም ፊትለፊት ካለው አግዳሚ ላይ ቁጭ እንድንል ነግሮን ወደውስጥ ዘለቀ።
ከጥቂት ደቂቃ በኋላ እስክንድርና ስንታየሁ ብቅ አሉ። ከፍርግርጉ ጀርባ ይመጣሉ ብዬ ስጠብቅ ፖሊሱ በሩን ገርበብ አድርጎ ወደኛ ላካቸው። ባንጨባበጥም እይተቃቀፍን ሠላም ተባባልን። የማስክ ነገር ሁለቱም ሊለዩኝ አልቻሉም… ወዲያው እስኬው እንዴ-እንዴ መቼ መጣህ፣ ወይስ እዚህ መስራት ጀመርክ አለኝ። ስለጤንነታቸው፣ ስላሉበት ሁኔታ በጋራ ካወራን በኋላ። ስንታየሁና ቤተሰቡ ነጠል ሲሉ ከእስክንድር ጋር ስለሀገር ጉዳይ መጨዋወት ቀጠልን።
በትግራይ ስላሚደረገው ጦርነት አሳስቦት ጠየቀኝ፣ እነሱም በመንግሥት ቴሌቪዥን ብቻ እንደሚከታተሉት ነገረኝ።እኔም እስክንድር ፖለቲከኛ ከሆነ ጀምሮ በውስጤ የማስበውን እጠይቀው ገባሁ። ትግሉ እንዳለ ሆኖ የትግል እቅዱ፣ ስትራቴጂው በፊት በተከሄደበት መንገድ መሆኑ፣ የጠመንጃ፣የኢኮኖሚና የስልጣን ኃይል ያለው ሥርዓትን ከመገዳደር በፊት አቅም ማበልጸግ አይቀድምም ነበር ወይ የሚለው ጥያቄዬ እስኬውን አላስደሰተውም ነበር።
“ካሳሁን እኛ አንዲት ጠጠር ሳንጥል መታገላችንን እንቀጥላለን፣ ደግሞም እናሸንፋለን” ብሎ በአጽንኦት ነገረኝ።  የእሱን ሠላማዊ ትግል እምነት እንደምረዳው ገልጬለት የኔ ጥያቄ ኃይል ሳያደራጁ እንደእሳት-ራት ከገዢዎች ጋር መላተም እያስከፈለ ያለውን ዋጋ ለማስረዳት ሞከርኩ። ትንሽ በዚሁ ዙርያ እየተከራከርን ፖሊሱ በቃችሁ የሚል ምልክት ደጋግሞ እያሳየን ነበር። እስክንድር ፈገግ ብሎ ካስሽ ላለመስማማት እንስማማ አለኝ። እኔም መቼ አለመስማማት ድረስ የሚያደርስ ተወያየን ብዬው ተሳስቅን ተሰነባበትን። የእስረኛው አያያዝ መጥፎ እንዳልሆን ነገርግን እነሱ ከመምጣታቸው በፊት በተገቢ ሁኔታ ይሰራ የነበረው ግርግም ውስጥ የተገጠመው በሳንቲም መደወያ የሕዝብ ስልክ አገልግሎት እንዳይሰጥ መደረጉን ነግሮኛል። በተረፈ በዋይታ ግቢ ውስጥ ስፖርት ይሰራል፣ መጽሐፍ ያነባል። ብዙ ስሜት እየተደበላለቀብኝ ከሲኦሉ ቃሊቲ ጠባቂዎቹን በአጋባቡ አመስግኜ ወጣሁ። በጥሩ ሁኔታ አስተናግደውናል። አዕምሮዬ ግን ይጠይቃል።
በኢትዮጵያ በፖለቲካ ማሰርና መታሰር የሚያበቃው መቼ ነው
እስክንድር ለዓላማው በመጽናቱ ታስረ ነገርግን እሱ ሲታሰር እሱ የመሠረተው የፖለቲካ ድርጅት የት አለ?
ባልደራስ ከእስክንድር በተጨማሪ ድርጅቱን በብቃት ሊያስጉዙ የሚችሉ አመራሮች አሉት ወይ? ማንዴላ ሲታሰሩ ANC አልተሸበሸበም።ቢያንስ በዓላማ አንድ የሆኑ ተጽእኖ ፈጣሪ ፀረ-አፓርታይድ ግለሰቦችና ሌሎች ድርጅቶች ነበሩ።  የኢትዮጵያ ድርጅቶች ግን ህልውናችው በጥቂት ሰዎች የአመራር ብቃት ላይ የተመሠረተ ነው።
እስክንድርን የሚወደው ሰው ብዙ ነው። እርሱ ለዓላማው ለብዙሐን ሲል ራሱን ሲሰጥ ግን ከጎኑ የሚሆኑት ስንቶች ናቸው? በቃሊቲ ያየሁት ያስፈራል፣ ያሳፍራልም። እነእስክንድርን የሚጠይቀው ሰው ጥቂት ነው። ይህንን ከስንታየሁ ሚስትም ሆነ ከሌሎች ጠያቂዎች ለማረጋገጥ ችያለሁ።
እርሱ ለብዙ ሺህዎች ዋይታ ሲል በቃሊቲ ዋይታ ዞን ሲታሰር እስክንድር ጀግና ነው… እያሉ መወድስ ከሚደረድሩት ውስጥ 5 ፐርሰንቱ እንኳ እሱን ለመጠየቅና ለማበርታት ሲሆን የት ገቡ?
እነዚህ ጥያቄዎችን እያሰብኩ የእስክንድር ጽናት ብርግግ አድርጎ በቁሜ አባነነኝ። እሱ በቀላሉ የሚሰበር ሰው አይደለም። በእስር ለሚከፍለው መስዋዕትነት ሳይሆን በአንድ ነገር ተበሳጭቷል። “ከቀረቡብኝ የሐሰት ክሶች ውስጥ ከልብ ያዘንኩት የሙስሊምና የኦሮሞ ጥላቻ የሚለው ክፍል ነው። ሌላው የተለመደ የኢህአዴግ ክስ ነው::
Filed in: Amharic