>
5:26 pm - Monday September 15, 4938

የኢትዮጵያ ብድር 2.01 ትሪሊዮን ብር ደረሰ ምን ማለት ነው...?!? (ጥላሁን እምሩ ((Phd)

የኢትዮጵያ ብድር 2.01 ትሪሊዮን ብር ደረሰ ምን ማለት ነው…?!?

ጥላሁን እምሩ (Phd)

ትናንት ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ የኢትዮጵያ ብድር 2.01 ትሪሊዮን ብር ደረሰ የሚል ቀልብን በሚገዛ አርእስት  የወጣ ዘገባ ብዙ ሰዎችን ሲያነጋግር ተመለከትኩና አጠር ያለች ማብራሪያ ለመስጠት ተነሳሳሁ። አጭር ማብራራያ እጽፍ ብዬ ስላስረዘምኩት ይቅርታዬ ይቅደም።
መነሻ
መንግስታት የእለት ተለት ወጪዎቻቸውን ለመሸፈን፣ አትራፊ ይሆናሉ ተብለው የሚጠበቁ የኢንቨስትመንት እድሎችን ፋይናንስ ለማድረግ እንዲሁም የመከፈያ ጊዜው የደረሰ ብድርን ለመክፈል ይበደራሉ። የአንድ መንግስት ብድር ሶስት መሰረታዊ የሚባሉ ገጽታዎች አሉት፥
(1) Ownership: ብድሩ የተገኘው ከሀገር ውስጥ አበዳሪዎች ነው ወይንስ ከውጭ ሀገር አበዳሪዎች?
(2) Denomination: መንግስት የተበደረው በብር ነው ወይንስ በሌሎች ሀገራት ገንዘብ (ለምሳሌ በዶላር)?
(3) Maturity Profile: ብድሩ በአጭር ጊዜ የሚከፈል ነው በረጅም ጊዜ?
አንድ ብድር የአንድ ሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከባድ ጫና ያሳድራል/አያሳድርም የሚለውን ለማየት እነዚህን ሶስቱን መስፈርቶች አንድ በአንድ ማየት ያስፈልጋል። የኢትዮጵያ መንግስት ያለበት የብድር ጫና ምን ያህል አሳሳቢ ነው የሚለውን ለማየት እነዚህን ሶስቱንም ነገሮች ወረድ ብለን አንድ በአንድ እንመለከታለን።
የኢትዮጵያ መንግስት ብድር መጠን ምን ያህል ነው?
ብድሩ ምን ያህል አሳሳቢ ነው የሚለውን ከማየታችን በፊት የብድሩን መጠን ምን ያህል እንደሆነ እንመልከት። ሪፖርተር ጋዜጣ 2.01 ትሪሊየን ብር ብሎ የዘገበው መጠን ትርጉም የሚኖረው ይህ ብድር ከሌላ macroeconomic variable አንጻር መመልከት ስንችል ብቻ ነው – 2.01 ትሪሊዮን ብር የሚለው አሃዝ በራሱ ብዙ ትርጉም አይሰጥም። ለምሳሌ 2.01 ትሪሊየን ብር የአመታዊ ጠቅላላ ምርታችንን ምን ያህል ድርሻ ይወስዳል? ከአመታዊ ኤክስፖርታችን ጋር ሲነጻጸርስ ምን ያህል ይሆናል? አምና ከነበረበት ደረጃ በምን ያህል ጨመረ/ቀነሰ? ከብሔራዊ ባንኩ የውጭ ምንዛሪ ጥርቅም ጋር ሲነጻጸር ምን ያህል ይሆናል? ወዘተ … ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል።
ኢትዮጵያ እስከ ሰኔ 2020 እ.ኤ.አ ያለባት ብድር 2.01 ትሪሊዮን ብር (ወይንም 54.7 ቢሊዮን ዶላር) ሲሆን ይህም የአመታዊ ምርታችንን 51% ገደማ እንደማለት ነው። 2018 ላይ ኢትዮጵያ ከነበረባት ብድር (የአመታዊ ምርቱ 59%) አሁን ያለው ብድር 8 ፐርሰንቴጅ ነጥቦች የቀነሰ ነው። 2020 ላይ ከሰሀራ በታች የሚገኙ ሀገራት ማዕከላዊ መንግስታት አማካይ ዕዳ 56.7% ገደማ ሲሆን ከዚህ አንጻር የኢቶዮጵያ ብድር ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የከፋ ነው የሚባል አይደለም። ለምሳሌ ያህል የኬንያ መንግስት ዕዳ በ2021 የኬንያን አመታዊ ጠቅላላ ምርት 70% ያህል ይደርሳል ተብሎ ሲጠበቅ የኢትዮጵያ ብድር ደግሞ የኢትዮጵያን አመታዊ ምርት 58.5% ያህል ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። (ምንጭ IMF) (ብዙ ያደጉ ሀገራት መንግስቶች ከታዳጊ ሀገራት መንግስቶች በሰፊው የሚበልጥ ዕዳ እንዳለባቸው ይታወቃል።)
የመንግስት ብድር አሳሳቢነት
ይህን ማለት ግን የዕዳ መጠኑ እንዲህ በግርድፉ ሲታይ ብዙ አለመምሰሉ ምንም አይነት አደጋ ይዞ አይመጣም ማለት አይደለም። ለበለጸጉ ሀገራት አሳሳቢ ያልሆነ የዕዳ መጠን ታዳጊ ሀገራት ላይ ችግር ሊፈጥር እንደሚችል በዘርፉ ላይ የተሰሩ ምርምሮች በግልጽ ያሳያሉ (ይህ ክስተት debt intolerance ይባላል)። ስለዚህ የኢትዮጵያ ዕዳ ከምን አንጻር ሲታይ አስጊ ሊሆን እንደሚችል ለመመልከት ከላይ ወደጠቀስኳቸው ሶስት መስፈርቶች ልመለስ፥
Ownership: ኢትዮጵያ ያለባት 54.7 ቢሊዮን ዶላር እዳ በአበዳሪዎች ሲከፋፈል 29 ቢሊዮን ዶላር (53%) የሚሆነው ከውጭ ሀገር ምንጮች የተገኘ ሲሆን 25.7 ቢሊዮን ዶላር (47%) ገደማ የሚሆነው ደግሞ ከሀገር ውስጥ (በተለይም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ) የተገኘ ብድር ነው። (በቅርብ ጊዜ ብሔራዊ ባንኩ መንግስት ላይ ያለው ብድር ከ230 ቢልዮን ብር በላይ መደረሱን የሚገልጽ አጭር ኖት ጽፌ እዚሁ ፌስቡክ ላይ አስተያየት ሰጥቼ ነበር።)
Denomination: ብር አለም ላይ ካለው ዝቅተኛ ተቀባይነት አንጻር ከውጭ የሚገኘው ብድር ሙሉ በሙሉ ማለት በሚቻል ሁኔታ በዶላር የሚገኝ ብድር ሲሆን ከሀገር ውስጥ የሚገኘው ብድር ደግሞ በብር የሚገኝ ብድር ነው።
እነዚህ ነጥቦች በኢትዮጵያ ብድር ላይ ያላቸውን አንድምታ እንይ:
አንድ: በዶላር የሚሰበሰብ ብድርን ለመክፈል ቋሚ የዶላር ምንጭ ያስፈልጋል። እንደሚታወቀው አመታዊ የኤክስፓርት ገቢያችን ከ3 ቢሊዮን ዶላር አይዘልም። ከremittance የሚገኘው የውጭ ምንዛሪም ወደ 5 ቢሊዮን ዶላር ገደማ እንደሆነ ማየቴን አስታውሳለው። እነዚህ ሁለቱ ተደምረው አመታዊ ኢምፖርታችንን እንኳ መሸፈን አይችሉም። ይህም ማለት ከውጭ የምናስገባውን ሸቀጦች ለመሸፈንም ሆነ አመታዊ የብድር ክፍያ ለመክፈል ተጨማሪ ብድር  ውስጥ መግባት ይኖርብናል ማለት ነው።
ሁለት: የብር ምንዛሪ ከጊዜ ወደ ጊዜ አየተሸረሸረ መምጣት በዶላር ያለው የብድር ጫና በብር ሲተመን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ እንዲሄድ ያደርገዋል። ይህም ማለት አሁን ያለው የዕዳ መጠን ምንም ጭማሪ ባያሳይ እንኳ የውጭ ምንዛሪው ከጊዜ ወደጊዜ እየቀነሰ ሲሄድ የዕዳ ሸክማችን እየከፋ እንዲሄድ ያደርገዋል። (This is one of the contractionary effects of devaluation. በሌላ ሀገር ገንዘብ የተበደሩ ታዳጊ ሀገሮች የገንዘባቸው የመግዛት አቅም ሲቀንስ ከሚያጋጥሙ ችግሮች አንዱ ነው።)
ሶስት: በዶላር የተሰበሰበ ብድርን ለመክፈል መንግስት በቂ የሆነ ዶላር መሰብሰብ ቢያቅተው ያለው አማራጭ ከአበዳሪዎች ጋር በመደራደር ጊዜያዊ እፎይታን ማግኘት፤ አሁን ያለውን ብድር በረጅም ጊዜ በሚከፈልና አመታዊ ክፍያው በሚቀንስ ሌላ ብድር መቀየር፤ ከአለም አቀፍ የፋይናንስ ማዕከላት በዝቅተኛ ወለድ ብድር በማግኘት ውድ የሆኑ ብድሮችን መክፈል፤ ሁሉም አልሳካ ሲል ደግሞ የአበዳሪዎችን ምህረት በመጠየቅ የብድር ጫናውን ለመቀነስ ሙከራ ያደርጋል። (ጠቅላይ ሚኒስትር አብይም ሚያዝያ ውስጥ The New York Times ላይ ባሳተሙት ጽሁፍ ግሩፕ 20 ሀገራት የዝቅተኛ ገቢ ሀገራትን ዕዳ ከማራዘም ይልቅ እንዲሰርዙ ተማጽኖ አቅርበው ነበር። ከዚህ ቀደምም የኢትዮጵያ መንግስት የParis club በሚባል የአበዳሪ ሀገራት ስብስብ በኩል የዕዳ ቅነሳ ተጠቃሚ ሆኖ ያውቃል።)
አራት: ከሀገር ውስጥ ምንጮች በብር የተሰበሰበው ብድርን ለመክፈል መንግስት በግብርና በቀረጥ የሚሰበስበውን ገቢ ማሳደግ ይኖርበታል። ይህ ካልሆነ ከሌሎች ልማታዊ ተግባራትም በማሸሽ ብድሩን ሊከፍል ይችላል። ይህ ደግሞ ኢኮኖሚው ላይ መቀዛቀዝ ሊፈጥር ይችላል – debt overhang። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ብሔራዊ ባንክ ሀገር ውስጥ ካሉ ተበዳሪዎች ዋነኞች እንደመሆናቸው ይህ ዕዳ የመሰረዝ እድሉ ሰፊ ነው። ከሌሎች ውስጣዊ ምንጮች የተሰበሰበውን ዕዳ ብሔራዊ ባንኩ ገንዘብ አትሞ ለመንግስት እያበደረ ብድሩ እንዲከፈል ሊያግዝም ይችላል። ይህ የመጨረሻው አማራጭ ሁለት አንድምታ አለው፥
(1) የኑሮ ውድነቱን የበለጠ ያንረዋል
(2) የኑሮ ውድነቱ መናር ብራሱ የውጭ ምንዛሪው የበለጠ አንዲሸረሸር በማድረግ ከላይ ነጥብ ሁለት ላይ ወደተጠቀሰው ችግር ይመልሰናል።
አምስት: በመንግስት ድርጅቶች (state owned enterprises) የተሰበሰበው ብድር የኢትዮ ቴሌኮም በከፊል ወደግል ይዞታ ሲዞር የመንግስት ዕዳ ጫና በመጠኑም ቢሆን የሚቀንስ ይሆናል። ሌሎች የመንግስት ድርጅቶች (መብራት ሀይል፣ የኢትዮጵያ አየር መንግድና የባቡር መንገድ ኮርፖሬሽንን የመሳሰሉት) ያሉባቸው ዕዳዎች መንግስት ላይ የሚቆዩ ናቸው። እነዚህ ድርጅቶች አትራፊ ሆነው ብድራቸውን መክፈል እስከቻሉ ድረስ የተበደሩት ብድር መንግስት ላይ የሚያሳድረው ጫና ብዙም አይሆንም።
ስድስት: የመንግስት ዕዳ መቼ መከፈል እንዳለበት (maturity profile) የሚገልጽ መረጃ በቅርበት ስላላገኘሁ ብዙ መናገር አልችልም። እንደ መርሕ በአጭር ጊዜ የሚከፈል ዕዳ በረጅም ጊዜ ከሚከፈል እዳ የበለጠ አደጋ እንዳለው ግልጽ ነው። ከውጭ ሀገር የተበደርነው ብድር አማካይ የመከፈያ ጊዜው 15 አመት እንደሆነ የሪፖርተሩ ዘገባ ይጠቅሳል። ይህ ከሆነ ብድሩን ለመክፈል በቂ የሆነ የመተንፈሻ ጊዜ አለን ማለት ነው። ከሀገር ውስጥ የሚሰበሰበውን ዕዳ በmaturity ለመከፋፈል ይረዳ ዘንድ በቅርቡ የተቋቋመውን የቦንድ ገበያ የአንድ አመት ተሞክሮ መመልከት ይረዳ ይሆናል። በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ቦንድ በመሸጥ የተገኘው ከ3 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚሆን ብድር ሙሉ በሙሉ ማለት በሚቻል ሁኔታ በአጭር ጊዜ mature የሚያድርግ ቦንድ ነው። ይህ መረጃ ከሀገር ውስጥ የተሰበሰበውን አጠቃላይ ብድር የሚወክል ከሆነ የሀገር ውስጥ ብድርም ከውጭ ሀገር ከሚገኘው ብድር ባልተናነሰ አስፈሪ ነው።
ማጠቃለያ
2.1 ትሪሊዮን ብር (ማለትም የአመታዊ ምርቱን 51%) በራሱ ከሌሎች ሀገራት ጋር ሲነጻጸር ብዙ የሚባል አይደለም። ነገር ግን የውጭ ምንዛሪ ማግኘት የሀገራችን ከባድ ፈተና ከመሆኑ አንጻር ከውጭ የተበደርነው በዶላር የተተመነ ብድር ለመክፈል አስቸጋሪ ይሆናል። የብር የመግዛት አቅም ከጊዜ ወደጊዜ እየተሸረሸረ መምጣት የዚህን ዕዳ  ጫና ከጊዜ ወደ ጊዜ የከፋ ያደርገዋል።
ተሳክቶልን ከቡድን 20 አበዳሪ መንግስታት የብድር ስረዛ ብናገኝ ራሱ ከprivate creditors ተመሳሳይ መስተንግዶ ማግኘት ቀላል አይሆንም። አንድ የግል አበዳሪ የአርጀንቲናን መንግስት ፍርድ ቤት አቁሞ 12 አመት ከፈጀ ክርክር በኋላ ብድሩ እንዲከፈልው ተፈርዶለታል።
መንግስት ከሀገር ውስጥ የተበደረውን ብድር ለመክፈል ብር ወደማተም ፊቱን ማዞሩ የሚቀር አይመስልም። ይህም የኑሮ ውድነቱን የበለጠ አንሮ ከቀን ወደቀን በሚገኝ ገቢ የሚተዳደረውን የማሕበረሰቡ ክፍል የዚህ እዳ ቀጥተኛ ተጎጂ/ከፋይ/ ያደርገዋል።
ከሀገር ውስጥ የሚሰበሰበው ብድር ላይ መንግስት የሚከፍለው ወለድ በኮሮና ምክንያት ከተቀዛቀዘው የኢኮኖሚው እድገት በላይ እስከሆነ ድረስ የሀገሪቱ የዕዳ ሸክም መጨመሩ የማይቀር ይመስላል። በፌዴራል መንግስቱና በህወሓት መካከል የተካሄደው ጦርነትና ተያይዞ የሚመኖሮ የመከላከያ ወጪ የመንግስትን ዕዳ የበለጠ ከፍ ሊያደርገው እንደሚችል መገመትም ከባድ አይሆንም።
(ከላይ የሰጠሁት በችኮላ የተጻፈ ማብራሪያ በጊዜው ላገኝ የቻልኩት መረጃ ላይ የተመሰረተ ነው። የተሻለ መረጃ ተሰብስቦ ጠንካራ ጽሁፍ መጻፍ ይቻላል፣ ይገባልም።)
Filed in: Amharic