>

"አጤ ቴዎድሮስ" በጳውሎስ ኞኞ  (አንተነህ ሰላም)

 “…የአጤ ቴዎድሮስ ነገር – ለመዓት የተባለው ለምሕረት – ለምሕረት የተባለው ለመዓት ይዳርግ  ነበር!!!”
አለቃ ተክለ ኢየሱስ ሲፅፉ

“አጤ ቴዎድሮስ” በጳውሎስ ኞኞ

 አንተነህ ሰላም
ካሳ ኃይሉ በኋለኛው ስማቸው አጤ ቴዎድሮስ ከጎንደር ከተማ 12 ኪ/ሜ ያህል ርቃ በምትገኘው ዳዋ ከተባለች መንደር ጥር ፮ (6) በ፲፰፻፲፩ (1811) ዓ/ም ከአባታቸው አቶ ኃይሉ ወልድ ጊዮርጊስ እና ከእናታቸው ወ/ሮ አትጠገብ ወንድወሰን ተወለዱ። (7)
ሔነሪ ዱፍተን እንደፃፈው “አጤ ቴዎድሮስ …ወደ ጥቁረቱ የሚያደሉ ናቸው። …ራሳቸው ጥሩ ቅርፅ ያለው ነው። ጠጉራቸው ከግንባራቸው ወደ ኋላ የተጎነጎነ ነው። ግንባራቸው ወጣ ያለ ነው።…
“ዓይናቸው ጥቁር ነው። … አፍንጫቸው በመጠኑም ቢሆን የሮማውያን ቅርፅ አለው። …አፋቸው ውብና ፈገግተኛ (ሳቂታ) ነው። …ጢማቸውም ሆነ ሪዛቸው በጣም ትንሽ ነው። ጠባያቸው ደስ የሚልና ትሁት ናቸው።” (125)
ዶ/ር ብላንክ ጽፎት አቶ ዳኜ ወልደ ሥላሴ እንደተረጎሙት ደግሞ “…በ1852 ዓ/ም ለመጀመሪያ ጊዜ አጤ ቴዎድሮስን ስንገናኝ ዕድሜያቸው 48 ዓመት ይሆን ነበር። መልካቸውም ከብዙዎቹ አበሾች ጠቆር ያሉ ወይም፣ አፍንጫቸው ደፍጣጣ፣ አፋቸው ሰፊ ከንፈሮቻቸው ትንንሽ ጠጋጋ፣ ቀጠን ያሉ፣ …በፈረሰኛነታቸውም በጦር አወራወር ስልታቸው በወታደርነታቸው የተመሰገኑ ነበሩ። ጎድጎድ ያሉት ጥቋቁር ዓይኖቻቸው አገላለጥ አስደንጋጭ ሲሆን በሠላም ጊዜ ደስ የሚያሰኙ፣ የሰውን ፍቅር የሚያስገኙ፣ ለስላሳ ሆነው በተቆጡ ጊዜ ደግሞ በርበሬ መስለው የሚያስደነግጡና የሚያሸብሩ እሳት ገሞራ የሚወረውሩ ነበሩ። በድንገት ሲቆጡ መላ አካላቸው የሰውን ልጅ ከፍ ካለ ድንጋጤ ላይ ይጥላል። ጠይም ገላቸው ሲኮሰኩስ፣ ስሱ ከንፈራቸው ሲንቀሳቀስና ጠጉራቸው ሲቆም በጠቅላላ ሰውነታቸው የአንበሳነት ጠባይ የያዘ አስደንጋጭ ይሆናል።” (127)
የአጤ ቴውድሮስ ጠባይ ተለዋዋጭ ነበር። በማያስቆጣ ነገር ይቆጣሉ፣ ይበሳጫሉ፣ ይቀጣሉ። በሚያስቆጣ ነገር ይስቃሉ፣ ይምራሉ ወይም ዝም ይላሉ። አለቃ ተክለ ኢየሱስ ሲፅፉ “…የአጤ ቴዎድሮስ ነገር ያስቸገረ ነበር። ለምሕረት የተባለው ለመዓት፤ ለመዓት የተባለው ለምሕረት ይሆን ነበር” ይላሉ። (128)
የሐገሬው  ሰው ሲጣላ “ከቴዎድሮስ መዓት ይጣልህ” እያለ ሲረግም፣ ሲወዳጅ ደግሞ “ከቴዎድሮስ በረከት ይክፈልህ” ይል ነበር። (129)
አጤ ቴዎድሮስ ለሀገራቸው ካበረከቱት ልማት መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስላቸው ሴባስቶፖል መድፍ ነው። በዛ የጨለማ ዘመን እንኳን መድፍ መስራት ቀርቶ ምንም ነገር መስራት በማይታሰብበት ጊዜ በሀገር በቀል ዕውቀት እንኳ ባይሆንም በሀገር በቀል ግብዓት ሰርተዋል።
ሌላው መድፉን ለማጓጓዝ ከደ/ታቦር እስከ መቅደላ የመንገድ ቅሰየሳና ጠረጋ በማስፈለጉ በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ ይመስለኛል የምንድስና ዕውቀት በሌለበት ወቅት በቻሉት አቅም የመኪና መንገድ የሚመስል ጎዳና አሳንፀዋል።
አጤ ቴዎድሮስ ትልቁ ሕልማቸው በዘመነ መሳፍንት በየመንደሩና በየጎጡ በጎበዝ አለቃ የተከፋፈለች ሀገራቸውን የታፈረች፣ የበለፀገች፣ አንድነቷ የጠነከረ ማድረግ ነበረ። የእሳቸው ጡብም ለቀጣይ መሪዎች ግብዓት ሆኖ አልፏል።
ሌላው ከሚያስደንቀኝና ከሚያስገርመኝ ባህሪያቸው ሁሉንም ነገር በሀገር መስራት ይቻላል ብለው ያምኑ ነበር። ከውጪ ከማስገባት ይልቅ እዚሁ በሀገር እውቀት እንኳ ባይቻል በሀገር እጅ ማስራት ነበር ፍላጎታቸው። በወቅቱ ይሄ ስበልቦና ዳብሮ ቢቀጥል ኖሮ አሁን የራሳችን አሻራ ያረፈበት ማዕዘን እስከ አሁን ይኖረን ነበር።
ለማንኛውም ጃንሆይ ለእምዬ እናት ሐገርዎ ኢትዮጵያ በቀናኢነት ላደረጉት መልካም ጡብ እናመሰግናለን!
ዛሬ በሕይወት ቢኖሩ ኖሮ 203ኛ የልደት በዓላቸውን ያከብሩ ነበር። እኛም ቀኑን በዚህ መልኩ ለማስታወስና ለማመስገን ወደድን!
“አጤ ቴዎድሮስ” በጳውሎስ ኞኞ አንተነህ ሰላም
Filed in: Amharic