>

እውን ባለፉት 3 ዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ የሽግግር ሥርዓት ነበር/አለ ወይ? (ከይኄይስ እውነቱ)

እውን ባለፉት 3 ዓመታት  በኢትዮጵያ ውስጥ የሽግግር ሥርዓት ነበር/አለ ወይ?

ከይኄይስ እውነቱ


በርእሰ ጉዳዩ ላይ አስተያየት ለመስጠት ምክንያት የሆነኝ ባንድ በተወሰነ ደረጃ የማውቀውና የማከብረው፣ አሁን በዐቢይ አገዛዝ ውስጥ ዕውቀቱና ልምዱ የፈቀደለትን እንደከዚህ ቀደሙ ለሀገሩ ለኢትዮጵያ ላበርክት በሚል መንፈስ የሚቻለውን ለማገዝ (ከአገዛዙ ባሕርይ የተነሳ እገዛውን ለማድረግ ይችላል የሚል እምነት ባይኖረኝም) የቀረበለትን ጥሪ ተቀብሎ ዛሬ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር በመሆን እየሠራ የሚገኘው ወንድሜ ዶ/ር ዳንኤል በቀለ በቅርቡ (እ.አ.አ. ጃንዌሪ 2/2021) በአባይ ሜዲያ ከጋዜጠኛ መዓዛ ሞሐመድ ጋር ባደረገው ቃለ መጠይቅ ስለ ሽግግር መኖር እና ባገራችን በዚህ ሦስት ዓመታት ገደማ እየተፈጸመ ያለው ምስቅልቅል በሽግግር ጊዜ የሚጠበቅ ነው በማለት ያነሳው አሳብና አቋም ነው፡፡ 

በርግጥ በቃለ ምልልሱ በርካታ ቁም ነገሮች መነሳታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ዳንኤልም በቃለ መጠየቁ ባነሳቸው አንዳንድ መሠረታዊ ነጥቦች ዙሪያ የተለየ አመለካከት ያላቸው ብዙ ዜጎች እንዳሉ መናገሩ እንዳለ ሆኖ፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት ገደማ በዐቢይ አገዛዝ ሽግግር እየተካሄደ ነው በሚለው ምልከታ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በዜጎች ባጠቃላይ፣ በተለይም በአማራው ማኅበረሰብ ላይ ነገድን እና ሃይማኖትን መሠረት አድርጎ እየተፈጸመ ያለውን ፍጅት ‹‹የዘር ማጥፋት ወንጀል ሥጋት አለ›› ብሎ ባሳነሰውም ረገድ እኔን ጨምሮ ብዙዎች ከሥጋት ባለፈ የዘር ማጥፋት ለሚባለው ወንጀል እንከን የለሽ፣ ዓይነተኛና በመደበኛ ሁናቴ ተቀባይነት ላለው ብያኔ (text book definition of genocide) ምሳሌ ተደርጎ የሚወሰድ ድርጊት በኢትዮጵያችን መፈጸሙን፣ እንዲያውም ከዛ አልፎ በጎጃሙ መተከል የዕለት ተዕለት ክስተት እየሆነ መምጣቱን እናምናለን፤ታዝበናልም፡፡ ዳንኤል ይህ ጠፍቶት አይመስለኝም፡፡ ብዙዎቻችን ተስፋ የቈረጥንበትን የዐቢይ አገዛዝ ምናልባት በሱ አመለካከት እንጥፍጣፊ ዕድል አለ ከሚል እምነት የመነጨ ይሆናል፡፡

ዛሬ ግን የማተኩረው ሕዝባዊ ዓመፃን ተከትሎ የወያኔ አገዛዝ ከመንበረ ሥልጣኑ ከተወገደና ወደ መለ ከተሸሸገ በኋላ (አሁን ከጦርነቱ በኋላ ከተደመሰሰና ርዝራዡ እየተለቃቀመ ባለበት ሰዓት) የወያኔን  የጐሣ ፖለቲካ፣ የቋንቋና የጐሣ ፌዴራሊዝም፣ ዜጎችን ከአገር ባለቤትነት ከነቀለ ‹ክልል› የተባለ መዋቅር፣ ይህንንም አገር አውዳሚ የጐሠኛነት ሥርዓት ሕጋዊ ሽፋን የሰጠውን የወያኔ ማስመሰያ ‹ሕገ መንግሥት› ተቀብሎና ለመጠበቅም ምሎና ተገዝቶ ወራሽ በሆነው በዐቢይ አገዛዝ የሥርዓት ሽግግር ሂደት ተጀምሯል ወይ? የሚለው ሲሆን፣ በተጓዳኝም ሁሉ የኛ/ለኛ የሚለው በሁሉም መስክ (መንግሥታዊ ሹመት፣ ሥራ ቅጥር፣ በተናጥል የሚወሰን የትምህርትና ቋንቋ ሥርዓት፣ የመሬት÷ የመኖሪያና ንግድ ቤቶች ወረራና ድልድል፣ የሕዝብ ስብጥር ቅየራ፣ወዘተ.) የሚስተዋለው ኦሕዴዳዊ/ኦነጋዊ የተረኛነት አባዜ ባንድ ወገን፤ አገዛዛዊ የመከላከያ፣ የፖሊስና የጸጥታ ኃይሎችን እንዲሁም አገራዊ ሀብትን ላንድ ግዛትና ቡድን ዓላማ ማስፈጸሚያ በማድረግ የሰፈነው ጭካኔ የተሞላበት የጐሣ መድልዎ (አፓርታይድ) ሥርዓት መንገሥ በሌላ በኩል፣ ዳንኤል እንዳለው በ‹‹ሽግግር ጊዜ›› የሚጠበቁና የሚያጋጥሙ ክስተቶች ናቸው ወይ የሚሉትን ጥያቄዎች በመጠኑ መቃኘት ይሆናል፡፡

ሀ/ የሽግግር ሂደት አጠቃላይ የጋራ ባሕርያት

1/ የሽግግር አስተዳደር የሚባለው የሽግግር ባለሥልጣናት ሰላምና መረጋጋትን በማምጣት ዓላማ ሕገ መንግሥታዊ ሽግግርን የሚያስተዋውቁበት ሂደት ነው፡፡

2/ ሽግግር ባጠቃላይ አነጋገር የአንድ ሀገረ መንግሥትን ዳግም ልደት ያመለክታል፤ በተለይም ለግጭቶችና ማኅበራዊ ቀውሶች መልስ ለመስጠት በማለም የሥርዓቱን ሕገ መንግሥትና ተቋማት ሙሉ በሙሉ በጥልቀት በመፈተሽ ሥርዓታዊ ወይም መሠረታዊ ለውጥ የሚያመጣ ዕድሳትን ይመለከታል፡፡

3/ በዝርዝር ሲታይ የሽግግር ሂደት የሚከተሉትን ይመለከታል፤ 

 • የመንግሥት አሠራርንና ተቋማዊ መዋቅሮችን እንዲሁም እነዚህ ከኅብረተሰቡ ጋር ያላቸውን መስተጋብር የሚቆጣጠሩ ቅርፀ መንግሥትን ወይም ሕግጋትን፣ ባህላዊና ማኅበራዊ ደንቦችን ወዘተ. የማሸጋገር ሂደትን፤
 • ሽግግሩም ሕገ መንግሥታዊ ባልሆነ መንገድ የሚፈጸም መሆኑን፤ 
 • ሕገ መንግሥታዊ ያልሆነ መንገድ ማለትም ጊዜያዊ የሕገ መንግሥት አቋም ባላቸው ሕጎች መተካትን፤ 
 • እነዚህ ጊዜያዊ የሕገ መንግሥት አቋም ያላቸው ሕጎች ማናቸውንም ዓይነት ቅርፅ (ዓለም አቀፍ ስምምነቶች፣ ባገር ውስጥ በግዛቶች መካከል የሚደረጉ ስምምነቶች፣ ጊዜያዊ/የሽግግር ሕገ መንግሥት፣ የውስጥ መግለጫዎች፣ ወይም የነዚህ ቅይጥ) ሊይዙ እንደሚችሉ፤ እና 
 • የሕጎቹም መነሻ የፖለቲካ ቡድኖች ሙሉ ስምምነት ወይም ተቃውሞን መሠረት ያደረገ ሊሆንም/ላይሆንም ይችላል፡፡ 

ለ/ የሽግግር አስተዳደር የሚከተሉት ዐበይት ገጽታዎች ይኖሩታል፤

1/ ሕግን የሚያከብር (ዓለም አቀፍ ሕግጋትን ጨምሮ)፤

2/ የታወቀ የጊዜ ገደብ ያለው፤

3/ አስተዳደሩ ሽግግርን በሚመለከቱ ርእሰ ጉዳዮች የተገደበ መሆኑ፤ ሽግግሩን የሚመራው አካል ዋና ተግባር ሽግግሩን ማስፈጸም፣ ጸጥታን በመመለስ አገሩን በጊዜያዊነት ማስተዳደር እና ራሱን ወደ ሥልጣን በማያሸጋግርበት መልኩ ለወደፊቱ መዘጋጀት ነው፤ በመሆኑም የወደፊቱን የሕገ መንግሥት አቋም በቋሚነት ለመወሰን ወይም በሽግግሩ ጊዜ የበላይነት እንዲኖረው ነፃ ሊሆን አይገባም፤ 

4/ አካታችነት፤ ተቋማዊ የሥርዓት ሽግግር በተግባር ሥልጣን ላይ ባለው አካል (de facto authority) ብቻ በተናጥል የሚወሰን አይደለም፤ በፖለቲካ ማኅበራት ውስጥ እና ሲቪል ማኅበራት መካከል ሰፋ ያለና ሐቀኛ ንግግርን እንዲጀመር የሚያደርግ መሆን ይኖርበታል፤

5/ የሽግግር ፍትሕ፤ የመንግሥታት ልምድ በበቂ ሁናቴ እንደሚያረጋግጠው የሽግግር ፍትሕ የሽግግር አስተዳደር አስፈላጊና መሠረታዊ አካል መሆኑ ይታመንበታል፤

እነዚህን የሽግግር አስተዳደር ገጽታዎች እና ከፍ ብለን ያነሳናቸውን የሽግግር ሂደት ባሕርያትን በመለኪያነት ወስደን ስንመለከት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በተግባር ሥልጣን ይዞ የሚገኘው የዐቢይ አገዛዝ የሽግግር አስተዳደር ሊያሰኘው የሚችል ጠባያት ወይም አገራችን በሽግግር ሂደት እንደምትገኝ የሚያመለክቱ ተግባራት አሉ ወይ? ለሚሉ ጥያቄዎች የምናገኘው መልስ የዐደባባይ ምሥጢር በመሆኑ ምክንያት በዚህ አስተያየት በመጠኑ እንዳስሳቸዋለን፡፡

1/ የሽግግር አስተዳደር ቀዳሚና ዋና ተልእኮ ባገር ላይ ሰላምና ጸጥታን ማስፈን እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በዚህ ረገድ ፍላጎትና ቆራጥነት የጎደለው የዐቢይ አገዛዝ መንግሥት የለም ለማለት በሚያስደፍር ሁናቴ ባገራችን ሥርዓተ አልበኝነት እንዲነገሥ አድርጓል፡፡ ‹‹ፍቅር›› በሚል ውስጠ ወይራ ኢትዮጵያን አኬልዳማ (የደም ምድር) አድርጓታል፡፡ አገዛዙ በልፍስፍስነት ብቻ ሳይሆን በየክፍላተ ሀገራቱ ለሚታየው የሰላምና ጸጥታ ችግር በተቆጣጠራቸው የጸጥታና ‹ልዩ ኃይሎች› አማካይነት በቀጥታ በመሳተፍ፣ ድጋፍ በመስጠትና በዝምታም ጭምር በማበረታታት የዜጎች እልቂትና መፈናቀል መደበኛ ክስተት ለመሆን ችሏል፡፡ ከወያኔ ጋር ለተገባውም ጦርነት ዋነኛ ተጠያቂው በ‹ትእግሥት› ስም እና በጋራ ወንጀለኛነት ምክንያት ከመነሻው ያሳየው ዳተኝነት መሆኑ አይካድም፡፡ ስለሆነም አገዛዙ የሽግግር አስተዳደር ለመሆን ብቃት የለውም፡፡ የሽግግር ሂደት ምልክቶችም የሉም፡፡

2/ ከመነሻው አገዛዙ ሥርዓታዊ/መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት ያለመ አይደለም፡፡ የወያኔን የማስመሰያ ‹ሕገ መንግሥት› እና በዚህም የተቋቋመውን የጐሣና ቋንቋ ፌዴራሊዝም እና ሕዝብን ለግጭትና ባይተዋርነት የዳረገ ‹ክልል› የተባለ መዋቅር በተረኛነት ይዞ ለመቀጠል የተስማማ አፓርታይዳዊ የጐሠኛነት አገዛዝ በመሆኑ ግጭቶችንና ማኅበራዊ ቀውሶችን ብሔራዊ መግባባት በማምጣት መንፈስ በተጠና መልኩ መሥራት ይቅርና በፓርቲው አማካይነት ግጭቶች ሳይሆኑ ከዘመነ ወያኔ የከፉ አገዛዛዊ ጭፍጨፋዎች በዜጎች ላይ እንዲፈጸሙ አድርጓል፡፡ አዳዲስ የሽብር ማዕከላትን ፈጥሮ አገርና ሕዝብ እየታመሰ ይገኛል፡፡ በአገር ውስጥ የዜጎች መፈናቀል የዓለምን ሬከርድ የሰበርነውም በዚህ አፓርታይዳዊ አገዛዝ ዘመን መሆኑ ምድር ላይ የሚታይ እውነት ነው፡፡ አሁንም ጭፍጨፋውና መፈናቀሉ ቀጥሏል፡፡ ስለሆነም አገዛዙ የሽግግር አስተዳደር ለመሆን ብቃት የለውም፡፡ የሽግግር ሂደት ምልክቶችም የሉም፡፡

3/ አገዛዙ የሕግ የበላይነት በመኖር የሚታማ አይደለም፡፡ በተቃራኒው በዘመነ ወያኔ የተስፋፋው በጥፋት ተጠያቂነት ያለመኖር ባህል (culture of impunity) እጅግ ሥር የሰደደበት ጊዜ ሆኗል፡፡ የአገዛዙ አለቃ በሚሊየን የሚቆጠር ዶላር ከየት አመጣህ ብላችሁ አትጠይቁኝ፡፡ እናንተን አይመለከትም ሲል የሕዝብ ያልሆነውን ምክር ቤት ደነዝ አባላት ሲናገር ተደምጧል፡፡ በሚወክለው ጽ/ቤት እና በያዘው ሥልጣን አማካይነት በኢትዮጵያ ሕዝብ ለምኖ ያመጣውን ገንዘብ አትጠይቁኝ ማለት ወንጀልና ቅጥ ያጣ ነውረኝነት ነው፡፡ አሁንም ከወያኔ በከፋ መልኩ የፍትሕ ሥርዓቱ የተረኞች ጐሣ ፖቲከኞች ማፌዣ ሆኗል፡፡ የነ እስክንድርና የልደቱ ክሶችና እስር ዓይነተኛ ማሳያ ናቸው፡፡ ወያኔ የፈጠራ ክስና የሐሰት ምስክሮችን አቀነባብሮ የተቀደሰውን ዓውደ ፍትሕ ያረክስ ነበር፤ ኦነጋውያኑ እነ ዐቢይ ደግሞ ተውኔቱንም በቅጡ ማስመሰል ተስኗቸው ቅጥረኛ ምስክሮችን ከመጋረጃ ጀርባ አድርገው ዳኝነትንና ፍትሕን ቀብረዋል፡፡ አይደለም እውነተኛ ተቃዋሚዎችንና ጋዜጠኞችን (በጋዜጠኛ ተመስገን ላይ ባደባባይና በግል የደረሰበትን ዛቻና ማስጠንቀቂያ ያስታውሷል) የራሱን ባለሥልጣናት ስለ አገር ጉዳይ አትናገሩ አትጻፉ ያለ አገዛዝ አይደለም እንዴ? ስለሆነም አገዛዙ የሽግግር አስተዳደር ለመሆን ብቃት የለውም፡፡ የሽግግር ሂደት ምልክቶችም የሉም፡፡

4/ አገዛዙ የሽግግር አስተዳደር ባለመሆኑ ስለ ሽግግር ፍኖተ ካርታም ሆነ የጊዜ ገደብ አልነበረውም፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ስለ ምርጫ የምናወራበት ጊዜ ባይሆንም ከወያኔ በወረሰውና በለመደው መንገድ ብቻውን ሮጦ ብቸኛ አሸናፊ ለመሆን የውሸት ምርጫ አደርጋለሁ ብሎ እየተዘጋጀ ይገኛል፡፡ ‹‹ታድሷል›› የተባለው የምርጫ ቦርድም የአገዛዙን ፈቃድ ለመፈጸም እየሠራ ይገኛል፡፡

5/ አገዛዙ ሕዝባዊ ዓመፃን መሰላል አድርጎ የሥልጣን መንበሩን ከተቆናጠጠበት ጊዜ ጀምሮ ራሱን እንደ ቋሚ መንግሥት እንጂ (ስለ ምርጫ የሚያወራውን ቅጥፈት ለጊዜው ትተን) ጊዜያዊ የሽግግር አስተዳደር ቈጥሮ አያውቅም፡፡ በዚህም ምክንያት ሥልጣኑ (mandate) ሳይኖረው በርካታ አገርንና ሕዝብን የሚጎዱ የማይቀለበሱ የጥፋት ተግባራትን ፈጽሟል፤ እየፈጸመም ይገኛል፡፡ ለአብነት ያህል ‹ቅዱስ መጽሐፌ› ነው የሚለውን የወያኔ ‹ሕገ መንግሥት› ሳያሻሽል ለግጭ መሠረት ከሆኑት መካከል አንዱ የሆነውን የአከላለል ለውጥ በገዛ ፈቃዱ አድርጓል (ሲዳሞ እና አሁን ደግሞ ደቡብ ምዕራብ የሚል)፤ አሁንም አትንኩብኝ የሚለውን ‹ሰነድ› ተላልፎ በተቈጣጠረው ሕግ አስፈጻሚ አካል አማካይነት የአገሪቱ የሥራ ቋንቋ ላይ ለውጥ አድርጓል፤ ዓላማውም በዐቢይ ሹመኛ ሽመልስ አብዲሳ አማካይነት ‹ኦሮሙማ› የሚባለው የኦነጋውያኑ ፕሮጀክት አንድ አካል ሆኖ እየተተገበረ ይገኛል፡፡ ከሕግ ውጭ የሥራ ቋንቋ ከተደረጉት መካከል ኦሮምኛ ብቻ ተለይቶ በትምህርት ሥርዓት፣ በሥራ ቅጥር ወዘተ. ተግባራዊ መደረጉ የተረኝነትና የማንአለብኝነት ዓይነተኛ ማሳያ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ በ‹ልማት› ስም ኦሮሙማ የሚባለው ኢትዮጵያን የማፍረስ እንቅስቃሴ አካል የሆነው ብሔራዊ ታሪክና ቅርስ የማጥፋት ዘመቻም በስፋት እየተካሄደ ይገኛል፡፡ ዝርዝሩ ወረድ ብሎ በተራ ፊደል ‹ሐ› ተመልክቷል፡፡ ምዕራባውያንን ለማስደሰት ሲባል የሕዝብ ሀብትና መኩሪያ የሆኑትን እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ቴሌኮሙኒኬሽን የመሳሰሉ ነባርና ብሔራዊ ተቋማትን  ወደ ግል ለማዘዋወር የተጀመረው እንቅስቃሴ የሽግግር ጊዜ ተግባር አይደለም፤ በወያኔ የጀመረው የጐሣ ጭቆናና በደል፣ የ100 ዓመት እና የአማራና ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስቲያኖች ጥላቻ የሐሰት ትርክቶች ጀምሮ አሁን የቀጠለው የ150 ዓመትና የቅኝ ግዛት እንዲሁም አ.አ. የኦሮሞ ናት የሚለው የሐሰት ትርክት ወዘተ. የሽግግር ጊዜያዊ አስተዳደር ዓላማና ተግባር ሳይሆን ሀገረ መንግሥትን የማፍረስ እንቅስቃሴ አካል ይመስላል፡፡ ባንፃሩም አገዛዙ ኢትዮጵያን በጊዜያዊነት እያስተዳደረ ሳይሆን በሁሉም ዘርፍ የበላይነትን ይዞ ያለ ሕዝብ ፈቃድ ራሱን በሥልጣን ላይ በማስቀጠል ዓላማ የወደፊቱን የአገራችንን ዕጣ ፈንታ በአሉታዊ መልኩ የሚወስኑ የረጅም ጊዜ ዕቅዶችን አውጥቶ በተግባር እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ስለሆነም አገዛዙ የሽግግር አስተዳደር ለመሆን ብቃት የለውም፡፡ የሽግግር ሂደት ምልክቶችም የሉም፡፡

6/ በዚህ ጽሑፍ እንደገለጽነው የሽግግር ሂደት አንዱ ገጽታ አካታችነት/አሳታፊነት ነው፡፡ 

ወደ ዴሞክራሲ በሚደረግ ሽግግር በፖለቲካ ሥርዓቱ አመራር ላይ ያሉ ግለሰቦች ብቃት ትልቅ ድርሻ እንዳለው ቢታመንም፣ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ላይ ለመድረስ የሕዝብ እንቅስቃሴዎች፣ የማኅበረሰብ ተቋማት፣ የፖለቲካ ማኅበራት፣ የሠራተኞች ማኅበራት፣ የሴቶች እንቅስቃሴዎች፣ ተማሪዎች፣ የሙያ ማኅበራት፣ የሃይማኖት ተቋማት ሚና ወሳኝ ነው፡፡ 

በተጨማሪም የማኅበረ-ኢኮኖሚ መዋቅሮች፣ የሕዝብ ስብጥር፣ የመልክዐ ምድር አቀማመጥ በፖለቲካ ላይ የሚያሳርፈው ተጽእኖ እና ጥልቅ ብሔራዊ ታሪክና ባህል የዴሞክራሲ ፍላጎትን እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ላይ ለመድረስ መወጣት ያለብንን መሰናክሎች ቅርፅ የሚያስይዙ መሆናቸውን የፖለቲካ አመራሮችና የዐደባባይ ምሁራን አበክረው ያስገነዝባሉ፡፡ 

በዚህ አግባብ አገዛዙን ስንመለከት ብሔራዊ መግባባትን መሠረት ያደረገ የሽግግር ሥርዓት እንዲኖር በእውነተኛ ተቃዋሚ ፖለቲካ ማኅበራት፣ በማኅበረሰብ ተቋማት፣ በሃይማኖት ተቋማት ባገር ውስጥም ሆነ በውጭ በሚገኙ ምሁራን እና አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በተደጋጋሚ ቢጠየቅም በጉልበት ባገኘው የበላይነት ተጠቅሞ ራሱ በመረጠው የጥፋት ጎዳና ኢትዮጵያን ዐዘቅት ውስጥ እየከተታት ነው፡፡ መልካም ገጽታ ለመፍጠር/ለማስመሰል አልፎ አልፎ ጣል ጣል ካደረጋቸውና አሽመድምዶ ካስቀመጣቸው ግለሰቦች በስተቀር በማዕከላዊም ይሁን በክፍላተ ሀገራት በሚሰጡ የመንግሥት የፖለቲካም ሆነ የአስተዳደር ሹመቶች የሚመድባቸው ወንጀለኞችን፣ ተረኛ ጐሠኞችን/ኦነጋውያነን፣ በእምነት ይመሳሰሉኛል የሚላቸው አድርባዮችን ወይም የራሱን ድርጅት ሰዎች ነው፡፡ ለላንቲካ ያቋቋማቸው የዕርቅ፣ የድንበርና ሌሎችም ኮሚሽኖች ወይ በወንጀለኞች ወይ በተረኞች የተሞሉ አይደሉም ወይ? የፋሽቱን ወያኔ ዋና አርኪቴክት በዐባይ ግድብ ጉዳይ ሹመኛ ያደረገ ነውረኛ አገዛዝ ውስጥ ነው እኮ ያለነው፡፡ ሕዝቡና እውነተኛ ምሁራን ባገራችሁ ጉዳይ አያገባችሁም ተብለው ተገልለው የተቀመጡበትን ጊዜ ነው የሽግግር የምንለው? ስለሆነም አገዛዙ የሽግግር አስተዳደር ለመሆን ብቃት የለውም፡፡ የሽግግር ሂደት ምልክቶችም የሉም፡፡

7/ ኢትዮጵያ ከ27 ዓመታት በፊት እንደ ነቀርሳ በበቀሉባት የወያኔ ፋሺስቶች፣ ባለፉት 3 ዓመታት ደግሞ አጋንንታዊ ጠባይን ገንዘብ ባደረጉና የወያኔ ወራሽ በሆኑ ኦነጋዊ ናዚዎች ጐሠኛነት በሕግና በመዋቅር ተተክሎባት ለህልውናዋ እያጣጣረች ያለች አገር ናት፡፡ ጐሠኛነት የአብሮነት፣ የአንድነት፣ የእኩልነትና የሰላማዊ ሕይወት ጠንቅና መፈልፈያ በመሆኑ ዛሬ በጐሣ ፖለቲከኞች የተረጨው መርዝ አለመተማመንን፣መለያየትንና ጥላቻን አንግሦ አንዱ ማኅበረሰብ ለሌላው የህልውና ሥጋት እስከመሆን ደርሰናል፡፡ ለዓመታት ያመረቀዙ ቁስሎች (ቂምና በቀል) እስከ የሌለው ምሬትና መገፋት ይዘን እህህ እያልን እንገኛለን፡፡ በኢትዮጵያችን በሠራ አካላቷ የናኘው ሥር የሰደደ ደዌ አገራዊ ፈውስ ይፈልጋል፡፡ ለዚህም ፍትሕ የሚገኝበትና ዕርቅ የሚወርድበት የሽግግር የፍትሕ ሥርዓት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ባለፉት 30 ዓመታት የተፈጸሙ በደሎችና ግፎች ይፋ ወጥተው፣ እውነቱ ተነግሮ እንደ ጥፋቱ ክብደት ለፍርድ የሚቀርቡት ጉዳያቸው በነፃ ዳኝነት እንዲታይና ቅጣታቸውን እንዲቀበሉ፤ በዕርቅና ይቅርታ የሚታለፉም ካሉ እውነቱን አምነውና ተጸጽተው፣ የበደሉትን ክሠው የቀሙትን መልሰው መዝጊያ ማበጀት ያስፈልጋል፡፡ የዐቢይ አገዛዝ ይህንን ለማድረግ ፍላጎቱም ቁርጠኝነቱም የለውም፡፡ በራሱ ጉዳይ ዳኛ ለመሆን የሚያደርገው ሙከራ በየትኛውም መመዘኛ ተቀባይነት የለውም፡፡ እኔ እስከማውቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ በወያኔ ዘመንም ሆነ የወያኔ ወራሽ በሆነው የዐቢይ አገዛዝ ለተፈጸሙና አሁንም ለቀጠሉት ግፍና በደል ፈጻሚዎች በግልም ሆነ  በቡድን ደረጃ ይቅርታ አላደረገም፡፡ እንደዚህም ብሎ መገመት ስህተት ነው፡፡ ባጠቃላይ አገዛዙ ባመዛኙ ላገር የማይበጁና ከሥልጣኑም ውጭ የሆኑ የፖሊሲና የሕግ ለውጦች አድርጓል፡፡ ስለሆነም አገዛዙ የሽግግር አስተዳደር ለመሆን ብቃት የለውም፡፡ የሽግግር ሂደት ምልክቶችም የሉም፡፡

ሐ/ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት ሦስት ዓመታት ገደማ የታዩት ምስቅልቅሎች በሽግግር ሂደት የሚጠበቁ ናቸው? 

 • በሕግና በመንግሥት መዋቅር (በክፍላተ ሀገራት መስተዳድሮች) በድርጊት ወይም ሆን ብሎ በዝምታ የታገዘ በዜጎች ላይ የተፈጸመውና እየተፈጸመ ያለው ዘግናኝ እልቂት/የዘር ፍጅት፤
 • መንግሥት የለም ሊያስብል የሚችል ሥርዓተ አልበኝነት (የማዕከላዊ መንግሥት በእጅጉ መዳከም)፣ የሰላምና ጸጥታ መደፍረስ፤ 
 • የአገር መከላከያ፣ የፖሊስና የደኅንነት ኃይላትን በጐሣ በማደራጀት ራሱን በገዢነት የሰየመው ፓርቲ ጠበቃ ማድረግ፤
 • በየግዛቱ ‹ልዩ ኃይል› ከሚባለው ሕገ ወጥ አደረጃጀት ጀምሮ በአሸባሪነት የተሠማሩ የውንብድና ቡድኖች መስፋፋት፤ 
 • አገዛዛዊ ንቅዘት፣ ዝርፊያ፣ ቅጥ ያጣ የመሬት ወረራ፤ 
 • በጉልበት የመንግሥትን ሥልጣን በያዘው ፓርቲ (ኦሕዴድ) በኃይል የውስጥ ግዛት ማስፋፋትና መዋጥ፤ ለምርጫ በታለመ መልኩ የሕዝብ ስብጥርን መቀየርና መታወቂያ ማደል (በተለይ በአ.አ.)፣ በዚህም ድርጊት ዜጎችን ማፈናቀል፤ 
 • ብሔራዊ ምልክት የሆኑ ነባር ተቋማትን (የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ወዘተ.) የማዳከም፤ 
 • ብሔራዊ ቅርሶችን የማጥፋት፣ 

የፈረሱ ብሔራዊ ቅርሶች (በብሔራዊ ቅርስነት የተመዘገበው የደጃዝማች አስፋው ከበደ ቤት ሙሉ በሙሉ ፈርሷል (ለኦሮሚያ ወታደር ካምፕ መገንቢያ በሚል)፤ፈረንሳይ ሌጋሲዮን የሚገኘው የደጃዝማች አበራ ካሣ ቤት በእነ ታከለ ኩማ ፈርሷል፤ ሐረር የራስ መኮንን ሐውልት ፈርሷል፤ የጀጎል ግንብ ፈርሷል፤ አ.አ. ላ ጋር ባቡር ጣቢያ የሚገኘው ቡፌ ደ ላ ጋር ፈርሷል፤ሜክሲኮ ዐደባባይ ዋቢ ሸበሌ ሆቴል አጠገብ የሚገኘው የሎምባርዲያ ሕንፃ በከፊል ፈርሷል፤ከዳግማዊ ምንይልክ ቤተመንግሥት ብሔራዊ ምልክታችን የሆነው ታሪካዊው የአንበሳ ምልክት በፒኮክ ተቀይሯል)

የማፍረስ ሙከራ የተደረገባቸውና በተረኞች እንዳይሠሩ የተከለከሉ ብሔራዊ ቅርሶች (የኢትዮጵያ የመጀመሪያ ዘመናዊ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት – ቀዳማዊ ምንይልክ ት/ቤት ፤ የኢትዮጵያ የመጀመሪያው ሲኒማ ቤት (በተለምዶ ሰይጣን ቤት የሚባለው) ለማፍረስ ሙከራ ተደርጎ ነበር፤  የጥምቀት ማክበሪያ በሆነው በጃንሆይ ሜዳ የተፈጸመው ታሪክ የማጥፋት ተግባር፤ የአ.አ. ከተማ ስያሜ ባለቤት÷ የዓድዋ ጦርነት ስትራቴጂስት የዳግማዊ ምንይልክ ባለቤት የሆኑት የእቴጌ ጣይቱ መታሰቢያ ሐውልት እንዳይገነባ – የመሠረት ደንጊያ እንዲነሳ መደረጉ፤ ከግማሽ ምእተ ዓመት በላይ ያስቆጠረው ፒያሳ የሚገኘው አንበሳ ፋርማሲ፤ኦርየንታል ኦርቶዶክስ የሚባለው ድረ ገጽ በያዝነው የፈረንጆች ዓመት (2021) የመጀመሪያ ወር አክሱም ጽዮንን ለማፍረስ የተቃጣ ሙከራ እንደነበር ዘግቧል)

 • በዜጎች መካከል ልዩነትን የሚያጎሉ የጥላቻ ሐውልቶችን የማቆም፤ 
 • ከአመራር ብቃት ማነስ፣ ከተሳሳት የውጭ ፖሊሲ፣ ከዲፕሎማሲ ብቃት ማጣት የተነሳ ሀገር ባለቤት አልባ እስክትመስል የውጭ ጠላት መፈንጫ መሆን፤ 
 • ወያኔያዊ የፖለቲካ ባህል ቀጥሎ በፓርቲና በመንግሥት መካከል ልዩነት አለመኖር፣ የሕዝብን/የመንግሥትን ሀብት ለፓርቲ ጥቅም ማዋል፤ 
 • የፍትሕ አስተዳደር ሥርዓቱ ከዘመነ ወያኔም የከፋ መሆን፤ 
 • ባጠቃላይ በሁሉም መስክ በኦሕዴድ/ኦነግ የሚታየው ዓይን ያወጣ የተረኝነት መንፈስና የጐሣ መድልዎ ሥርዓት መንገሥ፤
 • ትጥቅ ይዞ ዜጎችን እየጨፈጨፈ በሽብር የተሠማራው ኦነግ በሕጋዊ የፖለቲካ ፓርቲነት ተመዝግቦ መንቀሳቀስ፤ 
 • የገዛ ራሱን ባለሥልጣናት ባደባባይ ስለ አገራዊ ጉዳይ አትናገሩ አትጻፉ ብሎ በፓርቲ ሹመኛ በኩል የሚሰጥ ማስጠንቀቂያ፣ ወዘተ. ከየት ወዴየት የሚደረግ ሽግግር ይሆን?

ዳንኤል እንዳለው እነዚህ ለአብነት ያህል ከላይ የዘረዘርናቸው በሙሉ በ‹‹ሽግግር ጊዜ›› የሚጠበቁና የሚያጋጥሙ ክስተቶች ናቸው?

እነ እስክንድርን ባስቸኳይ ልቀቁ!!! ነፃነት ለኅሊና እስረኞች!!! 

ኦነግ ያገታቸው ልጃገረድ ተማሪዎች የሚገኙበትን ሁናቴ ለቤተሰቦቻቸውና ለኢትዮጵያ ሕዝብ አሳውቁ፡፡

ሕወሓትን እና ኦነግን ሕገ ወጥ በማድረግና በአሸባሪነት በመፈረጅ የኢትዮጵያን የፖለቲካ መልክዐ ምድር አስተካክሉ፡፡

 

ዋቢ ጽሑፎችና የመረጃ ምንጮች፤

 1. From Authoritarian Rule to Democratic Governance: Learning from Political Leaders, Abraham F. Lowenthal and Sergio Bitar

International Institute for Democracy and Electoral Assistance 2015

International IDEA

Stromsborg, SE-103 34, STOCHOLM, SWEDEN

 1. The Features of Transitional Governance Today. First Edition, Emmanuel De Groof, 2019; Political Settlements Research Programme (PSRP), Global Justice Academy, School of Law, Old College, the University of Edinburgh, South Bridge, Edinburgh, EH89YL

Ethio 360 Media, Zare Min Ale Programme ‹‹ኢትዮጵያን የማፍረስ ደባ›› 12 Jan. 2021

Filed in: Amharic