>
5:26 pm - Monday September 15, 4087

ጠቅላዩ "የኦሮሞን ጥያቄ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ እየሰራን ነው" ሲሉ እኛ የሚገባን....?!? (ተፈራ ወንድማገኝ)

ጠቅላዩ “የኦሮሞን ጥያቄ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ እየሰራን ነው” ሲሉ እኛ የሚገባን….?!?

ተፈራ ወንድማገኝ 

* እነሆ. . .! *የኦሮሞ ልሒቅ በተለመደው መንገድ “ፊንፊኔ ኬኛ” በማለት የአዲስአበባን ባለቤትነት ለማረጋገጥ እንደሚቸገር ገብቶታል። ስልጣን እንደያዙ ሰሞን የነበረው የመጠቅለል አካሔድ ችኮላ ከቅራኔ በቀር መዋቅራዊ ለውጥ እንደማያመጣ በማመን የስልትና ስትራቴጂ ለውጥ አድርገዋል።
እንደቀደመው ጊዜ “የልዩ ጥቅም” አጀንዳን ማራገብ በመተው በተግባር ልዩ ጥቅምን ለማረጋገጥ የሚያስችል የመዋቅር ቁጥጥር እየተሠራ ነው።
የጉዞው “ሳይንሳዊነት” የስነህዝብ ምጣኔ ብልጫ በማረጋገጥ በህዝበ – ውሳኔ የኦሮሞ መሆኗን ማረጋገጥ ነው።
ዓቢይ አህመድ “የኦሮሞን ጥያቄ ሳይንሳዊ በመሆነ መንገድ እየሰራን ነው” ሲል ምንና የቱን ጥያቄ ነው?
“በአዲስአበባው የባልደራስ ንቅናቄ ጦርነት እንገባለን” ሲልስ ለምን?
“መንግስታችን ተነካ ብለው ከቡራዩ ወደአዲስአበባ የተነሱ ነበሩ” ማለትስ ምንድን ነው?
እነዚህና መሰል ጥያቄዎች እንዳሉ ሆነው ‘በሳይንሳዊ መንገድ’ እየተፈታ ያለ የኦሮሞ ጥያቄ በአዲስአበባ ደረጃ ያለው የልሒቃኑ ጥያቄና ተግባር ስለመሆኑ እንመልከተው።
በአዲስአበባ ባለቤትነት ላይ ያለው ሳይንሳዊ ምላሽ አካሔድ ፥ የተዋከበ የባለቤትነት ጥያቄን ማለዘብ፣ የኢኮኖሚና ፖለቲካ ቁጥጥርና የበላይነት ማምጣት፣ የህዝብ ቁጥር
ብልጫ ማምጣት እና በመጨረሻ ባለቤትነትን ማረጋገጥ ናቸው። ይህን ማሳኪያ ተብለው የተለዩ “ሳይንሳዊ” አካሔዶች ምንድን ናቸው?
1- የከተማዋን ቢሮክራሲ መቆጣጠር ይህ በከተማ አስተዳደሩ የሚገኙ 23 ሴክተር መሥሪያቤቶችን ቢሮክራሲያዊ አገልግሎት የመቆጣጠር አካሔድ ነው። ይህ በዋናነት ከሹመት ኮታ በላይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የኦሮሞ ሠራተኛ በቀበሌ ፣ወረዳ ፣ ክፍለ ከተማና ከተማ አስተዳደር ደረጃ እንዲቀጠር ማድረግን ያካተተ ሲሆን እስካሁን በአስር ሺህዎች ሠራተኛ ከኦሮሚያ መጥቶ እንዲቀጠር ተደርጓል። የከተማው ነዋሪ በየወረዳው ሲሔድ እያስተዋለው ያለ እዉነታ ነው። በተጨማሪም አዲስአበባ በሚገኙ የፌደራል ተቋማት ጭምር ከፍተኛ ቁጥር ያለው የኦሮሞ ሠራተኛ እንዲቀጠር ማድረግ ተችሏል። በገቢዎች መስሪያ ቤት ሲሆን የነበረው ማሳያ ነው።
2- በአዲስአበባ ለኦሮሞ ወጣቶች ብቻ የስራ እድል መፍጠር በከተማው የስራ እድል ፈጠራ ስም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወጣት አስገብቶ በተዘዋዋሪ ፈንድ የገንዘብ እና የመስሪያ ቦታ አቅርቦቶች ማሰማራት ÷ የነዋሪነት መታወቂያ መስጠት ሌላኛው ነው። እዚህ ላይ በችኮላው ዘመን ከሱማሊ አዋሳኝ አካባቢ እስከማጓጓዝ የተሠራበት ነው።በ2011 ብቻ ለ150ሺህ ወጣት የስራ እድል መፈጠሩ ተነግሯል ። በ2012 ወደ 250 ሺህ ህዝብ የስራ እድል ተፈጥሯል ተብሏል። በቀጣይ 280ሺህ ነው። እነደረጀ ገረፋ ደግሞ ከአሁኑ ኦሮሞ 40% ደረሰ የምትል ፕሮፖጋንዳ ጀምረዋል። የስራ እድልን ለማመቻቸት የነዋሪነት መታወቂያን በማደል በስፋት የተሠራበት ነው። በአዲስአበባ የሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች በቤት ቁጥራቸው የመታወቂያ ፈቃድ እንዲሠጥ ትብብር እንዲያደርጉ እየተደወለ እስከመጠየቅና ማደል ተችሏል።
3- የከተማዋን ቦታዎች ለኦሮሞ ማደል በከተማዋ ያሉ ክፍት ቦታዎች በባለመሬቶችና የከተማ ግብርና ተደራጁ በሚባሉ የኦሮሞ ወጣቶች ማስያዝ ሌላኛው መንገድ ነው። ይህ በእርግጥ በከተማ ዙሪያ ልዩ ዞን ጭምር የሚከናወን ነው። ይህ በተለይ በየመንደሩ በአረንጓዴ ልማት የተዘጋጁ ቦታዎች ሳይቀሩ በሚገቡ ወጣቶች እንዲያዙ ማድረግ ÷ ሌሎች በተለየ ካርታ የሌላቸው አካባቢዎች በከተማ ግብርና ተደራጅተናል በሚል ሰበብ በከተማዋ የተለያዩ ሰፈሮች ቦታዎች እየታጠሩ ነው።
4- የልማት ተፈናቃይ ማቋቋምን እንደምክንያት መጠቀም በልማት ተፈናቃይነት ተነስተዋል በሚባሉ ነዋሪዎች ስም የገንዘብና የመኖሪያ ቤት አቅርቦት መፈፀም ሌላኛው የስነህዝብ ምጣኔ ሚዛን መንገድ ነው። ለልማት ተፈናቃዮች ማቋቋሚያን እንዲያስፈፅም ተከፍቶ ጊዜው ቢያበቃም ስራውን እንዲቀጥል በተደረገው ፕሮጀክት ፅ/ቤት
አማካኝነት የ800 ሚሊዮን ብር በጀት ተይዞ የተሰራበት ነው።  የከተማዋ ህዝብ ከ1997 ጀምሮ ቆጥቦ ከሚጠባበቀው ቤት ውስጥ 23,000 ቤት (አንዳንዶች 13ሺህ መሆኑን ያነሳሉ) እንዲሁም 8ሺህ ንግድ ቤት በመግዛት እንዲከፋፈሉት ተደርጓል። በርካታ የንግድ ቤቶችም በተመሳሳይተገዝተው እየታደሉ ነው። እዚህ ላይ የተመዘገበ የልማት ተፈናቃይ ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ ካድሬና አመራሩም እንዲወስድ እየተደረገ ነው።በተጨማሪም በተፈናቃይነት ከተቀመጡት 7 መስፈርቶች 1 ብቻ – መታወቂያ- በማየት እየተሠራ ነው። መታወቂያ ደግሞ ይታደላል። አስር ሆነው ሔደው ለሚመዘገቡ ከቤት ተጨማሪ 2ሚሊዮን ብር “ለስራ መጀመሪያ” በሚል ይታደላል። ከዚህ ውስጥ 1ሚሊዮን የማይመለስ ነው አንዱ ይመለሳል ቢባልም የሚመለስበት መቆጣጠሪያ መንገድ የለም።ማቋቋሚያ ፅ/ቤቱ በተለይም “መሬቴ ሳይያዝ ክፍት ነው” ብለው ለሚያመለክቱ ሁሉ እንዲፈቀድላቸው ደብዳቤ በመፃፍ ከገዙት ባለይዞታዎች ጋር ከፍተኛ አተካራ ቢፈጥርም ከመወሰድ የሚድን አይደለም። በዚህ መንገድ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አካባቢዎች እንዲያዙ ማድረግ ተችሏል። የባሰው ጉዳይ ግን የሸዋ ኦሮሞዎች ራሳቸው ከአሩሲ ሙስሊም እያሰፈሩብን ነው የሚል ቅራኔ እንዲገቡ አድርጓል።
5- የቀበሌና የመንግስት ቤቶችን ማደልና የቤት እድሎችን ማመቻቸት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታና ምዝገባን በማስቆም : ያልተመዘገቡ የኦሮሞ ተወላጆች የሚገቡበትን ሁኔታ ማመቻቸት ሌላኛው ነው። ይሔ የቀበሌ ቤትና የመንግስት ቤቶች ኮርፖሬሽን ቤቶችን በሠራተኛነት ለተመዘገቡ የታደለውን ሳይጨምር ነው።
(ከዚህ ቀደም በከተማው ነዋሪ ቁጠባ የተሠራው የ”ኮየፈጨ ሳይት” ኮንዶሚንየም መኖሪያ ቤት አይተላለፍም የሚል አተካራ ከተከፈተ በኋላም እጣ ሲወጣ 60% ለኦሮሞ ተወላጆችወጣ ተብሏል።)
6- አዲስአበባን በኦሮሞ እሴቶች እንድታንፀባርቅ ማድረግ የኦሮሞ የማንነት እሴት የሚያንፀባርቁ ተቋማትን ማስገንባት – ይሔ በዋናነት በስፋት እየተሠራበት ያለ ነው።
በአንድ በኩል የኦሮሚያ ቤተመንግስት ግንባታ እንዲሁም የኦሮሞ የእደጥበብ ማዕከላት በሚል በሶስት ክፍለከተሞች እንዲሠራ ተወስኗል። የኦሮምኛ የትምህርት ተቋማትን በማስፋፋት በኩል እንዲሁ በርካታ ትምህርት ቤቶች እየሠሩ ነው። የከተማዋን የንግድ መኪናዎች ታርጋ (plate) በኦሮምያ ክልል (ኦሮ/OR) በማስደረግ ከተማዋን በኦሮሞ እሴት ማንነቶች እና መገለጫዎች የመቀየር ስራ አለ። የኢሬቻና መሰል በዓላት መምጣትና አደባባይ መሰየም የዚያ ውጤት ነው። ለአዲስአበባ መስራች እቴጌ ጣይቱ መታሰቢያ ከልክሎ በአርቲስት ሐጫሉ መታሰቢያ ድልድይ: መንገድ: ፓርክ መሰየም የስሜቱን ልዩነት ይጠቁማል።
7- በንግድና ቢዝነስ ከተማዋን መቆጣጠር በትራንስፖርት ÷ በኢንቨስትመንት ቦታ ÷ የመንግስት ግዢ ጨረታዎችን ለአንድ ወገን በማብዛት ÷ የፖለቲካ ቁጥጥሩን በኢኮኖሚ ቁጥጥር ብልጫ በማገዝ ተፅዕኖን የማሳደግ ስራም አለ። በዚህ ረገድ የኦሮሞ ባለሀብቶች ኦሮሞ ሠራተኞችን እያመጡ እንዲቀጥሩ ማድረግም አንዱ አማራጭ ተደርጓል። ይህ በተለይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መሠል የገንዘብ ተቋማትን በመቆጣጠር ገንዘብ ማበደር ÷ የገቢ ሰብሳቢ መስሪያ ቤቱን በመቆጣጠር ለራስ ወገን የግብር ጫና ሲቀነስ ለሌላው የመጫንና የማማረር ስራዎች ተገቢ ጆሮ ያጡ ስልቶች ናቸው። ገንዘብ ያላቸውና የሚሰጣቸው ሰዎች በከተማዋ ለሽያጭ የሚቀርቡ ቤቶችን እንዲገዙ ማድረግ ፥በተለይ ከሪል-ስቴት አልሚዎች ጋር በተያያዘ የተለያዩ አልሚዎች የዚህ አላማ ተሳታፊ እንዲሆኑ ከዱባይም ጭምር እንዲሳተፉ እየተደረገ ነው።
8- ብሔር አልባን ከብሔር ድምር ማውጣትም አንዱ ስልት ነው። ቀጣዩን የህዝብና ቤት ቆጠራ መሠረት በማድረግ በተለይ የከተማዋ ነዋሪ የብሔር ማንነትን ለመቀበል የማይፈልግ መሆኑን በማየት አንድም የጥምር ብሔር አማራጭና ብሔር የማይገለፅበት የመታወቂያ አማራጭ በማንሳት ከዚህ ቀደም ሳይወዱም ወደተለያዩ ብሔሮች የሚመዘገቡትን የመቀነስ አማራጭ ታስቧል። እንደዚያ ሲሆን በከተማዋ ከፍተኛው ብሔር ማንነው ሲባል ራሱን ያልመደበውን ስለሚቀንስ የቁጥር ጨዋታውን ያሳድጋል።
9- የሌላ ህዝብ መግቢያ አማራጮችን መዝጋት ይህ በተለይ በኢኮኖሚ ስደት ወደከተማዋ ገብተው የሚኖሩና በሒደት ወደቋሚ ነዋሪነት የሚለወጡበት መንገድ እንዲዘጋ የታሰበ ይመስላል። የጎዳና ልጆች ማንሳት ÷ የምሽት መጠጥ ቤቶች (clubs) ንግድ ስራ እንግልትና ክልከላዎች በዚህ በኩል ይጠቀሳሉ።
10- አዲስአበባ ተኮር ንቅናቄን መድፈቅ በፊንፊኔ መተካት ይህንን አላማ ሊያደናቅፉ የሚችሉ እንደባልደራስ ያሉ ንቅናቄዎች ላይ ጨካኝ እርምጃና ዛቻ ማድረግ የአላማውን ተፈፃሚነት የሚያግዝ ነው ። ይህ በተለይ የከተማዋን ወጣት የሚያንቀሳቅስ ተግባር በኦሮሞዎች የተጀመረውን እንቅስቃሴ የሚያስተጓጉል እርምጃ በመሆኑ ከጅምሩ የከተማዋን ወጣት ሰብስቦ የማሠር ፥ ለኦነግና መሰሎች የሚፈቀዱ ጉዳዮች በተለይ የመሰብሰብ ፥ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ፥ ጋዜጣዊ መግለጫ የመስጠት እና መሰል እንቅስቃሴዎችን መከልከልና ማስፈራራት ትልቅ ሥራ ተደርጎ ጠቅላይሚኒስትሩ ድረስ ማስፈራሪያ የተሰጠበት ነው። አገር ከሚገረምበት የእነ እስክንድር መንታ የመንግስት መርህ በተጨማሪ የአማራ ወጣት ማህበራት ስብሰባዎችን የማወክ ተግባርም የዚሁ አካል ነው። “አሁን እንኳ ለሳምንታት ከተደረገው የኦሮሚያ ጭፍጨፋ ይልቅ በመጀመሪያዋ ቀን ቄሮ ከተማ ውስጥ ገብቶ የፈፀመውን ቀውስ የአዲስአበባ አድርጎ ማጉላት ይቀላቸዋል።”
11- በአዲስአበባ ወንዝ ልማት የከተማዋን መስራች ህዝብ ከይዞታው ማንሳት ይህ 29 ቢሊዮን ብር በጀት ÷ 54 ኪሜ ርዝመት ÷ የ30ሺህ ህዝብ (ቤተሰብ?) መፈናቀል
የሚጠብቀው መርሃግብር በዚህች የአርሶአደርና ድሃ ከተሜ አገር ቅድሚያ ያገኘበት ጥበብ እንቆቅልሽ መሆኑ አያነጋግርም። “something that has nothing to do with the people stomach ” አይነት ለአይንና ጆሮ እንጂ ለሆድ የሚሆን ማባበያ ነው።
ሆኖም የከተማ ልምላሜና የስነውበት ጉዳዮች በጥቅሉ ደስ የሚያሰኙ ቢሆኑም የአጠቃላይ ምጣኔ ሀብት ለውጥ ተዛማጅ ተፅዕኖ ውጤት (spillover effect ) እንጂ ከመሠረታዊው የልማት ስራ የሚቀድሙ ሆነው ታቅዶ ተጀምሯል። የአዲስአበባ ህዝብ አንገብጋቢ ጥያቄ የሆነው ቤት ችላ ተብሎ ይህ ቅድሚያ ያዘ ? ለምን? ካልን የከተማዋ መስራች ህዝብ ቀድሞ የከተመው የወንዝ ዳርቻዎችን ተከትሎ የእንጦጦ ቤተመንግስትን ይዞ ነው። ይህ ሲወርድ ሲዋረድ የተላለፈና በትውልድ የተያዘ አካባቢ ስነልቦናዊ ትስስሩና የከተማ ባለቤትነት ስሜቱ ከፍተኛ ነው። ለስራ ጉዳይ ባለፉት 20 ዓመታት መጥቶ ኮንዶሚንየም ላይ ከሚኖረው በላይ ለመቶ አመታት በትውልድ ተዋረድ ተወልዶ ያደጉበት ይዞታ ትልቅ ትርጉም አለው። ይህንን ባለቤትና መስራች ነይ የሚል ህዝብ “ከሌሎቹ እንደአንዱ” ማድረግ ጠቃሚው መንገድ ተደርጓል። ከልማት ስራው ጎን ይህን ማድረግ ጥቅም አለው። ባለቤትና መጤ ÷ መስራችና ባይታወርነት በመኖሪያ መንደር መገለፁ ይቀራል።
12- ከተማ ዙሪያ ማፅዳት – ለገጣፎ ÷ ቡራዩ ÷ ወዘተ – ይህ አሁንም ዙሪያዋ በአንድ ብሔር ግልፅ ባለቤትነት የተከበበች አዲስአበባ ከተማ የመፍጠርና የኋላውን እሰጥአገባ ለመጫን የሚያግዝ ስልት ነው። ሌሎች ብሔሮችን በማስወጣት በግልፅ በኦሮሞ የተከበበች ደሴት ከሆነች የባለቤትነት ጥያቄው ላይ አስተዋፅኦ ያደርጋል። የከተማዋን ህዝብ በመከበብ ስነልቦና ለማጠር ይመቻል።
እነዚህ ሁሉ አንድ በአንድ ባለፈው ሁለት ዓመት እየተተገበሩ ያሉ ናቸው። የከተማውን ወጣትና ህዝብ በምላስ እየሸነገሉና እያባበሉ ዓላማን የማሳካት ሒደቱ
ተጠናክሯል።
ይህ ከአዲስአበባ ባለቤትነት ጋር በተያያዘ ሁለት አማራጭ ይፈጥራል።
1) የመጀመሪያው ይህ የስነህዝብ ስሌታዊ ሒደትና እሴታዊ ቁጥጥር ከኢኮኖሚና የፖለቲካ የበላይነት ጋር ሲዳመር ሌላው ከባለቤትነትና የብልጫ ስነልቦና ወርዶ ተፈቅዶለት የሚኖር መሆኑን ተቀብሎ እንዲኖር ያደርጋል። በዚህም በእኛ ስር በእኛ ፈቃድ ኑር የሚል መደምደሚያ ላይ ያደርሳል።
2) የተረጋገጠ የህዝብ ብልጫ ሲመጣ : አጨቃጫቂውን የባለቤትነት ጉዳይ በሪፍረንፈደም እንቋጨው የሚል አጀንዳ አንስቶ ማስወሰን ነው። “ሳይንሳዊ” ያስባለው አሁኑኑ ዝም ብሎ “የእኛ ነች” ÷ “ልዩ ጥቅም” ከሚል የፊትለፊት ልፊያና አቀራረብ ይልቅ ቀስ ብሎ ህዝብን በማስገባት ነዋሪ ይወስን የሚል ፖለቲካዊ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ነው።
አዳራሽህ ገብተህ መላውን አጢነው!!
Filed in: Amharic