>
5:33 pm - Sunday December 6, 6139

በኢትዮጵያ የጎሳ ፌዴራሊዝም፣ወይንስ የጎሳ አምባገነንት ?  (ደረጀ መላኩ - የሰብዓዊ መብት ተሟጋች )

በኢትዮጵያ የጎሳ ፌዴራሊዝም፣ወይንስ የጎሳ አምባገነንት ? 

ደረጀ መላኩ ( የሰብዓዊ መብት ተሟጋች )

Tilahungesses@gmail.com


መግቢያ

የኢትዮጵያ ህዝብ በኢህአዲግ ጭንብል ( ሽፋን) ለሃያ ሰባት አመታት እንደ ሰም አቅልጦ፣ እንደ ብረት ቀጥቅጦ ሲገዛው የነበረውን የወያኔ ግፈኛና አምባገነን መንግስት ከምኒልክ ቤተመንግስት ስልጣኑ አሽቀንጥሮ ከጣለው ካለፉት ወዲህ በትረስልጣኑን የጨበጠው የዶክተር አብይ መንግስት መሆኑ የታወቀ ጉዳይ ነው፡፡ ወይም ክቡር ዶክተር አብይ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር እንዲሆኑ ይሁንታ ተሰጥቷቸዋል፡፡ የወጡበት ፓርቲም ሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ ኢትዮጵያ ነጻ፣ ገለልተኛ፣ ፍትሃዊና ርትአዊ የምርጫ ውድድር እስክታካሂድ ድረስ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር እንዲሆኑ ይሁንታ ሰጥተዋቸው የነበረው በሚከተሉት ምክንያቶች እንደነበር ማስታወስ ይገባል፡፡

  • ዶክተር አብይ የዲሞክራቲክ መንግስት ለመመስረት ቃል ገብተው ስለነበር
  • በእስር ላይ የነበሩ የፖለቲካ አባላትና አመራሮች በይቅርታ እንዲፈቱ ስለፈቀዱ
  • በስደት የነበሩ ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ተቃዋሚዎች፣ ወደ ሀገር ቤት እንዳይገቡ በወያኔ የተከለከሉ ኢትዮጵያውያን  የኢትዮጵያን ምድር እንዲረግጡ ሁኔታዎችን በማመቻቸታቸው
  • ከኢትዮጵያ ውጭ በሚገኙ የተለያዩ የአለም ክፍሎች የፖለቲካ ድርጅቶችን ከፍተው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የፖለቲካ ሀይሎች በሀገር ውስጥ ቢሮአቸውን ከፍተው ለመንቀሳቀስ በመቻላቸው
  • ከኤርትራ ጋር እርቅ በመፍጠራቸው ወዘተ ወዘተ ይጠቀሳሉ፡፡

ሆኖም ግን ይሁንና ባለፉት ሃያ ሰባት አመታት ከባድ ግፍ የፈጸሙ( ኢሰብዓዊ ድርጊት የፈጸሙ)፣ የዚችን ታሪካዊት ሀገር እና ምዝብር ህዝቧን ለከትና ሞራል አልባ በሆነ ሁኔታ የዘረፉ፣ የወያኔ የፖለቲካ ፊትአውራሪዎች እና ጋሻ ጃግሬዎቻቸው አሁን ድረስ በፍትህ አደባባይ ሊቀርቡ ባለመቻላቸው ምክንያት መንግስትን የሚወቅሱ ኢትዮጵያውያን ሞልተወ ተርፈዋል፡፡ ( በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ መንግስት የሜቴኩን ጄኔራል ክንፈ፣ አቶ በረከት፣የሶማሌ ክልል ፕሬዜዴንት የነበሩትን አቶ አብዲን ጨምሮ ባለፉት 27 አመታት የወያኔ የግፍ አገዛዝ ስር በሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ ወንጀልና ዝርፊያ የተጠረጠሩ የቀድሞ ሹመኞችን ማሰሩ የሚያከራክር አይመስለኝም፡፡ ዛሬም ግን የወያኔ  የፖለቲካ ፊትአውራሪዎች እና ሌሎች ወንጀለኞች በፍትህ አደባባይ አልቆሙሙ የሚለው የኢትዮጵያ ህዝብ መሰረታዊ ጥያቄ ይመስለኛል፡፡)

ይህ በእንዲህ እንዳለ ህገመንግስቱ የሚቀየረው በመቃብሬ ላይ ነው በማለት የኢትዮጵያን ህዝብ ከባድ ሀዘን ውስጥ ዶሎ የነበረው የወያኔ አገዛዝ በጦር ሜዳ ትግል ስለተሸነፈ  ከነበረበት የመቀሌ ከተማ ወደሚሸሽበት ከሸሸ ወዲህ  የኢትዮጵያ ህገመንግስት በሰለጠነ መንገድ ስለመሻሻሉ፣ ሀገሪቱን እያደማት ስለሚገኘው የጎሳ ፖለቲካ በተመለከተ እልባት እንዴት ሊሰጠው ይቻለዋል ለሚለው ለኢትዮጵያ ህዝብ መሰረታዊ ጥያቄ ቢያንስ አሁን ድረስ ከመንግስት አኳያ ስለሚሰጠው መልስ ምንም አይነት ፍንጭ አለመታየቱ ሲታሰብ፣ በእውነቱ ለመናገር የኢትዮጵያን እድል አሳዛኝ ያደርገዋል፡፡ በነገራችን ላይ በአለም ላይ ካሉት ሀገራት መሃከል የጎሳ ፖለቲካ እውን የሆነው በኢትዮጵያ ምድር ላይ ብቻ መሆኑ እየታወቀ ማእከላዊ መንግስቱ ከዚህ ክፉ የፖለቲካ ደዌ ኢትዮጵያን ለምን እንደማይገላግላት ሳስበው ይገርመኛል፡፡ ያሳዝነኛል፡፡ ማእከላዊ መንግስቱ የራሱ መሰረታዊ ምክንያቶች ሊኖሩት ቢቻለውም፣  ለእኔ ምክንያቱ እንቆቅሎሽ ነው፡፡ በነገራችን ላይ እንደ ኦነግ እና ሌሎች መሰረታቸውን በጎሳ ላይ ያደረጉ የጎሳ ፖለቲካ ድርጅቶች የጎሳ ፖለቲካ ከኢትዮጵያ ምድር ላይ እንዲመክን ፍላጎት እንደሌላቸው በተለያዩ መንገዶች ማሳየታቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የማእከላዊ መንግስቱን ስልጣን የጨበጠው የኢትዮጵያ መንግስት ህገመንግስቱ ስለሚሻሻልበት እና የጎሳ ፖለቲካ በህግ ስለሚታገድበት ሁኔታ በተመለከተ ኢትዮጵያዊ ምሁራኖችን ቢያማክር፣ ጥናታዊ ጽሁፎቻቸውን ገቢራዊ ለማድረግ ቢሞክር ኢትዮጵያን ይታደጋታል ብዬ አስባለሁ፡፡ ኢትዮጵያ በጎሳ ፌዴራሊዝም ምክንያት ከደረሰባት መከራ ለመማር ሰላሳ አመታት በቂ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በግድ ቤቴ ካልደረሰ ካላለ በቀር በጎሳ ፌዴራሊዝም ምክንያት የተፈጸሙትን ሰብዓዊ ቀውሶች መረዳትና መገንዘብ ቢያቅተው የሰማው ይመስለኛል፡፡

ባለፉት ሃያዘጠኝ አመታት በጎሳ ፌዴራሊዝም ምክንያት፡

  • በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች እትብታቸው ከተቀበረበት፣ አፈር ገፍትው ከሚኖሩበት መንደር ተፈናቅለዋል፡፡
  • በብዙ የሀገሪቱ ክፍሎች ረብሻና ሁከት ተፈጥሯል
  • ዘግናኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ፣ ከእብድ ውሻ በከፉ ሰው መሳይ አውሬዎች ተፈጽሟል፡፡
  • ሞራል አልባ ዜጎች እንደ እንጉዳይ ተፈልፍለዋል  
  • ለከት የሌለው የሙስና ወንጀል የፈጸሙ ሰዎች ( ለአብነት ያህል አንዳንድ የመንግስት ባለስልጣናት የነበሩ እና የጥቅም ተጋሪዎቻቸው ነጋዴዎች ወይም በሌላ ሙያ  የተሰማሩ እንዲፈጠሩ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል፡፡

የጎሳ ፌዴራሊዝም መሰረታዊ ችግሮች 

በእኔ የግል አስተያየት ባለፉት ሶስት አስርተ አመታት በኢትዮጵያ ምድር የሰፈነው የጎሳ ፌዴራሊዝም ስርአት  በሚከተሉት መሰረታዊ ችግሮች ታጅሏል ብዬ አስባለሁ

  • የጎሳ ፌዴራሊዝም ስርአት በኢትዮጵያ ህዝብ ጫንቃ ላይ የተጫነ እንጂ በህዝብ ይሁንታ ወይም ፍላጎት ላይ የተመሰረተ አይዶሎም ( የኢትዮጵያ ህዝብ የጎሳ ፌዴራሊዝም የሚጠቅመው ወይም የሚጎዳው ስለመሆኑ በነጻነት አልተጠየቀም፡፡)
  • በክልሎችና በፌዴራል መንግስቱ መሃከል ያለው የስልጣን ሀይል ሚዛኑን የጠበቀ አልነበረም
  • የጎሳ ፌዴራል ስርአቱ ምሉሄበክሉሄ የሆነ ዲሞክራቲክ ስርአት ማንበር አልሆነለትም
  • ማለቂያ የሌለው የዞን እና የክልል አስተዳደር ይገባኛል ጥያቄዎች የጎሳ ፌዴራሊዝም የተከለብን ነቀርሳ ነው፡፡
  • የጎሳ ፌዴራሊዝም ውህዳን የሆኑ ኢትዮጵያውያንን ባይተዋር ያደረገ ነው፡

በኢትዮጵያ የጎሳ ፌዴራሊዝም ጽንሰ ሃሳብ ያስተዋወቀው ማን ነው ? እንዴትና ለምን አላማ ነበር ገቢራዊ እንዲሆን የተፈለገው ? የጎሳ ፌዴራሊዝም በኢትዮጵያ እውን እንዲሆን ሁነኛውን ሚና የተጫወቱት በአልባኒያ የኮሚኒዝም ፍልስፍና የሰከሩት የሕውሃት ወይም ወያኔ አመራሮች ነበሩ፡፡ ዋነኛ አላማቸው ደግሞ ‹‹ ትግራይን›› ከ ‹‹ ኢትዮጵያ›› ነጻ በማውጣት ‹‹ ነጻ የትግራይን መንግስት ›› ለመመስረት ነበር፡፡ ሆኖም ግን በግዜው በነበረው የስልጣን ክፍተት በመጠቀም የኢትዮጵያ ገዢ ለመሆን ወግ ደረሳቸው፡ ወይም ‹‹ የትግራይ ትግሪኝ መንግስት ›› የሚለውን ህልማቸውን ለግዜው ገሸሽ በማድረግ ከሌሎች አጋሮቻቸው ጋር በመሆን ኢህአዲግን ከመሰረቱ በኋላ ኢትዮጵያን ለሃያ ሰባት አመታት መግዛታቸው የቅርብ ግዚ መራር ሀቅ ነው፡፡ በርካታ ምሁራን የተለያዩ ሀሳቦችን በማቅረብ ቢከራከሩም ( የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት የኢትዮጵያን እምቅ የተፈጥሮ ሀብት እና ገንዘብ ጥቅም ላይ በማዋል የትግራይን ደረቅ መሬት ስለማልማቱ፣ አጠቃላይ የትግራይን ህዝብ ስለመጥቀሙ ማለቴ ነው) የትግራዩ ነጻ አውጪ ድርጅት ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ኢንዱስትሪዎች በትግራይ መሬት ላይ ሰርቷል፡፡ የመገናኛ አውታሮች ዘርግቷል፡ የማህበራዊ ተቋማት ገንብቷል፡፡ እርግጥ ነው ይገባኛል ከ4ሚሊዮን በላይ የሚሆነውን የትግራይ ክልል ወገናችን ሁሉ አልፎለታል ብዬ የማስብ ተላላ አይደለሁም፡፡ ነብሳቸውን ይማርና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ አባት የነበሩት ታላቁ የኢትየዮጵያ ልጅ በአንድ ወቅት ባቀረቡት መጣጥፋቸው ላይ እንዳብራሩት የኢትዮጵያ ሀብት ሙሉ ትግራይን ዲታ ለማድረግ አይበቃም፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ኤፈርት የተባለው ድርጅት ( መሪዎቹ የትግራይ ነጻ አውጪ የፖለቲካ ፊትአውራሪዎች ነበሩ) ብቻውን ዘመናዊ ትምህርት ቤቶችንና ክሊኒኮችን በመላው የጥግራይ ወረዳዎች ሰርቷል፡፡ በርካታ ፋብሪካዎችና የትራንስፖርት ማመላለሻ ድርጅቶች ባለቤት ነው፡፡ በአጭሩ የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት የፖለቲካ ፊተአውራዎችና የፖለቲካ ሸሪኮቻቸው የኢትዮጵያ ጌቶች ለመሆን ከበቁ ወዲህ አዱኛ ቤታቸው ገብታለች፡፡

   ይህ በእንዲህ እንዳለ በርካታ የፖለቲካ ጠበብት በጥናታቸው እንደደረሱበት ከሆነ የጎሳ ፌዴራሊዝም በኢትዮጵያ እውን እንዲሆን ተፈልጎ የነበረው በሁለት መሰረታዊ ምክንያቶች ነበር፡፡ እነኚህም፡-

  1. ህውሀት ወይም ወያኔ የሥታሊን ዶግማ ከሆነው ማለትም የራስን እድል በራስ መወሰን ጽንሰ ሀሳብ መማር አለመቻል( የብሔር-ብሔረሰቦች የራስን እድል በራስ መወሰን እሰከመገንጠል የሚለውን ) ህውሃት ለኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ችግር መፍትሔው የስታሊን አስተምህሮ ብቻ ነው ብሎ ማመኑ ሌላው ችግር ነበር፡፡ አንተ ያለህ መሳሪያ መዶሻ ብቻ ከሆነ ለችግሮች ሁሉ መፍትሔው ሚስማር ነው ብልህ እንደማሰብ ማለት ነው፡፡ ለዚህም ነው የጆሴፍ ስታሊን አስተምህሮ የሆነው ‹‹ የራስን እድል በራስ መወሰን እሰከመገንጠል ›› የሚለው አደገኛ ጽንሰ ሀሳብ በኢትዮጵያ ህገ መንግስት ላይ እንዲሰፍር የተደረገው››  በነገራችን ላይ በአለም ላይ ካሉት ሀገራት ሁሉ ‹‹ የራስን እድል በራስ መወሰን እስከመገንጠል ›› የሚለው ጽንሰ ሃሳብ የሰፈረው በሀገራችን ኢትዮጵያ ህገ መንግስት ላይ ብቻ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ እንቅልፍ ሊነሳቸው ይገባል ባይ ነኝ፡፡

የህውሀት መሪዎች ምን ያህል ግትር አቋም እንደነበራቸው ለማሳየት ይረዳ ዘንድ አሌክስ በቀለ የተባሉ ምሁር በእንግሊዝኛ ቋንቋ ካቀረቡት የጥናት ጽሁፍ ላይ የሚከተለውን እጠቅሳለሁ፡፡

 

Who introduced this concept of Ethnic Federalism to Ethiopia, how, and for what purpose is determinative of its outcome for its subjects. It was introduced by the confessed Albanian type communist—the TPLF. Its goal was liberating Tigrai from the State of Ethiopia, and establishing an independent state of Tigray. TPLF, because of the power vacuum then created, became an opportunistic ruler of Ethiopia, with intent to develop Tigrai with the vast resources of the country. Hence, the Ethnic Federalism was the result of two complementary motives: one is TPLF’s incapability to unlearn its Stalinist dogma of the “the right of nations and nationalities to self determination up to and including secession.” Fresh out of the jungle, with no other experience in governance, or substantial reading in Western states craft and jurisprudence, TPLF believed this Stalinist dogma was the ostensible solution to all the ills our country has. As they say, “when the only tool you have is a hammer you start to think the solution to every problem is a nail.” Hence that jaded and obsolete Stalinist dogma became a constitutional mandate, making Ethiopia the only foolish country that constitutionalized session ( Alex Bekale)

  1. በጎሳ ፌዴራሊዝም ስም የወያኔን የበላይነት ለማስፈን፣ ሁላችንም እንደምናስታውሰው በኢትዮጵያ ክልላዊ ግዘቶች ወይም የጎሳ ፌዴሬሽን ውስጥ የወያኔ የበላይነት እንደነበር የሚያወሱ ዜናዎችና ዘገባዎች ከ 2010 ዓ.ም. ወዲህ ባሉ የተለያዩ ጊዜያት መሰማቱን እናስታውሳለን፡፡ በርግጥ የትግራዩ ነጻ አውጪ ድርጅት እንደው ዝም ብሎ ከመሬት ተነስቶ አልነበረም የበላይነቱን የተጎናጸፈው በዋነኝነት በራሱ አምሳል የቀረጻቸውን ሰዎች በየክልሉ በረቀቀ መንገድ ለማስቀመጥ በመቻሉ ነበር፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ  የኢትዮጵያ ህዝብ የጎሳ ፌዴራሊዝም ይጠቅመኛል ወይም አይጠቅመኝም ለማለት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ህዝባዊ ውሳኔ እንዳላደረገ ማስተዋሉ ተገቢ ሳይሆን አይቀርም፡፡ እንዲሁም የጎሳ ፌዴራሊዝም በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ በሃይል የተጫነ ሰለመሆኑ ቢጻፍ ስህተት አይመስለኝም፡፡ ስህተት የሚል ሰው ካለ ሊያስረዳን ይቻለዋል፡፡ ከዚህ ባሻግር ባለፉት ሃያ ሰባት ( 27) አመታት ኢትዮጵያውያን ከጎሳ ፌዴራሊዝምና ከአምባገነኑ የጎሳ አገዛዝ ከነበረው የወያኔ ቡድን የተረፋቸው ነገር ቢኖር ሽብር፣ የጭካኔ አገዛዝ፣ የሀገር ሀብት ዝርፊያ ነበር፡፡ በአጭሩ የጎሳ ፌዴራሊዝም በኢትዮጵያ ምንም አይነት ጥቅም አልሰጣትም፡፡ ወይም ኢትዮጵያን የዋይታና የሰቆቃ ምድር እንድትሆን ነው ያደረጋት፡፡ ተድላና ደስታ አመጣልን የሚሉ ካሉ በሃሳብ ሊሞግቱን ይቻላቸዋል፡፡

ሌላው የጎሳ ፖለቲካ ያመጣብን ራስ ምታት ቢኖር የመንግስትና የፓርቲ ስራ እንዲደበላለቅ የማድረጉ መራር ሁነት ነው፡፡ ከዚህ በሻግር ቀደም ብዬ ለመነካካት እንደሞከርኩት በፌዴራል መንግስቱና በክልሎች መሃከል የነበረው ግንኙነት ሚዛኑን የጠበቀ አልነበረም፡፡ በሌላ አነጋገር የፌደራል ማእከላዊ መንግስቱና የክልል መስተዳድሮች የነበራቸው ስልጣን ሚዛናዊ አልነበረም፡፡ ባለፉት ሃያሰባት አመታት የወያኔ የፖለቲካ ፊትአውራሪዎች በስውርም በግላጭ በክልል መስተዳድሮች ላይ ያደርጉት የነበረው ጣልቃገብነት የታወቀ በመሆኑ እዚህ ላይ ማንሳቱ አንባቢውን ማሰልቸት ስለመሰለኝ ትቼዋለሁ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፉት ሁለት አመታት በትረ ስልጣኑን የጨበጠው የብልጽግና መንግስት በክልሎች ጉዳይ ጣልቃ ስለመግባቱ ወይም አለመግባቱ ለመተቸት ጊዜው ገና መሰለኝ፡፡ ለማናቸውም ባለፉት ሁለትና ሶስት አመታት በትግራይ መቀሌ የነበረውን የወያኔ ህገወጥ ናእና ወንጀለኛ ቡድን ያለፌዴራል መንግስቱ እውቅና ክልላዊ ምርጫ እስከሚያካሂድ ድረስ በክልሉ ጉዳይ ጣልቃ አልገባም ነበር፡፡ የፌዴራል መንግስቱ በብዙ መልኩ ትእግስተኝነቱን አሳይቶ ነበር፡፡ በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች አስከፊ የሰብዓዊ መብት የሚጥሱ ጽንፈኛ እና የተደራጁ ወንጀለኞችን ለመቅጣት እንኳን የክልል መስተዳድሮችን ፈቃድ እየጠየቀ ነበር ወታደሮችን የሚልከው፡፡ ለማናቸውም ለወደፊቱ የጎሳ ፖለቲካ በሌላ ዲሞክራቲክ የፖለቲካ እሳቤ ካልተቀየረ የነበረው ችግር ተመልሶ እንዳያገረሽ በብርቱ እሰጋለሁ፡፡ በነገራችን ላይ ወያኔ ስልጣኑን ለማስጠበቅ እንዲቻለው ባለፉት ሃያሰባት አመታት ልዩነትን ብቻ ሲሰብክ እንደነበር፣ ኢትዮጵያውያን፣ ከኢትዮጵያዊነት ማንነታቸው ይልቅ በጎሳ ማንነታቸው ላይ እንዲያተኩሩ ቆላ መውረዱን፣ደጋ መውጣቱን ማስታወሱ ብልህነት ነው፡፡ ከዚህ ባሻግር ወያኔ የፌዴራል መንግስቱ ዋነኛ ማእከል ነበር፡፡ ፍጹማዊም ስልጣን ነበረው፡፡ አምባገነናዊ ስልጣኑንም ለማስጠበቅ ግዙፍ ወታደራዊ ሃይል ገንብቶም ነበር፡፡ ከማእከላዊ የመንግስት ልጣኑም ተሸቀንጥሮ ከወደቀ በኋላ በትግራይ ክልል ግዙፍ ወታደራዊ ሀይል ገንብቶ ተቀናቃኝ የሚለውን ክልል እና የፌዴራል መንግስቱን ለማስፈራራት ሞክሮም ነበር፡፡ ማስፈራራት ብቻ ሳይሆን  በመጨረሻም በፌዴራል መንግስቱ ላይ ጦርነት አውጆ መቀመጫውን መቀሌ ጨምሮ ሌሎች ወታደራዊ ካምፖቹን ለቆ ጠፍቷል፡፡  የመንግስት የዜና አውታሮች የመከላከያ ምንጮችን ዋቢ አድርገው እንደሚዘግቡት ከሆነ ገሚሱ የወያኔ የፖለቲካ ፊትአውራሪዎች እጅ ሰጥተዋል ወይም በጦርነት መሃል ህይወታቸው አለፏል፡፡

ከሶስት አመት በፊት ( በ2010 ዓ.ም. ማለቴ ነው) ከምኒልክ ቤተመንግስት የተባረረው የወያኔ አገዛዝ፣ በ2013 ዓ.ም. ደግሞ ከክልላዊ መስተዳድርነቱ በጦርነት ሽንፈት ምክንያት የለቀቀው የወያኔ ቡድን ዛሬ ከኢትዮጵያ የፖለቲካ አውድ ገሸሽ እንዳለ ቢታመንም ፣ ወያኔና የፖለቲካ ሸሪኮቹ ያጸደቁት ህገመንግስት እና የጎሳ ፖለቲካ ዛሬን ስራ ላይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ህገመንግስቱ ስለሚሻሻልበት ሁኔታ፣ እንዲሁም የጎሳ ፖለቲካ በህግ መሰረት የሚመክንበትን መንገድ በተመለከተ ያለውን አቋም ለኢትዮጵያ ህዝብ በግልጽ ባለመናገሩ ብዙዎችን ከባድ ሃሳብ ውስጥ የዶለ ይመስለኛል፡፡ ኢትዮጵያ አንድ ጠንካረና ዲሞክራቲክ ማእከላዊ የፌዴራል መንግስትና ነጻነታቸውን የጠበቁ፣ ለፌዴራል መንግስቱ ስጋት ያልሆኑ ክልሎች ያስፈልጓታል፡፡ ይህ የቅንጦት ሳይሆን የሕልውና ጉዳይ ነው፡፡ እንደቀደመው የወያኔ አገዛዝ የአንድ ፓርቲ የበላይነት የሰፈነባት ኢትዮጵያ፣ በሌላው የሳንቲሙ ግልባጭ ደግሞ ለፌዴራል መንግስት የማይታዘዝ ክልል ከዲምክራቲክ አስተሳሰብ ውጪ ነው፡፡ ብዬ አስባለሁ፡፡ እንኳን እኛ ገና ከመሬት ያልተነሳነው ይቅርና የአለም ሀገራት ሁሉ የዲሞክራቲክ ተምሳሌት በሆነችው የተባበረችው አሜሪካ የከተሰውን ከአለም የመገናኛ ብዙሃን ዘገባ የተከታተልን ይመስለኛል፡፡ በአለም በታወቁ አለምአቀፍ የዜና አውታሮች በቴሌቪዥን መስኮት እንደተከታተልነው ፕሬዜዴንት ትራምፕ በዲሞክራቲክ የምርጫ ውድድር ላይ ቀርበው የአሜሪካ ህዝብ ድምጹን ስለነፈጋቸው፣ ያቺን የአለም የዒኮኖሚና የፖለቲካ ሞተር የሆነችን ሀገር ዳግም ለመምራት አልተደሉም፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ከአሜሪካ የፖለቲካ ባህል ፍጹም ተጻራሪ በሆነ መልኩ የምርጫውን ውጤት እለቀበልም በማለት በአደባባይ ደነፉ፡፡ ይህም ብቻ አልነበረም ታህሳስ 28 ቀን 2013 ዓ.ም. የአሜሪካ ፖለቲካ ማእከል የሆነውን ካፒታል ሆልን በደጋፊዎቻቸው አስወረሩ፡፡ ውጤቱን የምታውቁት ይመስለኛል፡፡ ሀገሪቱ አሜሪካ በመሆኗ የተጠናከሩ የዲሞክራቲክ ተቋማት ስላሏት መንግስቷ አልተናጋም፡፡ ከዚህ የምንረዳው ቁምነገር ቢኖር ከዲሞክራሲ እና ነጻነት ተጻራሪ የሆነ ሁሉ ጠቃሚ አለመሆኑን ነው፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያ መንግስት ለግለሰብ ነጻነትና ዲሞክራሲ፣የህግ የበላይነትና ሰብዓዊ መብቶች መከበር በእውነት መሰረት ላይ ሆኖ እንዲሰራ እንማጸናል፡፡ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ባለፉት ሃያ ሰባት አመታት የሄዱበትን አሜኬላ ጎዳና ዳግም ማየት አይሹም፡፡ በነገራችን ላይ ባለፉት ሃያ ሰባት አመታት የኢትዮጵያ ችግር የነበረው የጎሳ ፌዴራሊዝም ችግር ብቻ አልነበረም፤ በአንጻሩ የጎሳ አምባገነንት ጭምር እንጂ፡፡ እባካችሁን አውቀን እንታረም፡፡

ያላወቁ አለቁ ነበረ ተረቱ፣

እያወቁ ማለቅ መጣ በሰአቱ ፡፡ የሚለው ብሂል እንዳይደርስብን እንጠንቀቅ፡፡

-ሌላው የጎሳ ፌዴራሊዝም መሰረታዊ ችግር ነው ብዬ የማነሳው ነጥብ ቢኖር የጎሳ ፖለቲካ ህዝብን ከማረጋጋት በተቃራኒው ህዝብን ያለመረጋጋት ባህሪ አለው ብዬ አስባለሁ፡፡ በጎሳ አጥር በታጠሩ ክልሎች ውስጥ ነዋሪ የሆነ የሌላ አካባቢ ተወላጅ ነኝ ብሎ የሚያስብ ስው ወይም ዜጋ በዛ የጎሳ አጥር ውስጥ ገበሬ ከሆነ እርሻውን በትጋት አያከናውንም፡፡ ነጋዴም ከሆነ ከዛሬ ነገ ንብረቴ በነውጠኞች ይቃጠል ይሆን ? ይዘረፍ ይሆን ? በማለት ኑሮው ኑሮ ከተባለ ማለቴ ነው የቆቅ ይሆናል፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ባለች ሀገር ከሰማኒያ በላይ ቋንቋዎች በሚነገርባት ሀገር፣ ህገመንግስታዊ መተማመን ያለው የራስን እድል በራስ የመወሰን እስከመገንጠል የሚል አንቀጽ ማስቀመጥ ለሀገሪቱ ብሔራዊ አደጋን የሚጋብዝ ነው፡፡

In a country like ours, where there are more than eighty linguistic groups, constitutionally guaranteeing the right to self determination up to and including secession is a national nightmare

ለአብነት ያህል የክቡር ዶክተር አብይ መንግስት በህገመንግስቱ በሰፈረው መሰረት የሢዳማ ህዝብ ላቀረበው የክልል እንሁን ጥያቄ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት እንዲከበር ፈቀደ፡፡ ይሄን ተከትሎ የሢዳማ ህዝብ በሰጠው ህዘበ ውሳኔ መሰረት የሲዳማ ክልል እውን ሆነ፡፡  በሳምንታት እድሜ ውስጥ የወላይታ ተወላጅ ኤሊቶች ላቀረቡት የክልል እንሁን ጥያቄ  ምላሹ የሀይል እርምጃ እንደነበር የሚያሳዩ የመገናኛ ብዙሃን ዘገባዎች ነበሩ፡፡ ነገሩ በዚህ ብቻ አላበቃም፡፡ በተለይም በደቡብ የኢትዮጵያ ክፍሎች ከ17 በላይ የዞን፣ክልል፣ ወረዳ መስተዳድር ይገባናል በማለት ጥያቄ የሚያቀርቡ ቡድኖች አሉ፡፡ ይህ እንግዲህ የራስን እድል በራስ መወሰን እስከመገንጠል የሚለው የክልሎች ጥያቄ ከመምጣቱ በፊት ያሉ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ በነገራችን ላይ የክልል እንሁን ጥያቄ፣ ወይም የዞን እና ልዩ ወረዳ አስተዳደር ጥያቄዎች ማለቂያ የላቸውም፡፡ የሚበጀን ይህን የተጠመደብንን ግዜውን እየጠበቀ የሚፈነዳ ፈንጂ በሰለጠነና ዲሞክራቲክ ዘዴ ማምከን ነው፡፡( አንቀጽ 39 የራስን እድል በራስ መወሰን እስከመገንጠል የሚለው አንቀጽ ለኢትዮጵያ እንደ ብሔራዊ አደጋ የሚቆጠር በመሆኑ መንግስትም ሆነ የፖለቲካ ተፎካካሪ ድርጅቶች በብርቱ ሊመክሩበት ይገባል)

በመጨረሻ ማንሳት የምፈልገው ( እንደ ቀላል ጉዳይ አይቆጠርም) በኢትዮጵያ የሰፈነው የጎሳ ፌዴራሊዝም ከዲሞክራቲክ አስተምህሮ ተጻራሪ የመሆኑ ጉዳይ ነው፡፡ ሁላችንም እንደምናስታውሰው የጎሳ ፌዴራሊዝም በኢትዮጵያ በዋነኛነት እውን እንዲሆን የተደረገው ጸረዲሞክራቲክ በሆነው አምባገነኑ የጎሳ አገዛዝ ወያኔ ነበር፡፡ የወያኔ የጎሳ ፌዴሬሽን ከዲሞክራቲክ መርህ ጋር የሚጣጣም አይደለም፡፡ ሁላችንም በአትኩሮትና ምክንያታዊ ሆነን የፌዴራል ስርአትን እንድንመረምር በአክብሮት አስታውሳለሁ፡፡ የፌዴራል ስርአት ከዲምክራቲክ ፍልስፍና አኳያ ገቢራዊ መሆን የሚችል ነው፡፡ የፌዴራል ስርአት የሰለጠነ የመንግስት አወቃቀር ነው፡፡ የፌዴራል ስርአት ለህዝብ ነጻነትን፣ እከሉነትን ለማጎናጸፍ በእጅጉ ይረዳል፡፡ መሰረቱን ጎሳ ላይ ያደረገ የፌዴራል ስርአት ግን ከዲሞክራቲክ ጽንሰ ሃሳብ የራቀ በመሆኑ አደጋን ይጋብዛል፡፡

እስቲ አንባቢውን አንድ ቀላል ጥያቄ ላቅርብለት፡፡ አረ ለመሆኑ የትኛው የኢትዮጵያ ክልል ነው የግለሰብ ነጻነትን ምሉሄ በክሉሄ በሆነ ሁኔታ ማስጠበቅ የሆነለት ? መልሱን በያላችሁበት ተወያዩበት፡፡ በእኔ በኩል አንድም ክልል ማግኘት አልቻልኩም፡፡ ምክንያቴን ዝቅ ብዬ ለማብራራት እሞክራለሁ፡፡ በሚከተለው ነጥብ ልጀምር፡፡ በበዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ውህዳን ዜጎች በኢትዮጵያ ይኖራሉ፡፡ እነኚህ ዜጎች ራሳቸው እንደ ኢትዮጵያዊ አድረገው ነው የሚቆጥሩት፡፡ ለአብነት ያህል አንዳንዶች እናታቸው ጎጃም ምድር የተወለዱ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ አባታቸው ደግሞ በቾ ሊሆን ይችላል፡፡ ወይም አባታቸው አድዋ ትግራይ፣ እናታቸው ደግሞ አገና ጉራጌ ምድር ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እንዲህ አይነት ከውህዳን ቤተሰብ የተገኙ ዜጎች ራሳቸውን አምሃራ፣ ኦሮሞ ወይም ትግራይ ብለው በመጥራት አባታቸውን ወይም እናታቸውን ማስቀየም አይፈልጉም፡፡ በአጭሩ እንዲህ አይነት ውህዳን ኢትዮጵያዊ ዜጎች በጎሳ ክልሎች ያላቸው መብት ምን እንደሆነ አይታወቅም፡፡ በአጭሩ በጎሳ ክልሎች ህገመንግስት መሰረት የግለሰብ ነጻነታቸው ተገፏል፡፡ ኑሮአቸው እንደ ቆቅ ነው፡፡ሽብርና እረብሻ በተነሳ ቁጥር የጥቃት ሰብዝ ይመዘዝባቸዋል፡፡ በመንግስት የስራ መስክ ለመሰማራት ውጣውረድ አለባቸው፡፡ የአካባቢውን ቋንቋ ባለመናገራቸው፣ የክልሉ ጎሳ ተወላጅ ባለመሆናቸው ብቻ የእንጀራ ገመዳቸው የተበጠሰ ውህዳንን ቤት ይቁጠራቸው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በአንድ ክልል ውስጥ ለዘመናት የኖሩ፣ የክልሉን ቋንቋ የሚናገሩ ሆኖም ግን ቁጥራቸው አነስተኛ የሆኑ ዜጎች፣ከክልሉ ተወላጆች አንጻር ያላቸው መብት ሲታሰብ አሳሳቢ ነው፡፡ ለአብነት ያህል መጤ በሚል ወፍዘራሽ ቋንቋ ከእርሻ ቦታቸው ይፈናቀላሉ፣ ነግደው ሰርተው ከሚኖሩበት ከተማና መንደር ይባረራሉ፡፡ ይሄም ብቻ አይደለም በጎሳ ፖለቲካ አቅላቸውን የሳቱ የከንቱ ከንቱዎች በሚሰነዝሩባቸው የሃይል እርምጃ የሚገደሉ፣አካለ ጎዶሎ የሚሆኑ በርካቶች ናቸው፡፡ ባለፉት ሃያዘጠኝ አመታት ከአርባጉጉ አሰቦት ገዳም እስከ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ መተክል ዞን ያየነው መራር ሀቅ ይሄው ነው፡፡

በዲሞክራቲክ የፌዴራል ስርአት ውስጥ ያሉ ጎሳዎች ወይም ዜጎች የፌዴራል መንግስቱ ዜጎች ናቸው፡፡ ማናቸውንም የዜግነት መብታቸውን የሚገፍ ክልል ካለ የፌዴራል መንግስቱን እንደተጋፋ ይቆጠራል፡፡ የዜግነት መብትን የሚገፍ ክልል ካለ በፌዴራል መንግስቱ መጠየቅ አለበት፡፡ ይህን የዜግነት መብትን በሁሉም ክልሎች ውስጥ ለማስከበር ግን የፌዴራል መንግስቱ ጠንካራና ዲሞክራቲክ መርህን የተከተለ መሆን ይገባዋል፡፡ ከዚሁ ባሻግር ሁሉም ክልሎች በህጋቸው ውስጥ የዜግነት መብትን የሚጠቅሱ አንቀጾችን ማካተት አለባቸው፡፡ ማካተት ብቻ ሳይሆን የግለሰብ ወይም የዜግነት መብቶችን ማክበር አለባቸው፡፡ በሌላ አነጋገር ለመሰራተዊ የሰብዓዊ መብቶች መከበር እውቅናና ከለላ መስጠት ግዴታቸው ነው፡፡ ሆኖም ግን በኢትዮጵያ የክልል መስተዳድሮች ውስጥ ይህ የተጠቀሰው መሰረታዊ የሰው ልጆች መብት ምሉሄ በኩልሄ እንዲሆን ከተፈለገ ከጎሳ ፖለቲካ መገላገል አለብን፡፡

ምን ይበጀናል ?

በእኔ የግል አስተያየት የመጣንበትን እረጅምና መራር ጉዞ ዛሬ መፈተሸ ያለብን ይመስለኛል፡፡( ለመፈተሸ ጊዜው አሁን ነው ብዬ አስባለሁ፡፡) እኔ ከላይ ያነሳሁትን ሃሳብና መደምደሚያ፣ ማለትም የጎሳ ፌዴራሊዝም እና የጎ አምባገነንት ለኢትዮጵያ እንደማይበጃት የሚለውን ነጥብ ማለቴ ነው፡፡ ብዙዎቻችሁን የሚያሳምን ይመስለኛል፡፡ ተቃራኒውንም ሃሳብ የያዛችሁ አትጠፉም፡፡ የጎሳ ፌዴራሊዝም ፍልስፍና ብዙዎችን ያሳተ ይመስለኛል፡፡ አንድ የፖለቲካ ስርአት ለሰላሳ አመት ተሞክሮ ካልሰራ ወይም አብዛኛውን የዣች ሀገር ዜጎች ከችጋር ካልገላገለ፣ ዲሞክራክ ስርአትን ማስፈን ካልረዳ ችግሩ ከፖለቲካ ስርአቱ ወይም ከግለሰቡ እንደሆነ ማሰብ የሰውነት ባህሪ ነው፡፡ ስለሆነም እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ምሁር በመጀመሪያ ራሱን በደንብ ከመረመረ በኋላ፣ ከራሱ ፍላጎት ውጪ በሆነ መንፈስ አንድ ታላቅ የውይይትና ንግግር መድረክ እንዲከፈት የበኩልን ጥረት ያደርግ ዘንድ ሳስታውስ በአክብሮት ነው፡፡ ይህን የውይይት መድረክ ለማዘጋጀት ከሁሉም ክልሎች ከተወጣጡ ቡድኖች እና የጎሳ አባላት ተወካዮች ቢሆኑ፣ እንዲሁም ፣ያለው የኢትዮጵያ መንግስት ደግሞ በቀናነት መንፈስ የውይይት መድረኩ እንዲዘጋጅ ሁኔታዎችን ቢያመቻች ከገባበት የፖለቲካ ማጥ ውስጥ ልንወጣ እንችል ይሆን? ብዬ እጠይቃለሁ፡፡ ዋናው ነጥብ ሁሉንም ነገሮች ፣ ህገመንግስቱን እን የመንግስትን ቅርጽ ጨምሮ ወደ ጠረቤዛ ዙሪያ ማምጣት መቻል አለብን፡፡በእውነት መሰረት ላይ ሆነን፣ ሁሉንም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅቶችን ፣ የሢቪል ማህበረሰብ ተወካዮችን፣ የሀይማኖት አባቶችን፣ የሐገር ሽማግሌዎችን፣ የሙያ ማህበራት መሪዎችን፣ ኢትዮጵያዊ ምሁራን፣ የሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍሎችን አካተን፣ አንድ የብሔራዊ ውይይትና እርቅ መድረክ እንፍጠር፡፡ በመጨረሻም ሁላችንም መግባባት ላይ ከደረስን በኋላ ሁለት ወይም ሶስት የዲሞክራቲክ ሰነድ ወይም ፐሮፖዛል በማዘጋጀት ለህዝብ እናቅርብ፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚበጀውን በነጻና ዲሞክራቲክ መርህ እንዲወስን እድሉ ይሰጠው የሚለው የግል አስተያየቴ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ መድማት የለበትም፡፡ አመጽ ወይም እርብሻ አሸናፊ አይደለም፡፡ አሸናፊው ነጻነት ነው፡፡

 

Filed in: Amharic