>
5:26 pm - Monday September 17, 2773

የማስጠላት ስትራቴጂ ....!!! (በላይ ባይሳ) 

የማስጠላት ስትራቴጂ ….!!!

በላይ ባይሳ 

ለዘመናት ከአያቶችህና ቅድም አያቶችህ ጀምሮ ከፍ ያለ ዋጋ የከፈልክበትን የራስህን የልፋት ውጤት እና መገለጫ የሆኑትን እሴቶች ሆን ተብሎ እንድትጠላው ትደረጋለህ።
 የራስህን እሴት እንድትጠላው የሚያደርግህ አካል ደግሞ በመላ፣ በዘዴ፣ በእቅድ ያንተኑ ወይም በጋራ ገንብተህ የነበረውን እሴት በገገማ “የኔ ብቻ ነው” ብሎ ጠቅልሎ የራሱ ያደርገዋል። በተቃራኒው ደግሞ የኔ ነው ብሎ የወሰደውን እሴት አንተ አምርረህ እንድትጠላው ያደርግህና ራሱ ብቸኛ ባለቤት ይሆንበታል። አንተም ያንተ ነው ብለህ ታረጋግጥለታለህ።
አንዳንዴ ሰዎች የራስህን ነገር ለራስህ መልሰው ሊቸሩህ ይፈልጋሉ። የራስህን ንብረት የራሳቸው አድርገው ጠብቅ ይሉሀል። የራስህን መብት የነሱ ገፀ-በረከት አድርገው ያቀርቡልሃል።
 ራሱን በኢትዮጵያዊ አንድነት ካባ ውስጥ ይደብቅና ጠርዝ በወጣ ፅንፈኝነቱ ታጅቦ ከመጋረጃ ጀርባ የእሴት ዝርፊያውን ያራምዳል። ቲያትሩን ይከውናል። እንደለመደው ሲሰርቅ እጅ-ከፈንጅ ስትይዘውም አይኑን በጨው ታጥቦ “መሬቱን ሳይሆን ማንነቴን ነው ያስመለስኩት” ይልሃል። የሌባ አይነደረቅ መልሶ ልብ አድርቅ ይሉሃል ይሄው አይደል?
ሌባው የማስጠላት ስትራቴጂውን ተጠቅሞ የሚከተሉትን እሴቶች በገገማ ወስዶብሃል አልያም ሊወስድ ጥረት አድርጓል።
1ኛ. ባንድራን/ሰንደቅን ማስጠላት
አያት ቅድም አያቶችህ በጀግንነት ደም እና አጥንት የገበሩለትን፤ ጀግኖች አትሌቶች በአለም አደባባይ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ፤ ጀግኖችና አርበኞች፤ ፈረስና ፈረሰኞች የተዋደቁለትን ሰንደቅ ያንተ አይደለም ብሎ ለራሱ መውሰዱ ሳያስገርም አንተም የኔ አይደለም ውሰደው ማለትህ ነው።
በእርግጥ ልሙጣዊ አስተሳሰቡንና አሃዳዊ አተያዩ ከ”የኔ ብቻ ነው” አመለካከቱ አመንጭቶ በማሳደግ ለዘመናት ርዕዮቱ አድርጎታል ማለት ይቻላል። ይሁንና በባንዲራ ዙርያ ሁል-አቀፍ ውይይት እና ብሄራዊ መግባባትን መፈጠር እንደሚገባ ልብ ይሏል።
2ኛ. ሃይማኖትን ማስጠላት 
ሃይማኖት የግል፤ ሃገር ደግሞ የጋራ ከሚለው ብሂል ያፈነግጥና የሃይማኖት ተቋምን የሆነ ማህበረሰብ ብቻ መገለጫ ነው ይልና የፓለቲካ ፍላጎቱንና የወራሪነትና የተስፋፊነት አጀንዳውን ያራምድበታል።
በሃይማኖት ሽፋን ሌላ ሌላ የጎሰኝነትና የጎጠኝነት ድብቅ ተልዕኮውን ያሳካበታል።  በዚህ ምክንያት ሃይማኖቱን እንደ በደል መፈፀሚያ መሳርያ ስለሚጠቀምበት እንድትጠላው ያደርግሃል። አብዛኛውን የዕምነት ተቋማት እንዲገነቡ መሬቱን ሳይቀር የለገሱት አያቶችህ መሆናቸውን ግን እንዳትረሳ።
3ኛ. መሬት መቀራመት 
በየደረሰበት ይሰፍርና “እርስቴ ነው” ፤ “ባትጋሩኝ!” ወዘተ… ይላል። የመሬት ቀበኛ ነው። ህጋዊነቱን ለማረጋገጥ ሲሶውን ከልሎ ደጀሰላም ያቋቁማል። ፀበል ፈለቀ፣ መስቀል ወደቀ … ብሎ ካስወራ በኋላ መሬቱን ይቀራመታል። በአገልጋይ ስም የሰው ሃይል ወደ አከባቢው ኢምፖርት ያደርጋል። ዲሞግራፊውን ይቀይረዋል። በአንፃሩ ለምን? ስትል “ዘረኛ” ይልህና አከባቢውን እንድትጠላው ጭምር ያደርግሃል። ያንተን ባህላዊ መገለጫ አክስቶ የራሱን ያበለፅጋል። ያንተን ማንነት በሱ ማንነት ለመቀየር ይተጋል።
4ኛ. ጦርነትን መስረቅ  
በሰሞኑ የተደረገውን የህግ ማስከበር ዘመቻ እንኳን “እኔ ነኝ የመራሁት” በማለት ተግባሩን ከሃገራዊ ገፅታው ይልቅ ክልላዊና መንደራዊ ለማድረግ ተውተርትሯል።
 ይሁንና የዚህ ፅሁፍ አላማ ምንም አበርክቶ አልነበረውም ለማለት ሳይሆን ጬኸቱና ፉከራውን በማጋነን ጦርነቱ የኔ ነው ብሎ ለመጠቅለል እና ለመንጠቅ እጅግ ተግቷል።
በአሟሟቂ ሚድያዎቹ በመታጀብ በእግር-በፈረስ አውርቷል አስወርቷል። እውነታው ግን ከሃገር እና ከህግ በላይ ነን ያሉትን ከሃገር እና ከህግ በታች ስለመሆናቸው ማስተማር የግድ ስለሆነ እንጂ አካኪ-ዘራፍ የሚያሰኝ ጦርነትም አይደለም።
 5ኛ. ከተማን አንዳንዴም ሃገርን መውረር  
ከተማው ወይም ሃገሩ የኔ ነው። አንተ ከየት እንደመጣህ አይታወቅም። አንዲት ሃገር በሚል ብሂል የሌሎችን ማንነት ሆን ብሎ በመጨፍለቅ ሸፍጡን እያራመደ “የኔ የምለው ሃገር የለኝም” ያስብልሃል ። ሃገርህን አስጠልቶህ ይቀማሃል። ባለቤቱ እኔ ብቻ ነኝ ይልሃል። አንተም ይህቺ ሃገር የኔ አይደለችም ትላለህ።
ከተማንም በተመሳሳይ በመውረርና በመሠግሰግ የባለቤትነት ማረጋገጫ ይጠይቃል። የራሱን ማህበረ-ኢኮኖሚ ፓለቲካ ለመገንባት ይጥራል። የዚህ ከተማን የመንጠቅ ኘሮጀክት ተግባር የከተማን ብሎም የአከባቢ ስም እስከመቀየርና ታሪክን እስከማስረሳት እንደሚደርስ ልብ ይሏል።
6ኛ. ዜግነትን ማስጠላት  
በዜግነትህ እንድትጠራጠር በማድረግ የማንነት ቀውስ አዙሪት ውስጥ በመክተት “ዜግነቴ ኢትዮጵያዊ አይደለም!” እንድትል ያደርግሃል። በአንፃሩ ደግሞ ወደ መንደር ዲቪዝዮን ያወርድህና ለራሱ የዜጋ ውሃ ልክ ማለት እኔ ነኝ ይልሃል።
 
7ኛ. የህዳሴውን ግድብ ባለቤትነትን መንጠቅ  
ከህዳሴው ግድብ  ጋር ተያይዞ በተዘጋጀ ሁነት ላይ ልሙጣዊ አስተሳሰበቡን በጬኸት በማጀብ ግድቡ የኔ ብቻ ነው፤ ካንተ ይልቅ የኔ አበርክቶ የጎላ ነው ይልህና ብሄራዊ ኘሮጀክቱን “ያንተ አይደለም” በሚል ድምፀት በዘረኝነት የታጀለ ስድቡን ጭመር እያሰማህ ያስጠላሃልደ። ግድቡ የኔ አይደለም እንድትል ይገዳደርሃል። ይህን አይነት ዝንባሌ ሃገራዊ ኘሮጀክቶች ላይ ሁሉ  ይስተዋላል።
8ኛ. ታሪክን መሻማት 
የታሪክ ሽሚያ፣ ንጥቂያና የትርክት ዝንፈት በመፈፀም ራሱን ባለታሪክ ያደርግና ሌላውን ታሪክ አልባና አንዳንዴም ተራ አጃቢ በማድረግ የራስወዳድ አባዜውን እና የታሪ ጨረታውን ያደራል። በዚህም ያለ የሌለ የታሪክ ዘውግ በመፍጠር በታሪክና በትርክት ተወዛግበህ ታሪክ ጠል እንድትሆን ያመቻችሃል።
ይሁንና በሃገሪቱ ማንኛው ታሪክ አንተ እንዳለህ እና ያላንተ ታሪኩ ባዶ እንደሆነ ግን ጠንቅቆ ያውቃል። የአንድን ወገን ታሪክ ያለልክ አግዝፎ መተረክ የሌባው ሌላኛው ስልት ነው። ጀግናዬ የሚላቸውንም ወደ አማልክት የተጠጋጉ ፍፁማን ለማለት ይዳዳል። ይህ ሚዛናዊ ስብዕናና ሞራል ካለው ሰው የማይጠበቅ ውገና ነው።
በአጠቃላይ ሌሎችን ይህን መሰል ብዙ ብዙ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል።   ይህ እጅግ አደገኛ አካሄድ ነው።
ስለዚህ ይሄንን የማስጠላት ስትራቴጂ በመጠቀም ብዙ እሴቶችህን በማስጠላት አስተዋፅኦህን በማሳነስ በሁለንተናዊ ገፅታው ቦታህን አስለቅቆሃል። በመሆኑም ይሄንን የሸፍጥ ስትራቴጂ ነቅተህ በመረዳት በዘዴ ወደለቀቅከው ስፍራ መመለስ ይኖርብናል። አቁም ልትለውም ይገባል።
በግል እና በጋራ በሚያስማሙ ጉዳዮች ላይም ማተኮር ለችግሩ እንደ መጀመሪያ ምእራፍ መፍትሄ ይታያል። ይህን አይነት የተዛነፈን አተያይና ተግባር በመታገል ወደ ትክክለኛው ቦታ በመመለስ አብዛኛውን ወደሚያስማማ ምእራፍ መሻገር ሁለተኛውና ዋነኛው ተግባር ሊሆን ይገባል። ያለ ምክንያት መውደድም ሆነ መጥላት ተገቢነት የለውምና። አመክኖዋዊነትም ሊቀድም ይገባል።  እኔ ያልኩትና የማስበው ብቻ ገዢ ሃሳብ ነው ከሚለው አመለካከት መፋታት ግድ ይላል።
ስለዚህ ይሄንን የሸፍጥ ፖለቲካ በመረዳት የማስጠላት ስትራቴጂን በንቃት መከላከል ግድ ይላል።
Filed in: Amharic