>

"እሽ አትበሉኝ የሹም ዶሮ"ነኝ...!!! (ጋዜጠኛ መአዛ መሀመድ)

“እሽ አትበሉኝ የሹም ዶሮ”ነኝ…!!!

ጋዜጠኛ መአዛ መሀመድ

የእነ አቶ ጃዋር ጠበቃ አቶ አብዱልጀባር ሁሴን በአባይ ሚዲያ አውድማ ፕሮግራም “የክስ መቃወሚያ ወይስ?”በሚል ርእስ ያደረግነውን ውይይት ‘በደንበኞቼ ላይ የተፈፀመ  ወንጀል በመሆኑ ተወያዮቹ ላይ በእርግጠኝነት ክስ እመሰርታለሁ’ ብለው እንደሚከሱን በፌስቡክ ገፃቸው ገልፀውልናል።
የክሱ ጉዳይ ይቆየንና፦
በፍርድ ቤት ላይ ተፅእኖ የሚያሳድረው ከፍርድ ቤት ችሎት ከቀናት በፊት የክስ መቃወሚያ ፅሁፉ ወደ ማህበራዊ ሚዲያ እንዲመጣ አድርጎ (የቴሌግራም ግሩፕ ሳይቀር ከፍቶ) መወያያ ማድረግና ነገሩ ከፖለቲካ አንፃር እንዲተነተን መግፋት ወይስ ተከሳሾቹ ፍርድ ቤት ከቀረቡ በኋላ ሀሳቡን በሚዲያ መተቸት?
በውይይታችን እንደገለፅነውም የወንጀል ጉዳይን በተከሰሱበት አግባብ መቃወምና መከራከር ተገቢ ቢሆንም በህገ መንግስቱ በግልፅ የተደነገገን የአዲስ አበባን የባለቤትነት ጉዳይ በመጥቀስ ክሱን ለፖለቲካ ፍጆታ ማዋል ለማንም እንደማይበጅ መጥቀስ የግለሰቦችን እንደ ነፃ የመቆጠር መብት የሚፃረረው እንዴት ነው?
አስገራሚው ነገር ጠበቃው “ተከሳሾቹ በፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ቢፈቱ የሞቱትን ሰዎች ፍትህ ማሳጣት እንደሆነ ገልፀዋል። ለዚህም እንፋረዳቸዋለን” ብለዋል። የህግ ሰው ትክክለኛ ፍትህ ይሰጠን ይላል እንጂ ደንበኞቼ በፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ይፈቱልኝ ይላል? በፖለቲካ ጣልቃ ገብነት መፈታት የለባቸውም የሚል አካልስ ጥፋተኛ የሚባለው በየትኛው ህግ ነው?
ነገሩ “እሽ አትበሉኝ የሹም ዶሮ” ካልሆነ በቀር ለክስ የሚያበቃ ነገር የለውም። አለ ካሉም መብትዎ ነው እንጠብቅዎታለን።
የእነ አቶ ጃዋር ጠበቃ አቶ አብዱልጀባር ሁሴን
በማህበራዊ ሚድያ ገጻቸው ይህን ምክር አይሉት ዛቻ አሰራጭተዋል
አባይ ሚድያ “አውድማ” በሚል ፕሮግራም  የጋዜጠኞች ውይይት  እነ አቶ ጀዋር ሲራጅ(14 ሰዎች)ን ከፍርድ በፊት እንደ ንፁህ የመቆጠር መብት (presumption of innocence) አደጋ ላይ የሚጥል:ጥላቻ-ወለድና የጋዜጠኝነት የሙያ ሥነ-ምግባር  የሚጥስ ነው።
እነ አቶ ጀዋር ሲራጅ(14 ሰዎች)  የመጀመሪያ ደረጃ  የክስ  መቃወሚያ በሚመለከት አባይ ሚድያ “አውድማ” በሚል ፕሮግራም በጥር 4, 2013 ዓ.ም.  ያቀረበው  የጋዜጠኞች ውይይት ተከሳሾችን ከፍርድ በፊት እንደ ንፁህ የመቆጠር መብት (presumption of innocence) አደጋ ላይ የሚጥል:ጥላቻ-ወለድና የጋዜጠኝነት የሙያ ሥነ-ምግባር  የሚጥስ ነው።
አባይ ሚድያ የተባለው ሚድያ  “አውድማ” በሚል ፕሮግራም  “የክስ መቃወሚያ ወይስ?” የሚል ርዕስ በመስጠት በጥር 4, 2013 ዓ.ም.  አራት ጋዜጠኞች እየተቀባበሉ እነ አቶ ጀዋር ሲራጅ(14 ሰዎች)  የመጀመሪያ ደረጃ  የክስ  መቃወሚያዎች ላይ አስተያየት ሰጥቷል።
ጉዳዩ በክርክር ላይ ያለ ውሳኔ ያልተሰጠበት ቢሆንም ጋዜጠኞቹ በአስተያየታቸው፦
“እነኚህ ግለሰቦች በቀሰቀሱትና ባነሳሱት ሁከት በቀጥታ የተጎዱ(የተጠቁ) በመቶ የሚቀጠሩ ዜጎች እንዳሉ።፤ በተከሳሾች ጥሪ የሰው ደም መፍሰሱን፤በክሱ ውስጥ የተጠቀሱትና ገና በማስረጃ የሚረጋገጡ ፍሬ ነገሮች እና በክሱ ውስጥ ያልተጠቀሱ አሉባልታዎችን ጨምሮ እንደተረጋገጡ በመውሰድ ተከሳሾች ወንጀል ሰርተው መካዳቸው ትክክል እንዳልሆነ፤ በፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ቢፈቱ (በኦሮሚያ ውስጥ የሞቱትን ሰዎች እነሱ እንደገደሏቸው በመውሰድ) የሞቱትን ሰዎች ፍትህ ማሳጣት እንደሆነ፤ ያቀረቡት የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ የፖለቲካ ሰነድ እንደሆነ የተከሰሱበትን ጉዳይ አሁንም ሕዝብን ለሁከት እያነሳሱ እንደሆነ፤ በመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ አሁንም እስር ቤት ሆነው የአመፅ ጥሪ እያደረጉ እንደሆነ፤ የፍርድ ቤትን የሥራ ነገር ስልጣን ከፌዴራል አወቃቀር ጋር በማዛመድ መቃወሚያ በማቅረብ ወንጀል መስራታቸውን ፤ በክሱ ውስ ለተጠቀሰው “ነፍጠኛ” ለሚለው ቃል መልስ መስጠታቸው አንደ ከዚህ ቀደሙ በቤተክሪስትያንና በአማራ ሕዝብ ላይ ጉዳት ለማድረስ የተደረገ ጥሪ እንደሆነ” እና መሰል በጥላቻ የተሞሉ ሆነ……አስተያየቶች ሰጥቷል።
የቀረበለትን ጉዳይ መርምሮ ዉሳኔ መስጠት ያለበት ፍ/ቤት ብቻ ነዉ፡፡ ሚድያና  በስመ የፖለቲካ ትንተና መረጃዎች መርምሮ የፍርድ  ዉሳኔ በመስጠት የዉሳኔ (የመደምደሚያ)  የማቅረብ ስልጣን የለዉም፡፡ አባይ ሚዲያ ላይ  የተከሳሾችን የመጀመሪያ የክስ መቃወሚያ በሚመለከት አራቱ ጋዜጠኞች የሰጡት አስተያየቶች ግን የወንጀል ድርጊቶች እንደተፈጸሙ ከድምዳሜ የደረሱ የሚያስመስል እና ፍ/ቤቱ ጉዳዩን መርምሮ ዉሳኔዉን በነጻነት እንዳይሰጥ ተጽእኖ ሊያሳድሩ የሚችል ነዉ፡፡  ይህ  የጋዜጠኞች አስተያየት ወይም ትንተና  አስቀድሞ የተወሰነ ፤ ፍ/ቤት እና ዳኞች ላይ ጫና የሚያሳድር አና ወደፊት ሊሰጥ የሚችለዉን ዉሳኔ ፍትሃዊነትና ገለልተኛነትን የሚፈታተን ስለሆነ በአለም አቀፍ የስቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃልኪዳን አንቀጽ 14(1) እና የኢፌዲሪ ሕ/መንግስት አንቀጽ 20(1) ሥር ማንም ሰው በተከሰሰበት ወንጀል ሚዛናዊ  የሆነ ፍርድ የማግኘት መብት የሚጻረር ነዉ፡፡
እነ አቶ ጀዋር ሲራጅ(14 ሰዎች)  በክሶቹ የተጠቀሱት  የወንጀል  ድርጊቶች አሉ ወይስ የሉም፣  ወንጀል መፈጸም አለመፈጸሙን፣ አንድ ድርጊት የተጠቀሱትን ወንጀሎች  ያቋቁማል ወይስ አያቋቁምም፣ ወንጀል ተሰርቷል ወይስ አልተሰራም እና መሰል የፍ/ቤቱን ዳኝነት በሚጠይቁ ጉዳዮች ላይ ማናቸዉም የሚዲያ ተቋማት የሆነዉን ነገር እንዳለ /Fact/ ከማስቀመጥ ባለፈ ዉሳኔ ሊሰጡበት አይገባም፡፡
ከላይ ለተነሱት ጥያቀዎች ሁሉ ግን የአባይ ሚድያ ጋዜጠኞች ስለድርጊቶቹ ዝርዝር ጉዳይ አቅርቦ ዉሳኔዉን ከፍ/ቤት በመጠበቅ ፋንታ ተከሳሾች ወንጀሉን እንደፈጸሙ ከድምዳሜ የደረሰበትን በሚመስል መልኩ ከላይ በተመለከተው መሠረት ለሕዝብ ገልጿል።
በዚህ ሁኔታ የተሰጠው የጋዜጠኞቹ ትንተና ከፍ/ቤቶች ነጻነትና ገለልተኝነት ፍልስምና መሰረት /Judicial Independence/ ጋር የማይስማማ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡
የተከሳሾችን ከፍርድ በፊት እንደ ንፁህ የመቆጠር መብት (presumption of innocence) አደጋ ላይ በመጣል ተከሳሾች ፍትሃዊ እና ተመጣጣኝ ውሳኔ እንዳያገኙ በማድረግ ፍርድ ያዛባል። ዓለም አቀፍ በስቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃልኪዳን አንቀፅ 14(1) መሠረት  የፍትህ አስተዳደርንና የተጠርጣሪን መብት አደጋ ለይ የሚጥል ከሆነና የተከሳሾችን የሚጎዳ ከሆነ ፍርድ ቤት ጉዳዩ በክርክር ላይ በለ ጊዜ ሚድያ ስለጉዳዩ የሚያቀርበውን ዘገባ በማገድ ሌሎች ሕጋዊ እርምጃዎችን መውሰድ ይችላል። ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ በስቪልና የፖለቲካ መብቶች ቃልኪዳን አፅድቃለች፡፡ በመሆኑም በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 9(4) መሠረት የሀገሪቱ ሕግ አካል ነዉ፡፡
በመሆኑም የሚድያውና የጋዜጠኞቹ  ተግባር የተከሳሾችን የፍሬ ነገር እና ስነ-ስርዐት መብቶችን (substantive and procedural due process rights) የሚጥስ በመሆኑ  ላቀረቡት ዘገባ ሕጋዊ እርምጃ ተወስዶ ለወደፊቱ ደግሞ ተመሳሳይ ዘገባ እንዳያቀርቡ እንድታገድልን መጠየቃችን የመይቀር ነው።
በሌላ በኩል ይህ በአባይ ሚድያ  “አውድማ ” በሚባል ፕሮግራም “የክስ መቃወሚያ ውይስ?..” በሚል ርዕስ  ተቀርፆ በመህበራዊ ሚዲያ በኩል ለሕዝብ የቀረበው የጋዜጠኞች አስተያየት  ተከሳሾቸ በህገ መንግስቱ  እና በወ/መ/ሥ/ሥ/ ሕግ የተረጋገጠላቸዉን የቀረበባቸዉን ክስ የመከላከል መብት በእጅጉ የሚጎዳ  ነው። በወንጀል የፍትህ ስርዓት አስተዳደር ዉስጥ የእዉነታ ፍለጋ እና የፍለጋዉ ሂደት ፍትሃዊነትና ሚዛናዊነትን ጎን ለጎን እያስማሙ መሄድ /To Strike a Balance Between the Search for Truth and the Fairness of the Process/ ሊዘነጋ የማይገባ አብይ ጉዳይ ነዉ፡፡  ለዚህም ሲባል በየትኛዉም ሀገር የወንጀል ፍትህ ስርዓት አስተዳደር ዉስጥ ግለሰቦችን ከመንግስት ያልተገባ ድርጊት ለመጠበቅ ሲባል በወንጀል ምርመራ ወቅት፣ በማስረጃ አሰባሰብ ወቅት እንዲሁም በክስ ሂደት ላይ በመንግስት ሊከተለዉ የሚገባቸዉን ሂደቶች በተመለከተ ግዴታዎችን /Due Process of Law/ በህግ ማስቀመጥ የተለመደ ነዉ፡፡ በመሆኑም ሕገ መንግስታችን ሆነ የወ/መ/ሥ/ሥ/ሕጋችን በተከሳሾች ላይ የሚቀርብ ማናቸዉም አይነት  በሚድያ የሚገለፁ ነገሮች የተከሳሾችን የመከላከል መብት የሚያጣብቡ መሆን እንደሌለባቸዉ በአጽንኦት የሚጠይቅ መሆኑን በአንቀጽ 20(4) እና ከአንቀጽ 136-149 ድረስ እንደቅደም ተከተላቸዉ ካሉት ንባቦች መገንዘብ ይቻላል፡፡ ይህን የህግ ዓላማ በሚቃረን ሁኔታ የተከሳሾችን የመከላከል መብት በሚያጣብብ መልኩ  ጋዜጠኞቹ የሰጡት የጥላቻ ትኔታኔ ተከሳሾች የመከላከል መብታቸዉን በተገቢዉ ሁኔታ እንዳይጠቀሙ እንቅፋት የሚሆን ጉዳይ ነው።
ጋዜጠኞቹ የተከሳሾችን የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ የመወያያ ርዕስ ያድርጉት እንጂ ዋና ዘመቻ በኦፌኮ እና ፖርቲው ወክለዋለው የሚለውን መህረሰብ ላይ ነው። ጋዜጠኞቹ ኦፌኮን  በብሔር ከተደረጁ ጥቃቅን የፖለቲካ ፖርቲዎች ውስጥ አንዱ እንደሆነ፤ ፖሊስ መቅረፅ የማይችል የሀሳብ ባዶ እንደሆነ እና ተከሳሾቹም የተከሰሱት ከህዝብ ጋር ለመተዋወቅ በእሮሚያ በተለያዩ ዞኖች አድርገውት በነበረው እንቅስቃሴ እንደሆነ ይገልፃሉ። ጋዜጠኞች ከዚህም አልፈው ተከሰሾችን በሰው ደምና ሞት የሚነግዱ ናቸው በማለት ውሳኔ ይሰጣሉ።
ለዚህ ሁሉ የአባይ ሚድያ እና ጋዜጠኞቹን በእርግጠኝነት በሕግ እንፋረደቸዋለን
Filed in: Amharic