ጭቆናን በብዕሩ የታገለው ደፋር ደራሲ …!!!
አንተነህ ቸሬ
‹‹አልወለድም›› በተሰኘው ገናና ልብ ወለድ ይታወቃል። ከ20 በላይ የልብ ወለድ፣ የድራማና የግጥም መጽሐፍትን ያሳተመ ደራሲ፣ ባለቅኔና ገጣሚ ነው። የጽሑፎቹ ጭብጦች በጭቆና፣ በሙስና፣ በመሃይምነት እና በማኅበራዊ ኑሮ ላይ ያተኮሩ ነበሩ። የመንግሥትን አስተዳደር ብልሹነት በሚተቹ ስራዎቹ ምክንያት በሹማምንት ጥርስ ተነክሶበት ለእንግልት ተዳርጓል።
ግፍንና ጭቆናን በብርቱ ታግሏል። ይህ ጠንካራና ደፋር አቋሙም ውድ ሕይወቱን አስከፍሎታል። ትውልድና መንግሥትን የነቀነቀው ደራሲ፣ ባለቅኔና ገጣሚ አቤ ጉበኛ ለኢትዮጵያ ይጠቅማታል ብሎ ያመነበትን አስተሳሰቡን ሳይፈራ የፃፈ የስነ-ጽሑፍ ጀግና ነው።
አቤ ጉበኛ የተወለደው በ1925 ዓ.ም ጎጃም ውስጥ ነው። የእውቀትን ማዕድ የቀመሰው በቤተ ክህነት ትምህርት ነው። ግዕዝን በይስማላ ደብረ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የኔታ ገሰሰ እና የኔታ አክሊሉ በተባሉ መምህራን ተማረ። አቤ በሁሉም የአብነት ትምህርቶች የተመሰከረለት ጎበዝ ተማሪ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በቅኔ፣ በአቋቋምና በዜማ ትምህርቶች ደግሞ የተለየ ብቃት ነበረው።
ይህ የቤተ ክህነት ትምህርትም ለዘመናዊ ትምህርት መንደርደሪያ ሆነው። ዘመናዊ ትምህርት ለመማር ወደ ዳንግላ ተጉዞ ትምህርቱን ጀመረ። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በቢትወደድ መንገሻ ጀምበሬ ትምህርት ቤት ከተማረ በኋላ በኅዳር ወር 1946 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ሄደ።
አዲስ አበባ ከደረሰ በኋላ በሐና ማርያም ቤተ ክርስቲያን መሪ ጌታ ሆኖ ማገልገል ጀመረ። በአገልግሎቱ ብዙም ሳይገፋበት የኑሮ ጉዞውን ወደሌላ አቅጣጫ በማዞር ጉዞውን ቀጠለ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ተምሮ አጠናቀቀ። በውስጡ የታመቀውን የስነ-ጽሑፍ ችሎታ ለማውጣትም ብዕርና ወረቀቱን የሙጥኝ አለ። በ1949 ዓ.ም በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ የመጀመሪያ ግጥሙን አቀረበ።
ከዚች ግጥም በኋላ ሌሎች ግጥሞችን እያዘጋጀ በጋዜጣ ማቅረቡን ቀጠለበት። ለአብነት ያህል የልዑል መኮንን ኃይለሥላሴን ሞት ምክንያት በማድረግ ያዘጋጀው ‹‹የሐዘን እንጉርጉሮ›› የተሰኘው የግጥም ስራው ተጠቃሽ ነው። ስለጭቁኑ አርሶ አደር የሚጽፋቸው ጽሑፎችም አቤ ወደፊት የተዋጣለት ጸሐፊ እንደሚሆን ያመላከቱ ነበሩ።
በ1949 ዓ.ም በጋዜጣ ላይ አሳትሟቸው የነበሩ ግጥሞቹን አሰባስቦ ‹‹ከመቅሰፍት ሰራዊት ይጠንቀቅ ሰውነት›› የሚል የግጥም መድብል አሳተመ። ይህ መጽሐፍ የተለያዩ የተባይ ዓይነቶች ከሰው ልጆች ጋር ያላቸውን ግንኙነት የሚተርክ ቢመስልም በውስጠ ወይራ ግን የሕዝቡንና በተባይ የተመሰሉትን የወቅቱን ጨቋኝ ገዢዎችን (ሹማምንት) ግንኙነት የሚያሳይ ነበር።
የአቤን የስነ-ጽሑፍ ችሎታ የተመለከቱ የማስታወቂያ ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች በ1951 ዓ.ም በጋዜጠኛነት እንዲቀጠር አደረጉት። የ1953 ዓ.ም የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ከመደረጉ አንድ ወር አስቀድሞ ያሳተመው ‹‹የሮም አወዳደቅ›› የተሰኘው የተውኔት መጽሐፉ ትንቢት ተናጋሪ ደራሲ አሰኝቶታል። ይህ መጽሐፉ አንባቢዎቹን ሲያስደስት ሹማምንቱን ደግሞ አስቆጣ።
‹‹የአቤ ጉበኛ ብዕራዊ ተጋድሎ›› የተሰኘው መጽሐፍ ደራሲ ኤልያስ አያልህ አቤ ‹‹የሮም አወዳደቅ›› በተሰኘው የተውኔት መጽሐፉ የንጉሳዊ ስርዓቱን እጣ ፈንታ ተንብዮና ለወቅቱ አስተዳደር ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ እንደነበር በመጽሐፉ ላይ ገልጿል።
የአቤ ጉበኛ ‹‹የሮም አወዳደቅ›› መጽሐፍ ከታተመ ከአንድ ወር በኋላ በነብርጋዴር ጀኔራል መንግሥቱ ነዋይ የተመራው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ተካሄደ። የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው ተባባሪ ናቸው ተብለው ይፈለጉ ከነበሩ ሰዎች መካከል አንዱ አቤ ሆነ። ራሱን በመሸሸግ አስቸጋሪውን ጊዜ አሳለፈ።
የመፈንቅ መንግሥት ሙከራው ከሽፎ አገር ከተረጋጋ በኋላ አቤ የቀድሞ መስሪያ ቤቱን በመልቀቅ በጤና ሚኒስቴር ተቀጠረ። በዚያም ሳለ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ቴያትር ቤት (የአሁኑ ‹‹ብሔራዊ ቴያትር››) ‹‹ቂመኛው ባሕታዊ›› የተሰኘ ድራማ ለሕዝብ አቅርቦ ተቀባይነቱን አሳደገ። በስራው አድናቆት ቢያገኝም ሳንሱር ፈተና ሆኖበት ለሕትመት ያዘጋጃቸውን ጽሑፎች ማሳተም አልቻለም ነበር።
አቤ ‹‹የአፍሪካ ነፃነት ጀግና›› እያለ ያወድሳቸው የነበሩት የኮንጎው ፓትሪስ ሉሙምባ ሲሞቱ ‹‹የፓትሪስ ሉሙምባ አሳዛኝ አሟሟት – The Tragedy of Patrice Lumumba›› የተሰኘ ድራማ ጽፎ አሳትሟል። አቤ ‹‹ሉሙምባ የአገሩን ነፃነትና አንድነት በጥብቅ የሚጠብቅ፤ የሕዝቡን ጥቅም በከንቱ የማያዘርፍ፤ ለአንዱ ክፍል የመንፈስ ባሪያ የማይሆን ትክክለኛና ንቁ መሪ ናቸው›› በማለት ያሞካሻቸው ነበር።
አቤ በወቅቱ ስለነበረው ጭቆናና ግፍ በድፍረት ይናገርና ይጽፍ ነበር። የውጭ ዜጎችንም ያካተቱ ትልልቅ ስብሰባዎች አዲስ አበባ ውስጥ በሚካሄዱባቸው ጊዜያት አቤ ከከተማ ውጭ እንዲቆይ ይደረግ ነበር። የመንግሥት ሹማምንት አቤንና ብዕሩን ይህን ያህል ይፈሯቸው ነበር።
በ1955 ዓ.ም ባሳተመው ‹‹የአመፅ ኑዛዜ›› ልብወለዱ ተምረውም ሆነ ሰርተው ሀብት ያገኙ ዜጎች ኑሮ ያልተመቸውንና ደሃ ወገኖቻቸውን እንዳይዘነጉ አሳስቧል። በዚሁ ዓመት ነበር አቤ እስካሁን ድረስ በብዙዎች ዘንድ ታዋቂ መሆን የቻለበትን ‹‹አልወለድም›› የተሰኘውን የልብ ወልድ መጽሐፉን ያሳተመው።
ይህ የአቤ ገናና መጽሐፍ አቤን ችግር ውስጥ የከተተው ገና ከጅምሩ ነበር። የንጉሳዊውን መንግሥት ጉድለቶች ያሳየበት ይህ መጽሐፉ ገና 800 ቅጂ ብቻ እንደተሸጠ ተሰብስቦ እንዲቃጠል ተፈረደበት። ይሁን እንጂ መጽሐፉ ከገበያ እንዲወጣ ቢደረግም በድብቅ እየታተመ ከ50 እስከ 60 ብር ይሸጥ ነበር።
የወቅቱን ስርዓት በተባ ብዕሩ የሞገተውና ለኢትዮጵያ መልካም ራዕይ የነበረው ደራሲ አቤ ጉበኛ፤ ከቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ዙፋን ፊት እንዲቀርብ እንደተደረገ፣ ንጉሰ ነገሥቱም አቤን ተመልክተው ‹‹አንተና መጽሐፍህ አንድ አይደላችሁም›› እንዳሉትና የተቃጠለው መጽሐፍ ዋጋ እንዲከፈለው ትዕዛዝ እንደሰጡ ይነገራል። ‹‹አልወለድም›› አቤን ለእስር ዳርጎታል። መጽሐፉ የፖሊስ የምርመራ ፋይል ተከፍቶበት ወከባ እንዲያጋጥመውና የመንግሥት ክትትል እንዲጠነክርበትም አድርጎታል።
ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ ስለአቤ ጉበኛ በጻፈው ጽሑፍ ላይ ‹‹ … አቤ በተለይ 1955 ዓ.ም ያሳተማት ‹አልወለድም› የምትሰኘው መጽሐፍ በንጉሱ ስርዓት ላይ ያለውን ጥላቻ ያሳየበት ነው። በዚህ ኢፍትሐዊነት ባለበት አገዛዝ፣ በዚህ አንዱ ተረግጦ፣ ሌላው ረግጦ በሚኖርበት ስርዓተ ማኀበር ውስጥ ‹አልወለድም› የሚልን ፅንስ መሠረት አድርጐ የተፃፈ ልቦለድ ነው። በዚህ ልቦለድ ውስጥ በአፄው ስርዓት ውስጥ የሚታዩ ጭቆናዎችና በደሎችን እያነሳ ያሳያል።
እነዚህ ግፎች በተከማቹበት አገርና ማኀበረሰብ ውስጥ አልወለድም የሚልን አስገራሚ ገፀ-ባህሪ ፈጥሯል። ገፀ-ባህሪው በእናቱ ማኅፀን ውስጥ ያለ ፅንስ ነው። ‹መወለድ የለብኝም› ብሎ የወቅቱን ፖለቲካዊ ትኩሳት ዝክዝክ አድርጐ የሚያሳይ ሥነ- ጽሑፍ ነው። ‹አልወለድም› በኢትዮጵያ የተቃውሞ ሥነ- ጽሑፍ ጐራ ውስጥ ግንባር ቀደም ሆና የምታበራ የጥበብ ስራ ነች …›› በማለት አብራርቷል።
አቤ በዚህ ሁሉ ወከባና ማስፈራሪያ ውስጥ ሆኖ ብዕሩን ለመጨበጥ አላረፈም። በ1956 ዓ.ም ‹‹የፍጡራን ኑሮ›› እና ‹‹The Savage Girl›› ስራዎቹን አሳተመ። ‹‹The Savage Girl›› መጽሐፉ በኢትዮጵያዊ የተፃፈች የመጀመሪዋ የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ለመባል በቃች።
የኢትዮጵያውያን ደራሲዎችን ታሪክ ‹‹Black Lions – The Creative Lives of Modern Ethiopia’s Literary Giants and Pioneers›› በሚል ርዕስ የፃፉት ኖርዌያዊው ሩዶልፍ ሞልቬር፤ አቤ ጉበኛን
ከኢትዮጵያ ታላላቅ ደራሲያን ተርታ አስቀምጠውታል። ከዚህ ባሻገርም ‹‹መጽሐፍ በመፃፍ ስራ ብቻ የሚተዳደር ብቸኛው ኢትዮጵያዊ›› በማለት ገልፀውታል።
የአቤ የስነ-ጽሑፍ ስራ በደመቀበት ወቅት በተከታታይ ካሳተማቸው ስራዎቹ መካከል ‹‹የራሄል እንባ›› የተሰኘውን የተውኔት ስራውን በ1956 ዓ.ም ለመድረክ አብቅቷል። በተመሳሳይ ዓመት ያሳተመው ‹‹ምልክዓም ሰይፈ ነበልባል›› መጽሐፉ ደግሞ አራት ጊዜያት በመታተምና 25ሺ ቅጂ በመሸጥ በጊዜው ከፍተኛ ሽያጭ ያስመዘገበ መጽሐፍ መሆን ችሏል።
አቤ ጉበኛ ሁልጊዜም ቢሆን ጭቆናንና ግፍን አጥብቆ ይቃወማል። አቤ ትውልድን፣ መንግስትን፣ ህዝብን የሚነቀንቅ ሞገደኛ ደራሲ ነበር። ብዙ ሰዎች እንደሚሉት፣ ከፖለቲከኛ ባልተናነሰ የመንግሥታትን ጉድፍ በማጋለጥና መንግሥትን በመተቸት አቤ ጉበኛን የሚወዳደር የለም። ለዜጎች ግንባር ቀደም ተቆርቋሪ መሆኑ ከድርሰት ስራዎቹ በተጨማሪ ተወዳጅነትን አትርፎለታል።
በብዕር ከሚያደርገው ተጋድሎ ባሻገር ለጭቁኖች ነፃነት ለመታገል ወስኖ በሰኔ 1957 ዓ.ም ለሚደረገው የእንደራሴነት ምርጫ ራሱን እጩ አድርጎ አቀረበ። ይህ የአቤ ድርጊት ያልተዋጠላቸውና ብዕሩ እንቅልፍ የነሳቸው ሹማምንት አቤን ለማጥቃት ቆርጠው ተነሱ። አቤን የሚደግፉ ሰዎች በመብዛታቸው በመንግሥት እገዳ ተጣለበት። በፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር እንዲውል ተደረገ። በግዞት ወደ ኢሉባቦር ጠቅላይ ግዛት ተልኮ ቆየ።
የሕዝቡን ችግር ለአደባባይ በማብቃቱ ግዞት ቢላክም ተስፋ ሳይቆርጥ የተለያዩ ጽሑፎችን ማዘጋጀት ጀመረ። ከግዞት እንደተመለሰም ‹‹የሐሜት ሱሰኞች›› የተሰኘ መጽሐፉን አሳተመ። በማስከተልም ‹‹አንድ ለእናቱ›› የተባለውን መጽሐፉን በ602 ገፆች ከሽኖ ለሕትመት አቀረበ። ‹‹መስኮት››፣ ‹‹እድል ነው በደል ነው›› እንዲሁም ‹‹ጎብላንድ አጭበርባሪዋ ጦጣ›› የተሰኙ ስራዎቹን ያሳተመው በዚህ ወቅት ነበር። ‹‹ጎብላንድ አጭበርባሪዋ ጦጣ›› ለዳኛቸው ወርቁ ‹‹አደፍርስ›› እና ለሰለሞን ደሬሳ ‹‹ልጅነት›› የተፃፈ ተሳላቂ የመልስ ምት ነው ይባላል።
ከዚህ በኋላ አቤ የ International Writing Fellowship Program ላይ ለመሳተፍ ወደ አሜሪካ አቀና። በወቅቱ በነበረው የተማሪዎች ንቅናቄ ውስጥ በተወሰነ መልኩ ተሳትፏል። ‹‹የሀገሬን ጉዳይ ሀገሬ ውስጥ ሆኜ እከታተላለሁ›› ብሎ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ።
ወደ ሀገሩ ከተመለሰ በኋላ ለውጡን (ሕዝባዊ አብዮቱን) ይጠቅማል ባለው መልኩ በብዕሩ ሃሳብ ማዋጣቱን ቀጠለ። ደርግ ወደ ስልጣን መጣ በኋላም ‹‹የወታደሮች አገዛዝ ለሀገር አይጠቅምም። ወታደር አገርና ሕዝብን ነው መጠበቅ ያለበት። ወታደር የሲቪል አስተዳደር ውስጥ ገብቶ ማተራመስ የለበትም›› እያለ ስርዓቱን በግልፅ ይቃወም ነበር።
ወታደራዊ ቡድን ወደ ስልጣን መምጣቱ ያልተዋጠለት አቤ፤የደርግ መንግሥት እንዲስተካከል ምክረ ሃሳብ በመስጠት ብዙ ጥሯል። አብዮቱ አገሪቱን ወደ አዘቅት ውስጥ እንዳይከታት በመስጋቱ ቀደም ሲል የታገደበትን ‹‹አልወለድም››ን ለማስተማሪያነት ብሎ በድጋሜ አሳትሞ አሰራጨው። ሹማምንቱ ግን አሁንም አልተደሰቱም።
በ1968 ዓ.ም ‹‹ፖለቲካና ፖለቲከኞቹ›› የተባለውን የተውኔት ስራውን በሐገር ፍቅር ትያትር ለሕዝብ አቀረበ። ይህ ስራው የዘመኑን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ሙልጭ አድርጐ የተቸበት ነው። ተውኔቱ የወቅቱን ሹማምንት ከማስቆጣቱም በተጨማሪ ‹‹ምሁራን ፋሺስቶች›› ከሚላቸው ሰዎች ጋር ያለውን ቅራኔ አሰፋው።
ለአማርኛ አንባቢው በውብ አማርኛ፤በእንግሊዝኛ ለሚያነቡ ዓለም አቀፍ አንባቢያን ደግሞ በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች ጽፎ በማሳተም ታላቅ የብዕር ሰውነቱን ያስመሰከረው አቤ ጉበኛ፤ በማስፈራራት የማይበገርና በገንዘብ የማይደለል መንፈሰ ጠንካራ ደራሲ ነበር።
አቤ ሲፅፍ እንዲህ ብሏል … ‹‹ … ሕዝብን የምትጨቁኑበትን መንግሥት በፍፁም እቃወማለሁ። በዚህ ምክንያት ልትገድሉኝ ትችላላችሁ። ሞት ስትፈርዱብኝም የምፀፀት ይመስላችኋል። እኔ በዚህ ብፀፀት እንደ እናንተ ቂል ነኝ። መጥፎ ሥራችሁንና ህዝብን መጨቆናችሁን የምትተው ካልሆነ መቶ ጊዜ እሞታለሁ። እንደገና ብወለድ፣ መቶ ጊዜ የገደላችሁኝ መሆናችሁንም ባስታውስ ይህ መቀጫ ሁኖኝ ዝም ልላችሁ አልችልም !››
ባለቅኔና ገጣሚ አቤ ጉበኛ ከ20 በላይ የልብ ወለድ፣ የድራማ፣ የግጥምና የቅኔ እንዲሁም የወግ መጽሐፍትን አሳትሟል። ከስራዎቹ መካከልም፡
– ከመቅሰፍት ሰራዊት ይጠንቀቅ ሰውነት
– የሮም አወዳደቅ
– ቂመኛው ባሕታዊ
– የፓትሪስ ሉሙምባ አሳዛኝ አሟሟት – The
Tragedy of Patrice Lumumba
– የአመጽ ኑዛዜ
– አልወለድም
– የፍጡራን ኑሮ
– የራሄል እንባ
– ምልክዓም ሰይፈ ነበልባል
– ከልታማዋ እህቴ
– የሐሜት ሱሰኞች
– አንድ ለእናቱ
– መስኮት
– መሬት የማን ነው?
– የደካሞች ወጥመድ
– እድል ነው? በደል ነው?
– ፖለቲካና ፖለቲከኞቹ
– The Savage Girl
– Defiance … የሚሉት ይጠቀሳሉ።
አቤ ጉበኛ ከ1969 ዓ.ም ጀምሮ አዲስ አበባን ትቶ ኑሮውን በባሕር ዳር አደረገ። በ1972 ዓ.ም ሲደክምበት የከረመውን ድርሰቱን ለማሳተም ወደ አዲስ አበባ ጎራ ያለበት አጋጣሚ የሕይወቱ ፍፃሜ ሆነ። የካቲት አንድ ቀን 1972 ዓ.ም አቤ አዲስ አበባ፣ ጎጃም በረንዳ አካባቢ መንገድ ላይ ወድቆ ‹‹አንሱኝ … ተጠቃሁ …›› እያለ ተገኘ።
በማግሥቱ እሑድ ወደ ሆስፒታል ቢወሰድም ሕይወቱን ማትረፍ ሳይቻል ቀረ። አስክሬኑ ወደ ትውልድ ቦታው ተወስዶም ማክሰኞ፣ የካቲት አራት ቀን 1972 ዓ.ም በባህር ዳር አውራጃ፣ በአቸፈር ወረዳ፣ ይስማላ ጊዮርጊስ ገዳም ተቀበረ።
የታላቁ ደራሲ አሟሟት ጉዳይ ለበርካታ ዓመታት ተዳፍኖ ቆየ። ኤልያስ አያልነህ ‹‹የአቤ ጉበኛ ብእራዊ ተጋድሎ›› በተሰኘው መጽሐፉ ላይ አቤ ከሞተ ከ19 አመታት በኋላ የዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል የአስክሬን ምርመራ ውጤትን ይፋ አደረገው። የምርመራ ውጤቱ እንደሚያስረዳው አቤ የሞተው ስለት በሌለው (በድልዱም) መሳሪያ ጭንቅላቱ ላይ በመመታቱ ምክንያት ብዙ ደም የቋጠረ እብጠት በታችኛው አንጐል ሽፋን ክፍል ሥር በመከሰቱ ነው። አቤ ከደርግ መንግሥት በተሰጠ ትዕዛዝ ሳይገደል እንዳልቀረ ብዙዎች ይስማማሉ።