>

ብሔር እና Nation ስለሚባሉት ነገሮች...!!! (አቻምየለህ ታምሩ)

ብሔር እና Nation ስለሚባሉት ነገሮች…!!!

አቻምየለህ ታምሩ

*….ብሔር እና Nation የሚባሉት የግዕዝና የእንግሊዝኛ ቃላት «ያ ትውልድ» ለመባል የበቃው ማሰብ የማይችል መንጋ “የነገድ መንግሥት” ለመመስረት ሲነሳ የአብዮት ፕሮግራሙ ማዕከል ያደረጋቸው  ንድፈ ሀሳቦች ናቸው።  ለመሆኑ ብሔር  እና Nation የሚባሉት ቃላት ያለፉትን 46 ዓመታት  የዘር ክፍፍል መሠረት የጣሉት የ “ያ ትውልድ” ደናቁርት ሲደጋግሙት የኖሩት ትርጉምና ፍቺ ያላቸው ቃላት ናቸውን?  “ነገርን ከስሩ ውኃን ከጥሩ” እንዲሉ እስቲ ብሔር እና Nation የሚባሉት ቃላት ስረ መሠረት[classical definition] ምን እንደሆነ  እንመልከት
ብሔር የግዕዝ ቃል ሲሆን ታላቁ የግዕዝ ሊቅ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ባዘጋጁት «መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ» በሚለው የመዝገበ ቃላት መጽሐፋቸው “ሰፈር፣ ምድር፣ ከተማ፣ ገጠር፣ በድንበር የተወሰነ፣ በመንግሥት በሕግ፣ በሥርዓት የተለየ አገር ማለት ነው።” ይሉታል። ሌለኛው የግዕዝ ሊቅ አለቃ ደስታ ተክለ ወልድ ደግሞ  “ዐዲስ፡ ያማርኛ፡ መዝገበ፡ ቃላት” በሚል ባዘጋጁት የመዝገበ ቃላት መጽሐፋቸው “ብሔር ማለት ሀገር ማለት ነው” ሲሉ ይፈቱታል።
ሁለቱ  የግዕዝ ሊቃውንት ከሰጡት ፍቺ  ብሔር ማለት ሀገር ማለት እንደሆነ መገንዘብ እንችላለን። ሀገር ማለት ደግሞ በድንበር የተከለለ መሬት፣ ባንድ መንግሥትና ሕዝብ ግዛት ሥር ሆኖ ግዛቱም በብዙኃኑ ዓለም አቀፍ አገራት እውቅና ያገኘ ነው። ይህ ማለት ብሔር  የሚገልጽው ሰውን ሳይሆን  መሬቱን ነው።  በመሆኑም በዚህ ብሔር ማለት ሰውን ከሰው ለይቶ አግላይነትና አድሏዊነት የሌለውን ሀገርን እንጂ ዛሬ በሀገራችን እንደሚታየው በአንድ አገር ውስጥ ሆኖ በዋናነት ቋንቋን ማዕከል በማድረግ ሰውን ከሰው ለይቶ አግላይ፣ አድሏዊና ኢሰብአዊ የሆነ የማንነት መገለጫ አይደለም።
Nation ወደሚለው የእንግሊዝኛ ቃል ስንሄድ  ጆሴፍ ስታሊን የሰጠውን classical ትርጉም  እናገኛለን። ጆሴፍ ስታሊን “Marxism and The National Question” በሚል ባሳተመው መጽሐፉ ከገጽ 7 – 8 ስለ Nation የሚከተለውን ትርጉም ሰጥቷል፤
“Nation በታሪክ የተጣመረ፣  በጋራ ቋንቋ፣  የግዛት አንድነትና ኤኮኖሚ ላይ የተመሠረተ በጋራ ባሕል መንጸባረቅ የሚችል ሥነ ልቡና ያለው የተረጋጋ ማኅበረሰብ ነው።”
ከዚህ በተጨማሪ ጆሴፍ ስታሊን  ስለNation የሚከተሉትን ነጥቦች አጽንኦት ሰጥቶ ጽፏል፤
1. Nation  እንደማንኛውም ታሪካዊ ክስተት ይለወጣል፤ ይፈጠራል፤ ይከስማልም።
2. ለNation  መለኪያነት የተቀመጡት መመዘኛዎች [ቀደም ሲል የተቀመጡትን ማለት ነው]  አንዳቸው ተመዘው Nationን ሊመሠርቱ አይችሉም።
3. ከተቀመጡት መመዘኛዎች አንዱ መመዘኛ እንኳን ቢጎድል Nation፣ Nation መሆኑ ያቆማል። ይህንም ለማብራራት እንግሊዝና አሜሪካውያን  አንድ ቋንቋ  እየተናገሩ ሌሎቹ መመዘኛዎች ባለመሙዋላታቸው አንድ Nation እንዳልሆኑ ይጠቅሳል።
ኦሮሞ፣ አማራ፣ ትግሬ ወዘተ. . . አገሮች ስላልሆኑ  የግዕዙን ብሔር አይወክሉም። በመሆኑም ብሔር የሚለውን ብያኔ የምታሟላ  አገር የሆነችዋ ኢትዮጵያ ናት።
ከዚህ በተጨማሪ የብያኔው ፈጣሪ ጆሴፍ ስታሊን በነገረን ትርጉም መሰረት አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ፣ ወዘተ. . . የሚባሉት የቋንቋ ብቻ ስብስቦች  ስለሆኑ ታሪክ፣ ባሕል፣ ኤኮኖሚ፣ ጂኦግራፊ የሚሉት መመዘኛዎች ሙሉ በሙሉ የጣሉ በመሆናቸው አንዳቸውም Nation አይደሉም።  ጆሴፍ ስታሊን  Nation የሚለውን ሲገልጽ ካስቀመጣቸው መመዘኛዎች አንዱ  እንኳን ቢጎድል Nation፣ Nation መሆኑን ያቆማል ስላለ በቋንቋ ላይ ብቻ የተመሰረተ ስብስብ  Nation ሊሆን አይችልም።
በመሆኑም የግዕዙ  ብሔር እና  የእንግሊዝኛው Nation  የሚገልጹት ኢትዮጵያን ብቻ ነው። ቀደም ሲል እንዳልሁት ብሔር የሚለው የግዕዝ ቃል አገር ማለት ስለሆነና ኢትዮጵያም አገር ስለሆነች ኢትዮጵያ ብሔር ነች ማለት ይቻላል።  በጆሴፍ ስታሊን  ክላሲካል ትርጉም መሰረት  አንድ Nation፣ Nation ለመባል ማሟላት የግድ ይለዋል ከተባሉ አምስት መመዘኛዎች መካከል ኢትዮጵያ አራቱን መመዘኛዎች ሙሉ በሙሉ ታሟላለች። ማለትም ኢትዮጵያ የተወራረሰ ባሕልና ታሪክ፤ በኢኮኖሚና በጂኦግራፊ አንድ የሆነ ማኅበረሰብ ያለባት አገር ስለሆነች ኢትዮጵያ ጆሴፍ ስታሉን Nation የሚለውን ቃል ለመበየን የተጠቀመባቸውን መመዘኛዎች ታሟላለች።
አምስተኛው መመዘኛ የጋራ መግባቢያ ቋንቋ ነው።  ኢትዮጵያ ውስጥ ዘጠኝ ክልሎችና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች ይገኛሉ። አማርኛ የፌደራል መንግሥት ተብዮው የስራ ቋንቋ  ብቻ ሳይሆን ከዘጠኙ ክልሎች  መካከል የአምስቱ  ክልሎች እና የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮችም  የስራ ቋንቋ ነው። ስለሆነም  አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ በአማርኛ ይግባባል። ይህ ማለት ኢትዮጵያውያን  ጆሴፍ ስታሊን አንድ Nation፣ Nation ለመባል ሊያሟላው ይገባል ያለውን አምስተኛውን መመዘኛ ማለትም  የጋራ መግባቢያ ቋንቋን  እንደ ማኅበረሰብ ባመዛኙ ያሟላሉ።  በአማርኛ የጻፍሑትን ይህን ጽሑፍ ካለበቡ በኋላ “አማርኛ ስለማንችል  ኢትዮጵያ Nation ለመባል አምስተኛውም መመዘኛ አታሟላም” ብለው በአማርኛ  ወይም በእንግሊዝኛ አስተያየት የሚሰጡ አንዳንዶች አይጠፉም 🙂
ባጭሩ ከአምስቱ የጆሴፍ ስታሊን የ Nation መመዘኛዎች መካከል አራቱ ለኢትዮጵያ አንድ Nation መሆን ይሰራሉ። አምስተኛው መመዘኛው ባመዛኙ ለኢትዮጵያ አንድ Nation መሆን ይሰራል።  ኢትዮጵያን የአማራ Nation ፣ የኦሮሞ Nation፣ የትግሬ Nation ፣ ወዘተ… የፈጠሯት አድርጎ የ80 ትንንሽ Nations ኅብረት ለማድረግ ግን የሚሰራው መመዘኛ ቋንቋ ብቻ ነው።
ስለዚህ ለማሰብ ፈቃደኛ ካልሆንን በስተቀር የብሔርም ሆነ የNation መመዘኛ  ተደርገው  በተቀመጡት መስፈርቶች መሰረት በግዕዝ ብሔር እና  በእንግሊዝኛ Nation ለመባል የምትበቃው ኢትዮጵያ  ብቻ እንጂ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ፣ ወዘተ የሚባሉት አይደሉም!
Filed in: Amharic