>
6:37 am - Friday March 31, 2023

እስክንድር ነጋ እና ምርጫ 2013 (ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ ታዬ)

እስክንድር ነጋ እና ምርጫ 2013

ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ ታዬ


ኢህአዲግ መራራ እውነትን የያዙ፣ በእውነት ላይ የማይደራደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ መሪዎችን እና ግለሰቦችን ‘አሸባሪ’ በሚል ስም ወንጀለኛ ሲያደርጋቸው እንደነበረ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ አሁንም ኦህዴድ/ብልፅግና ተመሳሳይ  መንገድ እየተከተለ ነው፡፡ የእነ እስክንድር ነጋ እና የባልደራስ አመራሮች ክስ እንደ ምሳሌ ሊጠቀስ የሚችል የፍትህ እጦታችን መገለጫ ነው፡፡

እስክንድር ነጋ እስር የሚገባው ዜጋ አልነበረም፡፡ እስክንድር ነጋ እውነትን ያነገበ፣ ኢትዮጵያዊነትን የሚያቀነቅን፣ ህዝቡን የሚያከብር፣ ለሀገር እና ለህዝብ ህይወቱን አሳልፎ የሰጠ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ እስክንድር ነጋ ቅን፣ ትሁት እና የዓላማ ፅናት ያለው ብርቱ ሰው ነው፤ እስክንድር ነጋ ጉምቱ ጋዜጠኛ እና የፖለቲካ አክቲቪስ ነው፡፡ እስክንድር ነጋ የፖለቲካ መሪ እና የፖለቲካ እስረኛ ነው፡፡ እስክንድር ነጋ በሁለት አንባገነን መንግስታት ከአስር ጊዜ በላይ ለእስር የተዳረገ ዜጋ ነው፤ እስክንድር ነጋ የተለያዩ ዓለም – አቀፍ ሽለማቶች ባለቤት ነው፤ እስክንድር ነጋ እረፍት – የለሽ የነፃነት ታጋይ እና የነፃነት ቀንዲል ነው፤ እስክንድር ነጋ የኢትዩጲያ ማንዴላ ነው፤ እስክንድር ነጋ የኢትዩጲያ  ጋንዲ ነው፤ እስክንድር ነጋ የኢትዮጵያ ማርቲን ሉተር ኪንግ ነው፡፡ እስክንድር ነጋ ለእውነት በመቆም የሚያስከፍለውን ዋጋ እየከፈለ ነፍሱን በእውነት እጦት ሳያራቁት፤ እውነትን ለስልጣን፣ ለምቾት፣ ለምድራዊ ድሎት ሳይቀይር በአንባ ገነኖች ፊት መራራ እውነትን እያነገበ፣ እውነትን በመናገር ፋና ወጊ የሆነ የነፃነታችን ምልክት ነው፡፡ 

ታዲያ ይህንን ሰው በግፍ አስሮ ምርጫ ማካሄድ እውን ምርጫውን ፍትሀዊ ያደርገዋል? እውን ይህንን ንጹህ ሰው ያለ ፍትህ አስሮ ምርጫ አሸነፍሁ ማለት ያስችላል? ገዥው ፓርቲ ማሸነፍስ አያሸንፍም እንዴው ‘’  ካልሰራ በስተቀር እንዴው ግን ኦህዴድ/ብልፅግና ቢያሸንፍ እንኳን እውን ምርጫው ተዓማኒነት ይኖረዋልን? የተፎካካሪ ፓርቲ መሪን በግፍ አስሮ በዓለም-አቀፍ የምርጫ መስፈርቶች አሸነፍኩ ለማለት የሚያስችል ‘ሞራል’ አለን

ገዥው ፓርቲ ወደ ቀልቡ ተመልሶ እስክንድርን እና የባልደራስ አመራሮችን እንዲፈታ እንጠይቃለን፡፡ እስክንድር ነጋ እና የባልደራስ አመራሮች መራራ እውነትን በማንገባቸው ምክንያት ብቻ ጥቃት የደረሰባቸው ዜጎቻችን ስለሆኑ ፍትህ ያስፈልጋቸዋል፡፡ የሻትናትን ፍትህ እናመጣታለን፣ እውነት ከእኛ ጋር ነው፤ ፍትህ ከእኛ ጋር ነው፡፡ ህዝባችን ከእኛ ጋር ነው፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ ፈጣሪ ከእኛ ጋር ነው፡፡  ፈጣሪ አገራችንን እና ህዝባችንን ይጠብቅ፡፡ ፍትህ ለባልደራስ አመራሮች፡፡

Filed in: Amharic