>
7:19 am - Thursday March 23, 2023

የአሰብን ነገር ካነሳን...!!! ጥላሁን እምሩ (PhD)

የአሰብን ነገር ካነሳን…!!!

ጥላሁን እምሩ (PhD)

ሰሞኑን ከወደ ኤርትራ ብቅ ያለ አንድ ዜና ማህበራዊ ሚዲያው ላይ መነጋገሪያ ሆኖ ብናይ ማብራሪያ ቢጤ ጣል እናደርግ ዘንድ ተነሳሳን። የዜናው ምንጭ Eritrean Press ቢሆንም ጉዳዩ አሳሳቢ ነውና ማብራሪያ ይሻል።
ዜናው በአጭሩ ሲጠቃለል «ኢትዮጵያ የአሰብን ወደብ በዶላር ሳይሆን በብር ልትጠቀም ነው።» የሚል ሲሆን ከዚህ አማላይ ርዕስ ወረድ ብሎ ለኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ምክንያት የሆነውና ኤርትራን ከሸማችነት ወደ ኤክስፖርተርናት የቀየረው በሁሉተ ሀገሮች መካከል ይካሄድ የነበረውን ንግድ የሚታከክ ሀሳብም ይዟል።
እዚሁ መንደር ያየሁት ዋና ትችት «ኤርትራ የአሰብ ወደብ ግልጋሎትን ሸጣ በምታገኘው ብር ሸቀጦችን ከኛው ገዝታ ኤክስፖርተር ትሆናለች» የሚል ነው። ይህ ትችት ብቻውን ውሀ የሚቋጥር አይደለም። የወደብ ሽያጩ በዶላር ቢካሄድም፣ ኤርትራ ከኢትዮጵያ የምትፈልገውን ነገር በዶላር ገዝታ ኤክስፖርት እንዳታደርግ የሚያግዳት ምንም ነገር የለም። አዋጪ ሆኖ እስካገኘቺው ድረስ።
ይህ እንዳለ ሆኖ «the devil is in the details» ኢንዲሉ በዚህ አጭር ዜና ውስጥም ውናው ችግር የተጠቀሰው የጽሁፉ ርዕስ ላይ ሳይሆን ወደ ታች ወረድ ብሎ ነው። ይህንን ችግርና ሌሎች ሊፈጠሩ የሚችሉ ተመሳሳይ ችግሮችን ወረድ ብዬ እመለስባቸዋለሁ።
እነዚህን ችግሮች ከመጥቀሴ በፊት፣ ዜናው ርዕሱ ላይ እንደተጠቀሰው ኢትዮጵያ አሰብን በብር ብቻ ብትጠቀም (ሌላ ምንም ተያያዥ conditionalities ሳይኖሩ) ኢትዮጵያ የምታገኛቸው ጥቅሞችን በአጭሩ ልጥቀስ። የመጀመሪያውና ቀጥተኛው ጥቅም ለወደብ ጥቅም ኢትዮጵያ በየአመቱ የምታወጣውን በቢሊዮኖች የሚቆጠር የዶላር ወጪን ማስቀረት ነው። በተጨማሪም፣ ተጨማሪ የወደብ አማራጭ ማግኘታችን የአፍሪካ ቀንድ ላይ ያሉ ሌሎች ወደቦችን (በተለይ የጅቡቲን ወደብ) አሁን ከምንከፍለው ባነሰ ወጪ መጠቀም እንድንችል ያደርጋል። ምናልባትም ኢትዮጵያ ምስራቅ አፍሪካ ላይ የሚኖራትን ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ የበለጠ ሊጨመረው ይችላል። ስለዚህ  በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል በመርህ ላይ የተመሰረተ ግንኙነት እንዲፈጠር ማድረግ ከተቻለ ኢትዮጵያ የአሰብን ወደብ መጠቀም መቻሏ የሚፈጥረው እድል ከኤርትራ ጋር ያለን ግንኙነት ላይ የተወሰነ አይሆንም። («በመርህ ላይ» የሚለው ይሰመርበት) የኤርትራ ማዕከላዊ ባንክ ብርን ማተም ስለማይችል፣ የወደብ አገልግሎት  ሽያጩ በብር ከተደረገ ብርን ከኢትዮጵያ ድንበር ውጪ ተቀባይነት ያለው ገንዘብ ስለሚያደርገው ብር የበለጠ ጠንካራ ይሆናል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገንዘብን ሲያትም የተወሰነው ብር ድንበራችንን ተሻግሮ ስለሚወጣ በአሁን ወቅት እየተፈጠረ እንዳለው የዋጋ ግሽበት የመፈጠር እድሉ ይቀንሳል።
ነገር ግን፣ ከላይ የጠቀስኳቸው በጎ ውጤቶች መሬት ላይ የሚወርዱት በሁለቱ ሀገሮች መካከል የሚደረገው ግብይት (የወደብ አገልግሎቱን ጨምሮ) በመርህ ላይ የተመሰረተ ከሆነና ኤርትራ ምንም ቅደመ ሁኔታ ሳታስቀምጥ ለምትሸጠው የወደብ አገልግሎት ብርን ለመቀበል ፈቃደኛ ከሆነች ብቻ ነው። ሌላው ይቅርና በአጭር ጊዜ ውስጥ እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች እንደማይሆኑ ግልጽ ነው። ይህ ከተፈጠረ ብዙ መዘዞች ተከትለው ሊመጡ ይችላሉ።
በመጀመሪያ ይኸው አጭር ጽሁፍ ኤርትራ ከኢትዮጵያ የኤሌክሪክ ሀይልንና ሌሎችን ሸቀጦች በናቅፋ («በናቅፋ» የሚለው ይሰመርበት) እንደምትገዛም ይገልጻል። ይህ መታሰብም የሌለበት መንገድ ነው። ሀገራችን ከውጭ ከምታስገባቸው ሸቀጦችና አግልግሎቶች እንዲሁም ከናቅፋ ደካማነት አንጻር ይህንን መፍቀድ ማለት ወርቅን በወረቀት ለመቀየር መስማማት ማለት ነው። ይህ እንዲሆን ከተፈቀደ የኤርትራ ማዕከላዊ ባንክ ከገንዘብ አታሚነት ሸቀጦችን ያለምንም ወጪ ወደሚያመርት ፋብሪካነት ተቀየረ ማለት ነው።
ሌላኛው ችግር በብር፣ በናቅፋና በዶላር መካከል ከሚኖረው የምንዛሪ ስርዐት ጋር የሚያያዝ ነው። በሁለቱ ሀገሮች መካከል የሚደረገው ንግድ በብር ሆኖም በገንዘቦቹ መካከል የሚኖርው ምንዛሪ የትወሰነ (pegged) ከሆነም ከላይ የተጠቀሰው ጣጣ በጓሮ በር መከሰቱ አይቀርም። ናቅፋ ከብር ጋር የሚኖረውን ምንዛሪ ከሚገባው በላይ በማድረግ (overvalued exchange rate) ኤርትራ ከኢትዮጵያ የምትገዛውን ሸቀጦችና አገልግሎቶች ርካሽ በማድረግ አላግባብ የሆነ ጥቅም ልትወስድ ትችላለች። በሁለቱ ገንዘቦች መካከል የሚኖረው ምንዛሪ ተንሳፋፊ ከሆነ (floating exchange rate) ኢትዮጵያ ከኤርትራ ከወደብ ውጪ የምትፈልገው ብዙ ነገር ስለማይኖር ምንዛሪው ናቅፋን ርካሽ ያደርገዋል። ይህም ማለት የኢትዮጵያ ሸቀጦች ለኤርትራውያን ውድ ይሆናሉ።
በብዙ ሀሳብ የታጨወው አጭር ዜና ሌላ የሚያሰጋ ሀሳብም ተለጥፎበታል።  ኢትዮጵያ ለኤርትራ የምትከፍለው የወደብ ክፍያ ብር ይሁን እንጂ የብር ዋጋ ከዶላር ጋር በሚኖረው ምንዛሪ ላይ ይወሰናል (dollar indexation)። የብር የመግዛት አቅም እየቀነሰ በሄደ ቁጥር የወደብ ክፍያው እየጨመረ ይሄዳል ማለት ነው። ብር ከዶላር ጋር ያለው ምንዛሪ ከጥቅምት 2012 እስከ ጥቅምት 2013 ድረስ በ28% ጨምሯል። የወደብ አገልግሎት በብር ቢተመን፣ ለኤርትራ የሚከፈለው የወደብ ወጪ በ28% ጨመረ ማለት ነው።
ሌላኛው ሊመጣ የሚችል አደጋ የፎርጅድ ብር መብዛት ነው። የወደብ አገልግሎት ሽያጩ ሙሉ በሙሉ በብር ቢደረግ እንኳ አንድ የውጭ ንግድ ላይ የተሳተፈ ኤርትራዊ ፎርጅድ የብር ኖቶችን ይዞ ወደ ኢትዮጵያ በመግባት ከኢትዮጵያውያን ኤክፖርተሮች ሸቀጦችን ሊገዛ ሊመጣ ይችላል። በቅርቡ የፎርጅድ ብር ኢኮኖሚው ውስጥ መብዛትን መቀነስ ከግንዛቤ ውስጥ አስገብቶ በብዙ ቢሊዮን ብር ወጪ የተደረገው የብሮ ኖት ቅየራ ትርጉም አልባ ሆነ ማለት ነው።
ኢትዮጵያ ውስጥ በሙስና የተዘረፈ ገንዘብ በቀላሉ ወደ ኤርትራ ሊሻገርም ይችላል። በአሁኑ ወቅት በሙስና የተከማቸ ገንዘብን ከኢትዮጵያ ለማሸሽ በሌሎች ሀገራት ውስጥ ተቀባይነት ወዳለው ገንዘብ (ዶላር፣ ዩሮ፣ … ) መቀየር ያስፈልጋል። ብር ጎረቤት ሀገሮች ውስጥ መንቀሳቀስ ከጀመረ ግን ይህንን ማድረግ አያስፈልግም። ብሩን ተሸክሞ ሌሎች ሀገሮች ድረስ ይዞ መሄድም ይቻላል። በሙስና የተዘረፈን ገንዘብ ለማሸሽ ቀላል በማድረግ ሙስናን ሊያበረታታ ይችላል ማለት ነው።
ለማጠቃለል፣ ለጊዜው ፖሊቲካዊ ግንኙነታችን ራሱ ጠንካራ በሆነ መሰረት ላይ ባልተጣለበት ሁኔታ ጣጣ ይዞ ሊመጣ የሚችል ነገር ከመጀመር ከሌሎች ሀገሮች ጋር እንደምንገበያየው በዶላርና አለም ላይ ተቀባይነት ባላቸው ገንዘቦች መቀጠል ይሻላል። ብር በጎረቤት ሀገሮች ውስጥ ያለው ተቀባይነት በጨመረ ቁጥር ለኢትዮጵያ ዘላቂ ጥቅም ያለው መሆኑ እሙን ቢሆንም፣ በመርህ ላይ ያልተመሰረተና በሩጫ የሚደረግ ስምምነት መጨረሻው እንደማያምር ለማወቅ የራሳችንን ታሪክ 20 አመት ወደኋላ ተጉዘን መመልከት ብቻ ይበቃል። «ሲሮጡ የታጠቁት ሲሮጡ ይፈታል» ነውና ነገሩ ነግሮችን ጊዜ ሰጥቶ፣ አውጥቶና አውርዶ መፈጸም የሀገርን ዘላቂ ጥቅም ከማስከበር በተጨማሪም ከጎረቤት ሀገር ጋር የሚደረግ አላስፈላጊ  እሰጣአገባን ከወዲሁ ያስቀራል።
Filed in: Amharic