>

‹‹የእምዬን ቆራጥነት፣ የእቴጌን ብልሃት ፣ የኢትዮጵያን ክብር ሰው ዝም ይበልና ተራራው ይመስክር››  (በታርቆ ክንዴ)

‹‹የእምዬን ቆራጥነት፣ የእቴጌን ብልሃት ፣ የኢትዮጵያን ክብር ሰው ዝም ይበልና ተራራው ይመስክር›› 

በታርቆ ክንዴ 

ተራራዎች እንደ ሰው ቢናገሩ፣ ያዩትን ቢመሰክሩ ስንቶች ባፈሩ፤  ኢትዮጵያዊያን ለክብር፣ ለፅኑ ኢትዮጵያዊነትና ለማይሸነፍ ጀግንነት የተመላለሱባቸው ተራራዎች አፍ ቢኖራቸው ምንኛ በተደነቅን ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ተራራዎች ውበት ብቻ ሳይሆኑ ለክብር ሕብረት መፍጠር የሚችሉ ናቸው፡፡ አፈጣጠራቸው ጠላት አያላውሱም፣ ለደፈራቸውም ከኢትዮጵያዊያን ጋር ሆነው ወደ ሀገሩ አይመልሱም፤ በዚያው ለወሬ ነጋሪ ሳያስቀሩ ይጨርሳሉ እንጂ፡፡
የዓድዋን ጀግንነት፣ የኢትዮጵያዊያንን ሕብረት፣ የኢትዮጵያዊነትን ፅናት፣ የአርበኞችን እንቢተኝነት፣ አልሞ ተኳሽነት ላስታወሰ ሁሉ ኢትዮጵያዊ ስለሆንኩ ተመስገን ማለቱ አይቀርም፡፡  ኢትዮጵያዊያን አስቀድመው አይፎክሩም፣ ወሬ ሰምተው አይደነብሩም፣ አይሸበሩም፣ በአውደ ውጊያ አያፈገፍጉም፤  አትንኩን ካሉ እነርሱን ማሸነፊያው አለመንካት ብቻ ነው፡፡ ክብራቸውን የነካ ወዮለት! የተወለደበትን ቀን ይረግማል፣ እንደ ጮራ የፈካው አልቦ ሕልሙ ይኮሰምናል፤ የጠነከረው ጉልበቱ ይደክማል፡፡
በዓድዋ ተራራ የጥቁሮች ፀሐይ ላትጠልቅ በራች፣ እብሪት የወጠራት የወራሪ ነጭ ጉልበት ኮሰመነች፣ በአፍሪካ ፀሐይ ወጣ፣ የጥቁር ነፃነት መጣ፤ የሮም ወይዛዝርት አለቀሱ፣ የሮም መኳንንት ኮሰሱ፣ ኢትዮጵያዊያን አርበኞች እንደ አንበሳ አገሱ፤ ዓለም  ግሩም አለች፣ አብዝታ ተደነቀች፣ ጣልያን አፈረች፣ ኢትዮጵያ ኮራች፤ ለምን ካሉ ጀግና ወልዳለችና፡፡
ዓድዋ ለኢትዮጵያዊያን የማይጠፋ አርማቸው፣ የማያረጅ ጌጣቸው፣ ከሩቅ የሚታይ ምልክታቸው፣ ዓለም የሰማው ድምፃቸው፣ የተባበረ ክንዳቸው፣ ከፍ ያለ ክብራቸው ነው፡፡ ዓድዋን ኢትዮጵያዊያን   ይመኩበታል ፣ ያከብሩታል፡፡
የውጫሌ ውል ከተደረገ በኋላ አጤ ምኒልክ የዛኔውን ደጅ አዝማች መኮንን ወደ ጣልያን ላኩ፡፡ ደጅ አዝማች መኮንን እና አብረዋቸው የሄዱት ሁሉ በሮም የክብር አቀባበል ተደረገላቸው፡፡ በሮም የሚገኙ ሥፍራዎችን ሁሉ ገበኙ፡፡ ፍቅር ሆነ፡፡ የኢትዮጵያዊያን የምር የጣልያን ግን ድብቅ ፍቅር፡፡ በዚያ መካከል የጣልያን ጋዜጦች ለኢትዮጵያዊያን እንግዳ የሆነ ነገር ይዘው መውጣት ጀመሩ፡፡
አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በሚለው መጻሕፋቸው ‹‹ በዚህ ደስታና ፍቅር መካከል ኢትዮጵያ በኢጣልያ መንግሥት ውስጥ ልትኖር ውል ተደረገ የሚል ወሬ በጋዜጣ ላይ ተጣፈ፡፡ እቴጌና ጃንሆይ ጥበብ ተማር ብለው ኢጣልያ ሀገር የሠደዱት አንድ አፈወርቅ የሚባል ትውልዱ የዘጌ የሆነ የኢትዮጵያ ልጅ ከዚያው ነበርና ይሄን ቃል ተጋዜጣ ላይ አይቶ ለደጅ አዝማች መኮንን በኢትዮጵያ ምነው እንዲህ ያለ ክፉ ነገር ተደረገበተት ብሎ ነገረ፡፡ ደጅ አዝማች መኮንን ቶሎ ብለው ይሄ ነገር ፍቅራችንን ያደፈርስብናልና ይሄ ወሬ ይታረም፣ አይሆንም ብለው ለኮንት አንቶኔሊ ተናገሩ፡፡ ወዲያው ደጅ አዝማች መኮንን እና ኮንት አንቶኔሊ ተጣሉ››
የጣልያን ውስጡ እሾህ የሆነ የውሸት ፍቅር መገለጥ ጀመረ፡፡ ደጅ አዝማች መኮንን ኢየሩሳሌምን ተሳልመው  ወደ ሀገራቸው ተመለሱ፡፡ ደጅ አዝማች መኮንንም ራስ ተብለው ወደ ሐረርጌ ሄዱ፡፡ ድብቅ ዓለማዋ የታወቀባት ጣልያን ኮንቴ ሳልምቤኒ የተባለ መልዕክተኛ ወደ ኢትዮጵያ ላከች፡፡ አጤ ምኒልክ አሳምረው ተቀበሉት፡፡ የውጫሌ ውል ጉዳይ  ተነሳ፡፡ አጤ ምኒልክም ‹‹ኢትዮጵያ ራሷን ቀጥ ለበጥ አድርጋ ችላ በመንግሥቷ አዝዛ ትኖራለች እንጂ በማንም መንግሥት ጥግ ትኖር ዘንድ ከዛሬ በፊትም ከታሪክ አልተገኘም፤ ለንግዴሁም እንዲህ ያለው ነገር አይታለም፤ የውጫሌ ውላችንም የፍቅራችንን፣ የንግዳችንን እንዲህ እንዲህ ያለውን ነገር ይናገራል እንጂ ኢትዮጵያ በኢጣልያ ጥግ ትኖራለች የሚል ታማርኛው ጽሕፈት አልተገኘም፡፡ አሁንም ፍቅራችን እንዳይበላሽ ባስራ ሰባተኛው ክፍል ያለውን ውላችን እናንተ አጥፍታችሁታል ተዉ፤ እኔ ያጠፋሁት ነገር የለኝም፡፡  ኢትዮጵያ በኢጣልያ ጥግ ትኖራለች የሚል ነገር እንኳን በውኔ በህልሜም አላሰብኩትም›› ማለታቸውን አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ መዝግበዋል፡፡
አባ ዳኘው ‹‹ኢትዮጵያ ራሷን ችላ ትኖራለች እንጂ በኢጣልያ ጥግ ልትኖር ምንም ውል አላደረኩም እወቁልኝ›› በማለት ለአውሮፓ ነገሥታት መልዕክት ላኩ፡፡ ጣልያን ውሉ እንዲፀና ብዙ ጥረት አደረገች፡፡ እቴጌና ጃንሆይ የሚቀመሱ አልነበሩም፡፡ ተሥፋ ያጣው የጣልያን መልዕክተኛ በአንበሶች ፊት አንቧርቆ ሄደ፡፡ ጦርነት እንደሚገጥሟቸውም ዛተ፡፡ እቴጌ ንዴታቸው ገነፈለ፡፡  ‹‹የዛሬ ሳምንት አድርገው በዚህ የሚደነግጥልህ የለም፡፡ ሂድ የፎከርክበትን አድርግ እኛም የመጣውን እናነሰዋለን፡፡ እግሩን ለጠጠር፣ ደረቱን ለጦር ሰጥቶ አገሩን የማያድን ሰው ከዚህ ያለ አይመስልህ፡፡ የገዛ ደሙን  ገብሮ ለገዛ ሀገሩ መሞት ጌጥ ነው እንጂ ሞት አይባልም፡፡ አሁንም ሂድ አይምሽብህ የፎከርክበትን በፈለከው ጊዜ አድርገው፤ እኛም ከዚሁ እንቆይሃለን›› አሉ፡፡
የደግ ሕዝብ መሪዎች ደጎቹ እቴጌና እምዬ እንዲያ ያንቧረቀባቸውን ሰው እንደ መልካም ዘመድ ለመጓዣ ሰጋሩን፣ ለመፍጠኛ ጮሌውን አጣምረው ሸኙት፡፡ የጣልያን መንግሥት እርቅ አይሉት ማታለያ በቀደመ ፍቅራችን እንኑር ሲል ትራበርሲን የተባለ መልዕክተኛ ላከ፡፡ የታሰበው ፍቅር ግን አልመጣም፡፡ ብልሁ ንጉሥ ምኒልክ በዚህ መካከል ከራሷ ከጣልያን ጥይት አስላኩ፡፡ ገሚሱ ጥይት ወደ መሀል ሀገር እንደገባ ገሚሱ ግን በአሰብ ወደብ እንዳለ ጣልያን  በጀግኖቹ  ምድር ጦርነት ለማድረግ ጦሯን ላከች፡፡
አባ ዳኘው አልቸኮሉም፡፡ ዝግጅታቸውን አጠናከሩ፡፡  የሀገሬውን ጀግና በአዋጅ አሰባሰቡ፡፡ ጣልያን ገሰገሰች፡፡ አውሮፓውያን ንጉሡ ምኒልክ ፈርቷል እያሉ ማስወራት ጀመሩ፡፡ ጦሩ ተዘጋጄ፡፡ ገስግስ ብለው ተጓዙ፡፡ ራስ መኮንን እና ፊት አውራሪ ገበየሁን ከፊት ለፊት መንገድ ጠራጊ አድርገው ገሰገሱ፡፡ መንገድ ጠራጊዎቹ በየደረሱበት የጣልያንን ተስፈኛ ጦር ለወሬ ነጋሪ ሳይቀር ይደመሰስ ጀመር፡፡ ፈሩ የተባሉት ንጉሥ ግርማቸው አልቻል አለ፡፡ የኢትዮጵያዊያን ክንድ በረታ፡፡ ከየአቅጣጫው የተሰበሰበው የኢትዮጵያ አርበኛ የጠላትን ፊት እንደ መንጠር እሳት ይለበልበው ጀመር፡፡
ጣልያን አምባላጌ ላይ እንዳልነበር ሆነች፡፡ የኢትዮጵያ አርበኛም ወደ መቀሌም ገሰገሰ፡፡ የኢትዮጵያ አርበኛ ምሽጉን ከቦ ያጣድፋት ጀመር፡፡ የጣልያን ወታደር ከምሽግ ሲወጣ በጥይት የሚያቅም አርበኛ አለበት፣ እንዳይቀመጥ ረሃብና ጥም ጠናበት ተጨነቀ፡፡ አባ ዳኛው እንኳን ለወዳጅ ለጠላትም ሩህሩህ ናቸውና እርሳቸውንና ሀገራቸውን ሊወጋ ባሕር ተሻግሮ የመጣውን የጠላት ጦር በከንቱ እንዳያልቅ ከምሽግ ወጥቶ እንዲሄድ ፈቀዱለት፡፡
ኢትዮጵያዊያን ያበጠውን ሊያስተነፍሱ፣ ወጀቡን ሊመልሱ፣ ክንዳቸውን በጋራ ሊያነሱ፣ በኢትዮጵያዊነት ቃል ኪዳን ታስረው ወደ አድዋ ገሰገሱ፡፡ የኢትዮጵያ ሠራዊት በአድዋ ሠፈረ፡፡ በተባበረ ክንዳቸውና አብዝቶ በሚወዳቸው አምላከቸው ተማምነው የልብ መፈተኛውን ቀን መጠባበቅ ጀመሩ፡፡
ጳውሎስ ኞኞ ቤርክሌይ የተባለውን ፀሐፊ ስለ አድዋ የፃፈውን እንዲህ አስቀምጠውታል፡፡
 ‹‹….በእኔ እምነት መሠረት በዘመናችን ታሪክ ውስጥ እንደ ዓድዋ ያለ ጦርነት የለም፡፡ ፓለቲካና ታሪክ አበቃ፡፡ በአፍሪካ ውስጥ ታላቅ የተወላጆች ኃይል መነሳቱ ታወቀ፡፡ የአፍሪካ ተወላጆች ታሪክ ተለወጠ፡፡ ጥቁሩ ዓለም በአውሮፓውያን ላይ ሲያምፅና ሲያሸንፍ የመጀመሪያው መሆኑ ነው፡፡ አበሾች አደገኛ ሕዝቦች መሆናቸው ከኦሪት ዘፍጥረት ጀምሮ ተፅፎላቸዋል››
አነሆ ያ ከፍ ባለ ተራራ ከፍ ብሎ የተሰቀለው ታሪክ ሲሠራ ኢትዮጵያዊያን በእግራቸው ተጉዘው ነበር ወደሥፍራው የሄዱት፡፡ ያን የእግር ጉዞ ለዚያውም ለጦርነት የሆነውን የሚያስቡ ኢትዮጵያዊያን በእግራቸው መጓዝ ጀምረዋል፡፡   እሾሕ አሜካላው፣ ሀሩርና ቁሩ ሳይበግራቸው የወላጆቻቸውን ታሪክ ለመዘከር እየተመሙ ነው፡፡ ያን ዘመን፣ በልባቸው እያሰቡ፣ መልካምን ሁሉ እየተመኙ፣ በፅናትና በጀግንነት ይጓዛሉ፡፡  እኛም ያን ጊዜ ልናስታውሰው ወደድን፡፡ የኢትዮጵያዊያንን ጀግንነት አፍ የለውም እንጂ  ተራምደውበት ያለፉት ምድር ሳይቀር ይመሰክራል፡፡
በዓድዋ የሆነውን ሁሉ የዓድዋ ዕለት፤ ሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ ይሁን፡፡
Filed in: Amharic